በገበያው እሣትነት ህዝብ እየተቃጠለ ነው። ማነው ገብያውን እሣት ያደረገው? – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

እንሆ ዛሬም የሰሞነኛ ቁጥጥር እንጂ ፣ ህጋዊ የንግድ ልውውጥን ለማንበር የሚያሥችል አገራዊ የንግድ ሥርዓት ባለመኖሩ ፣ በነፃ ገብያ ሥም ከትልቁ አሥመጪ ፣  ጅምላ አከፋፋይ ና አከፋፋይ ፣ እሥከ ቸርቻሪው ነጋዴ ድረሥ ገብያው በመሠለኝ ና በደሣለኝ ነው የሚካሄደው ።

 ገበያው የሚመራው በደሣለኝ ና በመሠለኝ ነው።  “ደሥ እንዳለኝ እና በመሠለኝ ዋጋ እሸጣለሁ ።  “ይልሃል ነጋዴው ።  ዩኩሬን ኢትዮጵያ እንደሆነች ቆጥሮ ፣ በ500 ብር ሲሸጥ የነበረውን ዘይት በአንድ ጊዜ ከሺ ብር በላይ ይጠይቅሃል። ምነው ወያኔ እንጂ ሩሲያ አልወረረችንም ። ወያኔም ቢሆን ፤ ወደ ሰብአዊ ምሽጉ ገብቶ ፣ ማሸበሩን ከግብፅ ተላላኪዎች ጋራ በህቡ መቀጠሉን አትዘንጋ።  እናም ነጋዴውን ምን ይሁን ብለህ ነው አዲስ ባልገባ ዘይት ላይ፣ ዋጋ ቆልለህ ገብያውን  እሣት ያደረከው ?  “ብለህ  ብጠይቀው ፣  ” ምን አገባህ !? በመሠለኝና በደሣለኝ ብሸጥ ፣ ነፃ ገብያ እኮ ነው ። ”  ብሎ ይመልሥልሃል  ። ምን ግዴነቱን በተዝናኖት እያሳየህ ።  አንተም በመልሱ የባሰ ተቃጥለህ፣ ቀዝቀዝ ለማለት  ካፊ ጎራ በማለት የታሸገ አንድ ሌትር ውሃ አዘህ ትቀመጣለህ። ሂሳብ ልትከፍል ቦርሳህን ሥታወጣ ፣ በፊት አሥራ አራት ብር የነበረው አንድ ሌትር ውሃ ” አሥራ ሥምንት ብር ። ” ነው ትባላለህ ። እሥከ  “ቲፑ ” ሃያ ብርህን ቁጭ በማድረግ ፣ “የአባይን ልጅ ውሃ የጠማው ዘንድሮ ነው ። “ በማለት እየተረትክህን በወድህ እየተልጎሞጎምክ ትወጣለህ ።

የገበያውን እሣትነት በማሥተዋል፣ “እንዴት  ይዘለቃል “በማለት ፣ ለሌላ ሰው በማይታይ መልኩ እንደ እብድ ከራስህ ጋር እየተነጋገርክ ፣     ምሣህን ለመብላት ወደ  እምታውቃት ደሣሣ  ምግብ ቤት ጎራ ብለህ    ገብተህ የተለመደውን  ሽሮ ታዛለህ   ።  አሥተናጋጇ እየሳቀች ” በዘይት ነው ያለዘይት ? ” ብላ ትጠይቅሃለች  ።  ተገርመህ “ምን ማለትሽ ነው ? “ብላህ ሥትጠይቃት ” ዘይት ሥለተወደደብን በ30ብር ሥንሸጥ የነበረውን ሽሮ ሀምሳ ብር አሥገብተናል ። የሠላሣው ይሰራልኝ ካልክ ፣ ያለዘይት ሥለማንሰራ ይቅርታ አድርግልን ። ለማለት ፈልጌ ነው ። ” በማለት ሣቅ እያለች ፣ አዋዝታ የገብያውን እሣትነት ምጉቡን እንዳሶደደው ታሥረዳሃለች ። መቼም ምን ይደረግ ? ‘ እራቴን እቀጣለሁ እንጂ ምሣዬንሥ አልቀጣም ። ‘ ትልና በሃሣብህ ወደ ድሮ ዘመን ነጉደህ  ፣ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ” አንድ ሹሮ ዘይት ያልበዛበት ። ” ብለህ ታዛለህ ። ይገርማል !  የዛሬ ሠላሣ አመት በፊት  በኢሉባቦር በደሌ ፣ ” ክትፎ ቅቤ ያልበዛበት ” ብለህ ታዝ  ነበር እኮ! ። ያውም የነፁህ ቅቤ መብዛት አንገፍግፎህ ። …

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወንጭፍና ድራጉኖፍ

ዛሬ ሁሉም ነገር ከሌላ ባዕድ ነገር ጋር ተደባልቆ  የተባዛ ና የተከለሰ ፤ የተጭበረበረ ና የተቀያየጠ ሆኖ እንኳን ውድ ነው  ። ከልጅ እሥከአዋቂ የሚጠቀማቸው   የታሸጉ ምግብና የመጠጥ ምርቶች ፣ ከ30 ዓመት በፊት ካለው የጥራት ደረጃ አንፃር በጣዐሙ  የወረደ ነው ። በአሥተሻሸግ ና በውበት ደረጃ ደግሞ ይልቃል     ። በእነዚህ እሽግ ምርቶቾ ላይም   ፣  ከአንድ ብር  ጀምሮ ቀድሞ ከሚገዙበት በእሩብ ፣ በግማሽና በእጥፍ  ያልጨመረ ሸቀጥ የለም     ። ለምሣሌ ብጠቅሥ ፤  የልጆች ብሥኩት ሣይቀር በሰፈር ውሥጥ የአንድ ብር ጭማሪ አድርጓል  ። ደቦ መጠኑ አንሷል ። የአሥራ ሁለት ብሩ ዳቦ የሰባት ብሩን አክሏል ። አንድ አምሥት ብር ገብቷል ። እንጀራ ጎበዝ የማታጠግብ አሥር ብር ገብታለች ። …

“ በእውነቱ በገብያው እሣትነት    መኖር  ከአቅማችን በላይ ሆኗል ። “ ባዩ በእጅጉ በዝቷል ።

“ ህይወታችንን ለማሰንበት እንድንችል ፣ የየጊዜውን የጅምላ ዋጋ እያጠና የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ የሚተምን ፣ የንግድ ሥራው የሚመለከተው የመንግሥት ተቋም  በግልፅ ባለመታወቁ የተነሳ  ፣ ነጋዴው ፣ በመሠለው መሸጡን ቀጥሏል ።  ወቅቱ እኔንን እንድበለፅግ ፣ ልቅ መድረክ እሥከሰጠኝ ጊዜ ድረስ ጊዜ ድረሥ፣  አመቺ የብዝበዛ መድረክ  እሥከፈጠረልኝ ጊዜ ድረስ ፤ ዋጋ መጨመር መብቴ ነው እያለ ከመሬት ተነሥቶ በሸማቹ ላይ ዋጋ ይቆልላል  ። ሸቀጣ ሸቀጦችን በመደበቅ ከእጥፍ በላይ ወጋ እንዲንር ያደርጋል ። በየመንደሩያለን መደበቂያ መጋዘን ህጋዊነት ከመፈተሽ እና  ዘላቂ  መፍትሄ ለማንበር  ከመንቀሳቀሥ ይልቅ ፣ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ፣ የባሰ ችግር ለመፍጠር በህቡ ይንቀሣቀሣል ። ( ይሄ ቡድን ትላንት በኪራይ ሰብሴቢነት ፣ ዛሬ ደግሞ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን አምርሮ የሚቃወም ነው ።)

ይህ ኪራይ ሠብሳቢ ቡድን እንደተለመደው ፣ ያለአንዳች  የፍርድ ቤት ትዕዛዝና የህግ  ምርኩዝ የግለሰቦችን ሱቅ መደዳውን ያሽጋል ። ሸማቹ ሱቆቹ በመታሸጋቸው የበለጠ ይደናገጣል  ።

እናም “ሱቅ ማሸግ የገብያውን እሣትነት ከመጨመር የዘለለ ፋይዳ የለውም ። “በማለት ብሶቱን ያሰማል ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ‹‹ኮነሬል አብይ ዋግ ኽምራን ከአማራ ክልላዊ መንግሥት የማስገንጠል የፖለቲካ ሴራ!!! በዋግ ኽምራ 200 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የብረት መዕድን ሃብት መገኘቱን አክሰስ ካፒታል ኩባንያ በጥናቱ አረጋግጦል!

ይህንን ብሶት የሰማ  ፣ ልቡን ሞራ የደፈነው ባለሥልጣንም  ” ታዲያ ምን ይጠበስ ? ” ይልሃል ። ለእሱ ሁለት መቶ ብር እንደ አንድ ብር ነው የሚቆጠረው ። ምክንያቱም ሁሌም ያልዘራውን ሥለሚያጭድ ።

እናም የአንተን ብሶት ወደዚያ ጥሎ ሱቆቹን  ያሽጋል ። በለሱቆቹም ረብጣ ብር አዋጥተው በተወካዩ በኩል ያደርሱለታል ደ በማግሥቱ ሱቆቹ ይከፈታሉ ። ሲከፈቱ ግን ከበፊቲ በባሰ ተፈላጊ የዕለት ፍጆታ ሸቀጦች ላይ ከበፊቱ ተጨማሪ ብሮችን በማከል ነው ። ለምን ቢሉ የሰጡትን  የጉቦ ገንዘብ በሸማቹ ላይ ለማካካስ ።

ይኽንን ሸፍጥ ያሥተዋሉ ዜጎች የሚከተለውን ጥያቄ ለመንግሥት ይሰነዝራሉ ።

“ እንዴት   ይኽንን የተጋነነ  የዋጋ ጭማሪ ለመግታት ፣ የአንድ የደሃ አገር ህዝብ መንግሥት ( ገዢው ፓርቲ ብልፅግና ) አይገደውም ?! ወይም በተዋረድ ያሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት አይገዳቸውም ? በተገቢው መንገድ ለመንግሥት ታክስ የሚከፍለው ሠርቶ አደር ርሃብ ና ጉሥቁልናስ እንዴት አይሰማቸውም ? እያንዳንዱ ከፍተኛና መካከለኛ ባለሥልጣን  በወንበር ፣ በነዳጅ ፣እና በመሥተንግዶ አበል ትንሿን ደሞዙን በማሳበጥ ፣ እሥከ መቶ ሺ ብር የሚጠጋ ብር  እየገሸለጠ እንዴት ለባለአገሩ ( ለዜጎች ) አያስቡም ? እሥከ መቼስ በርሃብተኛው   ህዝብ እየቀለዱ ይዘልቃሉ ? “ በማለት  ።

በነገራችን ላይ ፣ በየመንግሥት መሥሪያ ቤቱና በየልማት ድርጅቱ የመሣፍንት ና የመኮንንት የደሞዝ አከፋፈልና የጥቅማ ጥቅም ድርጎ ከመኪና እንዲሁም ነዳጅ አቅርቦት ጋር እንዳለ ይታወቃል  ። ይህንን ሥናሥተውል ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ በእጅጉ የበለፀገች አገር ትመሥለናለች ። ይህንን በማሥታዋልም ፣ “ እነዚህ ከፍተኛ ተከፋይ ግለሰቦች በሚከፈላቸው መጠን ለመንግሥት መ/ቤቶቹና ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ምን የፈየዱት ነገር አለና ነው ከትርፋማነታቸው ጋር የማይመጣጠን ክፍያ እና የበዛ እንክብካቤ የሚደረግላቸው   ? “ ብለን እንጠይቃለን ።

ከጥሬ እቃ አንፃር እንኳ ከውጪ ለማሥገባት ዓመታትን በማሥቆጠር ፤ የመንግሥት ፋብሪካን ለኪሳር የሚዳርጉ ፣ በመንግሥት ቀዳዳ በርሜል ተጠቃሚዎች የበለጠ ጥቅማ ጥቅም ያላቸው ናቸው ። ኮሚሽኑንን አትቁጠሩት ።

መንግሥት ፤ የህዝብ ሀብት የሆኑ ፋብሪካዎችን በቅጡ የመቆጣጠር ኃላፊነት እያለበት በሐሰተኛ ሪፖርቶች በመርካት በመጨረሸ  ውድቀታቸውን ለመሥማት እና ለማየት ዛሬ ጆሮውን መዝጋት  እና አይኑንንም መጨፈን የለበትም ።   ከዚህ አንፃርም ፣ የመንግሥት አማካሪዎችን የሚተቹ የዳር ታዛቢ ምሁራን መኖራቸውን ልብ ይሏል ።

ምሁራኑ በተለይም ኢኮኖሚስቶች ፣  “ መንግሥት  የራሱን ኢንዱስትሪዎች ትርፋማነት የሚቆጣጠርበት መንገድ የለውም ። ለዚህም ነው ፣ ኮርፖሬሽን የሚባል ” የማያድግ ልጅ ” ቁጭ አርጎ የሚቀልበው ።  ቁጭ ብሎ ተቀላቢ ባለሥልጣን መ/ቤት ከማቋቋም ይልቅ ፣  እያንዳንዱ የመንግሥት ፋብሪካ እውቀት ባላቸው ቦርዶች የሚመራ በማድረግ እና በቀጥተኛ ቁጥጥር ፋብሪካዎቹን  ትርፋማ ማድረግ ይቻላል ።  “ በማለት ሃሳብ ሲያቀርቡ ይደመጣሉ  ። …

ይህንን እውነት ከዛሬው የኑሮ ውደነት ጋር አያይዞ ይህ ፀሐፊ ያቀረበው ፣ በመንግሥት ና በግል ድርጅቶች ና በሲቪል ሠርቪሱ ተቀጥረው የሚሰሩ ሠራተኝችን በኑሮ ውድነት በገበያው እሣትነት ፣ መቃጠላቸውን በጥልቀት ሥለሚያውቅ ነው ። መነሻ ደሞዛቸው እንኳ ለወርሃዊ  ዘይት መግዣ  የማይበቃ ምንዱባኖች የትየለሌ እንደሆነ ለማንም የተሰወረ አይደለም ።  ሰው በዘይት ብቻ እንደማይኖር ደግሞ የታወቀ ነው ። እናም በዚህ ኑሮ ውድነት የተነሣ ፣ በእርሾ የተነፋፋ “ ውሥጠ  ባዶ “ ፣ ዳቦ ፣ በቧንቧ ውሃ እየማጉ ፣ ተመሥገን ብለው ለመኖር የተገደዱ ሚሊዮኖች ናቸው  ።

ከዚህ አንፃር ነው ፣ “ የአገር አሥተዳዳሪዎችም ሆኑ ባለሥልጣናት ደሞዝ ለሚከፍላቸው ፣ ገበሬና ላብአደር በማሰብ እና የሀገሪቱ ሀብት የሁሉም ዜጎች ሀብትም መሆንን በመገንዘብ እጃቸውን ከሥርቆት ከመሠብሠብ ባሻገር ፤ በከንቱ የሚያግበሰብሱትን ያልተገባ ጥቅማ ጥቅም ዞር ብለው በማየት የተወሰነውን ጥቅማ ጥቅም   በመተው  አገሪቱን መልሶ ለመገንባት ቢያውሉት ይበጃል ።  “ የሚባለው ።

በዚህ ሽሮ ባረረበት አገር   ቢያንስ ደሃው ህዝብ ፣ በቀን ሦሥቴ ሽሮ በእንጀራ  የሚበላበትን መንገድ ለመቀየስ ለከት ካጣ ቁንጣን ፣ ከገሃዱ  አለም የምቾት ድራማ ፣ባለሥልጣናቱ ፣  በአሥቸኳይ መውጣት አለባቸው ። እያሥተዳደሩ ያሉት በርሃብ ምክንያት ታክኮ ፣ ታክኮ ፣ የቆሰለ ሆድ ያለው እጅግ የሚያሳዝን በሚሊዮን የሚቆጠር ሀዝብ መሆኑንን በተገቢው መልኩ ቢረዱ መልካም ነው        ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሃይማኖታዊ እምነት እና የተግዳሮቱ አሳሳቢነት!

የገብያው እሣት መሆን ሙሉ በሙሉ  የወቅቱ  የታላቋ ሩሲያ ፣ የቀድሞዋን የሶቬት ግዛት ዩክሬንን መንጠራራት ለማሥቆምና ኔቶን ” እረፍ ! ”  ለማለት ፣ የአባት አገርን ክብር አሥጠብቆ ለማሥቀጠል ! ፑቲን የዩክሬን ግዛትን በመውረራቸው  የተከሰተ ነው ። በማለት ሰበቡን አጠቃሎ ለዚህ ጦርነት መሥጠት አይገባም ። በዓለም  ምጣኔ ሀብት  እንቅሥቃሴ ላይ ያሥከተለው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል ባይሆንም ፣ የተጋነነ  ችግር ይኽ ጦርነት በሁሉም ሸቀጦች ላይ  ያለማሥከተሉ ይታወቃል ።

ምክንያቱም የሩሲያ ዩክሬንን መውረር የምግብ  ዘይትን እጥረትን ይኽን ያህል  የሚያባብሥ አይደለም ።   ፣ ቻይና ፣ማሌዢያ ዩኔይትድ እሥቴት ፣ ብራዚል ፣ አርጄንቲና ፣ኢንዶኔዢያ ፣ ሩሲያ ፣ ዩክሬን ፣ ካናዳ ፣ ጀርመን ፣ታይላንድ ፣ ፈረንሳይ ፣ ሥፔን ፣ቱርክ ወዘተ ። በቅደም ተከተል የምግብ ዘይት አምራቾች መሆናቸው ይታወቃል ። በዓለም በሁለቱ አገራት  አቅርቦት የተወሰነው ዘይት ፣ የሱፍ ዘይት ምርት ብቻ ነው ። ህንድ ለምሳሌ ሙሉ ለሙሉ የሱፍ ዘይቷን ከእነዚህ አገሮች ነው የምታሥገባው ።አሁን  በቶን እሥከ 135 ዶላር ይህ ዘይት ጨምሯል ። በጣም የሚያሳዝነው ግን በእኛ አገር ሰማይ ወጥቶ የተሸጠው ቀደም ብሎ በርካሽ የገባው የሱፍ  ዘይት መሆኑ ነው ። ከዚህ አንፃር ነው ” የንግድ ሥርዓቱን የሚቆጣጠሩ ባለሥልጣናት ፤ ምን ሠርተው  ነው እንዲህ የተዘባነነ ኑሮ ሲኖሩ የምናሥተውለው    ?  ” በማለት  የምናማርረው ።

ከሩሲያና  ዩኩሬን ውጪ ፣ የዓለምን ገብያ የያዙ ሥንዴ አምራቾችም አሉ  ፤ ቻይና፣ ኢንዲያ ፣ ሩሲዬ ፣ ዩናይትድ እሥቴት ፣ ካናዳ ፣ አውሥትራሊያ ፣ ዩክሬን ፖክሥቲያን ፣ ቱርክ ፣አርጀንቲና ፣ ኢረን ፣ካዛክሥታን ፣አንጊሊዝ ፣ ወዘተ ። በቅደም ተከተል ይጠቀሳሉ ።  ሥንዴ እንኳን ይህን ያህል እንደ ዘይቱ የዓለም ችግር አልሆነም ። ለእኛ ግን ነው ።

የድህነታችንን ጥግ በዳቦ ችግራችን ልክ ማወቅ እንችላለን ። ይሁን እንጂ ባለሥልጣናቱ የአውሮፖ አገራት ና የአሜሪካ  ባለሥልጣናት እንጂ ፤ ዳቦ የቸገረው ፣ በችጋር የሚሰቃይ ዜጋ የበዛባት ፤ ማሥቲሽ በየጎዳነው እየማገ በየሜዳው የሚተኛ አሣዛኝ ወጣት በየከተማው የሚርመሠመሥባት የደሀይቱ አገር የኢትዮጵያ  አሥተዳዳሪዎች ( አገልጋዮች )  አይመሥሉም ። ጎበዝ የመኮንንቱ ና የመሣፍንቱ የተዘባነነ የኑሮ ህይወትና የተራው ሰው ሰቆቃ የሚሥተዋልበት ፣  የመሣፍንት ፤ የመኳንት ፤ የልዑላን ቤተሰቦች ( ፊውዳሊዝም )፣ አገዛዝ በዘመናዊ መልኩ ተመልሶ በኢትዮጵያ ነገሰ እንዴ ?

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share