July 5, 2022
43 mins read

የወልቃይት ጠገዴ እና ጠለምት እውነታዎች (ከታሪክ፣ ከሕግ እና ከስነ ሕዝብ ምህንድስና አንጻር) – ቴዎድሮስ ታደሰ በለይ

ክፍል ሁለት

በቀደመው ሳምንት የጥናት ሐተታችን የወልቃይት፣ ጠገዴ እና ጠለምት ታሪካዊ ዳራ ከቅድመ-አክሱም እስከ 1983 ድረስ የነበረውን የታሪክ እውነታ በማስረጃዎች በማጣቀስ የትግራይና የበጌምድር-ጎንደር (ዐማራ) ወሰን ተከዜ ስለመሆኑ ትግሬ እንጂ ትግራይ ተከዜን ተሻግራ እንደማታውቅ በዝርዝር ለማየት ሞክረናል፡፡ በይደር ባቆነው ሁለተኛው ክፍል ወያኔ በወልቃይት ስለፈፀመው የሥነ-ሕዝብ ምህንድስና፣ ስዘር ማፅዳት፣ በዐማራ መቃብር ላይ ስለተተገበረው የሰፈራ ፕሮግራም እና የወልቃይት የዐማራ ማንነት ጥያቄን በተመለከተ መረጃን መሰረት አድርገን ሁኔታዎችን እንፈትሻለን፡፡

welkeit

1.1 የሥነ-ሕዝብ ምህንድስና (Demographic Engineering)

የወያኔ ኃይል ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይትንና አካባቢውን በኃይል ወደ ትግራይ ክልል ካካለለ በኋላ ወዲያውኑ የሥነ-ሕዝብ  ምህንድስና ዘመቻ ማካሄድ ጀምሯል። ይህን ለመረዳት የሥነ-ሕዝብ ምህንድስና ምንነትን ተርጉመን እንነሳ። የሥነ-ሕዝብ ምህንድስና አንድ አካባቢ ያለውን ተፈጥሯዊ የሕዝብ አሰፋፈር እና ስብጥር በተለያየ መንገድ (ነባር ነዋሪን በማፍለስ እና በምትኩ አዲስ ነዋሪን በማስፈር) ሆነ ብሎ የአካባቢውን ሥነ-ሕዝብ ስብጥር በመቀየር አንድ የሆነ ብሔር መኖሪያ ብቻ የማድረግ ጥረት ነው። (Demography Engineering (DE) is a deliberate effort to shift the ethnic balance of an area, especially when undertaken to create ethnically homogeneous populations.)

5.1. የሥነ-ሕዝብ ምህንድስና በወልቃይት

የሥነ-ሕዝብ ምህንድስና ትርጓሜ እና ምንነት በአጭሩ ከተመለከትን ዘንዳ በወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ወያኔ የፈጸመውን የሥነ-ሕዝብ ምህንድስና በኢትዮጵያ በ1977፣ በ1987 እና በ1999 ዓ/ም የተደረጉ የሕዝብ እና የቤት ቆጠራ ውጤቶችን መሰረት በማድረግ እያነጻጸርን እንመልከት። በ1977 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የተደረገው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ የጎንደር ክፍለ ሀገር በከተማ እና በገጠር የሚኖረው ሕዝብ (ወልቃይት ጠገዴ ጠለምትን ጨምሮ) የብሔር ስብጥር ውጤት መሰረት፤ በጎንደር ክፍለ ሀገር በከተማ እና በገጠር የሚኖረው የዐማራ ብሔር ተወላጅ 2,545,732 በመሆን ከጠቅላላው ሕዝብ 84.3 % ሲሆን፤ በጎንደር ክፍለ ሀገር በከተማ እና በገጠር የሚኖረው የትግራይ ብሔር ተወላጅ ደግሞ 190,183 በመሆን 6.3 በመቶውን እንደሚይዝ ገልጿል። (በ1976/77 ዓ.. የተደረገው የጎንደር ክፍለ ሀገር ሕዝብ እና የቤት ቆጠራ ውጤት ይመልከቱ) በአንጻሩ በ1999 ዓ.ም. ማለትም ወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ወደ ትግራይ ክልል ከተካለሉ እና “ምዕራብ ትግራይ” ከተባሉ በኃላ የተደረገው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሰረት በቀጠናው የሚኖረው 92.28% ሕዝብ የትግራይ ተወላጅ መሆኑን ሲገልጽ 6.48 % በመቶው ደሞ የዐማራ ተወላጅ ናቸው ብሏል። ይህ ወልቃይት ወደ ትግራይ ክልል ከተካለለ በኃላ የተደረገው የሥነ- ሕዝብ ምህንድስና በውል ለመረዳት የሚከተለውን ቻርት እንመልከት።

 

ሠንጠረጅ 1 የ1977 ዓ/ም እና የ1987 ዓ/ም የጎንደር ክፍለ ሀገር እና የትግራይ ክልል የሕዝብ ቆጠራ ውጠት

3333

ከላይ በምስል 5 ከተመለከተው የሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሰረት የሠንጠረጅ አንድ መግለጫ እንደሚያሳየው የ1977 ዓ.ም. የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ከ1987 እና ከ1999 ዓ.ም. ጋር ስናነጽር በጠቅላላው ጎንደር ክፍለ ሀገር ይኖሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች 6 በመቶ ሆነው ሳለ እንዴት በስሜን ምዕራብ ጎንደር (ወልቃይት ጠገዴ ጠለምት) የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች 97 በመቶ ሊሆኑ ቻለ? የሚል መሰረታዊ ጥያቄን ያስነሳል። እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባው የ1987 እና የ1999 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የትግራይ ሕዝብና ቤቶች ቆጠራ የተደረገው በወያኔ አማካኝነት መሆኑ፣ “ከሦስት ሚሊየን በላይ የሆነ የዐማራ ተወላጅ ጠፍቷል” የሚል ሪፖርት በሕዝብ ተወካዮች ምክርቤት ጭምር የቀረበበት፣ ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል የመረጃ ምዝበራ የተደረገበት በመሆኑ የተቀባይነቱ ደረጃ ጥያቄ ውስጥ የገባ መሆኑን ነው።

ይህ የመረጃ ምዝበራ እና ቅቡልነቱ ጥያቄ ውስጥ የገባ የሕዝብ ቆጠራ ውጠት እንደተጠበቀ ሆኖ በዚህ ደረጃ የዐማራ ሕዝብ ቁጥር ሊያሽቆለቁል የቻለው በዋነኝነት በአራት ምክኒያቶች ሆኖ ይታያል፡-

አንደኛ፦ ወያኔ ባራመደው የሥነ-ሕዝብ ምህንድስና ፖሊሲ አማካኝነት በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆችን ለፖለቲካል-ኢኮኖሚ ዓላማው በወልቃይት አስፍሯል፤

ሁለተኛ፦ ወያኔ  በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ ነባር የወልቃይት ተወላጆችን በግዳጅ አፋናቅሏል፤

ስተኛ፦ ነባር የወልቃይት ተወላጆች በግዳጅ የዐማራ ማንነትን ጥለው የትግሬ ማንነት እንዲጫንባቸው አለም አቀፍ ባህላዊና ማህበራዊ መብቶችን በመጣስ ‹ካልቸራል ጀኖሳይድ› ፈጽሟል፤

አራተኛ፦ ይህን ያልተቀበሉትን በጅምላ በመግደል በኃይል በመሰወር በማሰቃየትእና በማሳደድ የዘር ማጥፋት እና በሰብዓዊነት የሚፈጸም ወንጀል ፈጽሟል።

እነዚህን እውነታዎች አንድ በአንድ እያነሳን እንመርምር?

1.2. የትግራይ ተወላጆች ሰፈራ በወልቃይት ጠገዴ ጠለምት

በቅርቡ አምኒስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎች የተባሉ አለም አቀፍ ተቋማት ባወጡት ሪፖርት እና የወያኔ ኃይል ሪፖርቱን እንደሚቀበለው መግለጫ የሰጠበት እና የዐማራ ክልል መንግሥት ሙሉ ለሙሉ እንደሚቃወመው በገለጸው ሪፖርት ላይ የትግራይ ተወላጆች እንዴት በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ሊሰፍሩ እንደቻሉ የሚከተለውን መረጃ አስቀምጧል።

  • ከ1986 እስከ 1989 ባለው ጊዜ ሠላሳ ሽህ የሚሆኑ የትግራይ ተወላጆች ቃፍታ ሁመራ ላይ ሰፍረዋል። (Between 1993 and 1996, around 30,000 Tigrayans were settled in villages in the Kafta Humera)
  • በ1989 ዓ.ም.ማይካድራ አካባቢ 746 የትግራይ ተወላጅ አባወራዎች ሰፍረዋል (By 1996, the Mai Kadra area hosted 746 Tigrayan households)
  • በ1989 ዓ.ም ራውያን በመባል የሚጠራው አካባቢ ላይ 18,107የትግራይ ተወላጆች ሰፍረዋል። (By 1996, Rawyan hosted 18,107 Ethnic Tigrayans)
  • በ1990 ዓ.ም.ሰላሳ ሽህ የሚሆኑ የቀድሞ የወያኔ ታጋዮች ዳንሻ አካባቢ ልዩ ስሙ ዲቪዥን በመባለ የሚጠራ ቦታ ላይ የእርሻ መሬት ተሰጥቷቸው ሰፍረዋል። (In 1997, around 30,000 former TPLF fighters, received agricultural plots in several resettlement sites now known as “Division.”)
  • በ1995 ዓ.ም.የተከዜ ወንዝ ተፋሰስን ተከትሎ 15,000  አባወራዎች በፌደራል መንግሥት አማካኝነት ሰፍረዋል። (In 2002, the federal government identified 15,000 additional households for resettlement along the Tekeze River in Western Tigray.)

 

ይህ መረጃ እንደሚያሳየው በድምሩ በአንድ አባወራ ቤተሰብ ውስጥ አምስት ሰው ይኖራል ብለን በትንሹ ብናሰላው ከሁለት መቶ ሀምሳ ሽህ በላይ የትግራይ ተወላጆች በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ለፖለቲካል-ኢኮኖሚ ዓላማ እንደሰፈሩ መረዳት ይቻላል። በአንጻሩ እነዚህ ሰዎች መጥተው ሲሰፍሩ በምትኩ በመቶ ሽዎች የሚቆጠሩ የዐማራ ተወላጆች ከቀጠናው እንደተፈናቀሉ የተለያዮ ጥናቶች አመልክተዋል።

1.3. የዐማራ ተወላጆች ከወልቃይት ጠገዴ ጠለምት በግዳጅ መፈናቀል

የዐማራ ክልል መንግሥት በህዳር ወር 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “ከአምስት መቶ ሽህ በላይ ዐማራዎች ከወልቃይት ጠገዴ ጠለምት እና ሰቲት ሁመራ አካባቢዎች በግዳጅ እንደተፈናቀሉ” ገልጿል። በተመሳሳይ ሁኔታ የወልቃይት ጠገዴ ዐማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ባቀረበው የማንነት ጥያቄ ላይ “በመቶ ሽህ የሚቆጠሩ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች በወያኔ ኃይል በግዳጅ እንደተፈናቀሉ” ገልጿል። ይህ በተለያዩ አካላት ሲገለጽ የሚስተዋለው የግዳጅ መፈናቀል የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጥናት ቡድን ባደረገው ጥናት “29 በመቶ የሚሆነው የወልቃይት ጠገዴ ተወላጅ ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በግዳጅ መፈናቀሉን” በጥናት ማረጋገጡን ገልጿል።

ይህን ሁኔታ ይበልጥ የሚያረጋግጥል በጎንደር ከተማ አንድ ትውልድ ዘመን በማይሞላ ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ፍጥነት የተመሰረቱት አዳዲስ የመኖሪያ አካባቢወች (ቀበሌ 18፣ መስጊድ፣ ልደታ፣ ገንፎ ቁጭ፣ ሀምሌ አምስት፣ ጎርጎራ እና ባህርዳር መውጫ መስመር) እጅጉን ባልተጠበቀ ሁኔታ በከፍተኛ የነዋሪዎች ቁጥር መጥለቅለቁ፤ እንዲሁም የጎንደር ከተማ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ለጎንደር ከተማ ሕዝብ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለሟሟላት መቸገሩን መግለጹ ይህም የሆነው የጎንደር ከተማ ሕዝብ ቁጥር በአስርት አመታት ውስጥ ከእጥፍ በላይ በመጨመሩ ምክኒያት የከተማውን ሕዝብ ቁጥር ግምት ውስጥ በማስገባት የተካሄዱት የንጹህ ውሃ መጠጥ የማስፋፋት ፕሮጀክት ፍላጎቱን ማሟላት አለመቻሉን እና ሌሎች ሁኔታዎችን በአንድ ላይ አንጽረን ስንመለከት ጤናማ ከሚባለው ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት ባሻገር የአንድ ከተማ ሕዝብ ነዋሪ በዚህ ደረጃ ቁጥሩ መጨመሩ ከወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ እና ጠለምት በግዳጅ የተፈናቀሉ የዐማራ ተወላጆች በጎንደር ከተማ መከተማቸው፤ እነዚህ አዳዲስ የዲሞግራፊ ለውጦች የተመሰረቱት ወያኔ በመዋቅር ከፈጸመው የተጠና የጅምላ መፈናቀል ውጤት ሆኖ ይታያል፡፡ በጎንደር ከተማ በተፈናቃዮች የተጨናነቁ አካባቢዎች ተፈናቃዮች በተፈናቀሉበት አካባቢ ስም እስከመሰየም (ወልቃቴዎች፣ ጠገዴዎች፣ ጠለምቴዎች፣… በሚል የመንደር ስያሜ እስከመሰጠት) መድረሳቸውን ስንመለከት ከላይ በጥናቶች የተገለጸውን እውነታ አስረጅ ሆኖ እናገኘዋለን።

