በዘር በቋንቋቸው በባትሪ በመብራት እየተፈለጉ፣
እንደ በግ እንደ ከበት ሰዎች ሲታረዱ፣
እግዜር ይጠይቃል ማን እንደነበሩ ስለቱን የያዙ፣
ትውልድ ያፋጥጣል እነማን አሳስረው ሕዝብ እንዳስጨረሱ፣
ታሪክ ይታዘባል ስንቶች ሆድ ለመምረግ አፍን እንደ ዘጉ፡፡
ግብር ገባሪዎች በደም በሥጋቸው እየተመረጡ፣
ተቤት ተእምነት ሥፍራ ለአውሬ ለጪራቆች ፍሪዳ ሲቀርቡ፣
ግብሩን የሚበሉት ፓርላማ ምንስቴር ወንጀል ሲደብቁ፣
እግዚአብሔር ይቆጣል ለዘር ማጥፋት ወንጀል ፍትህ በመጥፋቱ፣
ትውልድ ይዘግባል ምንስቴር ፓርላማ ማን እንደነበሩ፣
ታሪክም ያትማል ስንቶች ለከርሳቸው ሕዝብ እንደገበሩ፡፡
ለደም ለአጥንታቸው እየተፈለጉ በጎች ሲታረዱ፣
እረኞች “አባቶች” ይቺን ዓለም ወደው ዛሬም ዝም ሲሉ፣
እግዜር ልብ ያደርጋል በጥምጣም ካባቸው እንደሚያታልሉ፣
ትውልድ ያፋጥጣል በግን አሳልፈፈው ለምን እንደሰጡ፣
ታሪክም ይወቅሳል አቡነ ጴጥሮስን ስላልተከተሉ፡፡
ሕፃን ሴቶች ታርደው ደማቸው ከል ሲቀር፣
አምላክ ይጠይቃል ተችሎት ማን ነበር፣
ትውልድም ያስባል ሄሮድስ ቆሞ ሄዷል፣
ታሪክ ይዘግባል ሕግ ባለሙያው ጲላጦስን ሆኗል፡፡
በቋንቋ ቆንጨራ ትውልድ ሲመነጠር፣
እስተንፋስ ያለው ሰው ዝም ማለት ሲቀጥል፣
በሰው ልጅ ከንቱነት እግዜር ይቆዝማል፣
በዘመኑ ምሁር ትውልድ እፍር ይላል፣
ብዙው በአድፋጪነት ዝም ጪጭ እንዳለ ታሪክ ይዘግባል፡፡
እድሜ እንደ ጨርቅ ያልቃል ነፍስም ሽልብ ይላል፣
ታሪክና ትውልድ በእግዚአብሔር ቸርነት ዘላለም ይኖራል፣
እነማን ምን ሰርተው መቃብር እንደ ገቡ መሬት ላይ ይጥፋል፣
ጭራቁን ባንዳውን ሎሌውን አድፋጩን መዝግቦ ይይዛል፣
ጀግና ሰማእትን እንደ አቡነ ጴጥሮስ ሲያወድስ ይኖራል፡፡
እግዜር ይጠይቃል!
ትውልድ ያፋጥጣል!
ታሪክ ይዘግባል!
በላይነህ አባተ ([email protected])
ሰኔ ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ.ም.