October 10, 2022
56 mins read

“የዛሬው የአገራችን ሁኔታ ከዲፕሎማሲ አንፃር” በሚል አርዕስት ስር በአቶ ባይሳ ዋቅ-ወያ ለቀረበው ገለጻ የተሰጠ ሀተታዊ መልስ!

ፈቃዱ በቀለ(/)

ጥቅምት 10 2022

በአቶ ባይሳ ዋቅ ወያ “የዛሬው የአገራችን ሁኔታ ከዲፕሎማሲ አንፃር ሲታይ” በሚል አርዕስት ስር ተጽፎ በዘሃበሻ ድረ-ገጽ ላይ የወጣውን ጽሁፍ ከሞላ ጎደል አነበበኩት። ጽሁፉን በደንብ ላነበበ ሰው ብዙ ክፍተቶች ያሉበትና፣ ከተጨባጭ ወይም ክሳይንስ ሁኔታ በመነሳት የተጻፈ አለመሆኑን በቀላሉ ለመገንዘብ ይቻላል። አንድን ጽሁፍ ሳይንሳዊ የሚያደርገው ወይም ደግሞ ከተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት የተጻፈ ነው የሚያሰኘው በምድር ላይ የሚታዩ ማንኛውንም ነገሮች፣ ለምሳሌ ፖለቲካዊ፣ ሚሊታራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የህሊናና የባህል ቀውሶችን በደንብ አገናዝቦ የተጻፈ ከሆነ ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ የተወሰኑ የአሰራር ስልቶች ሲኖሩ፣ በተጨማሪም ተጽፈው የሚቀርቡ በተለይም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ነክ ሀተታዎች በደንብ ለመገንዘብ የግዴታ የተወሰነ ርዕዮተ-ዓለምን ተከትሎ መጻፍ አለበት። እንደሚባለው እሴተ-አልባ(Value-Free) የአጻጻፍ ስልትና አመለካከት ስሌለ አንድ ሰው የሚመራበትን ርዕዮተ-ዓለም መሰረት አድርጎ የማይጽፍ ከሆነ በመሰረቱ ውዥንብር ብቻ ነው የሚነዛው። ከዚህ ስንነሳ የባይሳ ዋቅ ወያ አጻጻፍ ምን ዐይነት የአስራር ስልትንና ርዕየዮተ-ዓለምን መሰረት አድርጎ እንደጻፈ ግልጽ አይደለም።

ወደ ጽሁፉ መሰረተ-ሃስብ ስንመጣ ባይሳ እንደሚነግረን ዛሬ በአገራችን ምድር ያለው ችግር በመንግስትና በአንዳንድ ተፋላሚ ኃይሎች የሚካሄድ እንጂ በመንግስቱ ወይም ስልጣንን በጨበጠውና በህዝቡ መሀከል ያለ ችግር አይደለም ይለናል። በሌላ አነጋገር፣ ባይሳ ሊነግረን የሚፈልገው በአቢይ አህመድ የሚመራው አገዛዝ ለስፊው ህዝባችን የሚፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ ስለሚያደርግ ህዝባችን አቅፎ ደግፎት ያለ አገዛዝ ነው፤ ችግር የሚፈጥሩት ተፋላሚ ኃይሎች ብቻ ናቸው ይለናል። እነዚህ ተፋላማ ኃይሎች ደግሞ እነማን እንደሆኑና፣ በምን ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም እየተመሩ ለስልጣን እንደሚታገሉ በፍጽም አይነግረንም፤ ወይንም ግልጽ አያደርግልንም። በደፈናው ብቻ ተፋላሚ ኃይሎች በማለት ግልጽ ሳያደርግ አድበስብሶ ያልፋል።

በአቢይ አህመድ ወደሚመራው አገዛዝ፣ በባይሳ አጠራር መንግስት ተብዬው ጋ ስንመጣ ባይሳ እንደሚነግረን ሳይሆን አቢይ አህመድና ግብረ-አበሮቹ ስልጣን ላይ ከወጡ ከዛሬ አራት ዓመት ተኩል ጀምሮ የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪኩ ውስጥ አይቷቸው የማያውቃቸው ነግፎች በሙሉ እንዲያይ፣ እንዲቀምሳቸውና እንዲለማመዳቸው ተደርጓል። ባጭሩ አረመኔነትን ልክ እንደጥሩ ስራ አድርጎ እንዲቀበለውና ከደሙ ጋር እንዲዋሃድ በማድረግ አረመኒያዊ ተግባሮች በሙሉ ከምንም እንዳይቆጠሩ ለመደረግ በቅቷል።  በመጀመሪያ ደረጃ ባይሳ ዋቅ ወያ ሞስኮ በነበረበት ጊዜ የተማረው ትምህርት የዓለም-አቀፍ ህግ ትምህርት ስለሆነ ከዚያ ጋር አስታኮ ስለመንግስት ምንነትና ተግባር ሳይማር  ወይም ሳያነብ ያለፈ አይመስለኝም።ለማንኛውም የአንድ አገዛዝ ወይም መንግስት ዋና ኃላፊነት በአንድ አገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ ጸጥታን ማስከበርና፣ ማንኛውም ግለሰብ ራሱን የሚገልጽበትን ሁኔታ በመፍጠር እንደ አንድ ዜጋ ሆኖ ሊኖር የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው። ይህም ማለት፣ የአንድ መንግስት ወይም አገዛዝ ዋና ተግባር በአገር ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት የሚፈጠርበትን ሁኒታ ማመቻቸትና በነፃነት ስም የጦር መሳሪያ ይዘው በተለይም ዘር ወይም ጎሳ ተኮር ጥቃት የሚያደረሱ ኃይሎች እንደልባቸው የሚፈነጩቡትን ሁኔታ መፍጠር ሳይሆን፣ እንደነዚህ ኃይሎች ከነስረ-መሰረታቸው ሊጠፉ እንዲችሉ ማንኛውንም እርምጃ መውሰድ የመንግስት ወይም የአንድ አገዛዝ ዋና ተግባር ነው። ይህ ብቻ ሲሆን ነው አንድ ህዝብ በእርግጥም በነጻ ለመንቀሳቀስና በስነ-ስርዓት ለመስራት የሚችለው። እንደሚታወቀው ለኢኮኖሚም ሆነ አንድን አገር በተሟላ መልክ ለመገንባት በአንድ አገር ውስጥ የተሟላ ሰላምና ጸጥታ መስፈን እንደመሰረታዊ ቅድመ-ሁኔታዎች መወሰድ ያለባቸው ጉዳዮች ናቸው።  ከዚህ ጋር ተያይዞ ሰፊው ህዝብም ሆነ ስልጣንን ጨብጠው የሚዘባነኑት ኃይሎች በሙሉ እንደሰው ለመኖር ከፈለጉ የግዴታ መብላት፣ ንጹህ ውሃ ማግኘት፣ መጠለያና ሌሎች መሰረታዊ ነገሮች ብለን የሚንጠራቸው ነገሮች በሙሉ ያስፈልጓቸዋል። ካለበለዚያ እንደሰው መኖር አይችሉም። ሊያስቡና ሊሰሩም አይችሉም። ከዚህ መሰረታዊ ጉዳይ ስንነሳ በተለይም በኢንዱስትሪ፣ በእርሻ መስክና በንግድ ዙሪያ ተሰማርተው የሚሰሩና ሰፊውን ህዝብ ለመመገብ ሌት ተቀን ደፋ ቀና የሚሉ የህብረተሰብ ኃይሎች የግዴታ ልዩ እንክብካቤና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። በተለይም ገበሬው ለሰው ልጅ አስፈላጊ የሆኑ የተለያዩ የስብል ዐይነቶችን አምርቶ ለበላተኛው የሚያቀርብ እንደመሆኑ መጠን ልዩ እንክብካቤና ድጋፍ ያስፈልገዋል። ስለሆነም እንደጠላት እየታየ ከቀዬው የሚሳደድበትና የሚገደልበት አንዳችም ምክንያት ሊኖር አይገባም። በአጠቃላይ ሲታይ አምራች የሆነውን የህብረተሰብ ኃይል የማይንከባከብና አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎችን የማይሰጥ መንግስት እንደመንግስት በፍጹም ሊቆጠር አይችልም። በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ይህን ያህልም ግንዛቤ ውስጥ ካልገባው ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ በኦርሚያ ክልል ተብሎ በሚጠራው፣ በተለይም በወለጋ ክፍለ-ሀገር በሚኖረው የአማራው ብሄረሰብ ወገናችን ላይ ላይ የሚደርሰው አራት ዓመት ተኩል ያህልን ያስቆጠረ የማፈናቀል፣ የመግደል፣ ንብረቱን ማውደምና፣ የተወሰነውም እንዲሰደድ ማድረግ እጅግ የሚያሳዝንና አንጀትን የሚያቃጥል ጉዳይ ነው። ከዚህ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በአማራው ክልል ውስጥ ዘልቆ በመግባት በአምራቹ ህዝብ ላይ ግድያን መፈጸምና ሀብቱን መዝረፍ ምን ዐይነት ፈሊጥ እንደሆነ በፍጹም ሊገባን የሚችል ጉዳይ አይደለም።

ወደ ሰሜኑ ክፍል ስንመጣ ደግሞ በተለይም ወያኔ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ በዚያ የሰፈረውን የሰሜን ዕዝ የሚባለውን ወታደር ከስምንት መቶ በላይ የሚቆጠሩ ወታደሮችና መኮንኖችን ከጨፈጨፈ በኋላ አጻፋውን ለመመለስ ተብሎ በተካሄደው ጦርነት አብዛኛዎቹ የወያኔ አመራሮች ሲገደሉ ሆን ተብለው ደብረ-ጽዮን፣ ጻድቃንና ጌታቸው ረዳ እንዲቀሩ በመደረግ ወታደሩ መቀሌንና አንዳንድ ቦታዎችን ለቆ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ ወያኔ ጀሌዎችን በማሰባሰብ በከፈተው ጦርነት እስከ ወሎና አፋር ድረስ  ዘልቆ በመግባት፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ጎንደርና ሰሜን ሸዋ ድረስ ዘልቆ በመግባት ለብዙ ሺሆች ወገኖቻችን መሞት ምክንያት ሊሆን በቅቷል። ብዙ የዋህ ሰዎች፣ ሽማግሌዎችና ህጻናት እንደከብት ታርደዋል። ይህንን የዋያኔን አረመኒያዊ ተግባር በተቀነባበረ መልክ መመከትና አስፈላጊውን ቅጣት ከመስጠት ይልቅ አቢይ አህመድ አዲስ አበባ ሆኖ ቀጭን ትዕዛዝ በመስጠት ተዋቸው በማለትና ወታደሩ እንዲያፈገፍግ በማድረግ በተደጋጋሚ ምንም ነገር በማያውቀው ህዝባችን ላይ አሰቃቂ ግፍ እንዲፈጸም ለማድረግ በቅቷል። በሌላ አነጋገር፣  ለዚህና ከላይ በመጠኑም ቢሆን በዘረዘርኳቸው ጉዳዮች ላይ የመንግስት ሚናና ኃላፊነትን ሳይረዳ ስልጣን ላይ ቁጥጥ ያለው በአቢይ አህመድ የሚመራው  የኦሮሞ ኤሊትና ግብረ-አበሮቹ በአለፉት አራት አመታት ተኩል እጅግ አረመኔያዊ የሆነ ተግባር ፈጽመዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን አቢይ አህመድና ለማ መገርሳ ጊዜው የእኛ ነው በማለት የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ በሲአይኤና በሳውዲ አረቢያ ለሚደገፈውና ለሚደጎመው ለእነ ጃዋር መሀመድ ለመሳሰሉት በመልቀቅና እንደፊለጉ እንዲፈነጩበት በማድረግ ህዝባችን በጭንቅት ዓለም ውስጥ እንዲኖር ለማድረግ በቅተዋል። ከዚህም በላይ በአዲስ አበባ ውስጥ የዲሞግራፊ ለውጥ  ማምጣት ያስፈልጋል በማለት ከሐረርና ከአንዳንድ የኦርሚያ ክልል ወጣቱንና ገበሬውን እያፈናቀሉ በማምጣትና በማስፈር አዲስ አበባን የወንጀለኞች መናኸሪያ ለማድረግ በቅተዋል። በዚህ ዐይነቱ ፀረ-ህዝብና አገር አፍራሽ ድርጊታቸው አብሯቸው ስልጣን ላይ ቁጥጥ ያለውም ከአማራ ብሄረሰብ የተውጣጣው ኢሌትም ተባባሪ በመሆን በድርጊታቸው እንዲገፉበት አድርጓቸዋል። ሌሎችም አንዳንድ ለስጣን ብቻ ያቆበቆቡ ምሁሮ ነን ባዮችና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች አቢይን አሁንም እናምነዋለን በማለትና ህዝብን በመደለል አቢይና ግብረአበሮቹ አገርን በማፍረስና በተለይም የአማራ ብሄረሰብ ተወላጅ የሆነው በአገሩ ተሸማቆ እንዲኖርና እንዲገደል የሞራል ድጋፍ በመስጠት አቢይን በወንጀል ስራው እንዲገፋበት እያበረታቱት ነው። ከእነዚህ ውስጥ ብርሃኑ ነጋ፣ አንዳርጋቸው ጽጌና ዲያቆን ዳንዔል ይገኙበታል። ሌኦችም ህሊና ቢስ የሆኑ ምሁር ነን ባዮች መንግስት ለሚፈጽመው ድርጊት ተባባሪ በመሆን የህዝባችንን ሰቆቃ እያባባሱትና እንዲራዘም እያደረጉት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በአንድነት የሕግና ሰብአዊ መብት ቋሚ ኮሚቴ የተዘጋጀ የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርት

በአጠቃላይ ሲታይ አቢይ አህመድና ግብረአበሮቹ ምንም ዕውቀት ሳይኖራቸው ስልጣን ላይ ቁጥጥ ካሉ ጀምሮ በህዝባችንና በአገራችን ላይ ከፍተኛ የባህል ጦርነት በመክፈት፣ በተለይም በኦርቶዶክስ ሃይማኖት አማኞች ላይ በየቦታው ከፍተኛ ዕልቂትና መፈናቀል ሊያደርሱ ችለዋል፤ ቤተ-ክርስቲያናትን አውድመዋል። እንደሻሸመኔ የመሳሰሉና ሌሎች ከተማዎችም በቀጥታ በመንግስት ተሳትፎ እንዲወድሙና ሰዎችም ለብዙ ዓመታት ይኖሩባቸው የነበሩ ከተማዎችንና መንደሮችን ለቀው እንዲወጡ ተገደዋል። የንግድ መደብሮችና ሆቴልቤቶች እንዳለ እንዲዘረፉና እንዲፈራርሱ ተደርገዋል። አቢይና አህመድና ግብረ-አበሮቹ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት መሪዎችና ተቋማት ኢትዮጵያን እንደ አገር ለመገንባት ያደረጉትን አስተዋፅዖ ግንዛቤ ውስጥ ባለመስገባትና፣ ታሪካችንና ባህላችን እንደ ዋና ጠላት በማየት፣ በተለይም አማራውና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ጨቁነውናል በሚል የተሳሳተ ትረካ በማስፋፋት፣ እንዲሁም የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን እንደአፀያፊ ነገር በመቁጠር በህዝባችንና በታሪካችን ላይ ከፍተኛ ዘመቻ ከፍተዋል። በአንፃሩ የጴንጤ ቆንጤ ሃይማኖት እንዲስፋፋ በማድረግ ቦዘኔነትና ጋጠወጥነት ተለምደዋል። ምንም ሳይሰሩ ገንዘብ ከደሃው ህዝብ እየሰበሰቡ የሚንደላቀቁ ሰባኪ ነን ባዮች እንደ አሸን እንዲፈልቁ በማድረግ በተለይም በወጣቱ ዘንድ ከፍተኛ ውዥንብር ሊስፋፋ ችሏል። እነዚህ ዐይነት በመንግስት የሚደገፉና የራሱ የአቢይ አህመድ አገዛዝ የሚያምንበት አገርን በአሻጥር ማስተዳደርና አገርን ማከረባበት ዋናው ችግር የፖለቲካ ፍልስፍናን አለማወቅና በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ቅራኔዎች እንዴት እንደሚፈቱና እንደሚያዙ፣ እንዲሁም ደግሞ ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጡ ደረጃ በደረጃ መወሰድ ያለባቸውን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና የማህበራዊ ጒዳዮችን በሚገባ ካለመረዳት የተነሳ ነው። በአጭሩ እንደዚህ ዐይነት በመንግስት የሚደገፉ ወንጀሎች የሚፈጠሩት የህብረተሰብንና የተፈጥሮን ህግ ካለመረዳት የተነሳ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በተፈጥሮ ውስጥ ልዩ ልዩ እንስሳትና አጽዋትም ያሉትን ያህል፣ አንድ ህብረተሰብም በአንድ ብሄረሰብ ብቻ ሊዋቀር በፍጹም አይችልም። ለምሳሌ በዓለም ላይ ወይም በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ልዩ ልዩ ዛፎችን አውድሞ ባህርዛፍን ብቻ እንተከል ቢባል፣ ከተተከለና ከአደገ በኋላ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ድርቀትን ብቻ ሳይሆን ዓለምም ራሷ እንዳለ ወደ በረሃነት የመለወጥ አደጋ ያጋጥማታል። ምክንያቱም የባህርዛፍ ስር በብዙ ሜትሮች ወደውስጥ ዘልቆ የሚሄድና በምድር ውስጥ ያለውን ውሃ የመምጠጥ ኃይሉ ከፍተኛ ስለሆነ የመጨረሻ መጨረሻ የአየር ለውጥንና የአካባቢ ውድመትን ያስከትላል። እንደዚሁም በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ልዩ ልዩ ብሄረሰቦችን አውድሞ ወይም አፈናቅሎ አካባቢውን ከአንድ ብሄረሰብ የተውጣጡ ግለሰቦችን ብቻ ማስፈር የባህልና የኢኮኖሚ ውድመትን ያስከትላል። ፈጠራና በስራ-ክፍፍል ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ያግዳል። ሳይንስና ቴክኖሎጂም እንዳይዳብሩ ይደረጋል። እነ አቢይ አህመድና ሺመልስ አብዲሳ በአለፉት አራት ዓመታት ተኩል ይህንን ዐይነቱን የህብረተሰብንና የተፈጥሮን ህግ የሚፃረር ወንጀል ሲሰሩ ነው የከረሙት። ታዲያ በምን ዐይነት የፖለቲካ ፍልስፍና ነው እንደመንግስት ወይም አገዛዝ ሊቆጠሩ የሚችሉት? ባይሳ ዋቅ  ወይ ይህንን ጥያቄ እንዲመልስልኝ እፈልጋለሁ።

ይህ ዐይነቱ ችግር ለምንድነው የሚፈጠረው? በአገራችንና በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች የተዋቀሩት መንግስታትና ስልጣንን የሚይዙ አገዛዞች በመሰረቱ ከታች ወደላይ ተኮትኩተው ያደጉና ከማቴሪያል ሁኔታዎች ጋር በማመዛዘን  እየተሻሻሉና   እየተስተካከሉ የተስተካከሉ ዲሞክራሲያዊ ባህርይ እንዲኖራቸው ሆነው የተዋቀሩ አይደሉም። አብዛኛዎቹ አገዛዞችም አንድ መንግስትና አገዛዝ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚረዱና የተረዱ አይደለም። የእገራችንም ሆነ የአብዛኛዎቹ የአፍሪካና የተቀሩት የማዕከለኛውና የደቡብ አሜሪካ አገሮች መንግስታት አወቃቀር ከውጭ በመምጣትና በኢምፔሪያሊዝም ርዕዮተ-ዓለም በመሰልጠን የተገነቡ ስለሆነ የዘራፊነትና የጨቋኝነት ባህርይ ያላቸው አገዛዞች ናቸው። የሚሊታሪው፣ የጸጥታው ኃይል፣ የፖሊስ፣ የሲቪል ቢሮክራሲውና ቴክኖክራቶች በሙሉ በኢምፔሪያሊስት ርዕዮተ-ዓለም የሰለጠኑና፣ ሰፈና ጠለቅ ያለ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ ሳይንስ ቲዎሪና የተፈጥሮ ሳይንስ ዕውቀት ስለሌላቸው አገሮቻቸውን እንደህብረተሰብ የመገንባት ኃይልና ዕውቀት የላቸውም። በአንፃሩ ወደ ዘራፊነት በመለወጥ የዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የሚባሉ እየመጡ የጥሬ-ሃብትን እንዲዘርፉ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ። ሰለሆነም የመንግስታት አወቃቀርና ራሳቸውም አገዛዞች የተገለጸላቸውና ጭንቅላትን በሚያድስ ዲሞክራሲያዊና ምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ባለማለፋቸው አዳዲስ ኃይሎች ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ የመንግስቱን መኪና አገርን መገንቢያ ከማድረግ ይልቅ  እንዳለ ወደመጨቆኛ መሳሪያነት በመለወጥ ህዝብና አንዳንድ ምሁራን በፍርሃት ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ ያደርጋሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዳይዳብር በማገድ እንደ ወዛደርና የገበሬ የሙያ ማህበራት የመሳሰሉት እንዳይቋቋሙ በማድረግ ራሳቸውን አጉልተው በማውጣት አንድ ህዝብ ደሃ ሆኖ እንዲኖር ያደርጋሉ። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ የአገራችን መንግስትና አገዛዙ ምን ዐይነት ርዕዮተ-ዓለም እንዳልቸው በፍጹም አይታወቅም። በሌላ አነጋገር፣ የፋሺሽት አገዛዝ፣ የቀኝ አገዛዝ፣ የሶሻል ዲሞክራቲክ አገዛዝ ወይንስ የኮሙኒስት አገዛዝ። ይህም ማለት ሁላችንም ስለመንግስትና አገዛዝ በምናወራበት ጊዜ ምን ዐይነት አገዛዝ በአገራችን ምድር እንደሰፈነ በዝርዝር፣ ከሳይንስና ከቲዎሪ አንፃር ለመተንተን አንችልም። በጭፍኑ ብቻ መንግስትና አገዛዝ እያልን እንጠራለን። የአቶ ባይሳ ዋቅ ወያና የሌሎችም ምሁራን ችግር ይህ ነው።

ለማንኛውም ቀደም ብሎም ሆነ አቢይ አህመድ ስልጣን ከያዘ ጀምሮ የሚሰሩት ወንጀሎች በሙሉ የመንግስትን ምንነትና ተግባር፣ እንዲሁም ፖለቲካ የሚባለውን ግዙፍ ጽንሰ-ሃሳብ ካለመረዳት የሚመነጭ ነው። ለማንኛችንም ግልጽ እንዲሆን መንግስት ለጥቂት ሰዎች የተሰጠ ወይም የሚሰጥ የግል ሀብት አይደለም። መንግስትም ወደ መጨቆኛ መሳሪያነት በመለወጥ ህዝብን ማሰቃያ መሳሪያ አይደለም። አንድን መንግስትና አገዛዝ መንግስት የሚያሰኛቸው የዲሞክራሲን መርሆችና የአሰራር ስልቶችን፣ እንዲሁም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን ህገ-መንግስትን ተከትሎ የሚሰራ ሲሆን ብቻ እንደመንግስትና እንደአገዛዝ ሊቆጠር ይችላል። ይህም ማለት በጠቅላላው በህገ-መንግስቱ ውስጥ ያሉትን በተለይም ደግሞ የህግ የበላይነትን ተከትሎ መስራትና ማንኛውም ዜጋ ካለምንም ወንጀል ሊጉላላም ሆነ ሊታሰር የማይችልበትን ሁኔታን መፍጠር ነው። ከዚህም ባሻገር በተለይም እንደ አገራችን ባለ በብዙ ችግሮች በተወጠረ አገር ውስጥ የመንግስት ዋናውም ተግባር ከታች ወደ ላይ ተቋማትን በመገንባት ህዝባዊ አገልግሎቶችን መስጠት ነው። በየቦታው የሰለጠኑ ተቋማት ሲቋቋሙ ብቻ ነው የአንድን አገር የተፈጥሮ-ሀብትና የሰውን ጉልበት በማንቀሳቀስና በማስተባበር አገርን በሁሉም አቅጣጫ መገንባት የሚቻለው። ህዝብም ቀስ በቀስ ሲማርና ሲያውቅ የበለጠ አርቆ-የማሰብ ኃይሉ ስለሚዳብር ተግባሩ ሁሉ ቁም ነገሮች ላይ ማትኮርና መስራት ይሆናል። ፖለቲካም ከዚሁ አስተሳሰብ የሚመነጭ እንደመሆኑ መጠን በመጀመሪያ ደረጃ ስልጣን ላይ የሚወጡ ሰዎች ከፍተኛ የሞራል ብቃት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል። በራሳቸው ድርጊት የማይኩራሩና እራሳቸውን አጉልተው የሚያሳዩ ሳይሆን በእርግጥም የህዝብ አገልጋይ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። ባጭሩ ፖለቲካ ጥበብ እንደመሆኑ መጠን ከሌሎች ዕውቀቶች ጋር በመጣመር ታሪክ የሚሰራበት መሳሪያ ነው። ይህም ማለት አንድን ህዝብ በዕውቀትም ሆነ በስራ ለማበልጸግና ተከታታይነት ያለው ህብረተሰብ ለመመስረት የሚያስችል መመሪያ መሳሪያ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለኢትዮጵያ ኮርናን ለመከላከል እቤታችሁ ተቀመጡ ከማለት ሌላ ዓማራጭ መታሰብ አለበት – ሰርፀ ደስታ

በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር አብዛኛዎቻችን መንፈሳችን በፊዩዳላዊ አስተሳሰብ የታነፀ እንደመሆኑ መጠን ፖለቲካና መንግስት የሚሉትን ጽንሰ-ሃሳቦች አለመረዳት ብቻ ሳይሆን ፖለቲካን ወደ አንድ ግለሰብ በመለወጥ አንድ ግለሰብ እንደፈለገው የሚፈነጭበት መሳሪያ አድርገን እንቆጥራለን። በዚሁ ዐይነቱ አስተሳሰባችንም ለአምባገነን ወይም ለፋሺስት አገዛዞች ሁኔታዎችን እናመቻቻለን። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ ዛሬ በአገራችን ያለው ትልቁ ችግር ከአለፉት አራት ዓመት ተኩል ጀምሮ የተፈጠረ ሳይሆን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣና ስር የሰደደ በሽታ ነው። በየጊዜው ስልጣን ላይ የሚወጡ ኃሎች ፖለቲካንና የመንግስትን መኪናን ቂም-በቀል መወጣጫ መሳሪያ በማድረግ ህዝብን ፍዳ የሚያሳዩበትና አገርን የሚበታትኑበት አድርገዋቸዋል።  እንደዕውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ከ1945-1974 ዓመታት ባለው ጊዜው ውስጥ ብቻ ነበር ከሞላ ጎደል እፎይ ብሎ ይኖር የነበረው። አብዮቱ ፈነዳ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ፣ ይህም ማለት ለ48 ዓመታት ያህል እፎይ ብሎ ኖሮ አያውቅም። እንደዚህ ዐይነቱ ህዝብን የማሰቃየትና አገርን የማፈራረስ ሁኔታ ሊፈጠር የቻለው በተራውና ባልተማረው ህዝባችን ሳይሆን ተማርኩ በሚለውና አገርና ህብረተሰብ ምን ማለት እንደሆኑ ባልገባውና የታሪክን ውጣ ውረድነት ባላገናዘበ፣ ከዚህኛውም ሆነ ከዚያኛው ብሄረሰብ በተውጣጣ ምሁር ነኝ ባይ ነው። ለማለት የምፈልገው ሁኔታው እየተከማቸ በመምጣት በእንደዚህ ዐይነት ሰዎች ትከሻ ላይ እንዲወድቅ በመደረጉ መንግስትንና ፖለቲካን አገርን ማከረባበቻና ህዝብን መግደያና ማፈናቀያ ለማድረግ በቅተዋል። ነገሩ ሁሉ ከአቅማቸው በላይ ስለሆነ ሁሉንም ነገር ማመሰቃቀል ሆኗል ዋናው ተግባራቸው። ይህ ዐይነት ጥራት የሌውና እየተከማቸ የመጣ የተወሳሰበ ችግር በህዝባችን ላይ በቀላሉ ሊወገዱ የማይችሉ ህሊናዊና ባህላዊ ቀውሶችን ፈጥሯል። ሽማግሌዎችና ባልቴቶች የማይከበሩብት አገር ለመሆን በቅቷል። ህፃናትና ለአቅመ-አዳም የደረሱ ሴቶች እንደልባቸው የማይንቀሳቀሱባቸው ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፤ጥቂት የማይባሉም ጾታዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል። በአሁኑ ወቅት ወደ 17 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎቻችን አብደዋል ይባላል። ይሁ ሁሉ የሚያረጋግጠው ጭቅንቃላቱ በደንብ ያልተዋቀረና ምሁራዊ ብስለት የሌለውና ከብዙ አቅጣጫ ማየት የማይችል ኃይል ስልጣን ላይ ሲወጣ፣ ወይም ደግሞ ስልጣን ላይ ካልወጣሁ ብሎ አጠቃላይ ጦርነት የሚያውጅ ሃይል የመጨረሻ መጨረሻ እንደዚህ ዐይነት በቀላሉ ሊፋቁ ወይም መፍትሄ ሊገኝላቸው የማይችሉ ባህላዊ፣ ማህበራዊና የህሊና ቀውሶችን ይፈጥራል። ለምሳሌ አብይ አህመድና ግብረአበሮቹ ስልጣን ላይ ሲወጡ ሰፋና ጠለቅ ያለ ዕውቀት ቢኖራቸው ኖሮ ወያኔ 27 ዓመታት ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የወሰዳቸውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች በመመርመርና በምድር ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በማገናዘብ ፖለቲካቸውን ማስተካከል በቻሉ ነበር። አብዛኛዎቹ ከወያኔ ጋር ሆነው ስልጣን ላይ በነበሩበት ወይም አሽከር ሆነው በሚያገለግሉበት ዘመን የወያኔ አገዛዝ ተግባራዊ የሚያደርጋቸውን፣ ለምሳሌ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲንና ያስከተለውንና የሚያስከትለውን መዘዝ በፍጹም ለመረዳት አልቻሉም። የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲም ምን ምን ዐይነት ይዘቶች እንዳሉት በፍጹም የሚያውቁት ነገር የለም። በእነሱና በአብዛኛዎቻችን አስተሳሰብ ኢኮኖሚክስ ሲባል አንድ ዐይነት ብቻ ነው። የተለያዩ የኢኮኖሚ ቲዎሪዎች እንዳሉና ኢኮኖሚክስ ከሌሎች ነገሮች ጋር፣ ለምሳሌ እንደፊዚክስና ኬሚስትሪ፣ ማሽን ኢንዱስትሪ፣ በአጠቃላይ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ ጋር በጥብቅ በመተሳሰርና በመታየት ብቻ አገር መገንቢያ መሳሪይ መሆኑን የምንረዳ በጣም ጥቂቶች ነን።

ያም ተባለ ይህ ወደ አቶ ባይሳ ዋቅ ወያ ጽሁፍ ጋ ስመጣ ባይሳ መንግስትና ፖለቲካ ምን ማለት እንደሆኑ በደንብ የተረዳ አይመስለኝም። ዝም ብሎ ብቻ ችግሩ በመንግስትና በህዝብ ዘንድ ያለ ሳይሆን በተፋላሚዎችና በመንግስት መሀከል ያለ ነው በማለት የችግሩን ምንነት ሳይረዳ ለማለፍ ይሞክራል። ተፋላሚ የሚላቸውንም ኃይሎች ስም በዝርዝር ቢነግረን ኖሮ የእነሱን የርዕዮተ-ዓለም መሰረትና ዕውቀት ለማሳየት በሞከርን ነበር። ይሁንና እነዚህ ተፋላሚ የሚባሉ ኃይሎችን በደፈናው ስንመለከት ምንም ዕውቀት ሳይኖራቸው እዚህና እዚያ የጦር ትግል የሚያካሂዱና ህዝባችንን ፍዳ የሚያሳዩ ናቸው። ከዚህ ውስጥ ወያኔና ኦነግ ሸኔ የሚጠቀሱ ሲሆኑ፣ እነዚህ ኃይሎች ደግሞ ሰውን ከመግደል በስተቀር ምንም ዐይነት ዓላማ የሌላቸው ናቸው። ይሁንና እነዚህ ኃይሎች የአገዛዙ አንድ አካል በመሆንና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመንግስትና በውጭ ኃይሎች በመደገፍ በህዝባችንና በአገራችን ላይ አጠቃላይ ጦርነት ያወጁ ናቸው። በእኔ ዕምነት እንደተፋላሚ ኃይሎች የሚቆጠሩና  የመንግስትን  አገር አፍራሽ አካሄድ አጥብቀው የሚቃወሙና የሚታገሉ እንደፋኖ የመሳሰሉ አርበኞች ብቻ ናቸው።  ባሁኑ ወቅት ከዚህ ውጭ መንግስትን የሚፋለም ሌላ ኃይል የለም። ለዚህ ነው አቢይና ግብረ-አበሮቹ የፋኖን ታጋዮች የሚያሳድዷቸው፣ የሚያስሯቸውና የሚገድሏቸው።

ወደሌላው ወደ አገር መፈራረስ ጉዳይ ላይ ስመጣ ይህች አገር ፈራርሳ በአዲስ መዋቀር አለባት ብሎ የተነሳ ኃይል በግልጽ ያለ አይመስለኝም። ይህ የአንተ የባይሳ ፈጠራና ፋንታዚ ብቻ ነው። አገርን ማፈራረስ አብዛኛውን ጊዜ የሚፈጠረው ካለማወቅ የተነሳ ወይም ለስልጣን የሚታገሉ ኃሎች ሳይንሳዊ ዕውቀት ሳይኖራቸው እዚህና እዚያ የሚፍጨረጨሩ ሲሆን ብቻ ነው። በመሰረቱም የአንድ አገር መፍረስና አለመፍረስ የሚፈጠረው በውስጥ ኃይሎች አማካይነት ብቻ ነው። የተማረ፣ የነቃና ፖለቲካ ማለት ምን ማለት እንደሆነ የገባው አገዛዝና ምሁራዊ ኃይል በአንድ አገር ውስጥ ካለ አንድ አገር የመፈራረስ አደጋ አያጋጥማትም። በአንፃሩ በራሱ የማይተማመን፣ ጠለቅ ያለ ዕውቀት የሌለውና የአገር ወዳድነት ስሜትን ያልተጎናጸፈ የፖለቲካ ስልጣንን ከተቀዳጀ አንድ አገር በቀላሉ የመፈራረስ አደጋ ያጋጥማታል። ስለሆነም ስለአገር መፈራረስ በምናወራበት ጊዜ የራሳችንን ዕውቀትና ሚና የግዴታ መመርመር አለብን። የችግሩ ምንጭም ራሳችን መሆናችንን መገንዘብ ያስፈልጋል። በሌላ አነጋገር፣ በቂ ዕውቀትና የሞራል ብቃት ስለሌልን እርስ በራሳችን እይተሻኮትን አገራችንን እዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ላይ ለማድረስ ችለናል። የውጭ ኃይሎችም የእኛን ድክመት በመጠቀም፣ አንተ ከዚኸኛው ብሄረሰብ የወጣህ ነው፣ በዚያኛው ብሄረሰብ ስትበደል የኖርክ ነህ፣ ስለሆነም ራስህን ነፃ ማውጣት አለብህ ብለው በማታለልና በመደገፍ በአንድ አገር ውስጥ የእርስ በርስ ግብግብ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። በተለይም ከ1945 ዓ.ም በኋላ የተፈጠረው ሁኔታ፣ በተለይም ደግሞ ከ1980ዎች ጀምሮ የተስፋፋው ግሎባላይዜሽን በየአገሮች ውስጥ ያለውን የተወሰነ ቀውስ ልዩ መልክ በመስጠት ሊያፋፍመውና ከአገዛዞች ቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ለማድረግ በቅቷል።  እንደኛ ያሉ አገዛዞች ከአቅማቸው በላይ ከሆነ ሁኔታ ስለሚጋፈጡ የሚሆን የማይሆን ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ባለው በሽታ ላይ ሌላ በመጨመር ሁኔታው እንዲባባስ ያደርጋሉ። ከዚህም በላይ የኮሙኒስት ብሎክ ከፈረሰ ከ1989 ዓ.ም በኋላ በአሜሪካን የተዋቀረና የሱን የበላይነት የሚያረጋግጥና፣ በአብዛኛዎቹ የካፒታሊስት አገሮች ተቀባይነት ያገኘ ዓለምና የዓለም ህዝብ በአንድ ህግና ደንብ መተዳደር አለባቸው( Rule Based System) የሚለው አምባገነናዊ አካሄድ አንዳንድ ሁኔታዎችን በመጠቀም ጣልቃ-መግባት እንዲቻል አድርጓል። ኢራቅ ውስጥ ጣልቃ መግባትና የብዙ ሺህ ዐመታት ያለውን የታሪክ ቅርስ ማፍረስና ሳዳምን አውርዶ የዛሬው ሁኔታ እንዲፈጠር የተደረገው የሳዳም ሁሴንን አገዛዝ አቶም ቦምብ ለመስራት የሚያስችል ዩራኒየም አከማችተሃል፣ እየሰራህበትም ነው በሚል የውሸት ውንጀላ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ አሜሪካ አቶም ቦምብ ከሰራ ሌሎች አገሮችም የመስራት መብት አላቸው። አቶም ቦምብን ለመስራት ለአሜሪካ ብቻ ማን ነው መብት ሰጠው? አቶም ቦምብንስ ለመስራት ለምን ያስፈልጋል?  የሚያድረሰው ጥፋትና አደጋ እየታወቀ አሜሪካና አንዳድ አገሮች እንደዚህ ዐይነቱን የሰውን ልጅ የሚያወድምና አካባቢን በራዲዮ አክቲቭ ንጥረ-ነገሮች የሚበክል ነገር ለምን ይሰራል? እንደዚህ ዐይነቱ አስተሳሰብስ ለምን ይደረሳል?  ለማንኛውም ጋዳፊም ከስልጣን እንዲወርዱና እንዲገደሉ የተደረገው አፍሪካን የኢንዱስትሪ አብዮት ባለቤት ለማድረግ የግዴታ በወርቅ የሚደገፍ ዲናር ተብሎ የሜጠራ ገንዘብ ማተማ ያስፈልጋል ብለው ስለተነሱ ነው። ይህም እንደ አደጋና የአሜሪካንና የተቀረውን የካፒታሊስቱን ዓለም የበላይነት የሚቀናቀን አካሄድ ሆኖ ስለተወሰደ እነ ጋዳፊ የመሳሰሉ መሪዎች ከስልጣን ላይ መወገድ አለባቸው። ዛሬ ሊቢያና የሊቢያ ህዝብ ያሉበትን ሁኔታ መመልከቱ በቂ ነው። ዛሬም በሩሲያ ላይ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም አቀነባባሪነት የሚካሄደው የውክልና ጦርነት ራሺያን አፈራርሶና ሰነጣጥቆ ሀብቷን ለመዝረፍ ነው። አንድ አገር ስትሰነጣጠቅና ስትከፋፈል ደግሞ  በቀላሉ የሚሆን የማይሆን  የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ፤ እንዲሁም ስልጣን ላይ ያሉትን ማኒፑሌት በማድረግ በአጠቃላይ ሲታይ አንድን ህዝብ ማዳከምና የራሱ የሆነ እሴትና ሃይማኖት እንዳይኖረው ማድረግ የአሜሪካና የተቀረው የካፒታሊስቱ ዓለም ዋና ዓላማ ነው። የዓለም ማህበረሰብ በጠቅላላው ኢ-ሞራላዊና እ-ስነምግባራዊ በሆኑ ነገሮች ጭንቅላቱ መወጠር አለበት። ብዥ ብሎና ነገሩ ሁሉ ተምታቶበት እንዲኖር ያስፈልጋል። የካፒታሊስቶ ዋናው ዓላማ ጥሬ-ሀብትን መዝረፍና የትርፍ ትርፍን ማካባት ብቻ ስለሆነ የዓለም ማህበረሰብ በሙሉ በዚህ ዐይነቱ ባህለቢስ አስተሳሰብ መተዳደር አለበት። በአጭሩ በአሜሪካን የሚመራው የካፒታሊስቱ ዓለም ጦርነትን በዓለም አቀፍ ደራጃ በማስፋፋት ህዝቦች በሰላም እፎይ ብለው እንዳይኖሩ ማድረግና፣ አገሮችን ማዳከም ነው። የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንዳይሆኑ በማደርግ ለዝንተ-ዓለም ደሃ ሆነው እንዲቀሩ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አደባባዩ ምን ያህል ይርቃል? – ከተመስገን ደሳለኝ (ጋዜጠኛ) ወደ ሌላው ባይሳ ወዳነሳው ነጥብ ስመጣ አቀራረቡ እርስ በርሱ የሚቃረን ነው። በአንድ በኩል በሶቭየት ህብረትም ሆነ በዩጎዝላቢያ በጊዜው የተፈጠረው ሁኔታና መፈረካከስ የውጭ ኃይሎች አሻጥር እንዳለበት ለማመልከት ሞክረሃል። ይህም ትክክል ነው። ችግሩ ግን ይህንን ጉዳይ ከኢምፔሪያሊዝምና ከግሎባል ካፒታሊዝም ጋር በፍጹም አላያያዝከውም። ግሎባል ካፒታሊዝም ወይም ኢምፔሪያሊዝም በመሰረቱ በመስፋፋትና ሌሎች አገሮችን በማዳከምና ወደ ጥሬ-ሀብት አውጭነት በመለወጥ የተፈጠረ ስርዓት ነው። ስለሆነም ተወዳዳሪ ኃይል እንዳይኖር የሚቻለውን አሻጥር ሁሉ ነገር ከማድረግ አይቆጠብም። በአንዳንድ አገሮች የአገዛዝ ለውጥ ወይም ሬጁም ቸንጅ እየተባለ የሚካሄደው ጣልቃ ገብነት ዋናው ዓላማውም አገሮችን መበታተንና ወደ ተበዝባዥነት መለወጥ ነው።

ከዚህ ሃቅ ስንነሳ አንተ ያነጋገርካቸው ዲፕሎማቶችና ኢትዮጵያ እንድትበታተን አንፈልግም ያሉህ ዕውነቱን አልነገሩህም። ሌባ ሌባ ነኝ ብሎ ራሱን እንደማያጋልጥ ሁሉ እነዚህ ዲፕሎማቶች የሚባሉት ኢትዮጵያ እንድትበታተን ነው የምሰራው ብለው ሊነግሩህ አይችሉም። እንደዚህ ብሎ ማመንና መቀበልም የአንተን አላዋቂነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን የአሻጥር ፖለቲካ በቅጡ አለመረዳት ነው የሚያሳየው። በመሰረቱ ለአንድ አገር መበታተን አንድ አገር እንደ አገር ብቻ ሆና መቆየቷ በቂ አይደለም። አንድ አገር እንደ አገር ልትኖርና ለተከታታዩም ትውልድ ለመተላለፍ የምትችለው በፀና የኢኮኖሚ መሰረት ላይ ስትገነባ ብቻ ነው። ልዩ ልዩ ተቋማትና ቆንጆ ቆንጆ ከተማዎች ሲኖራትና እነዚህም በተቀላጠፈና በዘመናዊ የመመላለሻና የመገናኛ ዘዴዎች ሲገናኙ ብቻ የአንድ ህዝብ የማስብ አድማስ ይሰፋል፤ ፈጣሪም ይሆናል። ጠንካራና ምሁራዊ የህብረተሰብ ኃይል በመፈጠር ለተከታታዩ ትውልድ ታሪክን በመስራት ያስተላፍል። እንደዚህ ዐይነት መሰረት የሌለው አገር የመፈራረስ ኃይሉ ከፍ ያለ ነው። በተለይም ከ1980 ዓ.ም ጀምሮ በአብዛኛዎች የአፍሪካ አገሮች፣ በአገራችን ምድር ደግሞ ህውሃት ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ የገበያ ኢኮኖሚን እናስፋፋለን ተብሎ የተወሰደው የጥገና ለውጥ የሚሉት በመሰረቱ የመዋቅር ማስተካከያ ፖሊሲ(Structural Adjustment Programs)  ዋና ዓላማው በሳይንስና በቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሰረተ የተወሳሰበና ግልጽነት ያለው የገበያ ኢኮኖሚ ማስፋፋት ሳይሆን ዘራፊ መንግስት በማቋቋምና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በማደለብ ሁለ-ገብ ዕድገት ተግባራዊ እንዳይሆን ማገድ ነው። የዓለም አቀፍ የገንዝበ ድርጅት፣ የዓለም ባንክና የአውሮፓው አንድነት የኢኮኖሚ ፍልስፍና ኒዎ-ሊበራሊዝም ሲሆን፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ይህንን የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ-በመሰረቱ ፖሊሲ  ያልሆነ- እንዲቀበሉት በማድረግ ሸመድማዳ አገርና መንግስት እንዲፈጠሩ ማድረግ ነው። ስለሆነም አንተ ያነጋገርካቸው ዲፕሎማቶችና ሌሎችም ዛሬ ኢትዮጵያ ለደረሰችበት ሁኔታ ተጠያቂ ናቸው። ወያኔን አቅፈው ደግፈው ስልጣን ላይ በማውጣት የጎሳ ፌዴራሊዝም ተግባራዊ እንዲያደርግ የገፋፉትና ህዝባችንም የአንድነት ስሜት እንዳይኖረው ያደርጉ አጭበርባሪዎች ናቸው። ዲፕሎማሲም ማለት ሳይንስ ሳይሆን ማጭበርበሪያ መሳሪያ ነው። ስለሆነም አንተ ያነጋገርካቸው ዲፕሎማቶችም ሆኑ፣ አሜሪካና የተቀረው የካፒታሊስቱ ዓለም ኢትዮጵያ እንድትበታተን አይፈልጉም የሚለው አጉል አባባል ከፖለቲካ ሳይንስ ውጭ የሆነ አስተሳሰብ ነው። አንድን አገር ለማፋረስ ብዙ መሳሪያዎች ስላሉና የረቀቁም ስለሆነ ጽሁፉን ላለማራዘም ስል እዚህ ላይ እቋጨዋለሁ። አንድ ሳልጠቅስ የማላልፈው ጉዳይ አለ። ይኸውም የጥቅምን ጉዳይ አንስተሃል። ሌሎች ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ተንታኝ ነን ባዮች አሜሪካ በኢትዮጵያና በአካባቢው ላይ የጄኦ ፖለቲካ ጥቅም አላት እያሉ ይናገራሉ። ለመሆኑ የአሜሪካንና የተቀረው የካፒታሊስቱ አገር ከኢትዮጵያ የሚፈልገው ጥቅም ምንድነው? እንደዚህ ብለን ስንጽፍስ ምን ማለታችን ነው? አንድን አገር ተቀጥያ ወይም ጭራ ማድረግና ዕድገቱና ማቀጨጭ? ወይስ ደግሞ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት እንድትሆን በማድረግ የተረጋጋ ማህበረሰብ ወይም ህብረተሰብ እንዲፈጠር ማድረግ?  በመሰረቱ የአንድ አገዛዝ ጥቅም በራሱ አገር ውስጥ ያለና አገሩን በተስተካለና በእኩልነት መገንባት ነው። ከሌሎች አገሮች ጋር የሚኖረው ግኑኝነት ግን በመከባበር ላይ ብቻ የተመሰረተ መሆን አለበት። ከዚህ ውጭ የሚታሰብ አስተሳሰብ ኢ-ሳይንሳዊና ኢ-ፍልስፍናዊ ነው። የተከበርከው ውድ ወንድሜ ባይሳ ዋቅ ወያ ይህንን ጉዳይ ግልጽ እንድታደርግልኝ እፈልጋለሁ።

መልካም ግንዛቤ!!

በቪዲዮ ኮንፈረንስ በአንዳንድ ነገሮች ላይ በግልጽ ለመወያየትና ትምህርት  ለመቅሰም የሚፈልግ  መመዝገብ ይችላል።  ሁሉ ነገር ተዘጋጅቷል።  ቢያንስ  20 ሰዎች  ተካፋይ  መሆን  አለባቸው። የውይይቱወይም የትምህርቱ ጊዜ ሁለት ሰዓት የሚፈጅ ሲሆን፣  በተካፋይ 20 ኦይሮ ወይም ዶላር የሚያስከፍል ነው። የሚሰጠውም ትምህርት ሳይንሳዊና በየጊዜው በአዲስ መልክ የሚቀርብ ይሆናል።

Fekadubekele@Gmx.De            

Www.Fekadubekele.Com   

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop