February 1, 2023
15 mins read

ደወል 2 ዘኢትዮጵያ ደወል 2፡ ቀዳሚው ፍቱን መድኃኒት ለኢትዮጵያ – ዶ/ር ዘላለም እሸቴ

5575994949በደወል 1 ዘኢትዮጵያ፥ ኢትዮጵያ በሚድን በሽታ ተይዛ ግን በሽታው እየገደላት እንደሆነ ተመለከትን።  አሁን ደግሞ ይህንን በሽታ ተመልክተን እንነቃበት ዘንድ ደወል 2 ዘኢትዮጵያን እንመለከታለን።  በሽታውን ስናውቅ መድኃኒቱ ይታየናል።  ይህንን ለማድረግ በኢትዮጵያ ያሉትን ሦስት ገፀ ባህሪያት ለምሳሌነት እንውሰድ።  አንደኛ የኢትዮጵያ ሕዝብን ተጠያቂ የሚያደርግ ሰሚ ያጣ ፈጣሪ አለ።  ሁለተኛ የኢትዮጵያ ልሂቃንን ተጠያቂ የሚያደርግ ሰሚ ያጣ ሕዝብ አለ።  ሦስተኛ ብዙ ሰሚዎችን ያገኙ የጠብ ገበሬዎች አሉ።

 

ሰሚ ያጣ ፈጣሪ፦ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይጠየቅ

 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከኑሮ ጋር እየታገለ ቀን ያልፍልኛል በማለት ተስፋ የሚያደርግና ተስፋ ባለመቁረጥ የሚታወቅ ነው።  ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው፥ ሰውን በሰውነቱ በማየት ከተለያዩ ብሔር ተወላጆች ጋር በጋብቻ የተገመደ ነው። አስቸጋሪ የሆነውን ኑሮ በአብሮነት እየተረዳዳና እየተደጋገፈ፥ ሃይማኖትና ዘር ሳይለየው ለዘመናት በፍቅር የኖረ ነው። ተረኛ ባለስልጣናት እየነገሱ ቢፈራረቁበትም፥ ሕዝብ ሁሉም ያለ ልዩነት የመከራን ገፈት እየተጋፈጠና ለሀገሩ ደሙን እያፈሰሰ ኢትዮጵያን እስካሁን ያቆየ ነው።  ሲቸግረው አመፅ አድርጎ መንግስት ቢቀየር፥ ቤተመንግስት አይገባ ነገር፥ ወደ ቤቱ አደራ ሰጥቶ ይመለሳል። ይሁን እንጂ ባለ አደራው መንግስት አደራውን ቀርጥፎ እየበላ ሕዝብን ባዶ እጁን ያስቀረዋል።  ይህም ሳያንስ መንግስት ሕዝብን ምረጥ እያለ ያታልለዋል።  ሕዝብ ስልጣን ተሰጠኝ ብሎ ቢመርጥም፥ ወይ ምርጫው ይሰረቃል፥ አለበለዚያም በሐቅም ተመረጠ ቢባል እንኳ አደራው ይበላል።  ኢትዮጵያ በመልካም ሕዝብ፥ በለምለም ምድር፥ በውብ የአየር ፀባይ ብትታደልም፥ እጣ ፈንታዋ ድህነት ሰቆቃና ሞት ሆነ።  ሕዝብ መውጫ ቀዳዳ አጥቶ፥ ሀገሩ እስር ቤት ሆኖበት፥ የቻለው ለመኮብለል ይናፍቃል።  እንባውን ለፈጣሪ እያፈሰሰ ለዘመናት ኖረ።

በሌላ በኩል ሰማይ ጥሪ ያቀርብልናል። ፈጣሪ እኛን እንዲሰማን እንደምንፈልግ ሁሉ፥ ፈጣሪም እርሱን እንድንሰማው ይፈልጋል። የሕዝብ ሀብትና ንብረት ብቻ ሳይሆን የሚዘረፈው፥ የተስፋ ቃሉ እንኳን ሳይቀር በባለተረኞች ይሰረቃል። ኢትዮጵያን በከፍታ ስፍራ የሚያስቀምጣት ፈጣሪ ራሱ ነው።  ግን በኢትዮጵያና በፈጣሪ መካከል እየገባ ቦታውን የሚወስድ ባለጊዜ ባለስልጣን ነው።  ያንን ደግሞ ሳያውቅ የሚያደርገው ሕዝብ ራሱ ነው።  የቀድሞ መሪን የይሁዳ አንበሳ ብለን ማስተጋባት ስናበቃ፥ የአሁኑን መሪ ደግሞ መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ሙሴ ብለን አረፍን።