1.4. ካልቸራል ጀኖሳይድ በወልቃይት

በንድፈ ሀሳብ ደረጃ የዘር ማጥፋት ወንጀል ድርጊትን በሁለት ከፍለን መመልከት እንችላለን። የመጀመሪያው በሰው ሕይወት፣ አካል ደህንነትና ጤና ላይ የሚፈጸም የዘር ማጥፋት ወንጀል (Physical Genocide) ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ አንድ የሆነ የብሔር፣ የኃይማኖት ወይም የባህል ማንነት ያለው ሕዝብ ላይ ማንነቱን ለማጥፋት የሚሰነዘር (cultural Genocide) ነው። ካልቸራል ጀኖሳይድ ወይም ማህበራዊ ምህንድስና ተብሎ የሚገለጸው ድርጊት የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት እና ሰቲት ሁመራ ዞን ዐማራ ሕዝብን ዐማራዊ ማንነት በማስጣል የትግሬ ማንነትን በግዳጅ ለመጫን በማሰብ በተጠና ሁኔታ በወያኔ ኃይል ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ተግብሮታል።

 

ለአብነት፡- ኢትዮጵያ ተስማምታ የተቀለቻቸው የሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳኖች (የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ፣ የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን፣ የኢኮኖሚ፣ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች ቃል ኪዳን፣ የሕጻናት መብቶች ስምምነት ወዘተ) በሰው ልጆች መብትነት የደነገጓቸውን የግለሰብ እና የቡድን መብቶችን በግልጽ በተቃረነ ሁኔታ የተፈጸሙትን ካልቸራል ጀኖሳይድ አንስተን እንመልከት።

 

  1. ህጻናት በወላጆቻቸው የአፍ መፍቻ አማርኛ ቋንቋ እንዳይማሩ አማርኛ ቋንቋን ከ1-4ክፍል ድረስ ከትምህርት ቋንቋነት አግዷል፤ በአንጻሩ የትግርኛ ቋንቋ ብቻ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት እንዲሰጥ አድርጓል፣
  2. የኃይማኖት አባቶች የአማርኛ ቋንቋን ለየትኛውም አይነት ኃይማኖታዊ አገልግሎት እንዳይጠቀሙ ከልክሏል፤ በአንጻሩ የትግርኛ ቋንቋን ብቻ እንዲጠቀሙ አድርጓል፣
  • የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የትኛውንም አገልግሎት በአማርኛ ቋንቋ እንዳይሰጥ ከልክሏል፤ በአንጻሩ ሁሉም አገልግሎቶች በትግርኛ ቋንቋ ብቻ እንዲሰጡ አድርጓል፣
  1. በዐማራ ሕዝብ የሚዘወተሩ የግለሰቦችን ስም ከአማርኛ ወደ ትግርኛ እንዲቀየሩ አስገድዷል (ተክሉን ተክሌ፤ ነጋሽን ነጋሲ ወዘተ)
  2. የቦታዎች፣ የከተሞች፣ የወንዞች፣ የተራሮች፣ የሀይቆች፣ የፓርኮች ወዘተ ስምን ከአማርኛ ወደ ትግርኛ እንዲቀየሩ አድርጓል (ወፍ አርግፍን አዲረመጥ፣ ቤት ሙሉን ማይጋባ ወዘተ)፣
  3. የዐማራ ሕዝብ የባህል መገለጫ የሆኑ የደስታ፣ የለቅሶ፣ የማህበራዊ ኑሮ ሥነ-ስርዓቶች፣ አለባበስ፣ የጸጉር አሰራር፣ አዘፋፈን ወዘተ እንዳይከወኑ/እንዳይደረጉ አግዷል፣
  • ሴቶች ያለ ፍቃዳቸው እና ልምዳቸው ከሚመስላቸው ማንነት ውጭ በግዳጅ እንዲያገቡ በማድረግ ሆነ ብሎ ማንነት የማዳቀል ተግባር ፈጽሟል (ከዚህ ጋር የሚነሳው የቀደመ ትዳራቸውን በማስፈታት የትዳር አጋሮቻቸውን በማሳደድ፣ በመሰወር እና በእስር በማሰቃየት በግዳጅ ሌላ የትዳር አጋር እንዲያገቡ (ልጆች ከአባታቸው ገዳይ የእንጀራ አባት ጋር እንዲኖሩ ወንድማማች እና እህታማች የአንዳቸው አባት የሌላቸው አባት ገዳይ በሆነበት ቤት እንዲኖሩ) በማድረግ በማህበራዊ ሕይወት ላይ በቃላት የማይገለጽ ከፍተኛ የሆነ ቀውስ ፈጥሯል።)

 

[ውድ አንባቢያን ከካልቸራል ጀኖሳይድ አንጻር ሊረዱት የሚገባ ጉዳይ በማንነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል መልሶ መካስ የማይቻል (በቋንቋው የመማር፣ ታሪክን የማወቅ፣ ባህልን የመከተል የማበልጸግ ወዘተ መብቶች ለላሳ መት የተከለከለ ትውልድ ያጣውን ነገር እንዴት መልሶ መስጠት ይቻላል?) መሆኑን ማንነትን ማጥፋት እና በምትኩ ሌላ ማንነት በግዳጅ ማላበስ ከፍተኛ የሆነ የልቦና ቀውስ እንደሚፈጥር ነው።]

1.5. አለም አቀፍ ወንጀል በወልቃይት

ከዓለም አቀፍ ወንጀሎች አንጻር የወንጀሎች ሁሉ ወንጀል ተደርጎ የሚወሰደው የዘር ማጥፋት ወንጀል ምንነት ሲነሳ ለወንጀል ድርጊቱ እምቅ ስያሜ ከሙሉ ትርጓሜ ጋር የሰጠውን እና በአለም አቀፍ ወንጀልነት በኑረን በርግ ቻርተር እና በጀኔቫ ቃልኪዳን እንዲካተት የማይተካ ሚና የተጫወተውን ፕሮፌሰር ራፋየል ላምኪንን አለማንሳት አይቻልም። ፕሮፌሰር ላምኪን ለወንጀል ድርጊቱ “ጀኖ” የተሰኘ ዘር የሚል ትርጓሜ ያለውን የግሪክ ቅጥያ ቃልን “ሳይድ” ከተሰኘ መግደል/ማጥፋት የሚል ትርጓሜ ያለውን የላቲን ቃል ጋር በአንድ ላይ በማጣመር ጀኖሳይድ ወይም ዘር ማጥፋት የሚል ስያሜን ሰጥቶታል።

ከዚህ ባሻገር ለወንጀል ድርጊቱየዘር ማጥፋት ስንል ርን ወይም ጎሳን ማጥፋት ወይም ማውደም እያልን ሲሆን ይህም ሲባል የአንድን ብሔር ወይም ጎሳ አባላትን በሙሉ በጀምላ ጭፍጫፋ መንገድ ማጥፋትን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን፤ ይህን ብሔር ወይም ጎሳ የተባበረ ዕቅድ ውጤት በሆኑ የተለያዩ ድርጊቶች አማካኝነት መሰረታዊ ህልውናውን ለማጥፋት በማሰብ የሚሰነዘረውንም ይጨምራል። የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚሰነዘረው አንድነት ባለው ብሄሩን ወይም ጎሳው ላይ ሆኖ ጥቃቱ የሚፈፅመው ግን በቀጥታ በግለሰቦች ላይ በግላዊ አቅማቸው ሳይሆን የብሄሩ ወይም የጎሳው አባል በመሆናቸው ብቻ ነው የሚል እምቅ ትርጓሜን አቀናጅቶታል። ይህኑ ትርጓሜ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለመከላከል እና ለመቅጣት የወጣው የጀኔቫ ኮኒቬንሽን እና የአለም አቀፍ የጦርፍርድ ቤት ማቋቋሚያ የሮም ድንብ ለወንጀሉ ማቋቋሚያነት የሚታዩ አለባዊያንን ጨምረው አካተውታል። ይህን ካልን ዘንዳ በወልቃይት ጠገዴ ጠለምት የተፈጸመውን አለም አቀፍ ወንጀል ጥናትን መሰረት አድርገን እንመልከት።

በቅርቡ ይፋ የተደረገው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥናት እንዳረጋገጠው በወልቃይት ጠገዴ እጅግ የከፋ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈጸም እንደነበር የጀምላ መቃብር ቦታዎችን ሳይቀር አስቆፍሮ በማውጣት ለሦስት አስርት አመታት በወልቃይት ሲፈጸመ የነበረውን ግፍ ይፋ አድርጓል። በዚህም መሰረት በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ሦስት አስርት ዓመታትን ባስቆጠረው የወያኔ አገዛዝ በቀጠናው ከስልሳ ሽህ በላይ ሕዝብ በጀምላ እንደተገደለ ይህም 25 በመቶ የሚሆነውን (በአካባቢው ይኖር የነበረውን) የዐማራ ሕዝብ ህልውና እንዳከተመ፣ 19 በመቶ የሚሆነው የወልቃይት ዐማራ ሕዝብ የደረሰበት እንደማይታወቅ እና 29 በመቶ የሚሆነው የወልቃይት ዐማራ ሕዝብ አካባቢውን ለቆ በመፈናቀል የአገር ውስጥ ተፈናቃይ እና ደንበር ተሻጋሪ ስደተኛ እንደሆነ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥናት ገልጿል።  (“We have conducted the research by assessing mass graves and by interviewing survivors. Accordingly, we have found that the whereabouts of 19 percent of family heads is still unknown after TPLF took them to prisons. Also, 25 percent of ethnic Amharas were killed while 29 percent of them were forced to leave their homes….” – press statement of University of Gondar study team.”)

