ሰኔ 19 ቀን 2014 ዓም(26-06-2022)
ቤትን ቤት የሚያሰኘው የሚንከባከበው ሰው ሲኖርበት ነው። እንግዳ ከቤቱ ደጃፍ ላይ ሲደርስ ድምጹን ከፍ አድርጎ እዚህ ቤቶች!ብሎ መጥራቱ ቤት ካለሰው ሰውም ካለቤት ተነጥለው ስለማይኖሩ በመተማመኑ ነው።ለቤት ጌጡና ክብሩ ሰው ሰው ሲሸት ነው።ሰው የሌለበት ወና ቤት በትንፋግና በቁንጫ ይወረራል።ለትንፋጉም ሆነ ለቁንጫው መኖር ነቅቶ ለመጠበቅና ንጽህናውን ለመቆጣጠር የሚችል ባለቤት አለመኖሩ ነው።አንድን ቤት ማራኪና የተከበረ የሚያደርገው የነዋሪው እንክብካቤ ሲጨመርበት ሲሆን የቤቱም ጽዳትና ማማር ለነዋሪው ኩራትና ክብሩ ነው።በመልካም ቁመና ፣ጠባቂና ባለቤት ያለውን ቤት ሌባም ሆነ ዘራፊ ሊደፍረው አይችልም።
በተመሳሳይ አንድ አገር ጠንካራ መንግሥትና ሕዝብ ካለው በውጭ ወራሪዎች ሊደፈር አይችልም።የውጭ ወራሪ የሚደፍረው በአገር ውስጥ ደካማ መንግሥትና አንድነት የሌለው ፣ በጎሳና በሃይማኖት ልዩነት አንዱ ለሌላው ጠላት ሆኖ እርስ በርሱ የሚናቆር ሕዝብ ሲኖር ነው። በነዚህ ድክመቶች ውስጥ የሚኖር አገርና ሕዝብ ባለቤት እንደለሌው ወይም ሰነፍ ባለቤት እንዳለው ቤት በውስጥና በውጭ ደካማ ጠላቶች ይደፈራል፤ይወረራል።
ይህንን እውነታ በአገራችን በኢትዮጵያ እያዬነው ነው።ጥንት ሊወሩ ቀርቶ ድንበር አካባቢ ዝር የማይሉት ሱዳኖች በሰሜንና ሰሜን ምዕራብ ከዚያም በደቡብ በኩል ድንበር ጥሰው ብዙ ኪሎሜትር መሬት ለመቆጣጠር ችለዋል።ከአስር ዓመት ወዲህ እንደ አገር ለመቆጠር የቻለችው ደቡብ ሱዳን ገና አፈሯን ሳታራግፍ ለመኖሯ የረዳቻትን የመቶ ሃያ ሚሊዮን ሕዝብ አገራችንን ኢትዮጵያን ደፍራ ከ150 ኪሎሜትር በላይ ድንበር አልፋ የወርቅ ማዕድን የሚገኝበትን ሰፊ ለም መሬት መቆጣጠሯና ኢትዮጵያውያኖችን ገላና አፈናቅላ የመሬቱ ባለቤት ከሆነች ወራት አልፈዋል።በቀጣዩም ዝም ካሏት ሁሉንም የጋምቤላ መሬት መንጠቋ አይቀርም።የሰሜኗ ሱዳንም እንዲሁ ከድምበር 50 ኪሎሜትር በላይ ዘልቃ የሁመራን አካል ለም እርሻ መሬት ከዓመት በላይ ተቆጣጥራ ተቋማትን ስትገነባ ፣አልፋ ተርፋም የአባይን ግድብና ወንዝ እቆጣጠራለሁ ብላ ስትዝትና ተደጋጋሚ ሙከራ አድርጋለች።በደቡብ በኩልም በሞያሌ ድንበር በኩል ኬንያ ሁኔታውን በማጥናት ወታደሮቿን አስፍራ ገባ ወጣ በማለት ላይ ናት፣ነገ ሞያሌንና አካባቢውን ላለመውሰዷ ዋስትና የለም።ጥንት የኢትዮጵያ ወደቦች የነበሩት ጅቡቲና በርበራም ከማን አንሼ ብለው ኢትዮጵያን ባላቸው የወደብ አቅም ሲፈታተኗትና ሲዳፈሯት ላያት ኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ አላት ብሎ ለማለት አያስደፍርም።እንደሷ የታሪክና ፣የነጻነት ባለቤት ባልሆኑ ደቃቃ አገራት በመደፈሯ በቁንጫ እንደሚወረረው ወና ቤቱ ሆናለች። ለዚህ ያበቃት ላለፉት 50 ዓመታት ተቀኝቶ ፣ላለፉት 32 ዓመታት የመንግሥት ሥልጣኑን በጉልበት የጨበጠው ኢትዮጵያዊነት የማይሰማው፣ኢትዮጵያን ለማፈራረስ አስቦና ተዘጋጅቶ የተነሳው የጎሰኞች ስብስብ አገሪቷን ከውስጥና ከውጭ ለመበታተን ከተነሱ ሃይሎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በመሥራት ላይ ስለሆነ ነው።ይህ ስብስብ ከውጭ ጠላት ይልቅ ለማጥፋት የመረጠው ለአገር አንድነትና ነጻነት የሕይወት ዋጋ ከፍሎ የኖረውን የአማራውን ማህበረሰብ መብት አስከባሪ የሆነውን ፋኖን ነው።ለባዕዳን መሬት ቆርሶም ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ቢያስረክብ ደንታ የለውም።ደንታው ኢትዮጵያ ፈራርሳ ማዬት ነው።ያማ ባይሆን ኖሮ ብዙ ጦር አዘጋጅቻለሁ ከማለት ባለፈ በተግባር የአገራችንን ዳር ድንበር ለማስከበር በደፈረ ነበር።
የጠላቴ ጠላት ወዳጀ ነው በሚል ብሂል ከውጭ ወራሪዎች ጋር እዬተመሳጠረ የአገርን ልዑላዊነት በማስደፈር ተግቶ በመሥራት ላይ ነው።ከዚህ መንግሥት ሰላም፣ነጻነትና እኩልነት አገኛለሁ የሚል ቢኖር ስለ አገር አንድነትና ስለሰላም ብሎም ስለእኩልነትና ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንዛቤ የሌለው ብቻ ነው።በኑሮ ውድነት እዬተጠበሰ፣በጥይት እዬተቆላ፣ በአሸባሪዎች እዬታመሰ መንግሥት አለኝ ብሎ የሚያምን ቢኖር የመንግሥትን ግዴታና ተግባር ያልተገነዘበ፣መገዛትን እንጂ መከበርን ያልወደደ፣ጅራፍ የመረጠ የሰው መንጋ ማለት ነው።
አገር ወዳድና በሕዝብ፣ለሕዝብ ፣የሕዝብ ያልሆነ ቡድን የአገረ መንግሥትነትን ክብር ሊይዝ አይችልም።መንግሥት ተብሎም አይጠራም።የአንድ መንግሥት ሃላፊነት የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት ፣የአገርን አንድነትና ዳርድንበር ማስከበር ነው።ያንን ያላሟላ ከመንግሥት ተራ አይመደብም።የቀድሞው ኢሕአዴግ የአሁኑ ብልጽግና ተብዬው ቡድን በአገራችን ላይ ለደረሰው ውድቀትና ቅሌት፣በሕዝቡ ላይ ለደረሰው ያላባራ መከራ ፣መፈናቀል ፣እልቂትና ለእርስ በርሱ ግጭት ተጠያቂ ነው።
ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪ፣ ከውስጥ አሸባሪና ተባባሪ ለማዳን፣ አሁን ከተዘፈቀችበት አሮንቃ አውጥቶ በዓለም ፊት በተለይም በአፍሪካውያን ዘንድ የነበራትን ክብር ለማስመለስ አገር ወዳድ የሆነ ሕዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋም ሁሉም አገር ወዳድ ተባብሮ መነሳት አለበት።ለአገር ጠሌዎቹ የጎሰኞች መንግሥት የሚሰጠው የዬአንዳንዷ ቀን ዕድል የአገርን መበታተንና የሕዝቡን እልቂት እያጠናከረውና እያፋጠነው ይሄዳል።በሰሞኑ የሚታዬው የሕዝቡ መነቃቃትና እምቢ ባይነት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።በውጭ አገርና በአገር ውስጥ የሚካሄደው የለውጥ እንቅስቃሴ እንዳይጨናገፍ ትግሉን የሚመራ ከሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች የተውጣጣ የጋራ አስተባባሪ አካል መቋቋም አለበት።አለበለዚያ እንደ ወና ቤቱ ባለቤት የሌለው ትግል ይሆንና ሥልጣኑ በአምባገነኖች እጅ ከመውደቁም በላይ አሁን በሥልጣን ላይ ባሉትና በውጭና በውስጥ ጠላቶች ትብብር አገር ይፈርሳል።እንደ አገርና ሕዝብም ከማይኖሩበት ደረጃ ላይ ይደረሳል።የጎሰኞቹ በአገር ውስጥ አጠናክረው የቀጠሉበት የአማራው ማህበረሰብ ጭፍጨፋና በአሜሪካና በአውሮፓ በሌላውም አገር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚያሳዬው ያንኑ እውነታ ነው።ይህንን የጥፋት ሃይል የሚቋቋም ብቻ ሳይሆን የሚያጠፋ ሃይል መፈጠር አለበት።በዬከተማው የሚካሄደውን የተማሪዎች ትግል መቀላቀል የሁሉም አገር ወዳድ ግዴታ ነው።አንዱ ሲገደል ሌላው ከዳር ቆሞ በማዬትና በመፍራት አይድንም።የሱም ተራ በቀጠሮ መያዙን ሊያውቀው ይገባል።ነገሩ ማነህ ባለሳምንት ነው።
ለሚተላለፈው አገር አድን ጥሪ ሁሉም ጆሮውን ሰጥቶ በተግባር መተርጎም አለበት።ጊዜው ለመዳን ወይም ላለመዳን የሚወስኑበት እንጂ ምን ይመጣብኛል ብለው የሚዘናጉበት አይደለም።
በመከላከያው በኩል የፋኖን ሃይል ማጠናከርና በፖለቲካው መስክም አመራር የሚሰጥ ለሕዝባዊ መንግሥቱ እርሾ የሆነ አካል መፍጠር ለትግሉ የተሳካ ውጤትና፤ለአገራችንም ህልውና ዋስትና ነው።
ሕዝባዊ ትግሉ ይፋፋም! እያለቀሱ መሞት ይብቃ!!
ከጎሰኝነት የጸዳ ከአገር ወዳዶች የተውጣጣ ሕዝባዊ አስተባባሪ አካል(የሽግግር መንግሥት) ይቋቋም!!!
አገሬ አዲስ