የእስራኤልን ዓላማ ኢትዮጵያ መኮረጅ አትችልም። የእስራኤል ሕዝብ ጥሪ በአንድ ሰው ያውም በአብርሃም ላይ የተመሰረተ ነው። ስለሆነም ያዕቆብ እስራኤል በመሆን የቃል ኪዳኑን ሕዝብ መሰረተ። ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች [1] ማለት፥ ጥሪው የቀረበው ለሕዝብ እንደሆነ ያሳያል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ጥሪ በሕዝብ ላይ የተመሰረተና ከእርሱ ጋርም የተያያዘ ነው። ለኢትዮጵያ ሙሴ ትላንት አልነበረም፥ ዛሬም የለም፥ ወደፊትም አይመጣም።  ፈጣሪ ኢትዮጵያን በግለሰብ እጅ ሳይሆን በሕዝብ እጅ ያሻግራታል። ለዚያ ጥሪው የቀረበለት ደግሞ ሕዝብ ነው። ኢትዮጵያን የሚያሻግር የሰው ሙሴ እንደሌለ ሁሉ፥ ኢትዮጵያን የሚበታትን የሰው ሰይጣንም የለም። ለደጉም ለክፉም ግለሰብ ላይ መንጠልጠላችን ይቅር። ይልቁንስ የኢትዮጵያ ሕዝበ ቤተሰብ መለኮታዊ ጥሪውን ለመቀበል ይነሣ። ያኔ ፈጣሪም ይነሣል። ቅዱስ ቃሉ እንዲህ ይናገራል፦ “ስለ ድሆች መከራ፥ ስለ ችግረኞች ጩኸት እግዚአብሔር፦ አሁን እነሣለሁ ይላል፤ መድኃኒትን አደርጋለሁ፥ በላዩም እገልጣለሁ” [2]።

 

ሰሚ ያጣ ሕዝብ፦ የኢትዮጵያ ልሂቃን ይጠየቁ

 

የኢትዮጵያ ልሂቃን ከኢትዮጵያ ሕዝብ አብራክ የወጡና እሴቱን የሚያንፀባርቁ ናቸው።  ራሳቸውን መስዋዕት በማድረግ ይህ ሕዝብ ያልፍለት ዘንድ እንደ ሻማ እያለቁ የሚያበሩ ናቸው።  በጥበብና በዕውቀት የተካኑ ትልቅ ሰዎች ናቸው።  ያም ቢሆን እስካሁን አልተሳካላቸውም።  ብርሃኑ እንዳያበራ ንፋሱ ሻማውን ያጨልመዋልና።  ሁሉ ከንቱ ሆኖባቸዋል።  ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ትርፍ ለሌለው ነገር ማንከራተት ሆኖባቸዋል። ምንም ያህል ሐቀኛና ታታሪ ቢሆኑ የሚያመክናቸው ነገር መኖሩ ነው።  ልፋት ብቻ።  ሁሉ ነገር የአንድ ሰሞን ጉዳይ ሆነ።

ብርታታቸው ራሳቸውን መስዋዕት ማድረጋቸው ነው። ድክመታቸው ደግሞ የራሳቸውን ግላዊ ራዕይ መሰዋት አለመቻላቸው ነው።  ሰው ብዙ ዋጋ እየከፈለ ግን መነሻ አሳቡ ስህተት ከሆነ ኢላማውን አይመታም። ሰው ሊሞት ይችላል። ብዙ መከራ ሊቀበል ይችላል። ያም ሆኖ የግልን ራዕይ ጥሎ፥ በአንድነት ለኢትዮጵያ ባለመነሳቱ ብኩን ሆኖ ሊቀር ይችላል። ዋናው ቁምነገር ከጀርባው የሚገፋው ሃይል ከእኔነት መፅዳቱ ነው።  በእኔነት ከተነዳን አንድ ሆነን መቆም አንችልም።  አንድነት እንዲመጣ ራስን ክዶ፥ ከሌላው ጋር በትሁት ልብ ሆኖ፥ ለሕዝብ ጥቅም ሙሉ በሙሉ መሰጠት አለብን። ፍሬያማ የመሆን ምስጢር  ያለው ለእኔነት ሞቶ፥ ከሌላው ጋር በአንድ ልብ መያያዝ መቻል ነው። በልብ እልከኝነት ያለ ፍሬ እንዴት ዕድሜያችንን እንጨርሳለን? አንቆ የያዘን ከእኛ ውጭ ያለው ሳይሆን፥ በእኛ ውስጥ የተደበቀው እኔነታችን ነው።

አስተሳሰባቸውና አመለካከታቸው የተለያየ መሆኑ ችግር አይደለም። ይህ የአሳብ ልዩነት ፀጋ ነው።  ግን የዚህ የአሳብ ብዝሃነት ፀጋ የሚገለጠው መነጋገር ሲኖር ነው።  መነጋገር ደግሞ ወደ መግባባት አምጥቶ ራሳቸውን የሰውለትን ለውጥ ማምጣት ያስችላል።  ደግሞ መግባባት ችግር አይሆንም ነበር።  ምክንያቱም በልባቸው ያለው ራዕይ ለሕዝብ ስለሆነ፥ ያ የጋራ ጥቅም ለማግባባት አቅም አለው።  ውይይት ቢኖር ልዩነቱ ተጋጭቶና ተፋጭቶ መድኃኒት ይወጣው ነበር።  አሁን የተያዘው መጮህ ነው።  እንደ ገደል ማሚቶ።  ጩኸቱን ሌላው አይሰማም። የሚጮህ ራሱ የራሱን ጩኸት ይሰማል።

