September 5, 2022
ጠገናው ጎሹ
ከሁሉም በፊት ይህ ሂሳዊ አስተያየቴ እጅግ ተደጋጋሚና አስከፊ ለሆነ ውድቀት ከሚዳርጉን ፈተናዎቻችን አንዱ የሽንፈት ወዶ ገብነትና የአድርባይነት ደዌ ነውና ይህንኑ መሪር እውነት ተጋፈጠን ወደ ትክለኛው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ አደባባይ መሳባሰብ እስካልቻልን ድረስ ፈፅሞ የትም አንደርስምና ከምር እንውሰደው ለማለት ነው እንጅ በጠቀስኳቸውም ሆነ ባልጠቀስኳቸው አካላት ውስጥ ወይም በአጠቃይ በማህበረሰቡ ውስጥ አድርባይነትን ከመፀየፍ አልፈው የሚቃወሙ ወገኖች ፈፅሞ የሉም በሚል ደምሳሳና ደንቆሮ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ እንዳልሆ ግልፅ ይሁንል።
ይህንን ካልኩ ወደ አስተያየቴ ልለፍ፦
የሽንፈት ወዶ ገብነት እና ሥር የሰደደ የአድርባይነት ባህሪ (the behavior of complete submissiveness and chronic opportunism) በግለሰቦች ወይም በቡድኖች መካከል ከሚኖር ግንኙነት አልፎ በፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ ምቹ ሁኔታ ሲፈጠርለትና እንደ መልካም ነገር እየተለመደ ሲሄድ የሚያደርሰው ጉዳት አስከፊ ነው። ለዚህ ደግሞ ከእኛው ከእራሳችን በላይ ግልፅና ግልፅ ማሳያ (ምሳሌ) የለም።
በአሥርና በአሥራዎቹ ሳይሆን በብዙ ሽዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ወገኖች በማንነታቸው ምክንያት ያለማቋረጥ የግፍ ግድያ ሰለባዎች በሆኑበት ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ንብረታቸው እየወደመና እየተዘረፈ መፈናቀል ለሚያስከትለው የቁም ሰቆቃ በተጋለጡበት፣ ለሥልጣን የበላይነት ሽኩቻ የገቡበትን እሰጥ አገባ ማስታረቅ ያልቻሉት ሁለቱ እኩያን አንጃዎች (ህወሃት እና ኦህዴድ መራሹ ብልፅግና) ባስከተሉት የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በአያሌ ሽዎች የሚቆጠሩ ነፍሶች (ህይወቶች) በጠፉበትና እንኳንስ ለደሃ ለበለፀገ አገርም በእጅጉ ከባድ የሆነ አጠቃላይ ውድመት በደረሰበት ግዙፍና መሪር ሁኔታ ውስጥ ለአድርባይነት ደዌ እራሱን አሳልፎ የሚሰጠው የአገሬ ሰው በቁጥርም ሆን በአይነት እየጨመረ ቀጥሏል። እንደ ማህበረሰብ ወይም እንደ ትውልድ ከዚህ የከፋ የፖለቲካ አስተሳሰብ ድህነት ፣ የሞራል ዝቅጠት እና የመንፈስ ጉስቁልና የሚኖር አይመስለኝም።
አድርባይነት እራስን ከሁኔታዎችና አጋጣሚዎች ጋር እያስማሙ (እያመቻቹ) ከተቻለ የግል ወይም የቡድን ጥቅምን የማሳደድ እና ካልሆነ ደግሞ መስሎና አስመስሎ የመኖር እጅግ ክፉ ባህሪ ነው ። አድርባይነት ከለየለት የመርህ አልባነትና የሞራል ዝቅጠት የሚመንጭ እጅግ አደገኛ ባህሪ ነው ።
በእኩያን ገዥ ቡድኖች ምክንያት በእድገትና በሥልጣኔ እጅግ ወደ ኋላ በቀረ በእንደ እኛ አይነት ማህበረሰብ ውስጥ ድንቁርና እና ድህነትም የአድርባይነት ምክንያቶች ቢሆኑ ከቶ የሚያስገርም አይሆንም። በየዘመኑ በሥልጣነ መንበሩ ላይ በተፈራረቁ ክፉ አገዛዞች ምክንያት መደበኛም ሆነ ኢመደበኛ የእውቀት እድል የተነፈገው ማህበረሰብ ግዴታን እንጅ መብትን የማወቅ እድልም አይኖረውም። ይህ ደግሞ በተራው የተለየ ጥቅም ባያስገኝለትም የትንንሽ መደለያዎች እና የአድርባይነት ሰለባ ያደርገዋል ። እዚህ ላይ ደግሞ ልክ የሌለው የድህነት ቀንበር ሲጨመርበት ሌላው ቀርቶ ከውጭ መፅዋዕች አገሮችና ድርጅቶች የሚላክለትን ምፅዋዕት ያለ ገዥዎች በጎ ፈቃድ ለማግኘት እንደማይችል ሰምቶ ሳይሆን በተግባር ስለሚያውቀው የአድርባይነት ሰለባ (ለፈጣሪ ከሚሰግደው እኩል ወይም የበለጠ ለገዥዎች ቢሰግድ) ከቶ የሚገርም አይሆንም።
