ይድረስ ለአገሬ ሕዝቦችና መሪዎች፣ እግዚአብሔር ለሕዝቦቹ የሚናገረው በሽማግሌዎች አንደብት ነው – ጆቢር ሔይኢ

ሁላችንም እንደምንገነዘበው በአሁኑ ጊዜ ሕዝባችንን  እርስ በርስ እያነካከስ ያለው የብሔርና የሃይማኖት ቅራኔ መሆኑ ግልጽ ነው። የብሔሮች የራስን እድል በራስ የመውሰንና፣በቋንቋ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር የጸደቀ፣ብዙዎች ሕዝቦች፣ከቅኝ አገዛዝ  ቀንበር ነፃ የወጡበት  መርህ ነው። በአገራችንም ጀብሓ፣ ሻቢያ፣ ሕወሐት፣ ኦነግና የመሳሰሉት የተመሠረቱት፣ብሔራቸውን  ነፃ ለማውጣት ነበር።

ይህም  የነፃነት ትግል፣ በተለይ ከፊልስጤምና ከእስራኤል ቅራኔ የተነሳ፣ በሊቢያ፣ በግብፅ፣ በሱዳን፣ በሱማሊያና በአረብ አገሮች  ይደገፍ ነበር።ስለሆነም ቅራኔው ሰፍቶ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ከዲስ አበባ ላማስነሳት  ጥያቄ ቀረበ። በዚህም ጃንሆይ ደንግጠው   ከእሥራኤል ጋር የነበራቸውን የዲፖሎማሲ ግንኙነት አቋረጡ። በአስመራ የሚገኘውንም የአሜሪካን ጦር ሰፈር ዘጉ።ሰለሆነም ንጉሱ ከውስጥም ከውጭም ደጋፍና  ተባባሪ  አጥተው ለወታደሮች እጃቸውን  ሰጡ።

ወታደራዊ መንግሥትም ሥልጣን እንደ ያዘ፣ ጄንራል አማን አምዶምን ወደ አስመራ ልኮ፣ከሸብያና ጀብሓ ጋር ድርድር አካሄደ።ድርድሩ የብሔርና የቋንቋ እኩልነትን የሚመለከት ስለ ነበር፣ በእኛ ዘመነ መንግሥት፣ የአማርኛ ቋንቋ የግዴታ ትምህርት  መሆኑ አይቀርም በማለት ድርድሩን ወድቅ አደርጎ፣ ጄኔራሉንና ስድሳዎቹን ብግፍ እሸነ። ከዚህም  የተነሳ ሕዝባችን ለአስራ ሰባት አመት በጦርነት ተማገደ። ኤርትራንም የባህር በሩንም አጣ።

ይህ ነበር እንግዲህ ኢሕአዴግን ለመንግሥት ሥልጣን ያበቃው፣ አሁን ላለውም ሁኔታ  መንሴ የሆነው። እኛም አሁን መጠንቀቅ የሚገባን፣ በመንግሥት ሥልጣንና በወታደራዊ ድሎች በደስታ  ሰክረን፣ ለልጅ ልጅ የሚተላለፍ ቂም በቀል ከማትረፍ፣በድልን ለፈጣሪ አሳልፎ በመስጠት፣ ሁሉንም በልኩ በማድረግ፣ለሰላም መሸንፍ ይገባናል።

በዚህም ረገድ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉ በሚገኙበት ክልል፣ዞንና ወረዳ፣ በመረጡት ቋንቋ፣ ራስቸውን በራስ የማስተዳደር መብታቸው ሊከበር ይገባል።የኢሕአዴግም ሆነ  የሕወሐት ስህተት፣ ይህን የሕዝቦች መብት  ብትክክል አለመፈጸም ነበር፣የመንግሥት ሥልጣን ያሳጣቸው። ብልፅግናም ያንኑ ስህተት ለመድገም ሕገ መንግሥቱን ሸብረክ አድርጎ፣አሐዳዊነትን በማቆለጳጰስ ላይ ይገኛል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የህልውና ተጋድሎው በዴሞክራሲያዊት አገር እውን መሆን ይጠናቀቅ ዘንድ...

ስለሆነም ይህ የሕዝቦች  መብት፣በፌድራል መንግሥቱ  ተገቢውን አጽንኦት አግኝቶ፣ ብሔር ብሔረሰቦች በሚገኙበት፣ክልል፣ ዞንም ሆነ፣  ወረዳ፣ በቋንቋቸው ራስን በራስ በማስተዳደር፣ እምነታቸውንና ባህላቸውን በመንከባከብ፣ ቀርሳቸውን የማበልጸግ መብታቸው ሊከበር ይገባል።ይህ ከሆነ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ያከትማል፣ ጥላቻ ይወገዳል፣ሰላማችንም ይሰፍናል።

ሌላው በሕዝባችን መካከል ያለው  ቅራኔ ከፌድራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ ጋር የተያያዘ ነው።አገራችን በቅኝ ግዛት ባለመያዟ የገዥው መደብ የመግባቢያ ቋንቋ አማርኛ ነበር። አገራችን ደግሞ በርዋን በአለም ሥልጣኔ ላይ ዘግታ፣ በጭለማ የቆየች በመሆኗ፣ ይህ  ቋንቋችን እንደተቀረው የኃይላን ቋንቋዎች፣በሳይንስና በቴክኖዎሎጂ ቃላት የዳበረ አይደለም። ለከፍተኛ ትምሕርት መስጫም አልዋለም፣ስለሆነም ከዓለም ሥልጣኔ ጋር እኩል ወደፊት ሊያራምደን አልቻለም።በዚህ ላይ  ሰባ ከመቶ ለሚሆነው ሕዝባች ሁለተኛ ቋንቋ ነው።ይህም ቋንቋ  የዕኩልነት መርሆን የሚያፋልስ ነው።በተለይ ደግሞ አንደበታቸውን በሌሎች ቋንቋዎች የፈቱ  ልጆች፣ የአማርኛ ቋንቋ መማር የግዴታ በመሆኑ፣ ለተጨማሪ የትምህርት ጫና ዳርጎቸዋል።  ይህም አድሎና ጫና ትምህርትን እንዲጠሉ፣ በፈተናም እንዲወድቁና በፌድራል የሥራ ዕድልን እንዳያገኙ በማድረጉ፣በአገራችን ያለውን የብሔር ቅራኔ ሊያባብሰው ችሏል።

ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣በቤንሻጉል፣በሱማሊያም ሆነ በገምቤላ  ላለው  ግጭት እውነተኛ መንስዔው፣ ይኸው በዳግማዊ አጼ ምኒልክ የግዛት ማስፋፋት ወረራ የተጀመረ፣ የብሔርና የሃይማኖት ጭቆናና አፈና ነው።በመሆኑም ነው ትግሬ በሕወሐት፣ ኦሮሞ በኦነግ፣ አማራም በአብንና በፋኖ የተደራጁት፡፡ስለዚህም ነው ከክልላቸው ውጭ የሚኖሩ አማራዎች ላይ ችግሩ ተንፀባርቆ፣በሰላም አብሮት ከኖሩት ብሔሮች ጋር እየተጋጩ ከመኖሪያ ቄዬአቸው የሚፈናቀሉት፡፡

ወንድሞች ቋንቋ መግባቢያ ነው ካልን፣ የምንግባባው  ስለ ምድራዊ ሕይወታችን ብቻ አይደለም።ምዕመናን  የፈጣሬያችውን እውነተኛ ቃልና ፈቃድን፣  ለይተው ለማወቅ የሚችሉት በቋንቋ ነው።ስለሆነም ነው ቅዱሳት መጽሐፍት፣ ከእብራይስጥ ወደ ግሪክና እንግሊዚኛ፣ ከዚያም ወደ አረብኛና ግዕዝ፣ብሎም በአለም ቋንቋዎች ሁሉ የተተረጎሙት፡፡ በዚህ ረገድ በአገራችን ለአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የተሰጠው ዕድል ፣ለሌሎች ቋንቋዎች ተናጋሪዎችም  ተሰጥቶ፣ ነፍሳት ሁሉ  የእግዚአብሔርን ቃልና ፈቃድ እኩል ተረድተው፣ከሰይጣንና ከጣኦት አምልኮ ነፃ በመውጣት፣ የእግዚአብሔርን  መንግሥቱ ለመውረስ እንድችሉ ማገዝ ይገባል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የዲዛይን ችግር የሚያንገላታው የአማራ ብልፅግና ፓርቲ - መስከረም አበራ

ሌላው ሕዝባችንን በእርስ በርስ ጦርነት እየማገደ ያለው፣ የመንግሥት ሥልጣን ጥያቄ ነው።የመንግሥት ሥልጣን የሚያስፈልገው ሕዝቡን በቅንነት በማገልገል በሰላም በማስተደደር ወደ ጋራ ብልፅግና ለመምራት ከሆነ፣ ሕዝቡ ራሱ መሪዎቹን መምረጥ ይኖርበታል። ሕዝብ የሚያምንባቸውን ሊመርጥ የሚችለው ደግሞ ለምርጫ ከሚቀርቡለት ዕጩዎች መካከል በመሆኑ፣የአቢዮታዊ ዴሞክራሲ የፓርቲ አመራር ተወግዶ፣ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች ሁሉ እኩል፣ሰላማዊ የውድድር  መድርክ ሊሰፋ ይገባል። ገዥው ፓርቲ በድርጅታዊ አሠራር ራሱን የሚያስመርጥበት፣ ፓርላሜንተሪያዊ  ቅርጸ መንግሥት ተወግዶ፣ በፕሬዚደንታዊ ቅርፀ መንግሥት ሊተካ ይገባል።ይህ የሥልጣን መወጣጫ ሥውር መሰላል ከተወገድ፣የቀረውን ችግር ሕዝባችን ራሱ በሂደት ይፈታዋል።

