በዶር አብይ አህመድ የሚመራው የኦህዴድ/ብልጽግና መንግስት ስልጣን ከጨበጠ አራት አመት ሆነው። ላለፉት አራት አመታት የነበረው ሁኔታ ፣ ለዘመናት በኢትዮጵያዉያን መካከል ያለውን መተሳሰር ከመቼውም ጊዜ በላይ ፈተና ላይ እንዲወድቅ ያደረገ ፣ ምን አልባትም በኢትዮጵያ ታሪክ የጨለማ ዘመን ሊባል የሚችል ነው።
የፌዴራልም ሆነ የኦሮሚያ ክልልን መንግስት የተቆጣጠረው የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ፣ እያራመደ ያለው፣ መረን የለሽ፣ የኦሮሞ ጽንፈኝነት፣ የመስፋፋትና የመጨፍለቅ ተረኛና ዘረኛ አካሄድ፣ በተለያዩ የአገሪቷ ግዛት ከፍተኛ ግጭቶችን፣ ጦርነቶች፣ እልቂቶች ፣ ጭፍጨፋዎችን፣ መፈናቅሎችን የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳቶችን እያስከተለ ነው። አገሪቷ ለስሙ መንግስት አላት እየተባለ መንግስት እንደሌላት አገር እየሆነች ነው።
በኦሮሞ ክልል በምእራብ ፣ በምስራቅ፣ በቄሌምና በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ፣ በሰሜንና በምእራብ ሸዋ፣ በጉጂና በምእራብ ጉጂ ዞኖች በመንግስት የተደገፉ ጽንፈኛ ታጣቂዎች በስፋትና በነጻነት እየሰለጠኑ፣ እየተደራጁ በመንቀሳቀስ፣ ለብዙ ቀውሶች ምክንያት መሆናቸው የአደባባይ ሚስጠር ነው።
በቅርቡ የኦሮሞ ጽንፈኛ ታጣቂዎች አድማሳቸውን በማስፋት በመንግስት ተሽከርካሪዎች ታግዘው፣ ወደ አማራ ክልል ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በመዝለቅ ፣ የሽብር ተግባራት ፈጽመዋል።በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ፣ የአሞራ ቤት ቀበሌ ውስጥ በምትገኝ አውራ ጎዳና በምትባል መንደር፣ የታጠቁ ኃይሎች የመንግስት ተሸከርካሪዎችን በመጠቀም ጉዳት ማድረሳቸውን ኢሰመጉ ባወጣው መግለጫ ገልጿል። በተፈጠረው ግጭት ከ26 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ከአዳማ ከተማ 17 ኪሎሜትር፣ ከመተሃራ 8 ኪሎሜትር፣ ከወለንጭቲ 7 ኪሎሚትር፣ ከሞጃ 15 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ያለ ወረዳ ሲሆን፣ በደቡብ በኩል ከኦሮሞ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ፣ ቦሰትና አዳማ ወረዳዎች ጋር ፣ በምእራብ በኩል ከሎሜ ወረዳ ጋር የተዋሰነ ነው።
በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ እንዲሆም በአጎራባች የምስራቅ ሸዋ ዞን ወረዳዎች፣ አማራው፣ ኦሮሞው፣ አርጎባው.. ለዘመናት እንደ ኢትዮጵያዊ ተከባብሮ፣ ተዋልዶ ሲኖሩባቸው የነበሩ፣ በአንጻራዊነት የተሻለ ሰለምና መረጋጋት የነበረባቸው ወረዳዎች ነበሩ። ነገር ግን አሁን ምንጃር ሸንኮራ፣ ፈንታሌና ቦሰት ወረዳዎች፣ በኦሮሞ ጽንፈኞች ቀስቃሽነት የግጭት ቀጠናዎች መሆናቸው በጣም ያሳዝናል።
በብዙ ቦታ መንግስት አለ እያሉ፣ እምነታቸውን መንግስት ላይ ብቻ በማድረጋቸው፣ ሳይታሰብ በደረሰባቸው ጥቃት በአሸባሪዎች የረገፉ፣ ያለቁ የተጨፈጨፉ ዜጎች ቁጥራቸው ተቆጥሮ አያልቅም። አዎን መንግስት እምነት የሚጣልበት ነበር። ግን በዶር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ፣ እንኳን እምነት ሊጣልበት፣ እንደውም ከአሸባሪዎች ጋር ተባባሪ ሆኖ ሕዝብን እያስጠቃ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።
የምንጃር ሸኮራ ወረዳ ሕዝብን በአሸባሪዎች ጥቃት ሲፈጸምበት የሚጠብቀው የመንግስት አካል ባለመኖሩ ተደራጅቶ ራሱን ለመጠበቅ ያደረገው እንቅስቃሴ የሚደገፍ ብቻ ሳይሆን ለሌላው ማህበረሰብ ትልቅ አርዓያ የሚሆን ነው።
ለሕዝብ የሚያስብ፣ ለሕዝብ የሚሰራ፣ ሕዝብን ለመጠበቅ የሚተጋ ፣ ሁሉንም በእኩልነት የሚያይ መንግስት እስኪመጣ ድረስ፣ ሕዝብ በየአካባቢው ተደራጅቶ ራሱን ከመጠበቅና ከመከላከል ውጭ ሌላ አማራጭ ሊኖረው አይችልም።