“በኢሕአዴግ መንግስት የሕግ የበላይነት ጭላንጭል በሐገራችን እየተዳፈነ ነው” – (ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ)

በኢሕአዴግ መንግስት የሕግ የበላይነት ጭላንጭል በሐገራችን እየተዳፈነ ነው!!!
(ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ)
ኢትዮጵያውያን የእስልምና እምነት ተከታዮች የሐይማኖት ነፃነታቸው እንዲከበርላቸውና የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ላለፈው አንድ አመት ያለማቋረጥ በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በሒደቱ መጀመሪያ አካባቢ መንግስት ከጥያቄ አቅራቢዎቹ የተወከሉትን የኮሚቴ አባላት እውቅና በመስጠት ሲያወያይ ከቆዬ በኋላ አብዛኛዎቹን የኮሚቴ አባላት በሽብርተኝነት ከሶ ወደእስር ቤት እንዲወርዱ አድርጓል፡፡ የተከሳሾቹ ጉዳይ በፍርድ ቤት እየታየ ባለበት በአሁኑ ሰዓት በሕገ መንግስቱ የተደነገገውን ማንም ሰው ወንጀለኛነቱ በፍርድ ቤት እስኪረጋገጥ ድረስ እንደንፁህ የመቆጠር መብትን በመጣስና ተከሳሾች ራሳቸው ጥፋተኛ መሆናቸውን እንዲያረጋግጡ በሚያስገድድ ሁኔታ የዜጎችን ስብዕና የሚያራክስ ዘጋቢ ፊልም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በተከታታይ በማሳየት ላይ ይገኛል፡፡ የተከሳሽ ጠበቆች የዘጋቢ ፊልሙ መተላለፍ ሕገ መንግስቱን የሚፃረርና የደንበኞቻቸውን መብት የሚጋፋ በመሆኑ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ፊልሙ እንዳይተላለፍ ያሳገዱ ቢሆንም በሕግ ምንም አይነት ይግባኝ ለማለት መሰረት በሌለው አካሄድ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ እገዳውን አስነስተናል በማለት ጉዳዩ የሚመለከተው ፍርድ ቤት ያሳለፈውን የእግድ ውሳኔ በመጣስ ኢቲቪ ዘጋቢ ፊልሙን እየደጋገመ አስተላልፏል፡፡ በሂደቱም ተከሳሾች መረጃዎችን በአስገዳጅ ሁኔታ ሊሰጡ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ድርጊቶች በዚሁ የዘጋቢ ፊልም ላይ የታዩ አንዳንድ ክስተቶች አመላክተዋል፡፡ በመሆኑም ሰማያዊ ፓርቲ ከላይ በተጠቀሱትና አስፈፃሚው አካል በህግና በዜጎች ሰብዓዊ መብት ላይ በፈፀማቸው ነገሮች ሁሉ እጅግ ያዘነ መሆኑን እየገለፀ፡-
1. ማንም ሰው ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት ነፃ ሆኖ የመታየት መብትን በመጋፋት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በህግ ስር በሚገኙ ዜጎች ላይ በተደጋጋሚ የፈፀማቸው ድርጊቶች እጅግ አሳፋሪ መሆናቸው፣
2. የአንድ ፍርድ ቤት ውሳኔ በአስፈፃሚው አካል ለህግ አልገዛም ባይነት ሲሻር ማየት ዜጎች በህግ ላይ ያለን እምነት እንዲሸረሸርና ተስፋ እንድንቆርጥ የሚያደርግ መሆኑ፣
3. ማንንም ሰው ከራሱ ፈቃድ ውጭ በማስገደድ መረጃ መውሰድና ይህንንም ያለፍርድ ቤት ፈቃድ ስብዕናቸውን በሚያረክስ መልኩ በመገናኛ ብዙሃን እንዲተላለፍ ማድረግ በህገ መንግስቱ የተከለከለና የዜጎችን ሰብዓዊ መብት የሚጥስ ተግባር የተፈፀመ መሆኑ፣
4. በዘጋቢ ፊልሙ የቀረቡ ነገሮች በሐገራችን ለብዙ ዘመናት ተቻችለውና ተከባብረው የኖሩ የተለያዩ እምነት ተከታይ ዜጎች እርስበእርሳቸው እንዳይተማመኑ የሚያደርጉ መልዕክቶች የተላለፉበት ስለሆነ እንዲህ አይነቱ መልዕክት ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ እውነት ነው ብሎ እንደማይቀበለው የታወቀ ቢሆንም የነገሩ አካሄድ ግን ለሐገራችን የማይጠቅም አደገኛ አካሔድ መሆኑ፣
5. አሁንም ከሂደቱ እንደምንረዳው ድምፃችን ይሰማ በማለት ጥያቄ ያነሱ የእስልምና እምነት ተከታዩች ጥቂት እንዳልሆኑና ትግሉም ከመብረድ ይልቅ ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑን ሰማያዊ ፓርቲ ይገነዘባል፡፡
በመሆኑም የኢሕአዴግ መንግስት ከላይ የተጠቀሱትን አፍራሽ ተግባራት ከመፈፀም እንዲቆጠብና የእምነቱ ተከታዮች ላነሷቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ወደዘላቂ መፍትሄ እንዲደረስ ሰማያዊ ፓርቲ አጥብቆ በአፅንዖት ይጠይቃል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የታክሲዎች ስራ ማቆም እንድምታ - በእስክንድር ነጋ
Share