በዚህም ረገድ ከሕዝባችን መካከል ያለውን ተፃራሪ ቅራኔዎችን ካስወግድን፣  ሕዝባችን በቋንቋው ራሱን በራሱ እያስተዳደረ፣ ባህሉን እየበለጸገ፣ቀርሶቹን እየተንከባከበ፣በሰላም እምነቱን እየተለማመደ፣በደስታ ይኖራል። በዚህም ታግዞ በሙሉ ኃይሉ ለሥራ ከተነሳ፣ ፈጥኖ በድኅነት ላይ ድልን ይቀዳጃል።በተረፈ ቅራኔን አፍኖ በልማት ላይ ብቻ ማተከር ትርፉ፣ የብብትን እያፈሰሱ መልሶ መልቀም ይሆናል።

ስለሆነም ሕዝባችን  አሁን ካለበት ጦርነትና ጥላቻ ለመገላገል፣ ከሁሉ በፊት የትግራይ ሕዝብ  በክልሉ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሕገ መንግሥታዊ መብቱ ሊከበርለት ይገባል። ሕወሐትም በበኩሉ  የፌድራል መንግሥት ሥልጣን አክብሮ፣ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን መፈጸም ይኖርበታል።

ለዚህም ከአፍሪካ አንድነት አደራዳሪ በተጨማሪ፣ በሐወሐት የተጠቋሙ ኬኒያታ  ሊታከሉ ይገባል።በባህላችንም አስታራቂ ሽማግሌ የሚመረጠው ከግራና ከቀኙ  ነውና። የአውሮፓ ኅብረትና የአሜሪካ ታዛቢነትም ወሳኝ ሰለሆነ መቀበል ይገባል።መቼም ቢሆን መቼ እርቁ ሊሰምር የሚችለው በአደራዳሪዎቹ ግፊት ብቻ አይደላም።የግራና ቀኝ አጫፋሪዎች እንደበታቸውን  ዘግተው፣ ሁለቱ ዋና ተደራዳሪዎችም  ለሰለም ፈቅደው ሲሸንፉ ነው።

ስለሆነም ያለፈው አልፏል አሁን በወገኖቻችን ላይ  ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ  ጦርነቱ  አሁን በሚገኙበት ሥፍራ መቆም ይኖርብርታል፡፡ለጊዜው  ጥላቻና ቅራኔ እስኪረግብ ድረስ በሁለቱ ጦር ግንባር መካከል የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ጓድ እንዲሰፍር መፍቀድ ይገባል።  ከዚያም ሕወሐት  የቡድን  የጦር  ትጥቅን በመፍታት ለሰላም ጓዱ ማስረከብ ይኖርበታል። ይህም በሚሆንበት ጊዜ የፌድራል መንግሥትም፣ ለትግራይ ሕዝብ የምግብና የሕክምና እርዳታ፣ የባንክ፣የቴሌፎን፣የማብራት አገልግሎት  አሟልቶ ሊያቀርብ ይገባውል።ጦርንርቱ በዚህ ከረገበ የተረፈውን ችግር፣ በአገራዊ ምክክር የሚፈታ ይሆናል።ፈጣሪ አምላኩን የሚያከብር፣ወንድሙን የሚወድ ቅዱስ ሕዝብ ፣እውነትን አይፈራም፣ሰላምንም አይጣላምና፣በዚህ የሰላም ጥረት ላይ የቸሩ ፈጣሪ አምላካችን ፈቃድ  እንዲታከልበት እማጸነዋለሁ!!!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለሴረኞች እየመሸ ይመስለኛል በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው  ሁሉ ይገለጥ ዘንድ ነው - ሰርፀ ደስታ

ምክሬን ስሙ። ቅራኔን በሰላም ፍቱ!

ጆቢር ሔይኢ ከሁስተን ቴክሳስ።

 

5 Comments

  1. በአስመራ የሚገኘውን የአሜሪካን ጦር ሰፈር የዘጋው ደርግ እንጂ አጼ ህይለሥላሴ አይደሉም።

  2. ዳሹሬ ያልከው ትክክል ነው። ሆኖም ጆቢርን በተመለከተ ያልተፈጽመ ሁኔታን እንደተፈጽመ አድርጎ ማቅረቡ ስህተት ብቻ ሳይሆን ውድቀትም ነው።በመሆኑም አሥመራ ይገኝ የነበረው የአሚሪካ ጦር ሰፈር ወይም ቃኘው ሻለቃን የዘጋው ዳሹሬ እንዳለው የደርግ አስተዳደር እንጂ የጃንሆይ አስተዳደር አይደለም።ከላይ በጠቀስካቸው አገሮች ጃንሆይም ደንግጠው ከእሥራኢል ጋር የነበራቸውን የዲፕሎማሲ ገንኙነት አልዘጉም። እንዲሁም የአፍሪካ አንድነት ድርጂትን ከአዲስ አበባ ለማስነሳት ጥያቄ ያቀረበው የሊብያ መሪ በነበረው ሞሐመድ ጋዳፊ በደርግ አስተዳደር እንጂ በጃንሆይ አስተዳደር አይደለም እና አስተያየትን ለሌሎች ማካፈሉ መልካም ቢሆንም ታሪክን አዛብቶ መጽፉ ግን የራስን ውድቀት ያመቻቻል።

  3. This piece of writing is full of the politics of simplicity or shallowness. distortion of facts and history, misleading, hatred toward the Amhara and Amharic language, highly deceptive way of looking into the very idea of individual and group rights. It ignores how to bring about a fundamental and long lasting solution by getting rid of the very criminal political system of EPRDF/OPDO/Prosperity by any necessary means . It is absolutely a political stupidity to talk about the emergence of democratic system under the current ruling elites !

  4. “ይድረስ ለሃገሬ ህዝቦችና መሪዎች” ከዚህ ስንኝ ስንነሳ ጸሃፊው በጎሳ ከተበታተኑት የአንዱ ጎሳ አባል ሁኖ ያሳለጠው ምክር ነው ወይስ ጠቅላላ ኢትዮጵያን የተመለከተ ነው? የአሜሪካ ህዝቦች፤የጀርመን ህዝቦች፤የሳውዲ አረቢያ ህዝቦች ሲባል አልሰማንም፡፡ በሁለት ዋልታ ከሚወጠሩ ይህን ጽሁፍ ወይ ለሽመልስ አብዲሳ ወይም ለቀረባቸው ጎሳ መሪና ህዝብ ቢያደርጉት መልካም ነበር፡፡ ሽማግሌ የተበተነውን ይሰበስባል የተጣላውን ያስታርቃል እንጅ እንዲህ መላ ቅጡ የጠፋ ነገር ተቀበሉ ባላለን ነበር፡፡ እንደ ጸሃፊው አባባል የቋንቋና የሃይማኖት ነጻነት ካልተከበረ ይላል፡፡ ሁለቱ ትላልቅ ሃይማኖት በመከባበር እስከ ዛሬ አብረው ቆይተዋል በወቅቱ እንደ ሳውዲ አረቢያ እንደ ም እራብ አዉሮፓ ሃገሮች እንደ አረብ ሃገሮች ኦርቶዶክስም የመንግስት ሃይማኖት ሁኖ ቆይቷል፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ በግብጽና በሌሎች የእስላም ሃገሮች እንደተደረገው ሌላውን ሃይማኖት ላጥፋ አላለም፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ሃይማኖትን በግድ የሚያስለውጥ ብለው የሚቀጣ ህግ አውጥተው ነበር የቅርቡ አጼ ሃይለ ስላሴ ቁራንን በገንዘባቸው አስተረጉመው ለእስላም ወንድሞቻችን በነጻነት እንዲያከብሩ አስደርገዋል፡፡
    የአቶ ጆቢር እሳቤ እንደሚመስለኝ ሌላውን ሃይማኖት አጥፍተው የሳቸውን ሃይማኖት የሚከተሉትን ማንበር የሌላውን ቋንቋ አጥፍቶ የነሱን ቋንቋ ማስፋፋት የፈለጉ ይመስላል፡፡ ይህን ሽመልስ አብዲሳ፤ቀጀላ መርዳሳ፤አብይ አህመድ፤ታከለ ኡማ፤አዳነች አቤቤ እያስፈጸሙት ስለሆነ መድከም አልነበረባቸውም በተረፈ ቀይ ባህር ያለውን ተንኮለኛ አሳ ለይቶ በሚያውቅ ህብረተሰብ በሚኖር ህዝብ እንዲህ ማላገጥ ባልተገባ ነበር፡፡ በምክር መልክ ሳይሆን በትችት ሃሳባቸውን ቢያቀርቡ እይታቸው ነው ብዬ ማለፍ እችል ነበር ነገር ግ ን ጽሁፉ መርዝ ያዘለ በመሆኑ አስተያየት መስጠት ተገቢ ነው እንግዴህ ሌላው ንቆ ካለትዎት ብዙ ትዝብትና ትችት ማስተናገዶ አይቀርም መልካም አዲስ አመት ይህችም ቋንቋ ሁና እንዳታግባባን እሷንም ካላጠፋን እያላችሁ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share