July 10, 2022
5 mins read

የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕዝብ ገንዘብ በሚተዳደሩ መገናኛ ብዙኃን ላይ ወቀሳ አቀረቡ

politicalparties press release

ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. መግለጫ የሰጡት እናት መኢአድና ኢሕአፓ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሕዝብ ገንዘብ የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙኃን የዜጎችን ሞት ዓይተው እንዳላዩና ሰምተው እንዳልሰሙ ሆነዋል ሲሉ ወቀሳ አቀረቡ፡፡

ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው እየተጨፈጨፈ ያለውን ማኅበረሰብ ጨምሮ፣ በሚሰበሰብ ግብር የሚተዳደሩት ‹‹የመንግሥትና አፍቃሬ መንግሥት ሚዲያዎች፣ በተራ ጉዳይ ጊዜያቸውን የሚያጠፉትን ያህል ለሰው ነብስ ግድ የማይሰጣቸውና ዓይተው እንዳላዩ እያለፉ ነው ሲሉ›› ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

ሦስቱ ፓርቲዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በዚህ ሥራቸው ስለጉዳዩ አብዝተው ለሚጮሁ አካላት የተቃርኖ ዘገባና ማስተባበያ መርሐ ግብሮችን በመሥራት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍርድ አያመልጡም፣ ትውልዱ በሚገባ መዝግቦ ይዞታል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በታሪክ በሚጠቀሱ የዘር ፍጅቶች መገናኛ ብዙኃን ያላቸው አስተዋጽኦ ትልቁን ድርሻ እንደሚወሰድና አንዳንዶች ግድያውን ደግፈው እንደሚቆሙ፣ ሌሎቸ ደግሞ ዓይተው እንዳላዩ ሰምተው እንዳልሰሙ ሆነው እያለፉት መሆኑን ፓርቲዎቹ አውስተዋል፡፡

ኦነግ ሸኔ ወደ አገር ቤት ከገባ ጀምሮ የተሠሩ መንግሥታዊ ስህተቶች ለመኖራቸው ጥርጥር የለውም ያለው መግለጫው፣ ቡድኑ አንድ እግሩን አዲስ አበባ አንድ እግሩን ምዕራብ ኦሮሚያ ጫካዎች ውስጥ ከተከለ በኋላም፣ በከፍተኛ ሁኔታ መንግሥታዊ መዋቅርንና ማዘናጊያዎችን እንደሚጠቀም ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል ብሏል፡፡

በረቀቀ መዋቅራዊ ትስስር የሚንቀሳቀሰው በቡድኑ ላይ ‹‹የማያዳግም ዕርምጃ ወስጃለሁ፣ በቡድኑ የተያዘ አንድም አካባቢ የለም፣ የተንጠባጠበው ሲፈረጥጥ ‹‹ዜጎች›› ተገደሉ፣ ቡድኑ ሥጋት መሆን የሚያስችለው አቅም የለውም፣ የተፈናቀላችሁ ወደ አካባቢያችሁ ተመለሱ›› የሚሉና ሰባራ መሣሪያዎችን ጨፍቆ ‹‹ከቡድኑ የተማረኩ›› በሚል መንግሥት ራሱ በሚዘውራቸው ሚዲያዎች አብዝቶ እያስተጋባ ስለመሆኑ በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

ይሁን እንጂ  መንግሥት የጭፍጨፋ መደላድሎችንና የማዘናጊያ መግለጫዎችን በማውጣት፣ በተለይ በአማራው ላይ የሚደርሰው የዘር ፍጅት እንዳይወገዝ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት እንዳያደርግበት፣ ለፍጅቱ የማይናቅ አስተዋጽኦ እንዳደረገ የፓርቲዎቹ መግለጫ አትቷል፡፡

ፓርቲዎቹ ‹‹ፍጅቱ ለጊዜው አንድ አካል ላይ ያነጣጠረ ይምሰል እንጂ፣ የመጨረሻ ግቡ አገር ማፍረስና ፍርስራሹ ላይ ጎጆ የመቀለስ ተልካሻ ህልም›› መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

የዘር ፍጅት ሰለባ በሆነው የአማራ ብሔር ላይ እየተፈጸመ ያለውን ዓለም አቀፍ ወንጀል ለማስቆምና ፍጅቱ በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ጥፋተኞች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ድርጊቱን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያሳውቅ ፓርቲዎቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሦስቱ ፓርቲዎች መንግሥት በአካባቢው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ አካባቢውን የመከላከያ ኃይሉ ብቻ እንዲቆጣጠረው እንዲያደርግ፣ ለጥቃት የተጋጠው ማኅበረሰብ ራሱን ከእልቂት እንዲያተርፍ በልዩ ሁኔታ እንዲያደራጃቸው ጠይቀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop