አቶ ስንታየሁ ቸኮል ይፈቱ!
የህሊና እስረኞች ይፈቱ!
አቶ ስንታየሁ ቸኮል የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ ሲሆኑ መንግስት እጅግ በሚያሳፍር ተንኮልና ሸፍጥ በበዛበት ሁኔታ አስሮ እያሰቃያቸው ይገኛል። እኒህ የባልደራስ ከፍተኛ አመራር የታሰሩት ባልደራስን ለማጥቃት በተደረገ ሴራ እንደሆነ መቼስ ለብዙ ኢትዮጵያውያን ግልጽ ነው።
አቶ ስንታየሁ ላይ የሚደረገውን ሴራ ስናጤን የሃገራችን የፍትህ ስርዐት ከመቼውም ጊዜ በላይ አሳፋሪ ደረጃ ላይ እንዳለ እናያለን። አቶ ስንታየሁ በመጀመሪያ ባህርዳር ከተማ ለስራ ጉዳይ ሄደው በዚያው ከታሰሩ በሁዋላ እዚያው ባህርዳር ፍርድ ቤት ቀርበው በሰላሳ ሽህ ብር ዋስትና እንዲፈቱ ስለተወሰነ ድርጅታችን ለእኚህ መሪ ዋስትና የሚሆን ገንዘብ ከፍሎ መፈታታቸውን ሲጠብቅ ፌደራል ፖሊስ አምጥቶ አዲስ አበባ ላይ እንደገና አሰራቸው። የዋስ መብታቸው ተከብሮ ይፈታሉ ሲባል እንደገና ፈደራል ፖሊስ ደግሞ ፍርድ ቤት ክስ መስርቶ ሲያመላልሳቸው ከቆየ በሁዋላ የአራዳ ፍርድ ቤት አንድ መቶ ሽህ ብር ከፍለው እንዲፈቱ ወሰነ ተባለ። በዚሁ መሰረት ድርጅታችን መቶ ሽህ ብሩን ከፍሎ የአቶ ስንታየሁን መፈታት ሲጠብቅ መንግስት እንደገና ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አዛውሮ አስራቸውና እንደገና ፍርድ ቤት ቀረቡ። ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ የዋስ ብር ከፍለው ሳይፈቱ የቀሩት አቶ ስንታየሁ እንደገና በአዲስ አበባ ፖሊስ ክስ ተመስርቶባቸው በአስር ሽህ ብር እንዲፈቱ ተወሰነ። ይሁን እንጂ ፖሊስ ይግባኝ በማለቱ እስክ ሰበር ሰሚ ችሎት ድርስ ጉዳዩ ደረሰ። ሰበር ሰሚ ችሎቱም አስር ሽህ ብር ከፍለው እንዲወጡ ወሰነ። የሃገሪቱ የመጨረሻው ፍርድ ቤት አቶ ስንታየሁ በዋስ እንዲወጡ ቢወስንም ፖሊስ አልፈታም ብሎ በዚህ ሰአት ካዛንችስ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እየተሰቃዩ ይገኛሉ። መንግስት አቶ ስንታየሁን አስሮ በየጊዜው ለዋስ የሚሆን ገንዘብ አየጠየቀ እስካሁን አንድ መቶ አርባ ሽህ (140,000) ብር ዘርፏል።ፖሊስ በአቶ ስንታየሁ ላይ ካቀረባቸው ክሶች አንዳንዶቹ፦ ሰዎችን አስተባብረህ ከንቲባ አዳነች አበቤን አሰድበሀል፣ በአድዋ በአል ላይ ባለስልጣን አሰድበሀል፣ በካራማራ የድል በአል ላይ ህገ ወጥ ነበርክ ወዘተ…. የሚሉ ለማመን የሚከብዱ እንቶፈንቶ ነገሮች ናቸው። ይህ በግልጽ የሚያሳየው ነገር እስራቱ ፖለቲካዊ መሆኑን ነው።
መንግስት ይህንን የሚያደርገው በአንድ በኩል አቶ ስንታየሁን በማሰር የድርጅቱን ስራ ለማስተጓጎል የተሸረበ ሴራ ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በየጊዜው በዋስትና ስም ድርጅታችንን በኢኮኖሚ መጉዳትና ማዳከም ነው። ባልደራስ ከሃገር ወዳድ አባላቶቹ የሚያገኘውን የገንዘብ ድጋፍ ለድርጅት ስራ እንዳያውል መንግስት በአጅ አዙር እየዘረፈ ይገኛል። ይህ ተቋማዊ ዘረፋ በፓርቲያችን ላይ ሲፈጸምና የፓርቲያችን አባላትና መሪዎች ነጻነታቸው ተገፎ ሲታሰሩ ዝም ብለን አናይም። መንግስት በባልደራስ ላይ የሚያደርገውን ግፍና ማዋከብ ባስቸኳይ እንዲያቆም እንጠይቃለን፤ በመሆኑም እንዲህ አይነቱን አሳፋሪ ተግባር በመላው አለም የምትገኙ የፓርቲያችን ደጋፊዎች፣ አባላትና መላው ኢትዮጵያውያን፣ የሰበአዊ መብት ተሟጋቾችና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊያወግዘው ይገባል።
የባልደራስ ድጋፍ በሰሜን አሜሪካ አቶ ስንታየሁ ቸኮል ባስቸኳይ እንዲፈቱ፣ የድርጅታችን አባል የሆነው ወጣት ቢንያም እንዲፈታ፣ መንግስት ከእንዲህ አይነቱ ተቋማዊ አሻጥር እንዲታቀብ የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ጀምሯል። በዚህ ዘመቻ ላይ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁሉ እንዲሳተፉ በአክብሮት ጥሪ እናስተላልፋለን። ሃገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆች መብት ተከብሮ እስክናይ ድረስ፣ የነጻነት አየር ህዝባችን ሲተነፍስ እስክናይ ድረስ የትግል ክንዳችን አይዝልም፣ አንታክትም።
ድል ለዴሞክራሲ
የባልደራስ ድጋፍ በሰሜን አሜሪካ
#ኢትዮጵያ