ያልተለመደ ወሲብ በተለይም በፊንጢጣ በኩል (anal sex) በመፈፀምና ከአንድ በላይ ወሲብ አጋር በመያዝ በሴቶች ላይ ከሚከሰቱ ካንሰሮች ውስጥ የሚፈረጀው የፊንጢጣ ካንሰር ነው፡፡ እንዶኒውስዊክ መፅሔት ሰፊ ዘገባ ከሆነ ይህን ካንሰር ለየት የሚያደርገው ችግሩ ከአንዳንድ ሴቶች ቅጥ ያጣ የወሲብ ባህሪ ጋር የሚያያዝ መሆኑና በዚህም ማህበረሰባዊነት በሌለው ባህሪ ሳቢያ የሚከሰተውን ካንሰር ለሌሎች ለመናገር አሳፋሪ (taboo) መሆኑ ነው፡፡
ለሰዎች በተለይም ለሐኪም የማይነግርበት አንዱ ምክንያት ሰዎች ችግሩን ከተለያዩ አሉታዊ ነገሮች ጋር ስለሚያያይዙትና መያዛቸው ስለሚያሳፍራቸው ይዘውት ይቆያሉ፡፡ ችግሩም ይባባሳል፤ ሌላውም ሰው ያስተላልፉታል ይላል መፅሔቱ፡፡
ብዙ ሰዎች የፊንጢጣ ካንሰር እንዳለባቸው ይነገራል፤ ነገር ግን ለሕይወታቸው የሚጠቅም ህክምና ለማድረግ በጣም ይቸገራሉ፡፡ ብዙ ጊዜ የቅርብ ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም የሚቀርቧቸው ጓደኞቻቸው ያለባቸውን ችግር ቢያውቁትም በሽታው ያለባቸው ሰዎች ለቤተሰቦቻቸውም ሆነ ለሐኪም ይህን በሽታ አውጥተው መናገር አይፈልጉም፡፡
በሽታው ያለባቸው ሰዎች ‹‹በግልፅ የቂጥ (የፊንጢጣ) ካንሰር አለብኝ›› ብሎ መናገር በጣም ያሳፍራቸዋል፡፡ ብዙ ጊዜም ስሙን ሸፋፍነውት ማለፍን ይመርጣሉ፡፡ በሽታው መኖሩና አለመኖሩ የሚታወቀው በተደጋጋሚ በሚደረግ የኮሎኖስኮፒ ምርመራ ሲሆን በዚህ ምርመራ የመቀመጫ ካንሰር ለበት ሰው በቀጣይ በሚደረግለተ ምርመራ ካንሰሩ በደም ስር ውስጥ ተዛምቶ ይሁን አይሁን ለማረጋገጥ ተጨማሪ ምርመራዎችን ሊያደርግ ይችላል፡፡
ህክምናው በአሜሪካ ሀገር ውስጥ በዓመት ለ8,000 ሰዎች ይደረጋል፡፡ የመቀመጫ ካንሰር ብዙ ያልተለመደ በሽታ ቢሆንም ግን የበሽታው ቁጥር ላለፉት ሦስት ዓመታት በሶስት እጥፍ ጨምሯል፡፡ በየዓመቱ በዚህ በሽታ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር በ2 በመቶ እየጨመረ ይገኛል፡፡ የቂጥ ካንሰር /anal cancer/ ህክምናውን ለመጀመር ብዙ ሰዎች ለውሳኔ ይቸገራሉ፤ ምክንያቱም ይህ ካንሰር የሚያጠቃውን የሰውነት ክፍል ለመግለፅ ስለሚያፍሩ ብዙ ሰዎች ዝምታን ይመርጣሉ፡፡
ይህ በሽታ ብዙ ጊዜ የሚከሰተው ከአንድ በላይ የሆነ የወሲብ ጓደኛ በመኖር ወይም ከተሌዩ ሰዎች ጋር ወሲብ በመፈፀም ነው፡፡ እንዲሁም ባልተለመደ መንገድ ወሲብ መፈፀም ማለትም በፊንጢጣ በኩል የሚደረግ ወሲብ ለዚህ በሽታ መንስኤ ተደርገው ከሚጠቀሱት ምክንያቶች ውስጥ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡
ከዚህ በላይ ይህን በሽታ እንዲባባስ የሚያደርገው ሰዎች በበሽታው ከተያዙ በኋላ የሚደርስባቸው ትልቅ የስነ ልቦና ጉዳት ነው፡፡ ‹‹ሰው ምን ይለኛል›› በሚል እሳቤ በሽታው ወደ መጨረሻ ደረጃ እንዲደርስ ከማድረጉም በላይ በቀላሉ ወደሌሎች ሰዎች ሊተላለፍ ይችላል፡፡
ዶ/ር ካርይ ኢንግ የካንሰር ህክምና ባለሙያ ሲሆኑ በአሜሪካን ሀገር በቴክሳስ ዩኒቨርሲቲ በሜድ አንደርሰን ሴንተር ውስጥ የካንሰር በሽታ ህክምና ለመስጠት እስፔሻላይዝ ያደረጉ ሲሆን እሳቸው እንደሚሉት ከሆነ በዚህ በሽታ ላይ ትልቅ መገለል እንዲሁም ከሌሎች በሽታዎች ተለይቶ የሚታይበት መንገድ አለ ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ለዚህ የካንሰር በሽታ የሚሰጡት ግምት እና ትኩረት እንደሌሎቹ የካንሰር በሽታዎች ሳይሆን ከዛ በላይ የሚጓዝ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ችግሩን አውጥተው ለመግለፅ ድፍረት ስለሌላቸውና ማህበረሰቡ የሚቀበላቸው ስለማይመስላቸው ነው፡፡
እንደሳቸው ገለፃ ሌሎች የካንሰር በሽታዎችን ማህበረሰቡ ለመግለፅና ለመናገር ምንም አይቸገርም፡፡ ለምሳሌ የጡት ካንሰርን ሴቶች ያለፍርሃትና ያለማፈር ጮክ ብለው ጣራን በሚሰነጥቅ ድምፅ ሊናገሩት ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም በማህበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ስላገኘ በበሽታው የተያዙ ሴቶች ስለበሽታው ያለፍርሃት ከሰዎች ጋር ያወራሉ፡፡
በ1914 (እ.ኤ.አ) ለመጀመሪያ ጊዜ ቤቲ ፎርድ የተላለፈ የጡት ካንሰር እንዳለባትና በዚህ በሽታ የተነሳ ጡቶቿ እንደተቆረጡ ተናገረች፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሰዎች በነጻነት ስለጡት ካንሰር መናገር ችለዋል፡፡ ይቺ ቤቲ ፎርድ የተባለችው የመጀመሪያዋ የጡት ካንሰር አብዮተኛ ተደርጋ ተወስዳለች፡፡ ይቺ ሴት ደፍራ ስለበሽታው በሚዲያ በመናገሯ በሌሎች የካንሰር ህሙማን ያለባቸውን በሽታ በግልፅ ያለፍርሃት እንዲናገሩ በር ከፍታለች፡፡
ይህ የቂጥ ካንሰር በሽታ ብዙ ጊዜ ሴቶችን የሚያጠቃ ቢሆንም በተሌ ሆሞሴክሽዋል ወንዶችም በበሽታው ይጠቃሉ፡፡ ብዙ ጊዜ በፊንጢጣ በኩል ደም ሊፈስና ቁስል ሊታይ ይችላል፡፡ በርካታ በዚህ በሽታ የተጠቁ ሴቶች እንደሚሉት ከሆነ ‹‹በጡት ካንሰር ብንያዝ ኖሮ በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እናገኝ ነበር፡፡ ነገር ግን በቂጥ ካንሰር ለተጠቁ ሰዎች ማህበረሰቡ ያለው ምላሽ ወይም አስተያየት ጤናማ ያልሆነ ወይም አስነዋሪ ህይወት እንዳለን ነው የሚቆጥረው›› ይላሉ፡፡ በዚህ የተነሳ በማህበረሰቡ ከሚሰጠው ዝቅተኛና ትንሽ ግምት ተነሳ ስለጉዳዩ ለመግለፅ ያፍራሉ፡፡
ለዚህ በሽታ መንስኤ 90 በመቶ የሚሆነው የሚከሰተው በወሲብ በሚተላለፈው ፓፒሎማ ቫይረስ (papilloma virus) ወይም በአጭሩ HPV በሚባል ሲሆን ይህ ቫይረስ በተመሳሳይ ለማህጸን በር ካንሰር እንዲሁም በወንዶችና በሴቶች ብልት ላይ ለሚፈጠሩ በሽታዎች መንስኤ ነው፡፡ ይህ HPV ቫይረስ ከሰው ወደ ሰው በቆዳ ንክኪ የሚተላለፍም ነው፡፡ በተለይ ያለ መከላከያ በአፍና በፊንጢጣ በኩል የሚደረግ የግብረሥጋ ግንኙነት ሊከሰት ሁሉ ይችላል፡፡
በአሁኑ ወቅት 79 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች በዚህ ቫይረስ ይጠቃሉ፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሰዎች በህይወታቸው ውስጥ በሚፈጠር አንዱ አጋጣሚ በዚህ ቫይረስ የመጠቃት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ከ79 ሚሊዮን ከሚሆኑ በዚህ ቫይረስ ከተጠቁ ሰዎች ውስጥ በአሁኑ ሰዓት 27 ሺ የሚሆኑት በየዓመቱ የካንሰር ምርመራ ይደረግላቸዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 5 ሺ የሚሆኑት ደግሞ በፊንጢጣ ካንሰር ተይዘው ህክምና የሚረግላቸው ናቸው፡፡
በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ በፊንጢጣ ካንሰር ህክምና መስራችና ተቆታጣሪ የሆኑት ዶ/ር ጆኤልፕላቪስኖ እንደሚሉት ከሆነ የ HPV ቫይረስ በሚሰጠው ክትባት በመቀነስ ላይ ይገኛል፡፡ እናም ክትባቱን መውሰድ ትልቅ መፍትሄ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
ክትባቱ በተጀመረባቸው 10 ዓመታት ውስጥ የዚህ ቫይረስ ስርጭት መከላከል ተችሏል፡፡ ምክንያቱም ክትባቱ ለሴቶችም ሆነ ለወንዶች ህፃናትን በ11 እና 12 ዓመታቸው (ለግብረ ሥገ ግንኙነት ዕድሜ ከመድረሳቸው በፊት) ስለሚሰጣቸው ወደፊት ከሚገጥማቸው በቫይረሱ ከሚመጣ የካንሰር በሽታ መታደግ ተችሏል፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ወላጆች ክትባቱን ለልጆቻቸው ለማስወገድ ፍቃደኛ አይደሉም፡፡
የዚህ ምክንያቱ አንዱም ስለዚህ በሽታ በቂ እውቀት ስለሌላቸው ነው፡፡ ሌላው የህፃናት ዶክተሮች ለወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ ሙያዊ ምክር ስለማይሰጧቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እስካሁን በአሜሪካን ሀገር 40 በመቶ ሴት ህፃናትና 20 በመቶ ወንድ ህፃናት ብቻ ናቸው የቅድመ ክትባት አገልግሎቱን ያገኙት፡፡
ይህ ሁኔታ ደግሞ ችግሩ እንዲባባስ ያደርገዋል፡፡ ከዚህም በላይ በበሽታው የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በሚያጋጥማቸው የስነ ልቦና ጉዳት የተነሳ ህክምናውን ለማድረግም ሆነ በሽታው ምን አይነት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለማወቅ ይቸገራሉ፡፡ በዚህ የተነሳ የማይነገር በሽታ አድርገው ውስጣቸውን ያሳምኑታል፡፡ ውስጣቸውን በማሳመናቸው የተነሳ ስለራሳቸው የበታችነት ስሜት እና ተስፋ መቁረጥ እንዲሁም ለራሳቸውና ለሌሎች ሰዎች ግድ ማጣት ይገጥማቸዋል፡፡ በዚህ የተነሳ በሽታውን ወደሌሎች ሰዎች በቀላሉ ሊያስተላልፉት ይችላሉ፡፡
ይህ የማይነገር የተባለውን በሽታ በመናገር እና ቅድመ ክትባት በማድረግ እራስንና ወገንን ከሞት እና ከስቃይ መታደግ ይቻላል፡፡ ለዚህም ከግለሰብ ጀምሮ እስከ ማህበረሰብ ድረስ ጠንካራ ስነ ልቦናዊ ጥንካሬ ያስፈልጋል፡፡ የህክምና ባለሙያዎችም ለወላጆች ልጆቻቸውን የፀረ ፓፒሎማ ክትባት እንዲያስከትቡ ሊመክሯቸው ይገባል በማለት ኒውስ ዊክ ዘገባውን ቋጭቷል፡፡