ቅራኔን መፍታት በብልሃት፣ (ከጆቢር ሔይኢ)

በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ከርሮ ያለው የብሔርና የሃይማኖት ቅራኔ ነው።ብሔር የኅብረተሰብን የእድገት ደረጃ ተከትሎ የተከሰተ፣በቋንቋ፣በባህል፣በልማድ፣በታሪክ የተሳሰረ፣ በባህርይ የሚንጸባርቅ ሥነልቦናዊ  ዘይቤ ያዳበረ፣በአንድ አርማና አላማ ሥር የተሰለፈ፣ጸንቶና ረግቶ በአንድ አገር፣ወይም አካባቢ የሚኖር ሕዝብ ነው። ብሔረሰብ የሚባለው ደግሞ በተለያየ ምክንያት፣ ከብሔሩ  ተለይቶ በሌላ አካባቢ የሚኖር ማኅበረሰብ፣ ወይም ወደ ብሔር ዕድገት ደረጃ ያልደረሰ ነገድ ማለት ነው። ሕዝብ የሚባለው የሰዎች ስብስብ ሁኖ ፣ የተለያየ ቋንቋ ባህል እምነትና እኔነት ያላቸው፣ ከተሜንም የሚያጠቃልል ነው።

የብሔሮች የራስን እድል በራስ የመውሰንና፣በቋንቋ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር የጸደቀ፣ብዙዎች ሕዝቦች፣ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነፃ የወጡበት ነው። በእኛ አገር እንኳን ኤርትራ ከኢጣሊያን፣ ጁቢቲ ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነፃ የወጡት በዚሁ መብት ነበር። የኤርትራ ሕዝብ ግን፣ በብሄሩ፣በቋንቋው፣ በእምነቱና በታሪኩ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በነበረው ቁርኝት የተነሳ፣በፌድሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር መኖርን ነበር የመረጠው።በወቅቱ ሥልጣን ይዞ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ይህን የኤርትራ ሕዝብ ምርጫ ማክበር ሲገባው፣ ክብሩን የሚቀንስበት መስሎት፣የኤርትራንም ሕዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ጨፍልቆ በብሔርና በቋንቋ ጭቆና ሊያስተዳድረው ወሰነ።ይህም ውሳኔ የሰላሳ አመት ጦርነትና የርስ በርስ ጭፍጨፋን አስከተለ።

ይህም ጦርነትና ጭፍጨፋ የኢትዮጵያዊያንንም ዓይን ከፈተ።የመጫና ቱለማ መረዳጃ ማኅበር ተመሥርቶ፣ መንግሥት በኦሮሚያ አካባቢ የፊደል ሠራዊትና የጤና አገልግሎት እንዳይስፋፋ በምስጢር ያሳለፈውን መመሪያ አጋለጠ።በዚህም አድማ የተቆጣው ዋቆ ጉቱ ኦሮሞን ነፃ ለማውጣት የባሌ ሕዝብን ለአመጽ አነሳሳ።ትግሉም በተለይ የሱማሊንና የአረብ አገሮችን ደጋፍ አገኘ።ይህም በአፍሪካ አንድነት ድርጅት በኩል በንጉሡ ላይ ተንጸባርቆ ፣ጃንሆይ ወዳጃቸው የነበሩትን እስራኤልንና አሜሪካንን ከድተው፣ከእሥራኤል ጋር የነበራቸውን የዲፖሎማሲ ግንኙነት አቋረጡ፣ የአሜሪካንንም የጦር ሰፈር ከአስማራ አስወጡ። ከዚህም የተነሳ ንጉሱ የምዕራባዊያን ድጋፍና ዕርዳታ አጥተው እጃቸውን ለወታደራዊ ደርግ ለመስጠት ተገደዱ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጆሮ ያለው ይሰማል! አይን ያለው ይመለከታል! ጆሮ ኖሮት የማይሰማ፣ ዓይን ኖሮት የማያደምጥስ? - ከድምፃችን ይሰማ

1ወታደራዊ መንግሥትም በትረ ሥልጣን እንደተረከበ፣ ጄንራል አማን አምዶምን ወደ አስመራ ልኮ፣ከሸብያና ጀብሓ ጋር ድርድር አካሄደ።ድርድሩ የብሔርና የቋንቋ እኩልነትን የሚመለከት ስለ ነበር፣ ደርጉ በእኛ ዘመነ መንግሥት፣ የአማርኛ ቋንቋ የግዴታ ትምህርት መሆኑ አይቀርም በማለት ድርድሩን ወድቅ አደረገ።ከዚህም ውሳኔ የተነሳ ሕዝባችን ለአስራ ሰባት አመት ጦርነት ተዳረገ።በመጨረሻም ኤርትራንም የባህር በሩንም አጣ። ከዚያም በኋላም ቢሆን ጦርነቱ

ቀጥሏል።ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የብዙዎች ደም በማፋሰስ ላይ ይገኛል። በዚህ ረገድ ትናንት ኢሕአዴግን ለመንግሥት ሥልጣን ያበቃውም ሆነ፣ አሁን ላለው ሁኔታ መከሰት መንሴ የሆነው የሕዝባችን መስዋዕትነት መሆኑ ገልጽ ነው። ስለሆነም ከግራዉም ሆነ ከቀኙ ያሉት ዛሬ የሚወስዱት እያንዳንዱ እርምጃ፣ነገ ሕዝባችንን ሌላ ተጨማሪ ደም እንዳያፋስስ፣ከትውልድና ከታሪክ ተጠያቅነትም ለመዳን ደግመውና ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል።

ሕገ መንግሥትን በሚመለከት፣ በረቂቁ ሁሉም፣ ብሔር ብሔረሰቦች ተሳትፈዉበታል። በድምጻቸውም በማጽደቅ፣ያራሳቸውን ዕድል በራሳቸው በመወሰን መብታቸው ተጠቅመዋል። ስለሆነም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉ በሚገኙበት ክልል፣ዞንና ወረዳ፣ በመረጡት ቋንቋ፣ ራስቸውን በራስ የማስተዳደር መብታቸው ሊከበር ይገባል።ይህ መብት ግን ፣በክልል ባለስጣናትና በፓርቲ አመራር የተነሳ፣ዛሬም በብዙዎች አካባቢ እየተሸራረፈ፣ የአስተዳደር በደልና የፍርድ መጓደል እየተፈጸመ ይገኛል።

ስለሆነም ይኸው ተገቢውን አጽንኦት አግኝቶ በክልል መስተዳድሮች ሥር በዞን፣ በወረዳም ሆነ በአሐድ ደረጃ የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ሁሉ በቋንቋቸው ራስን በራስ በማስተዳደር፣ እምነታቸውንና ባህላቸውን በመንከባከብ፣ ቀርሳቸውን ጠብቀው የሚያበለጽጉበት ሥልጣን ሊኖራቸው ይገባል።

ሌላው የዕድገታችንና የኅብረታችን ማነቆ ሁኖ የኖረውና ዛሬም ያልተፈታውና እየተሸፋፈነ ያለው ይፌድራሉ የሥራ ቋንቋ ነው።ሕገ መንግሥታችን የአንድ ብሔርና የአንድ እምነት ቋንቋን ነው፣ ለፌድራሉ የሥራ ቋንቋነት የመረጠው።የቋንቋ እኩልነት በሌለበት አገር፣ የብሔር እኩልነት ሊኖር አይችለም።ለብሔር ማንነት መለኪያው ቋንቋ ነውና።አንድ ቋንቋ የፌድራል መንግሥቱ የሥራ ቋንቋ ሆኖ፣ በመላው አገሪቱ እንዲሰራፋ መፍቀድ ማለት፣መሰል ዕድል የሌላቸውን ቋንቋዎች፣ አቀጭጮ እንዲውጣቸው መፈቀድ ማለት ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  “እንፈላለጋለን!” (ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ)

ስለሆነም በአገራችን ሰላምን ለማስፈንም ሆነ በኢኮኖሚ ለመበልጸግ ከተፈለገ ከሁሉ በፊት በሕብረተሰቡ መካከል ያለውን ቅራኔ ነቅሶ በማውጣት መፍታት ይገባል።አለበለዚያ ያለው ቅራኔ እያደር እየከረረ፣የብሔርና የእምነት ሊዩነት እያደር እየሰፋ ይሄዳል።ለዚህ ደግሞ ያለፈው ታሪካችን ራሱ ከበቂ በላይ የሆነ ምስክር ነው።በመሆኑም ይህን የቋንቋ ቅራኔ ለመፍታት፣አንደ አፍሪካ አህጉር፣ህንድና ፓክስታን ሁሉ የፌድራል የሥራ ቋንቋን እንግሊዘኛ ማድረግ ይገባል።

በዚህም ረገድ ስለ ቋንቋ ሲወሳ ችግሩ ፣ የአንዱ ብሔር ሌሎች ብሔርችን መዋጡ ብቻ ሁኖ መገመት የለበትም።ቋንቋ መግባቢያ ነው ካልን፣ የምንግባባው ደግሞ ስለ ምድራዊ ሕይወታችን ብቻ አይደለም።ምዕመናን የፈጣሬያችውን እውነተኛ ቃልና ፈቃድን፣ ከሰዎች ተረታ ተረት ለይተው ለማወቅ የሚችሉት በቋንቋ ነው።ስለዚህም ነው ቅዱሳት መጽሐፍት፣ከእብራይስጥ ወደ ግሪክ፣ከአረብኛ ወደ ግዕዝና አማርኛ የተተረጎሙት፡፡ በዚህ ረገድ ለአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የተሰጠው ዕድል ሁሉ፣ለሌሎች ቋንቋዎች ተናጋሪዎችም ተሰጥቶ፣ ነፍሳት ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃልና ፈቃድ እኩል ተረድተው፣ መንግሥቱን ለመውረስ እንዲችሉ ሊረዱ ይገባል። “ለአሕዛብ ንስሐ አባት ዲያቆን መቼ አነሰው?” የሚባልበት ዘምን አልፏል። ስለሆነም፣በድሬ ሼህ ሁሴን የአረብኛና የልዩ ልዩ ቋንቋዎች ጥናትና የምርምር ማእከል ተከፍቶ፣ቅዱሳት መጻሕፍት በየቋንቋዎቹ ተተርጉመው፣ሕዝባችን የሚከተለውን እምነት ምንነት አውቆ፣ ወዶና ፈቅዶ እንዲከተለው ማስቻል ይገባል።

ሌላው ሕዝባችንን በእርስ በርስ ጦርነት እየማገደ ያለው፣የብሔርና የፖለቲካ ፓርቲዎች የመንግሥት ሥልጣን ጥያቄ ነው።የመንግሥት ሥልጣን የሚያስፈልገው ሕዝቡን በቅንነት በማገልገል በሰላም በማስተደደር ወደ ጋራ ብልፅግና ለመምራት ከሆነ፣ ሕዝቡ ራሱ መሪዎቹን መምረጥ ይኖርበታል። ሕዝብ የሚያምንባቸውን ሊመርጥ የሚችለው ደግሞ ለምርጫ ከቀሩቡት ዕጩዎች መካከል በመሆኑ፣የአቢዮታዊ ዴሞክራሲ የፓርቲ አመራር ተወግዶ፣ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች ሁሉ እኩል፣ሰላማዊ የውድድር መድርክ ሊሰፋ ይገባል። ገዥው ፓርቲ በድርጅታዊ አሠራር ራሱን የሚያስመርጥበት፣ ፓርላሜንተሪያዊ ቅርጸ መንግሥት ተወግዶ፣ በፕሬዚደንታዊ ቅርፀ መንግሥት ሊተካ ይገባል።ይህ የሥልጣን መወጣጫ ሥውር መሰላል ከተወገድ፣የቀረውን ችግር ሕዝባችን ራሱ በሂደት ይፈተዋል። በዚህም ረገድ ከሕዝባችን መካከል ያለውን ተፃራሪ ቅራኔዎችን ካስወግድን፣ ሕዝባችን በቋንቋው ራሱን በራሱ እያስተዳደረ፣ ባህሉን እየበለጸገ፣ቀርሶቹን እየተንከባከበ፣በሰላም እምነቱን እየተለማመደ፣በደስታ ይኖራል። በዚህም ታግዞ በሙሉ ኃይሉ ለሥራ ከተነሳ፣ ፈጥኖ በድኅነት ላይ ድልን የቀዳጃል። ይህም ሁሉ የቸሩ ፈጣሪ አምላካችን ፈቃድ ይሁንልን!!!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ክብር እንክርዳድ ተዘርቶበት ስንዴ ሆኖ ለበቀለ ትውልድ!!! – ተስፋየ ኤልያስ

 

1 Comment

  1. Jobir:

    Enjoying life in the USA where people coming from the different corners of the world live in harmony, irrespective of their ethnic, religious, language and cultural differences, should have made you curse the primitive and backward ethnic-based politics which was introduced to Ethiopians by woyanes and practised in its worst form by fascist oromos.
    What goes around come around. First the victims of ethnic politics were Amharas, then tigres. Who will be the next? Obviously, oromos.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share