June 29, 2022
3 mins read

‘‘እናቴ ሀገሬ በጠና ታመሻል፤ እግዚአብሔር ይማርሽ!!’’

Cry Ethiopia 1እያመመው መጣ… …!!

ከሰሞኑን ከያኒ ቴዎድሮስ ካሣሁን/ቴዲ አፍሮ ‘‘ናዕት – እያመመው መጣ!’’ በሚል ለሕዝብ ያደረሰውን ዜማ ሳዳምጥ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊቃውንት ዘንድ ‘‘ደረቅ ሐዲስን ተናጋሪ’’ ተብሎ የሚጠራውና ከዐበይት ነቢያት ዘንድ የሚመደበው፣ የነቢዩ ኢሳይያስ የመጽሐፍ ቃል ወደ አእምሮዬ መጣ፡፡ እንዲህ ይነበባል፤

‘‘…  ራስ ሁሉ ለሕመም ልብም ሁሉ ለድካም ሆኗል፤ ከእግር ጫማ አንስቶ እስከ ራስ ድረስ ጤና የለውም፤ ቍስልና እበጥ የሚመግልም ነው፤  አልፈረጠም፥ አልተጠገነም፥  በዘይትም አልለዘበም፡፡  … ራስ ሁሉ ለሕመም ልብም ሁሉ ለድካም ሆኗል፡፡  ደግሞስ ዓመፃን እየጨመራችሁ ለምን ገና ትቀሰፋላችሁ?!…’’  (ኢሳ. ፩፤፭-፮)

በሕዝበ ክርስቲያን ዘንድ ‘‘የእናቴ ልጅ’’ በመባል የሚጠሩት ሰባኪ ወንጌል፣ ቀሲስ መንግሥቱ- ስለ እናት ሀገር ኢትዮጵያ አብዛኛውን ጊዜ ከአፋቸው የማትጠፋና ያለንበትን ከባድ ጊዜ በደንብ የምትገልጽ አንዲት ስንኝ አለቻቸው፡፡ ይህች የቀሲስ መንግሥቱ ስንኝ የወቅቱን የሀገራችንን የመከራ ዶፍ፣ የሕዝባችንን ሰቆቃ፣ ሞት፣ ስደትና መፈናቀል- በአጠቃላይ የኢትዮጵያችንን ብርቱ ሕመም፣ ጭንቅ የምትገልጽ ናትና፣ አካፍላችሁ ዘንድ ወደድኹ፤

እናት ሀገር ታማ፣ ተኝታ በአልጋ ላይ፣

አምላኬ አትግደለኝ፣ ሞት ሽረቷን ሳላይ፡፡

እንደ መውጫም፤ አንጋፋው ፖለቲከኛ ዶ/ር ኃይሉ አርዓያ፣ በተማሪነታቸው ዘመን (በ1959 ዓ.ም.) በቀድሞ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲተ ኮሌጅ/የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ‘‘የኮሌጆች ቀን’’ በዓል ካቀረቡት ግጥም ውስጥ- የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ የሚገልጽ ስንኝ ለስንብት ይኾነን ዘንድ ላጋራችኁ ወደድኹ፤ እነሆ ስንኟ፤

‘‘… ይኼው ትታያለች ለሕዝብ በይፋ፣

ጥቁር ተከናንባ ጥቁር ተጐናጽፋ፡፡

እኔስ መስሎኝ ነበር ዘመድ የሞተባት፣

የእናት ሞት የአባት ሞት፣

የልጅ ሞት ያጠቃት፣

ለካ እሷስ ኖራለች ዘመን የሞተባት፡፡’’

(ዶ/ር ኃይሉ አርዓያ/1959 ዓ.ም.)

‘‘እናቴ ሀገሬ በጠና ታመሻል፤ እግዚአብሔር ይማርሽ!!’’ (‘‘የእናቴ ልጅ’’የቀሲስ መንግሥቱ ምርቃትና ብሒል ናት)

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop