
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ በድርጅቱ ላያ ያጋጠመውን የኦዲት ግኝት ጉድለት የተነሳ ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን ሶስቱን አመራሮች ማገዱን አስታውቋል፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙት ሃላፊ ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት ሶስቱ የስራ አስፈፃሚ አባላት በድርጅቱ ፋይናንስ ላይ ከፍተኛ ብክነት መፈፀማቸው በውጪ ኦዲተር መረጋገጡን ተከትሎ ታግደዋል ብለዋል፡፡
የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት እና የስራ አስፈፃሚ አባል የሆኑት ዶ/ር ግሩም ሃብቴ ፤ የፖለቲካ ጉዳይ ዘርፍ ሃላፊ እና የስራ አስፈፃሚ አባል ኢ/ር ጌታነህ ባልቻ እንዲሁም የፓርቲው ፋይናንስ ሃላፊ እና ስራ አስፈፃሚ አባል ወ/ሪት ዘቢባ ኢብራሂም የተባሉት አመራሮች መታገዳቸውን ዶ/ር በቃሉ ተናግረዋል፡፡
አመራሮቹ የታገዱት ፕሬዝዳንቱ በቀለበላቸው ሪፖርት መሰረት በወሰኑት ውሳኔ ነው ያሉት ሃላፊው በቀጣዩ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ የታገዱትን አመራሮች ጉዳይ ይመለከታል ሲሉ ዶ/ር በቃ ጨምረው ለብስራት ሬድዮ ተናግረዋል፡፡