September 7, 2022
25 mins read

ሕወሃት አምናም ዘንድሮም ትክክል ነው –የፕሮፓጋንዳ  አቅጣጫው  (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

ሁሉም ያለሙያው የፖለቲካ ተንታኝ ሆኗል የሚል ብዙ ቅሬታ ይሰማል። ይሄ ቅሬታ ከሚመለከታቸው ሰዎች አንዱ ነኝ። ፖለቲከኛ ፣ የፖለቲካ ሳይንስ ተመራማሪም ሆነ ጋዜጠኛ አይደለሁም።   በአብዮቱ   መፈንዳት፣  በሶማልያ ወረራ እና በእርስ በእርስ ጦርነት መካከል በማደጌ ምክንያት ከሕፃንነት እድሜየ ፖለቲካን በውድም በግድም ስከታተል አድጌ ጎልምሺያለሁ። ፖለቲካ ሁላችንንም የሚነካ ጉዳይ ነው። የኑሮ ውድነት ፖለቲካ ነው፣ ረህብ ፖለቲካ ነው፣ ጦርነት ፖለቲካ ነው። ፖለቲካና ኮረንቲን በሩቁ ተብሎ በሽብር እንዲያድግ የተደረገው ትውልድ ነው ሀገሩን ለባንዳ ራሱን ለባርነት ሸጦ ዛሬ መከራውን የሚበላው።

ለእውቀት ድንበር አለው ብዬ ባላምንም ሙያ በባለሙያ መሠራት እንዳለበት እስማማለሁ። አንዳንድ ጊዜ ሙያቸው ነው ብላችሁ የምትከታተሏቸው ተንታኞች ግልጽ ስሕተት ሲሰሩና ሕዝቡን ያሳሳቱ ሲመስላችሁ ግን የግል አስተያየት ለመጻፍ ትገደዳላችሁ። ይህ ጽሑፍ የሚያትተው ስለ ፕሮፓጋንዳ  አቅጣጫ ብቻ ነው።

ሕወሃትንም ሆነ ብልጽግናን በመተንተን ኢትዮ 360 እጅግ የተዋጣ ሥራ ሠርተዋል። (በነገራችን ላይ እነዚህን ሰዎች ለማደናቀፍ እጅግ ብዙ መዋእለ ንዋይ ፈስሷል። ይሁንና ይህ የፖለቲካ ጥርሳቸውን የነቀሉበት ሥርዐት እስከቀጠለ አበጥረው እንደሚተነትኑት እርግጠኛ መሆን ይቻላል። የእነሱን ትንታኔ ለማዛባት፣ ተአማኒነት ለማሳጣት ሥርዐቱ ያለው እድል መለወጥ ብቻ ነው። አዲስና የማያውቁት ሥርዐት መሆን።  አብዮታዊ ዲሞክራሲን በአዲስ ስም ከነድሮው ቅርናቱ ይዞ እየተንገታገቱ ላዩን ሽቶ ቀባብቶ እነዚህን ሰዎች መሸወድ ይከብዳል።) ይሁንና አልፎ አልፎ አልተሳሳቱም ብዬ አላምንም።

ኢትዮ 360ዎችን ጨምሮ ብዙ ተንታኞች በተለይ ሕወሃት ከትግራይ ወጥቶ አማራና አፋርን በወረረበት ወቅት (ባለፈው ወረራው) ያካሄደው ፕሮፓጋንዳ የተሳሳተና ለፕሮጄክቱ እንቅፋት የሆነበት ነው ይላሉ። በእውነቱ አሜሪካና ሕወሃትን በፕሮፓጋንዳ አቅጣጫ ለማማት ያስቸግራል (እጅግ የተካኑበት መስክ ነውና)። ተሳሳቱ የሚባለው ኅቡእ ዓላማቸውን ካለመረዳት በመነጨ ነው።

(እዚህ ጋር ታገሱኝና አንዲት ሠርጥ ላስገባ። አሜሪካ ካፍጋኒስታን ተሸንፋ ወጣች ይላል የዋሕ። ምክንያቱም ስትገባ የነገረችውን ፕሮፓጋንዳ እንጂ ዋነኛ ዓላማዋን ስላልመረመረ። ሽብርተኝነትን ለመዋጋትና  ዲሞክራሲ ለማስፈን ያለችውን ፕሮፓጋንዳ ይዞ ቀርቷል። እሷ ግን አፍጋኒስታን የገባችበትን ዋና ኢኮኖሚያዊ፣ ጂኦፖለቲካዊ ዓላማ በደንብ አሳክታ ስለጨረሰች ከዚህ በላይ  የመቆየት ትርፉ ኪሳራ ብቻ መሆኑን ተገንዝባ ወጥታለች። ከጦርነት ያልተለየቸው አሜሪካ በየዘመኑ በጦርነት የምትሳተፍበትን ምክንያት በማርና ወተት ለውሳ የምታቀርበውን ይዘን ከዚህ ከነገረችን አኳያ እንጂ ከእውነተኛ የጦርነት ተሳትፎዋ መንስኤ አኳያ ባለመረዳት ተሸንፋ ወጣች ገለመሌ ስንል እንደመጣለን። በተመሳሳይ አቢይ አህመድ ሕግ ማስከበር በሚል ፕሮፓጋንዳ ትግራይ ዘምቷል። ትግራይን ጥሎ ድንገት ፈርጥጦ ሲወጣ አስተውሎ “ሕግ ሳይከበር ተሸንፎ ወጣ እሪ!” የሚል ብዙ አለ። እሱ ግን ወደ በሻሻ ቀይረናታል ሲልህ ትግራይ  የገባበትን እውነተኛ ዓላማ ነግሮሃል። ስለዚህ የሱን ዓላማ በስኬት እንዳጠናቀቀው ልትጠረጥር ይገባ ነበር። ድንገት ግር ካለህም ስብሐት ነጋን ፈትቶ ታዴዎስ ታንቱን ሲከረችም የሕግ ማስከበሩ ጭምብል ወልቆ ልታይ ይገባህ ነበር።)

 

ወደ ሕወሃት ስንመለስ

ደርግን በመጣል ሂደት አማራን እያጃጃለ፣ በተሳካ ሁኔታ አራት ኪሎ የዘለቀ ድርጅት እንዴት አምና ይህንን የሰማንያዎቹን ስኬታማ የፕሮፓጋንዳ መስመሩን ለውጦ፣ እንዲያውም በተጻራሪው “አማራ ወዮልህ! መጣሁበህ!” እያለ ሊመጣ ቻለ? ከዚህ የሚያገኘው ጥቅም ምንድነው? እንዴት የሚያስከትለውን እንቅፋትና ጉዳት አላጤነውም? ብለው ሳይጠይቁ የፕሮፓጋንዳውን አስቀያሚነት ብቻ በማጤን ሕወሃት በዚህ ፕሮፓጋንዳ የሚጎዳውን ነገር ሠራ፣ ተሳሳተ ወደ ማለት ሄደዋል። ይሄም የተዛባ ግምገማ ሕወሃትን በተመለከተ የጠለቀ ንቅትና ጥላቻ በመኖሩ በሕወሃት ጠላቶች እጅግ ብዙ ጊዜ የሚፈጸም ለሕወሃትም እጅግ ብዙ የጠቀመው የጠላቶቹ ሥሕተት ነው።

ሕወሃት ግን ትክክል ነበር። 

የሚበጀውን የፕሮፓጋንዳ መሥመር ነበር የቀየሰው። ሕወሃት ተምቤን ቆላ ውስጥ ተሸንቁሮ መቶ በመቶ አዲስ አበባ ተመልሼ ሥልጣን ላይ እወጣለሁ የሚልበት ሁኔታ ላይ አልነበረም። በዚህ ወቅት እጅግ አደገኛ እና ሊያጠፉኝ ነው ብሎ ያሰባቸው ሁለት ኃይሎች ነበሩ። ኦነግ ብልጽግና (ኦህዴድ) እና ኢሳያስ አፈወርቂ። ከሁለቱ ደግሞ ወሳኝ ምት የሆነበት በምሬትም የዘመተበት ኢሳያስ መሆኑን ያውቃል። የጀርባውን እሾህ – ዝንጀሮ መጀመሪያ መቀመጭያዬን ያለችውን መርጧል።  ስለዚህ ሕወሃት  በመጀመሪያ የኤርትራን ማነቆ ማላቀቅ ትኩረቱን ላይ ያደርገ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት ላይ አደረገ።  በከፍተኛ ደረጃ ኤርትራን በመክሰስና በማጋለጥ ላይ ያተኮረ ዘመቻ ከፈተ። ኤርትራ በከረመችበት የማእቀብና የመገለል ጥላ ምክንያት ዘመቻው እጅግ የተሳካ ነበር ለማለት ይቻላል።

በሁለተኛ ደረጃ ሕወሃት በብረት ጫማ እንደጆርጅ ፍሎይድ ጉሮሮው ላይ የቆመውን ኦነጋዊ የአቢይ አህመድ ኃይል ከጉሮሮው ላይ ማስነሳት ላይ አተኮረ። ለዚህም አቢይ አህመድን ብብቱን እንደኮረኮሩት የሚያፍነከንከውን ነገር አሳዳጊው ሕወሃት ያውቃልና በጣም ውጤታማ የሆነ የፕሮፓጋንዳ ኩርኮራ በማድረግ የኦህዴድን የብረት ጫማ ከተምቤን ዋሻ ጉሮሮው ላይ አስነሳ።

ምንድነው ኦነጋዊውን አቢይ አህመድ ብብቱን እንደኮረኮቱት አስቆ የብረት ቦቲውን ያስነሳው ?

እውን አቢይ አህመድ በጣር ላይ የነበሩትን ሕወሃቶችን ነፍስ ዘርቶባቸው ትግራይን የማስተዳደር እድል የሰጣቸው በአንቀጽ 39፣ በሕገመንግሥት፣ በጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት፣ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ እሳቤ ከርሱ አቋም ጋር ባላቸው የስትራቴጂክ አጋርነት በሰከነ መንፈስ አስቦ ነበር? አሊያስ የጭፍጨፋ ክስ ስላቀረቡበት የወንጀል አቻ ለመፍጠር በማሰብ ብቻ ነበር?

ሕወሃቶች ማን በድሮን እንደቀጠቀጣቸው፣ ማን በታንክ አፈር እንዳበላቸው እያወቁ የሱን ስም ሳያነሱየአማራ ልሂቃንን እንበቀላለንየዘመተብንን አማራ ልክ እናስገባለን ዓይነት ፕሮፓጋንዳ ሲነዙ በአማራ ጥላቻ ጥርሱን የነቀለው ኦህዴድ በደስታ እንደሚያብድ እርግጠኞች ነበሩ። እንደታሰበውም ጠቅላላ ጦሩን አንስቶ፣ እንዳይቸገሩ ነዳጅና መሣሪያ ጨምሮ እስከሸኖ በማፈግፈግ ያውላችሁ አማራ! እንደልባችሁ ዝረፉት፣ ጨፍጭፉት፣ ግደሉት ብሎ ፈቀደላቸው።  ሕወሃቶች አቅም ያለው ጠላታቸው፣ የታጠቀ፣ የተደራጀ መንግሥታዊ ሥልጣንን ሁሉ ጠቅልሎ የያዘው ኦህዴድ መሆኑን ያውቃሉ። ተምቤን ሸለቆ ታጉረው ኦህዴድ ላይ ቢፎክሩ ባንድ አዳር ወደ አመድነት እንድሚቀይራቸው ተረድተዋል። ስለዚህ ሕወሃቶች ኦህዴድን የሚጥመው ነገር መናገር ነበረባቸው። አደረጉት። ነፍስ ዘሩ። እርግጥ ኦህዴድ ከወረወርላቸው ሥጋ አልፈው ሊነክሱ ሲቅበዘበዙ ክፍ! (ብስ!) ብሎ መቀሌ መልሷቸዋል። እነሱም ጅራታቸውን ቆልፈው ተፈቅዶላቸው የዘረፉትን ተሸክመው ለሌላ ቀን ለመዘጋጀት ከብርሃኑ ጁላ በተስተካከለ ፍጥነት ወደ መቀሌ ሸምጥጠዋል።

 

ዛሬም ትክክል ናችው። 

ዛሬ በሕወሃትና በአራት ኪሎ መካከል በዋነኝነት እንቅፋት ሆኖ የሚገኘው የአማራ ሕዝብ ነው። ወይም በትክክለኛ አገላለጽ የሕወሃት ያምናና ያቻምና ክፋት ያስመረረው የአማራ ሕዝብ። ሕወሃት ዛሬን እየኖረ የመጣ ድርጅት እንደመሆኑ ዛሬን የሚሻገርበትን ድልድይ ሲሠራ ነገ የሚኖርበትን ቤት እያፈረሰ ጭምር ነው። በዚህም መሠረት አምና ከተምቤን ሸለቆ ለመውጣት፣ የትግራይን ሕዝብም በቁጣና በጥላቻ ለማስነሳት፣ በስንቅና በትጥቅ ለመደራጀት ይበጁኛል ያላቸው ስሌቶቹ ለዘንድሮ እንቅፋት ፈጥረውበታል። ቢሆንም ታሪካዊ ልምዱ ወንዙን ሲደርስበት መሻገር ስለሆነ አሁን አዲስ የፕሮፓጋንዳ ስልት ቀይሶ እየተንቀሳቀስ ነው። ሕወሃት የአማራ ክልልን ከተሻገረ ኦህዴድ እንቅፋት እንደማይሆንበት ይተማመናል። ሕወሃቶች ሲፋቅ ኦነግ እንዲሆን አድርገው ከውልደቱ የገነቡት ኦህዴድ ዓባይን ሲሻገሩ ወይም በሸኖ ብቅ ሲሉ ሁሉም ኦነግ ሆኖ እንደሚጠብቃቸው ይገምታሉ። ተራ ግምት ደግሞ አይደለም።

ሕወሃቶች ይህንን የፕሮፓጋንዳ ለውጥ ሲያደርጉ ታሳቢ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር ምንድነው?

ኦህዴድ ለዚህ አዲስ ቅዱ የሕወሃት ፕሮፓጋንዳ አመቺ ሆኖ ነው የከረመው። አማራውን በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ያርዳል/ያሳርዳል። ወሎዬው ከእርድ ተርፎ ወደ አያቶቹ አገር ሲመጣ ኦህዴድ  የመንግሥት  ከለላ ነፍጎ በሕወሃት አስወርሮ ለዳግም መፈናቀል ይዳርገዋል። ወሎዬው በአዲስ አበባ ለእርዳታ ተደራሽ ሆኖ እንኳን እንዳይጠለል በኦህዴድ ፖሊስ በዱላ እየነረተ ያባርረዋል። ኦህዴድ አማራ ክልል ገብቶ እህት፣ ልጅና እናታቸውን በሕወሃት ከመደፈር፣ መሠረተ ልማትና ቤተ እምነታቸው ከመዘረፍ፣ ከብታቸው ሃብታቸው ቀዬአቸው ከመወረር፣ እንዲድን የሚታገሉ ወደ ሃያሺ የሚጠጉ ፋኖና ታጣቂዎችን ዘብጥያ አውርዷል። ኦህዴድ መንግሥታዊ ሥልጣኑን እና ስትራቴጂክ አቀማመጡን በመጠቀም የአማራ መሠረተ ልማቶች ተመልሰው እንዳይሠሩ፣ የተፈናቀለው ሕዝብ እርዳታ እንዳይደርሰው አድርጓል። ዲያስፖራው ለእርዳታ የላካቸውን የመድኃኒት  እና ሌሎችም እርዳታዎች አስገድዶ ከመቀማት፣ አጨበርብሮ ከመውረስ ባልተናነሰ በቦሌ አየር ማረፊያ በኩል የገቡትን መቶ በመቶ ሊባል በሚቻል ወስዷል።

ሕወሃቶች እነዚያው ያምናው እኩይ ምላሶች መሆናቸው እንጂ ይህንን ፕሮፓጋንዳ ለአማራው ጆሮ እንዳይጥም የሚያደርገው፣ ሌላ የትግራይ ድርጅት ተፈጥሮና አዲሱ የትግራይ ትውልድ እየመራው ይህንን የፕሮፓጋንዳ መስመር ቢከተል እጅግ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አያዳግትም። ከነዚሁ ጠባሳቸው እንኳን በሕዝቡ ዘንድ የተዘበራረቀ ሃሳብና ሊደግፋቸው የሚችልም ስሜት እንዳለ የጎበዜ ሲሳይ የነሐሴ መጨረሻ ቃለ መጠይቆች ፍንትው አድርገው ያሳያሉ።  እዚያም መሄድ ሳያስፈልግ በእያንዳንዳችን ልቡና ውስጥ የብልጽግና ብልግናና ክህደት ምን ዓይነት የተዘባረቀ ስሜት እንደፈጠረብን ማስተዋሉ በቂ ነው። ብልጽግናም በጦርነቱ ወቅት የሠራውን ሸፍጥ አሳምሮ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ገናም በሕዝቡ ዘንድ የሚፈጥረውን ስሜት የተረዳ እንደሆነ በሰነዶቹ አሳይቷል። ለምሳሌ ብልጽግና ለጉባኤ በሚዘጋጅበት ወቅት አባላቱን ለማሰልጠኛ እና የተወሰኑትን አራግፎ ለመቀጠል በተጠቀመበት ሰነድ በግልጽ እንዳስቀመጠው አንዱ ተግዳሮታችን ተካድን የሚል ስሜት ነው ብሎ  ነበር።   ይህም ተካድን የሚል ስሜት የተንሰራፋው በተራው ሕዝብ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በራሱ በሆዳሙ፣ በአድርባዩ፣ የብልጽግና ካድሬ ሰልፍ ውስጥ ጭምር በጉልህ የሚንጸባረቅ መሆኑን ያመነ ሰነድ ነው።

ታድያ ይህንን የዳበረ መሬት የሚያርስ የፕሮፓጋንዳ አቅጣጫ መቀየሱ የሕወሃትን በዚህ ዘርፍ ያለው ብልጣብልጥነት የሚያሳይ ነው። ባይጠቀምበት ነበር ጅል፣ ጅላጅልና ጅላንፎ የሚያስብለው።  አምና ይህንን ፕሮፓጋንዳ ሊቀርጽ አይችልም ነበር። እርግጥ የአማራ ሕዝብ አቢይ ኦነግ ነው ባላበት ማግሥት ነው ጦርነቱ የተከፈተው። ቢሆንም የአማራ ሕዝብ በመንግሥት ላይ ያለው እምነት መንግሥት ተብዬውን ኦህዴድን ሕዝቡ በሀገር ክህደት ደረጃ እንዲጠረጥረው የሚያደርስ አልነበረም። ሕወሃትም በሀገር ክህደት ሠራዊቱን መምታቷ ገና ትኩስ ቁጣ የቀሰቀሰ ነበር። በሌላ አነጋገር ሕዝቡ ከመንግሥት ይልቅ በሕወሃት ላይ የከረረና የመረረ ጥላቻ ነበረው።  የተወሰነውም ሰው አማራን በየክልሉ የምታስጨፈጭፈው ሕወሃት ናት የሚለውን የኦህዴድ ብልጽግና/አቢይ አህመድ ፕሮፓጋንዳ ይቀበለው ነበር።

ሕወሃት ለራሷ ሰማይና ምድሩ ጨልሞባት ተምቤን ውስጥ ከዛሬ ነገ አለቀልኝ ብላ በምትቁለጨለጭበት ወቅት እጅግ የሞቀና የደመቀ በንጹሐን ደም የተጥለቀለቀ የአማራ ጭፍጨፋ መካሄድ መቀጠሉ የጭፍጨፋው ባለቤት አራት ኪሎ መከተሙን ለብዙዎች ግልጽ ያደረገ ወቅትን ፈጠረ።  ኦህዴድ ተፈናቃዮቹን መልሶ ለማቋቋም፣ ገዳዮቻቸውን ለፍርድ ለማቅረብ፣ በትንሹ ብሔራዊ የሐዘን መግለጫ ለማድረግ እንኳን ሲሸክከው በመታየቱ በደሙ መነከሩን እና የጄኖሳይዱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መሆኑን ግልጽ አደረገው።

የፕሮፓጋንዳውን አቅጣጫ ለመተንተን እንጂ ሕወሃት በአማራ ክልል በሰላም የሚያልፍበት ሁኔታ ቢፈጠርለት የአማራን ሕዝብ ከእስከዛሬው ሁሉ በከፋ ደረጃና ባለ በሌለ ሃይሉ ሊያጠፋ የሚሞክር እንጂ በረከት ወይም እፎይታ የሚያመጣለት ድርጅት ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው። ይልቁንም በትግራይ እንዳደረገው በስም ዝርዝር ይዞ ተቃወሙኝ እና ሊቃወሙኝ ይችላሉ በሚላቸው ሰዎችና ቤተሰቦቻችው የጀመረ የዘር ማጥፋት ስራ እንደሚሰራ ጠንቋይ ሳይቀልቡ መተንበይ ይቻላል። የዚህ ጽሑፍ ጭብጥ ይህ ስላልሆነ እንለፈው።

