የይህ አድግ መቅሰፍት ወርዶ ባገሪቱ፣
ለፍቶ አዳሪ ዜጎች በጭራቅ ሲፈጁ፣
ጉልቻ እንደራሴ ሚኒስቴር የሆኑ፣
የሟቾችን ግብር ደመወዝ እያሉ፣
ተአራጅ ተአሳራጅ እጅ እየተቀበሉ፣
በሰፊው ከርሳቸው ሲዝቁ ያድራሉ፣
ሕዝብና ትውልድን ታሪክን ሳይፈሩ!
በታቦት በመስጊድ ምዕመን ሲታረዱ፣
ካህናት ጳጳሳት ሐጂውና አቡኑ፣
የሰማእት አስራት ውጠው ይተኛሉ፣
በትንታ እሚያንቅን አምላክን ሳይፈሩ!
ህፃናት አዛውንት ሴቶች ሲታረዱ፣
ምሁር ፕሮፌሰር ዶክተር ነን ባዮቹ፣
በታረዱት ቀረጥ ትምህርት ያገኙቱ፣
ትንኝ እንዳልጠፋ ፀጥ ብለው ሲኖሩ፣
ሕዝብና እግዚአብሔርን ትንሽ እንኳ አያፍሩ!
ቀን የሰጠው ገዥ ከንቲባው አሽከሩ፣
ሎሌ ጋዜጠኞች እነ ሆድ አምላኩ፣
በቋንቋ ቢለዋ ዜጎች ሲታረዱ፣
ምላስና ስንበር መትረው ይበላሉ፡፡
በዚች ምድር በቅለው ዘላለም ላይኖሩ፣
በበሽታ አደጋ ነገ ሲው ሊሉ፣
የሕዝብ ግብር አስራት ደሞዝ የሚበሉ፣
ሚኒስቴር ጳጳሱ ሼሁና ምሁሩ፣
ጭራቆች በጎችን በመደዳ ሲያርዱ፣
ታፋና ፍሪንባ ዘንችረው ያድራሉ፡፡
ዘንችረው ያድራሉ!
ዘንችረው ያድራሉ!
ዘንችረው ያድራሉ!
እግዚኦ!
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ሰኔ ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ.ም.