ከመቅረት መዘግየት በሚል እሳቤ የቀረበ ጭፍን ጥላቻ አስተያየት አይደለም ሊሆንም አይችልም!! – አኒሳ አብዱላሂ

ኢሕአፓ 75ኛውን፣ ከዛም 100ኛውን አለፍ ብሎም 150ኛውንና 200ኛውን የሚያከብርበት ጊዜ ይመጣል።

ይድረስ ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ

በት

25.09.2022 . .

አኒሳ አብዱላሂ

እንደ መግቢያ

ማስታወሻ

በቅርቡ በወለጋ በደረሰው ኢሰብአዊ የሆነ የዘር ማፅዳት ፍጅት አንዲት ከጭፍጨፋው የተረፈች ሴት ሕፃን ልጅ ወላሂ ሁለተኛ አማራ አልሆንም የሚል አረፈተ ነገር መናገሯና በግድያው መትርፏ ያናደዳቸው ጨፍጫፊዎች ልጅ ወልደው ለመሳም ያልታደሉና የልጅን ፍቅር የማያውቁ አረመኔዎች ምንም ሳይሰቀጥጣቸው እየሳቁ በጥይት እሮምታ የልጅነት ሕይወቷን ሲቀጩት የሰሙ እናት ድርጊቱን ሕዝብ እንዲያውቀውና ከታሪክ ማህደር እንዲዘገብ አስተዋፅዖ ላባረከቱት እናት ልባዊ ምስጋና ይድረሳቸው። ውለታቸውንም መሰል ጭፍጨፋዎች በማናቸውም የህብረተሰብ ክፍል ሆነ ግለሰብ ላይ እንዳይደርስ በትግሉ ድል አድራጊነት እንዲቋጭ ካለፈው በበለጠ ሀገር ወዳድና ለሕዝብ ቀናኢ የሆኑ ሁሉ የየበኩላቸውን የሚቻላቸውን ያህል አስተዋፅዖ ለማበርከት የውስጥ ግፊት እንዲሰጣቸው አበክሬ እማፀናለሁ።

በውነቱ በዚች ሴት ሕፃን ላይ የወረደባት የጭካኔ በትር ማንንም የሰብአዊ ፍጡር በዘር ጥላቻ ሕሊናቸው ከታወሩት በስተቀር ያላሳዘነውና ያላበሳጨው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። በርግጥም የዚህ አይነት መሰል ድርጊቶች ለረጅም እድሜ ቀመስነት የታደልንና አራት አገዛዞችን ያሳለፍን ኢትዮጵያዊያን በየቦታው ኢሰብአዊ የግፍ ድርጊቶች በሰላማዊ ዜጎቻችን ላይ ሲፈፀም በሀዘን የተኮማተርንባቸውና ያለቀስንባቸው ቀናቶች አሁንም ድረስ ከሕሊናችን ያልጠፉ ናቸው።

በጃንሆይ አገዛዝ ዘመን በተደረጉ የግፍ ግድያና ጭፍጨፋ ሳቢያ አልቅሰናል፣ አዝነናል፣ ቀረርቶ አቅራርተናል፣ የትግል ቃል ኪዳን አድሰናል። በደርግ ጊዜም እንዲሁ ወገኖቻችን ሕፃን፣ ሽማግሌ፣ አሮጊት፣ ወላጅ እናቶችና አያቶች በመኖሪያ ቤታቸው ታጉረው በእሳት ተቃጥለው ሕይወታቸው እንድታልፍ ተደርጓል። በቀይ ሽብር ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለተለያዩ እንግልቶች የተዳረጉ፣ የቁም ስቅልን የቀመሱ ቁጥራቸው በቀላሉ የሚገመት አልነበረም። በወያኔ አገዛዝ 700 የሚበልጡ ዜጎቻችን በግፍ የተገደሉበት ብቻ ሳይሆን እናት በልጇ ሬሳ እንድትቀመጥ ተደርጋ ገዳዮች ሲሳለቁ አይተናል፣ ተመልክተናል፣ ከንፈር መጠናል፣ የሀዘን ልብስ ለብሰን ሬሳ ቀብረን አልቅሰናል፣ ሀዘናችን ወሰን አጥቷል።

በለከት የለሹ ፍፁም ዘረኛና ውሸታም ግፈኛ ግለሰብ በሚመራ አገዛዝ ሥር ደግሞ ትኩሱ ሬሳ ደረቁን አስረሳ ይመስላል ሕፃናትን እንደ ዶሮ የሚያርድና እርጉዝ ሴትን በሳንጃ ዘልዝሎ ለውልደት ያልበቃ ልጇን አውጥቶ ከሙት ደረት ማሳታቀፍ ብቻ ሳይሆን በገፍ የግድያ እርምጃ ተወስዷል። የሰጠነው ምላሽ ግን ድርጊቱን አቁሞ እንደ ሰው ፍጡር ለመኖር የሚያስችለንን ነፃነትን አልተላበስንም። ዛሬም ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ ሆኖብናል። የሀዘን እንባችን አልደረቀም። ልቦናችን እውነተኛ ደስታን አያንፀባርቅም። ከላይ የተጠቀሰቺው ህጻን ሕይወቷ እንዲቀጭ በተደረገበት ቀን በሺዎች ታርደዋል። ሬሳቸውንና የጅምላ መቃብራቸውን አይተናል። 20 ቀን ህጻን እስከ መቶ ዓመት አዛውንት በማንነታቸው ብቻ አዕምሮ ሊደርስበት፣ ብዕር ሊከትበው፣ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ተሰምቶና ታይቶ በማይታወቅ አረመኒያውነት በገዛ አገራቸው፣ ሰብአዊነት ውስጣቸው በሌለ ግፈኞችና ጨካኞች ሕይወት ሲቀጥፉ ምንም የማይስቀጥጣቸው አውሬዎች በተወለዱበት፣ ባደጉበት ለወግ ማዕረግ በደረሱበት ሀገራቸው ተመርጠው ስጋቸው ተዘልዝሏል፣ ቆዳቸው ተገፏል። ነፍሰ ጡሮች ጽንሳቸው በጪቤ ተተልትሏል።

ታዲያ መልሳችን ምን ሆነ? በምንም ይሁን በምንም በአምሳሉ ተፈጠረ ተብሎ የሚነገርለት ወገናችን ይህ ሁሉ ስቃይ እንዲደርስበት ምን ጥፋት ቢኖረው ነው? ለሚለው ጥያቄ ማንም መልስ ሊኖረው አይችልም። ከላይ የቀረቡት የተለያዩ የግፍ ተግባራት በወገናችን ቀርቶ በሌላም እንዳይደርስ ፅኑ ፍላጎት ቢኖረንም ማክተሚያውን አስመልክቶ የተለያዩ መላ ምቶች መቅረባቸው የምናስታወስ እናስታውሳለን። ምን ያህል እርምጃ ወደፊት እንዳራመድን ግን አላውቅም። ከስህተት ባለመማር በክፉ የበደል አዙሪት ውስጥ እየተርመጠመጡ ከሀገር ወዳድና ቅን አሳቢ የሚሰጥ ምክርን ለመስማት አሻፈረን የሚል በበዛበት ምከረው ምከረው እምቢ ካለ መከራ ይምከረው ተብሎ የሚታለፍ አለመሆኑን መገንዘብ የመጀመሪያው እርምጃ ይመስለኛል። በበኩሌ በዚህ ጉዳይ ላይ ከልቤ ውስጥ የታመቀውን ንዴትና በሀዘን የተሞላ ጭንቀቴን አርግፌ አንባቢን ተደራቢ ሰቀቀን ውስጥ መክተት አልሻም። ማለት የምፈልገውን ምናልባት ጠንከር ባሉ ቃላቶች እገልፀው ካልሆነ በስተቀር ጠገናው ጎሹና አገሬ አዲስ የተባሉ በተደጋጋሚ በሚገባ ከትበውታልና ምስጋና ይድረሳቸው።

ታዲያ በዚችን ሕፃን ሴት ላይ የደረሰባትን የግፍ ግፍ በመነሻነት በመውሰድ በአንድም ሆነ በሌላ የተለዩኝን የትግል አጋሮቼን ሻማ አብርቼ ያለፉትን የትግል አመታት በደስታም ሆነ በሀዘን ያሳለፍነውን ጊዜያቶች በሕሊናዬ እያስታወስኩ ራሴን በራሴ በማፅናናት ላይ እያለሁ ፕሮፌሰር ኃይሌ ላሬቦ የተባለ ቂመኛ ግለሰብ በሰው ቁስል እንጨት ስደድበት እንዲሉ የዚያን ትውልድ አባላት በሽብርተኝነት ወንጅሎ በሕይወት መኖራቸው ክፉኛ የተናደደበት ቅርሻቱን ሳልወድ በግድ እየተናነቀኝም ቢሆን አነበብኩት። ይህ ግለሰብ ራሱን የገለልተኝነትን ካባ አላብሶ እንደ ሰው ፍጡር እንኳን የዛ ትውልድ አባላት ያላቸውን ሰብአዊ ክቡርነትን ነፍጓቸዋል። በሌሉበትና ባልዋሉብት የሃሰት ታሪክ ፈልፍሎ ጥላሸት ቀብቷቸዋል፤ ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸውን ነጥቋቸዋል፣ ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ ሆነና የትግል አጋሮቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ከገደሉ፣ ለአካለ ጉድለትና ለሞት ለዳረጉ መጠነ ሰፊ የሆነ የመብት ጥሰቶችን ካካሄዱባቸው ጠላቶቻቸው ጋር በማዳበል ዘልፏቸዋል፣ አብጠልጥሏቸዋል፣ በውሸት ታሪክ ከሷቸዋል፣ ተዝካራቸውንም እንዲያወጡ ምክር ቢጤም ለግሷቸዋል፤ ሌላም ሌላም።

እንግዲህ መታገስም ገደብ አለውና ሳይፈልጉት ፈልጎ እማሬ ጣቱን ቀስሮ የጫረውን በአሎሎ እሳት ጠቅልሎ ወርውሯልና እሱ ራሱ እየበገነ ለመውደቅ የተቃረበች ሕይወቱ ታሸልማለች እንጂ በምንም አይነት በሱና በመሰሎቹ ዛቻ ትላንት ከትላንት ወዲያ አልጠፋንም፣ አሁንም አንጠፋም ወደፊትም የማንጠፋ መሆናችንን የሚገልጽ መልስ እስኪደርሰው ትዕግስቱን ይስጥህ እለዋለሁ።

አንባቢያን ይህ እንግዲህ ላሬቦ በጁላይ 6 2022 .. ለፃፈው የጥላቻ ትርከት በማስታወሻ መልከ የቀረበ ነበር። ከዛ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶችና እንዲሁም የጤና ችግር በመከሰቱ መጣጥፉን በወቅቱ አስናድቶ ለማቅረብ አልተቻለኝም ነበር። የሆኖ ሆኖ ከመቅረት መዘግየት መልካም ነው ይባላልና ከይቅርታ ጋር ለአንባቢያን ይኸው እላለሁ።

ምሁርነት ሌላ የምስክርነት መረጃ ሌላ

ፁሁፉን ለማቅረብ ውስጣዊ ግፊት የሰጠኝ በተለይ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምስክር መረጃ ያገኙ በተለይም ደግሞ የታሪክ ባለሙያ ነኝ ከሚሉ እንደነ ላሬባ አይነቶቹ የምሁርነት ካባ እየለበሱ አንድን ሁናቴ በተጣመመ መልኩ ሲያቀርቡ፣ ሲዋሹና ሲቀጥፉ በተደጋጋሚ በመታዘቤ ነው። ስለሆነም መሰል ሁናቴዎች በቸልታም ሆነ በግዴየለሽነት ከታለፉ በተለይ በወጣቱ ትውልድ ላይ የሚያስከትሉት አሉታዊ ተፅዕኖዎች በቀላሉ የሚገመቱ አይደሉምና በተከሰቱበት ቦታ ሁሉ እንዳቀራረባቸው ማጋለጡ ተገቢ ነው የሚል ፅኑ እምነት ያለኝ ብቻ ሳይሆን ለሕሊናዬ እረፍት የሚስጥ ማንነቴንም ገላጭ ነው። አሁን አሁንማ ቆዳዬ እየሳሳ ነው መሰለኝ በበኩሌ በዝምታ ፍ አይመቸኝም።

ይህንንም ስል ያለምክንያት አይደለም። ሁናቴው ከፖለቲካ አንፃር ሲገመገም በተለያዩ የእውቀት ዘርፎች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምስክርነት መረጃ ማግኘት በሙያው መስክ ካልሆነ በስተቀር በሀገር ጉዳይ፣ በነፃነት፣ በዴሞክራሲ፣ በእሴቶች፣ በማህበራዊ ሆነ ሀገራዊ አንድነት፣ በፍትህ ወዘተ የተለየ የከፍታ ቦታ ወይንም ደግሞ ልዩ አዋቂነትን የሚያላብስ አለመሆኑን መገንዘብ መልካምነቱ የማይታበል መሆኑን ከግምት በማስገባት ነው። ምክንያቱም የተማረ ሰው ሁሉ በደፈናው ምሁር ሊሆን አይቻለውምና። ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምስከር ወረቀት ማግኝት ምሁርነት ሳይሆን ባለሙያነትን የሚያላብስ ነው።

ምሁር ምን ማለት ነው?

ምሁር ለመሆን ከሙያተኛነት ባሻገር ለእውነት መኖርና ሁሌም እውነት መናገርን ይጠይቃል። በራሱ አሳቢ መሆን/በማረግ ምጥቁነትን የሚጠይቅ ነው። ምሁር የተወሳሰቡ ነገሮችን የመተንተን አቅም ኖሮት ለተለያዩ ችግሮች መፍትሄ ለማግኘት/ለማምጣት የሚጥር፣ በወቅቱ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን አስተሳሰብ ወደፊት የማያስኬድ ሆኖ ከተገኘ፣ ባጭሩ ለእድገት እንቅፋት ሆኖ ከተገኘ አውልቆ ጥሎ በአዲስ ለመተካትም ሆነ ለመቀየር ከልቡ ጥረት የሚያደርግ፣ ግለኝነት የማያጠቃውና በቡድን መስራትን የሚያምን በግሉም ሃሳብ አመንጪና በሙሉ ድፍረትም ኃላፊነት ወስዶ የሚወጣ፣ ሌሎችን በምክንያታዊ መረጃ በማስደገፍ የማሳመን/የማግባባት አቅም ያለው፣ የተበታተኑ ሃሳቦችን ወደ አንድ ቦታ ስብሰብ አድርጎ እምብርቱን ለማስረዳት ወይንም ለማሳየት ችሎታ ያለው፣ ያለፈውን ከወቅቱ ጋር አጣምሮ የወደፊቱን አማትሮ ለማየት ሁሌም ጥረት የሚያደርግ ነው። ምሁር በእውቀት፣ በምክንያትና በእውነታ ላይ የተመሰረተ ሰብዕና፣ አርቆ አስተዋይነት፣ ሚዛናዊነት፣ ፍትሃዊነት፣ ሕዝባዊ ወገተኛነት መገለጫ የተላበሱትን እንጂ በጭፍን ጥላቻ ተለክ ጠላትነትን በዜጎች መካከል የሚዘራ አይደለም። ምሁር የህብረተሰቡን ኑሮ በጥናት አስደግፎ ለእድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን ነጥሎ በማውጣት መፍትሄ ለማቅረብ የሚተጋ/የሚጥር ነው። በተለይም ደግሞ ተመክሮን ለእውቀት ማግኛ ጠቃሚነቱን የተገነዘበና ተግባራዊ ለማድረግም በከፍተኛ ደረጃ ጥረት የሚያደርግ ነው።

አንባቢያን ከዚህ ግንዛቤ ተነስቼ ትኩረቴን ወደ ላሬቦ ሳደርግ ግለሰቡን በግል ደረጃ አላውቀውም፣ ተገናኝተንም ስለማናውቅ ስለሱ የሰማሁት ለመጀመሪያ ጊዜ በኢሳት የቴሌቪዥን ስርጭት ቀርቦ በሰጠው ቃለ መጠይቅ ተከትሎ የሱ ተቃዋሚዎች ባቀረበው አስተያየት ላይ ተመርኩዘው ብቻ ሳይሆን በግለሰቡ ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ወከባዎችና የሱንም የአፀፋ መልስ ለመከታተል እድሉ በገጠመኝ ጊዜ ነው። ያም ሆኖ አልፎ አልፎም ቢሆን ለእይታ ያቀረባቸውን መጣጥፎችን ለማንበብ ብችልም ስለ ላሬቦ ማንነት በቅጡ አውቃለሁ ማለት አይደለም። ከዚህም ከዚያም ብዥታ የሚፈጥሩ ነገሮች መስማቴ ባይቀርም። ስለሆነም ከላይ እንዳቀረብኩት ትችቴ የሚያተኩረው ኢሕአፓ የተመሰረተበትን 50 ኛውን አመት በማክበሩ ምክንያታዊ ሳይሆን በጥላቻ ላይ ብቻ የተመሰረተ የጭቃ ጅራፉን በማጮሁ ነው። ምክንያታዊ የሆኑ በትክክለኛ መረጃ ላይ በመንተራስ የሚቀርቡ ማናቸውም ተቃውሞዎችና አስተያየቶች በተለይ በትግል ላይ ለተሰማሩ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ግለሰቦች ላይ ቢቀርቡ በገንቢነታቸው እንጂ በአሉታዊነት የሚታዩ አይደሉም። አይሆኑምም። በዚህ ክብሬ ተነካ ብሎ የሚያኮርፍ ግለሰብም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት ያውም በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት የሚጥሩ ከሆነማ ራሳቸውንም ሆነ ማንነታቸውን ከማስገመት ውጭ የሚያተርፉት ምንም ነገር አይኖርም። ላሬቦም የማቀርብበትን ሂስ በዚህ እይታ ቢመለከተው ይጠቅመዋል እንጂ አይጎዳውም። አይ ካለና በጀመረው መንገድ ከቀጠለ ግን በጭፍን ጥላቻ ላይ የተመረኮዘ በሽታው ይበልጥ ይጎዳዋልና ከወዲሁ ወደ ሕክምና ጎራ ቢል የሚል ምክሬን ተቀበለም አልተቀበለም እለግሰዋለሁ። ይህንንም ስል አለምክንያት አይደለም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የመለስ መታሰቢያ ተቋም (Foundation) የደቀነብን አደጋዎች! - ክፍል 1 - ከግርማ ሞገስ

ጭፍን ጥላቻን አስመልክቶ ምሁራኖች ምን ይላሉ?

ባለችን የእውቀት መስክ ስለ ጭፍን ጥላቻ ለመገንዘብ እንደቻልኩት በመስኩ በርካታ ጥናታዊ ምርምር ያደረጉ ምሁራኖች እንደሚገልፁት ጭፍን ጥላቻ የፍቅር ተቃራኒ ስሜት ሲሆን የሰውን ፍጡር ሰብአዊነቱን ማጥላላት ብቻ ሳይሆን የአካልና የመንፈስ ጉዳት እንዲደርስበት የሚገፋፋ ስሜትን ያቀፈ መሆኑን ነው። ምንጩም ከግል ጥቅም፣ ቅናት፣ የተሰናከለ ወይንም ደግሞ ለፅኑ ልባዊ ፍቅር አፀፋዊ መልስ ያላገኘ/የተነፈገ፣ ከፍ ያለ ጉጉት፣ ምኞት፣ ቅናት ላይ የሚፅነስ ሲሆን ፈጣን በሆነ ሁናቴ የሚሰራጭ /የሚሳፋፋ በመሆኑ የሚለከፉትን ሁሉ ለማይድን በሽታ የሚያጋልጥ አዕምሮን የሚመርዝ ነው። ጥላቻ እጅግ ጥግ የሚነካ ማጥላላት ሲሆን በሰው ፍጡር ላይ ብቻ ሳይሆን በተቋም ላይም የሚደረግ አስፀያፊ ተግባር ነው። አንድነትን ሳይሆን ክፍፍልን፣ መከባበርን ሳይሆን መናናቅን፣ እድገትን ሳይሆን ክስረትን፣ አዋላጅ ነው። ጭፍን ጥላቻ ወዳጅን ጠላት ጠላትን ወዳጅ ያስደርጋል፡፡ ጭፍን ጥላቻ እውነትን ሀሰት ሀሰትን እንደ እውነት ያሳያል፡፡ ጭፍን ጥላቻ ስሜታዊነትን ባለቤት በማድረግ ከምክንያታዊነት ያርቃል፡፡ ወያኔም ሆነ በብልፅግና ጉያ ተሸጉጠው በአማራና በኢትዮጵያዊነት ላይ የሚነዛው የማጥላላት ዘመቻ መሰረቱ ይኸው እንደሆነ ምስክር መጥራት/ማስረጃ ማቅረብ አይጠበቅብኝም። ጭፍን ጥላቻ ይሉኝታ ቢስነትን የማንነቱ መገለጫ በማድረግ ሕብረተሰቡ በመልካምነት ከተቀበላቸው የሞራል እሴቶች በእጅጉ ማራቅ ብቻ ሳይሆን ችግሮችን ይበልጥ ቀፍቃፊ ሆኖ ይከሰታል። ጭፍን ጥላቻ በአርቆ ማሰብ መቃብር ላይ ለአርቆ አለማሰብ ሃውልት ያሰራል፡፡ በአማራም ሆነ በሌሎች በርካታ ዜጎቻችን ላይ የደረሰው ጭካኔ የተሞላበት ግድያና ጭፍጨፋ የዚሁ ጥላቻ ነፀብራቆች ናቸው። የአኖሌ ኃውልት መገንባት የዚሁ ውጤት ነው።

ጭፍን ጥላቻ አቋም አልባነትን በመያዝ አቋም መያዝን በእጅጉ ይጠየፋል፡፡ መሃል ሰፋሪም ሆነ ገለልተኛነት ምንጫቸው ይህ እንደሆነ በርካታ ጥናቶች የሚያመላክቱት ናቸው። ጭፍን ጥላቻ ራስን ከመጠየቅ የበለጠ በሌላው ላይ በማተኮር ከታሪክም አንፃር ሲታይም ለወደፊቱ ሊሆን በሚችለው ሳይሆን ባለፈ ታሪክ ላይ ብቻ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ መመልከትን ባሕሪያዊ የህልውናው መሰረት ያደርጋል፡፡ ጭፍን ጥላቻ ዝቅጠትን እንደ ዕድገት፤ ውርደትን የተከበረ አይነታ አድርጎ የሚሰብክ በመሆኑ ብቅ ሲል ካልገቱት በዜጎች መካከል ሊኖር የሚገባውን መልካም ግንኙነት ያፋልሳል፣ ማህበራዊ ሰላምንና አንድነትን ያናጋል። መተማመን እንዳይኖር ያደርጋል። ጭፍን ጥላቻ ከዕምነት፣ ከሃቅ፣ ከመርህ፣ ከአቋም፣ ከነጻነት በእጅጉ ርቆ ከስሜት፣ ከውሸት፣ ከማስመሰል፣ ከሴራ፣ ከባርነትና ከበታችነት ጋር ተጣምሮ መገልገያ ካረጉት የሚያስከትለው ውጤት የብዙ ችግሮች ምንጭ ከመሆን ባለፈ የብዙ ሀገራዊና ሕዝባዊ ችግሮች መዳኛ የሕክምና አግልግሎት የሌለው ደዌ/በሽታ እንደሚሆን በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ላይ በተደረጉ ጥናቶች ለማረጋገጥ የተቻለበት ዘርፍ ነው። ለዚህም ነው ጭፍን ጥላቻ ያለ ጠላትነት ጠላትነት ያለ ጭፍን ጥላቻ ፈጽሞ ሊኖር አይችልም ተብሎ አፅንዖት በተሞላበት መልኩ እየተገለፀ የሚገኘው። ጭፍን ጥላቻና ስድብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎችን በመሆናቸው ያለ ስድብ ጭፍን ጥላቻ ሊከሰት አይችልም።

በመሆኑም ላሬቦ በጭፍን ጥላቻ የታወረ ግለሰብ በመሆኑ የኢህአፓን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎችን ከጥላቻና ከጠላትነት አንጻር ብቻ የተመለከተ እንደሆነ ባቀረበው መጣጥፉ ተመላክቷል። በዚህም የተነሳ የጠላውን አካል ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በአሉታዊነት በመተርጎምና ጥላሸት በመቀባት በደርግ ዋሾዎች ተመርኩዞ የማይገናኙትን በሰም አጣብቆ ለማውገዝ ተጠቅሞበታል። በጭፍን ጥላቻ የታወረ ግለሰብ፣ ቡድንና ተቋም ለነፃነቱ እታገልለታለሁ፣ እወክለዋለሁ ለሚለው ሕዝብ ፍቱን መድኃኒት ሳይሆን በሽታ ነው። አንድን ሀገር በሁለንተናዊነቱ የሚጎዳ ነው። ወያኔ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ ያለፉትን 30 -40 አመታት በጥሞና ብንመለከት ጥላቻን በመዝራት የጥላቻ ፍሬ እንዲበራከት ያስቻሉ ሁኔታዎችን እያዳበርን የምንገኝ ለመሆናችን በገሃድ የምንመለከተወና የምንኖረው እውነታ ነው። የላሬቦ መጣጥፍም የዚሁ ነፀብራቅ ነው። ለህዝብ ወግኖ መታገል ማለት የላሬቦንና መሰል መጣጥፎችን እንዳመጣጣቸው ፍትንትን አድርጎ በማጋለጥ ሕዝብ ወጊዱልኝ እንዲላቸው አበክሮ በፅናት መታገል ማለት ነው።

የምሁር በሉን ባዮች ዋሾነት ኪሳራ

ሁሌም የሚገርመኝ ነገር ቢኖር ምሁራን ነን ባዮች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም የተሰጣቸውን ወይንም ደግሞ ያገኙትን የምስክር መረጃ በግላቸው የሚያኮራቸው ለወገንም ሆነ ለወጣት ትውልድ በአርአያነት ለመመልከት ቢያበቃቸውም በሁሉም ጉዳይ እናውቃለን ጠባይ ለምን መላበስ እንደሚፈልጉ ወይንም ደግሞ መጠቀሚያ እንደሚያደርጉት ነው። በመሆኑም ትችቴ የሚያተኩረው ባቀረበው አስተያይት ላይ እንጂ እሱ አስቀድሞ ለመከላከያ ያመቸው ዘንዳ ፀሃፊውን መሳደብ፣ ያልሆነ ሥም በማውጣት ወይንም ከወራዳ ድርጅት ጋር በማያያዝ ማሸማቀቅ እንደ ኃይሞኖት ቀኖና አድርገው ይዘውታል እንደሚለው ሳይሆን ባቀረበው መጣጥፉ ላይ ብቻ የሚያተኩር ነው። በግለሰቡ ማንነት ላይ ሊሆን አይችልም። ይህንን በማድረጌ በማዕረጌ ቀንተህ ነው እንደማይለኝ ግን ተስፋ አደርጋለሁ። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የአንድን ሀገር ከፍተኛ የመንግስት ሥልጣን በተወሰነ የታሪክ አጋጣሚ ለመጨበጥ እድሉን ያገኙ ለምን ዋሾነት እንደሚያጠቃቸው ነው። የወያኔዎቹ ከፍተኛ ባላስልጣናት መለስም ሆነ ስዩም መስፍን የወቅቱም ኮሎኔል ጠሚዶ በዚህ በኩል በአይነተኛ ተምሳሌት ሊጠቀሱ የሚችሉ ለመሆናቸው ፀሃይ የሞቀው እውነታ ነው። ላሬቦም በዚሁ በሽታ የተለከፈ ለመሆኑ ትችቴን በማቀርብበት መጣጣፍ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም ተንፀባርቆ ይታያል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊደግፋቸውና እውቅናን ሊሰጣቸው የሚፈልገው በተጨባጭ ከጎኑ ቆመው ለትግሉ በሚያበረክቱት አስተዋፅዖ እንጂ ዶክተር፣ ኢንጂነር፣ ምኒስትር፣ ጀነራል ማርሻል፣ የቀድሞ ፓርላማ አባል፣ የዚህ ወይንም የዚያ መፅሃፍ አቅራቢ ነኝ እያሉ የራስን ተክለሰውነት በመካብ አይደለም፣ ሊሆንም አይችልም። ላሬቦም ይህንኑ ጠባይ ገና ከፅሁፉ መጀመሪያ ሲያንፀባርቅ ይገኛል። እንጥቀሰው።

የሀገራችን ሕዝብ ከታሪክ መማርም ቀልብ መግዛትም እንደተሳነው ነው ብል ስህተት አይመስለኝምበማለት ሲገልፅበአገራችን ማን ይንገር የነበረ፣ ማን ያርዳ የቀበረ የሚባል አባባል አለ። አባባሉ ትክክል ነው። በአካል በቦታው ተገኝቶ በገዛ ዐይኑ አይቶ ከሚነግር ሰው፣ የበለጠ ምስክርና ማስረጃ ሊኖር አይችልም። እኔም በአፄ ምኒልክ ዘመን አልኖርኩም። ግን የታሪክ ተመራማሪ እንደመሆኔ መጠን፣ በጊዜያቸውና ከሞቱም በኋላ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ፣ ስለሳቸው በኢትዮጵያና በሌላ አገር ሰዎች የተጻፈውን ሆነ፣ እሳቸውም በሕይወታቸው ዘመን ለአስተዳዳሪዎቻቸውና ለሌሎች የጻፉትን ጽሑፎች በሰፊው አንብቢያለሁ። በተጨማሪም ሳይጻፍ በአፈታሪክ ሰለሳቸው የሚወራዉንም ሰምቻለሁ። የታሪክ ምሁር እንደመሆኔ መጠን፣ የተጻፈዉን በሙሉ ደጉንም መጥፎውንም በድፍኑ እንደ እውነት አድርጌ አልቀበለውም። ጽሑፉ እውነተኝነት አለው ብዬ ከመቀበሌ በፊት፣ የታሪክ ምሁራን ዉስጣዊና ውጫዊ ኀሰሳዎች የሚሉትን ትንትኖች በጽሑፉ ላይ በመጠቀም፣ እውነቱን ከሐሰቱ፣ ድርጊቱን ከምናቡ ማበጠር ይኖርብኛል።

ኀሰሳውም፣ ደራሲው የጻፈበትን ምክንያት፣ ለመጻፍስ ምን ወይንም ማን እንዳነሳሳው፣ ወጪውን ማን እንደሸፈነለት፣ ለጽሑፉ አንባቢ ደግሞ ምን ዐይነት መልእክት ሊያስተላልፍ እንደፈለገ፣ የጽሑፉስ ግብ ምን እንደሆነ፣ ድርጊቱ በሚፈጸምበት ጊዜ በአካል ተገኝቶ ወይንም ከሌላ ምንጭ ወስዶ ነው የጻፈው፣ የሚሉትንና እነሱንም የመሳሰሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ያስገድደኛል።

ጥያቄዎቹም የጽሑፉን እውነተኝነት ለመገንዘብ በጥቂቱም ቢሆን ይረዳሉ። ለምሳሌ ያህል አንድ የኢጣልያን ተወላጅ የሆነ ዘውገኛና የስዊስ ሰው ባፄምኒልክ ላይ ቢጽፍ፣ ለመጽሐፉ ንጉሡ ከሰሩት ሥራዎች መካከል የሚመርጠው የራሱን ዓላማና እምነት የሚያራምደውንና የሚያንጸባርቀውን እንጂ የሚፃረረውን አያጐላም። ቢመርጥም ጥሩ ሁኖ የሚታየው ድርጊት ከንጉሡ የሥራ ልማድ ውጭ እንደሆነ አድርጎት ያቀርበው ይሆናል። የዘውገኛው ጣልያን ዝንባሌ ኢትዮጵያ የሚደነቅ ጥንታዊ ታሪክ ቢኖራትም፣ አሁን ያለችው በአረመነኔትና በጨለማ ዓለም ውስጥ ተዘፍቃ ስለሆነ፣ ኢጣልያ የማሠልጠን ግዴታ ሰላለባት፣ አገሩን በውድም በግድም መያዝና ማስተዳደር አለባት ነው።

ይህን በመመሪያነት የምገለገልበት በማለት የሚሰብከን ላሬቦ የደርግ የውሸት ታሪክ ፀሃፊዎች ያቀረቡትንና እያቀረቡ ያሉትን ምንም አይነት የማረጋገጫ ጥናት ሳያደርግ በውነትነት ተቀብሎ ሲያበቃ የኢትዮጵያ ሕዝብን ከታሪክ የማይማርና ቀልብ መግዛትም የተሳነው አድርጎ ስሎ ፊቱን ወደ ኢሕአፓ በማዞር ልክ እንደ ወያኔና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር መወገዝ፣ መሰደድና ከስረ መሰረቱ መጥፋት ያለበት ሽብርተኛ ድርጅት እንጂ እንደዚህ በአደባባይ መጠራት የሚገባው አይደለም በማለት ለአመታት በውስጥ አምቆ ይዞት የከረመውን የጥላቻ ትርከቱን አጋጣሚ አገኘሁ ብሎ ከአልባሌ ስድብ ጋር አደባልቆ ሲወቅጠው ትንሽ እንኳን አልሰቀጠጠውም። እንዲያውም በሌለበትና ባልነበረበት ሁናቴ ከወያኔ ጋር ደባልቆ 1960 ዎቹ .. ጀምሮ በኢትዮጵያ በየዘርፉ ለተከሰተው የሀሰት ታሪክ ስርጭትና የርዕዮተ አለም ቀውስም ሆነ ኢሰብአዊ ተግባር ተጠያቂ ያደርጋል ላሬቦ። ማስረጃ ሲባልም አይካድም የሚል ምንም ትርጉም የለሽ ቃል በመርወር የሚረካ ግለሰብ ሆኖ ይገኛል።

ላሬቦ በዚህ ብቻ አልረካም። ኢትዮጵያዊኖች በዋናነትም ኢሕአፓንና በስሩ የተሰባሰቡትን በራሳቸው ጥረት የራሳቸውን በማንም ተፅዕኖ ሥር የማይውል ድርጅት መስረታውና መታገል የማይችሉ አድርጎ በመቁጠር ስልጣን በመያዝ የጡት አባት ብሎ ላሬቦ ለሰየመው ለኤርትራ ነፃ አውጪ ድርጅት ሕልም ተግባራዊ ለማድረግ የተፈጠሙ አድርጎ ይከሳቸዋል። በዚህ ብቻ አያቆምም። ለአንድነታቸውም ሆነ ለተመሳሳይነታቸው ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ በማያቀርብበት የወያኔን ፀሃይ የሞቀውንና በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ የሚታወቀውን ኬይሲ ተግባራት እንደ አርጩሜ ይዞ ኢሕአፓን ከወያኔ ጋር በአንድ ላይ ደባልቆ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያንቋሽሹ፣ አባቶችንና ታሪክን የሚያዋርዱ፣ በአጉል ትምክህትና ትዕቢት ያበጡ፣ በጭካኔ ከማረድም ወደኋላ የማይሉ፣ ለሥልጣንና ለገንዘብ ሲሉ ሀገርን ከመሸጥ ወይንም ከጠላት ጋር ወግነው የገዛ ሀገራቸውን ከመውጋት አይናቸውን የማያሹ፣ ብዙኢሰብአዊወይንምአረመኔያዊ ባንዳዊ ተግባሮች የፈፀሙ እንደሆኑ በማለት ዘለፋውን እንዳሻ ሜዳ ላይ ዘርግፎና በታትኖ ታሪካቸው ይመሰክራል በማለት የፈረደበት ድርጅትን በምናቡ ከመሬት አጋድሞ የራሱ ቃል ልበደርና በጥላቻ ጅራፉ ይዠልጣል፣ ይገርፋል። ታዲያ በሌለሁበት ቢገርፉኝ አያመኝ ብዬ በዝምታ ባልፈው ለጥላቻው በተባባሪነት ተጠያቂ ከመሆን ያድናል? በበኩሌ አይመስለኝም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኦሮሞ ክልል ሙስሊም ቄሮዎች የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እንዲፈፅሙ ድጋፍ እና ጥበቃ የሚያደርጉላቸው ሙስሊም አስተዳዳሪዎች ናቸው

የፖለቲካ ትርጉምን አለመረዳት

የፖለቲካ ድርጅት የሚመሰረተው እኮ ላሬቦ የማንንም ጎፈሬ ለማበጠር ሳይሆን በመሰረቱ የፖለቲካ ሥልጣን መጨበጥ/መቀበል ሲሆን ኢህአፓን ከሌሎች የሚለየው ዋናው ቁም ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አንደበቴ ተናገር፣ እንደ ህሊናዬ አስበህልኝ ፍላጎቴንና ጥቅሜን አሟላልኝ በማለት መርቆ እንዲሰጠው አጥብቆ የሚታገል መሆኑ ነው። ላሬቦ ኢሕአፓን በሥልጣን ጥመኝነት ሲከስ የፖለቲካ ትግል ማሰሪያውም ሆነ መዳረሻው የፖለቲካ ሥልጣን አልገባውምና ቢያንስ መጠነኛ ጥናት አድርጎ ለመሟገት ፍላጎቱን በመጣጥፉ ቢያንፀባርቅ ኖሮ መልካም በሆነ ነበር። የኔም ምላሼ በተለየ ነበር። ግን አልሆነም። ላሬቦ እንዲገባው የሚያስፈልገው ኢሕአፓ ሥልጣንን ለራሱ በድርጅት ደረጃ በሞኖፖል ይዞ በሕዝብ ጫንቃ ላይ ለመቆናጠጥ ሳይሆን በመሰረቱ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት እንዲሆን በማድረግ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሕዝብ የፈለገውን ለተወሰኑ አመታት (ባብዛኛው 4 አመታት) እንዲያስተዳድር፣ ያብላጫውን ሕዝብ ድምፅ የተነፈገው ደግሞ በተቃዋሚነት ሚናውን እንዲወጣ ለማድረግ ነው። አራት ነጥብ። ስለሆነም ያለፍላጎቱ በአገዛዝ የተፈጠሙትን ጨቋኝ ቡድኖችን በእልህ አስጨራሽ ትግል አስወግዶ ሕዝባዊ ሥልጣንን ማስፈን ግዴታ የሚሆነውም በዚሁ ምክንያት እንጂ በሌላ አይደለም። ከዚህ ውጭ ተረት ነው የሚሆነውና በሕዝብም ዘንድ ተቀባይነት የለውም። በመሆኑም ኢሕአፓ ዋና አላማው ሥልጣን ነው ብሎ መክሰስ ትርጉም የማይሰጥ የውዳቂ ጥላቻ መግለጫ ከመሆን አያልፍም።

በውነቱ አሁን የፖለቲካን ውስጣዊ ይዘት ካለመረዳት ጋር ተዳብሎ ይህን ተወዳዳሪ የሌለው ለከት የለሽ ጥላቻውን እንደ ፈሳሽ ውሃ ላሬቦ ሲያፈስ በምን ማጠየቂያ ነው ታዲያ ይህ ግለሰብ የታሪክ ባለሙያ ተብሎ ካባንና ምሁርነትን የሚላበሰው? ከማን ጋር ተገናኝቶና ተወያይቶ ነው ምንስ መልስ ቢሰጡት ነው ከምህር እሳቤ የማይጠበቅ የዘቀጠ አስተያየቱን ይፋ ለማድረግ የተገደደው? ከሁሉ በላይ የሚገርመው የኢሕአፓን ባንዳነት ድርጅቱ በሱማሌ ወረራ ወቅት በፈፀመው ክህደት ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። ወረራውን መደገፍ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ ከሱማሌው መሪ ሲያድ ባሬ ወደ አምስት ሚሊዮን ብር ወደ ድርጅቱ እጅ እንደገባ ብሎ ሊቀመንበራቸው መንግሥቱ ኃይለማሪያምና የደርግ ቀጣፊዎች ያሰራጩትን ወሬ እንደ እውነት ተቀብሎ ያለምንም ስቅጠት፣ ያለምንም ማስረጃ ሲደግመውና ባልተገራ አንደበቱ ይነገራል አለባብሶ ሲያልፍ ማየቱ ከማስገረምም አልፎ በማንነቱ ላይ ጥያቄ ቢያስነሳበት ማንነው ተጠያቂ የሚሆነው? በዚያድ ባሬ አገዛዝ በውድ ሀገራችን ላይ የተደረገውን ወረራ የኢሕአፓ አባላትና ደጋፊዎቹ ሊደግፉ ቀርቶ በመከላከል ደማቸውን ፈሰሱ፣ አጥንታቸውን በመከስከስ መስዋዕትነት በከፈሉ የሀገራቸውን ዳር ድንበር ለማስከበር አስተዋፅዖ ባባረከቱት ላይ መሳለቅ ነውና ይህንን ረጋ ብለን ስናስበው ይቆጠቁጣል፣ ይዘገንናል፣ ያማል። በርግጥም የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ነው የሚባለው አለምክንያት አይደለም ለካ ወዳጆች!! በጥላቻ የተለከፈ የሰው ፍጡር ምን ያህል ሊጓዝ እንደሚችል ሲታሰብ በጥላቻ የታወከ አዕምሮ በተለይም በፖለቲካ ርዕዮት ተከናንቦ ሲቀርብ እንኳን መድኃኒት ቀርቶ ከተዳፈርኩ ይቅርታ ይደረግልኝና ፈጣሪም ቢሆን በቸርነቱ በፀሎት ሊፈውሰው ፍላጎት የሚኖረው አይመስለኝም። የስንት የቅርብ ዘመዶቼ በለጋ እድሜያቸው ላደረጉት ተጋድሎና የከፈሉት መስዋዕት በአሁኑ ወቅት በሕሊናዬ ተመልሼ ሳስታውሳቸው ራሴን ተመልሶ የሚያስወቅስና የሚያሳፍር የሚያስገምት ተግባር እንዳልፈፅም በማለት እየተናነቀኝ ላልፈው ብችልም ላሬባ በዚህ ክፉኛ ጥላቻን በተላበሰ ምግባሩ ራሱን በራሱ ያዋረደ ግለሰብ የሆነና ሰልፉም ከፋሺስቶች ደርግና ከባንዳዎች እንጂ ቅንነትን ከተላበሰው ከብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ጎን የቆመ አለመሆኑን ስለ ራሱ ሌላ ሳይሆን እራሱ ላሬቦ ማንነቱን በገሃድ አረጋግጦ ያጋለጠበት ሰነድ የፃፈ መጣጥፍ ማበርከቱን መግለፁ ግን አግባብነት ያለው ነው የሚል ፅኑ እምነት አለኝ። በነገራችን ላይ ላሬቦ በዋቢነት የሚጠቅሰው በደርግ ፋሺስታዊ አገዛዝ ዘመን በመረጃ ደህንነት የሕግ መምሪያ ኃላፊ የነበረው ዋሾው ሻምበል ተስፋዬ ርስቴ በሰጠው ቃለ መጠየቅ “ኢሕአፓዎች ሲነሱ ሽብርተኞች ነበሩ፣ ቅጥረኞችም ነበሩ” “ለኢትዮጵያ ቀውስ መነሾው ያ ትውልድ የሚባለው ኢሕአፓ ነው” እያለ በቀላመደበት ስለ ኢሕአፓ ሲጠየቅ በድርጅቱ ላይ ያለውን ጭፍን ጥላቸውን መላ ሰውነቱ እየንቀጠቀጠው መኢሶን የተባለውን ድርጅት ሲያመሰግን ላየና ላዳመጠ ማንኛውም ቅን አሳቢ ዜጋ በርግጥም ላሬቦ ይህንን የፋሽስት አገልጋይ የነበረን ግለሰብ በዋቢነት ለመጥቀስ የተገደደው ባለማወቅ ሳይሆን የጭፍን ጥላቻ ወዳጆች በመሆናቸው እንደሆነ ለመረዳት ልዩ አዋቂ መሆንን አይጠይቅም።

እውነታው ምንድን ነው?

ሀቁ ዛሬም ተደጋግሞ ይነገር ከተባለማ በዚያድ ባሬና አገዛዙ የተደገፈው፣ ከምዕራብ ሶማሊያ ጋር አንድ ሶስተኛ ኢትዮጵያ የሶማሌ ግዛት ነው ብሎ የተፈራረመው፣ ሞቃዲሾ ቢሮ እንዲከፍትና ያሻውን (ብላንኮቼክ) እንዲሰራ የተፈቀደለት፣ ለኬይሲ ተግባሩ ማሳኪያ ያገለግላቸው ዘንዳ የሶማሌ የዲፕሎማት ፓስፖርት በወቅቱ የድርጅታቸው ከፍተኛ ባለስልጣናት ለነበሩት ለምሳሌ መለስና ስዩም፤ እንዲሁም ለኢትዮጵያ በዋነኛ ጠላትነት ለተሰየሙት ከአረብ ሀገራት እርዳታ ይለገሰው ዘንድ በሶማሊያ የድጋፍ ወረቀት የተፃፈለትና ተጠቃሚ ሆኖ የነበረው ወያኔ እንጂ ኢህአፓ ጨርሶ አልነበረም። ለዚያድ ባሬና በምስራቅ ኢትዮጵያ ያካሄደውን ወረራ ኢሕአፓ ድጋፍ ሰጥቶ፣ ግማሽ የኢትዮጵያን ግዛት መሬት የሶማሊያ መሬት ነው ብሎ በወቅቱ በዚያድ ባሬ አገዛዝ ሙሉ ድጋፍ ሲንቀሳቀስ ከነበረው ከሶማሌ ነፃ አውጪ ድርጅት ጋር ተወያይቶ ተስማምቶ ያረጋገጠው ነገር ጨርሶ የለም። ይህ በሃቅ ላይ ያልተመሰረተ የጥላቻ ዘመቻ በፋሺስቶቹ ደርግና ባለሟሎቹ የተደረገን ዘመቻን በተደጋጋሚ ይፋ በተደረገ ገለፃ ሀሰት መሆኑን መጣጥፉን ከማቅረቡ በፊት እንደ የታሪክ ባለሙያነቱ ጥቂት የግል ምርምር አደርጎ የሚያውቅበት ሁናቴ ሳለ ባለማድረጉ ከተሳሳተ ድምዳሜ አድርሶታል። ለራሱ የቅድሚያ መከላከያ በሚል ሳይሆን አይቀርም ኢሕአፓ እንደለመደው ቢክድም በሚል አይኑን ከድኖ ጆሮዉን ደፍኖ መጋለቡ አንባቢን ከብዥታ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ለመክተት ይረዳኛል ብሎ ካሰበ ከጥፋተኛነት ነፃ እንደማያደርገው ማወቅ ነበረበት። መቼም ማልጎደኒ ብዬ ግን ጉድለቱን አላልፍለትም። የኢትዮጵያን ሉአላዊነትና አንድነት ማክበርና ማስክበር የትግሉ ሌላው ገፅታው ነበርና ነውናም በዚህ በአሉታዊነት ሊወቅስ የሚችል ከቶም አይኖርም። ቢያንስ ሌላውን ትተን በምዕራብ ኢትዮጵያ የሱዳ መንግሥት ያካሄደውን ወረራን በመቃወም በኢሕአፓና በአካባቢው ሕዝብ የተደረጉት በርካታ የሀገር ድንበር የማስከበር እንቅስቃሴዎች የሚሰጡትን ምስክርነት መገንዘቡ ስህተትን ከመስራት በጭፍን ከመታወርም ያድን ነበር። ግና ጥረት አልተደረገም

መቼስ ራሳቸውን በራሳቸው ያጋለጡ ጥራዝነጠቅነት የተጠናወታቸው የታሪክ ባለሙያዎች ግን አተላዎች መሆናቸውን ባለማወቅ ዘላብደው ሲገኙ ሃይ ካልተባሉ፣ ዋሾ መሆናቸው በግላጭ ካልተነገራቸው አይነኬ ጠባይ የሚያንፀባርቁ ለመሆናቸው በተደጋጋሚ የታየ ነው። ላሬቦም በዚሁ መጣጥፉ ይህንኑ ሀቅ ሲያረጋግጥ ይታያል። ኢሕአፓን አሁንም በለመደበት የባንዳነት ጠባዩ ከወያኔ ጋር አዳብሎ ከህቅ የተጣላ ግን ከጥላቻ ጋር የተጎዳኘ ዋሾነቱን በኢትዮጵያ ጥንታዊነትና ታላቅነት አያምንም በማለት ብቻ አያቆምም። እንዲያውም በኢህአፓ ላይ ያለው ጥላቻ በጣም ስር የሰደደና ጥግ የለሽ ከመሆኑ የተነሳ የኢትዮጵያ ጠላት ከሆነው የአውስትሪያ ቄሳራዊ ስርአት አቀንቃኝ (ኢምፔሪያሊስት) ባሮን ፕሮቻስካ ታማኝ ደቀመዛመርት ጋር አጣብቆ በሕዝብ ዘንድ እንዲጠላ ለማድረግ ተውገርግሯል። የኢህአፓ ነገር ሲነሳ አሎሎ እሳት እንደጨበጠ ሰው የሚንቀለቀለው ላሬቦ ምን ያህል እንደዘቀጠ የሚያመላክተው የርዕዮት ዘመዶቹ በስታሊን ኩረጃ ሲከሱት ላሬቦ ደግሞ የኢትዮጵያ ቀንደኛ የሆኑ ነጮች ስጋት እንዳትሆንብን በማለት የጠነሰሱትን የጥፋት አላማ በመኮረጅ መወረፍ ተሞክሮ ያልሰራ መሆኑ ያልገባው ጅላጅል መሆኑን ያሳብቅበታል እንጂ የሚያተርፍለት አንዳችም ቁም ነገር የለም። የሚገርመው ግን መሰረት የሌለው ትችት ካቀረበ ምነዋ ታዲያ የሚኖርበትና በአስተማሪነት ተቀጥሮ እያገለገለ ያለበትን ሀገር ፖለቲካ ለምን አልጠቀሰም? የወቅቱ ጠሚዶ በማን ጥንሥስና ድጋፍ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ለመቆናጠጥ እንደበቃ የሚታወቅ ነውና ኢሕአፓን በወረፈበት፣ በነካ እጁ እስቲ በዚህም አንድ ቢልና የግሉን አስተዋፅዖ ቢያበረክት ልታሸልም ጥቂት አመታት ለቀራት ሕይወቱን ንስሃ ቢገባላት መልካም በሆነ ነበር። አንባቢያን የራሳቸውን ግንዛቤ እንዲያዳብሩWalelegn M(1969) Vs BaronRoman Prochäzka (1885) on the fate of Ethiopia በሚል ዕስ በድረገጽ አፈላልገው እንዲመለከቱት የዚህ መጣጥፍ አቅራቢ ይጋብዛል።

ላሬቦ ኢህአፓን በሚከስበት ወይንም ደግሞ የእማሬ ጣቱን በቀሰረበት የተቀሩት ሶስቱ ጣቶቹ በሱ ላይ እንደተቀሰሩበት የማይረዳ፣ እሱ ብቻ የታሪክ ምሁር ብሎ ስላመነ ጥራዝነጠቅነቱ የማይጋለጥበት የሚመስለው፣ ክብሩን ያላወቀ ክብረነክ ዘለፋ አስተጋቢ እሱ ራሱ መሆኑን ለመገንዘብ ያልቻለ፣ የታሪክ ባለሙያ ነኝ ይበል እንጂ የታሪክን ይዘትና ምንነት በመሰረቱ ያልተገነዘበ፣ በጭፍን ጥላቻ እንጂ በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ ተቃውሞን ሆነ አስተያየት ማቅረብና ማስተናገድ የማይችል ግለሰብ፣ በዋሾነታቸው የተጋለጡና በውሸት ትርከታቸው ዝናን ለመጎናፀፍ ፈላጊዎችንና የታሪክ አተላዎችን (ሻምበል ተስፋዬ ርስቴን ይመለከቷል) በአንቱነት በዋቢነት አቅርቦ የሚኩራራና አዋቂነት የተላበሰ የሚመስለው በጅምላ ወቀሳ የተካነ ግብዝ ግለሰብ ነው። እስቲ ራሱኑ ላሬቦን እንዳምጠው። እንዲህ ይላል ላሬቦ፣

ኢህአፓዎች የተካኑበት ሌላም መልክ አለ። ኃቁ ሲነገራቸው አንዲት ብጣሽ ዓረፍተ ነገር እንኳን መዘዞ በማውጣት ሀሰቱ ከምን ላይ እንደሆነ ሳይገልጡ በጭፍን የውሸት ታሪክ ነው በማለት ማጥላላትና መኮነን አንዱና ዋነኛው ነው። ከዚያም ባለፈ ፀሃፊውን መሳደብ፣ ያልሆነ ሥም በማውጣት ወይንም ከወራዳ ድርጅት ጋር በማያይዝ ማሸማቀቅ እንደ ኃይማኖታቸው ቀኖና አድርገው ይዘውታል። ሁለተኛ ባህሪያቸው እስከሚመስል ድረስ።

አንባቢ እስቲ ይህንን አረፈተ ነገር አስፋፍተን በዚሁ ባቀረበው መጣጥፍ ጋር እያመሳከርን እንመልከተው።

በተሳሳተ ትርከት ላይ ተመስርቶ ምንም አይነት የማጣራት ተግባር ሳያደርግ

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአፍሪካ ሕብረት ለአሜሪካና ለምዕራቡ ዓለም ተንኮል እጅ አይስጥ - ሰማነህ ታ. ጀመረ

የሚያጥላላና የሚኮንን ራሱ ላሬቦ፣

የታሪክ ምሁር ነኝ በማለት ግን ማስረጃ በሌለው ትርከት ተሳዳቢ ራሱ ላሬቦ

ከወራዳ ድርጅት ጋር አያይዞ ለማሸማቀቅ የጣረ ራሱ ላሬቦ

የቀጣፊን ምስክርነት እውነት አድርጎ የተቀበለ ራሱ ላሬቦ

ከታሪክ መማር ያቃተው ቢኖር ራሱ ላሬባ

ቀልብ መግዛት ያቃተው ሕዝብ ሳይሆን ራሱ ላሬቦ

ጭንጋፍ ብሎ ተሳዳቢ ራሱ ላሬቦ

ያልተረጋገጠን እሳቤ ተቀብሎ የሚያስተጋባ ራሱ ላሬቦ

የደርግ ሊቀመንበር መኃማ ኢህአፓን ለማስጠላት ዚያድ ባሬን ደገፈ ብሎ

በቅጥረኞቹ የተለፈፈውን የሀሰት ትርከት የተቀበለ ራሱ ላሬቦ ሌላም ሌላም።

ለዚህም ነው ላሬቦ ከስህተት ተነስተህ የደረስክበት ድምዳሜ አንተው ራስህ ያውም የታሪክ ባለሙያ ነኝ እያልክ በገሃድ የሚታየውን እያዛባህ በመገኘትህ ከታሪክ አለመማርና ቀልብ ያልገዛኸው አንተ እንጂ ሕዝባችን አይደለም። በመሆኑም ሕዝብ ኢሕአፓን እንዲያወግዝልህ ከስረ መሰረቱ እንዲጠፋልህ አልፎ ተርፎም ከሀገር ወጥቶ እንዲሰደድልህ የኢትዮጵያን ሕዝብ መጋበዝ ሕልም ሆኖ ይቀራል እንጂ በምንም አይነት ተግባራዊ ሊሆን አይችልም። አንተማ የመወሰን ሥልጣን ቢኖርህ፣ አሳደህ ለማሳደድ ቢቻልህ፣ ገለህ ለማስቀበር ወደ ኋላ የማትል ለመሆንህ በድርጅቱና በዛ ትውልድ ላይ ያለህ ጥላቻ ያሳብቅብሃል። ራስህን በራስህ አጋለጥክ እንጂ ያተረፍከው ወደፊትም የምታተርፈው አንዳችም ነገር የለም። ከሁሉ የሚያስገርመው ከኑግ የተገኘ አብረህ ተወቀጥ እንዲሉ ከተጠሉ ክፍሎች ጋር ደባልቀህ ጥፋተኛ ለማድረግ የሄድክበት ጥግ የለሽ ጥላቻ በራስህ ጭንቅላት ውስጥ በመሽከርከሩና ሕሊናህን ስለጋረደው ታሪክን ወደኋላ ዞሮ ለማየትና ለማጥናት ብሎም ሀቁን ለመረዳት ላስቻለህም። ያሳዝናል። ለዚህም ነው በምንም አይነት የማይመሳሰሉ ክፍሎችንና ድርጅቶችን በአንድ ሙቀጫ ውስጥ ከትቶ መውቀጥ ከመሆን የማያልፍ ትርከትን በማስተናገድ የታሪክ ባለሙያነትን በፍፁም አያላብስህም በማለት አፅንኦት በተሞላበት መልኩ ለመግለፅ የተገደድኩት። ወያኔና ኢሕአፓ በአላማቸውና በርዕዮተአለማቸው ብለህ ግን ዘርዘር አድርገህ ሳትገልፅ ማለፍህ ብሎም ደባልቀህ መውቀጥህ የሁለቱን ድርጅቶች የኋላ ታሪክ ሆነ በተግባር የፈፀሙትን ገድል በሚገባ ለመለየት ያልቻልክ መሆንህን ያሳብቅብሃል እንጂ ሌላ ምንም ትርጉም የለውም።

ማሳረጊያ/መደምደሚያ

በመስኩ ጥናታዊ ምርምር ባደረጉ በርካታ ምሁራኖች ተበክሮ እንደሚገለፀው ጥላቻ የዘረኝነት፣ የትምህክትና የጠባብነት ውላጅ በመሆኑ እንደ ላሬቦ የመሰሉ እጅጉን በጭፍን ጥላቻ የታወሩ፣ ማስተዋል የሚሳናቸው ከዚህ በታች በስፋት የተጠቀሰው የመጣጥፉ ጥቅስ በግልፅ ያስረዳል የሚል ፅኑ እምነት አለኝና ልጥቀሰው። እንዲህ ይላል ላሬቦ፤

በገዳይነትና በጭካኔው ኢሕአፓ ከሕወሃት አያንስም። በማንኛውም መመዘኛ ከደርግ ይከፋል እንጂ አይሻልም ማለት ይቻላል። በማለት ሲደነፋ በምን ማጠየቂያነት ነው አንድን ትውልድ የመተረ ደርግ የሚባል ፋሺስታዊ አገዛዝ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ራሱንና ደጋፊዎችን ለመከላከል ኢሕአፓ በወሰደው እርምጃ በተነጻጻሪነት የሚወሰደው? ይሁንና ሕወሃት ሥልጣን እንደጨበጠ ለቀድሞ የሽብር አጋሩ ለኢሕአፓ የዋለው ከፍተኛ ውለታ ቢኖር የቀይ ሽብር ፈፃሚዎችን ለፍርድ አቅርቦ ሲቀጣ በኢሕአፓ ለተጨፈጨፉት የነጭ ሽብር ሰለባዎች ግን ደንታም አልሰጠም። ታሪክ ረስቷቸው ደማቸው ደመከልብ ሁኖ ቀርቶ ዛሬም የፍትህ ያለህ እያሉ እንደጮሁ ናቸው። ፍትህ የአሸናፊዎች ደንገጡርናት ካልተባለ በስተቀር ለነሱም መልስ ሊሰጣቸው ይገባል። እነዚህ የሞቱት ኢሕአፓ በራሱ ቀስቃሽነት በጀመረው በነጭ ሽብር መሆኑ ይታወቃል። ታዲያ ኢሕአፓ ቅንጣት የምታክል ልቦና ካለው በዚህ የውድመት ተግባሩና ታሪኩ ማፈርና መጸጸት ሲገባው መኩራትና ሸር ጉድ ማለት ለትዝብት ከዚያም ባሻገር በድርጅቱ ሰለባዎችና እሱም ባደረሰው በአገሪቷ ቁስል ስደድበት ለማለት ካልሆነ በስተቀር ፋይዳው ግልጥ አይደለም። የፍልስፍና አባት እንደሆነ የሚነገርለት ሶቅራጠስያልተፈተሸ ሕይወት መኖር ብላሽ ነውያለው ዘይቤ የኢሕአፓና ተከታዮቹ ዕጣ ፈንታ ሁኖ ከቆረ ቆይቷል። ከታሪኩና ከድርጊቱ ጋር ለመታረቅና ለመጣጣም የማይፈልግ ድርጅት አቅመቢስ ከመሆን ባሻገር ፋይዳ ቢስም እንደሆነ የህይወት አመክሮ ይነግረናል። በዚህ እይታ ኢሕአፓ እያከበረ ያለው የሕያዊነቱን የወርቅ ኢዮቤልዩን ሳይሆን የሞት ተዝካሩን ነው ማለት ይቻላል። ገና ከጥንስሱ የሞተ ነበርና። ይህም የድርጅቱ ሕልውናና ማንነት ትክክለኛ መገለጫ መሆኑ የሚያከራክር አይመስለኝም።የጥቅሱ መጨረሻ።

ላሬቦ የኢሕአፓን የኢዬቢልዩ በአሉን በሞት ተዝካር ሰይሞታል። ቅንጣት ታህል ልቦና ካለው ይልናበውድመት ተግባርና ታሪኩ ማፈርና መፀፀት ሲገባው መኩራትና ሸርጉድ ማለትአይገባውም በማለትም ተፈጥሟል። ኢሕአፓ ባደረገው ተጋድሎ የሚያፍርና የሚፀፀት ሳይሆን የሚያኮራ፣ የበኩር ልጅ በመሆኑም በአርአያነት የሚመለከቱት፣ ከትግል ታሪኩም ተመክሮ የሚቀስሙበት፣ በኢትዮጵያ የታሪክ መዝገብ ሁነኛ ቦታ የተሰጠው፣ በበርካታ ኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ የተቀመጠ እንጂ ማንም ከቶ ማንም ጥላሸት ቀባው፣ ረገመው፣ ሰደበው፣ ገደለው የሚለውጠው ነገር የለም። የትግል ታሪኩ የሕዝብ ቅርስ ነው። በርካታ ጀግኖች አጥንታቸውን ከስክሰውለት፣ ደማቸውን አፍስሰውለት ከሕዝብ ጎን የተሰዋ እንጂ ፈንጠር ብሎ፣ ልምራ ብሎ በነሱ ትከሻ ለመረማመድና ከሥልጣን ማማ ለመቆናጠጥ ያሴረ አልነበርም፣ አይደለምም። አባላቱ መከራ የተቀበሉበት ታሪክ ነው ያላቸው በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ ፍቅርና አክብሮት እየለገሰው የሚገኝ እንጂ ምንም አይነት ነቀፌታ የለውም።

እንግዲህ ላሬቦ እንደ ሬት ቢመረውም የታሪክ ሀቅ እንደ ከባድ ክብደት እንዳለው አሎሎ ሸክሙ ቢክበደውም፣ አንጀቱ ያራል፣ ሕሊናው በንዴት ይቆስላል እንጂ ኢሕአፓ 75ኛውን፣ ከዛም 100ኛውን አለፍ ብሎም 150ኛውንና 200ኛውን የሚያከብርበት ጊዜ ይመጣል። ይህም ሲባል ያለታሪካዊ ምሳሌነት አይደለም። ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ ትውልድ ተስፋ ሰጪና አነቃቂ እሳቢዎች የሚለግሱት የአፍሪቃውያን የጥቁር ሕዝቦች ኩራት የሆነውን አድዋ ጦርነት መላው ሕዝባችን በጋራ ዳር እስከዳር በአልገዛም ባይነትና የሀገሬ ሉዓላዊነቴ አይደፈርም በሚል ጀግንነት በቁጭት ተንቀሳቅሶ ያስገኘው ታሪካዊ ድልና እንዲሁም የመላው ሕዝባችን ቅርስ የሆነው የኢትዮጵያ አርበኞች ድል ቀን በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው።

ኢሕአፓ ከሚታገልበት የትግል መፈክሩ አንዱና ዋነኛው የዴሞክራሲና የነፃነት ጥያቄዎች ናቸው። በሀገራችን ሕዝባችን የነፃነት መብቱን ተጎናፅፎ ዴሞክራሲያዊ ሥርአት ከመሰረተ በኋላ ኢሕአፓ እንደ ድርጅት ተኖ የሚጠፋበት ሳይሆን ከሕዝብ ከሀገር ወዳዱ ኃይላት ጋር የመሰረተው ሥርአት በጮሌዎች ተጠልፎ እንዳይቀለበስ አባላቱም ሆኑ ሕዝቡ ሥርአቱን እንደ አይንብሌናቸው የሚንከባከቡት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለም። የወደፊቱ ትውልድና ኃላፊነት የሚረከቡት ድርጅታዊ ሚናቸውን እየተወጡ ከወቅቱ ሁናቴ ጋር የሚስማማ የትግል ዘዴ በመቀየስም ሥርአቱን ይንከባከቡታል እንጂ አሁንስ በቃን ብለው እጃቸውን አጣጥፈው የሚቀመጡ ሊሆኑ አይችልም።

በግንቦት 23 ቀን 1863 .. በጀርመን ላይብዚግ ከተማ የተጠነሰሰው የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ 2013 .. 150ኛውን የምስረታ በአል ማክበሩ የታሪክ ድርሳናት የሚያመላክቱት ናቸው። ይህ የፖለቲካ ድርጅት ከጀርመን የፖለቲካ መድረክ ሊነጠል የማይችል አሻራውን ያሳረፈ መሆኑ ታሪካዊ ገድሉ ይመሰክራል። በርካታ ጠቅላይ ምኒስትሮችን፣ ርዕሰ ብሔሮችን፣ በተለያዩ የፌደራሉም ሆነ የክልሉ የመንግስት የሥልጣን እርከኖችን በሕዝባዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ በመረከብ በግሉም ሆነ በጥምር ክሌሎች ፓርቲዎች ጋር በማበር የማስተዳደር ኃላፊነትን የተረከቡ አባላትን ያፈራና ሕዝብን ያገለገለ አሁንም በወቅቱ ይኸው ድርጅት በመራሄነት የሚመራው መንግስት ገንብቶ ኃላፊነቱን በመወጣት ያለ ድርጅት ነው። በስልጣን አገልግሎታቸው ከፍተኛ ከበሬታን ከሕዝቡ የተጎናፀፉ አባላና ደጋፊዎቹ በርካታዎች ናቸው። ይህ ድርጅት ይህን የመሰለ ታሪክ ለመስራት የቻለው የተነሳበትና የታገለላቸው ከላብአደርነት ጀምሮ እስከ ሕዝባዊ ፓርቲነት ለመድረስ የቻለባቸው ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ የዴሞክራሲ፣ የነፃነት፣ የእኩልነትና የፍትህ፣ የወንድማማችነት ጥያቄዎቹና የትግል መፈክሮቹ ናቸው። ድርጅቱ በነዚህ በርካታ አመታት ይህ ነው የማይባል በደሎችና እንግልቶች ደርሰውበታል። በርካታ አባላቱ ታስረዋል፣ ተገለዋል ለእስርም ሆነ ለስደት ተዳርግዋል። ከድርጅታዊ መከፋፈልና መዳከምም ነፃ የሆነ አልነበረም። በነዚህ አመታት ሁሉ በአባላቱ ቆራጥነትና ታጋሽነት መከፈል የሚገባውን መስዋዕትነት በመከፈል ከሁለተኛ አለም ጦርነት ማብቃት አንስቶ የተመሰረተውን ዴሞክራሲያዊ ስርአቱንና የነፃነት መርሆዎችን እንደ አይን ብሌኑ እየተንከባከበ ወቅቱ በሚጠይቀው መስፈርት የሕዝቡ የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል የእኩልነት መስክን በማስፋፋት ወንድማማችነትም ሆነ እህትማማችነት የጠነከረበት ሕብረተሰብ እያደገ እንዲሄድ የራሱን አስተዋፅዖ እያበረከተ የሚገኝ አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅት ነው። በህብረተሰቡ አባላት መካከል ያለውና መኖር ያለበት አንድነት እንዳይፋለስ በመንከባክብ የትግል መፈክሮችን በአዳዲስ መንፈስ እያዳበረ መልስ እንዲያገኙ በመታገል ላይ ያለ ድርጅት ነው። ምሁራንም ከዚህ ድርጅት ጋር ያላቸው ቀረቤታም በቀላሉ የሚገመት አይደለም። መሰል እይታ ካላቸው በተለያዩ የአለም አካባቢ ካሉ ድርጅቶች ጋር መልካም ግንኙነትን በመፍጠር በጋራ ጥናታዊ ምርምር በማድረግ ለሰላም መስፈንና ለሰብአዊ መብት መከበር የበኩሉን ጥረት እያደረገ ያለ ድርጅት ነው። በዚህም የተነሳ ድርጅቱ የተጠነሰሰበትንና የተመሰረተበትን ታሪካዊ አመት፣ ከየት ተነስቶ በወቅቱ እስከሚገኝበት ድረስ በተለያዩ ጥናታዊ ፅሁፎች እየቃኘ፣ ከደጋፊዎቹና በክብር እንግድነት ከሚጋበዙ ሀገራዊም ሆኑ የወዳጅ ሀገር እውቅ እንግዶች ጋር በመሆን እያከበረና በርካታ ተመክሮዎችንና እውቀቶችን እየቀሰመበትም የሚገኝ ነው

በበኩሌ ከኔ በበለጠ ለሀገሬ የሚቆርቆሩ በርካታ ዜጎቻችን እንዳሉና እነሱም ሁኔታው እስከፈቀደላቸው ድረስ ታግለው በለስ ቀንቷቸው ለድል ከበቁ ቀሪውን ለተተኪው ትውልድ ያስተላልፋሉ። ሕይወት ትቀጥላለች የራሷንም ኃላፊነት የሚወጣላት ዜጋንም ታፈራለች። አመት በአመት እየተተካ በሄደ ቁጥር አያት ቅድመ አያቶቻቸው ድርጅታቸው የተፀነሰበትን አመት በማስታወስ ብቻ ሳይሆን ብርቱ ተግባር የፈፀሙትንና መስዋዕት የሆኑትን በአርአያነት በማስታወስና በመዘከር ለቀሪው ደግሞ የትግል ቃልኪዳናቸውን በማደስ ታሪክ እየሰሩ ያልፋሉ። የሕይወት ተመክሮ የሚያሳየው ይህንኑ ነው። ከዚህ እይታ ስነሳ የእድሜ ባለፀጋ ለመሆን ካበቃኝ ጤንነቴ ተሟልቶ እስካለ ድረስ ስኖር በሕይወቴ ስሞት በመንፈሴ እያልኩ በአሉን እንደሁናቴው እንደማክበረው ሙሉ እምነቴ ነው ብል የሚሞግተኝ ቢኖር መንገዱን ጨርቅ ያርግለት እላለሁ። አበቃሁ!!

ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች”

መልካም ንባብ

3 Comments

  1. ነብስህን አስጨነካት እንጅ ሐይሌ ላሬቦን ከማማው ማውረድ አይቻልም።ከሀይሌ በላይ የድርጅት አባሎቻችሁ ስለ ኢህአፓ ክፉ ስራው ጽፈዋል። ተው ወዳጄ ክንድ አትጠምዝዝ። በተንኮለኞች ተታልለው ለሞቱት ምርጥ የኢትዮጵያ ልጆች ልባችን ይደማል ያሳዝናል ሳይመረምሩ ገብተው ጭዳ ሆኑ አገርም እንዳይሆን ሆነ። ክእናንተ ያተረፍነው በ’ቸ’ ና ‘ሸ’ መጠፋፋት፣ ዜጎችን ከፋፍሎ መፍጀት፣ሌሎችም እንዲፈጁ መመሪያ መስጠት፣ለጠላት መጠቀሚያ መሆን ከብዙ በጥቂቱ ነው። በተረፈ ኢህአፓን ያለቀለሙ ቀለም መስጠት አይጠቅመውም። አንተም ስድቡን ቀነስ አድርገው አንድም መረጃ የሰጠኸን የለም ስድብ እንጅ ። እንዴት ነው እንደ ሃይማኖት አንድ ቦታ ተቸንክሮ መቅረት? ጥፋት ላይ ጥፋት መስራታችሁ ለሞቱት ሰማእት የሆናችሁ ይመስላችሗል መሰል? ሻቢያና ወያኔን ዚያድ ባሬ ምናምን ሁሉ strategical alliance ስትሉን አልነበረም? አንተም እኮ ትማገድ ነበር ይሄኔ እስር ባጠገብህ አላለፈም። ሰላም ሁን ወዳጄ ለሀገር የሚደክሙ ወዳጆችን ግን አትተናኮልብን። ሌሎች ወገኖች የሰጡት አስተያየት ባንተ ጸሎት ወርዷል ግን አንብበኸዋል ህዝብ ስለ ኢህአፓና ሐይሌ ላሬቦ ያለውን አመለካከት ይጠቁምሀል ብዬ እገምታለሁ።

  2. ውድ የዘሃበሻ ኤዲተሮች ይህንን ጽሁፍ አስመልክቶ ከዚህ ቀደም የተጻፉትንና የተለጠፉትን ሂሶች በሙሉ የት አደረሳችኋቸሁ? ዛቻ ስለደረሰበባችሁ ነው ወይ ሁሉንም ከቦታቸው ያነሳችኋቸሁ? ከዚህ ቀደም የተለጠፉት ሂሶች ተነስተው እንደነበር አስታውሳለሁ። የምንኖረው በከበርቴው ዲሞክራሲ ውስጥ ስለሆን ግለሰቦች የማስፈራራት መብት የላቸውም። ስለሆነም የተነሱት ሂሶች በሙሉ እንደገና ቦታቸው መመለስ አለባቸው። ካለበሊዚያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ፣ ዲሞክራሲ ዲሞክራሲ እያልን የምንጮኸው በሙሉ ምንም ትርጉም የላቸውም።

    ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

  3. ዶር ፍቃዱ በቀለ በጻፈው እንደ ሁልጊዜው እስማማለሁ ቀደም ሲል የተለጠፉ ጽሁፎችን መልሱዋቸው ሃገር ወዳድ ወንድሞቻችን ጭንቅላታቸውን ጨምቀው የሰጡት አስተያየት ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share