ይህ ጥናት ያረጋገጠው ለአብነት ያህል ያካተትኩት በወልቃይት ጠገዴ ጠለምት የተፈጸሙ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች በዚህ በደርዝ በደርዝ በተዘጋጀ የተለያዩ ሥነ-ምግባሮች አንጻር የተቃኘ አጭር ጽሁፍ ሊጠቃለል አይችልም። ወደፊት ይህን ጉዳይ ራሱን ችሎ እንደምመለከተው እየገለጽኩ ወደ ቀጣዩ ክፍል ላምራ።

  1. 2. የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ምንነት

የወልቃይት፣ ጠገዴ ጠለምት ሕዝብ የማንነት ጥያቄን ከመመልከታችን በፊት ጥያቄው በትውልድ ቅብብሎሽ ያለፈበትን ሂደቶች በአጭሩ በመዳሰስ እንነሳ። የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት የዐማራ ማንነት ጥያቄ ትግልን በትውልድ ቅብብሎሽ አማካኝነት ያለፈበትን ምዕራፍ በአምስት ከፍለን ማይት ይገባናል።

እነዚህም፦ አንደኛ፤ በ1972 ዓ.ም. የተመሰረተው እና እስከ 1985 ዓ.ም. ድረስ እልህ አስጨራሽ ተጋድሎ ያደረገው የከፋኝ ኢትዮጵያ ጀኞች ግንባር የአርበኝነት ተጋድሎ፣ ሁለተኛ፤ በ2006 ዓ.ም. የተመሰረተው እና እስከ አሁን ድረስ በትግል ላይ ያለው “የወልቃይት ጠገዴ ዐማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ” ትግል፣ ሦስተኛ፤ “የወልቃይት ጠገዴ ዐማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ” ያነሳውን ጥያቄ ወደ ህዝባዊ እንቢተኝነት የቀየረው በ2008 ዓ.ም. የተጀመረው የጎንደር ሕዝብ ታሪካዊ ተቃውሞ እና እንቢተኝነት፤ አራተኛ፤ የጎንደር ሕዝብ እንቢተኝነት ተከትሎ በመላው ዐማራ የተቀጣጠለው የዐማራ ሕዝብ፣ ሕዝባዊ እንቢተኝነት እና በዐማራ ክልል እና ቀደም ሲል በኦሮሚያ ክልል የተደረገው ሕዝባዊ እንቢተኝነት ተከትሎ ለወጥን በሻቱ አመራሮች ትግል የተፈጠረው አገራዊ ለውጥ ሂደት እና ይህን ተከትሎ የወያኔ ኃይል ‹‹እኔ ያልገዛኋት ኢትዮጵያ ትፍረስ›› በሚል እብሪት ሰሜን ዕዝን በማጥቃት ራሱ በከፈተው ጦርነት ተሸንፎ ወልቃይት ጠገዴ ከአፓርታይዳዊ አገዛዝ ነፃ የወጣበት ደም እና አጥንት የተከፈለበት ደማቅ ታሪክ በዋነኝነት ተጠቃሽ ናቸው።

ይህ በትውልድ ቅብብሎች ካለፈው አንጻባራቂ ታሪክ መካከል በሕዝብ ዘንድ የታሪኩን ክብደት ያክል በስፋት ያልታወቀውን ‹‹የከፋኝ ኢትዮጵያ ጅግኖች ግንባር የአርበኝነት ተጋድሎ›› በጥቂቱ አንስተን እንመልከት። ከፋኝ ትርጓሜው፤ (እንየው ውብነህ አቸነፈ) ‹‹የቀድሞው ተህሓት/ወያኔ የትግራይ ወሰን በማስፋፋት ተከዜን ተሻግሮ፣ ስሜን ምዕራብ ጎንደርን በመውረር፣ ከሱዳን ጋር ለመዋሰን፣ የወልቃይትን ሀብት ለመበዝበዝ እና ነባር ዐማራ ነዋሪውን የመጨፍጨፍ እና የማጥፋት እንቅስቃሴን መቃወም እና መታገል ማለት ነው።›› በዚህ የትግል ሂደት (1972-1985) ከወልቃይት፣ ከጠገዴ፣ ከአርማጭሆ፣ ከጠለምት፣ ከዳባትና ከወገራ (ሸማ ማጠቤትን ታላቅ እና ታናሽ የወደቁባትን) የተነሱ በሽህ የሚቆጠሩ አርበኞች ከፋኝ ብለው ወያኔን ከአማጺነቱ ጊዜ ጀምሮ ተፋልመዋል።

ለአብነት፡- ቀኝ አዝማች ሲሳይ አበራ (የወፍ አርግፍ ም/አስተዳዳሪ) ልጆቻቸውን ዘውዴ ሲሳይ እና ነጋ ሲሳይ ይዘው ሚያዚያ 27 ቀን 1972 ዓ.ም. ከወያኔ ጋር ውጊያ ከገጠሙ በኋላ ‹‹በግንባሬ ከተመታሁ ቅበሩኝ በጀርባየ ከተመታሁ እንዳትቀብሩኝ›› በማለት ከስድስት ሰዓት ውግያ በኋላ ተሰውተዋል። ይህ የከፋኝ ጀግኖች ግንባር ተጋድሎ የወያኔን አገዛዝ እየታገለ እስከ 1985 ዓ.ም. ድረስ መዝለቅ የቻለ ሲሆን፤ ከዚህ በኋላ በሺህ የሚቆጠሩ ታጋዮች ወደ ሱዳን በመሄድ ትግላቸውን በውጭ ሀገር ሆነው ሲያካሂዱ ቆይተዋል። (ላሊበላ ሙላው ገብሬ፣ ከፋኝ፣ 2013)

2.1. የማንነት ጥያቄ በጠቅላላው

የማንነት ጥያቄ (identity claim) መነሻው አንድ የተወሰነ ወይም ልዩ የሆነ የራስ መገለጫ ባህሪ አለኝ ብሎ ከማሰብ የሚመነጭ ነው፡፡ ማንነት ብዙ አይነት መልክ ያለው ሁናቴ ነው፡፡ ግለሰባዊ ማንነቶች እንደ ተጠበቁ ሆነው ሰዎች በጋራ የሚጠቀሟቸውና የሚጠይቋቸው ማህበራዊ የሆኑ ማንነቶችም አሏቸው፡፡ እነዚህ ማህበራዊ የሆኑ የጋራ ማንነቶች ከምን እና እንዴት ተፈጠሩ ለሚለው ጥያቄ ጥናቶች ጥንተ-መሰረት ህልውና እንዳላቸው ያትታሉ፡፡

የማንነት ጥያቄዎች ብዙ አይነት መልክ እና ባህሪያት አሏቸው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ጥያቄው እውቅናን ለማግኘት ብቻ ሊሆን ይችላል፤ ማለትም ጥያቄው የቋንቋ ወይም የኃይማኖት ወይም የባህል እውቅና  የመጠቀም ጥያቄ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ሲሆን ለተጠየቀው የማንነት ጥያቄ አወንታዊ መልስ በመስጠት ብቻ ምላሽ መስጠት ይቻላል፡፡ የማንነት ጥያቄን ተከትለው የሚመጡ ሌሎች ጥያቄዎችም አሉ፡፡ ከነዚህ ጥያቄዎች መካከል የመጀመሪያው ጥያቄ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ነው፡፡

ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ (self-administration) ፖለቲካዊ ጥያቄ ሲሆን፤ ጥያቄው በተወሰነ መልካምድር ላይ የሚኖሩና ተመሳሳይ ማንነት አለን ብለው የሚያስቡ ማህበረሰቦች የራሳቸው የሆነ አስተዳደራዊ መዋቅር ኑሯቸው የራሳችን በሚሉት ሰው መመራት መቻል ነው፡፡

ሌላኛው የማንነት ጥያቄን ተከትሎ የሚመጣ ጥያቄ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ (self-determination) ነው፡፡ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ ራስን በራስ ከማስተዳደርም ከፍ ያለ ፖለቲካዊ የቡድን መብት ነው፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ህጋዊ እውቅና አግኝቶ የህዝቦች መብት መሆን የጀመረው በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር ነው፡፡ ቻርተሩ በአንቀፅ 1(2) ላይ የእያንዳንዱ ሀገር ሕዝብ የራሱን ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በራሱ የመወሰን መብት እንዳለው ደንግጓል፡፡

ወደ ሀገራችን የሕግ ማዕቀፍ ስንመጣ ደግሞ የማንነት ጥያቄንና ተያያዥ መብቶችን በመደንገግ ደረጃ የመጀመሪያውና ዋነኛው ሕግ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ሕግ-መንግሥት ነው፡፡ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 39 ላይ እንደተደነገገው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ብሔር ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት አላቸው፡፡ ማለትም ብሔር ብሄረሰቦች እና ሕዝቦች ማንነታችን የሚሉት ባህላቸው፣ ቋንቋቸው እና ኃይማኖታቸው በሕግ እውቅና እንዲሰጠውና የራሳቸውን ባህል፣ ቋንቋ እና ኃይማኖት የመጠቀምና የማሳደግ መብት እንዳላቸው፤ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እና የመገንጠል መብት ናቸው፡፡ (ዝኒከማሁ፣ አንቀፅ 39)

2.2. የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት የማንነት ጥያቄ

የዚህ ጥናታዊ ጽሁፍ አንባቢያን ሊረዱት የሚገባ የሕግ ጭብጥ የወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ወደ ትግራይ ክልል በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የተካለሉት በ1967 ዓ.ም. የወያኔ አማጽያኖች በትጥቅ ትግል ወቅት በነበሩበት ጊዜ ያወጡትን ማንፌስቶ መሰረት በማድረግ ሲሆን፤ በሕግ ያልተደገፈ ‘ዲፋክቶ’ (de-facto) ድርጊት ደረጃ የተያዙት ደግሞ የወያኔ አማጽያኖች በትጥቅ ትግል ወቅት ከውጭ አገር ጋር የሚያገናኝ  ኮሪደር በመፈለግ ከ1980ዎቹ ወዲህ ቀጠናውን በሽምቅ ውጊያ (Gorilla Fighting) በወረራ በመያዛቸው ነው። በዚህም ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት እና ሰቲት ሁመራን ወደ የትግራይ ክልል የአስተዳደር ወሰን ያካለለ አንድም የፌደራል ሕግ (ሕገ-መንግሥት፣ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ) ባለመኖሩ፤ በወረራ የተያዙትም ከላይ የተመለከቱት ሕጎች (የሽግግር ጊዜ ቻርተር ፣ አዋጅ ቁ/ር 7/1984 እና የኢፊድሪ ሕገ-መንግሥት) ከመውጣታቸው በፊት በመሆኑ እና ሕግ በመርህ እና በልዮ ሁኔታ ደረጃ ወደ ኋላ ተመልሶ የማይሰራ በመሆኑ፤ የወልቃይት፣ ጠገዴ እና ጠለምት መልክዓ ምድር ሆነ በመልክ ዓምድሩ የሚኖር የወልቃይት ዐማራ ሕዝብ ወደ ትግራይ ክልል አስተዳደራዊ ወሰን የተካለሉበት ሁኔታ ወጥ ዲፋክቶ  (de-facto) ድርጊት በሕግ  ፊት  የማይፀና፣  የሕግ መሰረት የሌለው እና እንዳልተደረገ የሚቆጠር ቮይድ (Void) ፈራሽ ድርጊት መሆኑን ነው።

በመሆኑም ወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ሕዝብ ያነሳው ጥያቄ የሕዝቡን ማንነት፣ ታሪክ እና ማህበራዊ ትስስር ከግምት ውስጥ ያላስገባ በመሆኑ ከትግራይ ክልል ወጥቶ ይህን ግምት ወስጥ ወደ ሚያስገባ የዐማራ ክልል የመካለል ጥያቄ መሆኑን ልብ ሊባል ይገባል። በዚህም የወልቃይት ጥያቄ ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ጥያቄው ያልሆነውን ነገሮች በአሉታዊ የትርጓሜ ዘዴ (Negetive definition mechanism) በመጠቀም “The Right to Self-Determination vis-à-vis Irredentism: A Critical Analaysis on the Nature and the Legal and Institutional Framework of the Wolkaite Case” በሚል ርዕስ በጎንደር ዩኒቨርሲቱ ሕግ ት/ቤት ‹‹የሰብአዊ መብቶች ሕግ›› ድህረ-ምረቃ ፕሮግራም ስር በአበራ አበበ የተሰራ ጥናት መሰረት አድርገን እናብራራው።

በዚህ ማዕቀፍ

  1. የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ጥያቄ የማንነት እውቅና የማግኘት ጥያቄ ነውን?
  2. የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ጥያቄ ራስን በራስ የማስተዳደር ነው?
  • የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ጥያቄ  የራስን እድል በራስ የመወሰን (የመገንጠል)ጥያቄ ነው?
  1. የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት ጥያቄ የግዛት መስፋፋት ጥያቄ ነው?
  2. የወልቃይት ጥያቄ የደንበር/የወሰን ግጭት ነው?

የሚሉ ተጠይቆችን በሕግ መነፅር በቀጣይ በዝርዝር እንፈትሻለን፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop