ግልጽ ደብዳቤ 06-02-2022
ይህችን ማስታወሻ ዛሬ ለዕርሶዎ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ዋናው ምክንያት ሰሞኑን በህግ ማስከበር ስም ሺዎችን በግፍ ማሰር ፤ መሰወር ፤ እንዲሁም የህግ ታሳሪዎችን በአደባባይ ማሰደብደብ የአገዛዞ አይነተኛ መገለጫ እየሆነ በመምጣቱ ድርጊትዎ አገዛዞን የማያጸና በህግ ፊት ተጠያቂነት ያለው መሆኑን ለመጠቆም ነው።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር- በርሶው አገዛዝ በብዙ መቶ ሺህ በላይ ዜጎች ባላአስፈላጊ የርስበርስ ጦርነት ውድ ሀይወታቸውን እንዲያጡ ሆነዋል። አቅፈው ደግፈው በያዙት የዘር ፖለቲካ ብዙ ሚሊዮኖች ከቤት ነብረታቸው ተፈናቅለው ተመጽዋች ሆነዋል። በአገዛዞ ሀገራችን በተፈናቀሉ ዜጎች (IDP) ቁጥር የመጀመርይ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በርካታ ጋዜጠኞችን፤ማህበሪያዊ አንቂዎችን፤ ከህጻን እስክ ሰማንያ አመት ሽማግሌ ሳይቀር አፎኖ መሰወር ያገዛዞ የዘወትር ስራም ሆናል።
የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስቴር – በርሶው አገዛዝ ሀገር አዝናለች። ልጆችዋ ተሳዳጅ፤ ተቅበዝባዥ ሆነዋል ። የኑሮ ውድነት ያጎበጠው ህዝብ የአገዛዞን አፈና መሸከም ተስኖታል። እርሶ ግን የአፈር ማዳበሪያ ለሚጠብቀው የሀገሮ ገበሬ እሳት የሚተፋ ድሮን ና አልሞ ተኮሽ በመላክ ህዝቦትን በማሸበር ስራ ለይ ተጥምደዋል። አገዛዞ ዛላቂ የልማት ፕሮጀክቶችን ከመገንባት፤ ሽቅብ ብቻ ለሚነጉደው የኑሮ ውድነት ሀገራዊ የአጭርና የረዥም ግዜ መፍትሄ ከማፈላልግ ይልቅ የተከሉት አባባ መጥፋት፤ የከተማዋ ህንጻዎች ቀለማት መዥጎርጎር እርስዎ የመጡበት ጎሳ “የዘር መዝመር” በከተማዋ ት/ቤቶች አለመዘመር አብዝቶ ሲያስጨንቆት አንዳንዴም ሲያናደዶት ይስተዋላል። በአጠቃላይ በእርሶዎ አገዛዝ ሀገራችን ሰላሞን ያጣች ተስፋ ቢስና ለመበታተን አንድ ሀሙስ የቀራት ሀገር አድርገዋታል።
ስለዚህ ክቡር ጠቅልይ ሚኒስቲር- በቆዩበት የስልጣን ዘመንዎ ዘረኘነትን ፤ተረኝነትን ና ጥላቻን እንጂ ሰላምና ፍቅርን በምድሪቱ ላይ አያሰፈኑ አይደለም። ይህችን ታላቅ ሀገር የመምራት ችሎታውም ሆነ ቅንንነቱ ያልታየቦት በመሆኑ ስልጣኖን ለግዚያዊ የሽግግር መንግስት በማስረከብ ሀገሮትን ከመበታተን፤ ህዝቦትንም ከእርስበርስ ግጭት በማውጣት ያሳዘኑትን ህዝብ ውለታ አንዲውሉለት ስል በትህትና እጠይቆታለሁ።
ከሰላምታ ጋር
ተፈራ መኮንን (ዶር)