ነገር ግን ይህ ሁሉ ታሪክ የሚቀየርበት ጊዜ አለ።  ያም የኢትዮጵያ ሕዝብ ፈጣሪን ሰምቶ ለተሰጠው መለኮታዊ ጥሪ ራሱን መልስ አድርጎ ሲቆም፥ ልሂቃንም እንደዚሁ ሕዝብን ሰምተው በአንድ ልብ ለመገለጥ ግድ ይላቸዋል።

 

ብዙ ሰሚዎችን ያገኙ የጠብ ገበሬዎች

 

ፈጣሪና ሕዝብ ባልተሰማበት ሁኔታ እነዚህ ግን ብዙ ሰሚዎችን አገኙ።  እነዚህ ሰርጎገብ ናቸው።  የኢትዮጵያ አይደሉም።  የግላቸው ናቸው።  ሁሉም ውስጥ ተደብቀው ሀገር እንዲታመስ ምክንያት የሚሆኑ ናቸው። የትም ከለላ ውስጥ ቢሆኑ የሚያመሳስላቸው አንድ ነገር ነው።  ያም ለግል ጥቅም የሚኖሩ ናቸው። ፖለቲከኛ ሽፋን ውስጥ ሲገኙ ራሳቸውን ለማኖር እንጂ ለሕዝብ ሊኖሩ አይደለም።  ሃይማኖት ውስጥ ሲሸሸጉ ለፈጣሪ ክብር ሊያመጡ ሳይሆን ለራሳቸው ክብር ለማምጣት ነው።  ሕዝብ ውስጥ ሲደበቁ ለሕዝብ ተቆርቁረው ሳይሆን፥ ብሔራቸውን መነገጃ ለማድረግ ነው። እነዚህ ኢትዮጵያን ለማቃጠል እሳት የሚጭሩ ክብሪት የሆኑ ናቸው።

ሥራቸው የጠብ ግብርና ነው።  የሚዘሩት ዘር ደግሞ ጠብ ይባላል።  ቃሉ ስለነዚህ እንዲህ ይላል፡ “እግዚአብሔር የሚጠላቸው ስድስት ነገሮች ናቸው፥ ሰባትንም ነፍሱ አጥብቃ ትጸየፈዋለች፤ ትዕቢተኛ ዓይን፥ ሐሰተኛ ምላስ፥ ንጹሕን ደም የምታፈስስ እጅ፥ ክፉ አሳብን የሚያበቅል ልብ፥ ወደ ክፉ የምትሮጥ እግር፥ በሐሰት የሚናገር ሐሰተኛ ምስክር፥ በወንድማማች መካከልም ጠብን የሚዘራ” [3]። ፈጣሪ ከሃጢያት ሁሉ ይበልጥ ነፍሱ አጥብቃ የምትፀየፈው በወንድማማች መካከል ጠብ የሚዘራ መሆኑን ልብ እንበል። በወንድማማች መካከል የሚዘሩት ጠብ የሚያበቅለው ሁለት አይነት ፍሬ ይታጨዳል።  በአንድ በኩል ሕዝብ አለመደማመጥና አለመግባባትን እያጨደ እርስ በርስ ይበላላል። በሌላ በኩል በሕዝብ ሰቆቃ ላይ የጠብ ገበሬዎች ሀብት ዝናና ስልጣን እያጨዱ ለራሳቸው ጥቅም ትርፋቸውን ይበላሉ።

 

የነገሩ ፍፃሜ ምንድነው?

 

ሲጀመር የሚሰማ ጆሮ ይኑረን። መሰማት ያለበትን አስቀድመን እንስማ።  የሕዝብ ጆሮ ሰሚ ያጣውን ፈጣሪ ለመስማት ይከፈት።  የልሂቃን ጆሮ ሰሚ ያጣውን ሕዝብ ለመስማት ይከፈት። ያንን ከሰማን ወደ እርስ በርስ መደማመጥ እንመጣለን።  ስንደማመጥ ደግሞ ወደ መግባባት እንደርሳለን።  ስንግባባ አብረን እንደ አንድ ሆነን እንቆማለን።  አንድ ላይ አንድ ሆነን ስንቆም፥ ያኔ ከመድኃኒታችን ጋር እንገናኛለን። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ። በተከታታይ መመልከታችንን እንቀጥላለን።  በደወል 3 ዘኢትዮጵያ እንገናኝ።

 

ፀሐፊውን ለማግኘት: www.myETHIOPIA.com

ተጠቃሽ፦ [1] መዝሙረ ዳዊት 68፡31 | [2] መዝሙረ ዳዊት 12፡5 | [3] መጽሐፈ ምሳሌ  6:16-19

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop