የአልሸባብ የጥቃት ሙከራ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን  ለቀጠናውና ለምእራቡ አለምም የማስጠንቀቂያ ደወልነው

ሀምሌ  24, 2014  (July 31,2022)

አክሊሉ ወንድአፈረው (ethioandenet@bell.net)

ህወሀት በትግራይ ክልል ተመድቦ ያገለግል በነበረው የሰሜን እዝ ላይ ድንገተኛ (መብረቃዊ)  ጥቃት ፈጽሞ ኢትዮጰያ በታሪኳ ታይቶ የማይታወቅ ውስጣዊ ግጭት መቀስቀሱን ተከትሎ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጰያ ላይ ታላቅ ሁለገብ  ተጽእኖ እያሳደረች ነው፡፡ ይህም የኢትዮጰያን አንጻራዊ መዳከም በአንጻሩም የአልሸባብን መጠናከር አልፎ ተርፎም የሰሞኑን የቀጥታ ወረራ ሙከራ አስከትሏል፡፡ ይህ ሁኔታ በቀጣይ ሊያስከትል የሚችለውን እንደምታ መመርመርና አስቸኳይ የርምት እርምጃ መውስድ አጣዳፊ ጉዳይ ነው፡፡

በዚህ ውስጥ ቁልፍ ሚና የተጫወተችው እና እየተጫወተች የምትገኘው አሜሪካ ነች፡፡ አሜሪካ የትግራይን አማጺ ሀይል ፣ ሀወውሀትን፣ በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ካከካሄደ በዃላ መልሶ እንዲያንሰራራና ከተቻለም ወደ ሥልጣን እንዲመለስ የሚረዳ እጅግ ብዙ ተግባሮችን ሰርታለች፡፡

ለምሳሌም በኢኮኖሚው መስክ አሜሪካ ብቻ ሳትሆን አጋሮቿንም አስተባብራ ለኢትዮጰያ እርዳታ እንንዳይሰጡ በማድረግ ኢኮኖሚዋ እንዲደቅ ተድርጓል፡፡ ከእርዳታቸው አልፎ የንግድ ስምምነቶችን ( ለምሳሌ አገዋ) በመሰረዝ ቀና ማለት ጀምሮ የነበረውን የእንዱስትሪ መስክ  አሽመድምደውታል፡፡ይህም በኢትዮጰያ ቀድም ሲልም አስከፊ የነበረውን በተለይም የሴቶችንና የወጣቶችን ሰራ አጥነት እጅግ ከፍ አድርጎታል፡፡

በዲፐሎማሲው መስክ ኢትዮጰያ ለ 13 ጊዜ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ምክር ቤት አጀንዳ ሆና እንድትወቀስ ብቻ ሳይሆን ቢቻላቸው ታላቅ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዝ የተባበሩት መንግስታት ዉሳኔ እንዲተላለፍ ጥረት ተደርጓል፡፡ እያንዳንዱ ስብሰባ የተጠራውም በአሜሪካ ወይም በሸሪኮቿ ነበር፡፡ ይህ ሙከራቸው በቻይና፣ሩስያ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገሮችና በህንድ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ እንዳይሳካ ቢሁንም ታላቅ ጉዳትን አድርሷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጰያ በአፍሪካም ጭምር ተቀባይነቷ ላይ ታላቅ ተጽእኖ እንዲደርስባት በተለይም በግብጽ ግፊት ልማቷን እንኳ እንዳትገፋበት በተለያዩ ጎረቤቶቿ ተደጋጋሚ የማስፈራራትና የሴራ ኢላማ እንድትሆን ብዙ ተሞክሯል፡፡ የሱዳንን የደቡብ ሱዳንን የጅቡቲ፣ የዛምቢያን ወዘተ ጉዳይ ማንሳት መረጃ ይፈነጥቃል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚደንት ትራምፐ በይፋ የህዳሴ ግድብ በግብጽ እንዲመታ ጥሪ አድርገው እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ስዊድን

ይህ ሁሉ ሀወሀትን አና ሌሎች የውስጥ ህይሎችን (ለምሳሌ በጉምዝ፣ በኦሮሚያ  ጋምቤላ) በወታደራዊ ሀይል ያሻቸውን በህዝብ ላይ ለመጫን ትልቅ ወረራ እንዲፈጸሙ በቀጥታም ይሁን በተዛዋሪ ገፋፍቶ (አበረታትቶ)  እነሆ ኢትዮጰያ ታላቅ ቀውስ ውስጥ ገብታለች፡፡

በትግራይ የተከሰተውብ እና ኳላም ወደ መሀል አገር የገፋውን ጦርነት ተከትሎ የኢትዮጰያ ሰራዊት ያለውን ሀይሉን ወደ ትግራይ፣ ጎንደር፣ ወሎና አፋር  ሰላዞረ  በምስራቅ የሀገራችን ክፍል አል ሸባብ ላይ የነበረው ትኩረትና ቀድሞ የማጥቃት ተግባሩ  እንደ ቀደምት አመታት እንዳይቀጥል  ሆኗል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የኢትዮጰያ የደህንነት ክፍል ትኩረቱን ያሰጉኛል ባላቸው የውስጥ ሀይሎች ለምሳሌ በፋኖ ላይ ያደረገ በመሆኑ በአልሸባብ ላይ በሚደረገው ክትትል እና ሴራውን ቀድሞ ማክሸፍ ላይ  ተጨማሪ ክፍተትን ፈጥሯል፡፡

አል ሸባብ ከላይ የተዘረዘረውን እና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተሸረሸረ የመጣውን የጠቅላይ ሚኒስቴር አብይን ድጋፍ  በማየት ሁኔታ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ራሱን እጅግ አጠናክሮ ቀደም ሲል ተዋጊዎቹን አሾልኮ ለማስገባት አሁን ደግሞ በግልጽ ኢትዮጰያን በሰፊው ለመውረር ሙከራ አድርጓል፡፡ ይህ ወረራ ቢቀለበስም፣ የሚያመለክተው ግን የምእራቡ እስትራተጂ ለአልሸባብ መጠናከር ታላቅ አስተዋጸኦን እንዳደረገ ነው፡፡

ይህ ጉዳይ አደገኛነቱ ለኢትዮጰያ ብቻ ሳይሆን ለመላ ቀጠናው፣ ለቀሪው አፍሪካና ለምእራቡ አለምም ጭምር ነው፡፡

ባለፉት 2 አመታት የተለያዩ የሀይማኖት ጽንፈኞች ከአልሻባብና ከቦኮ ሀራም ጋር ተባብረወና ተናበው ከሞዛምቢክ እስከ ኮንጎ ታንዛንያና ኬንያ ጭምር መስፋፋታቸው  ጥቃትም ማካሄዳቸው ይታወቃል፡፡

የሀይማኖት ጸንፈኞች በምእራብ አፍሪካም ከናይጀሪያ እስከ ማሊ አጎራባች ሀገሮች እየትሰፋፉ እንደሆነ ከሌሎች ቦታዎች ሁሉአፍሪካን መአከል አድርጎ ለማስፋፋትና፣ ለመጠናከር እንደሚጥሩ ይታወቃል፡፡

ይህን ሁሉ በግንዛቤ ውስጥ ስናስገባ የምእራቡ መንግስታት በኢትዮጰያ ላይ የሚያደርጉት እጅግ ጽንፍ የያዘ ተጸእኖና ግፊት ምን እያስከተለ እንደሆነ ኢትዮጰያን ብቻ ሳይሆን የቀጠናውን ሀገራት እና የራሳቸውንም ጸጥታና ጥቅም እጅግ እየጎዳ እንደሆነ ተገንዝበው አሥቸኳይ የእርምት እርምጃ ሊወስዱ ይገባል፡ በዚህ አንጻር፡ ሁኔታውን ለመቀልበስ፡

 • በኢትዮጰያ ላይ የጣሉትን የእርዳታ ክልከላ ባስቸኳይ ሊያነሱ ይገባል
 • በንግዱ አንጻር ያስተላለፉትን የንግድ መአቀብ ሊያነሱ ይገባል
 • ቀደም ሲሉ ይሰጡ የነበረውን እና ከአለፈው ሁለት አመት ወዲህ የከለከሉትን የወታደራዊ ወይም የጸጥታ ትብብር ሊያድሱና ተገቢውን የገንዘብ እና ሊሎችም ድጋፍ ሊቀጥሉ ይገባል
 • በዲፐሎማቲክ መስኩ የሚያደርጉትን ቀጥተኛ የሆነና ተዘዋዋሪ ተጽእኖ ሙሉ በሙሉ ሊያቆሙ ይገባል፡፡
 • በኢትዮጰያ የውስጥ በፖለቲካ የሚያደርጉትን ቀጥተኛና ተዛዋሪ  ጣልቃ ገብነት ሊያስተካክሉና በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ት አ ዛዝ መስጠትን ባስቸኳይ ሊያቆሙ ይገባል፡፡
 • የኢትዮጰያ ወስጣዊ ፖለቲካ እጅግ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን ሲበዛ ውስብስብ መሆኑን በግንዛቤ ውስጥ በማስገባትም ከጣልቃ ገብነት ውጭ ቅራኔን በውይይት ለመፍታት የቴክኔክ እና የማቴርያል ድጋፍ መሰጠት፣ የተወሰኑ ተቃዋሚወችን የማጠናከር እርምጃ መስሎ ከሚታይ አካሄድ ራስን ማቀብ አስፈላጊ ይሆናል፡፡
 • የአልሽባብ እና ሌሎችም ጽንፈኞች ጥቃትና አደጋ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ የቀጠናው መንግስታት በጋራ እንዲቆሙ ማበረታታ እንጂ ማደናቀፍ ከቶውንም አይገባም፡፡
ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰበር ዜና- እስካሁን ድረስ ሰባት Ethiopian Online Activists and Bloggers በፖሊስ ታድነው ታስረዋል

የኢትዮጰያ መበታተን የማይገዳቸው ሀይሎች ከአልሸባብ ጋር የሚግባቡበት  አንዱና ዋነኛው ጉዳይ ኢትዮጰያን ቢቻል ማፍረስ ባይቻል በቀውስ ውስጥ እንድትቀጥል ማድረግ ነው፡፡ የተበታተነችም ሆነች በቀውስ ውስጥ የምትቆይ ኢትዮጰያ ለሁለቱም ክፍሎች አላማ ሰኬት ነው፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጰያ እንደ ሶማሊያ ብትሆን ለኢትዮጰያውያን፣ ለቀጠናውም ሆነ ለምእራቡ አለም ደህነነት እጅግ አደገኛ ነው፡፡

የምእራቡ አለም መንግስታት ተወካዮች በኢትዮጰያ ውስጥ የሚታየው የፖለቲካ ምስቅልቅል በአግባቡ በመረዳት በማንኛውም እርምጃቸው ወገንተኛ እንዳልሆኑ ለማሳየት ማንኛውንም ኢፊሴላዊ ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የሚደረግ ግንኙነት ሁሉን አቀፍ በሆነው በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክርቤት በኩል ቢሆን የተመረጠ ነው፡፡ ይህ ሲሆን በምእራብ መንግስታት ላይ የሚታየውን ወገንተኝነት እና የእምነት መሸርሸር ቀስ በቀስ ለመጠገን ይቻል ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጭ አሁንም የምእራቡ መንግስታት የተወሰኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች  ጋር ብቻ የሚያሳዩትን ቅርርብ በሌሎች ፖለቲካ ድርጅቶች እና በህዝብም ላይ የሚኖረውን አሉታዊ እይታ ሊያጤኑ ይገባል፡፡ ላለፉት ሁለት አመታት የታየው ከመስመር የወጣና ልኡላዊነትን የሚጋፋ ግንኙነት የሚያስተላልፈው መልእክት ኢትዮጰያን አሳንሶና አጋር የሌላት አድርጎ የሚያቀርብ እጅግ አፍራሽ መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ደግሞ የኢትዮጰያ ገዥ ፓርቲ፣ ብልጽግና የምእራቡን መንግስታት ተጸእኖ መላላት ያላግባብ እንዳይተረጉመው እና የህዝብን መብት ለመርገጥ እንዳይጠቀምበት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ የመብት ጥስትና ረገጣውን ከቀጠል የተፈለገውን ሀገራዊ መረጋጋትና የአልሸባብንም ጥቃትና መስፋፋት ማምከን  እጅግ ይከብዳል፡፡

በተጨማሪም የችግሮቹ ሁሉ ምንጭ የምእራቡ መንግስታት ፖሊስ አይደለም እና የዶክተር አብይ መንግስት ራሱን የእስካሁን ፖሊሲና ተግባሩን ገምግሞ ሰሀተቶቹን በተግባር አርሞ ወስብስብ ችግሮቻችንን ከስር መሰረቱ ለመፍታት በአዲስ መንፈስ ለመንቀሳቀስ (reset  ) ቁርጠኛና አስቸኳይ እርምጃዎችን በተጨባጭ ሊወስድ ይገባል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  እንደ ጺላጦስ እጅን ታጥቦ ከወንጀል ንፁህ ለመሆን መሞከር ያስተዛዝባል ! - ተዘራ አሰጉ ከምድረ እንግሊዝ

በዚህ አኳያ ምራባውያኑ በመንግስትና በተቃዋሚዎች መካከል ችግርን በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚቻልበት ምህዳር እንዲዘጋጅ እናም ተግባራዊ አንዲሆን ገንቢ ሚና ሊጫወቱ የሚችሉበት ሁኔታን  መነጋገር እና በጋራ ማመቻቸት  ያስፈልጋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጰያ ውስጥ መብትን ሳያከብሩ ሰላምን እውን ማደረግ በአጭርም ሆነ በረጅም ጊዜ እጅግ ከባድ ነው፡፡

የአሁኑ የአልሸባብ የወረራ ሙከራ ለኢትዮጰያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናውም ሆነ ለምእራቡ ሀገራት ታላቅ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው፡፡ የምእራቡ አለም በኢትዮጰያ ላይ ያሳደረው ወደር የለሽ ተጸእኖ  ከመንግስት የተለያዩ ስህተቶችና ፖሊሲዎች ጋር ተደማምሮ እነሆ አፍራሽ ጎኑ ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ ይህን ሁኔታ ባስቸኳይ መቀልበስ ጠቀሜታው ለምእራቡ አለም ለቀጠናውና ለኢትዮጰያም ጭምር ነው፡፡ ሁኔታው እጅግ አጣዳፊ ትኩረትንም የሚሻ ነው፡፡

7 Comments

 1. ዋናው አልሻባቦች ጁዋር መሃመድ፤አህመዲን ጀበል፤አቡ በከር፤አቡ ሃይደርን አቡ በከርን እና ሌሎች አቡዎችን አስቀምጦ ሶማሌ ድምበር ነገር ፍለጋ መሄድ ለመን አስፈለገ።

 2. ጸሃፊው ያሉት እንዳለ ሆኖ ሌላ ጎኑንም ማየት ጥሩ ነው። አልሸባብን አምርሮ በመዋጋቱ በኩል የሱማሌ ክልል መንግስት፣ ህዝብ እና የጸጥታ ህይሎች እያደረጉ ያሉት ድንቅ ተግባር ለኢትዮጵያ ስላም እና አንድነት የሚክፍሉት ዋጋ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በደርግ ጊዜ በነበረው የዚያድ ባሬ ጦርነት የኛው ሶማሌዎች ስለተባበሩ ዚያድ ባሬ ጦሩን ድሬዳዋ እና ሓረር ድረስ ማስገባት ችሎ እንደነበር ማስታወሱ መልካም ነው። አልሽባብም ይሁን ሌላ የሽብር ድርጅት የአካባቢው ማህበረስብ እስካልተባበረው ድረስ ከባህር እንደወጣ ዓሳ ይቆጠራል።

 3. ወንድሜ አክሊሉ ያስቀመጥካቸው ነጥቦችና ትንተና ማለፊያ ነው። ችግሩ ሰሚ አለ ወይ? ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በስደተኛ ስም በተጠጉና በኗሪዎቹ ሰዎች የሚፈጸመውን የግፍ አይነትና ብዛት ስትሰማና ስትመለከት በእውነት መንግስት አለ ያስብላል። “መግደል መሸነፍ ነው” በሚል ፓሊሲ ዝም የተባሉት እነዚህ ነፍሴ አውጭኝ ብለው ከየስፍራው ወደ ኢትዮጵያ የተሰደድ ከሌሎች ጋር ተባብረው የሚዘርፉት፤ የሚገሉት፤ የሚያፍኑት ከእለት ወደ እለት እየበዛ ነው። በዚህ ላይ የኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኞች ከወያኔ ጋር በማበር የሚያደርሱት መከራ ይህ ነው አይባልም። አሜሪካና አውሮፓ ላይ ተመችቷቸው ተቀምጠው መገንጠልን፤ መገዳደልን፤ ዘረኝነትን የሚያቀነቅኑ ስመ ምሁራኖች ብዙ ናቸው። የሚያሳዝነው የሚኖሩበትን ሃገር ለቀው እንዲወጡ ቢታወጅ ምን ይሉን ይሆን? ባጭሩ የሃበሻ የዘር ፓለቲከኞች ጭንቅላት እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ነው። ዝንተ ዓለም ስንገዳደል፤ ስንሳደድና ስናሳድድ ነው የኖርነው ያለነውም። ይህ ጉዳይ አያቆምም።
  አሁን እንሆ የአልሸባብ ከፍርስራሽ ከተረፈችው ከወደ ሱማሊያ በኩል ብቅ ብሎ ህዝባችን ማመሱ ታዞ እንጂ በራሱ ፍላጎት አይደለም። ወያኔ፤ ኦነግ ሸኔ እንዲሁም ሌሎች በሃገሪቱ የሚርመሰመሱ አጥፊ ሃይሎች ሁሉ ከህዋላ የሚገፋቸው የውጭ ሃይል እንዳለ ሁሉ አልሸባብም ዘዋሪው የውጭ ሃይሎችና ወያኔ ናቸው።
  አብሮት ለዘመናት የሰራውን ወገኑን በተኛበት ከሚያርድ አራዊት ጋር ድርድር ገለ መሌ ማለቱ ዘላቂነት የለውም። አንድ ነገር ልጥቀስ ወያኔ ሌሊቱን በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ሊያደርስ ወደ ማታ መኮንኖችን ለራት ጠርቶ ሰው እየበላ ነው፡ አንደኛው የወያኔ ሻለቃ ለሌላው ሻለቃ ስማ ደህና አድርገህ ብላ ከዛሬ ወዲያ እንዲህ ያለ ምግብ አታገገኝም ይለዋል። ሻለቃውም ፈገግ በማለት ግድ የለም አንተው ሰርተህ ታበላኛለህ ይለዋል እየቀለደ። አይ አንተ የለህማ ይለዋል መልሶ። ያ የትግራይ ሻለቃ በዚያው ቀን በተደረገ የተኩስ ልውውጥ የለም። የተቀለደበት ሻለቃ ለቀናት ታስሮ ከተነዳ በህዋላ በአየር ሃይልና መልሶ በተደራጀው ወታደራዊ ሃይል ነጻ ወጥቶ ዛሬ በህይወት አለ። ወያኔዎች ከሰው ተራ የወጡ ድርቡሾች ናቸው ሲባል ያለመረጃ አይደለም። የሚያሳዝነው በራሳቸው ቴሌቪዥን ላይ በእለቱ ቀርበው ሳይቀድሙን ቀደምናቸው፤ መብረቃዊ ጥቃት አደረስንባቸው እንዳላሉን ሁሉ አሁን አይ እኛ ጦርነቱን አልጀመርንም ይሉናል። ትዝ ይለኛል አንድ መጽሃፍ ያነበብኩት ” One of us is lying” እንዲህ ነው የሃበሻ ፓለቲካ መቀላመድ፤ በሰው ደም መንገድና ለራስ ብቻ የመኖር ናፍቆት።
  ፓለቲካ የቀትር ጥላ ነው። በጉራ የተነፉ ብዙዎች ደንክረውበት የሚሽቀነጠሩበት። አይተናል፤ አንብበናል፤ ፓለቲካ ዝናብ የለሽ ደመና ነው። ለዚህ ነው ሰው እኖራለሁ በሚል ተስፋ ወንድምና እህቱን በዘርና በቋንቋ እንዲሁም በሃይማኖች እያሳበበ የሚያርደው። ንጽህ ጭንቅላት ላለው ሰው ማንም ይሁን ምንም (እንስሳትም ጭምር) ሲጎዳ ማየት ደስ ሊለው አይገባም። በዘርና በቋንቋቸው ለሰከሩ ደግሞ ሻምፓኝ ያስከፍታል። ይህ ሁሉ ከንቱነትን ያሳያል። ትላንት ሃገራችን አይደለችም ትቅርብን ብለው ጥለው የወጡና በወያኔ የአይናችሁ ቀለም አላማረንም የተባሉት ኤርትራዊያን ዛሬ በዓለም ዙሪያ ሲበተኑና በኢትዮጵያ በሃገራቸው ስደተኛ ሲባሉ ማየት የፓለቲካውን ቆሻሻነት ያሳያል። ነጻነትን ሽቶ ባርነትን ይሉሃል ይሄ ነው።
  በእኔ እምነት ኢትዮጵያ ልትወጣ የማትችልበት ማጥ ውስጥ ገብታለች። ጉዳዪን ላስረዳ። በሻቢያና በወያኔ የሙት ፓለቲካ ዘር እንደ ሰንደቅ ተውለብልቦ በፈጠራ ታሪክ አማራ ጨቋኝ ነው እያሉ ህዝባቸውን ካስተማሩ በህዋላ ሁሉም የክልልና የቋንቋ ባንዲራውን ይዞ እኔም ሃገር ነኝ ካለ ቆይተናል። ይህም ጉዳይ ከክልሌ ውጣልኝ በማለት ሰውን እያራወጡ እስከማረድ አድርሷቸዋል። አሁን ላይ እንደመር ቢባል ሰሚ የለም። የለውጡ አካል የነበሩት አቶ ለማ ወደ አሜሪካ በመመላለስ ከኦሮሞ ጽንፈኞችና ከአሜሪካው የስለላ ድርጅት ጋር ከተገናኙ በህዋላ “እኔ መደመር አይገባኝም” ነበር ያሉት። ያው ያቺ ሱሴ ናት ያሏት ሃገር በኦሮሞ ስም በሚንቀሳቀሱ ሃይሎች በየቀኑ ሰዎች ሲታረድ ድምጻቸው አይሰማም። ስለዚህ የዘር ፓለቲካው በጣም ገኖ ስር ስለሰደደ ያን መልሶ ለማርገብ ጭራሽ አይቻልም።
  ሁለተኛ – ዘር፤ ቋንቋ፤ ሃይማኖት ሳንለይ ሰው ራሱ ኑሮና መከራ ያደነዘዘው በመሆኑ የሚታዪትን የመከራ ቱሩፋቶች በህቡዕም ሆነ በይፋ ለመፋለም ፈቃደኛ አይደለም። ሶስተኛ – የውጭ ሃይሎች በልዪ ልዪ መንገድ በሃገሪቱ ውስጥ ሰርገው ስለገቡ ከውጭ በሚያገኙት ድጋፍና ሌላም የሃብት ምንጭ ንግድንም፤ ቤቱንም ሌላውንም ስለተቆጣጠሩትና ስለሚቆጣጠሩት ሌላው ህዝብ የበይ ተመልካችና አንገት ደፊ ያደርጉታል እያደረጉትም ነው።
  አራተኛ – ምንም ይሁን ምንም ወያኔ እያለ የትግራይ ህዝብ ሰላም አያገኝም። በዚህም ሳቢያ አጎራባች ክልሎችና ሃገሮች ጋር በውጭ ሃይሎች እየተረዳ የደፈጣም ሆነ የፊት ለፊት ውጊያ ማድረግ መቀጠሉን አያቆምም። ወያኔ ለትግራይ ህዝብ ገዶት አያውቅም። ይገደዋል የሚሉን ሁሉ በወያኔ የዘረፋ ሰንሰለት ውስጥ ገብተው ባለጠጋ የሆኑ የትግራይ ተወላጆችና ሌሎችም ተለጣፊ ብሄርተኞች ናቸው። አዲስ አበባ የሌላውን የሃገሪቱን ክፍል መልክ እንደማያሳይ ሁሉ መቀሌ የትግራይን ምድር ጠቅላላ ሁኔታ አያመላክትም። ወጣ ብሎ የገጠሩን አፈር ገፊና መከራ ተቀባይ ህዝባችን ማየት ሰውን ሚዛናዊ ሊያረገው ይችላል። በእነዚህ አራት ምክንያቶችና በሌሎች ጊዜ ወለድ ችግሮች ሃገራችን ተጠፍራ ተይዛለች። የአልሸባብ ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ ለመግባት ያደረገውና የሚያደርገው ሙከራም ከምዕራባዊያን ዓይን የተሰወረ አይደለም። ሴራቸው ረቂቅ ነው። መንግስት ሊፈርስ ነው ብለው እኮ ኤምባሲያቸውን ዘግተው ነበር። ስልታቸው ይህ ነው አይባልም። የጠ/ሚሩ መጥፋትም አሳሳቢ እንጂ የሚያስፈነድቅ አይሆንም። ስንቶች ተመርዘው ሞተዋል? አሁን ማን ይሙት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ታሞ ነው የሞተው? የህመሙ ምንጩ ከየት መጣ? ብዙ ጉድ አለ። እኛ ግን ቆም ብለን እንደ ሰው ሰውን በሰውነቱ መዝነን ሰው ሲጎዳ እኔን ብለን እጃችን የምንዘረጋው መቼ ነው? ከዚህ ዘርና ቋንቋ ልወለድ ብሎ መርጦ የተወለደ አለ? የፓለቲካ አተላዎች ግን ዛሬም የሚያቀነቅኑት ያስረሽ ምችው ፓለቲካ በዚህም በዚያም እነርሱን ጭምር ጠርጎ ይወስዳቸዋል። ታሪክ የሚያሳየን ይህኑ ሃቅ ነው። በቃኝ!

 4. አቶ አክሊሉ፤
  ከባዱ ጉዳት የሚደርሰዉ በኢትዮጵያ ፌደራልና የኦሮሞ ክልል አስተዳደሮች እንደሆነ ለምን ይረሳል? ወናዉ ችግር ከዉስጥ ሆኖ ሳለ አሜሪካን ብቻ መኮነኑ ምን እረብ ይኖረዋል?
  • ወያኔን በአየር ላይ የተበተነች ዱቄት አደረግናት ያለዉ አቢይ ተመልሰዉ እንዲያንሰራሩ አደረጋቸዉ፤ ሠራዊታችን ጥጥቁን አስረክቦአቸዉ እንዲሸሽ አደረገ
  • የርሱ ፍላጉት ወያኔን አጠናክሮ አማራን ለማስወጋት እንደሆነ ግልፅ ነዉ፤ በአማራና በአፋር ያደረሱትን ጭፍጨፋ ለምን ትረሳላችሁ?
  • የወደመዉን ንብረት ለምን ትረሳላችሁ?
  • አልሸባብም ቢገባ ወይ በሴራ ነዉ፤ ወይም ደግሞ ድክመታችንን በማየቱ ነዉ።
  • መሬታችንን ለሱዳን አስረክቦ የተቀመጠ መንግሥት ተብዬዉ አልሸባብ ቢገባ ጉዳዩ አይመስለኝም፤
  • እርሱ የዛሬ ትኩረቱ ንፁሓን ፋኖዎችን ማሳደድነ አገር ማፍረስ ነዉ፤
  • በፈረሰች ኢትዮጵያ ላይ የነርሱን ኦሮሙፋ ለመመስረት እንደሚፈልጉ ደጋግመዉ ነግረዉናል፤
  • የዉጪ ጠላቶች ሊያጠቁን የሚችሉት እኛ ጥሩ መሪ ስናጣና ስንከፋፈል ብቻ ነዉ።
  • ይሄን አደጋ አዉቆ መላዉ ወገን መነሳሳት ይኖርበታል፤ ማስመሰልና ከንቱ መመጻደቅ ለማንኛችንም አይበጀንም፤ ተይይዞ መጥፋትን ያስከትላል።

 5. ሰለ ግብአቱ ሁላችሁንም አመሰግናለሁ፣ የጽሁፉ ትኩረት የአልሸባብ ጥቃት አደጋን ማሳየት ነው፡፡ ለሸባብ መደራጀትና መጠናከርም የምእራቡ ጫና ያደረገውን ተጨባጭ አስተዋጻኦ ማሳየት ነው፡፡ ይህ ማለት ሀገርን አደጋ ላይ የሚጥል ቀዳዳ የሚከፍት ውስጣዊ ፖለሲ የለም ማለት አይደለም፡፡ እንዳውም በጽሁፉ ላይ ይህንንም ለማሳየት ሞክሬአለሁ፡፡ ለማናኛውም ወይይቱ ይቀጥል ሁላችንም እንማርበታለን፣ በድጋሚ አመሰግናለሁ

 6. በተለይም ሃይማኖትን አስታኮ የተነሱ አሸባሪ ኃይሎች ከ1980ዎቹ ዓመታት በፊት ያልነበሩና፣ በተለይም አሜሪካ ብቸኛው ኃያል መንግስት ሆኖ ከወጣበት ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰት አዲስ ሁኔታ ነው ማለት ይቻላል። ለምሳሌ የአልሻባብን አፀናነስ ብንመለከት ከአልቃይዳ መወለድና ማደግ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው። አልቃይዳ ደግሞ ሊፈጠር የቻለው የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ሶቭየቶችን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት በነበረው ስትራቴጂ የካርተር አስተዳደር ለታሊባኖች በጊዜው 500 000 000 $ ከመደበ በኋላ ነበር። ከአ1950ዎቹ ዓመታት ጀምሮ እስከ 1980ዎቹ ዓመታት ጊዜ ባለው ውስጥ አፍጋኒስታን ዘመናዊ የነበረችና የእስልምና አክራሪ ኃይሎች የሚታወቁ አልነበሩም። በሌላ አነጋገር፣ ለእስልምና አክራሪ ኃይሎች መፈጠር ዋናውን ሚና የተጫወተው አሜሪካ ነው ማለት ይቻላል። ከዚያ በኋላ የኢስላሚክ ስቴት(ISIS) አፀናነስን ለተመለከተ በሃሰት ውንጀላና በአሜሪካ የማን አለኝበት የሳዳም ሁሴን አገዛዝ እንዲደመሰስ ከተደረገ በኋላና እስከዚያ ጊዜ ድረስ የሳዳም አገዛዝ የገነባቸው ልዩ ልዩ ተቋማት ከፈራረሱ በኋላ ነው ማለት ይቻላል። ብዙ የምርምር ጥናቶች እንደሚያረጋግጡት ከሆነ አክራሪ ኃይሎች በተፀነሱባቸው አገሮች ሁሉ ዋናው ምክንያት የአሜሪካ ጣልቃ ገቢነት እንደሆነና፣ የአሜሪካ የስለላ ድርጅት(CIA) አክራሪ ኃይሎችን በመደገፍና በመገፋፋት ለአሜሪካ አንታዘዝም የሚሉ ኃይሎችን ለመጣል የሚጠቀምበት ስትራቴጂ አንደኛው ዘዴ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ይህም ማለት የአሜሪካን ኤምፔሪያሊዝም የመስፋፋት ዕቅድና አገሮችን በእሱ የስትራቴጂ ክልል ውስጥ ማምጣትና የአሸባሪ ኃይሎች አነሳስና መጠናከር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት ይቻላል።
  ወደ አልሻባብ ስንመጣ አልሻባብ የሰይድ ባሬ አገዛዝ ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የሚታወቅ ጉዳይ አልነበረም። ሁላችንም እንደምናውቀው በሰይድ ባሬ አገዛዝ ዘመን የተቋቋመው አገዛዝ በፀና መሰረት ላይ ስላልነበረና፣ በተለይም በ1977 ዓ.ም ለመጨረሻ ጌዜ የአገራችንን የምስራቁ የተወሰነ ክፍል ከወረራና እንዲመለሰ ከተደረገ በኋላ እንደመንግስት ለመቋቋም አልቻለም። ምናልባት የምናስታውስ እንደሆነ በአብዮቱ ጊዜ የሰይድ ባሬ አገዛዝ ኢትዮጵያን እንዲወር አሜሪካና የሰሜኑ የጦር ስምምነት(NATO) ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ያደርጉ እንደነበር ይታወቃል። አብዮቱም ለመክሸፍ የቻለውና የመንግስቱ ኃይለማርያም አገዛዝ እንዲወድቅ የአሜሪካ የስለላ ድርጅትና የአሜሪካ መንግስት ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል። ወያኔና ሻቢያ አዲስ አበባ ድረስ ለመምጣትና ስልጣን ላይ ቁጥጥ ለማለት የቻሉት ከአሜሪካ የስልለላ ድርጅት ጋር ይሰሩ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን የሚሊታሪ፣ የስለላና የሲቪል ቢሮክራቶች አማካይነት ነው። አልሻባብም ቀስ በቀስ መጠናከር የቻለው ወያኔና አሜሪካ በሱማሊያ ውስጥ ጣልቃ ከገቡ በኋላ ነው። የወያኔ ወታደርም ሆነ የአሜሪካን በሶማሌ ውስጥ ጣልቃ መግባት አልሻባብን በምንም ዐይነት አላዳከመውም። ምክንያቱም አሜሪካኖች የሚከተሉት ስትራቴጂ የተሳሳተ ስለሆነ ነው። በአንድ አገር ውስጥ አሸባሪ ኃይልን ለማዳከምና የመጨረሻ መጨረሻም ለማስወገድ የግዴታ ሰፋ ያለና የጠነከረ ተቋማት መገንባት ሲያስፈልግ፣ በዚያው መጠንም ኢኮኖሚው ሰፋ ባለ መልክ መደራጀትና አለበት። በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ የሚመካበት መንግስታዊ ተቋም ካለና ኢኮኖሚውም በጠንካራ መሰረት ላይ ከተገነባ አሸባሪ ኃይሎች የመፀነስ ዕድል አይኖራቸውም ማለት ነው። አሜሪካኖችና የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስ ዓለም ይህንን ማድረግ አይፈልጉም። አሜሪካንም ሆነ የተቀሩት የካፒታሊስት አገሮች ዕድሜያቸውን ለማራዘም የሚችሉት አገሮችን ወደ ጦር አውድማነት የለወጡ እንደሆን ብቻ ነው።
  ወደ አገራችን ተጨባች ሁኔታ ስንመጣ ከአልሻባብ ይልቅ ለአገራችን ብሄራዊ ነፃነትና ለህዝባችን በከፍተኛ ደረጃ አደገኛ እየሆነ የመጣው ስልጣን ያለው የጽንፈኛው የአቢይ አገዛዝ ነው። አራት ዓመት ያህል ተኩል በተለይም አማራውን ከነበረበት ቀዬው ያፈናቅላል፤ እንዲገደልም ያደርጋል። በወለጋና፣ በሻሸመኔና በሰሜን ሸዋ ለደረሰው የህዝባችን መሞት፣ መንደሮችና ከተማዎች መፈራረስ፣ እንዲሁም ህዝቡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ ማድረግ ተጠያቂው አቢይ አህመድና ሺመልስ አብዲሳ እንጂ አልሻባብ አይደለም። አቶ አክሊሉ በሀተታህ ውስጥ አንድም ቦታ ላይ የአገዛዙን ፋሺሽስታዊ ድርጊትና ዘራፊነቱን በፍጹም ለማሳየት አልቻልክም።
  የኢኮኖሚውን ጉዳይ ለተመለከተ አሜሪካና ግብረአበሮቹ ማዕቀብ ማድረግ ከጀመሩ ጊዜ አይደለም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መንኮታኮት የጀመረው። በመጀመሪያ ደረጃ መንኮታኮት የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ ለሳይንሳዊ ገለጻ የሚያመች አይደለም። ከ1950ዎቹ ዓመታት ጀምሮ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አወቃቀር ለተመለከተ ኢኮኖሚው በጸና መሰረት ላይ የተገነባ አለመሆኑን ነው። በኢኮኖሚው ውስጥ ይታይ የነበረውን የተቋም ቀውስ ለመቅረፍ በደርግ አገዛዝ ዘመን አንዳንድ እርምጃዎች ለመወስድ ቢሞከረም በነበረው አስቸጋሪ ሁኔታ ጤናማ ኢኮኖሚ ማወቀር አልተቻለም። ወያኔ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ተግባራዊ እንዲያደርግ የተሰጠው ትዕዛዝ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ የሚባለውን በይበልጥ ውንብድናንና ብልግናን የሚያስፋፋና፣ በተለይም ደግሞ ጥቂቱን በማበልጸግ አብዛኛውን ህዝብ የሚያደኸይ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው። የአሜሪካኖችና የተቀረው የምዕራቡ ካፒታሊስት አገሮች ስትራቴጂ ማንኛውም አገር ራሱን እንዳይችል ማድረግ ነው። ይህም ማለት፣ ማንኛውም አገር በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚና ሰፋ ያለ የውስጥ ገበያ ኢኮኖሚ እንዳይገነባ ማድረግ ነው። ስለሆነም በህውሃት አገዛዝ ዘመን አደገ የተባለው ኢኮኖሚ በንግድና በተቀረው የአገልግሎት መስክ ላይ የተመሰረተ እንጂ በትናንሽ፣ በማዕከለኛና በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ላይ የተመረኮዘ አልነበረም። አንድ አገር ኢኮኖሚዋ ሊጠነከርና ህዝቦቿንም ልትመግብ የምትችለው በሁሉም አቅጣጫ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፋ ያለ ኢኮኖሚ ስትገነባ ብቻ ነው። ሌሎች ነገሮች ሁሉ ሊጠናከሩ የሚችሉት በዚያ አማካይነትና በተለያዩ ዘርፎች መሀከል መተሳሰር ሲኖር ብቻ ነው። የውጭው ዕርዳታ ስለቀነሰ ወይም ማዕቀብ ስለተደረገ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተከሰከሰ የምትለው ትክክለኛ አባባል ያልሆነና ኢ-ሳይንሳዊ ነው። ስለፖለቲካ ኢኮኖሚ፣ ስለብሄራዊ ኢኮኖሚ አገነባብ፣ ሰለመንግስት አወቃቀርና በሰለጠነ ተቋማት ላይ መቆም፣ ስለሙያ ማስልጠኛ ተቋማት መኖር… ወዘተ. ግንዛቤ ካለ የአንድ አገር ኢኮኖሚ የመከስከስ ጉዳይ ሊታይ አይችልም። የአንድን አገር ኢኮኖሚ መጠናከርና መዳከም እንደ ሰውነታችን መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ሰውነታችን በልዩ ልዩ ኦርጋኖች በመደገፍና በስራ-ክፍፍል አማካይነት ነው ሊንቀሳቀስ የሚችለው። ከዚህም በላይ ለጤንነት የሚስማማ ምግብ ከተመገብንና ስፖርትም ከሰራን የማሰብና የመስራት ኃይላችንም ከፍ ይላል። ብዙ ዓመታትም ልንኖር እንችላለን። በአንፃሩ ጤንነትን የሚያቃውሱ ምግቦች ከበላን፣ በየቀኑ አልክሆል ከጠጣንና ሲጋራ የምናጨስ ከሆነ ጤንነታችን ይቃወሳል። የእኛ ሰውነት ጤንነት ሊወሰን የሚችለው ባለን ንቃተ-ህሊና አማካይነት ነው። የአንድ አገርን ኢኮኖሚ፣ የሰላምን መኖር፣ የመፍጠርና የስራን ባህል ማዳበር ጉዳይ ሊወሰን የሚችለው የሚያስብ መንግስታዊ ኃይልና ሰፋ ያለ በሁሉም መስክ ሊሰማራ የሚችል የተማረ የሰው ኃይል ሲኖር ብቻ ነው።
  በአጭሩ የአገራችን ሁኔታ በእኛ የሚወሰን እንጂ በአሜሪካኖችና በተቀሩት የምዕራብ ካፒታሊስት አገሮች አማካይነት ነው። እንደዚህ ብለን የምናስብ ከሆነ ሰው አይደለንም ወይም እንደሰው አንቆጠርም ብሎ እንደማሰብ ነው። ቻይናዎች በራሳቸው ኢንተለጀንስና በመንግስታቸው ታታሪነት አማካይነት ይኸው እንደምናየው ወደ ኃያል መንግስትነት በመለወጥ ላይ ናቸው። አሜሪካንና የተቀሩትን የካፒታሊስት አገሮች እያሯሯጣቸው ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን ባለን እጅግ ደካማ ንቃተ-ህሊና ምክንያት የተነሳ ሁልጊዜ የምዕራቡን ዓለም እየተማፀን እንኖራለን። ካለነሱ ቡራኬና ፈቃድ ምንም ነገር መስራት የምንችል አይመስለንም። በጣም የሚያሳዝን አስተሳሰብ።
  ለማንኛውም የአገራችን ፖለቲካ አስተማማኝ በሆነ መሰረት ላይ ከተገነባ፤ ህዝባዊ ተሳትፎ ካለ፣ ህዝቡ ከተማረና ከነቃ፤ ዘመናዊና የሰለጠኑ ተቋማት በየቦታው የሚገነቡ ከሆነ፣ ኢኮኖሚው ሰፋ ባለ መልክና ከህዝባችን ፍላጎት አንፃር የሚዋቀር ከሆነ፣ ለሰፊው ህዝብ፣ በተለይም ለወጣቱ የሙያ ማስለጠኛ ተቋማት ከተከፈቱና ከሰለጠነም በኋላ ተቀጥሮ የሚሰራበት ዕድል ካጋጠመው፣ መንደሮችና ከተማዎች በስርዓትና ባህላዊ በሆነ መንገድ የሚገነቡ ከሆነ፣ አንድን አገር አንደ አገር የሚያሰኙት አስፈላጊው ነገሮች ከተነጠፉ… ወዘተ. አልሻባብም ሆነ ሌሎች አሸባሪ ኃይሎች እንደስጋት ሊቆጠሩ አይችሉም። አሸባሪ ኃይሎች የሚፈጠሩት ቀዳዳ ነገሮች በመጠቀም ብቻና ደካማ መንግስት ካለ ብቻ ነው። ስለሆነም ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን ከመገንባት ውጭ ሌላ አማራጭ ነገር ሊኖር በፍጹም አይችልም።
  በተረፈ ሰፋ ላለ ጥናት የሚከተለውን ድረ-ገጽ፤ http://www.fekadubekele.com
  ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share