…. ሰሞኑን ካለሁበት አካባቢ ርቄ ወደ ደመቀው የዋሽንግቶን ዲሲ፣ ሜሪላንድ እና ቨርጂንያ አካባቢ ተጉዤ ነበር፡፡ የጉዞዬ ዋና ምክንያት ደግሞ፣ በአገራችን ብቸኛ በሆነው በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ውስጥ ያለፍን የቀድሞ ተማሪዎቹ ሁሉ በእጅጉ የምናከብረው፣ የምንወደውና አያሌ የሙዚቃ ስራዎችን በዘመኑ የከወነውን ጋሼ አማኒ ኢብራሂምን ለማግኘት ነበር፡፡ ያለፈውን ታሪክ ለመጪው ትውልድ ሰንዶ ለማስቀመጥ በሚደረግ የመፍጨርጨር ዓላማ ሂደት ሳቢያ!
… ወደ ዲሲ አካባቢ እንደደረስኩ፣ ብሩህ ሰማይ ተንጣሎ ይታይ የነበረ ቢሆንም፣ ከቀናት በኋላ፣ ደመና አጥልቶበት፣ እንደ ካፊያ ዝናምም እየሞካከረው ነበር። ወቅቱ በጋው ወደ ክረምት የሚሸጋገርበት ጊዜ ቢሆንም፣ እንዳንድ ወዳጆች “አንተ ይዘኸው የመጣኸው አየር ነው፤ ሰሞኑን ብራ ነበር…” ብለው እንደመቀለድም አድርጓቸዋል፡፡ ሰማዩ ደመና ቢያጠላበትም፣ እኔ ግን ምድሩን በእጅጉ ወድጄው ነበር። ከበረሃማው የዩናይትድ ስቴትስ ግዛት ስለመጣሁ ነው መሰል፣ ከየመንገዶቹ ዳር እጅብ ብሎ፣ ጥቅጥቅ ያለው የደን ውበት መንፈሴን ስቅዞ ይዞ፣ ሰላምን በውስጤ ዘርቶ ነበር የሰነበተው።
… ዲሲ ከተማን በመኪና መዞር በራሱ ሙዚየሞችን እንደመጎብኘት ያህል ስሜት ይሰጣል። ግዙፎቹና ያማሩ የመንግስት መቀመጫ ህንፃዎች፣ ለመታሰቢያነት የተሰየሙ ስፍራዎች፣የተንጣለለው የፓቶሚክ ወንዝና ድልድዮቹ፣ እንዲሁም ከወንዙ ባሻገር ያለው የቨርጂንያ ደን ውበት… በማየው ነገር ሁሉ መንፈሴ ረካ፤ ይህንንም.. ያንንም.. ለአገሬም ተመኘሁ፤ በተለይም፣ በሰላም ወጥቶ፣ በሰላም ተዘዋውሮ፣ በሚያዩት ሁሉ በመደነቅ፣ በደስታ መንፈስን አርክቶ፣ በነጻነት ካሰቡበት መድረስን…።
… “አበሾች ይኑሩ” የሚል ግጥም ወይም ጽሁፍ ባንድ ወቅት ያነበብኩ ይመስለኛል፤ ግጥም ከሆነ፣ ምናልባት የዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ሊሆን ይችላል፤ አጓጊና ተነባቢ ጽሁፍም ከሆነ ደግሞ፣ የድንቁ ተራኪ የጋሼ አሰፋ ጫቦም ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ ከኔ ግምት ውጭ ሌላም ሰው ጽፎት ሊሆን ይችላል፤ ብቻ ዋናው ነገር፣ ባሉበት ቦታ ሁሉ “አበሾች ይኑሩ”!
