(ዘ-ሐበሻ) የአርቲስት ታምራት ሞላ የቀብር ስነ- ሥርዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ቤ/ክ ተፈጸመ። በርከት ያሉ አድናቂዎቹና ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት በተፈጸመው የቀብር ስነስ-ር ዓቱ ላይ የአርቲስቱ የሕይወት ታሪክ ተነቧል። ከሕይወት ታሪኩ መረዳት እንደተቻለ አርቲስት ታምራት ሞላ በ19 36 ዓ.ም ከአባቱ ከፊት አውራሪ ሞላ ዘለለውና ከእናቱ ከወይዘሮ አበራሽ የኔነህ ፥ በጎንደር ከተማ ተወለደ። ባለ ትዳር እና የ3 ወንድ እና የ2 ሴት ልጆች አባት የነበረው ይኸው አርቲስት በ19 53 ዓ.ም ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ ከአጎቱ ጋር በመምጣት በክቡር ዘበኛ የልጅ ወታደር በመሆን የሙዚቃውን አለም አሃዱ ብሎ እንደጀመረ የሚያስረዳው የሕይወት ታሪኩ ከአራት አመት በፊት ባጋጠመው ህመም ሳቢያ በአሜሪካ እና በታይላንድ ህክምናውን ሲከታተል ቆይቶ በ69 አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።
በ19 55 ዓ.ም አብዛኛውን የሙዚቃ ህይወቱን ያሳለፈበትን የምድር ጦር ሰራዊትን የተቀላቀለው አርቲስት ታምራት ፥ ሃገራዊ ፣ ማህበራዊ እና ፍቅርን መሰረት ያደረጉ ሙዚቃዎችን ከመጫወቱ ባለፈ ድራማ እና ቲያትርን ምክንያት አድርጎ መድረክ ላይ መቆም መቻሉን ከተነበበው የሕይወት ታሪኩ መረዳት የተቻለ ሲሆን በተለይም ትግላችን በሚል ቲያትር በመሪ ተዋናይነት ለመጫወቱም ባለፈ ፥ የበርካታ ዜማዎች ድርሰትን ቀምሮ ለህዝብ አቅርቧል።
በሃገር ፍቅር ቲያትር ቤት ለረጅም ጊዜያት በድምጻዊነት ያገለገለው አርቲስት ታምራት ፥ ከ50 አመታት በላይ ባስቆጠረው የሙዚቃ ህይወቱ ከአድማጭ ጆሮ የማይጠፉና የማይረሱ ሙዚቃዎችን ተጫውቷል።
አርቲስት ታምራት ሞላ ለረዥም ጊዜ በደም ካንሰር ሲሰቃይ እንደነበርና ከዚህም ህመም በጸበል መፈወሱ ይታወሳል። ድምጻዊው ሙዚቃ አቁሞ መዝሙር ለመዘመር ሃሳብ እንደነበረውም በአንድ ወቅት መናገሩ አይዘነጋም።