በሰሜን ጎንደር ዞን በምዕራብ ጠለምት፣ በማይጠብሪ፣ በአዳርቃይ አካባቢና በአዳርቃይ ከተማ ከሐምሌ 05/2013 ዓ.ም ጀምሮ ከ14 ወራት በላይ ወራሪ ቡድኑ በቆየባቸው አካባቢዎች ዘግናኝ የኾነ ሰብአዊና ቁሳዊ የንብረት ውድመት አድርሷል።
በወራሪው የሕወሓት ታጣቂ ቡድን ዘግናኝ ግፍ ከተፈጸመባቸው መካከል አንዱ ወጣት አብርሃ ዓለሙ በማይጠብሪ አካባቢ ነዋሪ ትውልዳቸው አማራ ሲኾን ወገኖቻችን አንዋጋም በማለት ተሸሽገን ነበር ይላል። ነገር ግን በጎረቤታቸው አካባቢ መረጃ አስቀምጠው አፍነው እንደያዙት ነው የተናገረው። የአማራ ብልጽግና ናችሁ በማለት በገመድ አስረው አንድ ቀን ሙሉ ፀሐይ ላይ እንደጣሉትና መሣሪያ አምጣ እያሉ ልብሱን አውልቀው እጅና እግሩ አስረው እንደደበደቡት ገልጿል። በደረሰበት ሰቆቃ ሁለት እጁን ተደብድቦ መመገብና ሥራ መሥራት እንዳይችል ሽባ ተደርጓል።
ሌላኛው ግፍ የደረሰበት የምዕራብ ጠለምት ወረዳ የሰራኮ ቀበሌ የ10ኛ ክፍል ተማሪ ወጣት አስፋው ዓለሙ በወቅታዊ ችግር ትምህርቱን አቋርጦ አርሶአደር አባቱን እያገዘ ባለበት ሰዓት ለምን አትታገልም፣ አንተ ባንዳ የሕወሓትን ንብረት ወስድሃል በማለት እጅና እግሩን አስረው በቢላዋ ጎኑን እየወጉ በሰደፍ እየቀጠቀጡ ፀሐይ ላይ እንደጣሉት አስረድቷል። የጭካኔያቸው ጥግ ከአንድ የሰው ፍጡር ለሕዝብ ነፃነት እታገላለሁ የሚል ታጋይ የሚፈጸም አይደለም ብሏል።
ሌላኛው ችግር የደረሰበት ወጣት ደስታ ታከለ ለምን አትታገልም እያሉ ሲያሮጡት እንደነበር ገልጸው የአማራ ክልል መታወቂያ ይዘሃል፣ በማለት በጠቋሚ ይዘው በመቀጥቀጥ ዘግናኝ ግፍ ተፈጽሞበታል። ባንዳ ሽፍታ መረጃ ነህ በማለት ተራ በተራ መደብደባቸውን አሳይቷል።
ልጆቻቸው ጉዳት የደረሰባቸው የምዕራብ ጠለምት ወረዳ የማይጠብሪ ዙሪያ ነዋሪ አቶ ዓለሙ አበባው ሁለት ልጆቻቸውን ጨምሮ ከ40 በላይ የሚኾኑ የምዕራብ ጠለምት ነዋሪ የአማራ ተወላጆች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ገልጸዋል። ልጆቻችሁን ለጦርነት አምጡ በማለት ከ40ሺ ብር በላይ እንደዘረፉአቸው ተናግረዋል።
በደረሰባቸው የአካል ጉዳት የሕክምና ድጋፍ መንግሥት እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል። በዚህ ዘግናኝና ሰቆቃ ሰዓት የኢትዮጵያ ጥምር ጦር ደርሶ ነጻ መውጣታቸውን አድንቀዋል። በመጨረሻም ይህ ነፍሰ በላ አሸባሪ ቡድን ዳግም ከተከዜ እንዳይሻገር ከመንግሥት ጎን ኾነው እንደሚታገሉም ጠቅሰዋል።
ዘገባው፦ የሰሜን ጎንደር ኮሙዩኒኬሽን ነው።