በዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ
(ከእንግሊዝኛው ጽሁፍ የተተረጐመ)
ይህን መጣጥፍ ሰኔ 13 ቀን 2014 ዓ.ም በመፃፍ ላይ ሳለሁ አሶሽዬትድ ፕሬስ የተባለው የዜና ወኪል የሚከተለውን መረጃ አሰራጨ፡፡ “የዓይን እማኞች ዛሬ እሁድ ሰኔ 12 ቀን በአብዛኛው የአማራ ተወላጆች የሆኑ ከ2‚000 በላይ ሰዎች በአገሪቱ ኦሮሚያ ክልል መገደላቸውን ገልፀዋል፡፡”
በኢትዮጵያ የሚገኝ ምንጬ እንደገለፀልኝ ከሆነ ደግሞ 400 አማሮች የተገደሉ ሲሆን፣ 6‚000 ሕይወታቸውን ለማትረፍ ተሸሽገው ይገኛሉ፡፡
ሌላ ምንጭ አዛውንት የሆኑ አንድ ሙስሊም አማራን በመጥቀስ የሚከተለውን ዘግቧል፡፡ “ሸሽተን መስጂድ ውስጥ ተደበቅን፡፡ ተከትለውን መስጂዱ ውስጥ በመግባትም 46 ሰዎችን ገደሉ፤ ከተገደሉት ውስጥ 12ቱ የኔ ቤተሰቦች ናቸው፡፡ እኔንም ገድለውኝ ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡ አላህ ስለምን አተረፈኝ? ከነርሱ ጋር ብሞት በወደድሁ፡፡”
ይህ ጽሁፍ ለሕትመት በበቃበት ጊዜ ተሰብስቦ የተቀበረ የሟቾች ቁጥር 1‚511 የነበረ ሲሆን፣ 300 ያልተቀበሩና ከ10,000 በላይ ሸሽተው በየጥጋጥጉ እንደሚገኙ በቦታው የሚገኙ የሰብዓዊ መብት አንቂዎች ገልጸዋል፡፡
ከዚያም ወዲህ በቄለም ወለጋ ዞን፤ ሮብ ገበያ ወረዳ፣ ለምለም በተባለ ቀበሌ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም በ5 ሰዓታት ውስጥ ከ200 በላይ አማራዎች ተገድለዋል፡፡ ብዙዎች ተፈናቅለዋል፡፡
መጋቢት ወር ላይ እንዲሁ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባለው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባወጣው መግለጫ፣ የትግራይ ወራሪ ኃይሎች በንፋስ መውጫ፣ ጨና፣ ቆቦ እና ሌሎችም ሥፍራዎች በአማራ ተወላጆች ላይ የተፈፀሙትን የጅምላ ጭፍጨፋዎች አስገድዶ መድፈርና ዝርፊያ በፅኑ ኰንኗል፡፡
እ.ኤ.አ ህዳር 2020 ዓ.ም በአማሮች ላይ ማይካድራ በተፈፀመው ጭፍጨፋ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የ1100 ሲቪሎች አስከሬን መቁጠሩን የገለፀ ሲሆን፣ ቀይ መስቀል በበኩሉ ከአንድ ወር ያክል በኋላ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ይኖሩ በነበሩ 22ሺ የአማራና የአገው ሲቪል ነዋሪዎች ላይ ጭፍጨፋ መካሄዱን አጋልጧል፡፡
እንግዲህ ባለፉት አራት አመታት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተስፋፉ የመጡት ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶች እኒህን የመሰሉ ነበሩ፡፡
የሰው ልጅ በቀደሙት በርካታ አሰርት አመታት በወገኖቹ ላይ እጅግ አስከፊ ድርጊቶችን ሲፈፅም ቆይቷል፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ሰዎች ይህ ድርጊት “ምንጊዜም እንዳይደገም” በማለት በተነሱ ጊዜ ዘር ማጥፋትን የመሳሰሉ ወንጀሎችን የፈፀሙ የሚጠየቁበት አዲስ ስርአት እና ሀብትንና ግዛትን ለመቆጣጠርና በሰዎች ላይ ፍፁም ያልተገደበ ስልጣንን ለማረጋገጥ ግድያ፣ ማፈናቀልና ሰዎችን መጨቆን የሚካሄድበትን አሮጌና ኋላቀር ስርአት ይተካል የሚል እምነት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ዓለማቀፉ የዘር ማጥፋት ወንጀል ድንጋጌ እ.ኤ.አ በ1948 ዓ.ም ከፀደቀ ወዲህም ስምምነቱን 152 አገሮች ፈርመዋል፡፡ በዚያን ጊዜ አገሮች የዘር ማጥፋት ወንጀልን በጋራ ለመከላከል ቃል ገብተው ነበር፡፡
ሆኖም ከካምቦድያ እስከ የቀድሞዪቱ ዩጐዝላቪያ፣ ኢራቅ፣ ሶርያ፣ አፍጋኒስታንና ላይቤርያ ድረስ በተፈፀሙት አረመኔያዊ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች እና በሩዋንዳ፣ ስርብረኒካና ዳርፉር በተካሄዱት ጭፍጨፋዎች፤ እንዲሁም ባሁኑ ሰዓትም ከ2‚000 ዓመታት በላይ ታሪክ ባላት ጥንታዊቷ አገር ኢትዮጵያ እንደሚታየው ግድያዎች አልቆሙም፡፡ ይህች ጥንታዊት አገር ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ (ዳግመኛ) “ምንጊዜም እንዳይደገም” በማለት ድምጿን ስታሰማ መቆየቷ ተዘንግቶ ሰዎችን በማንነታቸው የተነሳ የማጥፋት ሥራ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የዘር ማጥፋት ወንጀልን “ምንጊዜም እንዳይደገም” ሳይሆን “ደግሞ ደጋግሞ መፈፀም” የሚለው ሐረግ የዘር ማጥፋት ወንጀል ድንጋጌ በ1946 ተቀባይነት ካገኘ ወዲህ ባሉት ዓመታት የተፈፀመውን ድርጊት ይበልጥ በትክክል ይገልፀው ይሆናል፡፡
በዚህ ፅሁፍ አማሮች (ሙስሊሞች፣ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችና ኦርቶዶክስ ኦሮሞዎች) በ1948ቱ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቅጣት የወጣው ስምምነት ውስጥ ለሰላሳ ዓመታት የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባዎች ሆነው የቆዩትን ለመግለፅ “ቡድኑ” የሚለው ቃል ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ (“ቡድን”የሚለው ቃል በተመድ ድንጋጌ ውስጥ group የተባለው ነው፡፡) አማሮች በኢትዮጵያ በመስፋፋት ላይ ያለው ዘር የማጥፋት ወንጀል የምለው በመንግሥት ስፖንሰርነት (ድጋፍ) የሚካሄድ ሽብር ዒላማዎች ሆነዋል፡፡ ክስተቱንም እያደባ ወይም እያጨለገ በማስፋፋት ላይ የመጣ የዘር ማጥፋት ወንጀል ያልኩት ባንድ በተወሰነ ጊዜ የተካሄደ ድርጊት ባለመሆኑ ነው፡፡ በዚህ አገባብ፣ እያደባ ወይም እያጨለገ ማለት “በዝምታ እያደገ የመጣ ወይም ቀስ በቀስ አይን በማይገባ መልኩ የሚከናወን” ድርጊት መሆኑን ለመግለጽ ነው፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚለው ሐረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለአግባብ ጥቅም ላይ በመዋል ላይ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ እ.ኤ.አ እስከ ሐምሌ፣ 2019 ድረስ በ152 አገሮች በተፈረመው ድንጋጌ የዘር ማጥፋት ወንጀል ራሱን የቻለ ወንጀል ሆኖ ተቀምጧል፡፡ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ እንደገለፀው ድንጋጌው በተለምዶ ተቀባይነት ያገኘው ሕግ አካል የሆኑ ዓለም አቀፍ መርሆዎችንም ያካትታል፡፡
“ይህም ማለት አገሮች የዘር ማጥፋት ወንጀል ድንጋጌን ፈረሙም አልፈረሙም ሁሉም የዘር ማጥፋት ወንጀል በዓለም አቀፍ ሕግ የተከለከለ ወንጀል መሆኑን አውቀው በህጉ እንዲገዙ ይገደዳሉ፡፡ በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የዘር ማጥፋት ወንጀልን መከላከል በዓለም አቀፍ ሕግ የማይጣስ መሆኑን በመጥቀስ ከዚያ ውጭ ወይም ነፃ መሆን የማይፈቀድ መሆኑን ገልፆአል፡፡
ኢትዮጵያ ድንጋጌውን ከመፈረሟም በተጨማሪ ከአሥር ዓመታት በኋላ ተመሳሳይ አንቀፆችን በወንጀለኛ መቅጫዋ አካታለች፡፡ በአህጉራችን በአፍሪካ የጦር ወንጀሎች፣ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ወይም በሰው ልጆች ላይ የተፈፀሙ ጭፍጨፋዎች የተካሄዱባቸውን ቦታዎች ሁሉ ተመልክቻለሁ፡፡ ከዚህም በመነሳት ኢትዮጵያ ውስጥ በመንግሥት በሚደገፉ ታጣቂ ኃይሎች ከሚፈፀሙት ወንጀሎች ይበልጥ አሰቃቂ የሆነ ወንጀል አለማየቴን ወይም አለመስማቴን በሐቅና በድፍረት መናገር እችላለሁ፡፡ እነዚህ ጭካኔ የተመላባቸው ወንጀሎችም የተከበረውን የነፍሰ ጡር ሴቶች አካል በመቅደድ በሽሉ መጫወት ወይም ሰውን ከነህይወቱ በእሳት ማቃጠል፣ የወንዶች ብልትን ሰልቦ በኩራት ማሳየት፣ እጃቸውና እግራቸው የታሰረ ሰዎችን በአውቶማቲክ ጠመንጃ መግደልን የሚያካትቱና በአገሪቱ አብዛኛዎቹ ክፍሎች በተደጋጋሚ የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ እነዚህን አረመኔያዊ ድርጊቶች በቪዲዮ ያላየ ጐልማሳ ኢትዮጵያዊ የለም፡፡ የሚያስገርመው በዚህ ሁሉ መካከል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም መንግሥት አንዲትም የውግዘት ቃል ያለማሰማት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን እንዴት ወደዚህ የዘቀጠ ደረጃ እንደወረዱና ከሁሉም በላይ ደግሞ እንዴት ይህን አይነቶቹን የወንጀል ድርጊቶች በአገር መሪ ደረጃ መላመድ እንደተቻለ መረዳት አዳጋች ነው፡፡ በእውነቱ ይህ ጠቅላይ ሚኒስትርና ተከታዮቹ በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ለፍርድ ካልቀረቡ፣ ማንም ሰው መቅረብ የለበትም፡፡ ይህ መሪ እጅግ በጣም ጨካኝ፣ ኃላፊነት የማይሰማውና ወደ እብደት በተቃረበ ራስን የማምለክ በሽታ የተለከፈ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በዓለማችን ያልታየ ፍጡር ነው፡፡ አሁኑኑ ሃይ ካልተባለም የከፋ ድርጊት እንደሚከተል ዓለም ሊያውቀው ይገባል፡፡