…በሚገርም ሁኔታ ዲሲ፣ ቨርጂኒያና ሜሪላንድ የአበሾቹ አገር ነው የሚመስለው። ከአየር ማረፊያ አስከ ሆቴል … ፣ አስከ ሱቆች… ድረስ ሁሉ ያስተናገዱኝ ባለፈገግታዎቹና ቀናዎቹ አበሾች – ያገሬ ልጆች ነበሩ። ባንድ ወቅት አንዱ ወዳጄ፣ ወደ ዲሲ አካባቢ ከሄድክ፣ ‘እዚህ ቤት የሚሸጥ እንጀራ አለ’፤ የሚል ማስታወቂያና ድሮ አገር ቤት ጠላ የሚሸጡ ኮማሪዎች በራቸው ላይ የሚተክሉት የተደፋ ጣሳ የያዘ እንጨት ሁሉ ተተክሎ ልታይ ትችላለህ ብሎ ፈገግ አሰኝቶኝ ነበር። በዚህን ሰሞን ዲሲ አካባቢ ያየሁት ጉድ ግን፣ ያቺ ቀልድ ወደምርነት የምትቀየርበት ሁኔታ ቢፈጠር እንኳን የሚገርመኝ አይሆንም። ብቻ ለማንኛውም፣ ኖረው እንዲያኮሩ- “አበሾች ይኑሩ” እያልኩ ወደ መነሻ ሃሳቤ ልዝለቅ።
የተነሳሁበት ሃሳብ ወደ ዲሲ አካባቢ የወሰደኝ ምክንያት ነበር። ምክንያቱም እንዳቅሚቲ ታሪክ ለመዘገብ በመሻት ነው። “የኋላው ከሌለ – የለም የፊቱ” በሚለው መርህ መሰረት፣ የኋላውን ጊዜ ታሪክ ለመጪው ሰንዶ ለማስቀመጥ።
ጋሼ አማኒ ኢብራሂም ከያሬድ የሙዚቃ ት/ቤት የመጀመሪያዎቹ ተመራቂዎች አንዱ የነበረ ሲሆን፣ በወቅቱ ትምህርቱን በላቀ ደረጃ በማጠናቀቁ ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ ልዩ ሽልማት ተቀብሏል። በት/ቤቱ ታሪክ ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ ታቅዶ በተተገበረ የላቀ የሙዚቃ ኮርስ ለ 2 ዓመታት ተከታትሎ አሁንም በላቀ ደረጃ አጠናቋል። ከዚያም ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ሕንድ አገር ዘልቆ፣ በተፈጥሮና በትምህርት ያገኘውን የሙዚቃ ሙያን ወደ ከፍተኛ ደረጃ አሸጋግሮ፣ በሙዚቃ ድርሰት፣ አቀናባሪነት፣ መሪነትና መምህርነት ክህሎትን አዳብሮ- ወደ እናት አገሩ ተመልሷል። የሙዚቃን ጥበብ ሀሁ በቀሰመበት በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት በመምህርነትና በርዕስ-መምህርነት አገልግሏል፤ በብሔራዊ ቴአትር፣ በባህል ሚ/ር ፣ በአገር ፍቅር ትያትር በኃላፊነት ቦታዎች ላይ ከመሥራቱም በላይ፣ በተጓዳኝና በተደራራቢ ሥራ በየአመቱና በየበአላቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ዝግጅቶች ላይ፣ የሙዚቃ ድርሰቶችን በመጻፍ፣ በማሰራትና በመምራት፣ ከአገሪቱ ቁንጮ የጥበብ ባለሙያዎች ጋር በመሆን አያሌ ተግባራትን ከውኗል። ከሚጠቀሱት መካከል… ከደማችን – አስከ ጉዟችን፤ ከአንድነት ዝማሬ – እስከ አዲስ አበባ መቶኛ ዓመት፤ እስከ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሃያ አምስተኛ ዓመት ክብረ-በዓል ዝግጅት… ፤ በያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት እና በከፍተኛ አስራ አምስት የኪነት ቡድን ያስዘምራቸው የነበሩት የአገር ፍቅርን ስሜት በወጣቶች ላይ ያሰርጹ የነበሩ ጥዑም መዝሙሮች…፤ ለብዙዎች ድምጻዊያን ያበረከታቸው የሙዚቃ ቅንብር ስራዎች…፤ ብርቅዬ ድምጻውያኑን እነ ብዙነሽ በቀለን፣ ጥላሁን ገሠሠን፣ አመልማል አባተን… ሌሎችንም ድምጻዊያን እና የባህልና ዘመናዊ የሙዚቃ ቡድኖችን በመምራት በተለያዩ አገራት አገራችንን በመወከል በመገኝት…፤
