ኢትዮጵያ ድሀ የነበረች ጊዜ – ያኔ ያለው ለሌለው ያካፍል ነበር፤ የሌለው ጎዳና ወጥቶ፣ ደብር ተጠግቶ ለምኖ በልቶ ያድር ነበር፡፡ የድሀ ልጅ በባዶ እግሩ ትምህርት ቤት እየተመላለሰ ፊደል ይቆጥር ነበር፡፡ በኩራዝ ጭለማ ይረታ ነበር፡፡ . . . . ያኔ ነብስ ካወቅን ጀምሮ የሀገራችን ከድህነት መውጣት ያሳስበን ነበር፡፡ ወጣት ሆነን ሀገራችንን ከድህነት ለማውጣት እድገት በህብረት ዘመትን፣ መሰረተትምህርት ዘመትን፤ ሰላም እንድትሆን በብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ዘመትን፡፡
በወጣትነቴ ጠመንጃ ይዤ ዘብ የቆምኩላት ሀገር ዛሬ በጎልማሳነቴም ሰላም አለማግኘቷ ልቤ ድረስ ይጠዘጥዘኛል፡፡ ድህነቷንም እናፍቀዋለሁ፤ ድሀ ለምኖ የሚበላበትን፣ አባወራ ጥጥ ለቀማ ቆላ የሚወርድበትን፣ ‹‹ግፋ ቢል አዶላ!›› ብሎ ወርቅ ቁፋሮ በቀን ሰራተኝነት የሚሰደድበትን፣ . . . . ድህነቷን እናፍቀዋለሁ፤ ሊያሳስበኝ ግን ልቦናዬ ጊዜ የለውም፡፡
ህይወት ረከሰ፤ ሞት ነገሰ፡፡ ከእንቅልፌ የሚቀሰቅሰኝ የወፎች ዜማ ሳይሆን የሞት ዜና ነው፡፡ በድህነት ያለፉት እናትና አባቴ ሰው ተሰቅሎ ሲሞት አይተው ለሳምንታት እንቅልፍ አይተኙም ነበር፡፡ የእኔ ዘመን አገዳደል ያኔ አልነበሩም፤ የሀገሬ ልጆች ከዚያ ወዲህ ተጠበው የደረሱባቸው የጭካኔ ፍሬዎች ናቸው፡፡ ከእንቅልፌ ስነቃ ስለምሰማው ሞት ሳስብ ውዬ ስለእሱው ሳስብ ያሸልበኛል፡፡
በየት በኩል ስለሌላ ነገር ማሰብ ይቻላል! የሀገሬ መልክ ሆኖ የሚያሳስበኝ ሞት እንጂ ድህነት አይደለም፡፡ ስለሞት ባሰብኩ ቁጥርም በልጅነቴ የኖርኩት ሰላማዊ ድህነቷ ይናፍቀኛል፡፡ ሞት በሚዘመርባት ሀገሬ ውስጥ እየኖሩ፣ ከድህነት ሊፈውሷት የሚጥሩ ዜጎቿን ልረዳቸው አቅቶኛል፡፡ እኔ ግን እላለሁ! ኢትዮጵያ ከድህነቷ የምትወጣው ማለቂያ በሌለው የዜጎች ሞት ከሆነ፣ ለዘለአለም ድሀ ሆና ትኑርልን፤ እንኑርባት፡፡