ከታሪኩም ካየን የአማራም ሆነ የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨቋኝ ሥርዐትን መንግሎ ለመጣል ብርቱ ትግል የማካሄድ ልምድ ባይኖረውም፣  ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት ጨቋኝ ሥርዐት ሲበሰብስ ወይም ሲንገዳገድ ገፍቶ ለመጣል ለመተባበር ግን አያመነታም።

በዚህ መካከል የብዙ ሰው ምኞት እነዚህን ሁለት ቁማርተኛ የባንዳ ስብስቦችን (ሕወሃትና ብልጽግና) ያፈሰሱት የንጹሐን ደም በቅቶና ጽዋችሁ ሞልቷል ብሎ ቸሩ አምላክ ቢያስወግዳቸውና ኢትዮጵያ ወደ እውነተኛ ሰላም ብትሸጋገር ነው።

አዲሱ አመት ኦነግ፣ ሕወሃትና ብልጽግና የሚባሉ ድርጅቶች እና ቁራሌ አጃቢዎቻቸው ከስመው የኢትዮጵያ ተስፋ የሚያብብበት፣ ሰላም የሚሰፍንበት ያድርግልን።

 

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.

78665
Previous Story

በቀን ሁለት እስር ፣ጠዋት ጎበዜ አሁን መዓዛ! እስር ይቀጥል ይሆናል ትግል ግን አይቆምም ! (መስከረም አበራ)

የአቢይ አህመድ ጨለማ ጉዞ!
Next Story

ጭራቅ አሕመድ፤ የአማራ ሕዝብ ዋና ጠላት – መስፍን አረጋ

Latest from Blog

blank

አርበኛ አስረስ ማረ እና ምርኮኞቹ | ስለ ፋኖ የብሔራዊ ባንክ ገዥው ያልተጠበቀ ንግግር |

#ሰበር_ዜና #AmharaFano ➢መሰከረም 29/01/2017 ዓ.ምብዙ ድሎችን አግኝተናል፣➢1️⃣115 ምርኮኛ ➢2️⃣70 እስረኞችን አስለቅቀናል➢3️⃣ 7 ብሬን➢4️⃣2 ድሽቃ➢5️⃣ 4 ስናይፐሮችን➢ለትግል የሚጠቅሙ የነፍስ ወከፍ ክላሾችንተተኳሾችን መኪኖችም ገቢ… pic.twitter.com/GbYaOAtFtr — ትዝብቱ🔔 (@Geteriew1) October 12, 2024 በፋኖ የተማረኩት ኮሎኔል
blank

ትግሉ ይጥራ – ከጥሩነህ ግርማ

የህልውና ትግሉን ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ለማሸጋገር የኦይዶሎጂ ብዥታን ማጥራትና በመሬት ላይ ያለውን ተንኮል መጋፈጥና ማፅዳት ያስፈልጋል የህልውና ትግሉ በአማራ ብሄርተኝነት ላይ ያጠነጠነ እንደመሆኑ የመኖር አለዚያም እንደ ህዝብ  የመጥፋት ትግል ነው: ሌላው ኢትዮዽያዊ ወገን
blank

የፋሽስቱ አብይ አህመድ አሊ ኢትዮጵያ ውስጥ በአማራ ላይ እየተካሄደ ስለሚገኘው ጦርነት ከመስከረም 13 እስከ 27/2017 ዓ.ም በተለያዩ ቦታዎች ላይ የደረሰ የጉዳት !!!መረጃ:

ሸዋ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት መርሀቤቴ አውራጃ በደራ ወረዳ ልዩ ስሙ ኮሉ በተባለ አካባቢ ላይ በሚገኙ የአማራ ተወላጆች ላይ አሸባሪው የሸኔ ቡድን ከኦሆዴዱ ጥምር ጦር ጋር ቅንጅት በመፈጠር መስከረም 22 ቀን 2017ዒ.ም ከለሊቱ
Go toTop