መግለጫ
የአዲስ አበባ ከተማ ከኦሮምያ ክልል ጋር የአስተዳደር ወሰን እንዲኖራት ለማድረግ መስመር በማስመር ላይ ነን የሚል ዜና ከወይዘሮ አዳነች አበቤ ቢሮ ተሰምቷል። እኚህ ከንቲባ የኦሮምያን ህገ መንግስት ተግባራዊ ለማድረግ አንደሚሰሩ በቅርቡ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ያሳወቁ መሆናቸው አይዘነጋም። ከንቲባዋ ይህንን ባሳወቁ በጥቂትጊዚያት ዛሬ ደግሞ በአዲስ ኣበባና በኦሮምያ መካከል የአስተዳደር ወሰን ለማስመር ሲጣደፉ እየታዩ ነው። መቼስ ይህ ጥድፊያ አሻጥር እንዳለው ለማንም ግልጽ ነው። ከሁሉ በላይ ግን የሃገራችን ህዝብ የህወሃት ኢሕአዴግን መንግስት በቃኝ ብሎ አምርሮ ታግሎ የጣለው በሃገራችን ውስጥ መዋቅራዊ ለውጦች እንዲመጡ፣ በፌደራል ስርዓቱ ላይ ምክክር አድረገን አጠቃላይ የሃገራችንን የፖለቲካ አሃዶች ለመከለስ፣ ብሎም በዚህ በሚሻሻል የመዋቅር ለውጥና የህገ መንግስት ማሻሻያ ስር የአዲስ አበባም የመልካም አስተዳደር ጉዳይ፣ የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ፣ የከተማዋ የፖለቲካ አሃድነት ጥያቄ ጉዳይ እንዲፈታ ነበር። ባለፉት አመታት መንግስት በአንድ በኩል የአስተዳደር፣ ወሰንና ማንነት ኮሚሽን አቋቁሜ የሃገሪቱን ተያያዝዥ ጉዳዮች እፈታለሁ ብሎ ሶስት ኣመት ሙሉ ኮሚሽኑ ለአ ስተዳደር፣ ማንነትና ወሰን ጉዳዮች አንዲት ጠብታ መፍትሔ ሳያቀርብ የህዝብን ገንዘብ አክስሮ እንዲከስም ተደርጓል። መንግስት በአጠቃላይ ላሉ የኣስተዳደርና ወሰን ጉዳዮች እልባት መስጠት ተስኖት እስካሁን አለ። ከፍ ሲል እንደገለጽነው ብዙ ሳንካና ግጭት ያለበትን ህገ መንግስት አሻሽሎ ለአዲስ አበባ ከተማ በሚገባ የተጠና ማስተር ፕላን ሰርቶ በዚያ መሰረት ወሰን ለመመስረት መነሳት የከተማዋን እድገት ያሳልጣል። ነገር ግን በተለይ በዚህ ወቅት ማንነትና መሬት በተጣበቁበት ሃገር ውስጥ የወሰን ጉዳይን አንስቶ በጥድፊያ ለመከለል መሞከር ግጭትን መጥመቅ ነው። የአዲስ አበባ አስተዳደር በዚህ ወቅት የህዝቡን ስራ ማጣትና የኑሮ ሁኔታ ለመፍታት እንደ መታገል ወቅታዊነት በሌለው የግጭት ስራ ላይ ተጠምዶ ይገኛል።
በእኛ እምነት ይህ የአዲስ አበባ ወሰን ጉዳይ መጀመሪያ በሃገር ደረጃ የፌደራል ስርዓትና የህገ መንግስት ማሻሻያ ተደርጎ ሊከወን የሚገባው ጉዳይ ነው። ሃገሪቱ በገለልተኝነት የሁለት ክልሎችን አስተዳደራዊ ወሰን የሚከውን የባለሙያ ተቋም እንኳን የሌላት ሃገር ናት። ስለሆነም ሃገራችን አሁን ያለችበትን ያለመረጋጋት ከግንዛቤ በማስገባትና የሚጠበቀውን የህገ መንግስት መሻሻል ስራ ከግንዛቤ በማስገባት የአዲስ አበባን ወሰን ከማስመር መታቀብ ያስፈልጋል። በተለይም ደግሞ የአዲስ ኣበባ ህዝብ ቆጥቦ የሰራቸውን የኮንደምንየም የመኖሪያ ቤቶች ወዲያና ወዲህ ማድረግ መሬትና ማንነት በተጣበቀበት መርህ ስር ብዙ እምቅ ግጭቶች አሉበት። ስለሆነም የአዲስ አበባ አስተዳደር ከልማት ይልቅ በየጊዜው ግጭት ባላቸው ጉዳዮች ውስጥ አየተዘፈቀ የከተማችንን ህዝብ ሰላም መንሳት የለበትም። ከዚህ ስራው ታቅቦ የሃገራችን የፖለቲካ አሃዶች እንደገና በጥናት እንዲከለሱ የአዲስ አበባ አስተዳደር ጉዳይም በዚህ ማእቀፍ ስር እንዲሆን ቅቡልነት ባለው የምክክር ሂደት ሊፈታ ይገባል። ስለሆነም ይህ ህገ ወጥና ህዝብ ያልመከረበት ድርጊት ተቀባይነት እንደሌለው እየገለጽን መላው የአዲስ አበባ ህዝብ መብትህን ለማስከበርና ከተማህን ለመጠበቅ ቆርጠህ አንድትነሳ ጥሪያችንን አናቀርባለን። ዘወትር ከግጭት ጠማቂነት የማይታቀበው የወይዘሮ አዳነች አስተዳደር በህዝባችን ንቁ ትግል ሊገታ ይገባል።
የድጋፍ በሰሜን አሜሪካ