ጉራጌ ለምን ክልል መሆን አስፈለገው? (ይርጋዓለም ብርሃኑ እንደጻፈው)

መቅድም

የዚህ ጽሑፍ ዋና ምክንያት ሰሞነኛው የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ነው። የጉራጌ ቀደምት ታሪክ የሚያስረዳው በነገሥታቱ ዘመን የራስ ገዝ አስተዳደር ኖሮት ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ጥብቅ ትሥሥር እንደነበረው የታሪክ መዛግብት ይመሰክራሉ። ለዚህም ብዙ የታሪክ ጸሐፊዎች ዘግበውታል፤ለምሳሌ የነገስታት ዜና መዋዕሎች፣ድርሳናት እና ከመካከለኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ወደ ኢትዮጵያ የጎበኙ የውጭ ሀገር ዜጎች የጻፏቸው በመጽሐፍቶቻቸው ጠቅሰዋል ። አሁን ያለችው ዘመናዊ ኢትዮጵያ በዳግማዊ አጼ ሚኒልክ ከተመሰረተ በኋላም ጉራጌ የራሱ የሆነ ‘ጉራጌ ክፍለ ሀገር’ በማለት ተሰጥቶት ለማዕከላዊ መንግሥት እየገበረ ኢትዮጵያን ሲገነባ ሲኖር የነበረ ሕዝብ ነው። በዘመነ ኢሕአዴግ አሁን ያለውን የብሔር ፌደራሊዝም ሲቋቋም ግን ጉራጌ ቀድሞ የነበረውን የራስ ገዝ አስተዳደር ተነጥቆ በደቡብ ክልል አስተዳደር ውስጥ ላለፉት 30 ዘመናት ሲተዳደር በመቆየቱ የራሱን ባህል እና አካባቢውን ሳያለማ እንደኖረ የክልል ጥያቄው ዋነኛ ማጠንጠኛ ሆኖዋል።

ሐተታ

1 የጉራጌ ሕዝብ ራስ ገዝ አስተዳደር ታሪካዊ መሠረቶች አሉት

የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፍት የጉራጌ ሕዝብ በተመለከት በተለያየ አረዳድ ጽፈውታል። በቅርብ ዘመን ዊሊያም ሻክ የተባለው ተመራማሪ በ1966 የአውሮፓያውያን ዘመን አቆጣጠር ላይ በጻፈው ጥናታዊ መጽሐፍ ‘A People of the Ensete Culture’ ላይ የጉራጌ ሕዝብ ታሪክ አስመልክቶ ጥንታውያን የተለያዪ ጸሐፍትን በማጣቀስ፤ ለምሳሌ ጀምስ ብሩስ፣ ቤክንግሀም፣ አለቃ ታዬ፣ፖችቹጋላውያኑ ካቶሊካውያን አልቫሬዝ እና ፈርናንዴዝ፣ኢሰንበርግ፣ሌስላኡ እና ሌሎችም ስለ ጉራጌ የጻፉትን በመዘርዘር የጉራጌ ታሪክ በመጠኑ ጽፎታል። ያው የውጭ ሀገር ጸሐፍት እንደሚታወቀው ለራሳቸው ዓላማ እና ግብ ይጽፋሉ።

ይህ የ William A. Shack መጽሐፍ የመሥክ ጥናት የያዝ ፎቶ ግራፎች እና የተለያዪ ቻርቶች እንዲሁም ቃለ መጠይቆችም አካቶዋል። ይህ መጽሐፍ በገጽ 17 ጉራጌ ለአጼ ገላውድዮስ መንግሥት ይገብር እንደነበር እንዲህ አብራርቶታል “during the reign of Gelawdewos(1540-1559), Gurgage paid an annual tribute in Gold figurines, hides, and 1000head of cattle in order to retain some messure of political autonomy”። ይህም ለኢትዮጵያ መካከላዊ መንግሥት በመገበረ እስከ አጼ ሠርጸ ድንግል ዘመነ መንግስት ድረስ ማለትም (1563-1596) ድረስ እንደዘለቀ በዚሁ ከላይ በተገለጸው መጽሐፍ የተገለጸ ሲሆን ነገር ግን ለንጉስ ሱስንዮስ ላለመገበር ከንጉሱ ጦር ጋር እንደተዋጋ በዚሁ ጥናታዊ መጽሐፍ በገጽ 17 እንዲህ አብራርቶታል “Gurage resistance to Ethiopian domination is seen in the writing of Father Fernandez (1613-14) who records that ‘there are people call Gurage who do not obey the emprror Susneyos and they faught on hourseback as well as with bow and arrow”።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ 2ኛ ዓመት ቅጽ 2 ቁ 72 - PDF

FUTUH AL-HABASA ፍቱህ አል ሐበሻ መጽሐፍ ደራሲ አህመድ ቢን አብድር ቃድር በሌላ ስሙ አረብ ፋቂህ ‘The conquest of Abyssinia’ ተብሎ በተተረጎመው ይህ መጽሐፍ ላይ የጉራጌ ሕዝብ ከንጉሱ ከአጼ ልብነ ድንግል ጎን ተሰለፎ የኢማም አህመድ ቢን ኢብራሂም በተለምዶ ስሙ ግራኝ አህመድ ጦር ጋር ተዋግቶዋል። በዚህ FUTUH AL-HABASA መጽሐፍ በገጽ 169 ራስ ወሰን ሰገድ ስለ ንጉሱ ጦር ብዛት በማብራራት ለአህመድ ግራኝ በደብዳቤ ላይ ጉራጌ የንጉሱ ጦር አካል እንደሆነ እንዲህ ገልጸውለታል “For the king’s army has grown to it’s previous size; and with the king now an army greater than any you have ever seen heard of before this. It comprises Gurage, Gafat and Damot, people from Enarya and Zait and Jimma”. የጉራጌ ሕዝብ በወቅቱ ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ትሥሥር እንደነበር እና ጉራጌ ራሱን እያስተዳደረ ለማዕከላዊ መንግሥት ሲገብር ይኖር እንደነበረ ያስረዳል።

በኢትዮጵያ ታሪክ በዘመነ መሳፍንት ወቅት ጉራጌ የራሱ የሆነ ፖለቲካል ማኅበረሰብ ፈጥሮ የራስ ገዝ አስተዳደር ነበረው። በዘመነ መሳፍንት ዘመን ጉራጌ መስፋፋት ላይ በነበረው ከኦሮሞ እና ከሲዳማ ጋር ብዙ ግጭቶች እና ጦርነቶች ያካሄድ እንደነበረ ዊልያም ሻክ ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፍ የታሪክ መዛግብት እያጣቀሰ ጽፎታል። በዚህ መጽሐፍ ገጽ 18 ላይ “often they joined forces with Sidamo and Arussi Oromo tribes who, when not being threated by external foreces themselve, were constantly making attacks on Gurage” በማለት ገልጾታል። በዚሁ ዘመን የሸዋ ገዢ የነበሩት ንጉስ ሣህለ ስላሴ የተወሰኑ የጉራጌ አካባቢዎች ማስገበር በመቻለቸው ራሳቸው የጉራጌ ንጉስ ብለው እንደተጠሩ በገጽ 18 እንዲህ ይጠቅሰዋል “Although the Gurage had not been completely subjucted by 1840, nevertheless, Sahla Sellassie began to call himself ‘King of Gurage’”። ዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ ሀገር ምስረታ ባደረጉት ዘመቻ ላይ በተወሰኑት ቤተ ጉራጌ አካባቢዎች ብዙ ደም መፋሰስ ቢኖርም በመጨረሻ ግን ጦርነቱ በእርቅ ተፈጽሞ ሀገር አብሮ እየገነባ የኖረ ሕዝብ እንድሆነም በዘመንዊው ኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍት ተዘግቦዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ትንቢታዊ መልእክት ከቆሼ – ያየያየ ይልማ

2 ጉራጌ የራሱ የሆነ ባህል፣ የሽምግልና ሥርዓት እና የአኗናር ዘይቤ አለው

የጉራጌ ሕዝብ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የራሱ የሆነ ብዙ ባህል፣ ወጎች እና የሽምግልና ሥርዓት እና አስተዳደር ነበሩት፤ አሁን ቢደደበዝዝም የተወሰኑ አሉ። በቅርብ ዘመን በተለይ ከዘመነ ኢሕአዴግ አገዛዝ ጊዜ አንስቶ እየተዳከመ የመጣው የጉራጌ የሽምግልና ሥርዓት በሰባት ቤት ጉራጌ የጆካ ይባላል። ጆካ የቦታ ስም ነው። በዚህ ቦታ ላይ ከሁሉም የሰባት ቤት የጉራጌ የጎሳዎች ሽማግሌዎች ወይም ነገር አዋቂዎች የሚወከሉበት እንደየ ደረጃቸው በተለያዪ ጉዳይ ላይ ተቀምጠው የሚወያዪበት እና የተለያዩ ውሳኔዎች የሚያሳልፉበት ቦታ ነበረ፤ይህ ቦታ የመጨረሻው የሕግ እና የአስተዳደር ምክር ቤት ነበር። በሰባት ቤት ጉራጌ የጆካ የመጨርሻው የፍርድ ቦታ ነው፤ በአሁን ዘመን በአሜሪካ ሱፕሪም ኮርት፤ በኢትይጵያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደማለት ነው። በታችኛው ደረጃ በየ አካባቢው በየ ጎሳው መሪዎች/ሽማግሌዎች አማክኝነት የሚካሄዱ የሽምግልና ሥርዓት እና የአካባቢ ምክር ቤቶች ነበሩ። ከአንድ አንስተኛ መንደር እስከ ላይኛው ሙሉ ጉሳ ከፍ እያለ መጨረሻው የጆካ ድረሰ የሚሄድ የሽምግልና ሥርዓት እና አስተዳደር ነበረ። የጆካ የሚሄድ በጣም ትላልቅ ጉዳይ ብቻ ነው። በታችኛው የጎሳ ወይም የአካባቢ መዋቅር የሽምግልና ሥርዓት የማይፈቱት ጉዳዮች ብቻ በተወካዪ የጎሳ መሪ ወይም ነገር አዋቂ አማካኝነት ወደ የጆካ ይሄዳል። የጆካ ሽማግሌዎች የመጨረሻ ውሳኔ ያሳልፋሉ፣በጉራጌ ባህል በየጆካ የማይፈታ ምንም ዓይነት ጉዳይ አይኖርም ነበረ። መንግስት ወደሚያዋቅረው ፍርድ ቤት በእኔ እድሜ እንኳን እንደ ማይኬድ አውቃለሁ። ይህ የሽምግልና ሥርዓት በሌሎችም ከሰባት ቤት ውጪ ባሉ ቤተ ጉራጌዎች ዘንድ በተለያየ ስም ተመሳሳይ አፈጻጸም ያለው ሥርዓት አላቸው። በዚህ በአሁን ዘመን ከሁሉም ቤተ ጉራጌዎች የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች ‘የጉራጌ ሸንጎ’ የሚል የባሕል ሽማግሌዎች ስብስብ አለ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የታሪክ ጥናት አብነት -የታሪክ ትምህርት ተግዳሮት

በሁሉም ቤተ ጉራጌ ማሕበረሰብ ዘንድ የጉራጌ ቂጫ፣የጉራጌ ሴራ፣ ጉርዳ፣ ኸተራ፣ አንቂድ የሚባሉ ከማሕበረሱቡ ጋር የኖሩ ሥርዓቶች አሉ።ጉራጌ ዘምናዊ ፍልፍፍናን ያዘሉ ለአሁን ትውልድ በትምህርት መዋቅር ገብቶ ቢማር እጅግ ጠቀሚታ ያለው ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር የሚሄድ የሚጨበጥ ባህል እና እሴቶች ነበሩት፤ ነገር አሁን በመጥፋት ላይ ናቸው።

መደምደሚያ

በመጥፋት ላይ ያለው የጉራጌ ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ እንደ ጥንቱ ጉራጌ የራስ ገዝ አስተዳደር እንዲመሰርት መፈቀድ አለበት ብዬ አምናለሁ። ለዚህም ደግሞ ኢትዮጵያ እየተዳደርች ያለችው በብሔር ፌደራሊዝም እስከሆነ ድረስ ጉራጌ በክልል ላለመደራጀት የሚያግደው ምንም አይነት ምድራዊ ምክንያት ሊኖር አይችልም። እንዲሁም የጉራጌ ማሕበረሰብ ለኢትዮጵያ ያበረከቱት በጎ አስተዋጽዎ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የተጠየቀውን የክልልነት ጥያቄ በቅንነት ተመልክቶ የፌደራል መንግስት እገዛ ሊያደርግለት ይገባል። ሥለዚህ ጉራጌ ራስ በራስ የማስተዳደር ታሪካዊ መሠረት ስላለው የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት እስካልተቀየረ ድረስ ጉራጌ ራሱን ችሎ በክልል ለመደራጀት የሚከለክል የታሪክም ሆነ የሕግ መሠረት ስለሌለ ለሌላ ብሔር የተሰጠውን በክልልነት መዋቀር ለጉራጌ አለመፍቀድ ባህሉን እና ቋንቋው እንዲጠፋ እንዲሁም አካባቢውን እንዳያለማ መከልከል ይሆናል።

የግርጌ ማስታወሻ፦

እኔ የብሔር ፖለቲካ አቀኝቃኝ አይደለሁም። የብሄር ፌደርሊዝም ፈርሶ አሁን ያለውን ሕገ መንግሥት ተቀይሮ ፣ የሰው ልጆች ሁሉ በእኩልነት በፈለጉት የኢትዮጵያ አካባቢ እንዲኖሩ እና እንዲቀሳቀሱ ጸኑ ፍላጎቴ እና ጸሎቴም ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share