… ይህ ሁሉ ታሪክ ነው፤ የአንድ ሰው ብቻ ሳይሆን፣ በውስጡ የአያሌ ባለሙያዎችንና ያገር ባለውለታዎችን ታሪክ የያዘ ታሪክ! የሚመራመር ትውልድ ከመጣ፣ ኋላውን ሊያይበት – ፊቱን ሊያሳምርበት የሚያስችለውንና የምርምር መነሻ ሊሆነው የሚችል ሰነድ በየሙያ ዘርፉ የተከወኑ ስራዎችን ብናስቀምጥለት፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በጽናት የማስቀጠል ኃላፊነትና ተግባር አካል እንደሚሆን በተስፋ በማመን ነው።
በዚሁ አጋጣሚ፣ ከጋሼ አማኒ ኢብራሂም፣ ከቀድሞ ተማሪዎቹ ከመለሰ አስፋውና ከእስክንድር ገድሉ፣ በስራ ዓለም አብረው ከሰሩት መካከል ከአለምፀሐይ ወዳጆ፣ ከባለቤቱ ከአዲስ ሕዝቂያስ ጋር … ላደረኳቸው ውይይቶች፣ ሁሉም ጊዜያቸውን ሰውተው ላደረጉልኝ የቀና ትብብር ልባዊ ምስጋናዬን ላቀርብ እወዳለሁ። ጊዜውን ሙሉ ለኔ ሰጥቶ በሚያዋዛ ቀልዶቹ ታጅቦ በቀረጻ የረዳኝ፣ ሲሳይ አለማየሁ እና አሱንም ያገናኙኝ፣ ዘገየና አረጋ ሳይዘነጉ!
… ከምስጋና በላይ የላቀ ፤ምስጋና የሚገባቸው ሁለቱ እንስት፣ አዲስ እና አለም ይሆናሉ።
አዲስ – በቆይታችን ሁሉ ቤቷን ከፍታ እንደልባችን እንድንሰራ ከመፍቀዷም በላይ፣ በየዕለቱ ቁርስ፣ ምሳና ራት ብፌ በሚመስል ደረጃ በማዘጋጀት፣ የቤተሰባዊነት ስሜት በተላበሰ ሁኔታ በግሩም መስተንግዶ ስለተቀበለችን፤ የጣይቱ ማዕከሏ አለምፀሐይ ወዳጆ ደግሞ፣ በከፍተኛ አድናቆት ሳልገልጸው የማላልፈው፣ ለጀመርኩት ተግባር ሃሳቧን እንድታካፍለኝ ከወር በፊት በጽሁፍ መልእክት ሳቀርብላት፣ እለቱኑ በቅጽበት ምላሿን ሳገኝ፣ የተሰማኝ ደስታና ክብር የላቀ ነበር። አግራሞቴን የጨመረው ደግሞ፣ አያሌ ሃላፊነቶችን ተሸክማ በውጥረት ላይ ሳለች፣ አኔን ያለዕቅዷ በጎን የገባሁባትንም፣ ወደ ጎን ሳታደርግ ጊዜ ሰጥታ በአክብሮት መጋበዟ ነበር። በወቅቱ መልእክት የሰደድኩላቸው ጥቂቶች እስካሁንም ድረስ ምላሽ ስላልሰጡኝ፣ የሚሰራ ሰው “ጊዜ የለኝም” እንደማይል የተማርኩበትም ክስተት ጭምር ነው። በዚህ አጋጣሚ ወደ ዲሲ አና ሜሪላንድ አካባቢ የሚሄዱ አበሾች ሁሉ፣ በቅርሳ-ቅርስና በታሪካዊ ፎቶዎች ያሸበረቀችውንና ትንሿ ኢትዮጵያን የምትመስለውን የጣይቱን ማዕከል ቢሮ እንዲጎበኙ እመክራለሁ።
የጉዞ ማስታወሻዬን ለመጨረስ፣
…አራቱ ድምጻውያን ባንድ ወቅት ያዜሙትን “ሁሉም ቢተባበር” የሚል ዜማ፣ ለፕሮግራም ማሳመሪያና ለብሶት ከማሰማትና ከመስማት ባሻገር፣ የምር “ሁሉም ቢተባበር- የት ይደረስ ነበር”ን በተግባር እንተርጉመውና ስላለፈው ጊዜ የምታውቁ ሁሉ፣ የምታውቁትን አጋሩንና የተበታተነውን ሁሉ ሰብሰብ አርገን፣ ባንድ ቋጥረን በመሰነድ፣ ታሪክን – ለታሪክ እናስረክብ የሚል ነው አቤቱታው!
ጌታቸው አበራ
ጥቅምት 2015 ዓ/ም
(ኦክቶበር 2022)