መንደርደርያ
ደመቀ መኮንን፣ ተመስገን ጡሩነህና አበባው ታደሰ ሆዳም አማሮች የሚባሉት ለምንድን ነው? አማራ ማለት በመላ ዓለም ተሰራጭቶ የሚኖር ራሱን አማራ ነኝ የሚል ማለት ነው፡፡ ሆዳም አማራ ማለት ደግሞ አማራ ሁኖ ካማራነቱ ይልቅ ሆዱን የሚያስቀድም ማለት ነው፡፡ ደመቀ መኮንን፣ ተመስገን ጡሩነህና አበባው ታደሰ አማራ ናቸው የሚባሉበት ምክኒያት ምንድን ነው? ስማቸው ቆንጆ ያማራ ስም ስለሆነ? በአማራዊ ስም የሚጠሩ፣ አማራ ያልሆኑ፣ የአማራ ለምድ የለበሱ ፀራማራ ተኩላወች ቢሆኑስ? ትክክለኛ ማንነታቸውን ከስማቸው በላይ ተግባራቸው በትክክል አይመሰክርም ወይ? አማራን ፍጹም የሚጠላ የለየለት ፀራማራ ካልሆነ በስተቀር፣ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህል አማራዊነት የሚሰማው ሰው የአማራ ሕጻናትን እያረደና እያሳረደ ደማቸውን ለሚጠጣና በደማቸው ለሚታጠብ ጭራቅ ፍጹም ሎሌ መሆን እንዴት ያስችለዋል? አማራን ለማጥፋት ምሎ ተገዝቶ፣ ቆርጦ የተነሳው ጭራቅ አሕመድ እነዚህን ሁለት ግለሰቦች በአማራ ሕዝብ ስም ከቀደሞ ጌታቸው ከፀራማራው ከወያኔ ጋር እንዲራደሩ ለምን መረጣቸው? ውነት ካንደበቱ ሊወጣ የማይችለው፣ ውሸታሙ ጭራቅ አሕመድ ስለ ተደራዳሪወቹ ሲናገር ደመቀ አማራ ነው ለማለት ምን አስፈለገው? የአማራ ዋና ጠላቱ ሆዳም አማራ ነው ወይስ በአማራ ስም የሚጠራ፣ አማራ ያልሆነ፣ የአማራ ለምድ የለበሰ ፀራማራ ተኩላ?
ሆዳም አማሮች ወይስ የአማራ ለምድ የለበሱ ፀራማራ ተኩላወች?
የአማራ ጠላቱ ሆዳም አማራ ነው የሚል፣ በየሙያቸው አንቱ የሚባሉትን ጨምሮ አያሌ ሰወች የሚጠቀሙበት አባባል አለ፡፡ ይህ አባባል ግን ባብዛኛው ትክክል ያልሆነ፣ የአማራን ሕዝብ ቅስም ለመስበር ወያኔወች ባይፈጥሩትም በስፋት እንዲለመድ ያደረጉት አባባል ነው፡፡ ሆዳም አማራ ማለት ለሆዱ ያደረ አማራ፣ ከአማራነቱ በፊት ሆዱን የሚያስቀድም አማራ፣ ለሆዱ ሲል የፀራማሮች ሎሌ ለመሆን የማያቅማማ አማራ ማለት ነው፡፡ በዚህ ብያኔ መሠረት ሆዳም አማራ እንዳለ ሁሉ፣ ሆዳም ትግሬ አለ፣ ሆዳም ኦሮሞ አለ፡፡ ሆዳምነት በሁሉም ብሔሮች ውስጥ እንጅ በአማራ ውስጥ ብቻ ተለይቶ የሚገኝ እኩይ ባሕሪ አይደለም፡፡
ይህ ከሆነ ታዲያ፣ ሆዳምነት በአማራ ሕዝብ ውስጥ በስፋት የሚታይ የሚመስለው ለምንድን ነው? ለዚህ መሠረታዊ ጥያቄ አጭሩ መልስ፣ ባማረኛ ስም የሚጠሩ አማራ ያልሆኑ፣ የአማራ ለምድ የለበሱ፣ ፀራማራ ተኩላወችን እንደ ሆዳም አማራ ስለምንመለከታቸው ነው የሚለው ነው፡፡
ለምሳሌ ያህል አባዱላ ገመዳን እንውሰድ፡፡ አባዱላ ገመዳ በወያኔ ዘመን የወያኔ ሎሌ ሁኖ ኦሮሞን ይጨፈጭፍና ያስጨፈጭፍ የነበረ ሆዳም ኦሮሞ ነበር፡፡ አባዱላ ገመዳ ግን ኦሮሞ ነኝ ብሎ ስለሚያምን ሆዳም ኦሮሞ የሆነው ሆዱ ስለሚበልጥበት እንጅ ኦሮሞን ስለሚጠላ አልነበረም፡፡ ላለመሆኑ ማስረጃው ደግሞ ሆዱንም ኦሮሞንም የሚጠቅምበት ዕድል ሲፈጠርለት፣ እድሉን ወዲያውኑ ተጠቅሞ፣ ወያኔን በግላጭ ከድቶ በግላጭ ኦነጋዊ መሆኑ ነው፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የብአዴኑን አዲሱ ለገሰን እንውሰድ፡፡ አዲሱ ለገሰ አማራን ለሃያ ሰባት ዓመታት የጨፈጨፈና ያስጨፈጨፈ፣ የአማራ ሕዝብ ቁጥር በሦስት ሚሊዮን ቀንሷል በማለት ሥራየን በሚገባ ሠርቻለሁ በሚል ስሜት ፓርላማ ላይ ተኩራርቶ የተናገረ፣ ወያኔን በፍጹም ታማኝነት ያገለገለ፣ የወያኔ ፍጹም ሎሌ ነበር፡፡ የወያኔ ሎሌ የነበረው ግን ለሆዱ ብቻ ሳይሆን የወያኔን ፀራማራነት የሚደግፍ ምናልባትም ከራሱ ከወያኔ በላይ ፀራማራ ስለሆነ ነበር፡፡ ለከርሱ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ወያኔ ለሁለት አንጃወች ተከፍሎ የነ ሰየ አብርሃ አንጃ ጠቅላይ ሚኒስትር እናርግህ ሲለው፣ እድሉን ተጠቅሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ሁሉን በጁ በደጁ አድርጎ ከርሱን እንዳሻው ይሞላ ነበር፡፡ እሱ ግን ከሆዱ ይልቅ ፀራማራነቱ በለጠበት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሁኖ የፀራማራውን የወያኔን ክፍፍል ይበልጥ በማባባስ፣ ወያኔ ይበልጥ እንዲዳከም ብሎም እንዲከስም ከማድረግ ይልቅ ተቃራኒውን መረጠ፡፡ ወያኔ በመለስ ዜናዊ አምባገነናዊ መሪነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲወጣ ወሳኝ ሚና በመጫወት፣ የመለስ ዜናዊ ፍጹም ሎሌ ሁኖ አማራን መጨፍጨፉንና ማስጨፍጨፉን ቀጠለ፡፡
ቀጥለን ደግሞ ደመቀ መኮንንን እንመልከት፡፡ ይህ ግለሰብ ልክ እንደ አዲሱ ለገሰ አማራን ላያሌ ዓመታት የጨፈጨፈና ያስጨፈጨፈ የወያኔ ፍጹም ሎሌ ነበር፡፡ የወያኔ ፍጹም ሎሌ የሆነው ደግሞ ልክ እንደ አዲሱ ለገሰ ለሆዱ ሲል ብቻ ሳይሆን የወያኔን ፀራማራነት የሚደግፍ፣ ምናልባትም ከራሱ ከወያኔ በላይ ፀራማራ ስለሆነ ነበር፡፡ ለሆዱ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ወያኔ ሲወድቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆን ሲችል፣ ከወያኔ የበለጠ ፀራማራ መሆኑን ለሚያውቀው ለቅርብ ጓደኛው ለጭራቅ አሕመድ ቦታውን በሙሉ ፈቃደኝነት አይለቅም ነበር፡፡
ደመቀ መኮንን ሆዳም ቢሆንም ከሆዳምነቱ በላይ ግን ፀራማራነቱ ይበልጥበታል፡፡ ወያኔንም ሆነ ኦነግን በፍጹም ታማኝነት ለማገልገል ፍጹም ደስተኛ ነው፡፡ ፀራማራነቱን ይበልጥ የሚያረካው ግን ሁለቱ ፀራማራወች ወያኔና ኦነግ ባንድነት ተጋግዘው አማራን ከምድረገጽ ቢያጠፉለት ነው፡፡ ለዚህ ነው፣ በመጀመርያ የወያኔ ፍጹም ሎሌ፣ ቀጥሎ የኦነግ ፍጹም ሎሌ፣ አሁን ላይ ደግሞ የሁለቱም ፍጹም ሎሌ ለመሆን ወያኔንና አነግን ለማደራደር ሽር ጉድ የሚለው፡፡
ተመስገን ጡሩነህም፣ ሆዳም ቢሆንም ከሆዳምነቱ በላይ ፀራማራነቱ የሚበልጥበት፣ በአማራዊ ስም የሚጠራ፣ የአማራ ለምድ የለበሰ፣ ፀራማራ ተኩላ ነው፡፡ ከርሳም ቢሆንም፣ ለአማራ ሕዝብ ጥቅም ቁሞ፣ ከርሱን ይበልጥ ከሚሞላ ይልቅ፣ የኦነግ ሎሌ ሁኖ አማራን እያስጨፈጨፈ የኦነግን ፍርፋሪ ቢለቃቅም ይመርጣል፡፡ ሽመልስ አብዲሳ ያስጨፈጨፋቸው አማሮች ደም ሳይደርቅ ሽመልስ አብዲሳን ባሕር ዳር ድረስ ጠርቶ ካባ ለመሸለም የተሸቀዳደመው፣ የሽመልስ ዘግናኝ ጭፍጨፋ የልቡን ስላደረሰለት ነበር፡፡ ይህ እኩይ ፀራማራ ግለሰብ በላዔ አማራ የሆነው የጭራቅ አሕመድ ባልደረባ ብቻ ሳይሆን ጃንደረባ ነው፡፡ በትክክል ለመናገር ደግሞ ይህ እኩይ ፀራማራ ግለሰብ የጭራቅ አሕመድ (ለቃላት ምርጫየ ይቅርታ ይደረግልኝና) የጭን ገረድ ነው፡፡ ይህ እኩይ ፀራማራ ግለሰብ በሰኔ 16ቱ የባሕርዳር ጭፍጨፋ ወቅት የጭራቅ አሕመድ የደህንነት ኃላፊ ስለነበር፣ በጭፍጨፋው ላይ በቀጥታም ሆነ በተዛዋሪ ወሳኝ ሚና እንደተጫወተ ግልጽ ነው፡፡ በዲባቶ አምባቸው ቦታ ወዲያውኑ የተተካውም አማራን መሪ አልባ በማድረግ ፀራማራነቱን በሚገባ አስመስክሮ ጭራቅ አሕመድን ስላስደሰተው እንደሆነ፣ ክልሉን መምራት እንደጀመረ ፋኖን እያሳደደ መግደል መጀመሩ በግላጭ ይመሰክርበታል፡፡
ስለዚህም የአማራ ዋና ጠላቱ የአማራ ለምድ የለበሰ ፀራማራ ተኩላ እንጅ ሆዳም አማራ አይደለም፡፡ አዲሱ ለገሰ፣ ደመቀ መኮንን፣ ተመስገን ጡሩነህ፣ ይልቃል ከፋለ፣ ሰማ ጡሩነህ፣ አበባው ታደሰ፣ ብናልፍ አንዷለም፣ ግርማ የሽጥላ፣ ቆንጆ ያማራ ስም ስላላቸው ብቻ ሆዳም አማሮች ናቸው ከማለታችን በፊት አማሮች መሆናቸውን ማጣራት አለብን፡፡ እነዚህ የአማራን ለምድ የለበሱ ፀራማራ ተኩላወች፣ ለምዳቸው ይበልጥና ይበልጥ እየተገፈፈ ማንነታቸው ይበልጥና ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጣ እንጅ፣ አማራን ከዱ ሊባሉ አይችልም፣ መቸም ቢሆን ካማራ ጋር ወግነው አያውቁምና፡፡
መስፍን አረጋ