ኢትዮጵያና ግብጽ የአፍሪካ እግር ኳስ ጠንሳሾች ናቸው። ይህን ታሪክ ይጋሩት እንጂ ዛሬ ላይ የሁለቱ አገራት የእግር ኳስ ደረጃ ልዩነቱ ሰፊ ነው።
የደረጃ ልዩነቱ የቱንም ያህል ቢሰፋ ግን በተለያዩ ምክንያቶች የተቀናቃኝነት ስሜታቸው ለአፍታም ደብዝዞ አያውቅም።
ሁለቱ አገራት የአለም ብሎም የአፍሪካ ጥንታዊ ስልጣኔ መገለጫ ከመሆናቸው ባሻገር በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የገጠሙት ጦርነትና የአባይ ወንዝ ትስስር በእግር ኳሱ መንደር ሲገናኙ ፍልሚያቸውን ይበልጥ ያጦዘዋል።
በተለይም ሁለቱ አገራት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና ውሀ ሙሌት ጋር በተያያዘ ከቅርብ አመታት ወዲህ የገቡበት ውዝግብ ባላንጣነታቸውን አደባባይ እንዳወጣው በርካቶች ይስማሙበታል።
ዋልያዎቹ ከፈርኦኖቹ፣ ሁለቱ አገራት ውጥረት ውስጥ ባሉበት፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታም ተጀምሮ ሶስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ሊከናወን በተቃረበበት በዚህ ወቅት ዛሬ በታላቅ የእግር ኳስ መድረክ ተገናኙ።
በ2023 ኮትዲቯር ለምታዘጋጀው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በማጣሪያ ጨዋታ በምድብ አራት የተደለደሉት ዋልያዎቹና ፈርኦኖቹ በገለልተኛ አገር ማላዊ ላይ ሁለተኛ የምድብ ጨዋታቸውን አከናወኑ።
ብርቅዬዎቹ ዋልያዎችም ያልተጠበቀ ድል በፈርኦኖቹ ላይ ተቀዳጅተው ለሁለቱም አገራት ከእግር ኳስም በላይ ትርጉም ባለው የክብር ፍልሚያ ታሪክ የማይረሳው ገድል ፈጸሙ።
ኢትዮጵያ ይህን ታላቅ ፍልሚያ በሜዳዋ ማስተናገድ አለመቻሏ ቁጭት ውስጥ የከተታቸው ዋልያዎቹ በጄነራላቸው ውበቱ አባተ እየተመሩ በፊት አውራሪዎቹ ዳዋ ሆጤሳና አቡበከር ናስር ቅንጅት የፈርኦኖቹን መረብ ለመድፈር 25 ደቂቃ እንኳን አልፈጀባቸውም።
በታሪክ አጋጣሚ ባለፉት በርካታ አመታት ፈርኦኖቹ ዋልያዎቹን በአስራ አንድ ጨዋታ ሙሉ በሙሉ ማሸነፍ ችለዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ፈርኦኖቹና ዋልያዎቹ ሲገናኙ ዋልያዎቹ በሰፊ የግብ ልዩነት እንዳይሸነፉ ደጋፊው የሚጨነቅበት ዘመን የሚዘኘጋ አይደለም።
ዛሬ ግን ታሪክ ተቀየረ፣ ዋልያዎቹም ቀንዳቸው መዋጋት ጀመረ። የፈርኦኖቹን መረብ ዳግም ለመድፈር ጨዋታ አቀጣጣዩ ሽመልስ በቀለ ሁለተኛውን አርባ አምስት ደቂቃ መጠበቅ አላስፈለገውም።
ዋልያዎቹ በፍጹም የጨዋታ ብልጫ ፈርኦኖቹ የሚይዙትንና የሚጨብጡትን ሲያሳጡ ሁለቱ አገራት በአፍሪካ እግር ኳስ የደረጃ ሰንጠረዥ ሶስተኛና አርባ ሶስተኛ ላይ የሚገኙ ናቸው ብሎ ለማመን አይቻልም።
ይህን ተአምርና ጣፋጭ ድል ዋልያዎቹ በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት ማጣጣም ቢችሉ ምንኛ መልካም ነበር። ሆኖም ይህን ቁጭት ትርጉመ ብዙው ድል አካክሶታል።
ዋልያዎቹ ይህን ታሪክ ለመጻፍ ለአገራቸው ክብር ያላቸውን ሁሉ ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ ስፖርት “ታሪክ ተሰራ” ለአትሌቲክስ ጀግኖች ነበር የሚሰራው። ይህን የዋልያዎቹን ገድል “ታሪክ ተሰራ” ከማለት ውጪ ምን ሊገልጸው ይችላል?።
በቦጋለ አበበ
ETV
——————–
ሰሞኑን ባቀረብነው ጽሑፍ በርካቶች የግብጽ ቡድን በሰፋ የግብ ልዩነት ያሸንፋል ሲሉ ገምተው ነበር። ውጤቱም ኾነ የጨዋታው ብልጫ ግን የተገላቢጦሽ ኾኗል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) በዛሬው ጨዋታ የግብጽን ቡድን በሚገባ በልጠው ታይተዋል።
እሁድ በተከናወነው የመጀመሪያው የአፍሪቃ ዋንጫ የማጣሪያ ግጥሚያ የኢትዮጵያ ቡድን በማላዊ ቡድን የ2 ለ1 ሽንፈት አስተናግዶ ነበር። የዛሬው ድሉ በዋሊያዎቹ ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃት ፈጥሯል።
በሌላ ግጥሚያ ተመሳሳይ ምድብ ውስጥ የሚገኘውየማላዊ ቡድን በጊኒ 1 ለ0 ተሸንፏል። በስታዲየሙ የተገኙ የማላዊ ደጋፊዎች ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ድጋፋቸው ሲገልጡ ታይተዋል። የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ከግብጽ ጋር ስለሚኖረው ግጥሚያ ቀደም ሲል ተጠይቀው፦ «የማላዊን ማሸነፍ ተከትሎ የሚገቡ የእነሱ ደጋፊዎቻቸው ከእኛ ጎን ይሆናሉ ብዬ አስባለሁ» ብለው ነበር። ማላዊዎች ኢትዮጵያን በማሸነፋቸው ግብጽ ብትሸነፍ ከምድቡ በነጥብ ከፍ ብሎ ለመገኘት ስለሚረዳቸው ኢትዮጵያን ሊደግፉ ይችላሉ ተብሎ ተገምቶም ነበር።
ለብሔራዊ ቡድናችን በቀጣይ ጨዋታዎችም መልካም እድል እንመኛለን።
ፎቶ፦ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን
DW
https://youtu.be/q-LSL5S0kP8