ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ ለሶስተኛ ጊዜ በጸጥታ ኃይሎች ታሰረች – ኢትዮጵያ ኢንሳይደር
“ሮሃ ሚዲያ” የተሰኘው የዩቲዩብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና ባለቤት የሆነችው መዓዛ መሐመድ ዛሬ ረቡዕ ጷጉሜ 2፤ 2014 በፌደራል ፖሊስ አባላት ተይዛ መወሰዷን የስራ ባልደረባዋ እና ጓደኛዋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገረች። መዓዛ በፖሊሶች የተያዘችው ከቀኑ 11 ሰዓት ገደማ በሽሮ ሜዳ አካባቢ በግብይት ላይ ባለችበት ወቅት መሆኑን በስፍራው አብራት የነበረችው ጓደኛዋ ምስራቅ ተፈራ ገልጻለች።
ጋዜጠኛዋ በፖሊሶች ከመያዟ በፊት፤ አንድ ሲቪል የለበሰ ሰው መታወቂያዋን እንድታሳየው ጠይቋት ነበር የምትለው ምስራቅ፤ መዓዛ “ለምንድን ነው መታወቂያ የማሳይህ?” የሚል ምላሽ መስጠቷን አስረድታለች። ጥያቄውን ያቀረበው ግለሰብ መታወቂያ ማውጣት ሲጀምር፤ ሁለት የፌደራል ፖሊስ መለዮ የለበሱ የጸጥታ አካላት ወደ እነሱ መምጣታቸውን ምስራቅ ተናግራለች።
ይህን ተከትሎም ሲቪል የለበሰው ግለሰብ “የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ካሉ መታወቂያ ማሳየት አይጠበቅብኝም” ማለቱን የ“ሮሃ ሚዲያ” ባልደረባ ገልጻለች። ከዚህ ምልልስ በኋላ ሁለቱ ፖሊሶች መዓዛን በአቅራቢያቸው ወደ ቆመ ፒክ አፕ መኪና በመውሰድ እንድትሳፈር እንዳደረጓት አብራርታለች። የዓይን እማኟ በመኪናው ውስጥ መለዮ የለበሱ አራት የፌደራል ፖሊስ አባላትን ተመልክቼያለሁ ብላለች።
መዓዛ ወደየት እንደተወሰደች ታውቅ እንደሆነ ከ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ጥያቄ የቀረበላት ምስራቅ፤ “የት ነው የምትወስዷት ብዬ ነበር። ወደ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ብለውኛል። ግን [ወደዚያ ሄጄ] ሊያስገቡኝ አልቻሉም። ሰዓትም ስለሄደ እሷን አላገኘኋትም” ስትል ምላሽ ሰጥታለች።
ጋዜጠኛ መዓዛ እየተገባደደ ባለው 2014 ዓ.ም. ለእስር ስትዳረግ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። መዓዛ ለመጀመሪያ ጊዜ የታሰረችው በጥቅምት ወር ላይ ታውጆ በነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ ነበር። ፖሊስ መዓዛን “ሁከት እና ብጥብጥ የሚያነሳሱ መልዕክቶችን በማስተላለፍ” እንደጠረጠራት በወቅቱ ቢገልጽም፤ ጋዜጠኛዋ አንድም ጊዜ ችሎት ፊት ሳትቀርብ ለአንድ ወር ገደማ በእስር ላይ ከቆየች በኋላ ተፈትታለች።
መዓዛ ለሁለተኛ ጊዜ የታሰረችው ከሶስት ወራት በፊት ባለፈው ግንቦት ወር ውስጥ ነበር። መዓዛ በዚህኛውም እስር የተጠረጠረችው በተመሳሳይ “ሁከት እና ብጥብጥብ በማነሳሳት ወንጀል” ነው። ለ20 ቀናት ገደማ በእስር ላይ የቆየችው መዓዛ በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ በ10 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር መፈታቷ ይታወሳል።