ለሩብ ምእተ ዓመት በህወሃት አሽከርነት ተሠማርተው በድህትነት እና በድንቁርና ያጎሳቆሉትን መከረኛ ህዝብ “ምርጫህ እኛና እኛ ብቻ ካልሆን የምንቸርህን ፍርፋሪ ታጣታለህ” በሚል በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ስም ጨካኝ የፖለቲካ ቁማር ሲቆምሩና ሲያቋምሩ የኖሩት የዛሬዎቹ የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ተረኞች (ኦህዴድ መራሽ የኢህአዴግ አንጃ ቡድኖች) እንደነበሩ ነጋሪ የማያስፈልገው እውነት ነው።
አገርን ምድረ ሲኦል እያደረገ ያለውን አገዛዛቸውን በማስኬድ ላይ የሚገኙት ያንኑ ያደጉበትንና የሰለጠኑበትን መከረኛውን ህዝብ በድህነትና በድንቁርና እየጠረነፉ ምቹ የግፍና የዝርፊያ ሥርዓታቸው ተገዥ በሚያደርገው ጨካኝ የፖለቲካ ስልታቸው ነው። የምርጫ ካርዱን በምርጫ ሳጥናቸው ውስጥ እንዲጨምር በማስደረግ “የታሪካዊ ዴሞክራሲያዊ ተመራጭነታቸውን ያበሰሩን” እና ጥያቄ የሚያነሳን ሁሉ እንደ የህዝብ ጠላትና አመፀኛ የሚያዋክቡትና የሚያሳድዱትም ለዚህ ነው።
እነዚህ እኩያን ገዥ ቡድኖች ከምር በሆነ የነፃነትና የፍትህ ትግል በቃችሁ እስካልተባሉ ድረስ እራሱን ለአድርባይነት አሳልፎ በሰጠውና ለመስጠት በተዘጋጀው የህብረተሰብ ክፍል እየታገዙ ይቀጥሉበታል።
እናም ለዚህ ነው የተሸናፊነት ወዶ ገብነትና የአድርባይነት ባህሪ ማህበረሰባዊ ወይም ትውልዳዊ ወረርሽ ሆኗልና የሚሻለው በመሪሩ ሃቅ ዙሪያ ባሉ ጉዳዮች ላይ መሽከርከርን ትቶ የሚበጀውንና ዘላቂውን መፍትሄ አምጦ መውለድ ነው ብሎ መከራከር ትክክለኛና ተገቢ የሚሆነው። ብቸኛው መፍትሄ ደግሞ የዘመናት መከራና ውርደት ዋነኛ ምክንያት (root cause) የሆነውን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ነጋዴዎች (merchants of ethnic identity politics) ሥርዓት በተባበረና በማይታጠፍ ትግል አስወግዶ ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሸጋጋር ነው። ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ እየከፋና እየከረፋ በመሄድ ላይ ያለውን የአድርባይነት ወረርሽኝ አምርሮ መታገልን ግድ ይላል።
አድርባይነት ከአሉታዊ (ከጎጅ) ሰብአዊ ባህሪያት አንዱ በመሆኑ በፍፁምነት (in absolute terms) ማስወገድ አይቻልም። የሚቻለው በህግ አግባብ እና በሥነ ምግባራዊ ሥርዓት (በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት) ከቁጥጥር ውጭ እንዳይሆንና ማህበረሰባዊ ቀውስ (societal crisis) እንዳያስከትል ማድረግ ነው።
ይህ እውን ይሆን ዘንድ ደግሞ ጉልሁን (ትልቁን) ሚና መጫወት የሚጠበቅበት የተማረው የህብረተሰብ ክፍል ነው። ከዚህ በፊት የተሞከሩት የፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ እንቅስቃሴዎች ሁሉ የውድቀት ሰለባዎች መሆናቸው የሚያሳዝን መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ጉልሁን ሚና የተጫወተው ይኸው የህብረተሰብ ክፍል እንደነበር የሚረሳ አይደለም። አሁንም አስከፊ ከሆነው ተደጋጋሚ ክሽፈት (ውድቀት) ከምር በመማር ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች የድንቁርና እና የድህነት ሰለባ አድርገው የሚገዙትን መከረኛ ህዝብ አንቅቶ፣ አደራጅቶና መርቶ የነፃነትና የፍትህ ሥርዓት ምሥረታን እውን የማድረግ ታሪክ መሥራት ያለበት ይኸው የህብረተሰብ ክፍል ወይም ትውልድ ነው።
ይህንን አሳዛኝ ሁኔታ ደግሞ ሸፍጠኛና ሴረኛ ኦህዴዳዊያንም (ብልፅግናዊያንም) ሆኑ ከቤተ መንግሥት ፖለቲካ ተባረርኩ በሚል ያዙኝ ልቀቁኝ የሚለው ህወሃትም አሳምረው ያውቁታል ። የሥልጣን ሽኩቻቸው የፈጠረውን የእርስ በርስ መተራረድ (ጦርነት) እንደ የተቀደሰ ጦርነት አድርገው ደንቆሮና ጨካኝ ፕሮፓጋንዳቸውን ሲተፉበት (ሲያስታውኩበት) “እናንተ እነማን ናችሁ? ወንድም ከወንድሙ ጋር እና እህት ከህቷ ጋር ለሚፈፅሙት እጅግ ዘግናኝ መገዳደል ዋነኛ ምክንያቶች እነማን ሆኑና ነው አሁን ደርሳችሁ የሰላም አቃቤዎች (ጠበቃዎች) በመምሰል በንፁሃ ደም የምትቆምሩት? የእናንተን የመከራና የውርደት ቀንበር መሸከሙ ሳያንሰን ለምን ታጋድሉናላችሁ? አይበቃችሁም እንዴ?” ብሎ በመጠየቅ መሪሩን ሃቅ የሚጋፈጥ የዴሞክራሲ አርበኛ ምሁር የህብረተሰብ ክፍል ብርቅየ በሆነበት እና አድርባይ ምሁር እንድ አሜባ በሚራባበት የፖለቲካ አውድ ውስጥ ዴሞክራሲያዊት አገርን ከመፈለግ የከፋ የፖለቲካና የሞራል ዝቅጠት ከቶ የለም።
እናም ለዚህ ነው “ጦርነታችሁ የሥልጣን ሽሚያችሁ ውጤት እንጅ ሁለት የተለያየ ዓላማ ያላቸው የአንድ አገር ሃይሎች ወይም የወራሪና የተወራሪ ጉዳይ አይደለምና ይህኑ አውቃችሁ በአስቸኳይ ሁሉን አቀፍ ወደ ሆነ የመፍትሄ ጠረጴዛ ቅረቡ ፤ ካልፈለጋችሁ ግን ከእርስ በርስ እልቂት የፖለቲካ አውድ ገለል በሉ” የሚል ግልፅና ቀጥተኛ የዴሞክራሲ አርበኝነት ትግል ነገ ሳይሆን ዛሬኑ የግድ መሆን ያለበት።
የትክክለኛ ምሁርነት ትርጉምና ጠቀሜታ ውድቀትን በፍጥነት ተገንዝቦና አምኖ ተቀብሎ ተገቢውን እርምት ማድረግ ሆኖ ሳለ በእኛ አገር እየሆነ ያለው ግን የካፈርኩ አይመልሰኝ አድርባይነትን የሙጥኝ የማለትንና የመለማመድን እጅግ አሳፋሪ ባህሪ ነው።
ቀደምት ትውልዶች (አያቶቹና ቅድመ አያቶቹ) ሠርተው ያስረከቡትን ድንቅ ታሪክ በኩራት ተቀብሎ በማስከበርና ተፈፀመ የሚለውን ስህተት ደግሞ በአግባቡ እየለየና እንዳይደገም እያደረገ የእራሱን ዘመን (21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን) የዴሞክራሲ አርበኝነት ታሪክ ከማስመዝገብ ይልቅ በየጎሳውና በየቋንቋው እየተቧደነ ተሠርቶ የተረከበውን በጎ ነገር ሁሉ ድምጥማጡን ካላጠፋሁ እንቅልፍ አይወስደኝም የሚልና የእራሱን እጣ ፈንታ ጨክኖ የሚያበላሽ ትውልድ የአድርባይነት ደዌ ተሸካሚና አስተላላፊ ቢሆን ከቶ የሚገርም አይሆንም ።
አድርባይነት በዋናነት የሚከተሉት አደገኛ ማለትም ፦ ሀ) በመንበረ ሥልጣን ላይ ከሚፈራረቁ ሴረኛና ግፈኛ ገዥዎች ጋር በመተሻሸት ከተቻለ ልክ የሌለው የግል ወይም የቡድን ፍላጎትንና ጥቅምን የማጋበስ ለ) ይህ ካልሆነ ደግሞ ከህዝብ ጉሮሮ እየተነጠቀ የሚሰጠውን ፍርፋሪ የማስጠበቅና መስሎና አስመስሎ የመኖር ሐ) ለዚህ “ችሮታ” ውለታ ይሆንለት ዘንድ በአደንቁሮ ገዥዎች ምክንያት የድንቁርና (የመሠረታዊ እውቀት እጦት) ሰለባ በመሆኑ የሚነገረው በጎ ቃል ሁሉ እውነት የሚመስለውን መከረኛ ህዝብ በርካሽ ፕሮፓጋንዳ (propaganda of cheap popularity) የማታለል ሐ) በሴረኛ ገዥ ቡድኖች እና በህዝብ መካከል ያለው ግንኙነት የተካረረ ሲመስል ደግሞ በመካከል ሆኖ የመደነስና አሸናፊ ወደ ሚሆነው የመለጠፍ ገፅታዎች (ባህሪያት) አሉት።
ለዚህ ነው እንደ እኛ አይነት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ ሥርዓት ለውጥ የግድ የሚላቸው ንቃተ ህሊና ፣ ቅንነት፣ መቻቻል፣ የጋራ መርህ ፣ የጋራ ራዕይ፣ የጋራ ዓላማና ግብ እና ድርጅታዊ አቅምና አቋም በእጅጉ ወደ ኋላ የቀረባቸው ማህበረሰቦች የግፈኛ ገዥዎችና የአድርባይ ሸሪኮቻቸው ሰለባዎች ቢሆኑ ያሳዝን እንደሆነ እንጅ ከቶ የሚገርም የማይሆነው።
ይህንን ክፉ ደዌ ቢቻል ትርጉም ባለው ሁኔታ ለመግታት ቢያንስ ግን አደብ ለማስገዛት የሚያስችል ሚና መጫወት የሚጠበቅበት በዓለማዊው ወይም በመንፈሳዊው ወይም በሁለቱም የትምህርት አውዶች ምሁር ነኝ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል እራሱ የለየለት አድርባይነት ሰለባ የመሆኑን መሪር እውነታ ለመከላከል ሰንካላ ምክንያት ከመደርደር ተገቢውንና ወቅታዊውን የእርምት እርምጃ መውሰድ ነው የሚሻለው።
ለዘመናት ከመጣንበትና አሁንም በአስከፊ መልኩ ከቀጠለው የአድርባይነት ደዌ ለመላቀቅ ዛሬውኑ ከየእራሳችን ጋር እና በመካከላችን ቃል ተገባብተን መሬት ላይ ወርዶ የሚዳሰስና የሚጨበጥ ሥራ ለመሥራት ካልቻልን ሌላ የሦስት አሥርተ ዓመታት ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ የሆነ የመከራና የውርደት ዘመንን እንደምናስቆጥር ለማወቅ የተለየ እውቀትን ወይም ነብይነትን አይጠይቅም።
ለዚህ ደግሞ መወሰድ ካለባቸው እርምጃዎች ቀዳሚው እርምጃ የአድርባዮች ምሽግ በመሆን የህዝብን መከራና ውርደት እያራዘመ ያለውን የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማር ሥርዓትን ወደ መቃብር ሸኝቶ ዜጎቿ በእኩልነትና በነፃነት የሚኖሩባት ፌደራላዊት ዴሞክራሲያዊት አገርን እውን ማድረግ ነው። ከዚህ ያነሰ ትግል የእኩያን ገዥዎች ሥጋ ለባሽ አሻንጉሊቶች ሆነን ለመቀጠል ካልሆነ በስተቀር ፈፅሞ የትም አያደርሰንም ።
ስለ እውነት ከተነጋገርን ሥር የሰደደ የአድርባይነት ፖለቲካ ደዌን ከምር በመፀየፍና በመዋጋት የመከራውንና የውርደቱን ሥርዓት አቅም ለማሳጣት ያለመቻላችን ውድቀት ይኸውና ከእራሳችን ሁለንተናዊ ጉስቁልና አልፎ የዓለም መሳለቂያ አድርጎናል።
አንድ በሥራ አጋጣሚ የማውቀው አሜሪካዊ ከሚዲያ ስለ ሰማው የመገዳደል ፖለቲካችን ጠየቀኝና “አዎ ከፖለቲከኞች የሥልጣን ሽኩቻ የሚነሳ አሳሳቢ ችግር አለ” የሚል አጭር መልስ ስመልስለት የርሃብ ቸነፈሩስ (how about the famine?) የሚል ጥያቄ አስከተለ። ይህን ሲል በአሁኑ የሰላም እጦት ምክንያት የተከሰተውን ርሃብ ብቻ ማለቱ ሳይሆን ከ1960ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ ለእለት ምግብ ችጋር (famine) ትርጉም በመዝገበ ቃላት በምሳሌነት ስለሚጠቀሰውና በሴረኛና ጨካኝ ገዥዎች ምክንያት አሁን ድረስ መውጫ ስላላገኘንለት አስቃያሚ (አንገት የሚያስደፋ) የታሪካችን አካል ማንሳቱ ነበር። የተለመደውን የታላቅና የባለታሪክ አገር ሰው መሆኔን መናገሩ ብዙም እንደማያስኬድ (“በዚህ ዘመን ከርሃብ በላይ እርስ በእርስ መገዳደላችሁ ለምን አልኩ እንጅ የአገርነት ታሪካችሁን ጥያቄ ውስጥ አላስገባሁም”) ቢለኝ አጥጋቢ ምላሽ ስላልነበረኝ ህሊናየን እያመመው አደናቁሬ አለፍኩት።
ታዲያ ይህ አይነት የአንድ ሰው ጥያቄና ግንዛቤ ምን አንገት ያስደፋል? ፖለቲካ ወለድ መገዳደልስ በእኛ ተጀመሯል ወይ? የሚልና በዋናነት ከጨካኝ ገዥዎችና ከለየላቸው የአድርባይነት ልክፍተኛች ወይንም ደግሞ ከድንቁርና የሚነሳ ጥያቄ ሊኖር እንደሚችል እገምታለሁ።
አዎ! ርሃብ (ችጋር) እና ፖለቲካ ወለድ መገዳደል የእኛ ብቻ የታሪክ ፈተና አይደለም። ይሁን እንጅ ሀ) ከእውቁ የአገርነትና ሌላም አኩሪ ታሪካችን አንፃር ለ) ለግማሽ ምእተ ዓመት ከመጣንበት ደጋግሞ የመውደቅ ክፉ አዙሪት መማር ካለመቻል አንፃር ሐ) ለሩብ ምእተ ዓመት የጎሳ አጥንት ስሌት ፖለቲካ ቁማርተኞችን የመከራ ቀንበር ተሸክመን ከኖርንበት መሪር እውነታ አንፃር መ) በተለይም ከዛሬ አራት ዓመት በፊት ያገኘነውን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ወርቃማ እድል (አጋጣሚ) ከማበላሸታችን አንፃር ሠ) እናት ምድር ንፁሃን ልጆቿ ከእለት ጉርስ ተመፅዋችነት መውጣት አለመቻላቸው አልበቃ ብሎ በደማቸው ስትጨቀይ እና በሰቆቃ እንባቸው ስትጥለቀለቅ ትርጉም ያለው የፖለቲካ ሥራ ለመሥራት ካለመቻላችን አሳፋሪ ሁኔታ አንፃር እራሳችንን ስንገመግም “በእኛ አልተጀመረም” የሚለው አጠቃላይና የተለመደ መልስ (መከራከሪያ) ጨርሶ ውሃ አይቋጥርም።
ይህንን አይነት ሂሳዊ አስተያየት ከምርና ከቅንነት ተቀብሎ የሚበጀውን ለማድረግ የሚያስችል የፖለቲካ ባህል በእጅጉ እንደሚቸግረን እረዳለሁ። በእውን ዴሞክራሲያዊት የሆነቸና ከተመፅዋችነት ነፃ የወጣች ኢትዮጵያን የምንሻ ከሆነ ሃቁን ከመጋፈጥ ውጭ ሌላ የተሻለ አማራጭ ጨርሶ የለም። ሊኖርም አይገባም።
ሰንካላ ሰበብ እየደረደርን እራሳችንን መሸንገሉን (ማታለሉን) ትተን ስለ እውነት ከተነጋገርን አድርባይነት የአገራችን አስከፊ ማህበረሰባዊና ትውላዳዊ ወረርሽኝ (severe societal and generational pandemic) እየሆነ የመምጣቱን መሪር እውነት ከቶ የምንሸሸው ጉዳይ አይደለም። የሚሻለው በገዥዎች ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን በተጠቂው ማህበረሰብ (በተለይ በአድርባዩ የህብረተሰብ ክፍል) ድክመትና ውድቀት ምክንያት ጭምር እየከፋ በመሄድ ላይ የሚገኘውን የመከራና የውርደት መሪር ሃቅ አምኖ በመቀበል ተገቢውን የጋራ መፍትሄ ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ አምጦ መውለድ ነው።
I. ለመሆኑ በለየለት የአድርባይነት ክፉ ደዌ ያልተበከለው የትኛው የመንግሥት አካል ነው?
2) በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ መጫወቻ ካርድ እና የአድርባይነት ልክፍተኞች ሰለባ ያልሆነው ከሚከተሉት የትኛው ነው?
የምርጫ ቦርድ ተብየው? የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተብየው? እንባ ጠባቂ ተብየው? የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚሉት? የሰላምና እርቅ ኮሚሽን ተብየው? የማንነትና የወሰን ጉዳዮች ኮሚሽን የሚባለው?
ከላይ የጠቀስኩትን የፕረዝደንቷን ጽ/ቤትን ጨምሮ የእነዚህን አካላት ከላይኞቹ የተለዩ የሚያስመስላቸው “ከፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ነፃ የሆኑ ሰዎች የሚመራቸው ናቸው” የሚለው የለየለት የማታለያ ታፔላ (አዋጅ) ብቻ ነው። ስለ እውነት ከተነጋገርን እንዲያውም የአደገኛ አድርባይነት ቫይረስ (ደዌ) ተሸካሚዎች እነዚህኞቹ ናቸው። የመጀመሪያዎቹ አቋምና ቁመና ግልፅ ስለሆነ ከምር ለመታገል ዝግጁ ለሆነ የነፃነትና የፍትህ ታጋይ የአገሬ ሰው ብዙም የሚያደናግሩ አይደለምና።
II. የተቃውሞው ፖለቲካ ጎራ ፖለቲከኛ ነኝ የሚለውስ?
2) በአማራ ማህበረሰብ መከራና ውርደት ስም በመማልና በመገዘት ሲያልሙት የነበሩትን የተከበሩ የፓርላማ አባልነት እና ሌላም የሥልጣን ወንበር በእጃቸው ሲያስገቡ “ለአገር ህልውና እና ለሰላም ስንል ከለውጡ ሐዋርያት ጋር ተባብረን እየሰራን ስለሆነ አትረብሹን” በሚል ቁርጡን የነገሩንን የአብን (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ተብየ) ፖለቲከኞችን ከምር ልብ ለሚል ሰው የሽንፈት ወዶ ገብነትንና የአድርባይነትን አስከፊነት ለመረዳት አይቸገርም። ይህ አይነት ክፉ የፖለቲካ ደዌ በተለይ አመራር ነን በሚሉ ግለሰቦች ላይ ደርሶ ጉብ ያለ ሳይሆን ከመጀመሪያውም (ስብስቡ ሲወለድም) አብሮ የተወለደ መሆኑን ለመረዳት የኢትዮጵያን ፖለቲካ በጥሞና ለተከታተለና ለሚከታተል ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ የአገሬ ሰው በፍፁም ከባድ አይደለም።
3) እንደ ኢዜማ (ማህበራዊ ፍትህ ለዜጎች) ያሉት ተቀዋሚ (ተፎካካሪ ተብየ) ድርጅቶችን እጅግ የገነገነ (ሥር የሰደደ) የአድርባይነት ደዌን ከወዳጃቸው ብልፅግና እና ከመሰሎቹ በስተቀር ለማስተባል የሚቃጣው ባለ ሚዛናዊ ህሊና የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።
4) እንኳንስ በእንደኛ አይነቱ እጅግ እልህ አስጨራሽ ትግል በሚጠይቅ የፖለቲካ አውድ በአንፃራዊነት በተሻለ ደረጃ በሚገኝ የፖለቲካ ሁኔታ ውስጥም በሥራ ላይ ሊሳሳት እንደሚችል ማነኛውም ሰው ስህተት ሊሠራ እንደሚችል እንደተጠበቀ ሆኖ እስክንድር ነጋን ያህል ፅዕኑ ኢትዮጵያዊ መውጫ መግቢያ አሳጥቶ ያልፈለገውን ውሳኔ እንዲወሰን ያደረገው በዋናነት የአብይ አህመድ አገዛዝ ቢሆንም እራሱ ፓርቲው (ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲም) የአድርባይነት ደዌ አይነካካውም ብሎ ማመን የሚቻል አይመስለኝም።
5) ሌሎች አገር አቀፍ ነን የሚሉትስ ቢሆን ከግል ፍላጉትና ከአድርባይነት ደዌ በሚመነጭ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር በተለይ በዚህ አገር እጅግ ከባድ ፈተና ላይ በወደቀችበት በአብይ አህመድ አገዛዝ ወቅት ተፈላልገውና ተመካክረው ትግሉን በሚመጥን ቁመና እና አቋም ላይ ለመገኘት ለምንና እንዴት ተሳናቸው? እነዚህም ኋላ ቀር ከሆነውና ከአገር ፍላጎትና ጥቅም ይልቅ በግልና በቡድን ፍላጎትና ጥቅም ከመጓተት የፖለቲካ ባህል ሰለባነት ነፃ ባለመሆናቸው ከአድርባይነት ቫይረስ ተሸካሚነትም ነፃ ሊሆኑ አይችሉምና ከእራሳቸው ጋር በግልፅ መነጋገር ይኖርባቸዋል።
III. የሙያና የሠራተኛ ማህበራትስ?
1) በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ ቀዳሚ ሚና የነበራቸው እንደ የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር እና የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር የመሰሉ አካላት አገር ለንፁሃን ልጆቿ ምድረ ሲኦል ስትሆን ህልውናቸው ያከተመ እስኪመስል ድረስ የመጥፋታቸው ምክንያት እጅግ በለየላቸው አድርባዮችና ምናልባትም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሴረኛው ገዥ ፓርቲ ካድሬዎች የተጠረነፉ በመሆናቸው ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ሌላ አሳማኝ ምክንያት አይኖርም።
2) ከህዝብ ወጥቶ ወደ ህዝብ መልሶ በሚያንፀባርቀው ሙያዊ ሥራ ሁለንተናዊ የህይወት ነፀብራቅ እንደሆነ የሚነገርለት የኪነ ጥበቡ ዘርፍም በቦሌም ሆነ በባሌ (by hook or crook) መንበረ ሥልጣኑን ከሚቆጣጠረው ገዥ ቡድን ጋር እየተገለባበጡ እራሳቸውን ብቻ ሳይሆን ህዝብን ጨምረው በሚያዋርዱ ወዶ ገቦችና አድርባዮች የተበከለ ነው ።
ይህ ክፉ የአድርባይነት ደዌ ከአገር ቤት እስከ ውጭ አገር በሙያውም ሆነ በሥራ ተሞክሮ የበለፀጉ እንደሆኑ ሲነገርላቸው (ሲመሰክርላቸው) የነበሩትን ጨምሮ ያልለከፈው የኪነ ጥበብ ሰው ቁጥር እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። ይህ በእጅጉ የማያሳስበን ከሆነ ኪነ ጥበብን ከተራ ጊዜ ማሳለፊያነት እና የኑሮ ገቢ ማስገኛነት ያለፈ ዋጋ (value) እየሰጠነው አይደለም ማለት ነው።
ሁሉን ነገር የሚያውቅ የሚያስመስል የፖለቲካ ሰብእና የተጠናወተው አብይ አህመድ በአዳራሽ ውስጥ አጉሮ እንደማነኛውም አንብቦና አይቶ መገንዘብ እንደሚችል ሰው ስለ ኪነ ጥበብ ከየመጽሐፉ የቃረመውንና ከየመድረኩ የለቃቀመውን በሰላ አንደበቱ ሲደሰኩርለት ለምንና እንዴት ብሎ ሳይጠይቅ የሙያው ባለሙያነቱን ረስቶ (እራሱን አዋርዶ) እጁ እስኪላጥ የሚያጨበጭብ የኪነ ባለሙያ ለሴረኛና ግፈኛ ገዥ ቡድኖች በአድርባይነት እራሱን አሳልፎ ለመስጠት ዓይኑን አያሽም ።
3) በነገራችን ላይ ለመሆኑ በአሁኑ ወቅት በጎሳ አጥንት ስሌት ላይ የተመሠረተ እንጅ በኢትዮጵያ ስም የሚመሠረትና በኢትዮጵያዊነት ለኢትዮጵያዊነት የቆመ ማህበር (አካል) አለ ወይ? የሚለውን ፈታኝ ጥያቄ በአወንታዊነት ለመመለስ በማንችልበት መሪር እውነታ ውስጥ ነው የምንገኘውና በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል።።
IV. የአክቲቪስትነቱ ነገርስ?
አክቲቪዝም ቀጥተኛ ድጋፍን በማሰበሰብ ፣ የተሰባሰበውን በማጠናከር ፣ መላ ህዝብን በማሳወቅ (በማንቃት) እና በፅኑ ዓላማና መርህ ላይ በመቆም የተወሰነ ጉዳይን ለማስፈፀም የሚደረግ እጅግ እልህ አስጨራሽ ሥራ ነው። ወደ ፖለቲካው ጉዳይ ስንመጣ ትክክለኛው አክቲቪዝም በተበላሸ ሥርዓት ውስጥ የሚደረግ የማታለያ ተሃድሶንና የገዥ ግለሰቦችን በተረኝነት መቀያየር እንደ ስኬት እየቆጠሩ የስኬት ድል የማወጅ ጉዳይ ሳይሆን መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ እስኪመጣ ድረስ ፀንቶ የመቆም ትልቅ ሥራ ነው ። ከዚህ አንፃር እውን አክቲቪዝም በትክክለኛ ትርጉሙ የአገራችን የፖለቲካ ታሪክ አካል ነበር ወይ? አሁንስ ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ ብዙ የሚያወያይ ነው የሚሆነው ።
ይህም ሆኖ በተለይ በዘመነ ህወሃት/ኢህአዴግ በወጉ በተደራጀ መልኩ ባይሆንም የአክቲቪስትዝም ይዘት ያላቸው እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ አይካድም። አሳዛኙ ጉዳይ የተሟላም ባይሆን አበረታች የክቲቪስትነት ሥራ ይሠሩ የነበሩና የህዝብ ቀልብና ደጋፍ ተችሯቸው የነበሩ አክቲቪስቶች ኢህአዴግን እራሱ ኢህአዴግ (ያውም ይበልጥ አስከፊ በሆነ ሁኔታ) የተካበትን የፖለቲካ ቁማር እንደ ተልእኳቸው የድል ብሥራት በመቁጠር በሴረኛና ሸፍጠኛ ገዥ ቡድኖች እግር ሥር ሲወድቁና አገር ቤት እየተመላለሱ በፖለቲካ አመንዛራነት አረንቋ ውስጥ ሲዘፈቁ መታዘባችን ነው። ታዲያ ይህ እጅግ አስቀያሚ የአድርባይነት ልክፍት (ደዌ ) ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
V. የሃይማኖት ተቋማትስ?
1) የሃይማኖታዊ እምነት ጉዳይ ከሌሎች ጉዳዮች በተለየ ስስ የሆነ ስሜታዊነት ያለው በመሆኑ ይህ ሂሳዊ አስተያየቴ ለብዙ አማኝ ወገኖቼ ስሜት እንደሚያስቸግር በሚገባ እረዳለሁ። ይህ አይነቱ ስሜት የሚመነጨው ለሃይማኖታዊ እምነት ተቋማትና ለመሪዎቻቸው ተገቢው ጥንቃቄና ከበሬታ ላይሰጥ ይችላል ከሚል ቅንና ገንቢ እሳቤ (እምነት) ከሆነ ተገቢነቱ አያጠያይቅም። ከሚታይ (ከተጨባጭ) እውነታ የሚነሳን ሂሳዊ ትችት ከመፍራት ወይም ከመሸሽ ወይም የሃይማኖት መሪን መተቸት እንደ ኅጢአት በሚቆጥር ደምሳሳ አአስተሳሰብ ከሆነ ግን ከገሃዱ ዓለም አልፎ የእውነተኛው አምላክ ፍላጎትም አይደለምና ትክክል አይሆንም።
2) እናም በእውነተኛው አምላክ ስም ስለ እውነት ከተነጋገርን የስፋቱና የአስከፊነቱ ደረጃ ይለያይ እንደሆነ እንጅ በሩብ ምእተ ዓመቱ ህወሃት መራሽ የኢህአዴግ አገዛዝ ያስተዋልነው እና በተለይ ደግሞ በአራት ዓመቱ ኦህዴድ መራሽ ኢህአዴግ/ብልፅግና አገዛዝ እያየነው ያለነው የሃይማኖት ተቋማትና የመሪዎቻቸው ተልእኳቸውን የመወጣት ውደቀት ለማስተባበል የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት የሚኖር አይመስለኝም።
5) በአጠቃላይ ለሦስት አሥርተ ዓመታትና በተለይ ደግሞ አገር ለአያሌ ንፁሃን ልጆቿ ታይቶና ተሰምቶ በማይታወቅ ሁኔታ ምድረ ሲኦል ከሆነችባቸው የአራት ዓመታት የኦህዴድ/ብልፅግና አገዛዝ አንፃር የትኛውም የሃይማኖት ተቋም (የሃይማኖቶች ጉባኤ የሚባለውን ጨምሮ) ተወጣሁት የሚለው ሃላፊነትና ተልእኮ ጨርሶ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ይህ እንደሚሆን ተስፋ እያደረግሁ አበቃሁ!