በዘር ማጥፋት ወንጀል ውስጥ እጅግ በጣም አዳጋቹ ጉዳዩ የድርጊቱን ዓላማ ወይም ፍላጐት ማወቅ ሆኖ ቆይቷል፡፡ አንድን ወንጀል ዘር ማጥፋት ብሎ ለመወሰን “በፈፃሚዎቹ በኩል የአንድን ጐሳ፣ ዘር ወይም ሃይማኖት ቡድን በአካል ለማጥፋት ዓላማ ስለመኖሩ የተረጋገጠ ፍላጐት መኖር አለበት፡፡ ባህልን ማጥፋት የሚለው በቂ አይደለም፤ አንድን ቡድን ለመበተን ብቻ የተፈፀመ ፍላጐትም እንዲሁ፡፡ ይህ ልዩ ፍላጐትም ነው የዘር ማጥፋት ወንጀልን የተለየ የሚያደርገው፡፡” በመሆኑም የዘር ማጥፋት ወንጀል ሁለት ዋና ዋና ባህርያት አሉት፤ እነሱም አካላዊ (የወንጀሎቹ መፈፀም) እና የወንጀሎቹን ዓለማ የሚወስነው አዕምሯዊ ሁኔታ ናቸው፡፡ ከዚህም በላይ ማስረጃዎቹ የወንጀሉ ሰለባዎች በድንጋጌው ከተጠበቁት ከአራቱ ቡድኖች (የብሔር፣ ዘውግ፣ ዘርና ሃይማኖት) የአንዱ አካል በመሆናቸው ወይም መስለው ስለታዩአቸው ሆን ተብሎ ወይም ታስቦበት ዒላማ መደረጋቸውን ማረጋገጥ መቻል አለባቸው፡፡ “ይህም ማለት የጥፋቱ ዒላማ ቡድን እንጂ አባላቱ በግላቸው ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀል የቡድኑ አንድ አካል ተለይቶ ሊታይ የሚችል እስከሆነ ድረስ (በመልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የተከለለ አካባቢ ጭምር ከሆነ) በቡድኑ ላይ ብቻ ሊፈፀምም ይችላል፡፡”
የዓለም አቀፍ ሕግ ተማሪ፣ ከፍተኛ ልምድ ያካበተ ዲፕሎማትና ከሁሉም በላይ በዘር ማጥፋት ወንጀልና በሰው ልጆች ላይ ወንጀሎችን በመፈፀም የተከሰሱ ሰዎችን የፍርድ ሂደት በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች እንደተከታተለ ሰውና ባለሙያ ፤ እንዲሁም ለሁለት ዓመታት በአራት የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተፈፀሙ ድርጊቶችን በጥንቃቄ ከመረመርኩ በኋላ እንደተገነዘብኩት በኢትዮጵያ ውስጥ በዘር ማጥፋት ወንጀል ድንጋጌው የተቀመጡትን ቃላት በቀጥታ ሳይቀር የሚገልፅ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈፀሙን አረጋግጣለሁ፡፡ በነዚህ አራት አካባቢዎች በቡድኑ ላይ የተፈፀሙትን የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ዓላማ ማረጋገጥም በጣም ቀላል ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ዓላማዎቹን ወይም ፍላጐቶቹን የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ከ15 ዓመቱ ጀምሮ አባል የነበረበት የኢሕአዲግ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በግልፅ አስቀምጦታል፡፡ የሕወሓት መሥራችና የኢሕአዲግ ከፍተኛ አመራር የነበረው ስብሃት ነጋ ባንድ ወቅት፣ “የኢሕአዲግ አጀንዳ እንዳይፈፀም መሰናክል የሚሆኑት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና አማራ ስለሆኑ መወገድ አለባቸው” ብሏል፡፡ ይህን ቃል በቃል ያልተናገረው ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም አማራና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የኢሕአዲግ አጀንዳ ጠላቶች ተደርገው እንደሚታዩ መነገሩ የተረጋገጠ ነው፡፡ ይህን ዓላማ ወይም ፍላጐት ያለጥርጥር የሚያረጋግጡ ብዙ የተቀዱና የተሰነዱ ማስረጃዎች አሉ፡፡ እኔ ራሴ፣ የሥራ ባልደረቦቼና ዓለም አቀፍ የሕግ ባለሙያዎች የመረመሯቸው የዘር ማጥፋት ወንጀሎች በሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ በድምፅ፣ በቪዲዮና በፅሁፍ የተሰነዱ ሲሆኑ፣ የበርካታ ምስክሮች የስም ዝርዝርም አለ፡፡ አራቱን ጉዳዮች በተመለከተ የዓለም አቀፍ ህግ ባለሙያዎች በነዚያ አካባቢዎች የዘር ማጥፋት ወንጀሎች መካሄዳቸውን የሚያረጋግጡ ከበቂ በላይ ማስረጃዎች መኖራቸውን ያረጋገጡ ሲሆን፣ እነዚህም ማስረጃዎች ለቀጣይ ምርመራና በነዚህ ወንጀሎች እንደተሳተፉ የተለዩ ከፍተኛ ባለስልጣኖችን ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለማቅረብ የሚያስፈልጉትን እንደሚያሟሉ ደምድመዋል፡፡ (ሻሸመኔ፣ ወለጋ፣ መተከል፣ እና አጣዬ)*፡፡
ማስረጃዎቹ የመንግሥት አካል ሳያውቅ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ በየአካባቢዎቹ በነበሩ ነፃ መርማሪዎች አማካይነት የተሰበሰቡ ናቸው፡፡ መንግሥት እንዲህ አይነቶቹ ወንጀሎች ወደተፈፀሙባቸው አካባቢዎች ነፃ መርማሪዎችን ማስገባት ቀርቶ ጋዜጠኞች እንኳን እንዲታዩ አይፈቅድም፡፡ መንግሥት በነዚህ ወንጀሎች ተሳታፊ ስለነበረ ነፃ መርማሪዎችን ለመቀበል አለመፍቀዱ አይደንቅም፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት የተፈፀሙት ወንጀሎችን በመመርመር ላይ ሳለን ሌሎች ከነዚያም የከፉ ጉዳዮች እየተቆለሉ በመምጣታቸው ምርመራውን በቅርቡ እ.ኤ.አ ከህዳር 2021 ጀምሮ በመንግሥት የተፈፀሙ የጦር ወንጀሎችን በአገሪቱ ሰሜን ክፍል ከሕወሓት ኃይሎች ጋር በተካሄደው ጦርነት እንዲመረምር ሃላፊነት ከተሰጠው ከተመድ ሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ጋራ በመተባበር ካልሆነ በስተቀር ሥራውን ማከናወን አልተቻለም፡፡ ባሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አንቂዎች እየጠየቁ ያሉት የተመድ ሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ውሳኔውን በመከለስ የጊዜ ማዕቀፉን ይህ ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እንዲያደርግና ባሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ እጅግ በጣም አጣዳፊና አሳሳቢ የሆነውን የአማራን ዘር የማጥፋት ወንጀል እንዲያካትት ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት እ.ኤ.አ በ2002 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤትን የመሠረተው የሮም ስምምነት አካል አይደለም፡፡ በመሆኑም የዘር ማጥፋት ወንጀልን ወደ ፍርድ ቤቱ ማቅረብ አስቸጋሪ ቢሆንም ፈፅሞ የማይቻል ግን አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ በዳርፉር ከተካሄደው የዘር ማጥፋት ወንጀል ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ሱዳን ከዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ አልነበረችም፡፡ የሮሙ ስምምነት ፈራሚ አገር ስላልነበረች የመተባበር ግዴታም አልነበረባትም፡፡ ነገር ግን የተመድ ሰብአዊ መብት ምክር ቤት ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት ፀጥታ ምክር ቤት እንዲታይ ሃሳብ አቀረበ፡፡ የፀጥታ ምክር ቤቱም “በሱዳን የሚታየው ለዓለም ሰላምና ፀጥታ ስጋት እንደሆነ በመወሰን” ጉዳዩን እ.ኤ.አ መጋቢት 2005 ዓ.ም ወደ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት መራው፡፡ የዳርፉር ሁኔታ በተባበሩት መንግሥታት ፀጥታ ምክር ቤት ወደ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የተመራ የመጀመሪያው ጉዳይና የሮምን ስምምነት ባልፈረመ አገር ግዛት ውስጥ የተካሄደ የመጀመሪያው የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት ምርመራ ነበር፡፡ የዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት የዘር ማጥፋት ውንጀላ የመጀመሪያው ምርመራም ነበር፡፡ የሱዳኑ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሺር በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የሚፈለግ የመጀመሪያው በስልጣን ላይ ያለ ፕሬዝዳንትና በፍርድ ቤቱ በዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ የተመሰረተበት ሰው ሆኗል፡፡ ዳሩ ግን ሁለቱም በስሙ የወጡ የፍርድ ቤት ማዘዣዎች ተፈፃሚ ባለመሆናቸው እስከ ዛሬ ፍርድ ቤት አልቀረበም፡፡
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን፣ በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችንና የጦር ወንጀሎችን የመዳኘት ስልጣን የተሰጠው ተቋም ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ስምምነት አባል አገሮች ዜጐችንና ወንጀሎች በተፈፀሙበት ግዛት የተወነጀሉ ሰዎች ዜግነት ምንም ይሁን ምን ህግ ፊት የማቅረብ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የፀጥታው ምክር ቤት ጉዳዮችን ሲመራለት የማየት ስልጣን አለው፡፡ የደንቡ አንቀን 86 የአገራት ትብብርንና የፍርድ ቤት ትእዛዞችን ማክበርን የሚመለከት ነው፡፡ በዚህ አንቀፅ መሰረት፣ “አባል አገራት በደንቡ ለፍርድ ቤቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት በሚያደርጋቸው የወንጀል ምርመራዎችና ክሶች ሙሉ በሙሉ የመተባበር ግዴታ አለባቸው፡፡” አንቀፅ 87 (5) የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት አባል ያልሆኑ አገሮችን ትብብር የተመለከተ ነው፡፡ አንቀፁ ፍርድ ቤቱ “የደንቡ ፈራሚ ያልሆነን ማንኛውንም አገር በዚህ ክፍል (አንቀፅ) መሰረት በጊዜያዊ ስምምነት፣ ወይም ሌላ አይነት አግባብነት ባለው አሰራር እርዳታ እንዲደረግለት ሊጋብዝ ይችላል፡፡” የመተባበር ግዴታ ያለባቸው ግን አባል ወይም ፈራሚ አገሮች ብቻ ናቸው፡፡ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ሥልጣን የሚኖረው በአባል አገሮች ግዛት፣ ፈቃደኞች በሆኑ አባል ያልሆኑ አገሮች ወይም አባል ባይሆኑም ጉዳያቸው በተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ወደ ፍርድ ቤቱ በተመሩ አገሮች ላይ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ፈራሚ አገር ስላልሆነች ጉዳዮቿ ወደ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ሊቀርቡ የሚችሉት በመንግሥቱ ፈቃደኝነት ወይም እንደ ዳርፉሩ ጉዳይ በተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ሲመራ ብቻ ነው፡፡
በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል የዘር ማጥፋት ወንጀልን ትርጉም ያላዛበ ለመሆኑ አንዳችም ጥርጣሬ ሊኖረን አይገባም፡፡ የኦነግ ተከታዮች እንደ መካከለኛው ዘመን ወራሪዎች የአማራ መንደሮችን አቃጥለዋል፤ ዘርፈዋል፤ ገድለዋልም፡፡ ኦነግ በአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አመራር ስር የሚመሠርታትን አዲሲቷ የኦሮሞ ግዛት ለማመላከት “ኦሮሙማ” የሚል ሐረግ ፈጥሯል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እናቱ ሁሌም “ሰባተኛው የኢትዮጵያ ንጉስ” እንደሚሆን ትነግረው እንደነበር ለፓርላማ ገልፆአል፡፡ በዚህ የእናቱ ትንቢት እንደሚያምንም ተናግሯል፡፡ ለብዙዎች ያን ግዛት ለመገንባት በአጣዳፊ ስራ የተጠመደ ይመስላቸዋል፡፡
የዚህ ግዛት መመስረት ዋነኛ መሰናክሎች አማሮች ናቸው፡፡ ምክንያቱም ሙከራው በአማራ ሥልጣኔ፣ ባህልና ሃይማኖት ፍርስራሽና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አማሮችና ተባባሪዎቻቸውን በመደምሰስ አገር ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ ስድስት ሚሊዮን ህዝብን የሚወክለው ሕወሓት ዳግመኛ ለስልጣን እንደማይበቃ ቢታወቅም፣ የኔ ነው የሚለውን የአማራ መሬት በድርድር ለመያዝ እንዲፈቀድለት ለማድረግ የሚገለገልበት አስፈሪ ኃይል ገንብቷል፡፡ በ”ኦሮሙማ” ግዛት ስር የራስ ገዝ አስተዳደር በመመስረት (ለመገንጠል አመቺ ጊዜ እስኪፈጠርለት ድረስ) ለመቆየት ፈቃደኛ ነው፡፡ አማሮች በ“ኦሮሙማ” ውስጥ በሁለተኛ ደረጃ ዜግነት ዝቅ ብለውም ሆነ የአባቶቻቸውን መሬት ለሕወሓት ሰጥተውና ባህላቸውን፣ ማንነታቸውንና ሃይማኖታቸውን የመካከለኛው ዘመን አስተሳሰብ ለተጠናወታቸው የኦሮሞ አክራሪዎች አሳልፈው ለመስጠት፤ እንዲሁም በፈጠራ ትርክት የአማራ መሬትን ሊወስዱ ለሚፈልጉት የሕወሓት ኃይሎች የሚፈልጉትን ለመስጠት ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ የፈጠራ ትርክቱን ሐሰተኝነት የሚያረጋግጡ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ታሪካዊ ሰነዶች፣ በሕይወት ያሉ ታሪክ አዋቂዎችና ታዛቢዎች አሉ፡፡
እነዚህ የምናያቸው ግድያዎችና ሐፍረተ ቢስ ወረራዎች በገዳ ስርዓት ውስጥ የሚመሰረተው የ“ኦሮሙማ” ግዛት መምጣት ምልክቶች ናቸው፡፡
ኬንያ የሚገኘው አፍሪካን መሰረት ያደረገ የኒሎቲክና ኦሞቲክ የአፍሪካ ሕዝቦች (NOPA) ህብረት የኦሮሞ አርብቶ አደሮች በእድሜ ላይ የተመሰረተውን ገዳ ስርዓት በዓለም ቅርስነት መመዝገብ በመቃወም ለዩኔስኰ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት) ደብዳቤ ፅፎአል፡፡
“ራሱን ኦሮሞ (ጋላ) ብሎ የሚጠራውና የኢትዮጵያን ግዛት በአዳል-ኡስሊም የጂሃድ ጦርነት በ16ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ የወረረው ጐሳ በኢትዮጵያ ለም ደጋ መሬቶች ላይ ሰፍሮ የግብርና ኑሮ ጀመረ፡፡ ከዚያም የዘላኑን ገዳ ስርዓት በመተው በተለይ ወደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የፈለሱት አንዳንድ ጐሳዎች እንደ ጐረቤቶቻቸው በንጉስ የሚመራ መንግሥትን መሰረቱ፡፡ የገዳ ሥርዓት ቅሪት ዘላንና አረማዊ በሆኑ ደቡብ ኢትዮጵያ የሚገኙ የቦረና ጐሳዎችና ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው በሆኑት በኬንያ የታና ሸለቆ የሚገኙ ኦርማ (ታና ጋላ) ይታያል፡፡ ጋሎች በታና፣ ጁባና ሸበሌ ወንዞች የሚገኙ የአገሬውን ተወላጅ ባንቱ ጐሳዎች አፈናቅለዋል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ገድል በሆነው በአረብኛ ቋንቋ “ኪታብ አል-ዛኑጅ” እንደተዘገበው በዚያም በፖኰም፣ ጊርያማ፣ ንዪካ ወዘተ ላይ አሰቃቂ ወንጀል ፈፅመዋል፡፡ ባሁኑ ሰዓት የኦሮሞ ብሔረተኞች የገዳ ሥርዓትን በመናፈቅ ላይ ናቸው፡፡ በመሆኑም እፁብ ድንቅ ስለሆነ “አገር በቀል ዲሞክራሲያዊ” ተቋም ተረት እየፈበረኩ ይገኛሉ፡፡ በቅርብ ጊዜ የፈጠሩት የፓን-ኦሮሞ ርዕዮተ ዓለም የገዳ ወካይነትን በመጠቀም የኦሮሞን ማንነትንና ብሔረተኝነት አሳይቷል፡፡ እዚህ ላይ ክቡርነትዎን ማስገንዘብ የምንፈልገው እጅግ ጨካኝ የነበሩት የጋላ አርብቶ አደሮች በሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ያደረጉት የተስፋፊነት ጦርነት በኢትዮጵያና በኬንያ ይኖሩ የነበሩ ብዙ የዳበሩ ማህበረሰቦችንና የሰለጠኑ ግዛቶችን ማውደማቸውን ነው፡፡ ስለዚህ የገዳ ሥርዓትን በማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት መዝገብ ውስጥ የማስገባቱ ሃሳብ አንድም የሰው ልጆችን መስደብ ነው አለያም ከ16ኛው ምዕተ አመት ጀምሮ በኦሮሞ አርብቶ አደሮች ለሚጨፈጨፈው የሰሜን ምሥራቅ አፍሪካ ጩኸት ጆሮ ያለመስጠት ነው፡፡
የገዳ ሥርዓት በጨለማው ዘመን ከሚካሄዱት አረመኔያዊ ልማዶች አንዱ ነው፡፡ የኦሮሞ ነገዶች የማረኳቸውን ጠላቶች በጭካኔ በመስለብና በመደምሰስ የታወቁ ናቸው፡፡
ይህ በአውሮፓና በአፍሪካ ቤተ መጻሕፍት እንዲሁም በኢትዮጵያ የታሪክ መጻሕፍት (በዚህ መንግሥት በዘዴ በመውደም ላይ ካሉት) ተሰንደው የሚገኙ የገዳ ሥርዓትን ኋላቀርነት መዝግበው ካቆዩልን በርካታ ፅሁፎች አንዱ ነው፡፡ የብዙኃኑ አማሮች ፍላጐት የዚህ በበላይነትና በወረራ የኢትዮጵያን ሕዝብ በሙሉ በኃይል ለመቆጣጠር የሚንቀሳቀስ ሥርዓት ተቃራኒ ነው፡፡ አማሮች የሚፈልጉት ትክክለኛና አድልዎ የሌለበት ሁሉም ህዝብ በአገሪቱ ሕግ ጥላ ስር በእኩልነት የሚታይበትን ሥርዓት ነው፡፡ አማሮች የራሳቸው የሆነውን ጠብቀው ማቆየት ይፈልጋሉ — መሬታቸውንና ሰብአዊ መብቶቻቸውን፡፡ ነገር ግን አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት አማሮች ባሁኑ ጊዜ ይሰደባሉ፤ ይጨፈጨፋሉ፣ ቤተ ክርስቲያን እንደገባች ውሻ ይሳደዳሉ፤ ከነሕይወታቸው ይቃጠላሉ፣ በተገኘው መንገድ ሁሉ በሕወሓትና በኦሮሞ ፅንፈኞች ይዋረዳሉ፡፡ ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስና ቅዱስ ቁርአን መሠረት ለትክክለኛ ነገር የመታገል ጥልቅ ስሜት አላቸው፡፡ የ“ኦሮሙማ” ግዛት አይመሰረትም፤ ሕወሓትም የአማሮችን ከጥንት ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ መሬት ፈፅሞ አይወስድም፡፡ አማሮች ከ2000 ዓመታት በላይ በገነቡት አገር ይህን የመደምሰስ ወይም የመገለል ሙከራ አይቀበሉም፤ ይቋቋሙታል፡፡ በዚህ ጥርጥር የለኝም፣ በግልፅ የሚታወቅ ነገር ነው፡፡ አማሮች ህዝብ በሰላም ተቻችሎ የሚኖርባትና የተሻለ ጊዜ የሚጠበቅባት አገርን እንደገና መገንባት የሚቻለው እነዚህ ሲሳኩ ብቻ በመሆኑ ስለሚያምኑ ቃልኪዳን ገብተዋል፡፡ አዲስ የተፈጠሩት የኦሮሞ ልሂቃን ግን የሚያስቡት ተቃራኒውን ነው፡፡
አማሮች ለምዕተ ዓመታት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ሲያስከብሩ ኖረዋል፡፡ የአክሱም ስልጣኔ ወራሾች ከሆኑት የትግራይ ተወላጆች ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ዛሬ ያለችበት አድርሰዋታል — የበለፀገችና የጥንታዊ ባህል ማዕከል፣ ድንቅ የፅሁፍ ቋንቋ መገኛ፣ ቅኝ ገዢዎችን ድል በማድረጓ የምትኮራ አገር፣ የነፃነት ጠንካራ ምሽግ፣ በመላው ዓለም የሚኖሩ የጥቁር ሕዝቦች የተስፋ ምድር፡፡ ኦሮሞዎች በኢትዮጵያ ለፖለቲካ ስልጣን የበቁት ዘግይተው ነው፡፡ አመጣጣቸው ከአሁኗ ኢትዮጵያ በስተደቡብ ጫፍ ነው፡፡ ከትግራይ፣ ከአማሮችና ሌሎችም ነገዶች ጋር ያደረጉት ፈጣን ውህደት ኢትዮጵያን ጠንካራና የማትበገር አገር ከማድረጉም በተጨማሪ ከጊዜ በኋላ ኢትዮጵያውያንን የሚከባበሩና ብዝሃነት ያለው ህብረተሰብ መፍጠር እንዲችሉ አድርጓል፡፡ ኦሮሞዎች ከጊዜ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ማዕከል በመምጣት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት በመጠበቅና በመከላከል እንዲሁም ኢትዮጵያን ወደ ዘመናዊው ዓለም በማምጣትና በሁሉም ረገድ ንቁ ተሳታፊዎች ሆነው ቆይተዋል፡፡ ኢትዮጵያን በመመስረትና በማፅናት ረገድ እያንዳንዱ ነገድ የተጫወታቸው ሚናዎችና ወደ ማዕከል (ደጋ) የተደረገው አመጣጥ ቅደም ተከተላቸውም የሁሉንም ዜጐች መብቶች በመወሰን ረገድ ቁም ነገር ተደርጐ ሊወሰድ አይገባም፤ አግባብነትም የለውም፡፡ መቼም አገሮችን የመሰረቱ ሰዎች አንድ ቦታ ላይ ባንድ ጊዜ አልደረሱም፡፡ በሂደትም ሊጠኑ፣ እውቅና ሊሰጣቸውና አገርን ከራሷ ጋር እንድትታረቅ በማድረግ ረገድ ሊያግዙ የሚችሉ ባርነትን፣ መሬት መንጠቅን፣ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችንና ግጭቶችን የመሳሰሉ ታሪካዊ ስህተቶችን ፈፅመዋል፡፡ እነዚህን በማዛባት ሰዎችን በጐሳቸውና በሃይማኖታቸው ላይ በመመስረት የመካከለኛውን ዘመን አይነት ምደባ ወይም ፍረጃ እንደገና ለማምጣት መሞከር አይገባም፡፡ ይህ መንግሥት ግን ይህን ሙትና በሁሉም የተጠላና ኋላቀር ሥርዓት በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለጥናት ብቻ ሊነሳ ቢገባም ሥርዓቱን ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡
ይህች አገር የሁሉም ኢትዮጵያውያን ትሆናለች ወይም የማንም አትሆንም፡፡ በጦር አበጋዞች የምትተዳደርና ለቀጠናው ሰላም ደህንነት ቋሚ ስጋት ከመሆንም በላይ ከአፍሪካ ቀንድ ባሻገር በሌሎችም ላይ ችግርን የምታስከትል የከሸፈች አገር ትሆናለች፡፡ የማያባራ የእጅ አዙር ጦርነት የሚካሄድባት ምድር ትሆናለች፡፡ የኦሮሞ አክራሪዎችና የሕወሓት ተስፋፊዎች ይህን ማየት እንዴት ይሳናቸዋል? ኢትዮጵያ የተለያዩ ባህሎችና ታሪክ ጥልፍ እና ጐሳን ከቁብ ሳይቆጥር ሲጋባና ሲዋለድ የኖረ ሕዝብ ያለባት አገር በመሆኗ ከሃምሳ ዓመታት በኋላ የበቀሉ ጥቂት ልሂቃን እንደሚመኙት በዘውግ/ጎሳ ላይ የተመሰረቱ ነፃ ሉዓላዊ አገሮችን መመስረት አይቻልም፡፡ ቀላል አመክንዮ ብንጠቀም ኢትዮጵያ ልትቀጥል የምትችለውና ህዝቧም በስምምነት ተዋዶና ተዋህዶ ሊኖር የሚችለው በሽግግር ፍትህ አማካይነት መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
እያደባ (እያጨለገ) በመስፋፋት ላይ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል ዓላማ አስገዳጅ የወሊድ ቁጥጥር በመፈፀም የአማራን ሕዝብ ቁጥር መቀነስ (የዘር ማጥፋት ድንጋጌ፣ አንቀፅ 11 )፤ ሰዎችን ከትውልድ ቀዬአቸው ማፈናቀል፣ ህፃናትን በማፈን ያልተረጋጋ ሁኔታን መፍጠርና ዘለቄታዊ ስጋትን መፍጠር (አንቀፅ 11 e እና c)፤ ማንኛውንም የቡድኑን ሰው ማሰቃየት፣ ጅምላ ጭፍጨፋና ግድያ መፈፀም፤ እና ሴቶችን በባለቤቶቻቸውና ልጆቻቸው ፊት መድፈር ነው፡፡ በኢትዮጵያ በክርስቲያኖችም ሆነ በሙስሊሞች (የጄኔቫ ድንጋጌ፣ አንቀፅ 11 a እና b) ላይ የሚፈፀመው ወንጀል የህዝቡ ዕጣ ፈንታ የአንድ ጐሳን የበላይነት በሚያምኑ የመካከለኛው ዘመን መሪዎች እጅ በመግባቱ ተገቢው ትኩረት አልተሰጠውም፡፡ ከፍ ብለው የተዘረዘሩት በሙሉ በአሁኗ ኢትዮጵያ ተፈፅመዋል፡፡ እንዲህ አይነቱ መረን የለሽ ስልጣንና አይን ያወጣ የሕዝብ መብቶችን መጣስ የሚፈፀመው ደግሞ የሰብአዊ መብቶች ሻምፕዮኖችና የዘር ማጥፋት ወንጀል ድንጋጌው ጠባቂዎች ነን የሚሉት ምዕራባውያን መሪዎች እያወቁ ነው፡፡ ይሁንና ሁሉም ድርጊቶች ባግባቡ ተሰንደውና ተጠብቀው ለፍርድ ቤት የሚቀርቡበትን ቀን እየተጠባበቁ ነው፡፡
ወንጀለኞቹ አማራን እንደ ሕዝብ ማጥፋትና ባህሉን፣ ቋንቋውንና በታሪክ ውስጥ ያለውን ስፍራ ፈፅሞ መደምሰስ እንደማይችሉ ያውቃሉ፡፡ ይህ ሁሉ ጥረት የሚደረገው የሕዝብን ብዛት ለማዛባት፣ እጅግ አስፈሪና ሕዝብን አዋራጅ ድርጊትን በመፈፀም ሕዝቡ አንገቱን እንዲደፋና በፖለቲካ ረገድ ከወንጀል ተባባሪውና ከትውልድ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣ የአማሮችን መሬት ጨምሮ መንጠቅ ከሚፈልገው ሕወሓት ጋር የአገሪቱን 1/3ኛ ስለተቆጣጠረ ለወራሪ አክራሪ ኦሮሞዎች የበላይነት እንዲያጐበድድ ለማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን ኩሩዎቹ አማሮች ለመንበርከክ ፈቃደኞች አይደሉም፤ ይልቁንም ማንም ከማንም የማይበልጥባት፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተች አገር ለመመስረትና የኢትዮጵያን ፖለቲካ ዳግመኛ መታነፅ ለማረጋገጥ አጥብቆ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
“በ208 ዓመተ ዓለም የሮማ ጦረኛ ንጉሥ ሴፕቲሙስ ሲቪሩስ በደሴቲቱ ሰሜን የሚኖሩ ጐሳዎችን ለመግዛት በማሰብ ብሪታኒያ ገባ፡፡ እነዚያ ጐሳዎች ባሁኑ ጊዜ የዘመናዊቱ ስኰትላንድ ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ሲቪሩስ እነዚህ ጐሳዎች (ያሁኖቹ ስኰትላንዳውያን) አሻፈረኝ፣ አንገዛም ማለታቸውን ባወቀ ጊዜ ሊጠርጋቸው (ባሁኑ ጊዜ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመባል የሚታወቀውን) ፖሊሲ ነደፈ፡፡ በ210 ዓመተ ዓለም የዘር ማጥፋት ዘመቻውን ጅምላ ጨፍጫፊው እብድና ወደ በኋላውም ወንድሙ ጌታን እናቱ ፊት የገደለው ልጁ ካራኩላ እንዲፈጽም መደበው፡፡ የዘመቻውን እድሜ አሳጥሮ ስኰትላንድን ከጥፋት ያዳናት ምናልባት የሲቪሩስ በዓመቱ መሞት ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ካራኩላ በታሪክ አዋቂዎች የሚታወቀው እጅግ በጣም ክፉ ከሚባሉት የሮማ ነገሥታት አንዱ በመሆኑ ነው፡፡ በጥንታዊቱ ሮም የዘር ማጥፋት ወንጀል ቀድሞ በአንድ አካባቢ በሚኖሩ ኗሪ የአገሬው ሕዝቦች ላይ ከተፈፀመ ተቀባይነት እንዳለው ወታደራዊ ስልት ነበር የሚቆጠረው፡፡
የስኰትላንዱ መሪ ሮማውያንን በማውገዝ ከውጊያው በፊት ለወታደሮቹ ባደረገው ንግግር የሚከተለውን ብሎ ነበር፡፡
“የዓለም ወራሪዎች (የሆኑቱ እኒህ ሰዎች) በሁሉም ስፍራ በሚያካሂዱት ዘረፋ ምድርን መዝብረዋል፤ በዝብዘዋል፡፡ ጠላታቸው ሃብታም ከሆነ፤ ስግብግብ ይሆኑበታል፤ ድሃ ከሆነ በበላይነት የመግዛት ከፍተኛ ጉጉት ይኖራቸዋል፡፡ ምሥራቅም ሆነ ምዕራብ አላረካቸውም፡፡ በሰዎች መካከል ብቸኛ ሆነው ለድህነትና ለሃብት እኩል ይቋምጣሉ፡፡ ለዝርፍያና ጭፍጨፋ ግዛት የሚባል የሐሰት ስምን ያላብሱታል፤ ብቸኝነትን (ጭር ያለ ሁኔታን) ፈጥረው ሰላም ነው ይሉታል፡፡” ባሁኑ ጊዜ የመጨረሻው ዓረፍተ ነገር በስፋት እየተሰራጨና እየተጠቀሰ ይገኛል፡፡ ምክንያቱም “በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የዘር ማጥፋት ወንጀለኞችን ድሮም ሆነ አሁን ህብረተሰብን ፈፅሞ በማጥፋት የሚያሻሽሉት (የሚያሳድጉት) የሚመስላቸውን ሰዎች አስተሳሰብን በትክክል ስለሚገልጽ ነው፡፡”
ዛሬ ማንኛውም አስተዋይ ኢትዮጵያዊ የአክራሪ ኦሮሞች መሪ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና የሕወሓት ተስፋፊዎች የአዕምሮ በሽተኞች መሆናቸውን ያውቃል፡፡ እንዲህ ካልሆነ እንደምን ጤናማ አዕምሮ ያለው ሰው ይህን የማያባራ ግድያ ሊረዳ ይችላል? እንደምን ከዚህች ብዝሃነትን እንደ ጥንካሬ የሚያከብርና የባህልና የቋንቋ ልዩነቶችን መጠበቅ የሚሻ የሰለጠነ አዕምሮ ህዝብ ያለባት አገር ነፃ አገሮችን ቆርሶ መፍጠር ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ይረዳል? አሁን እየተሰበከ ያለው ነገር ጭካኔን የሚወልድ ምናባዊ አገርን በሕዝብ ላይ ከመጫን የዘለለ አይደለም፡፡ ሊዮ ቶልስቶይ “ዘ ሎው ኦቭ ላቭ ኤንድ ዘ ሎው ኦቭ ቫዮለንስ” በሚለው መፅሐፉ የሚከተለውን ፅፏል፡፡
“ሁላችሁም ልብ በሉ፣ በተለይ ወጣቶች፤ በሌሎች ላይ በኃይል ምናባዊ መንግሥትን ለመጫን መፈለግ ግልብ የሆነ አጉል እምነት ብቻ ሳይሆን የወንጀል ስራም ጭምር ነው፡፡ ይህ ተግባር የሰውን ልጅ ደህንነት ማረጋገጥ ካለመቻሉም በላይ ውሸትን፣ግብዝነትንና በውስጣችን ያለን እጅግ የወረደ ስሜት ለመሸፋፈን የሚደረግ መሆኑን ተረዱ፡፡”
በኢትዮጵያ የጥላቻ መነሻዎች ሐሰተኛና ምናባዊ ወይም የተፈበረኩ ትርክቶች ናቸው፡፡ እነርሱን ተከትለው የሚመጡትም በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ የዘር ማጥፋትና የጦር ወንጀሎች ናቸው፡፡ መንግሥት በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የእርስ በርስ ጦርነት የሚያየው ክፉውን ከስሩ መንግሎ በመጣል የጠቅላይ ሚኒስትሩ በሆነው ብልፅግና ፓርቲ ስር የብልፅግናን መንገድ ለመጥረግ አስፈላጊ እንደሆነ ሂደት ነው፡፡
እስከ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ድረስ የዘር ማጥፋት ወንጀል አብዛኛውን ጊዜ “ለእድገት” የሚከፈል ዋጋ ተደርጐ ነበር የሚቆጠረው፡፡ በ16ኛው ምዕተ አመት የስፔን ቅኝ ገዢዎች የሒስፓኒዮላን (ባሁኑ ጊዜ ሐይቲና ዶሚኒካን ሪፐብሊክ) ተወላጆች ብዛት በአንድ ትውልድ እድሜ ብቻ ከ400‚000 ወደ 200‚000 አወረዱት፡፡ የቤልጂየም ቅኝ ገዢዎች የኰንጎን ሕዝብ ከ20 ሚሊዮን በግማሽ ቀነሱት፡፡ ስታሊን በዩክሬን ላይ ረሃብ ፈጥሮ ወደ 5 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ገደለ፡፡ እነኚህ ሰዎች በሙሉ የፈጸሟቸው ዘር የማጥፋት ወንጀሎች ለሰለጠነው ዓለም ጠቃሚ ነገር እንዳበረከቱ ያምናሉ፡፡ ስድስት ሚሊዮን አይሁዶችን የፈጀው ሒትለር በርሱ ክፉና የታመመ ጭንቅላት እሳቤ የሰው ልጆች ወረርሽኝ የሆኑትን አይሁዳውያን በማስወገዱ አንድ ቀን እንዸሚያደንቁት ያምን ነበር፡፡
ተባባሪነትና አምስተኛ ረድፈኝነት
ጥቃት የሚፈፀምበት ቡድኑ ስለምን ጉዳዩን ለዓለም አቀፍ ተቋሞችና ለመላው ዓለም ማቅረብ ተሳነው? የዚህ አንዱ ዋነኛ ምክንያት ይህን ማድረግ የሚችሉት ወገኖች ቸለልተኝነትና የብዙዎች ልሂቃን ትብብር፣ እንዲሁም የአብዛኛዎቹ በአገር ቤትም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ልሂቃን የዘር ማጥፋትና በሰዎች ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን ለማስቆም በሚዸረገው ትግል የአምስተኛ ረድፈኝነት ሚናን መጫወታቸው ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ይበልጥ በአሜሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን የሕክምና ዶክተሮች፣ በሌላ የትምህርት መስክ የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው፣ ፕሮፌሰሮች እና ምሁራን አሉ፡፡ እኒህ ዜጐች ሊሰሩ ይችሉት የነበረው ትንሹ ነገር ለሰለባዎቹ መከራከርና በነፃዎቹ አሜሪካና አውሮፓ ሊደረግ የሚችለውን ሁሉ ማድረግ ነበር፡፡ ከነዚህ አብዛኞቹ በኢትዮጵያ ነፃ ትምህርት ያገኙና በአሜሪካም እንዲሁ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በመሆናቸው የተማሩ ወንዶችና ሴቶች ናቸው፡፡ ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ ለቤተሰብ ገንዘብ ከመላክ ውጪ በኢትዮጵያ የሚፈፀመውን አሰቃቂ ወንጀል በዝምታ የሚታዘቡ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈፀሙትን ወንጀሎች በስማቸው ለመጥራትና የዚህ መንግሥት ፖሊሲዎችን ለማውገዝ ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ አሜሪካውያን፣ አውሮፓውያንና መላው ዓለም ለዘር ማጥፋት ወንጀልና በሰው ልጆች ላይ ለሚፈፀሙ ወንጀሎች ሰለባዎች ያሏቸውን በጐ ስሜቶች በማሰባሰብ ንቅናቄ መፍጠር አልቻሉም፡፡ ብዙዎቹ አጥር ላይ ተንጠልጥለዋል፣ ወይም ከአጥሩ ወዲያ ማዶ የመንግሥት ካምፖች ውስጥ መሽገዋል — የያዙትን (ያላቸውን) ወይም በኢትዮጵያ ሊኖራቸው የሚፈልጉትን ላለማጣት በኢትዮጵያ ስላለው እውነታ ከመናገርና ከመፃፍ ይልቅ መሬት ላይ ስለሌለ ጉዳይ ምሁራዊ ውይይት ማድረግን ይመርጣሉ፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለራስ ጥቅም ሲሉ ወይም ስለ ንግግር ነፃነት ባለን የተሳሳተ ፅንሰ ሃሳብ የተነሳ የዚህኑ ያክል ጠቃሚ የሆነውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ፖለቲካዊና ሞራላዊ ገፅታዎች መካድ የወንጀሉ አባሪ ተባባሪ መሆን ነው፡፡
የዩጐዝላቪያና የሩዋንዳ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤቶች መተባበርን የፍርድ ቤቱ ሥልጣን በሚያዝበት ስፍራ ለተፈፀመ ወንጀል ሁሉንም አይነት እርዳታ ወይም ከፍተኛ መገፋፋት/ማዸፋፈር ያዸረገ፣ወይም ተፅእኖ ያሳደረ በማለት ይገልፀዋል፡፡ ይህን በተመለከተ የዩጐዝላቪያ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ የሚከተለውን ብሏል፡፡
“ምንም እንኳን አንዳንድ የቡድን አባሎች ብቻ በአካል የወንጀሉን ድርጊት ቢፈፅሙም … አብዛኛውን ጊዜ የወንጀሉን ድርጊት በማመቻቸት ረገድ የሌሎች የቡድኑ አባሎች አስተዋፅኦ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም የዚህ አይነቱ ተሳትፎ ሞራላዊ ክብደት አብዛኛውን ጊዜ የተጠቀሰውን ድርጊት ከፈፀሙት አያንስም ወይም አይለይም፡፡”
ፕሮፌሰር ሻባስ እንደሚለው፤ “መተባበር አንዳንድ ጊዜ በሁለተኛ ደረጃ ተሳታፊነት ይገለፃል፡፡ ሆኖም ወደ ዘር ማጥፋት ወንጀል ስንመጣ “ሁለተኛ ደረጃ” የሚባል ነገር የለም፡፡”
“ተባባሪው” ብዙውን ጊዜ እኩይና “ዋናው ጥፋተኛ” ነው፤ በማሺኑ ውስጥ ያለ ትንሽ ብሎን፡፡ ሒትለር በቀጥታ ሰው አልገደለም ወይም አላሰቃየም፤ ከህግ አኳያ ካየነው የተፈፀመው ዘር የማጥፋት ወንጀል ተባባሪ “ብቻ” ነበር፡፡
…የዘር ማጥፋት ወንጀሉ ድንጋጌ አርቃቂዎች “የዘር ማጥፋት ወንጀልን የሚያደራጁ፣ የሚመሩ ወይም የሚያበረታቱ፤ ሆኖም ግን በአካል አውቶማቲክ ጠመንጃን ወይም ቆንጨራን ፈፅሞ ያላነገቡ ወይም ያልተጠቀሙትን ለመያዝ በተባባሪነት የተሳተፉ ጥፋተኞች እንዲከሰሱ የሚያስገድድ አንቀፅ አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝበው ነበር፡፡” በሌሎች ሁኔታዎች ግን የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባባሪና ረዳት፣ ምናልባትም እኩዩ ተዋናይና የዘር ማጥፋት ወንጀሉን የተለየ ዓላማ የማያውቅ ሊሆን ይችላል፡፡ ይልቁንም የዘር ማጥፋት ወንጀሉ የድርጊቶቹ ውጤት ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህም ማለት የዘር ማጥፋት ወንጀል ድንጋጌውና የጊዜያዊ ፍርድ ቤቶቹ ደንቦች መተባበርን በተመለከተ ያካተቷቸው አንቀፆች ሁለት በጣም የተለያዩ የወንጀል ምድቦችን ለይተው ያስቀምጡ ይመስላል — የዘር ማጥፋት ወንጀልን ቢያቅዱም ያልገደሉ፤ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል እቅድ የሌላቸው ነገር ግን የድርጊቶቻቸው ውጤት የዘር ማጥፋት ወንጀል መሆኑን የሚያውቁ በማለት፡፡
በዚህ መሰረት የአማራን ዘር የማጥፋት ወንጀል ውሎ አድሮ የዓለም አቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤት በሚደርስበት ጊዜ የዚህ ወንጀል ተባባሪዎች በዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፃሚነት ሊጠየቁ ይችላሉ፡፡ ይህም እንደዚህ አይነት ወንጀሎች መፈፀማቸውን ያውቁ የነበሩ፣ አንዳች ነገር ማድረግ ሲችሉ እንዳላየ አይተው ያሳለፉ ወይም የዘር ማጥፋቱ ወንጀል ንቁ ተሳታፊ የሆነውን መንግሥት የደገፉ ወይም በዝምታና በግዴለሽነት የወንጀሉን መፈፀም ያበረታቱ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሊያጠቃልል ይችላል፡፡ በጐሳቸው ምክንያትም ይሁን፣ ያላቸውን ወይም ሊኖራቸው የሚችለውን እንዳያጡ ከመነጨ ፍርሃት እያወቁ በስልጣን ላይ ያለው መንግሥትና አንዳንድ ባለስልጣኖች እንዳይከሰሱ ወይም በአንዳንዶቹ ወንጀሎች እንዳይቀጡ ሲከላከሉላቸው ቆይተዋል፡፡ ይህ መንግሥት የተወሰነ ድጋፍ ያለው መሆኑ በጣም ግልፅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ መንግሥትን ማጋለጥ ወይም ማውገዝ የሚያስፈራ መሆኑን በቀላሉ መረዳት የሚቻል ቢሆንም፣ ዳያስፖራ ያለው ተባባሪ ቁጥር ከፍተኛ መሆን ግን አይገባኝም፡፡ ውሎ አድሮ ከፍትሕ አያመልጡም፣ ይደርስባቸዋል፡፡ ምክንያቱም እንዲህ አይነቶቹ ያፈጠጡ ወንጀሎች በሚካሄዱበት ማንም ገለልተኛ ወይም የመንግሥት ደጋፊ ሊሆን አይችልም፡፡
አንዳንድ እውነቱን መቀበል የማይፈልጉ ሰዎች ወንጀሎቹን በስማቸው “የዘር ማጥፋት ወንጀል” ብሎ ላለመጥራት ቁጥርን በምክንያትነት ያቀርባሉ፡፡ ዳሩ ግን በዘር ማጥፋት ወንጀል ድንጋጌው ውስጥ የተሰጠ የተወሰነ ቁጥር የለም፡፡ ቁጥር ሳያነሳ ቡድኖች በማለት ይገልፀዋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ወንጀል የመከላከል ኰሚሽን ዳይሬክተር “የዘር ማጥፋት ወንጀል ስንል ምን ያክል ማለታቸውን ነው?” ለሚለው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥታለች፡፡
“ቁም ነገሩ ቁጥሩ ላይ አይደለም፡፡ ስለቁጥር ማውራት ከጀመርን ነገሮች እየተወሳሰቡ ይመጣሉ፡፡ ለምሳሌ፣ በቦስንያ ሄርዞጐቪና ከ8‚000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ በሩዋንዳ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ አንድ ሚሊዮን ሰዎች ተገድለዋል፤ (በአይሁዳውያን) ላይ በተፈፀመው እልቂት 6‚000 ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ኪጋሊ (ሩዋንዳ) የዘር ማጥፋት ወንጀል ሰለባዎች መዘክር ብትሄድ በሩ ላይ የተሰቀለ ፅሁፍ ታያለህ — “ብዙውን ጊዜ ሰዎች ስለዘር ማጥፋት ወንጀል ሲያስቡ አዕምሯቸው ውስጥ የሚመጣው ቁጥር ነው” የሚል፡፡ ሰዎች አንድ ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል የሚለውን ለመስማት ይጠብቃሉ፡፡ ሆኖም ማገናዘብ የማይችሉት ስድስት ሰዎች እዚህ ይሞታሉ፤ ሦስት እዚያ፤ ነገ ደግሞ 20፣ ከነገ ወዲያ እንዲሁ ተጨማሪ አምስት እያለ ይቀጥላል፡፡ እነዚህ ቁጥሮች ሁሉ ተደምረው አንድ ቀን የምትጠብቀው አንድ ሚሊዮን ላይ ይደርሳሉ፡፡ ስለዚህ ወደ ዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያመሩ ሁኔታዎች እስካሉ ድረስ በጣም ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ እነዚያ መጀመሪያ ላይ ሦስት ወይም 12 የነበሩ ሞቶች የዘር ማጥፋት ወንጀል መጀመሪያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡”
በሌላ አባባል ባለፉት 30 ዓመታት በግዳጅ የተፈፀመ የወሊድ ቁጥጥርን፣ መፈናቀልንና ከመላ አገሪቱ በቡድኑ ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ብንቆጥር ወደ ሚሊዮኖች ይገባል፡፡ ጥያቄው ይህችን በጦርነትና ግጭቶች የታመሰች አገር (ኢትዮጵያ) ወደ ፍፁም ሥርዓተ አልበኛ ሥርዓት እንዳትገባ እንዴት ማዳን ይቻላል የሚል ነው፡፡ አገሪቱን መልሶ የመገንባት ሥራ ገና አልተጀመረም፡፡ ስጋቱ ጭርሱኑ ላይጀመርም ይችላል የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ጥያቄው ፍርድ ወይም እውቅና እንኳን ስላልተሰጣቸው የዘር ማጥፋትና የጦር ወንጀሎች ምን መደረግ አለበት? ይሆናል፡፡ አስተዋይ ሰዎች እንደተናሩት፣ “የፍትህ ጐማ የሚንቀሳቀሰው በግዝታ ነው፡፡ ሆኖም የሚፈጨው ድቅቅ አድርጐ ነው፡፡” ምንም እንኳን ፍትሕ በፍጥነት ላይገኝ ቢችልም ፍትሕ ርትእ በሚወርድ ጊዜ በዳዮቹ የሚገባቸውን ቅጣት በፍጥነት ያገኛሉ፡፡ ለዚህ ነው ማስረጃ መሰብሰብና በዳዮቹን መለየት የአንቂዎችና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የማይቋረጡ ስራዎች መሆን ያለባቸው፡፡ ምክንያቱም የፍርድ ቀን ሲመጣ የዓለም አቀፍ ወንጀል ሕግ የሚጠይቃቸው ማስረጃዎች በሙሉ በእጃችን እንዲኖሩ ያስችሉናል፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀልን የመፈፀም ስልጣንና አቅም ያላቸው ሰዎች ተፅእኖዎች በጣም ሃይለኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ችግሩም በመካድና ማስረጃዎችን በማጥፋትና ነፃ ጋዜጠኞችን በማሰር ይጀመራል — ልክ ባለፈው ወር ከ6‚000 በላይ የሚሆኑ ጋዜጠኞችና የለውጥ ተሟጋቾች ተሰብስበው እስር ቤት እንደታጐሩት ወይም ወዳልታወቁ ቦታዎች እንደተወሰዱት፡፡ ኢትዮጵያውያን በነኚህ ለፍርድ የሚቀርቡ ሰዎች ላይ ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው በፊት ሊሰሯቸው የሚገቡ በዳዮችን ተጠያቂ የሚያደርጉ በጣም አስፈላጊ ስራዎች አሉ፡፡ እነኚህን በማከናወን ረገድ ሊተጉ ይገባል፡፡ ይህ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶችና በአገር ውስጥም ሆነ ውጭ የሚኖሩ መርማሪዎች ተግዳሮት መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የሚናፍቁት የፍርድ ቀን ሲመጣ ወንጀለኞቹ ብቻ አይደለም ወህኒ የሚበሰብሱት፣ ሽምጥጥ አድርገው የሚክዱትና የዘር ማጥፋት ወንጀልን ማቆም ሲችሉ ተገቢውን ጥረት ባለማድረጋቸው የተከሰሱ ተባባሪዎቻቸውም ጭምር እንጂ፡፡ ክሱም ከክፋት ጋር በመተባበር የሚል ነው የሚሆነው፡፡ በዚህም በታሪክ መዝገብ ውስጥ ለዘላለም በወራዳ ተግባራቸው ተመዝግበው ይኖራሉ፡፡
ኤሊ ዊስል የዘር ማጥፋት ወንጀል ክህደትን “እጥፍ ግድያ” በማለት ይገልፀዋል፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀልን መካድ የጭካኔ የመጨረሻ ጥግና ለሰለባዎቹ ያለ ጥላቻ መገለጫ ነው፡፡ ሕይወታቸውን ያጡትና ከሞት የተረፉት እንዲሁም ማንነታቸውን በሙሉ ትዝታቸውን ጭምር ሳይቀር ለማጥፋት በማሰብ የታሪክ ቁሻሻ ማስወገጃ ውስጥ ተጥለዋልና፡፡ እነኚያ እንደ እንስሳ የታረዱት፣ በሕይወታቸው ሳሉ የተቃጠሉት፣ አንዳንዴ በልጆቻቸውና ባለቤቶቻቸው ፊት የተደፈሩት፣ የተዋረዱትና ወላጆቻቸው ከኖሩበትና እነርሱም በሕይወታቸው ከዚያ ሌላ ከማያውቁት መንደር የተፈናቀሉት አማሮችን ዓለሙ ለፖለቲካ ሲል አይቶ እንዳላየ ቢያልፋቸውም ሁሉን ተቋቁመው ላለመጥፋት ቆርጠዋል፡፡ ነገር ግን በዚህ በዲጂታል ዘመን አንድ ቀን እውነቱ ወጥቶና በዓለም አቀፍ ሕግና የሰው ልጅ ሕሊና ውስጥ በገባ ጊዜ “ፈፅሞ እንዳይደገም” የሚለው ቃል ኪዳን እንደገና ለተግዳሮት ይዳረጋል፡፡
አሜሪካና የሰብዓዊ መብት ፖለቲካ
ራሷን በሰብዓዊ መብት ረገድ ከዓለም ግንባር ቀደም አገር በማድረግ የምትኩራራው አሜሪካ ከርሷ የሚጠበቀውን ማሟላት አልቻለችም፡፡ ምንም እንኳን አገሪቱ በባርነትና በቀደሙ ነዋሪዎች ላይ ባደረሰችው አያያዝ የምትመሰገን ባትሆንም ሁሉም ሰው በሰብዓዊ መብት ረገድ መሪነቷን ለመቀበል ዝግጁ ነበር፡፡ ሆኖም በተደጋጋሚ፣ ደግማና ደጋግማ በትራምፕ አስተዳደር ዘመን አመኔታዋን እጅግ በጣም በከፋ መልኩ በማጣቷ የነበረቻትን ጥቂት የሞራል አመኔታ አጥታለች፡፡ አሜሪካ የዘር ማጥፋት ወንጀልና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፋለም ረገድ ራሷን መሪ አድርጋ ብትቆጥርም የዘር ማጥፋት ወንጀል መከላከልና ቅጣት ድንጋጌን የፈረመችው ድንጋጌው በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ በአንድ ድምፅ ከፀደቀ ከአርባ ዓመታት በኋላ ነበር፡፡ ሳማንታ ፓወር እንደፃፈችው፤
“የሃያኛው ክፍለ ዘመን የመጨረሻ አሠርት ዓመት በታሪክ እጅግ በጣም የበረከተ ሞት የተመዘገበበት ነበር፡፡ የሩዋንዳ ሁቱዎች በ1994 (እ.ኤ.አ) የውጭ ኃይል ጣልቃ ስላልገባ በቀን ወደ ስምንት ሺ የሚሆኑ ቱትሲዎችን ለአንድ መቶ ቀናት እንደልባቸው መጨፍጨፍ ችለው ነበር፡፡ የዘር ማጥፋት ወንጀል ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላም ተፈፅሟል፤ የሰብዓዊ መብት ቡድኖች ከተበራከቱ በኋላም ተፈፅሟል፤ እንዲሁም ፈጣን ግንኙነት ማድረግ ከተቻለበት የቴክኖሎጂ ዘመን በኋላና በዋሺንግተን ዲሲ ከሆሎኰስት ሙዚየም መገንባት በኋላ ተፈፅሟል፡፡ የአሜሪካ መሪዎች አንድም አይተው እንዳላዩ በመሆን፣ ወይም በተለመዱት ስትራቴጂያዊ ስጋቶች የተነሳ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ የተካሄደውን በአይሁዳውያን ላይ የተፈፀመ እልቂት እንዳልተቃወሙ ሁሉ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲካሄድ ፈቅደዋል፡፡
አሜሪካ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ አርመናውያን በቱርክ በተገደሉ ጊዜ ያደረገችው አፀፋዊ መልስ፤ ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በፖል ፖት የሽብር ዘመን ባለቁ ጊዜ፣ በኢራቅ ከአንድ መቶ ሺ በላይ ኩርዶች በተጨፈጨፉ ጊዜ፣ የቦስኒያ ሰርቦች ወደ ሁለት መቶ ሺህ ሙስሊሞችንና ክሮአቶችን በገደሉ ጊዜና ሁቱዎች ቱትሲዎችን ከምድረ ገፅ ለማጥፋት በሞከሩ ጊዜ አሜሪካ ጦር ሠራዊቷን በማሰማራት የጭካኔ ተግባራቱን ለማስቆም ፈቃደኛ ያለመሆኗ አይደለም ችግሩ፡፡ በምዕተ አመቱ ጣልቃ ገብነትን እጅግ በጣም የሚያራምዱ አገሮች እንኳን አሜሪካ የምድር ኃይሏን እንድታስገባ ለማግባባት ሞክረው አያውቁም፡፡ እጅግ በጣም አስደንጋጩ ነገር የዋሺንግተን ፖሊሲ አውጪዎች ወንጀሎቹን ለመከላከል አንዳችም ነገር ያለማድረጋቸው ነው፡፡ የአሜሪካ “ወሳኝ ብሔራዊ ጥቅሞች” በተራ የዘር ማጥፋት ወንጀል ለአደጋ መጋለጥ እንደሌለባቸው ይታመን ስለነበር አሜሪካ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለማስቀረት ሊጐዳት የሚችል እርምጃን ለመውሰድ ፈቃደኛ ሳትሆን ቆይታለች፡፡
ዛሬም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ተጉዞ እንደተለመደው ንጉሡን እጅ ነስቶ የአሜሪካን ድጋፍ ዘላቂነት ለመግለፅ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡ ፕሬዝዳንት ባይደን ሳዑዲ አረቢያን የሚጐበኘው ሳዑዲ አረቢያ የሰብዓዊ መብትን በመጣስ ቀዳሚ አገር መሆኗ በሚታወቅበት ጊዜ ነው፡፡ እ.ኤ.አ የካቲት 2021 ከአሜሪካ መረጃ ክፍል በወጣው ሪፖርት መሐመድ ቢን ሳልማን የዋሺንግተን ፖስት ጋዜጠኛ የነበረው የጀማል ካሾጂ ግድያ እንዲፈፀም ፈቅዷል፡፡ ይህም እየታወቀ ግን የአሜሪካ መንግሥት ሳዑዲ አረቢያን ለወንጀሉ ተጠያቂ ለማድረግ አንዳችም እርምጃ አልወሰደም፡፡ ባይደን ለፕሬዝዳንትነት ይወዳደር በነበረበት ጊዜ የርሱ አስተዳደር ሳዑዲ አረቢያን ከዓለማችን የተገለለች አገር እንደሚያደርጋትና “ለፈፀሙት ወንጀል ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው” ሲገልፅ ነበር፡፡ የባይደን ዘመቻ አስተያየቶች ባዶ ቃላት ናቸው፤ ምክንያቱም ሳዑዲ አረቢያን ለፈፀመቻቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች (የካሾጂን ግድያ ጨምሮ) ተጠያቂ የሚያደርጋት አንዳችም እርምጃ አልተወሰደም፡፡ የፕሬዝዳንቱ ጉብኝት ዓላማ ከርሱ በፊት እንደነበሩት መሪዎች ሁሉ የሁለቱ አገሮች ስትራቴጂያዊና ኤኰኖሚያዊ ትብብር ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ሌሎችም ጉዳዮች በላይ መሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ሳዑዲ አረቢያ ከተፈጠረችበት 70 ዓመት ጀምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከሁሉም በላይ ከሚጥሱት አገሮች አንዷ ሆና የቆየች ስትሆን፣ በዓለማችን ሁሉም የጂሃዲስት እንቅስቃሴዎች ማለት በሚቻል መልኩ (በዋሃቢ ርዕዮተ ዓለም አማካይነት) መፈልፈያ ነች፡፡
አሥራ ሦስት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች (ሂዩማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ) ለፕሬዝዳንት ባይደን በጋራ በፃፉት ደብዳቤ ጉብኝቱ ተጨማሪ የመብት ጥሰቶችንና ተጠያቂ ያለመሆንን የሚያበረታታ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ዋናውና ከሁሉም የበለጠው ስሌት የራስ ጥቅም ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ግን ጉብኝቱ የሚያስተላልፈው መልእክት አይደለም፡፡ ሳዑዲ አረቢያ ነዳጅ እስካቀረበችና የኢራንን መስፋፋት መከላከል እስከቻለች ድረስ የፈለገችውን ለማድረግ ይበልጥ ትደፋፈራለች፡፡
የሰብዓዊ መብት ጉባኤ
የተባበሩት መንግሥታት የፖለቲካ ድርጅት እንደመሆኑ በዚያ የሚተላለፉት ውሳኔዎች በአገሮች ፍላጐትና ጥቅም ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ ለተመድ ብዙ ገንዘብ የሚያዋጡት፣ ወታደራዊና ኢኰኖሚያዊ የበላይነት ያላቸው አገሮች በውሳኔዎች ላይ በቀላሉ ተፅእኖ ማሳደር ወይም ውሳኔዎችን መግዛት ይችላሉ፡፡ የተመድ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ በብዙ ውጣ ውረድና ድርድር አንዳንድ መንግሥታትን በሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲወገዙ ማድረግ ችሏል፡፡፡ ነገር ግን እንደዚህ አይነቶቹ ውሳኔዎች እምብዛም ተፅእኖ ፈጥረው አያውቁም፡፡ የተወሰኑ እርምጃዎችን ለመውሰድ ውሳኔዎቹ ለፀጥታ ምክር ቤቱ መላክ አለባቸው፡፡ በዚያ አምስቱም ቋሚ አባሎች ካልተስማሙበት አብዛኛውን ጊዜ ወድቆ ይቀራል፡፡ የተመድ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ ፍትሕን ለማውረድ ወይም የዘር ማጥፋት ወንጀልንና በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን የማስቆም ስልጣን የሌለው የወረቀት ላይ ነብር ነው፡፡ እስራኤል ከ2013 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ ባለው ጊዜ በተመድ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ በ45 ውሳኔዎች ተወግዛለች፡፡ ይኸው ድርጅት ከተፈጠረበት 2006 (እ.ኤ.አ) ጀምሮ በዓለማችን ባጠቃላይ ካስተላለፋቸው ውግዘቶች በላይ በእስራኤል ላይ ብዙ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ ዳሩ ግን እሥራኤል (በአባል አገሮች ላይ ሕጋዊ ተፈፃሚነት ያላቸው፤ የተመድ ቻርተር አንቀፅ 25) 25 ውሳኔዎችን ጥሳለች፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፖለቲካ ድርጅት በመሆኑ ሳንታገልና ማድረግ የሚያስፈልገውን ሁሉ ሳናደርግ ፍትሕን ከርሱ መጠበቅ የለብንም፡፡ የተመድ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ ጥርስ የሌለው አንበሳና እንደ ወላጅ አባቱ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እጅጉን ፖለቲካ የተጠናወተው ነው፡፡ ተመድ አባል አገሮች የሚፈልጉትን ይወስናል፤ የተመድ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ ግን የሚወስነው አምስቱም ቋሚ የፀጥታ ምክር ቤት አባል አገሮች ሲፈቅዱ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያን በመሳሰሉት አገሮች ወንጀለኞችን ለፍትሕ ማቅረብ የሚችለው ዓለም አቀፍ ድርጅት ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ብቻ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤቱ የተመድ ወይም የሌላ ድርጅት ቅርንጫፍ አይደለም፡፡ ባሁኑ ሁኔታ ፍትሕ ሊጠየቅና በኢትዮጵያ የሚታየውን እብደት ለማስቆም የሚያስችለው ብቸኛ አማራጭ መንገድ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ይመስላል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ፍርድ ቤቱን ያቋቋመው የሮም ደንብ ፈራሚ ባለመሆኗ በዚያ በኩል ፍትሕን ለማግኘት መሞከር አዳጋች ነው፡፡ የአማሮች ጉዳይ ወደ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ሊደርስ የሚችለው ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግሥታት ፀጥታ ምክር ቤት ሊያቀርብ በሚችለው የተመድ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ በኩል ሲሆን፣ የተመድ ፀጥታ ምክር ቤት በዳርፉር ጉዳይ እንዳደረገው ሁሉ ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሊያስተላልፈው ይችላል፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን አምስቱም ቋሚ አባሎች ከተስማሙ ወይም ድምፅን በድምፅ የመሻር መብታቸውን ካልተጠቀሙ በመሆኑ ዓለምን ከኢትዮጵያ ጐን ለማሰለፍ ዳያስፖራው ብዙ ሥራ ይጠበቅበታል፡፡ የተከፋፈለች ኢትዮጵያን ማየት ለየትኞቹም ሃያላን አገሮች አይበጅም፡፡ በተፃራሪ የከሸፈች ኢትዮጵያ ለአካባቢው፣ ለአህጉሩና ለዓለምም ስጋት ነው የምትሆነው፡፡ የኢትዮጵያውያን፣ በተለይም የቡድኑ ተግዳሮቶች ኃያላኑ ኢትዮጵያን እንዲያግዙ በአንድነትና በጥበብ መስራት ነው፡፡ ይህ ሊፈፀም የሚችለውም ለሰላምና ለኢትዮጵያ መረጋጋት በሚቆሙ ሐቀኛ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተዋናዮች ብቻ ነው፡፡ እነዚህ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተዋናዮች በሚገባ ሊንቀሳቀሱ የሚችሉትም በነፃ ህብረተሰብ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ዳያስፖራው ሁለት አማራጮች አሉት — ወራዳ ታሪክ ማውረስ ወይም በአንድነት በመነሳትና የኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ተቃውሞን በመደገፍ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ላይ ትርጉም ያለው እርምጃ ከመውሰድ ውጪ አማራጭ እንደሌለ እንዲታወቅ የሚያደርጉ ተፅእኖዎችን መፍጠር፡፡
ፖለቲካ (realpolitik) በዓለም አቀፉ መድረክ አገሮች ጥቅማቸውን ለማስከበር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነው፡፡ በመሆኑም አገሮች ከነርሱ ውጪ የሆነን ሞራላዊና ሰብዓዊ መብት አብዛኛውን ጊዜ የሚያዩት ከራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም ወይም በሞራል ሽፋን ከብሔራዊ ጥቅማቸው አንፃር ነው፡፡ ለዚህም ዩክሬን አይነተኛ ምሳሌ ልትሆን ትችላለች፡፡ በሰብዓዊ ፍጡራን ላይ በሚደርስ ስቃይ መለኪያ ኢትዮጵያ ከዘር ማጥፋት ወንጀል እስከ ረሃብ የሚዘልቅ እጅግ በጣም አስከፊና ውስብስብ ሰብዓዊ ቀውስ ያለባት አገር ነች፡፡ አልጀዚራ፣ ዓለም ስለምንድነው ባለፉት ሳምንታት ለዩክሬን የሚያሳየውን መቆርቆር በከፊል እንኳን ለአፍሪካ ያላሳየው? በማለት ይጠይቃል፡፡ የዚህ አይነቱ ማዳላት መንስኤ አንድም ዘረኝነት አለያም ጂኦ-ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ ሃያላን የሚያደርጉት በዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ነው፡፡ R2P በመባል የሚታወቀው ሰብዓዊ ፍጡርን የመጠበቅ ሃላፊነት እ.ኤ.አ በ2005ቱ የዓለም ጉባኤ (World Summit) ላይ ከሩዋንዳው የዘር ማጥፋት ወንጀል በመማር የተቀመረ ዓለም አቀፍ ስምምነት ነው፡፡ ሰዎችን ከዘር ማጥፋት ወንጀል፣ የጦር ወንጀሎችና በሰው ልጆች ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎችና ዘርን የማፅዳት (የማጥፋት) ተግባር ለመጠበቅ የሚያገለግል ነው፡፡ ጠቃሚ የዓለም አቀፍ መርህ እውቅናንም አግኝቷል፡፡ R2P ሦስት የሃላፊነት አምዶች አሉት፡፡ ሦስተኛው አምድ የሚለው፤
“አንድ አገር ወይም መንግሥት ህዝቡን በግልፅ መጠበቅ ካልቻለ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አግባብነት ያለው የጋራ እርምጃን በወቅቱና ቁርጥ ባለ መልኩ በተመድ ቻርተር መሠረት ለመውሰድ ዝግጁ መሆን አለበት፡፡”
ዓለምና አፍሪካ የኢትዮጵያን ችግር በዓለም አቀፍ ደረጃ መመለስ እንዳለባቸው ማወቅና ይህንም ዓለም አቀፍ ስትራቴጂያዊ፣ ሰብዓዊና ሞራላዊ አስጨናቂ ምርጫ አድርገው ሊቆጥሩት ይገባል፡፡ ዓለም እየፈረሰች ያለችውን ኢትዮጵያ ከራሷ ጥፋት ሊጠብቃት ይገባል፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያውያን ለመሠማት ይበልጥ ጠንክረው መስራትና አንድ መሆን አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ የምለው ለአማሮች የሚሰጥ ፍትህ ለኢትዮጵያም በመሆኑ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕልውና የሚረጋገጠው ለአማሮች ፍትህ ሲሰጣቸው ብቻ ነው፡፡
በአሜሪካ ጅምላ ግድያ መካሄዱን ተከትሎ ባይደን ሲናገር፣ “ምን ያክል እልቂት ለማስተናገድ ፈቃደኞች ነን?” ብሏል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ይህን ይጠይቃሉ፤ “ተመድ ምን ያክል እልቂት ለማስተናገድ ፈቃደኝ ነው?”
ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ፤ የአፍሪካ ስትራቴጂና ደህንነት ጥናት ኢንስቲትዩት ኤክሴክዩቲቭ ዳይሬክተር