July 18, 2022
127 mins read

የግለሰቦች ውስጣዊ ፍላጎት ማርኪያ የሆነው የብሄረሰብ ጥያቄና መዘዙ! – ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)    

ፈቃዱ በቀለ (/)          ሐምሌ 18 2022

መግቢያ

የኢትዮጵያን ህብረተሰብ አመሰራረትና አወቃቀር በደንብ ግንዛቤ ውስጥ ሳያስገቡ በተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች የተነሳው የብሄረሰብ ጥያቄ በተለይም ከትግሬና ከኦሮሞ ብሄረሰብ ለተውጣጡ ኤሊቶች ወደ ቂም-በቀል መሳሪያነት በመለወጥ ይኸው ዛሬ አገራችንን ወደማፈራረስና፣ በተለይም በአማራው ላይ ያነጣጠረ እልቂት እንዲደርስ ዋናው ምክንያት ለመሆን በቅቷል። የህብረተሰብን ዕድገት ውጣ ውረድነት በደንብ ሳያጠኑና ሳይንሳዊ ግንዛቤ ሳይኖር የሚደረግ ትግል የመጨረሻ መጨረሻ ዕውነተኛ ነፃነትን ሳይሆን የሚያስገኘው ህዝባዊ ዕልቂትንና የኋሊት ጉዞን ነው። ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ ግንዛቤ ሳይኖረው የሚደረግ የብሄረሰብ ትግል የሚሉት ፈሊጥና በሌላም መልክ የሚደረግ የፖለቲካ ትግል በተለይም ለኢምፔሪያሊስት ኃይሎችና የተሟላና ዕውነተኛ ነፃነትን ለሚቀናቀኑ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ቀዳዳ በመክፈት ወደ ውስጥ የንጹሃን ዜጎች ደም መፍሰሱ ብቻ ሳይሆን ለሁለ-ገብ ዕድገት የሚያገለግል የተፈጥሮ ሃብትና በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ከአለአግባብ እንዲወድም ይደረጋል። በመሰረቱ ተጨቆን፣ ተበደልን ብለው የሚነሱ ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጡ ኤሊቶች በምሁራዊ እንቅስቃሴ ሂደት ውስጥ ያላለፉና የተፈጥሮን ህግም ሆነ የህብረተሰብን ውስብስበነትና ውስጣዊ ኃይልና ዕድገት ያልተገነዘቡ በመሆናቸው የሰከነና ምሁራዊ የሆነ ውይይት እንዳይደረግ መንገዱን ሁሉ ለመዝጋት በቅተዋል። በተለይም አንገብጋቢ ወደሆኑ የህዝብን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ ሳይሆን፣ በተሟላ መልክ አገርን ለመገንባት በሚያስችሉ  እንደ ፊዚክስ፣ አስትሮኖሚ፣ ማቲማቲክስ፣ ባይሎጂና ኬሚስትሪ፣ የህንፃ አሰራር ቴክኒኮች፣ የከተማ አገነባብ ዕውቀቶች፣ የማህበረሰብና የሶስዮሎጂ እንዲሁም የፍልስፍና ዕውቀቶችና፣ በተጨማሪም የኪነ-ጥበብ ነክ ጉዳዮች ላይ ርብርቦሽ እንዳይደረግ በብሄረሰብ ዙሪያ ብቻ በመሽከርከርና ይህንንም ዋናው የትግል ዘዴ በማድረግ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነትን እንዳይጎናጸፍና እፎይ ብሎ በሰላም እንዳይኖር ከፍተኛ እንቅፋት ለመፍጠር በቅተዋል። ከኋላ በመነሳት ዛሬ አነሰም በዛም የተሟላ ዕድገትን ከተጎናጸፉ እንደ ጃፓን፤ ደቡብ ኮሪያና ቻይና፣ እንዲሁም ሲንጋፖርና ራሺያ ትምህርት ከመቅሰምና ኃይልን ሰብሰብ አድርጎ በጋራ ከመነሳት ይልቅ የጦር ትግልን በማስቀደምና አስተሳሰብን በዚህ ብቻ በመወጠር አውሬ የሆኑና ምንም የማይገባቸው አስፈሪ ኃይሎች ብቅ እንዲሉና ህብረተሰባችንን እንዲያተረማምሱ ለማድረግ ችለዋል።

Ethiopia

በአገራችን የፖለቲካ ትግል ታሪክ ውስጥ ያለው አስቸጋሪው ነገር የህብረተሰብን ዕድገትና የመንግስትን መኪና አገነባብና ሚና አስመልክቶ የተደረገ ጥናት ስለሌለና ለማድረግም ስለማይፈለግ የአስተሳስበ አድማሳችንን ለማጎለመስ በፍጹም አልተቻለም። ምሁራን ነን ብለው እዚህና እዚያ ንግግር የሚያደርጉትንና አንዳንድ ጽሁፎችን የሚያቀርቡትን ለሚያነብ ሰው የሚገነዘበው ጉዳይ አብዛኛዎቹ አቀራረቦች ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ ይዘት የጎደላቸው በመሆናቸው ተከታታይነት ላለው ክርክርና ጥናት የሚጋብዙ አይደሉም። ያለፈውን ወደ ስድሳ ዓመት ኃይል የሚያስቆጥር የምሁራኖችን አስተዋፅዖ ለተመለከተ ጽሁፎቹ ሳይንሳዊ ናቸው የሚያስብላቸው አንዳችም ነገር የለም። የአብዛኛዎቹም አጻጻፍና አስተሳሰብ ለሁለ-ገብ ዕድገትና ሰፋ ላለ የምሁራዊ እንቅስቃሴ፣ እንዲሁም ለሰላም መስፈን የሚያመች አይደለም። ስለሆነም እንደዚህ ዐይነት ምሁራዊ ክፍተት በመኖሩ በፖለቲካ ስም ለማወናበድ የሚፈልጉና የጨለማውን ዘመን የሚያራዝሙ ኃይሎችና፣ እንደዚሁም  ከዚህም ሆነ ሆነ ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጡ በጣም ጠባብ አስተሳሰብ ያላቸው ኤሊቶች፣ በመሰረቱ የኢምፔሪያሊስቶችና የአረብ አገር አሽከሮች የሆኑ የፖለቲካ ሜዳውን በመያዝ ህዝቡን ግራ ሲያጋቡ ይታያል።

ስለሆነም በአገራችን ያለው ትልቁ ውዝግብና ወደ ጦርነት ያዳረሰን ጉዳይ በሰፊው የአማራውና በሰፊው የትግሬ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ በሰፊው የኦሮሞና በአማራው እህቶቻችንና ወንድሞቻችን፣ እንዲሁም በአማራውና  በተቀሩት ብሄረሰቦች እህቶቻችንና ወንድሞቻችን መሀከል በተፈጠረ ልዩነትና አለመግባባት ሳይሆን፣ ለእንደዚህ ዐይነቱ ውዝግብና  ጦርነት ዋናው ተጠያቂዎች ከዚህና ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጡ የራሳቸውን ጥቅም ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር ያገናኙና የእነሱ አሽከር በሆኑ ጥቂት ኤሊቶች  ነው። ትግላችንም መሆን ያለበት ሰፋ ያለና የጠለቀ ዕውቀት ሳይኖራቸው የዶክትሬት ዲግሪን በጨበጡና በፖለቲካ ስም በመነገድ ወንድምን ከወንድምና፣ እህትን ከእህት ጋር በማጋጨት ሰፊው ህዝብ ዕውነተኛ ነፃነትን እንዳይጎናጸፍና የሳይንስና የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን የተከበረ አገር እንዳይገነባና ለተከታታዩ ትውልድ እንዳያስተላልፍ የሚያወናብዱትንና እንቅፋት የሚፈጥሩ ጥቂት ኃይሎች ላይ ያነፃፀረ መሆን አለበት። ከዚህ በመነሳት ለሁላችንም ግንዛቤን የሚሰጥ በብሄረሰብ ዙሪያ የሚደረግ አግባብነትና ሳይንሳዊ መጨበጫ የሌለው ጉዳይ እንዲቋጭ አጠር ባለ መልክ ለማቅረብ እወዳለሁ።

የህብረተሰብ አመሰራረት ጉዳይ!

የስልጣኔና የህብረተሰብን ዕድገት በቅጡ ላጠናና ለተከታተለ ከዝቅተኛ ሁኔታ በመነሳት ነው ውስጣዊ ኃይል እያገኛና እየተወሳሰበ በመምጣት ከአንድ አካባቢ በማለፍ ሌላ አካባቢዎችን በማዳረስ የበለጠ ውስጣዊ ኃይል ሊያገኝ የሚችለው። በህብረተሰብ ግንባታ ታሪክ ውስጥ ምናልባት በአንድ አካባቢ የሚኖር ጎሳ ወይም ብሄረሰብ የሚሉት ነገር “የተወሰነ የአገዛዝ መዋቅር ቢፈጥርም” የበለጠ ውስጣዊ ኃይል ሊያገኝና ሊዳብር የሚችለው ከሌላ አካባቢ የመጣ ስልጣኔን ውስጣዊ(Internalize) በማድረግና በመስፋፋት ብቻ ነው። በተፈጥሮ ውስጥም እንደዚህ ዐይነቱ ነገር ይታያል። ማንኛውም አትክልትና ዛፍ፣ በጠቅላላው ተፈጥሮ ብለን የምንጠራው ነገር ሁሉ የመዳበር ኃይል ሊያገኝ የሚችለው በፀሀይ፣ በውሃና በልዩ ልዩ ንጥረ-ነገረች አማካይነት ብቻ ነው። እነዚህን እንደምግብ በመጠቀም ነው ቀስ በቀስ ሊያድግና ፍሬ በመስጠት የኋላ ኋላ ለሰው ልጅ ጠቀሜታ ያለው ነገር ሊያበረክት የሚችለው። ይህ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ለምግብ የሚያገልግል ሰብልም ሆነ ፍራፍሬዎችን የሚለግስ አትክልት የግዴታ እንክብካቤ ያስፈልገዋል። በኢንሴክቶች እንዳይጠቃና ፍሬያማነቱ እንዳይቀንስ ከተፈለገም የግዴታ አጥቂ ኢንሴክቶችን የሚገድል ወይም ሊያባርር የሚችል የተባይ ማጥፊያ መርጨት ያስፈልጋል። ከዚህም ባሻገር የተፈጥሮን ህግና የልዩ ልዩ አትክልቶችንና ሰብሎችን ባህርዮች ለማወቅ ሲቻል ብቻ ነው ማባዛትና፣ አሳድጎ ለምግብ ማዋል የሚቻለው። የልዩ ልዩ አትክልቶችንና ዛፎችን ትርጉምና ጠቃሚነታቸውን ለመረዳት በየጊዜው ሳይንሳዊ ምርምር ማድረግ ያስፈልጋል። የተፈጥሮ ሚዛን እንዳይናጋና የአየርና የአካባቢ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ የትሞላበት እርምጃ መውስደ ያፈልጋል። ምክንያቱም የሰው ልጅ በተፈጥሮ ላይ ጥገኛ እንደመሆኑ መጠን የተፈጥሮን ምንነት ሳይረዳ የሚወስዳቸው እርምጃዎች በሙሉ የተፈጥሮን ሚዛን የሚያናጉና የመጨረሻ መጨረሻም የሰውን ልጅ ጤንነት የሚያቃውሱ ይሆናሉ።  በሌላ አነጋገር፣  የተፈጥሮን ህግ ሳይረዱ በጭፍኑ በተፈጥሮ ላይ የሚደረግ ዘመቻ ከፍተኛ ቀውስን በማስከተል የመጨረሻ መጨረሻ ለብዙ ሺህ ሰዎች ህይወት መቀጠፍ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ይህ ብቻ ሳይሆን ተከታታዩ ትውልድ የሚመካበት የተፈጥሮ ሀብትም እንደልብ አይገኝም።

የህብረተስብን ዕድገት ጉዳይ ስንመለከትም ማንኛውም በዓለም ላይ የተመሰረተና ቀስ በቀስ እየዳበረ የመጣ ማህበረሰብ  በራሱ ኃይል ብቻ ያደገበት ጊዜ በፍጹም የለም። ሊዳብርና ከአንድ የዕድገት ደረጃ ወደ ተሻለ ለመሸጋገር የግዴታ በዕውቀትና በከፍተኛ ንቃተ-ህሊና መታገዝ አለበት። ለተሟላ ዕድገት፣ ለህብረተሰብ መተሳሰርና፣ በልዩ ልዩ መልኮች በሚገለጽ ባህላዊ ክንዋኔ ለመበልጸግ የግዴታ ከሌሎች ሻል ብለው ከሚገኙ ማህበረሰቦች ጋር በንግድና በሌሎችም እንቅስቃሴዎች አማካይነት ግኑኝነት መፍጠር አለበት። ይህ መሰረታዊ ጉዳይ ሲሆን፣ በአንድ አገር ውስጥ የሰፈነ መንግስታዊ ስርዓት ከውጭ የሚመጡ ስልጣኔዎችን ስርዓት ባለው መልክ ተግባራዊ ለማድረግና ሁለ-ገብ ዕድገትን ለመጎናጸፍ የግዴታ ከስልጣን ውጭ ባሉ ምሁራዊ ኃይሎች መታገዝና መገፋት አለበት። ምክንያቱም የንቃተ-ህሊና መዳበርና የዕውቀት መፈጠር  አብዛኛውን ጊዜ ከስልጣን ውጭ ባሉና ልዩ ዐይነት ስጦታ ባላቸውና፣ ተልዕኮም አለን ብለው በሚረዱ ጥቂት በሆኑና በተገለጸላቸው ሰዎች አማካይነት ስለሚፈጠር ብቻ ነው። በዓለም ታሪክ ውስጥ በየአገሮች ውስጥ በተፈጥሮ ጥበብን በተካኑና ልክ በአምላክ የተላኩ በሚመስሉ ኃይሎች አማካይነት ብቻ ነው በተፈጥሮና በኮስሞስ ላይ ምርምር በማድረግ ቀስ በቀስ ግን ደግሞ በእርግጠኝነት ለስልጣኔ የሚሆኑ ነገሮች የተፈጠሩትና የሚፈጠሩት። በሌላ ወገን ደግሞ ስልጣንን የተቆናጠጡ ኃይሎች ስልጣናቸው እንዳይነካባቸው ስለሚፈልጉና ይህንንም ዋናው የኑሮ ፍልስፍናቸው አድርገው ስለሚቆጥሩ አስተሳሰባቸው ስልጣንን በመያዝ ብቻ ስለሚጠመድ በዕውቀት ወይም ሳይንሳዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ርብርቦሽ የማድረግ ኃይል አይኖራቸውም። ስለሆነም አንድ ህብረተሰብ ከሞላ ጎደል በስምምነት እንዲኖር ከተፈለገ የተገለጸላቸው ምሁራን አስተዋፅዖ ከፍተኛና ወሳኝ ሚናን ይጫወታል። በዚህም ምክንያት ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የፖለቲካ ፍልስፍና በግሪክ ምድር ሲዳብር በፍትህ ላይ ርብሮቦሽ የተደረገውና፣ የፓለቲካ ፍትሃዊነት ጉዳይ ከሌሎች የማህበረሰብ ጥያቄዎች ጋር በመያያዝ ቀስ በቀስ በጊዜው የሰፈነውን በጨቋኝና በተጨቋኝ መሀከል የሚገለጸው ህብረተሰብአዊ ውዝግብ በምሁራዊ ኃይል ጣልቃ-ገብነት ሊፈታ የቻለው። ስለሆነም ነው እንደ ዲሞክራሲ የመሳሰሉት ጥያቄዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ህብረተሰቡን ሊየስተሳሰሩ የሚችሉ ልዩ ነገሮች፣ ማለትም እንደኪነትና ስፖርት፣ ከዚያም በላይ ኢኮኖሚያዊ የስራ-ክፍፍል የመሳሰሉ ጉዳዮች በመነሳትና መልስም በማግኘት ቀስ በቀስ መንፈሱ የተረበሸውና በጦርነት የተጠመደው ህዝብ መንፈሱን በመሰብሰብ ፈጣሪ ለመሆን የበቃው። በዚህም አማክይነት ብቻ ነው የኋላ ኋላ ሳይንስ፣ ኪነት፣ ስነ-ጽሁፍና ልዩ ልዩ የፈጠራ ስራዎችና አስተሳሰቦች ሊዳብሩ የቻሉት።

በሌላ ወገን ደግሞ በአንድ ማህበረሰብ ወይም ህብረተሰብ ውስጥ ከውስጥ የተገለጸላቸው ኃይሎች ብቅ ማለት ካልቻሉና  በስልጣን ላይ ያለውን ኃይል መንፈሱን የሚያድሱ ዕውቀቶችን ማዳባር እስካልቻሉ ድረስ እንደዚህ ዐይነት አገዛዝ ግዛቱን የሚያስፋፋው በጉልበት ብቻ ይሆናል። ይሁንና ግን የተወሰነ ተቀባይነት ለማግኘት ሲል ሳያውቀው አንዳንድ ህዝቡን ሊያስተሳሰሩና ተቀባይነትን ሊያገኙ የሚችሉ በተለይም ባህል በመባል የሚገለጹ ነገሮች  ተግባራዊ እንዲሆኑ ያደርጋል። በአጭሩ በህብረተሰብና በህብረ-ብሄር ግንባታ ታሪክ ውስጥ ከውዝግብና ከጦርነት ነፃ በሆነ መልክ አንድ አገር እንደ ህብረተሰብና ማህበረሰብ የተገነባበት ታሪክ የለም። በተለይም በአብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ አገርን እንደማህበረሰብ ወይም ህብረ-ብሄር ለመገንባት ኃይል ወይም ጦርነት ወሳኝ ሚናን ተጫውተዋል። በአንድ ግዛት ውስጥ አንጠቃለልም ያሉትንና ወደ ጦርነት ያመሩ መሳፍንታዊ ኃይሎችን በአንድ አገዛዝ ጥላ ስር ለማምጣት ሲባል የግዴታ ጦርነትን ማካሄድ አስፈላጊ ነበር። በተለይም በጀርመን የህብረ-ብሄር ምስረታ ውስጥ ጦርነት ከፍተኛ  ሚና እንደነበረው የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ከዚህም በላይ የህብረ-ብሄርን ምስረታ መልክ ለማሲያዝና አገርን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማቆም የግዴታ ጥገናዊ-ለውጦችን ተግባራዊ ማድረግና ሁለ-ገብ የሆነ የኢንዱስትሪ ፓለቲካ መከተል አስፈላጊ ነበር። በተጨማሪም በአንድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን በአንድ ግዛት ውስጥ ከተማዎችንና መንደሮችን መገንባትና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ማገናኘት አገርን የመገንባት መሰረታዊ የፖለቲካ ፍልስፍና ነበር። ምክንያቱም በአንድ አገር ውስጥ የሚኖር ህዝብ አገሩን አገሬ ብሎ ሊጠራ የሚችለው የሚያስተሳስሩት ልዩ ልዩ ነገሮች ሲኖሩ ብቻ ነው። በዚህም አማካይነት ብቻ ነው ህብረተሰብአዊ ኃይል ሊፈጠር የሚቸለውና የኗሪውም የመፍጠር ኃይል ሊዳብር የሚችለው። ምክንያቱም የሰው ኃይል ተሰበጣጥሮ በሚገኝበትና የማያቋርጥ ሽኩቻ በሰፈነበት አገር ውስጥ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ማዳበር ስለማይቻል ነው።

ያም ሆን ይህ የአውሮፓን አገሮች  የህብረተሰብና የአገር ግንባታ ታሪክ ስንመለከት ትግል፣ መዋሃድና መዋዋጥ፣ እንዲሁም ጦርነት ወሳኝ ሚናን ለመጫወት ችለዋል። ስለሆነም ከሌላው የተሻልኩ ነኝ ብሎ የሚሰማው ኃይል፣ በመሰረቱ የብሄረሰብን ፍላጎት ሳይሆን የግዛት መስፋፋትን አስፈላጊነት የተገነዘበና፣ በዚህም የሚያምን በመነሳት ነው አብዛኛዎቹ የአውሮፓ አገሮች እንደ አገር ሊገነቡ የቻለው። በሌላ አነጋገር፣ በአንዳች ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም ተፈጥሮአዊ ነገር ከትንሽ ነገር ተነስቶ የማደግና የመስፋፋት ውስጣዊ-ኃይል ያለውን ያህል ከሞላ ጎደል የህብረተሰብም አመሰራረት ይህንን ዐይነት ሂደት ይዞ በመጓዝ ነው ትልቅ ሊሆንና ሊስፋፋ የሚችለው። ተፈጥሮ ኃይለኛ ሙቀትን፣ ኃይለኛ ዝናብንና ጎርፍን፣ እንዲሁም የመሬት መንቀጥቀጥን እየተቋቋመችና አንዳንዴ ደግሞ አንዳንድ ነገሮች እየወደሙ የምታድገውንና የምትስፋፋውን ያህል ህብረተሰብም ብዙ ውጣ ውረዶችንና ህብርተሰብአዊ ውዝግቦችን በመቋቋም ነው ቀሰ በቀሰ እያለ እየዳበረና እየተሻሻለ የሚሄደው። ይሁንና የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል ስላለውና ትክክለኛውን ዕውቀት እስካገኘ ድረሰና በየጊዜውም ራሱን የሚጠይቅና መንፈሱን የሚያድስ እስከሆነ ድረስ በህብረተሰብ ውስጥ ሊደርሱ የሚችሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ መዛባቶችን በማረም ህብረተሰቡ ፈሩን ለቆ እንዳይሄድ የማድረግ ችሎታ አለው።

ስለሆነም በአገራችንም ይህ ዐይነቱ ሂደት ከአክሱም አገዛዝ ጀምሮ እስከፊዪዳሊቱ ኢትዮጵያ ድረስ በመዝለቅና እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ በመሻሻል ሁላችንንንም፣ ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ የተውጣጣን በማዋሃድና በማስተሳሰር የኋላ ኋላ ኢትዮጵያ የሚባል አገር ሊፈጠርና የዛሬውን ቅርጽ ለመውሰድ ችሏል። ከአክሱማዊት አገዛዝ ጀምሮ እስከ ፊዩዳሊቱ ኢትዮጵያ ድረስና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ካፒታሊዝም በተቆነጸለ መልክ ሲገባ የተፈጠረውን የህብረተሰብ ዕድገት ሁኔታ ስንመለከት ስልጣንን የተቆናጠጡ ነገስታት በሙሉ አንድም ቦታ ላይ እኔ የዚህ ብሄረሰብ አባል ነኝ፣ ስለሆነም ብሄረሰቤን በመወከልና ጥቅሙን በማስጠበቅና በሌሎች ብሄረሰቦች ላይ የበላይነትን ማስፈን አለብን ብለው የተነሱበትና ትግል ያደረጉበት ጊዜ በፍጹም አልነበረም።  በጊዜውም እንደዚህ ዐይነት ነገር በፍጹም አይታወቅም ነበር። በኢትዮጵያ የአገዛዝና የህብረተሰብ ዕድገት ታሪክ ውስጥ እስከ ደርግ አገዛዝ መውደቅ ድረስ አንዳችም ኃይል በመነሳት የአማራውን ብሄረሰብ ጥቅምና ባህል አስጠብቃለሁ በማለት በሌሎች ላይ የበላይነቴን ማስፈን አለብኝ ብሎ የተነሳበት ጊዜ በፍጹም አልነበረም። የሚፈጠሩና የሚያድጒ ነገሮች፣ በተለይም በባህል የሚገለጹና እንደቋንቋ የመሳሰሉ ነገሮች በአንዳንድ አገሮች ካልሆነ በስተቀር አንድ ሻል ያለ ቋንቋ በራሱ ውስጣዊ ኃልይ በመዳበርና በሌሎች ዘንድ ተቀባይነትን በማግኘት የአብዛኛው ህዝብ አፍ መፍቻና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ በሰዋስው መልክ በሚገባ በመቀረጽና በመሻሻል የመጻፊያና የስነ-ጽሁፍ መገለጫ ቋንቋ ሊሆን የሚችለው። በመሆኑም በአገራችንም የአማርኛ ቁንቋ ሻል ብሎ በመገኙትና ውስጣዊ ኃይል ስላለው ብቻ ነው ብሄራዊ ቋንቋ ለመሆን የቻለው።

እንደ ሌሎች አገሮችም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለይም ከአራተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ከነገስታቱ ባሻገር የክርስትና ሃይማኖት ዛሬ ኢትዮጵያ ለምትባለው አገር የራሱን አስተዋፅዖ ለማበርክት ችሏል። እንደ ግዕዝ ፊደልና ቋንቋ፣ የኋላ ኋላ ደግሞ የግዕዝን ፊደል በመውሰድ የአማርኛ ቋንቋ መጻፊያና መናገሪያ ለመሆን የተቻለው የሃይማኖት ሰዎች ባደረጉት ከፍተኛ የጭንቅላት አስተዋፅዖ አማካይነት ብቻ  ነው። በጠቅላላው ሰዋሰውም ሆነ ሰነ-ጽህፍ፣ ዜማና ቅኝት፣ እንዲሁም የሙዚቃ መሳሪያዎች የተፈጠሩትና የዳበሩት በቤተክርስቲያን አካባቢ በቀሳውስቱ አማካይነት ነው። ቀሳዋስቱም ቋንቋንና ዜማን ሲፈጥሩና ሲደርሱ ሌሎችን ለመጨቆንና የእነሱን ቋንቋ ለመቅበር ሳይሆን በውስጣዊ ፍላጎትና ኃይል በመነሳሳት ብቻ ነው። ስለሆነም እነሱ የፈጠሩልንን የምናከብርና የምናወድስ መሆን አለብን እንጂ እንደመጨቆኛ መሳሪያ አድርጎ በመቁጠር አንዱን ኬላው ጋር ለማጣላትና ለማባላት መታገል ያላዋቂነት ነው፤ አሊያም በሰይጣናዊ ኃይል በመገፋፋት አገርን ለማውደም የሚደረግ ተንኮል ነው።

ከዚህ ስንነሳ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ ከአስራአራተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በተለይም በሰሜኑ ክፍል ብቻ ተወስኖ የቀረው ፊዩዳላዊ ስርዓት ሊሰፍንና በውስጡም ደግሞ፣ እህል በመዝራትና ልዩ ልዩ ሰብሎችን በማዳበር፣ እንጀራን በመጋገር፣ ጠላንና ጠጅን እንዲሁም ካቲካላን በመጥመቅ የሚገለጽ ማሀብረሰብ ለመመስረት ተችሏል። ከአስራአራተኛው ክፈለ-ዘመን ጀምሮ የክርስትናን ሃይማኖት ለማስፋፋት በሚል ደብተራዎችንና ቄሶችን ወደ ተቀረው፣ እንደ ከፋ ወደ መሳሰሉት አካባቢዎች ከመላክ በስተቀር የፊዩዳሉ ስርዓት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ግዛት ብቻ ተወስኖ የቀረ ነበር። የፊዩዳሉ ስርዓት ተመሰረተ ከተባለበት ከአስራአራተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እስከ አስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ከአምስት መቶ ዓመታት በላይ በሰሜኑ የፊዩዳል አገዛዝ ይበዘበዝ የነበረው የአማራው ገበሬ ብቻ ነበር። በሌላ አነጋገር፣ ከአስራአራተኛው ክፍለ-ዘመን እስከ አስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ የሰሜኑ ነገስታትና የአሪስቶክራሲው መደብ በዛሬው መልክ የሚታየውን የደቡቡን ክፍል የበዘበዙብትና ባህሉም ቀጭጮ እንዲቀር ያደረጉበት ጊዜ በፍጹም አልነበረም። በሌላ ወገን ግን አንዳንድ በደቡቡ ክፍል ያሉ አገዛዞች የክርስቲያኑን አገዛዝ ዕውቅና በመስጠት በመሀከላቸው ትስስርና፣ የደቡቡ ክፍል ነገስታትም ግብር(Tribute) ይከፍሉ እንደነበር ይታወቃል። ከዚህ አጠር መጠን ያለ ገለጻ ስንነሳ የአማራው ፊዪዳላዊ ስርዓት በመስፋፋቱ የተነሳ ነው የተቀሩት በዛሬው መልክ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የተጠቃለሉት ግዛቶች ወይም ብሄረሰቦች ባህላቸው ሊቀጭጭ የቻለው፤ ወይም በያዙት የስልጣኔ ሂደት ሊገፉበት ያልቻለው የሚለው አባባል በኢትዮጵያ የህብረተሰብ የግንባታ ታሪክ ውስጥና በሳይንስ የሚረጋገጥ ጉዳይ አይደለም። የደቡቡ ክፍል ከሰሜን በመጡ መጤዎች ሊጨቆን ችሏል ብለው የሚያወሩ የትግሬና የኦሮሞ ኤሊቶች በተለይም ከአውሮፓው የህብረተሰብና የህብረ-ብሄር አገነባብ ታሪክ ጋር ያልተዋወቁ ብቻ ሳይሆን፣ ተፈጥሮ ራሷ እንዴት እያደገችና እየተስፋፋች እዚህ ዐይነቱ ደረጃ ላይ ለመድረስ እንደቻለች ለመረዳት የማይችሉ ናቸው።

ይህን ትተን ወደ ዘመናዊት ኢትዮጵያ አመሰራረት ታሪክ ስንመጣ የዘመናዊ ኢትዮጵያ አስተሳሰብ በአፄ ቴዎድሮ ቢጸነስም፣ ተግባራዊ ለመሆን የቻለው ግን በአፄ ምኒልክ አማካይነት ነው። አፄ ምኒልክም ሲነሱና የኋላ ኋላ ጣሊያንን ድል አድርገው ለዘመናዊ አገዛዝና ማህበረሰብ የሚሆኑ አንዳንድ ነገሮችን ተግባራዊ ሲያደርጉ ጭቆናንና ብዝበዛን፣ ወይም የአንድ ብሄረሰብን የበላይነት ለማስፈን በሚል አስተሳሰብ በመነሳት ሳይሆን፣ አዲስና የተሻለ፣ እንዲሁም ዘመናዊ ህብረተሰብ ለመፍጠር ብቻ ነው። አፄ ምኒልክ ግዛታቸውን አስፋፉ እስከተባለበት ጊዜ ድረስ በተቀረው የኢትዮጵያ ግዛት እንደ ህብረተሰብ የሚገለጽ ስርዓት በፍጹም አልነበረም። በደቡቡ ክፍል የነበሩ አምስት ነገስታት  ከ16ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ እንዳሉ በኦሮሞዎች መስፋፋት የተነሳ ሊዋጡና ሊወድሙ ችለዋል። ኦሮሞዎች ሲነሱና ሲስፋፉ ደግሞ በከብት እርባታ የሚተዳደሩና በጎሳ መልክ የተደራጁ ስለነበር ያገኙትን በሙሉ አይ በመደምጠጥ፣ አሊያም ደግሞ በመዋጥ ነው ለመስፋፋትና በቁጥር በልጠው ለመገኘት የቻለት። በተስፋፉባቸው ቦታዎች በሙሉ ቋንቋቸውን በኗሪዎቹ ላይ በመጫን መግባቢያ ቋንቋ እንዲሆን ለማድረግ ችለዋል። ከሌሎችም ጋር በመጋባትና ተቀማጭ በመሆን ቀደም ብሎ ከነበራቸው ባህርይና ባህል ቀስ በቀስ እየተላቀቁ ለመምጣት ችለዋል። ይህም ማለት ዛሬ ኦሮሞዎች ነን ብለው የሚጠሩ ሰዎች ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር ሳይጋቡና ሳይዋለዱ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሱበት ጊዜ የለም። በህብረተሰብ ዕድገት ሂደት ውስጥም በመጋባት ብቻ ነው እርስ በርስ መተሳሰርና  በስራ-ክፍፍልና በንግድ ወደ ሚገለጽ  ወደ ተሻለ ማህበረሰብ ለመሸጋገር የሚቻለው። በሌላው ወገን ደግሞ እንደ ቋንቋ የመሳሰሉት በአንድ አካባቢ የሚፈጠሩና የሚዳብሩ ነገሮች በመሆናችው ራስን የመግለጫ መሳሪያዎች እንጂ በመሰረቱ ከባዮሎጂ አንፃር አንደኛው ሰው ከሌላኛው ጋር ሲነፃፀር ልዩ መሆኑን የሚያረጋግጡ አይደለም። አሁንም በሌላ አንጋገር፣ ማንኛው ሰው  በእግዚአብሄር አምላክ የሚፈጠር ሲሆን ብሄረሰብ በራሱ ተፈጥሮአዊ ሳይሆን የተወሰኑ ሰዎች በአንድ አካባቢ ሲኖሩና የተወሰነ የሚያስተሳስራቸው ባህል ነክ ነገሮች ሲፈጥሩ  ከሌሎች የሚለዩ መሆናቸውን የሚገልጽ አንዳች የብሄረሰብ ስም ይሰጡታል። ይሁንና በጎሳ መልክ የሚገለጽ የሰው ቁጥር በዚያው ተወስኖ የሚቀር አይደለም። ተወስኖ የሚቀር ከሆነ የማሰብ ኃይሉን ለማንቀሳቀስ የማይችልና ራሱን ከሌላው ሻል ብሎ ከሚገኘው ማህበረሰብ ጋር በንግድም ሆነ በስራ-ክፍፍል ለመገናኘት ያልፈለገ እንደሆን ብቻ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ እንደዚህ ዐይነቱ ሰው ውስጣዊ ፍላጎት የሌለውና፤ የተወሰኑ ነገሮችንም እየተመገበ የሚኖር ብቻ ነው። በአሁኑ በዘመነ-ግሎባላይዜሽን ዘመን ራሳቸውን ከሌላው የማህበረሰብ ክፍል አግልለው የሚኖሩ ጎሳዎች በተወሰኑ አገሮች የሚኖሩ ብቻ ናቸው። እነዚህ ዐይነት ጎሳዎችቭ ደግሞ መንፈሳቸው የረጋና ሌላውን እንግዳ ነው ብለው የሚገምቱትን የማይገድሉ ወይም የሚያባርሩ አይደሉም። እንደዚህ ዐይነቱ ሌሎች ጎሳዎችን መጤ እያሉ ማፈናቀል፣ ማሳደድና አሰቃቂ በሆነ መንገድ መግደል በእኛ አገር ብቻ በአሁን በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ጎልቶ የሚታይ አጸያፊ ተግባር ነው። ይህንን ደግሞ የሚያደርጉት አብዛኛዎቹ ብሄረሰቦች ሳይሆኑ፣ ከአሮሞና ከትግሬ የተውጣጡና ወደ አውሬነት የተለወጡ ኤሊቶች ናቸው። የያዙትን መሬትና ተፈጥሮን በጠቅላላው የፈጠሯቸው ይመስል በእህቶቻቸውና በወንድሞቻቸው፣ እንዲሁም በህጻናትና በልጆች ላይ ግድያ በመፈጸም መቆሚያና መቀመጫ ለማሳጣት በቅተዋል። ይህ ዐይነቱ አረመኒያዊ ተግባር እስከ ህንድ ድረስ በመሰማቱ አገራችንን በጣም ኋላ-ቀርና ሰው በላ ሰዎች የሚኖሩባት አገር ናት በማለት ሲጠሩ ይሰማል።

ለማንኛውም እስላም በኢትዮጵያ በመባል የሚታወቀውና በትርሚንግሃም የተጻፈው መጽሀፍ(J.Spencer Trimingham; Islam in Ethiopia) በመሰረቱ የሚያትተው ስለ እስላም ሃይማኖት መስፋፋት ሳይሆን፣ አብዛኛው አትኩሮው ስለኦሮምዎች መስፋፋትና ሌሎች ሻል ብለው ይገኙ የነበሩ አገዛዞችንና የአኗኗር ስልቶችን በመዋጥ የራሳቸውን ቋንቋ በመጫን እንዴት እንደጨፈለቋቸው ነው። በዚህ መጽሀፍ አገላለጽም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ውድመትን ያስከተሉት አማራዎች ሳይሆኑ የኦሮሞ የጎሳ መሪዎች ናቸው። ኦሮሞ የሚባለው ጽንሰ-ሃሳብ ከየት እንደመጣና ትርጉሙም ምን እንደሆነ በፍጹም አይታወቅም። ለምሳሌ አማራ ማለት የተራራ ላይ ኗሪ ሰዎች በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ ኦሮሞ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ አይደለም። እንደሚባለው ከሆነ ኦሮሞ የሚባለው መጠሪያ በአንድ የጀርመን የቅኝ-ግዛት አቀንቃኝ እንደተሰጠ ነው የሚታወቀው። ምክንያቱም ኦሮሞዎች በመጀመሪያ መጠሪያ ስማቸው ጋላ በመባል በሚታወቀው ለመጠራት ባለመፈለጋቸው የተነሳ ነው። ይሁንና ግን ጋላ የሚባለው አጠራር በሶማሌዎች ለኦሮሞዎች የተሰጠ ሲሆን፣ ትርጉሙም እንግዳ ወይም ከሌላ ቦታ የመጣ ማለት ነው። ምክንያቱም ኦሮምዎች ከሌላ ቦታ በመምጣት ከሶማሌዎች ጋር ግኑኝነት በመፍጠራቸው ነው። የቦረናው ኦሮሞ የሆነው ፕሮፈሰር ጉፉ ኦባ(Prof. Gufu Oba) „Nomads in the Shadows of Empires“ በሚለው በጣም ግሩም መጽሀፉ የሚያረጋግጠው ጋላ የሚለው ስም የማንቋሸሺያ መጠሪያ ሳይሆን በሶማሌዎች የተሰጠ መሆኑን ነው። ያም ሆነ ይህ እስከ 19ኛው ክፍለ-ዘመን ድረስ ኦሮምዎች በተሻለ የአኗኗር ስልትና የስራ-ክፍፍል የሚገለጽ ማህበረሰብ እንዳልነበራቸው የሚታወቅ ጉዳይ ነው። አብዛኛው የኦሮሞ ማህበረሰብም በከብት እርባታ የሚተዳደር ስለነበር ከዚህ በመላቀቅ ሻል ያለ የስራ-ክፍፍል በማዳበር ወደ ንግድ ልውውጥና የገበያ ኢኮኖሚ በመሸጋገር የተሻለ ማህበረሰብ ለመመስረት የቻለ አልነበረም። ይህ ዐይነቱ ኋላ-ቀርነት በሌሎች የአገሪቱ ግዛቶችና በአማራውም ክፍል የነበረና የሚታይ  ጉዳይ ነው። ይሁንና ሌሎችን ከኦሮሞዎች ለየት የሚያደርጓቸው ተቀማጭ በመሆን ዋናው የኑሮአቸው መሰረት እርሻ እንደነበር ይታወቃል።

ለማንኛውም በኦሮሞ ኤሊቶች ከሳይንስና ከህብረተሰብ ዕድገት ወጭ የሚተረከው የተሳሳተ አባባል አፄ ምኒልክ በመስፋፋተቸው ነው ስልጣኔያችን ሊፈራርስ የቻለው የሚለው አነጋገርና አፃፃፍ ሳይንሳዊ መሰረት የሌለውና በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ግንባታ ታሪክ ውስጥም በፍጹም ሊረጋገጥ የሚችል አይደለም። አፄ ምኒልክ እስከተስፋፉበት ጊዜ ድረስም ቢሆን ከሌላው ጋር በመጋባት የተቀላቀለው ኦሮሞ እስካልሆነ ደረስ አብዛኛው የኦሮሞ ጎሳ በእርሻ የሚተዳደርና፣ ተቀማጭ በመሆን የስራ-ክፍፍልን በማዳበር በንግድ ግኑኝነትና በገንዘብ አማካይነት የሚገለጽ ማህበረሰብ ለመመስረት የቻለ አይደለም። እንደሚታወቀውና ፈላስፋዎችና የአንትሮፖሎጂ ምሁራን እንደሚያስተምሩን ከሆነ አንድ ማህበረሰብ በዕድገት(Progressive) የሚገለጽ ነው:: ይሁንና ማንኛውም ማህበረሰብ ወይም ህዝብ ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ ሊሸጋገር የሚችለው ከሌሎች ጋር ሲዋሃድ፣ ሲጋባ፣ ከሌሎች ሲማርና የተማረውን ወይም የኮረጀውን ሲያሻሽል ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ ሂደት የአብዛኛው የሰው ልጅ ዕድገት ታሪክ ነው።

 

አፄ ምኒልክ ወደ ደቡቡ ክፍል ሲስፋፉ በጊዜው በነበረው ውስን ሁኔታ ወይም ዕድገት ያለመኖር ሁኔታ፣ የተማረ የሰው ኃይል አለመኖር፣ ፈላስፋዎችና ሳይንቲስቶች አለመኖር፣ በአጭሩ የነበራቸው የማህበረሰብ መሰረት ያልተማረና ያልተገለጸለት ስለነበር የህብረ-ብሄር አመሰራረቱና ኢትዮጵያን ዘመናዊ የማድረጉ ጉዳይ እሳቸው በፈለጉትና በተመኙት መንገድ ሊሄድ አልቻለም። የግዴታ ሆኖ በነበረው የስልጣን አደላደል የተነሳ ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ለየት ባለ መልክ ፊዩዳላዊ ስርዓት ሊፈጠር ችሏል። በሌላ አነጋገር፣ በደቡቡ ክፍል ርስትና ጉልት የሚባሉ የመሬት አደላደሎች በፍጹም አይታወቁም። ስለሆነም በሰሜኑ የፊዩዳል ስርዓትና በደቡቡ መሀከል ከፍተኛ ልዩነት አለ። አፄ ምኒልክ ግዛታቸውን ወደ ደቡቡ ክፍል ሲያስፋፉ አብዛኛው መሬት ጠፍ ወይም ያልለማ ስለነበር፣ ወይም የእርሻ ተግባር የሚከናወንበት ስላልነበር ነፍጠኛ የሚባሉት መሬት ሲሰጣቸው ከይዞታው የተፈናቀለ የየአካባቢው ኗሪ ህዝብ በፍጽም አልነበረም። በመሰረቱ ነፍጠኛ በመባል የሚወነጀሉት ሰዎች ወደ ደቡቡ ክፍል ሲላኩ አካባቢውን እንዲያስተዳድሩና እንዲያለሙ ብቻ እንጂ ከመጀመሪያውኑ በኗሪዎች ላይ የራሳቸውን ቋንቋና ባህል ለመጫን አልነበረም።  በሌሎችም አገሮችም እንደታየው በዚህ ዐይነቱ አዲስ የአገዛዝ መዋቅር መስፋፋትና የአመራረት ስልት መዳበር የተነሳ የአማርኛ ቋንቋና ልዩ ልዩ ባህሎች በኗሪው ህዝብ ዘንድ ሊወሰዱ ችለዋል። ይህ ጉዳይ ታዲያ እንደ መጥፎ ነገር ወይም የሌሎችን ቋንቋና ባህል እንደመጨፍለቅ መታየት ያለበት ሳይሆን በራሱ ውስጣዊ ኃይል ለመዳበር በመቻሉና ሻል ብሎም በመገኘቱ ብቻ ነው። በሌላ ወገን ግን  አፄ ምኒልክ በጊዜው የነበረውን በእነ አባጅፋር የሚካሄደውን የባሪያ ንግድና ጭቆና ለማስቀረት ችለዋል። ከዚህም በላይ ጨቋኝና በመደብ የተደራጀው የገዳ ስርዓት ሳይወድ በግድ እንዲፈርስ ለመደረግ በቅቷል። እነ አቢይ አህመድና ሌሎች የኦሮሞ ኤሊቶች  እንደሚነግሩን የገዳን ስርዓት ዲሞክራሲያዊና እኩልነት የሰፈነበት ስርዓት ሳይሆን ጭቆና የተስፋፋበትና የበለጠ በጦርነት የሚገለጽ “ስርዓት” እንደነበር የሚታወቅ ጉዳይ ነው። አንደኛ፣ በገዳ ስርዓት ውስጥ ማንኛውም ግለሰብ የመሳተፍ መብት የለውም። የተወሰኑ ስዎችን የሚያሳትፍና  በመደብ ላይ የተመሰረተ አገዛዝ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ሴቶች የመሬት ባለቤት የመሆን መብት የላቸውም። በሶስተኛ ደረጃ፣ ዘመናዊ በሚባሉ ዲሞክራሲያዊ አሰራሮች የሚገለጽ ስላልነበር ለሳይንስና ለቴክኖሎጂ ዕድገት፣ እንዲሁም ለሌሎች የፈጠራ ስራዎችም የሚያመች አልነበረም። ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ መሰረቱም ምን እንደሆነ በፍጹም አይታወቅም። በእነ ፍሪድሪሽ ኤንግልስ አተናተን መሰረት እንደዚህ ዐይነቱ ስርዓት ኋላ-ቀር ናቸው በሚባሉ ማህበረሰቦች ውስጥ የነበረ የአኗኗር ዘዴ ነው። ዋናው ተግባሩም ጦርነትን ማካሄድና ሌሎችን በማሸነፍ የሚገለጽ እንጂ ስልጣኔን አፍላቂና ስልጣኔን አስፋፊ አይደለም። ከዚህ ሀቅ ስንነሳ ዛሬ ኦሮሚያ ክልል ተብሎ የሚጠራው ሌሎችን በማፈናቀል ወይም ከራስ ጋር በማዋሃድ በኃይል የተወሰደ ቦታ ከመጀመሪያውኑ ኦሮሞ በመባል የሚጠራው ጎሳ መኖሪያ አልነበረም። የገዳ ስርዓትም ኋላ-ቀር ስለነበር የአገዛዝ መዋቅር አልነበረውም። ስለሆነም ስርዓቱ በዘመናዊ ኢንስቲቱሽንና በቢሮክራሲያዊ አሰራር ዘዴ የሚተዳደር እንዳልነበር ነው ታሪኩ የሚያረጋግጠው። ዛሬ የኦሮሚያ ክልል ተብሎ የሚጠራው ክፍል የሀዲያዎች፣ የከንባታዎች፣ የጃንጀሮዎችና የየም ኗሪዎች ቦታ የነበረና በኦሮሞ ወራሪዎች የተነጠቀ ነው። ስለዚህም ኦሮሞዎች መልሰው ሌላውን መጤ እያሉ የሚያሳድዱበት ምክንያት በፍጹም ሊኖር አይችልም፤ መብትም የላቸውም። ኦሮሚያ በመባል አርቲፊሻል ስም የተሰጠው ቦታ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላው ኢትዮጵያ የጠቅላላው ኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት ነው።፡ቀደም ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት ኦርሞዎች ከመስፋፋታቸው በፊት ከአስራአራተኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ አንዳንድ አማራዎች በደቡቡ ክፍል እየተላኩ ሃይማኖትን ያስተምሩና፣ እዚያውም በመቅረትና በመጋባት እንደተዋሃዱ የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ዛሬ ኦሮሚያ ተብሎ የሚጠራው ክፍል ቀደም ብሎም ሆነ ኋላ ላይ በአማራዎችና በሌሎች የብሄረሰብ ኗሪዎች ይለማ እንደነበር፣ በተለይም አፄ ምኒልክ ግዛታቸውን ሲያስፋፉ በዚያው መጠንም የእርሻ ስራና ልዩ ልዩ የሰብል ዐይነቶች ሊስፋፉና አነሰም በዛም የስልጣኔ መሰረት ሊሆን እንደቻለ የሚታወቅ ጉዳይ ነው።

 

ስለሆነም የኦሮሞ ኤሊቶች ትረካ ሳይንሳዊ መሰረት የሌለውና በታሪክም የሚረጋገጥ አይደለም። በሌላ ወገን ደግሞ የግዴታ የገዳን ስርዓት መመለስ አለብን ብለው የሚታገሉት እነ አቢይ አህመድና ሺመልስ አብዲሳ፣ እንዲሁም ሌሎች የኦሮሞ ኤሊቶች በመኪና ከመሄድ ይልቅ በፈረስ መጋለብ አለባቸው። በቪላ ቤትና በቤተ መንግስት ውስጥ ከመኖር ይልቅ በጎጆ ቤቶች ውስጥ መኖር አለባቸው። በተጨማሪም ሌሎች ብሄረሰቦች የፈጠሯቸውን እንደ እንጀራና ወጥ፣ እንዲሁም ጠጅና ጠላ መብላትና መጠጣት የለባቸውም። ስለሆነም ባህላችን ነው፣ ይህንን ነበር ስንመገብና ስንጠጣ የነበርነው የሚሏቸውን ነገሮች መመገብ አለባቸው። በአጭሩ ዘመናዊ ከሚባሉ የአኗኗር፣ የአመራረትና የፍጆታ አጠቃቀም ዘዴዎች በሙሉ በመላቀቅ ወደ ኋላ ተጉዘው የገዳን ስርዓት መመስረት ይችላሉ። ይህንን ለማድረግ ከፈለጉ ደግሞ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ ሳይሆን ሌላ ቦታ መፈለግ አለባቸው። ምክንያቱም ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ የአመራረትና የአኗኗር ዘዴን ስለሚመኝና፣ በአርትስ፣ በቆንጆ ቆንጆ ከተማዎች የሚገለጽ ማህበረሰብ በመመስረት ሰው መሆኑን ለማረጋገጥ ስለሚፈልግ ነው። ስለሆነም የዚህ ዐይነቱ የስልጣኔ መሰረት ገዳ ሳይሆን. ፍልስፍናና ሳይንስ፣ ኢኮኖሚክስና ሶስዮሎጂ፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ የህብረተሰብን ችግር መፍቻ ዕውቀቶች ናቸው።       

 

የካፒታሊዝም መግባትና የብሄረሰብ ጥያቄ መነሳት!

የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎች በአገራችን ውስጥ ነበር ስለሚባለው የብሄረሰብ ጭቆና ሲያወሩ የካፒታሊዝም ወደ አገራችን መግባት የፈጠረውን አዲሱን የህብረተሰብ አወቃቀርና፣ ህዝባችን በብሄረሰብ ሳይሆን በመደብ የተከፋፈለ ህብረተሰብ(Social Differentiation) መሆኑን በደንብ ለመመርመር የቻሉ አልነበሩም። ሰለመደብ መኖር ቢያወሩም፣ በጊዜው የነበረው ጭቆና አጠቃላይና፣ አንደኛውን ብሄረሰብ ከሌላው ብሄረሰብ ሳይነጠል በሁሉም ላይ የሰፈነ መሆኑን በፍጹም የተገነዘቡ አልነበሩም። በሌላ አነጋገር፣ የተማሪው እንቅስቃሴ መሪዎችና የብሄረሰብ አቀንቃኞች ስለማህበረሰብ ሳይንስ(Sociology) የነበራቸው ግንዛቤ ወይም ዕውቀት ይህ ነው የሚባል አልነበረም። ከዚህም ባሻገር ካፒታሊዝም በምን መልክ እንደገባና የራሱ የሆነ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደነበረው የጻፉትና የሚያውቁት ነገር የለም ብል የምሳሳት አይመስለኝም። እንደምገምተው ከሆነ ከ1960ዎች ዓመታት ጀምሮ በተለይም በምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮች ይካሄድ በነበረው ስለህብረተሰብ ለውጥና(Transformation Debate)፣ በአንትሮፖሎጂና በፍልስፍና ዙሪያ በሚደረገው ክርክርና ጥናት ውስጥ የተሳተፉ አልነበሩም። በአብዛኛዎች የሶስተኛው ዓለም አገሮች ስለሚታየው ያልተስተካከለ ዕድገት(Unequal Development) ዋናው ምክንያት ምን እንደሆነ የሚያውቁት ነገር ያለ አይመስለኝም። ስለሆነም ካፒታሊዝም ወደ አገራችን ምድር ሲገባ በደንብ ተጠንቶ ተግባራዊ ባለመሆኑና ውስጣዊ ኃይሉም ደካማ ስለነበር  ያልተሰተካከለ ዕድገት(Uneven Development) እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ ጠጋው ብለው ለመመርመር የፈለጉና የታያቸውም አልነበረም። የፖለቲካ ትግላቸውንም ሲጀምሩ ከፍልስፍናና ሰፋ ካለ የህብረተሰብ ሳይንስ አንፃር መሰረት አድርገው ባለመነሳታቸውና በአወቅኹኝ ባይነት ወደፊት በመገስገሳቸው የህብረተሰብአችንን አወቃቀር ደረጃ በደረጃ ለማጥናትና ለመመርመር በፍጹም አልቻሉም። ቢያንስ የራሺያ ማርክሲስቶች እንዴት ያጠኑና ይከራከሩ እንደነበርና፣ ሌኒንም የጻፈውን ትልቅ መጽሀፍ፣ The Development of Capitalism in Russia“ የሚለውንና፣ ታላቁ የግብጽ ኢኮኖሚስትና የህብረተሰብ ሳይንስ ተመራማሪ የነበረውን የፕሮፌሰር ሳሚር አሚንን መጽሀፍ፣ Accumulation on a World Scale: A Criticque of the Theory of underdevelopment“ እና ሌሎችንም ስለ ዓለም አቀፋዊ ካፒታሊዝምና ስላልተስተካከለ ዕድገት የተጻፉ አያሌ መጽሀፎች ጋር ትውውቅ ቢኖራቸው ኖሮ የብሄረሰብን ጥያቄ በሌላ መልክ ለማየትና ለመተንተን በቻሉ ነበር። ከዚህም ባሻገር አውሮፓና አሜሪካ ከኋላ-ቀር ስርዓት፣ በተለይም አውሮፓ ከፊዩዳሊዝም ወደ ካፒታሊስት ስርዓት እንዴት እንደተሸጋገረና፣ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለሽግግሩ የሚያመቹ ቅድመ-ሁኔታዎች ተግባራዊ ለመሆን እንደቻሉና፣ የኋላ ኋላ ደግሞ ካፒታሊዝም ዓለም አቀፋዊ ባህርይ እንዴት ለመያዝ እንደቻለ በቂ ጥናትና ምርምር ቢደረግ ኖሮ ስለአገራችን የህብረተሰብ አወቃቀርና የህብረ-ብሄር ግንባታ አስቸጋሪነት የተሻለ ግንዛቤ ሊኖራቸው በቻለ ነበር። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም ሰፋ ያለ ዕውቀት፣ የከተማዎችና የመንደሮች መገንባት ለህብረ-ብሄር ግንባታ ያላቸውን ከፍተኛ ሚናና አሰተውፆ ግንዛቤ ውስጥ ቢያስገቡ ኖሮ የብሄረስብን ጥያቄ አጉሎተው ባላሳዩ ነበር። ቀደም ብሎም ሆነ የኋላ ኋላ በ1950ዎቹና 60ዎቹ ዓመታተ የነበረውን የአገራችንን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ሁኔታ ወደ ኋላ መለሰ ብለን በምንመረምርበት ጊዜ የህብረተሰብአችንን አወቃቀርና እንደ አገር መገንባት ጉዳይ የቱን ያህል አስቸጋሪ እንደነበር መገንዘብ በታቸለ ነበር። ለማንኛውም ከ1950ዎቹ በኋላ ይታዩ የነበሩ ድህነትና የኋላ ኋላ ደግሞ የረሃብ መከሰት ጉዳይ፣ በአገሪቱ ያልተስተካከለ ዕድገት መታየት፣ አብዛኛው ህዝብ ከዕውቀት የራቀ መሆኑና አቅመ-ቢስ እንዲደረግ መደረጉ፣ የብሄረሰብ ጭቆናን መኖር የሚያሳይ ሳይሆን የተለያዩ ስርዓቶች በመጣመር ለዕድገት እንቅፋት እንደሆኑ መገንዘብ ይቻላል፡ ፕሮፌሰር ሳሚር አሚን በተለይም ስለ ዕድገትና ፀረ-ዕድገት እዚያው በዚያው መኖር ሲያብራራ እንደ አገራችን በመሳሰሉ ኋላ-ቀር ስርዓት ባላቸው አገሮች  ውስጥ ኋለ-ቀር የአመራረት ስርዓት ዘመናዊ ከሚባለው ጋር በሚገናኝበት ጊዜ ዕድገትን አምጭ ሳይሆን የተዘበራረቁ ስርዓቶች እንደሚፈጠሩ ነው። በዚያው መጠንም የተገለጸለት የህብረተሰብ ክፍል ሳይሆን የሚፈጠረው የተዘበራረቀ ሃሳብ ያለውና የሚያደርገውን የማያውቅ የህብረተሰብ ክፍል በመፈጠር በራሱ ፀረ-ዕድገት ኃይል ይሆናል። ለማንኛውም የተማሪው እንቅስቃሴ ደብዛው ከጠፋና አብዮቱም ከከሸፈ በኋላ ከላይ በጠቀስኳቸው መሰረታዊ ነገሮች ላይ አሁንም ቢሆን ጥናቶችና ክርክሮች ሲካሄዱ በፍጹም አይታይም። በጥብቅ እንደምክታተለው ከሆነ ፖለቲካዊ ውይይቶች ከዕውቀት፣ ከቲዎሪ፣ ከሳይንስና ከፍልስፍና ጋር በመያያዝ ክርክር ስለማይደረግባቸው በሁላችንም ዘንድ ግራ መጋባት ይታያል። ስለሆነም ስለህብረተሰብ አገነባብና፣ አንድ ማህበረሰብ እንዴት እንደሚገነባና ምን ምን ዐይነት መሰረተቾና ቅድመ-ሁኔታዎች እንደሚያስፈልጉት በቂ ግንዛቤ እስከሌለን ድረስ  ከተጨባጩ ሁኔታዎች የራቁ ሀተታዎች በመስጠት የባሰውኑ ውዥንብር ለመንዛት እንገደዳለን ማለት ነው።

ያም ሆነ የካፒታሊዝም በአገራችን ምድር መግባት በአንድ በኩል ህብረተሰብአዊ መሰበጣጠርን(Social Differentiation) ሲፈጥር፣ በሌላ ወገን ደግሞ በአንድ በኩል ዕድገትን፣ በሌላው ወገን ደግሞ ባልተስተካከለ ዕድገት የሚገለጽ ሁኔታን ሊፈጥር ችሏል። የፋብሪካዎች መቋቋምና ንግድ መስፋፋት፣ በተለይም የዘመናዊነት መገለጫ የሆኑ የፎቅ ቤቶች መሰራትና መስፋፋት፣ የዘመናዊነት መገለጫ የሆነ የፍጆታ አጠቃቀምና የአኗኗር ስልት፣ የመኪናዎች መግባት፣ የቲያትርና የሲኒማ ቤቶች መቋቋም፣ በዘመናዊ መሳሪያዎች ሙዚቃን መጫወት፣ ከአገር ባህል በተለየ መልክ አዳዲስና ደስ የሚሉ ዘፈኖችን መቃኘትና መዝፈን፣  የትምህርት ቤቶች መሰራትና የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲ መቋቋም፣ እንዲሁም በአንዳንድ ቦታዎች የዕደ-ጥበብ ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት መስፋፋት፣ እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ የኢንዱስትሪውንና የንግዱን ዘርፍ በገንዘብ አማካይነት ማገናኘትና፣ ከዐይነት በዐይነት የንግድ ልውውጥ ይልቅ በገንዘብ አማካይነት መገበያየትና፣ ገንዘብ አንደኛው የሀብት መተመኛና ማስቀመጫ ዘዴ መሆኑ፣ ወዘተ. …፣ እነዚህ ነገሮች በሙሉ ሊያያዙ የሚችሉት ከካፒታሊዝም ወደ አገራችን ምድር ከመግባት ጋር ነው። ይህንን ዐይነቱን መተሳሰርና የሂደት አዝማሚያ ማንኛውም ማህበረሰብ ሊያመልጠው የሚችለው ጉዳይ አይደለም። በሌላ ወገን ደግሞ  ካፒታሊዝም ወደ አገራችን ከመጣ በኋላ አንዳንድ ከዕድገትና ከመሻሻል ጋር የሚያያዙ ነገሮች ቢፈጠሩም፣ ከዕውቀት ማነስ የተነሳ በውስን መልክ የገባው ካፒታሊዝም የህብረተሰብአችንን አወቃቀር መሰረታዊ በሆነ መልክ አልቀየረውም። ይህንን ጉዳይ ከጃፓኑ፣ ከደቡብ ኮሪያው፣ ከታይዋኑ፣ ከሲንጋፖርና፣ አሁን ደግሞ ከቻይናው የኢንዱስትሪና የቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር ማነፃፀር ይቻላል። በእነዚህ አገሮች ውስጥ ተግባራዊ የሆነው የኢንዱስትሪ ፖለቲካ ከሞላ ጎደል ለተስተካከለ ዕድገት አመቺ ሁኔታን የፈጠረ ሲሆን፣ ወደ እኛ አገር የገባው  ካፒታሊዝም  ከተስተካከለ ዕድገት ይልቅ ያልተሰተካከለ ዕድገት እንዲፈጠር ለማድረግ በቅቷል። በተለይም ይህ ጉዳይ በከተማዎችና በገጠሩ ህዝብ የአኗኗር ሁኔታ የሚገለጽ ሲሆን፣ በካፒታሊዝም መግባት የተነሳ በጊዜው ከነበረው ወደ ሰላሳ ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ 5% የሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል ብቻ ነበር ተጠቃሚ ለመሆን የቻለው። ይህም ማለት ከብሄረሰብ ልዩነት ባሻገር 95% የሚሆነው ህዝባችን ወደ አገራችን በገባው ካፒታሊዝም ምክንያት የተነሳ ተጠቃሚ ሊሆን አልቻለም ማለት ነው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ ውስጣዊ-ኃይል የሌለው ካፒታሊዝምና በተወሰኑ አካባቢዎች የተተከሉት ኢንዱስትሪዎችና የከተማ ግንባታዎች-በመሰረቱ በአዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የቀረ፣ ይህም ቢሆን በአዲስ አበባ ውስጥ በተወሰኑ ቦታዎች የሚታይ ዘመናዊነት- የብሄር-ጭቆና የሚለውን የተሳሳተ ትረካ ጎልቶ እንዲወጣ ሊያደርገው ችሏል።

በዚህ ዐይነቱ ያልተስተካከለ ዕድገት በተለይም አማራው የተጎዳ ቢሆንም´፣ በተሳሳተ መልክ በመተርጎም አማራው እንደ ተጠቃሚና እንደ ጨቋኝ የህብረተሰብ ክፍል ሊታይ ችሏል። ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ የኢትዮጵያን ህብረተሰብ አወቃቀር በደንብ ለተከታተለ በበጋ ጊዜ ለቡናና ለሌሎች ሰብሎች ለቀማ በሚል(Seasonal Worker) ከጎንደር፣ ከጎጃም፣ ከወሎና ከትግሬ ወደ ደቡቡ ክፍል የሚዘምተው አብዛኛው የአማራው ብሄረሰብ ተወላጅ ነበር። ያልተስተካከለ ዕድገትም በድንብ ጎልቶ ይታይ የነበረው በአማራው ክፍል እንጂ፣ ኦሮሞዎችና ሌሎች ብሄረሰቦች በሚኖሩበት ክልል አልነበረም። በተለይም ረሃብ በየጊዜው የሚከሰተው በአማራው ክልል፣ በተለይም በወሎ ክፍለ-ሀገር እንጂ ኦሮሞዎችና ሌሎች ብሄረሰቦች በሚኖሩበት የደቡቡና የምስራቅ ደቡቡ ክፍል አልነበረም። ታዲያ በምን ተዓምር ነው አማራው በጋርዮሽ ጨቋኝ ሊሆን የሚችለው?  ይህንን ´ጉዳይ እስካሁን ድረስ ማንም ምሁር ግልጽ ለማድረግ ወይም ለማብራራት በፍጹም አልቻለም።  ለማንኛውም አማራውን እንዳለ እንደ ጨቋኝ መደብ አድርጎ መወሰዱ ይኸው ዛሬ እንደምናየው በጥሩ ሁኔታ የሚኖረው አማራ ሳይሆን የሚገደለው፣ የሚፈናቀለውና የሚሰቃየው ደሀውና በስንት ጥረትና ድካም እያረሰ ሰፊውን ህዝብ የሚመግበው ደሃው አማራ ነው።

ለማንኛውም በኢንዱስትሪዎች መቋቋም የተነሳ፣ በንግድ መስፋፋትና በባንኮችና በመድህን መስሪያቤቶች መቋቋም ምክንያት ልዩ ዐይነት የህብረተሰብ ክፍል ሊፈጠር ችሏል። አንዳንዶች ይህንን በመደብ የተከፋፈለ ነው ብለው ሲጠሩት፣ ሌሎች ደግሞ በገቢ በመከፋፈል(Income Groups) የተለወጠውን ሁኔታ ለመግለጽ ይሞክራሉ። ይህ ዐይነቱ ህብረተሰብአዊ ለውጥም የሚያረጋገጠው ማንኛውም ማህበረሰብ በአንድ የተወሰነ ስርዓት ላይ ቆሞ እንደማይቀር ነው። ከዚህ ሁኔታ ስንነሳ ከሁሉም ብሄረሰብ የተውጣጡ በፋብሪካ ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ነበሩ፤ ዛሬም አሉ። በባንክና በሌሎች የአገልግሎት መስጫ ድርጅቶች፣ እንዲሁም በመንግስት መስሪያ ቤትም፣ ይኸኛው ወይም ያኛው ብሄረሰብ ብቻ መቀጠር አለበት ሳይባል ተቀጥሮ የመስራት ዕድል ነበራቸው።  አንዳንድ ግለሰቦች ከዚህ ብሄረሰብ የመጣህ ነህ፤ ስለሆነም የመቀጠር መብት የለህም በሚል የተመለሰ አልነበረም። ማንኛውም ስራ ለመቀጠር የሚፈልግ፣ የስራ ቦታ እስካለና ማስታወቂያ እስከወጣ ድረስ በዕውቀትና በችሎታ እንዲሁም በስራ ልምድ ነበር የሚቀጠረው። በሌላ አነጋገር፣ አንተ ከትግሬና ከኦሮሞ ብሄረሰብ የመጣህ ስለሆንክ የመቀጠር መብት፣ ወይም ሚኒሰተር የመሆን መብት የለህም ተብሎ የተባረረ በፍጽም አልነበረም። የአገዛዙም ፍልስፍና ይህ አልነበረም። የኦሮሞ ወዝአደር የነበረውንና ያለውን ያህል፣ ከአማራውና ከሌላው ብሄረሰብ የተውጣጣ እንዲዘሁ አለ። የኦሮሞ ነጋዴና የከበርቴ መደብ ያለውን ያህል፣ ከአማራውና ከጉራጌውም የተውጣጣ አለ። ስለሆነም የአማራው ከበርቴ የሚጋባው፣ የሚበላውና የሚጠጣው፣ እንዲሁም ወደ ዋና የሚሄደው፣ በየቡናቤቶች በመገናኘት የሚዝናናው ከተመሳሳዩ ከኦሮሞና ከትግሬ ከበርቴ ጋር እንጂ፣ ከአማራውና ከኦሮሞው፣ እንዲሁም ከትግሬው መስኪን ደሃ ገበሬና ሰራተኛ ጋር አይደለም።

ከዚህ ሀቅ ስንነሳ የብሄረሰብ ጭቆና መኖር ከአለአግባብ የተነሳና ከሁኔታው ጋር የሚያያዝ አይደለም። የኋላ ኋላ ከተማሪው መሪዎች ቀበል አድርገው ማራገብ የጀመሩት የትግሬና የኦሮሞ ኤሊቶች ሻል ካለ የህብረተሰብ ክፍል የተውጣጡና  ዩኒቭርሲቲ በመግባትም የመማር ዕድል ያገኙ ነበሩ። የብሄር ጭቆና አለ ብለው አጉልተው ለማሳየት የሞከሩት በእርግጥም ነገሩ ገብቷቸውና፣ እንወክለዋለን የሚሉትን ሰፊውን ህዝብ ነፃ ለማውጣትና የኑሮውን ሁኔታ ለማሻሻል ሳይሆን የራሳቸውን ውስጣዊ ስሜት ለማሟላት ብቻ ነው። ከዝቅተኛ አስተሳሰብ በመነሳትና የራሳቸውን በልጦ የመገኘት አጀንዳ ተግባራዊ ለማድረግ ብቻ ነው የብሄረሰብ ጭቆናን አንስተው የፖለቲካ ሜዳውን ማጣበብ የጀመሩት።  አብዛኛዎች የትግሬ ኤሊቶች፣ በተለይም ህወሃትን የመሰረቱትም የባንዳ ልጆች እንደነበሩ ይታወቃል። የኦሮሞን መጨቆን ያነሱ የነበሩት ደግሞ ከጀርመንና ከሌሎች የአውሮፓ አገሮች የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ተቋማት ጋር  የጠበቀ ግኑኝነት የነበራቸውና በእነሱ የሚጠመዘዙና፣ በጀርመን የስለላ ድርጅት የሚደገፉና የሚመከሩ እንደነበር ይታወቃል።  በሌላ አነጋገር፣ በአገራችን ምድር የብሄር ጭቆና የሚሉት ፈሊጥ ይነሳ የነበረው ከደሃው ገበሬና ሰራተኛ የመነጨ አስተሳሰብ ሳይሆን በቅንጦት ደልቷቸው ይማሩ ከነበሩና፣ የኋላ ኋላ በየመስሪያቤቱ ተቀጥረው የመስራት ዕድል ካጋጠማቸው ውስጥ ነው። እነዚህ የብሄረሰብን መጨቆን ያራግቡ የነበሩና፣ ኋላ ደግሞ ስልጣን ላይ የመውጣት ዕድል ያገኙት ግለሰቦች በሺህ ድሮች ከኢምፔሪያሊስትና  ከአረብ አገሮች ጋር በጥቅም የተሳሰሩና የእነሱን አጀንዳ የሚያስፈጽሙ ናቸው። የጥቁር ህዝብ ጠላቶች የሆኑና በአጋጣሚ ወይንም የታሪክ ግዴታ ሆኖ በኢትዮጵያ ምድር የተወለዱና ያደጉ ናቸው። እነ አቢይና ሺመልስ አብዲሳም በልዩ እንክብካቤ ተይዘው ያደጉ የሚመስሉ እንጂ ከጭቁኑ ገበሬ እንዳልወጡ ሁኔታቸው ያረጋግጣል።

በአጠቃላይ ሲታይ የትግሬ ኤሊት ከኢምፔሪያሊስት ኃይሎች ጋር የተቆላለፈና የውክልና ጦርነት የሚያካሂድ ሲሆን፣ የኦሮሞ ኤሊቶች ደግሞ በጀርመን የስለላና የፕሮቴስታንት ሃይማኖት መሪዎች የሚደገፉና የቅንጦት ኑሮ የሚኖሩ ናቸው። የሚያካሂዱትም ጦርነት ኦሮሞን ነፃ ለማውጣትና የእያንዳንዱን ኦሮሞ ህይወት ለማሻሻል ሳይሆን በዚያው ቀጭጮ እንዲቀርና የውጭ ኃይሎች ተገዢ ሆኖ እንዲቀር ለማድረግ ነው።  እነዚህ የብሄረሰብ አቀንቃኞች አንድም ቀን ስራ ሰርተው አያውቁም፤ ሳይንሳዊ መጽሀፎችንም ጽፈው አያውቁም። ውስኪ በመጠጣትና የቅንጦት መኪናዎችን በመንዳትና፣ የኢምፔሪያሊስት ኃይሎችና የአረብ ቱጃሮች በሚከፍሏቸው ገንዘብ የተንደላቀቀ ኑሮ በመኖርና ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር በመመላለስ በአገራችንና በህዝባችን፣ እንዲሁም በጠቅላላው ጥቁር ህዝብ ላይ ጦርነት ያወጁ ናቸው። ለምሳሌ ጀዋር ኢትዮጵያ ከመጣ በኋላ ስድሳ ሚሊዮን  የኢትዮጵያ ብር የሚያወጣ ቪላ ቤት ለመስራት በቅቷል። የተንደላቀቀ ኑሮም ይኖራል። አሁን ደግሞ አሜሪካና አውሮፓ ድረስ በመምጣት ሳይንሳዊና ፍልስፍናዊ መሰረት የሌለው ነገር ይናገራል። ከሎጂክና ከሳይንስ ውጭ የሆኑ ነገሮችን ሲዘላብድ ይሰማል። በዚህ ዐይነቱ ምንም ዐይነት ፍልስፍናዊ መሰረት በሌለው የተበላሸ  አነጋገሩም እንደትልቅ ሰውና ፖለቲከኛ ሲከበር ይታያል። የሚያድረውና የሚበላውም በትላልቅ ሆቴልቤቶች ውስጥ ነው። ታዲያ ይህንን ሁሉ ገንዘብ ከየት አመጣው?  እንደ ጀዋር የመሳሰሉትን በፖለቲካ ስም ስንትና ስንት ወንጀል የሚሰሩትንና የውጭ ቅጥረኛ የሆኑትን ኃይሎች የሚቆጠጠር አገዛዝ ባለመኖሩ እንደፈለጋቸው ይወጣሉ፣ ይገባሉ። የገቢ ምንጫው ምን እንደሆነ የሚያጣራ መንግስት ስለሌለና ቀረጥም ስለማይከፍሉ በፖለቲካ ስም ወንጀል እንዲፈጽሙ መንግስታዊ ትዕዛዝ የተሰጣቸው ይመስላሉ። በአለፉት አራት ዐመታት አቢይን የሚያማክሩት ሌሎች የኦሮሞ ኤሊቶችም፣ በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም የሚደገፉና የእነሱን አገርን የመከፋፈልና፣ ወንድምን ከወንድምና እህትን ከእህት የሚያጫራሱና የእነሱን አጀንዳ ተግባራዊ የሚያደርጉ ናቸው። ዋና ዓላማቸውም በኢትዮጵያ ምድር በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽና የተረጋጋ ማህበረሰብ እንዳይመሰረት ማድረግ ሲሆን፣ በዚያው መጠንም በጦርነትና በበሽታ ምክንያት የህዝብ ቁጥር እንዲቀንስ ማድረግ ነው።  በአጭሩ ስልጣንን የተቆናጠጠው የኦሮሞ ኤሊትና፣ እዚህና እዚያ የሚዘላብደውና የጥላቻ ቅስቀሳ የሚያካሂደው ሌላው የኦሮሞ ኤሊት የጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች ብቻ ሳይሆኑ የጥቁር አፍሪካዊ ህዝብም ጠላቶች ናቸው። ጭቁኑ ህዝባችን በሳይንስና በቴክኖሎጂ የሚገለጽ ህይወት እንዳይኖርና አዲስ ማሀበረሰብ እንዳይመሰረት ለማድረግ በውስጥና በውጭ ኃይሎች የተሸረበ ሴራ ነው። ትግላቸውም ስልጣንን ተገን በማድረግ ድንቁርናንና ኋላ-ቀርነትን ማስፋፋት ነው።

አንድን ህዝብ ወይም ጎሳን ነፃ ለማውጣትና እያንዳንዱ ግለሰብ የራሱን ዕድል በራሱ እንዲወስን ለማድረግ ከተፈለገ የግዴታ ሰፋና ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያስፈልጋል። ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው ትግልና እንደአጋጣሚ ስልጣን ላይ መቆናጠጥ በራሳቸው አንድን ብሄረሰብ ዕውነተኛ ነፃነትን አያጎናጽፉትም። ማንኛውም ግለሰብ ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ ይወለድ ለመኖር ሲል የግዴታ መስራት አለበት። መስራት ሲችልና የተወሰነ ገቢ ሲያገኝ ብቻ ነው ራሱን መመገብና ቤተሰብም መመስረት የሚችለው። ማንኛውንም ፍላጎቶቹን ሊያሟላና እንደሰው ሊኖርና ሊታይ የሚችለው ሲሰራና በቂ ገቢ ሲያገኝ ብቻ ነው፡፡ በዕውቀትና በስራ አማካይነት ብቻ ነው ራሱን መግለጽ የሚችለው። እያንዳንዱን ዜጋ ራሱን እንዲችል ለማድረግ ደግሞ የግዴታ ሳይንሳዊ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። አብዛኛውን ህዝብ የሚያደኸይ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ እያደረጉ አንድን ብሄረሰብም ሆነ ግለሰብን ነፃ ለማውጣት በፍጹም አይቻልም። በወያኔ የ27 አገዛዝ ዘመን የተመለከትነው በኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ሰፊው የትግሬ ብሄረሰብ ከድህነት እንዳልተላቀቀና ራሱን እንዳልቻለ ነው። በአንፃሩ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የወያኔን ካድሬዎችና አመራሩን ነው የጠቀመው። እንደዚሁም እነአቢይ አህመድ ሳያውቁትና ሳይገባቸው ተግባራዊ የሚያደርጉት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሰፊውን ኦሮሞ ከቡና ተካይነትና ለቀማ፣ እንዲሁም ከአበባ ተካይነት በፍጹም አላላቀቀውም። አብዛኛው ኦሮሞ ዘመናዊ ከሚባሉ ነገሮች፣ ለምሳሌ የተሻለ ቤት፣ ትምህርትቤት፣ ንጹህ ውሃ፣ ህክምናና የተሟላ ምግብ ማግነት፣ ከእነዚህ መሰረታዊ ፍላጎች በጣም የራቀ ነው።  በአጭሩ ፍልስፍናዊና ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው ስልጣን አንዳንድ የብሄረሰብ ኤሊቶችን ከመጥቀም ሊያልፍ አይችልም። እንደነዚህ ዐይነት ኃይሎች  ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ፣ በአንድ በኩል የብሄረሰብን መጨቆን አጉልተው ያሳያሉ፣ በሌላ ወገን ደግሞ አገር አፍራሽ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመከተል እንወክለዋለን የሚሉትን ብሄረሰብ የባሰ ደሃ ያደርጉታል። ዋና ተግባራቸውም የኢምፔሪያሊስት ኃይሎች አሽከር በመሆን ጠቅላላውን የኢትዮጵያን ህዝብ ማድኸየትና አገራችንንም ወደጦርነት አውድማ መለወጥ ነው። ዛሬ የምናየው ይህንን ሀቅ ነው።

ከዚህ ሀተታ ስንነሳ የብሄረሰብ አቀንቃኝ ኃይሎችንና አጋሮቻቸውን፣ ኢምፔሪያሊስቶችንና አረቦችን መዋጋት የምንችለው በረቀቀ ዕውቀትና በተባበረ ክንድ ብቻ ነው። ባረጀ አስተሳሰብና በብሄረሰብ አካባቢ በመሰባሰብ ሳይሆን፣ ሳይንሳዊ አስተሳሰብን(Scientific Knowledge) ከጭንቅላት ጋር በማዋሃድና እሱን መመሪያ በማድረግ ብቻ ነው ጠንካራ አገር መመስረት የምንችለውና እያንዳንዱን ግለሰብ ነፃ ማውጣት የሚቻለው። በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ሳይንሳዊ ዕውቀት ባለመዳበሩ ምክንያት የተነሳ ሁልጊዜ ስንጨቃጨቅ እንገኛለን። በተለይም ለኢትዮጵያ አንድነትና የአማራውን መበደል፣ መፈናቀልና መገደል አንስተው የሚታገሉ ኃይሎች በአብዛኛው አመለካከታቸው ከሳይንሳዊ አስተሳሰብ የራቁ ናቸው። አብዛኛውን ነገር የሚመለከቱት በፍልስፍና፣ በሶስዮሎጂ፣ በሳይንስና  በስነ-ልቦና የሳይንስ መነፅር ሳይሆን  በቂ ግንዛቤ ሊስጠን ከማይችል ሁኔታ በመነሳት ነው የአገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ ለመረዳት የሚፈልጉት። አንዳንዶችም ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር በጥቅም የተሳሰሩ ሲሆን፣ አሜሪካን ገብቶ ያስታርቀን የሚሉ ናቸው። ይህም የሚያረጋግጠው እነዚህ ኢትዮጵያውያን ኃይሎች ከሃምሳ ዐመታት በላይ የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና የተቀረው የምዕራቡ የካፒታሊስት ዓለም ኢትዮጵያን ለመበታተን የተጫወተውን ሚና በደንብ ያልተከታተሉና ሊረዱም የሚፈልጉ አይደሉም።  በተለይም በአብዮቱ ወቅት በነጭና በቀይ ሽብር ስም ተሳቦ የተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ሲአይኤ በከፍተኛ ደረጃ እንደተሳተፈበት ለመቀበል አይፈልጉም። አሜሪካንን እንደ ቅዱስ ኃይል አድርገው ነው የሚቆጥሩት። ከአሜሪካ ውጭ ምንም ነገር ማድረግ የሚቻል አይመስላቸውም። በአብዮቱ ወቅት አሜሪካን ከወታደሩ ውስጥ ያሉ ኃይሎችን በመመልመልና በማሰልጠን ነው በአገዛዙ ዘንድ ጥርጣሬ እንዲፈጠር ለማድረግ የበቃው። ሶማሌን በማስታጠቅ እንድትወረን አድርጓል። ሻቢያና ወያኔ በከፍተኛ ደረጃ በሲአይኤ ይደገፉና ይታጠቁ እንደነበር ይታወቃል። ኢድህና አንዳንዶችም በማርክሲዝም ሌኒንዝም ስም ይምሉና ይገዘቱ የነበሩ በጊዜው ከአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጋር የጠበቀ ግኑኝነት እንደነበራቸው የማይታበል ሀቅ ነው። ስለሆነም ወጣቱን በማሳሳት ለከፍተኛ ዕልቂት ዳርገውታል። በአገራችንም ምድር ሰላም እንዳይመጣ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ አድርገዋል። ጉግማንጉግን እንዋጋለን በሚልና በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም በመመከርና በመደገፍ  በአገራችን ምድር ህዝቡ በጋርዮሽ ተነሳስቶ አገሩን በፀና መሰረት ላይ እንዳይገነባ ከፍተኛ እንቅፋት ለመፍጠር ችለዋል።  በደርግ ውስጥም ክፍፍል እንዲፈጠር በማድረግ አንዳንድ መኮንኖችና ጄኔራሎች እንዲገደሉ መንገዱን አመቻችተዋል። በተለይም በደርግ ውስጥ በተፈጠረው ቅራኔና አለመተማመን የተነሳ ነው ብዙ ነገሮች ሊዘበራረቁና ሊበላሹ የቻሉት።

ሌላው በደንብ ሳይመረመርና ሳይጠና ተቀባይነትን ያገኘው ጉዳይ ባለፉት አርባ ዐመታት በአገራችን ምድር ለተፈጠረው ቀውስና ዛሬ አገራችን ላለችበት አስቸጋሪ ሁኔታ ዋናው ምክንያት የግራን ቲዎሪ ወይም ማርክሲዝምን-ሌኒንዝምን አንግቦ የተነሳው የተማሪው እንቅስቃሴ መሆኑን አምኖ መቀብሉ ነው። ይህ ዐይነቱ በጥናትና በሰፊ ምርምር ላይ ሳይሆን በስሜት ላይ የተመረኮዘ አባባል እጅግ አሳሳችና በጣምም አደገኛ ነው። እንደዚህ ብለው የሚያወሩና የሚያምኑ ኃይሎችና ድርጅቶች ደግሞ በአሜሪካን ድጋፍ ስልጣን ላይ ለመውጣትና በሌላ መልክ የአሜሪካንን የኋላ-ቀር አስተሳሰብ ተግባራዊ ለማድረግ የሚፈልጉ ናቸው። እነዚህ ኢትዮጵያውያን ኃይሎች በአለፉት ሰባ ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተፈጠረውንና የተስፋፋውን፣ አገሮችን የማከረባበት እርኩስ ተግባር ያልተከታተሉና፣ በምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያልተሳተፉ ናቸው። ጭንቅላታቸውን ለምሁራዊ ክርክር ክፍት ያላደረጉና፣ አንድን ነገር በጥቁርና በነጭ በመሳል የሚያዩ ናቸው። የአገራችንን የተወሳሰበ ሁኔታና በተለይም በምሁሩ ዘንድ የነበረውን ከፍተኛ የግንዛቤ እጦት ቁጥር ውስጥ ያስገባ አስተሳሰብ አይደለም ያላቸው። እነዚህ ኃይሎችና ድርጅቶች ከመጀመሪያውኑ መሪ ለመሆን እንችላለን ብለው የሚገምቱና ካለአንዳች የፍልስፍናና የሳይንስ መሰረት ብዙ ተከታዮችን ለማፍራት የቻሉ ናቸው። በእነዚህ ግለሰቦችና ድርጅቶች ዕምነት እስከዛሬ ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተካሄደው ዕልቂትና በየአገሮች ውስጥ ለሚታየው ድህነት ተጠያቂው የማርክሲዝም ርዕዮተ-ዓለምና ሶሻሊዝም ናቸው የሚል ነው። ስለሆነም ይህን ተፈጥሮአዊ ያልሆነና የጉግማንጉን አስተሳሰብ መዋጋት አለብን በማለት ከአሜሪካን ጎን በመሰለፍ ብዙ የዋህ ኢትዮጵያውያንን በማሳሳት ላይ ይገኛሉ። በሌላ ወገን ግን በዚህ ጸሀፊ ዕምነት ለአገር የሚደረግ ዕድገት ከሳይንስና ከፍልስፍና አንፃር መታየትና መገምገም ያለበት ጉዳይ ነው። ይህ ሲሆንና ለአገር መገንቢያና ህብረተሰብን በፀና መሰረት ላይ ለማቆም የሚያመቸውን ነገር በቅጡ ከተገነዘብን ከሞላ ጎደል የርዕዮተ-ዓለም ውዝግብን ልንቀንሰው እንችላለን። መነሳት ያለበትም ጥያቄ፣ የትኛው ዐይነት ሳይንስና ፍልስፍና፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ ቲዎሪና የህብረተሰብ ሳይንስ ናቸው ለአገር መገንቢያ መሰረት ሊሆኑን የሚችሉት? የሚለው ጥያቄ ነው መነሳት ያለበት እንጂ  ብዙም ሳይገባን በነፃ ገበያና በሶሻሊዝም ዙሪያ የምናካሂደው ጭቅጭቅ ህብረተሰብአችንን ከድህነትና ከድንቁርና ሊያላቅቁት የሚችሉ አይደሉም። በተለይም በነፃ ገበያ ሽፋን ህዝብ የሚካሄደውን የምዕራቡን የካፒታሊስት አገሮች ሴራ ልንረዳና ልንዋጋ የምችለው በሳይንስና በፍልስፍና ስንታጠቅ ብቻ ነው። ስለሆነም በፍልስፍናና በሳይንስ መነጽር ብቻ ነው የአገራችንንም ሆነ የዓለም አቀፍ ሁኔታን መረዳት የምንችለው።

ያም ሆነ ይህ ሶሻሊዝምን ወይም ማርክሲዝምን-ሌኒንዝምን በዓለም ላይ ለተከሰቱት ችግሮች በሙሉዝ ተጠያቂ ማድረግ በቲዎሪም ሆነ በኢምፔሪካል ደረጃ የሚረጋገጥ ጉዳይ አይደለም አይደለም። ስልጣን ለመውጣት የሚፈልጉ ኃይሎች ርዕዮተ-ዓለምንም ሆነ ሃይማኖትን መሳሪያ በማድረግ በታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ወንጀል ፈጽመዋል። ድርጊታቸው በሙሉ ማርክስና ሌኒን፣ እንዲሁም ሌሎች ማርክሲስቶች ከጻፉት ጋር የሚጣጣም አይደለም። እንዲሁም በማዕከለኛው ክፍለ-ዘመን በአውሮፓ ምድር  በሃይማኖት ስም የተለያየ ዕምነትን እንከተላለን በሚሉ መሀከል ከፍተኛ ጦርነት ተከፍቶ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ሞተዋል። በ17ኛው ክፍለ-ዘመን ነው በካቶሊክ ሃይማኖትና በፕርቴስታንት ሃይማኖት መሪዎች መሀከል በተነሳው ጦርነት በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ ሁለት ሶስተኛው የሚሆነው ህዝብ ለመሞት ችሏል። የእርሻ ማሳዎችና መንደሮችና ከተማዎች ወድመዋል። ይህም የሚያረጋግጠው በጊዜው ለነበረው ጦርነት ሶሻሊዝም እንደምክንያት ሊወሰድ አይችልም፤ ጽንሰ-ሃሳቡም አይታወቅም ነበር። በአስራምስተኛው ክፍለ-ዘመን ደግሞ በካቶሊክ ሃይማኖት መሪዎች በተቆሰቆሰው የመሰቀል ጦርነት የተነሳ ነው በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ እስላሞች ሊገደሉ የበቁት። የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነት የተቀሰቀሱትና ለብዙ ሚሊዮን ህዝቦች መገደል ምክንያት ለመሆን የበቁት ከካፒታሊዝም ውስጥ በፈለቁ ናዚዎች አማካይነት ነው። ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ኮሙኒዝምን ለመዋጋት በሚል ሰበብ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ጦርነት በአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝምና በግብረአበሮቿ አማካይነት የተጠነሰሰና ጦርነትን ዓለምአቀፋዊ ከማድረግ ጋር በጥብቅ የተያያዘ ነው።  እነዚህ ሁሉ ጦርነቶች የተቀሰቀሱትና የሚቀሰቀሱት አንዳች ምክንያት በመፈልግና  ርዕዮተ-ዓለምን ሽፋን በማደረግ ነው። ይሁንና በሁላችንም ጭንቅላት ውስጥ የተቀረጸውና ብዙም ሳናነብ በጥላቻ የተቀበልነው ነገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተነሱት ጦርነቶችና ለደረሱት ዕልቂቶች ሁሉ ተጠያቂው ማርክሲዝምና ሶሻሊዝም የሚባሉት ነገሮች ናቸው። ይህም የሚያረጋግጠው አብዛኛዎቻችን የቱን ያህል የዕውቀት ግድፈት እንዳለብንና፣ በተለይም ደግሞ ሰለካፒታሊዝም አፀናነስና ዕድገት፣ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ባህርይ መውሰድ ያለን ዕውቀት እስከዚህም አለመሆኑን ነው። በተለይም ደግሞ የባሪያ ንግድና የቅኝ-ግዛት አስተሳሰብ መፈጠርና አፍሪካን ቅኝ ግዛት አድርጎ ሀብቷን መዝረፍና ህዝቡን ደሃ ማድረግ የተፈጠረው በማርክሲዝምና በሶሻሊዝም ሳቢያ ሳይሆን በካፒታሊዝም ምክንያት የተነሳ ነው። ከዚህና ከአያሌ ምርምሮች ስነሳ በኢትዮጵያ ምድር ለደረሰው ውድቀትና ለህዝባችን መሞትና መሰደድ ዋናው ተጠያቂ የማርክሲዝምን አስተሳሰብ በመከተላችን ሳይሆን፣ በተሳሳተ መልክ የኢትዮጵያንና የዓለምን ታሪክ በመተርጎማችንና በመቸኮላችን ብቻ  ነው። ማርክሲቶች ከሚባሉት ኢትዮጵያውያን ውስጥ አንዳቸውም ቢሆን የማርክስን ዳስ-ካፒታልና መሰረታዊ ስራዎችን ያነበበ የለም። ቀደም ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት አብዛኛዎች በስድሳዎችና በሰባዎቹ ዓመታት በአውሮፓና በአሜሪካ ምድር ይማሩ የነበሩ የግራን ዝንባሌ አስፋፉ የሚባሉት በጊዜው ከነበረው ሰፋ ባለ መልክ ይካሄድ ከነበረው ምሁራዊ ክርክር ጋር የተዋወቁ አልነበሩም። እንደዛሬው ዐይነት ምሁር ነኝ፣ አክቲቪስት ነኝ እንደሚለው ኢትዮጵያዊ ኃይል ክርክሩ የሚካሄደው ከተገለጸለት የፈረንጅ ምሁራን ጋር በመገናኘትና ከእነሱ ጋር በመወያየት ሳይሆን እዚያው በዚያው በሚሽከረከር ጠባብ አስተሳሰብ ነው። ስለሆነም ትላንትም ሆነ ዛሬ ከፍተኛ ግድፈት ይታያል። ይሁንና ከምሁር ንቃተ-ህሊና አንፃር የስድሳዎቹና የሰባዎቹ ምሁር የተሻለ አመለካከትና ዝንባሌ ነበረው ብሎ መናገር ይቻላል።

ያም ሆነ በአገራችን ምድር ስለተፈጠረው ቀውስ ዋናው ምክንያት የእኛ የግንዛቤ እጦትና ጠለቅ ብሎ ለማጥናት ያለመፈለግ ነው። አንድን ነገር በጥቁርና በነጭ እየሳልን፣ ይህ መጥፎ ነው፣ ያኛው ደግሞ ጥሩ ነው የምንል ከሆነ በተጨባጭ ሲታይ የምንታገለው ለዕድገትና ለስልጣኔ ሳይሆን አገራችንና ህዝባችን ከድህነት እንዳይላቀቁ ነው። በተለይም በሚዲያ ዙሪያ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦችና አሁን በመታወቅ ላይ ያሉ የሚያራግቡት የተሳሳተ መረጃ ታዳጊው ትውልድ አንድን ነገር ከተለያዩ አንፃሮች እንዳያይ እያገዱት ነው። ስለሆነም ከሳይንሳዊ ዕውቀትና ከፖለቲካ ዲሶኮርስ ውጭ፣ እንዲሁም በቲዎሪ ሳይደገፍ የሚደረግ ግብግብ የመጨረሻ መጨረሻ ወደ መጠፋፋት ነው የሚያመራን። በመሆኑም ወደ ፖለቲካ አክቲቪዝም ከማምራትና ሚዲያውን ከማጣበብ በፊት በቂ የሆነ የህብረተሰብ ሳይንስና የፖለቲካ ፍልፍናና ቲዎሪ ግንዛቤ እንዲኖረን ያስፈልጋል።

               የጎሳ ፖለቲካ የየግለሰቦችን ውስጣዊ ፍላጎት ማርኪያ እንጂ ዕውነተኛ ነፃነትን  

                                የሚያጎናጽፍ አይደለም!

የብሄረሰን አርማ ይዘው የተነሱትን ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ታሪክ በምንመረምርበት ጊዜ የምንገዘበው ሀቅ አንዳቸውም ቢሆኑ ሰፋና ጠለቅ ባለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያላለፉ መሆናቸውን ነው። ሁሉም ማለት ይቻላል ለዕውቀትና ለሳይንሳዊ ምርምርም መሰረት የሚሆን ጽሁፎችንም ሆነ መጽሀፎችን ያልጻፉ ናቸው። ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የሚነሱትም ከተሳሳተ ትረካ፣ በሳይንስና በህብረተሰብ ግንባታ ታሪክ ውስጥ በማይደገፍ መረጃ በመነሳት ነው። አስተሳሰባቸው ጠባብና በጥላቻ ላይ የተመረኮዘ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በነፃነት ስም ከተደረገው እንቅስቃሴና ትግል የሚለይ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። ጭንቅላታቸው በጥላቻ መንፈስ ስለተወጠረና ምንም ዕውቀት ስለሌላቸው እነዚህ ኃይሎች የውጭ ኃይሎች መሳሪያ ከመሆን በፍጹም አያልፉም። በሌላ አነጋገር፣ በብሄረሰብ ስም እስካሁን ድረስ የተደረገውና የሚደረገው ትግል፣ ስልጣንም ላይ ቁጥጥ ካሉ በኋላ በብዙ መልኮች የሚገለጽ በህዝባችን ላይ የከፈቱት ጦርነት በመሰረቱ የአሜሪካንና የተቀረውን የምዕራቡን ካፒታሊስት ዓለምና የአረቦችን ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ነው።

ወያኔ ስልጣን ላይ የወጣው በአሜሪካኖችና በግብረአበሮቹ በመደገፍ ነው። ለ27 ዓመታት ያህል ስልጣን ላይ በቆየበት ዘመን ተግባራዊ ያደረገው የኢኮኖሚ ፖሊሲና የጎሳ ፖለቲካ በመሰረቱ የኢትዮጵያን ህዝብ የሚያደኸይ፣ ሰፊውን ህዝብ ለብዙ ዓመታት ጥገኛ እንዲሆን የሚያደርገውና፣ በጎሳ ፌዴራሊዝም የተነሳ ውስጣዊ አንድነትና ጥንካሬ እንዳይኖረው ለማድረግ ነው። በተለይም ወያኔ ተግባራዊ ያደረገው ኒዎ-ሊበራሊዝም በመባል የሚታወቀው የኢኮኖሚ ፖሊሲ በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ይህን ያህልም አልተጠናም። ለዕዳ መቆለል፣ ለውጭ ንግድ መዛባት፣ ለዋጋ ግሽበት መናር፣ በደሃና በሀብታም መሀከል ስላለው ገቢ ልዩነት፣ ወዘተ. … ዋናው ምክንያት የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመባል የሚታወቀው መሆኑን ለሁላችንም ግልጽ አይደለም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ በነፃ ንግድ አማካይነት የአገሪት ገበያ ክፍት ከሆነ በኋላ የአካባቢ መቆሸሽ፣ መርዛማ የሆኑ ነገሮች በየቦታው መሰራጨት፣ የሴተኛ አዳሪ መስፋፋት፣ የግብረሰዶማዊነት ጉዳይ እንደባህል መወሰዱ፣ መንፈሱ የሰከረ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ኤሊት መፈጠሩና፣ የህብረተሰብአችንን ዕድገት ማዛባት መቻሉ፣ ወዘተ. … እነዚህ ነገሮች ሁሉ ደረጃ በደራጃ ስላልተጠኑ የፖለቲካ ትግላችን ከአጉል ጥላቻና ከልፍለፋ ሊያልፍ አልቻለም። ስልሆነም ወያኔን ስንታገል ብቻውን እንደቆመና በራሱ ዕውቀትና ኃይል በመንቀሳቀስ ብቻ የአገራችንን ሀብት ይበዘብዛና አገራችንንም ያመሰቃቅል እንደነበር አድርጎ መውሰዱ ትግላችን የተሟላና ለዕውነተኛ ነፃነት እንዳያመች አድርጎታል ማለት ይቻላል።

አቢይና ግብረአበሮች ስልጣን ላይ ለመውጣት የቻሉት በአሜሪካንና በሳውዲ አረቢያ ድጋፍ እንደሆነ ለአብዛኛዎቻችን ግልጽ አይደለም። በተለይም አቢይ የእነዚህን የውጭ ኃይሎች ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚሰራ ስንቶቻችን እንደተገነዘብን ከምናካሄደው ትግል መረዳት ይቻላል። በሌላ አነጋገር፣ አቢይና ግብረ-አበሮቹ፣ እንዲህም በአገዛዝ ውስጥ የተሳተፉት ከአማራውና ከሌሎች ብሄረሰብ የተውጣጡት ግለሰቦችም ሆነ ድርጀት አለን የሚሉት በመሰረቱ የየብሄረሰቦቻቸውን ጥቅም የሚያስጠብቁ አይደሉም። የእነሱንም መሰረታዊ ፍላጎቶ ለማሟላት ሲሯሯጡ የሚታዩ አይደለም። ስለሆነም በደሃው ህዝባችንናን በእነዚህ አዲስ የገዢ መደቦች መሀከል ከፍተኛ የኑሮ ልዩነት ይታያል። እነሱ በቪላ ቤት ውስጥ ተንደላቀው ሲኖሩ አብዛኛው ህዝባችን ዝናብ ከላዩ ላይ እየፈሰሰበት በደሳሳ ጎጆ ቤቶች ውስጥ ይኖራል። በአጭሩ ብሄረሰባችንን እንወክላለን የሚሉት ሁሉ ዋናው ዓላማቸው የራሳቸውንና የውጭ ኃይሎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ብቻ ነው። አቢይ አህመድ ስልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ በመሰረቱ ከወያኔ የኢኮኖሚ ፖሊሲና የጎሳ ፌዴራሊዝም ያለመላቀቁ ብቻ ሳይሆን በከፍተኛ ፍጥነት የኢትዮጵያን ውድቀት በማፋጠን ላይ ይገኛል። ተግባራዊ የሚያደርገውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ስሙንና የሚያመጣውን ውጤት በፍጹም አያውቅም። የጎሳ ካባ በመልበስ የሚያካሂደው ጦርነት፣ በተለይም ደግሞ በአማራው ላይ ያነጣጠረ ጦርነት በመሰረቱ አሜሪካኖችና የተቀረው ኢምፔሪያሊስት ኃይሎች የሚፈልጉትን ነው። በእነሱ ዕምነትና አስተሳሰብ አማራው ብሄረተኛና የኦርቶዶክስ ሃይማኖትም ደግሞ አብዛኛውን ህዝብ ያስተሳሰረ ኃይልና ባህል ነው ብለው ስለሚያምኑ ሁለቱም ኃይሎች በከፍተኛ ደረጃ መዳከም አለባቸው። አማራው ኃይሉ እስኪዳከም ድረስ በየቦታው ጦርነት እንዲከፈትብት ያስፈልጋል። አቢይና ግብረአበሮች፣ እንዲሁም ወያኔ ከከፈቱብን ጦርነት ባሻገር  የአሜሪካን፣ የእንግሊዝና የሌሎች የምዕራብ የስለላ ድርጅቶች በኦሮሚያ ክልል በሸኔ ስም የሚንቀሳቀውንና፣ እስከተወሰነ ደረጃ ድረስም በመንግስት የሚደገፈውን በድረግ (በሃሺሽ) ጭንቅላቱን በመመረዝ በህዝባችንና በአገራችን ላይ ግልጽና ድብቅ ጦርነት ከፍተውብናል። ወያኔ ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን የምዕራቡ ዓለም የስለላ ሰዎች ሃይማኖት ሽፋን አድረገው በመግባት በተለይም በደቡቡ የኢትዮጵያ ክፍል የጥላቻ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ ነበር። በተጨማሪም በዕርዳታ ስም የሚንቀሳቀሱት ኃይሎች ከስለላ ድርጅቶቻቸው ጋር አብረው በመስራት በህዝባችን ዘንድ አለመተማመን ለመፍጠር ችለዋል።  በዚህ ዐይነቱ ኢትዮጵያን የማጥፋት ወይም የማዳከም ሴራ ውስጥ የአረብ አገሮች፣ በተለይም ሳውዲ አረቢያ፣ ሱዳንንና ግብጽ ተባባሪ በመሆን የአገራችንን ውድመጥ በማፈጠን ላይ ይገኛሉ። በአጭሩ የተከፈተብን ጦርነት በሁሉም አቅጣጫ ሲሆን፣ እኛው ራሳችንም ሳናውቀው የጥፋቱ ተባባሪ ለመሆን በቅተናል። ምክንያቱም በግልጽ ለማጥናትና ለመወያየት ስለማንፈልግ ነው።

ለማንኛውም አቢይና ግብረ-አበሮቹ፣ እንዲሁም አማራን እወክላለሁ ብሎ ስልጣን ላይ የተቀመጠው የደንቆሮዎች ስብስብ አሜሪካኖች ባዳበሩት ጭንቅላትን በሚሰውር ሃርፕ በሚባል ቴክኖሎጂ የተመረዙ ይመስል በራሳቸው ኢጎ በመጠመድና  በጊዜያዊ ዝና በመታወር የዓለም ማህበረሰብ እስኪሳለቅብን ድረስ አገራችን ለአንዴም ለመጨራሻም ጊዜ ለማውደም ደፋ ቀና ሲሉ ይታያሉ። አቢይ አህመድ በብሄር ጎጠኝነት ብቻ ናላው የዞረ ሳይሆን፣ ሃይማኖተኛ ነኝ ባይም ነው። እንደሚነግረንም ከሆነ በቀን ውስጥ ሁለት ጊዜ መጽሀፍ-ቅዱስን እንደሚያነብ ነው። ታዲያ እንደዚህ በቀን ሁለት ጊዜ መጽሀፍ ቅዱስን አነባለሁ፣ ሃይማኖትም አለኝ ከሚል ሰው አራት ዓመት ተኩል ያህል በአማራው ላይ ያነጣጠረ ግድያ፣ ማፈናቀልና ማሰቃየት ሲካሄድ ለምን ዝም ይላል? እሱ የሚያነበው መጽሀፍ-ቅዱስ ውስጥ ከእሱ የተለየ ሃይማኖትን ተዋጋ፣ ምዕመናን ግደል፣ ቤተክርስቲያናትን አፈራርስ፣ ከዚያም በላይ ደግሞ በአንድ ብሄረሰብ ላይ ያነጣጠረ አሰቃቂ ዕርምጃ መውሰድ አለብህ የሚል ቃል ተጽፏል ወይ? ሁላችንም እንደምናውቀው እስካሁን ድረስ ያለው አንድ ዐይነት መጽሀፍ-ቅዱስ ብቻ ነው። በመጽሀፍ-ቅዱስ ውስጥ አስር የተከለከሉ ወይም አንድ የክርስቲያን ሃይማኖት ተከታይ ነኝ የሚል ሰው ማድረግ የሌለባቸው መሰረታዊ ነገሮች ተጽፈዋል። ከአስሩ ውስጥ፣ የእኔን የአምላክህን ስም አታጉድፍ፣ በስሜም መጥፎ ነገር አትስራ ይላል፤ አባትህንና እናትህን አክብር፤ አትግደል፤ ጋብቻህን አትጣስ ወይም ካገባህ ሌላ ሴት አትመኝ፤ አትስረቅ፤ በጓደኛህ ላይ መጥፎ ነገር አታሳብ፤ የአንተ ያልሆነውን ነገር አትመኝ ይላል። ፍልስፍናውም ተመሳሳይ ነገር ነው የሚያስተምረን። በጀርመኑ ፈላሳፍ በኢማኑኤል ካንት፣ ካቴጎሪካል ኢምፔራቲቭ በሚለው የሞራል ትምህርቱ መሰረት፣ ለአንተ ብለህ ያሰብከውን ወይም እንደህግ የደነገከውን ጥሩ ነገር ለሌላውም አድርግለት ይላል። በሌላ አነጋገር፣ ለአንተ መጥፎ ነገር የማትመኘውን ያህል ለሌላውም ሰው መጥፎ ነገር አትመኝለት ይላል። በመጽሀፍ-ቅዱስም ሆነ በፍልስፍና ውስጥ እነዚህን የመሰሉ ሞራላዊ ግዴታዎች ከሰፈሩ የፔንጠ-ቆንጤ  ሃይማኖት ተከታዮች የሆኑት አቢይና ግብረ-አበሮች ከየት አምጥተው ነው አራት ዓመት ተኩል ያህል ህዝባችንን እረፍት የሚነሱትና፣ በተለይም ደግሞ ደሃ አማራውን እይተከታተሉ የሚገድሉት? እግዜአቤሄር አይመለከትንም ብለው ነው እንደይዚህ ዐይነቱን ውርጅብኝ በህዝባችን ላይ የሚያወርዱት? በእኔ ዕምነትና ተጨባጭ ሁኔታውም እንደሚያረጋግጥልን ከሆነ አቢይና ግብረአበሮች ምንም ዐይነት ሃይማኖት የላቸውም። የሚሰሩት ስራ በሙሉ የእግዚአብሄር ጠላት የሆነው ሰይጣን የሚሰራውን ስራ ነው። መንፈሳቸው በአምላክ የሚመራ ሳይሆን በሰይጣን ነው ማለት ይቻላል።

ባጭሩ በአገራችን ምድር የብሄረሰብን ካባ ለብሶ ስልጣን ላይ መውጣት የራስን ኢጎ ከማሟላት፣ ወይንም ራስን ከማንገስ ባሻገር ዘልቆ የሚሄድ አይደለም። ቆሜለታለሁ ለሚሉትና ለሚከተላቸው ሰው ዕውነተኛ ነፃነትንና በራስ መተማመንን የሚያጎናጽፍ ሳይሆን፣ መንፈሱ ተረብሾ እንዲኖር የሚያደርግ ነው። ከጠቅላላው የአገራችን ሁኔታ ስንነሳ ደግሞ ጠቅላላው ህዝባችን ከድህነት እንዳይላቀቅ የሚያደርግ፣ መንፈሱ በጦርነትና በፍርሃት እንዲጠመድና እንደሰው ተከብሮ እንዳይኖር የሚያደርግ አካሄድ ነው። ስለሆነም አቢይና ግብረአበሮቹ፣ አንዲሁም በአካባቢው የተሰባሰቡና የስልጣንም ተካፋይ የሆኑት ኃይሎች በሙሉ የጠቅላላው ህዝባችንና የጥቁር አፍሪካ ህዝብ ጠላቶች ናቸው። ብሄራዊ ባህርይ የሌላቸውና ብሄራዊ ኩራት የማይሰማቸው ናቸው። የዛሬውን አገዛዝና ግብረአበሮቹን ህይወት ለማሳጠር የግዴታ የሰከነና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ትግል አስፈላጊና ወሳኝም ነው።  በትክክለኛ ወይም ሳይንሳዊ ዕውቀት ላይ ያለተመሰረተ ትግል ወደ ሰላምና ወደ ዕውነተኛው ነፃነት ሊያመራን በፍጹም አይችልም። መልክካም ግንዛቤ።

[email protected]

በተጨማሪ ይህንን ድረ ገጽ ተመልከቱ፣ www.fekadubekele.com

ለሳይንሳዊ ምርምርና ለተከታታይ ጽሁፍ በሃሳብም ሆነ በገንዘብም ድረ –ገጼን ይርዱ

የጀመርኩትንና በስራ ብዛት ያቋረጥኩትን የዩቱብ ቻናል ስርጭቴንም በማሻሻል  ለማቅረብ እሞክራለሁ።

የዩቱብ ቻናል ስሙ፣ Ethiopian Renaissance ነው።

የፖድካስቱም ስም እንደዚሁ፣ Ethiopian Renaissance ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop