April 4, 2013
32 mins read

የስደት ኑሮ ቅኝት

                        

መጋቢት 30 ቀን 2013

በታክሎ ተሾመ

በዚህ ርዕስ ዙሪያ እንዳተኩር  ያስገደዱኝ የተለያዩ ሁኔታዎች  በአእምሮዬ እየተብላሉ በስሜቴ ውስጥ ተወሽቀው  በርካታ  ዓመታትን ያሳለፉ  ኩነቶች በመኖራቸው ምክንያት ነው።

የሰው ልጅ ተፈጥሮ  እንደግል ባሕሪው ይለያያል። እንደ ግለሰቡ ( እንደ ሰውየው) አስተሳሰብ  ማንኛውም ሰው ነገሮችን በትክክል አገላብጦ ማየትና ማሰብ ከቻለ የሚፈጠሩ ችግሮችን በቀላሉ ማርገብ ይችላል። የሰው ልጅ ተወልዶ ማሰብ እስከ ጀመረ ድረስ በራሱ የሚያከናውነው ወይም የሚያሳያቸው ባሕሪያቶች አሉት። በራሱ ስነ-ልቦና ዙሪያ  የሚያጠነጥን ሆኖ የሌላውን ሰው ስሜት ላለመጉዳት የሚያሳየው ቅንነት ይኖረዋል። ባንፃሩ የሰው ልጅ ባሕሪ የተለያየ እንደመሆኑ መጠን ሁሉም እንደ ባሕሪው የተለያየ ስለሚሆን  ለሌላው ሰው ክብር ከመስጠት ይልቅ ራሱን ያስቀድማል፤ ራሱን ከፍ  አድርጐ ያስቀምጣል። በዚህ ምክንያት ወደ ”ግለኝነት” በሚያደላ ንፍገት (ራስ ወዳድ) የተሞላበት በመሆኑም ይመስላል ከሌላው ሰው ጋር ከሚቀራረበ  ሃሳብ  ላይ ለመድረስ ብሎም አንድ በሚያደርገው  የጋራ  ሃሳብ (ግብ) ከመቀራረብ  ይልቅ ለመራራቅ የሃሳብ ልዩነቶችን  ለማራገብ  ይቸኩላል።

 

ከላይ እንደተጠቀሰው የሰው ልጅ ራስ ወዳድነት ባሕሪ ቀስ በቀስ እድገት ያሳያል። የራስ ወዳድነት ባሕሪ ለጠብ አጫሪነትም ምክንያት መሆኑ ሃቅ ነው።  በዓለማችን ወይም በራሳችን ማኅበረሰብ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት አለመግባባት ብቻ ሳይሆን እስከ ሕይወት መጥፋት እየደረሰ  ነው። አካባቢያችንን ስንቃኝ  ከቤተሰብ  እስከ ማኅበረሰብ ድረሰ የሚደረጉ ግጭቶች ዋቢ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ በአገር ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶች እስከ አጐራባች አገሮች  ሳይቀር ይዘልቃል። ሩቅ ሳንሄድ የትላንቷ የኢትዮጵያ አካል በነበረችው ኤርትራ እንዲሁም በፈጠረው የጐሳ ፖለቲካ ጨዋታ የርስ-በርስ ቅራኔና ግድያዎችን ማስታወስ ይበቃል።

 

ከላይ ይህን ካልኩ ዘንዳ ወደ ራሳችን ማኅብረሰብ ልመልሳችሁ። እኛ ኢትዮጵያዊያን ከአፍሪካ አልፎ በዓለም የነፃነት ተምሳሌዎች መሆናችን የተረጋገጠ ነው። አገራችን የሃይማኖት ማፍለቂያ የፍቅር አውድማ፤ ልምላሜዋ በተፈጥሮ የተሞላ፤ የሰው ዘር የሉሲ መገኛና ሌላም ብዙ  ማዕድን የሚገኝባት ውብ አገራችን ስለመሆኗ ማንም ከቶ ሊክድ አይችልም። የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩንና ሃይማኖቱን የሚወድ፤ ጠላት ሲመጣ በጋር የሚቆም፤ ዘር ሳይለይ ተጋብቶና ተዋልዶ ተከባብሮ የኖረ ሕዝብ ስለመሆኑ የታሪክ ተመርራማሪዎች ዘገባ ያስረዳል። ኢትዮጵያ የ 5000 ሽህ ዘመን ታሪክ እንዳላት ዶር ፍቅሬ ቶሎሳ በቅርቡ ባሳተመው የምርምር መጽሃፍ ያስርዳል።

 

ጠቅለል ባለ መልኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተራበን በማብላት፤ የታመመን በመጠየቅ፤ የሞተን በመቅበር ባጠቃላይ የሰው ዘርን ሁሉ አክባሪ ሕዝብ መሆኑ እርግጥ ነው። ኢትዮጵያ ቅዱስና ተወዳጅ አገር ብትሆንም  ከአብራኳ  በተፈጠሩ ገዥዎች ሕዝብ እንደ ሕዝብነቱ በስላም መኖር አልቻለም። በግፍ አገዛዝ ብዙዎች የመከራን ኑሮ መቋቋም እያቃታቸው ለአገርና ለሕዝብ ሊጠቅሙ የሚችሉ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሞትና ስደት እጣ ፈንታቸው ሆኗል።

 

የኢትዮጵያውያን ስደት መቼ  ተጀመረ ብሎ የሚጠይቅ ካለ ስደት የተጀመረው በደርግ ስርዓት መሆኑን ጥናቶች የሚያመላክቱ ሲሆን በወያኔ ዘመን ግን በዓለም ዙሪያ በስደት የሚኖረው የወገን ቁጥር እጅግ ብዙ ነው ብሎ ማለፍ ይቻላል። የስደት ዓይነቶች የተለያዩ ይሁኑ እንጂ አንድኛው በፖለቲካ ችግር ምክኒያት መሆኑ አያጠያይቅም። በስደት አገር በተናጥል ከመኖር ይልቅ ስደተኛው ከየትም ተጠራርቶ በያለበት ሊያሰባስብ የሚችል አማራጩ ማኅበር ነው። ከሱዳን፤ ከኬኒያ፤ ከጅቡቲ፤ ከግብጽ ወዘተ ጀምሮ በተለያየ መንገድ በኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማኅበር አማካኝነት በጋራ ለመደራጀት ተሞክሯል። ከዚህ በተጓዳኝም በእድር፤ በሰንበቴ፤ በቅዱሳን ሥም በማኅበር ፀሎቶችም መሰባሰብ የተለመደ  ነው።

 

በስደት የተበተኑ ኢትዮጵያዊያን በያሉበት ሆነው የአገራቸውና የሕዝባቸውን ክብር ለማስጠበቅ በሚደረገው ሁሉ ከገንዘብ እስከ ጉልበት ከመለገስ እንደማይቆጠቡ በየጊዜው  የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ማስረጃዎች ናቸው። ስደተኛው የመተጋገዝ፤ የመከባበር፤ አብሮ የመብላት፤ የታመመ በገንዘብ መርዳትና  መጠየቅ፤ የሞተን መቅበር ዋነኛ መለያዎች  ናቸው።

 

ከፍ ሲል እንዳልኩት ብዙ አኩሪ ባሕሎች እንዳሉን ሆኖ ነገር ግን ብዙ አስቀያሚና ጐጅ ባሕሎች መኖራቸው የሚካድ አይሆንም። አገር ቤት ያለውን ሕዝባችን ለጊዜው ወደ ጐን  አድርገን በስደት አገር የምንኖር ኢትዮጵያዊያን ብዙ የሚቀሩና የሚጐድሉን ያባሕሪ ለውጦች  አሉን። አብዛኛዎቻችን የተሰደድነው በፖለቲካ ችግር ምክኒያት ነው። ባለንበት አገር  ሊያሰባስበን የሚችል ማኅበር እንደሚያስፈልግ ይታመናል። ለዚህ ዋናው አሰባሳቢ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማኅበር ስለመሆኑ ከዚህ በፊት ጠቅሻለሁ። ይሁን እንጂ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያቶች የተዋቀሩ ማኅበራት በየጊዜው እየተዳከሙና  እየፈረሱ ስናይ ምን ያህል በውስጣችን ችግር እንዳለ አመላካች ነው።

 

እንደ አለመታደል ሁኖ አሁን አሁን በውጭ አገር ከምንታወቅባቸው ነገሮች ውስጥ በጋራ አለመቆማችን ግንባር ቀደሙ  ነው። ይባስ ብሎ በጋራ  አለመቆማችን  ብቻ  ሳይሆን  አንዱን አንዱ ለማጥፋት(ለመጉዳት) እርስ በርሳችን ጉድጓድ እንጭራለን። ይኽ ለምን ይሆናል? ብሎ መጠየቅ ተገቢ  ይመስለኛል። የውጭ ባዕዳን  የሚያውቁን  በጀግንነታችን በነፃነታችን በአፍሪካ  ተምሳሌነታችን  ሆኖ  እያለ የራሳችን ክብር ራሳችን ለምን እንደምናዋርደው መፍትሄ ያልተገኘለት ጥያቄ  መሆኑ  አልቀረም።

 

ከሀገር ውጭ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ያለንበትን የምቾች ኑሮ ሳንመለከት አገራችንና ሕዝባችን በምን ሁኔታ ትገኛለች የሚለውን ወደ ኋላ ተስበን ልናስተውለው ይገባል። “አንገት የተፈጠርው አዙሮ ለማየት” ነው የሚባለው  አባባል እንዲህ ቀላል ትርጉም ሊሰጠው የሚገባ አይደለም። ቤተሰቦቻችን ከእኛ የዳቦ መግዣ ገንዘብ ይጠብቃሉ። ከዚህ በተጓዳኝም ለዴሞክራሲ ለሚደረገው ትግል  እንድናግዛቸው ይሻሉ።

 

ከላይ የተጠቀሰውን ለማሟላት ፍቅርና አንድነት ብሎም በማኅበርም ሆነ በድርጅት  መደራጀት አንድና ሁለት የለውም። ይኽን ሁላችንም በአፍ አዘውትረን ስንናገር  እንደመጣለን። ይሁን እንጂ”ዱባና ቅል አበቃቀሉ እየቅል”እንዲሉ በሆነ ባልሆነ ነገር  አንድነትን ከሚሰብኩ ቃላት ውጭ ሊያነጣጥሉ የሚችሉ ሃሳቦች በየጊዜው እየተበራከቱ የአንድ አገር ልጆች ያውም በደም ተሳሰርን ላለመግባባት ያልሆኑ ምክንያቶች ለምን እየፈጠርን እንደምንጣላ ምስጢሮች እንቆቅልሽ  መሆናቸው  ያሳዝናል።

 

በስደት ሊያሰባስበን የሚችል ባሕላችን፤ ቋንቋችን ብዙ ብዙ ሊያግባቡ የሚችሉ የአንድነት ምልክቶች እያሉን  እነሱን አዳብረን መታየት ስንችል ከሌሎች ማኅበረሰቦች  ባነስ ሁኔታ በእኛ ላይ ብቻ ለምን እርስ በርሳችን መካረርና ወደ ጥላቻ እንደምናመራ ምክንያቶቹን ለማወቅ  ሁሉም ሊመራመርበት ይገባል።

 

የውጩን ድክመት ስፋ አድርጐ መመልከት ከስህተት ለመዳን የሚጠቅም ይመስለኛል። አገራችንና ሕዝባችን በምን ሁኔታ እንደሚኖር ለማንም የተሰወረ ስለማይሆን ነጋሪ አያስፈልግም። ግለሰብም፤ ድርጅቶችም፤ ፓልቶኮችም፤ ሬድዮኖችም ወዘተ ብዙ  እያሉ ነው። ዲያስፖራው በተለያየ ጊዜ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚወጣ ብዙ ጊዜ ታይቷል። ነገር ግን  በሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች  ላይ ስንቶቻችን ነው  በጋራ  ወጥተን ጭሆት ያሰማነው  ለሚለው  ጥያቄ በድፍረት ሁላችንም ብሎ መመስከር የሚቻል አይመስለኝም። ለዚህ ደግሞ ችግሩ  ፍቅርና መቻቻል አለመኖሩ ነው። ፖለቲካ በመቻቻልና በመደማመጥ ከተሠራ ለትብብርና ለአንድነት ጠንቅ ሰለማይሆን የሰዎችን አንድነት ሊያናጋ አይችልም። ድርጅቶችም፤ የእምነት ቤቶችና የኮሚኒቲዎች ማኅበር በሕገ-ደንብ ከተመራ ደጋፊዎችም ተጠናክረው ማገዝ ይችላሉ።

 

በቅርበትም ሆነ በሕዝብ መገናኛ መገንዘብ እንደተቻለው ከሆነ በስደት ብዙ አስደናቂ ነገሮችን በትዝብት አተኩረን ስንቃኛቸው የተለያዩ ጠቃሚና ጐጅ ባሕሎች የሚታዩበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ባለንበት በሰው አገር ስንኖር የጥንት የፍቅር ባሕላችን የምንገልጽባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎችን እንጠቀማለን። ለምሳሌ ሻይ ቤት፤ ከርስትና፤ በልጆች የለደት ቀን፤ በእምነት ቤታችን በሰርግና በተለያዩ አጋጣሚዎች እንገናኛለን። በዚህ ጊዜ ለሄድንበት ጉዳይ ሳይሆን ስለአገራችንና ስለሕዝባችን ጉዳይ ሳናነሳ የምንለያይበት ቀን አለ ለማለት ይከብደኛል። ሁሉም አገሩን ይወዳል፤ወገኑን ሕዝቡንና ባሕሉን ይወዳል።ያስደስታል፤ እሠየው ያስብላል፤ጥሩ ነው።

 

ነገር ግን የስደተኛውም ሆነ የድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ በመጣ ቁጥር ያ ነበር የተባለው   ፍቅርና መተሳሰብ እየቀነሰ በምትኩ አንዱ ከአንዱ የተሻለና አዋቂ ለመሆን ሲባል የሠይጣን ሥራዎች ቦታቸውን ያዙ። እርስ በርሳችን ለመጠፋፋት የሚደረጉ ሙግቶች በጣም አሳፋሪ መሆናቸው አልቀረም።

 

የረጅም እንቅስቃሴዎችን ተመልሰን ስንቃኛቸው ለትብብርም ሆነ ለአንድነት ትልቁ ጠንቅ  አንዳንዶች የፖለቲካውን ምንነት ያልተረዱ ወይም እያወቁ ሆን ብለው በሚያሰራጩት ያልሆነ ወሬ ለቅራኔዎች ምክንያት ናቸው የሚል እምነት አለኝ። በዚህ የተነሳ በጋራ መቆም ሲገባን በቡድንና በቤተሰብ ተወስነን ሌላውን አግሎና በጐሪጥ አይቶ በአገራችን ጉዳይ ተከፋፍለን በማይረባ እኔ ባይነት በፖለቲካ አቋም ዙሪያ አንድ  መሆን ተስኖን  የሕዝባችን ስቃይ ሊራዘም ችሏል።

 

እውነት የምናወራው ሁሉ ቁምነገር ያዘለ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ለዘመናት ለጨቋኞች፤ ለዋሾዎች፤ ለጐጠኞች የተመቸ ዳውላ ባልሆን ነበር። ይህ ሲባል ግን  አንዳንድ ቆራጦች  ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ሲሉ መስዋዕት የከፈሉና ዛሬም ቢሆን ለዴሞክራሲና ለመልካም አስተዳደር ሲሉ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ የሉም ማለት አይቻልም።ይሁን እንጂ ለአገርና ለሕዝብ አሳቢዎች የሚደረግላቸው ማበረታታም ሆነ ፈለጋቸውን ለመከተል የድርጅቶችም ሆነ የማኅበሮች በጋራ አለመደራጀት ለጥረታቸው መሳካት እንቅፋት መሆኑ አልቀረም። ለዚህ ችግር የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ድክመት ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል። እኔም ስለአንድነት ድክመት ሳወራ ከወሬ ያለፈ ሥራ ምን ሠራሁ የሚለውን መቀበልና የተጠያቂነት ድርሻም ልወስድ እንደምችል አምናለሁ።

 

ከፍ ሲል ለማሳየት እንደሞከርኩት ሁሉም ኢትዮጵያዊ በባሕሪ አንድ አይሆንም። ነገር  ግን አንድ በሚያደርጉ ጉዳዮች ማለት ኢትዮጵያ በምትለው ሥም አንድ መሆን ይቻላል። ተለያይተንና ቡድን ፈጥረን በሥም ማኅበራችን፤ ድርጅታችን ብንል የሚፈይደው ነገር አይኖርም። ሰብአዊ መብትን በተመለከት በሚደረጉ ሰላማዊ ሰልፎች በሃሳብ ተለያይተን የሚደረጉ ሰልፎች ውጤት አልባ መሆናቸው አያጠያይቅም። ከዚህ በፊት በተለያዩ አጋጣሚዎች የታየውም  እንዲሁ ነው።

 

የማይካድና በሁላችን ያጠላብን የጐሳ ፖለቲካ ብዙዎቻችንን እንደወረርሽኝ የተስቦ በሽታ ከፋፍሎናል። ተጠቃሚና  ተጐጅ የማኅበረሰብ ክፍል እስካለ  ድረስ የፖለቲካ  ልዩነት መኖሩ  የሚጠበቅ ነው። ይሁን እንጂ  የመንግሥት ወይም የገዥው ተጠቃሚ ያልሆነው ክፍል ለምን ወደ አንድነት በመምጣት ተጠናክሮ በጋራ መቆም አልቻለም የሚለውን ጥይያቄ ሁሉም ሊያስብበትና  መፍትሄ ሊፈልግበት ይገባል። አንድ  ነገር መጥቀስ አስፈላጊ ነው። በስደት እየኖርን በሥም አገራችን ዳር ደንበሯ ተሸራረፈ ሕዝባችን ተጨቆነ፤ አማራና እርቶዶክስ አከርካሪው ተቆረጠ እየተባለ በተለያዩ የዜና  አውታሮች  ይደመጣል። በመሆኑም ተደራጅቶ በጋራ ቁሞ ለችግሩ መፍትሄ መፈለግ ሲገባ በሰለጠነ ዓለም የሚኖር  ስደተኛ  ከመፍትሄው  ይልቅ እሳት እየጫሩ እርስ በርስ መናቆር ምን ያህል ጐጅና አሳፋሪ እንደሆነ ሁሉም ሊያስብበት ይገባል።

 

እውነት ሳይሸራረፍ ይነገር ከተባለ በኮሚኒቲ፤ በስፖርት፤ በድርጅት፤ በክርስትና፤ በሰርግ  በሰላማዊ ሰልፍ ወዘተ ጐራ ለይተን ተከፋፍለን አንዱ የሰራውን ሌላው የሚንደው ከሆነ ጠላት ከሚሰራው ሥራ በምን ሊሻል ይችላል? በስደት አገር ሁሉም እንደ ችሎታውና እንደ ዝንባሌው ሰርቶ የሚያድርበት አገር መሆኑ አያጠያይቅም። ለምሳሌ የእውቀት ባለፀጋው፤ ነጋዴው ወዘተ ሁሉም እንደ ጥረቱ ያቅሙን ያገኛል። በዚህ ሁሉም ሊኮራበት ይገባል። ባንፃሩ ግን መልካምና ክቡር ባሕላችንን በመዘንጋት አንዳንዶቻችን በአልሆነ የመንፈስ ቅናት ተወጥረን እርስ በርሳችን ሥም መጠፋፋቱ ምን ያህል ለአንድነታችን ጠንቅ መሆኑ አልቀረም።

 

በስደት የምንኖር  ኢትዮጵያዊያን ቁጥራችን ብዙ  እንደሆነ ከዚህ በፊት ለማሳየት ተሞክሯል። እንዲሁም ሌሎች ከተለያየ ዓለም ተሰደው በተለያየ ክፍለዓለም የሚኖሩ ሰዎች በኮሚኒታቸውና  በእምነት ቤታቸው  አማካኝነት ተሰባስበውና ተደራጅተው ማንነታቸውን አስከብረው ሰርተው  የከበሩበት  አገር ነው። ለዚህ ምሳሌ በከፊል ቻይናዊያን፤ ግሪካዊያንንና ሌሎችንም የማኅበረሰብ ክፍሎች ዋቢ ማድረግ ይቻላል። ይኽ እሰየው አበጃችሁ በርቱ ተበራቱ ሊያሰኛቸው ይገባል። በዚህ ሁኔታ ብዙዎች ማንነታቸውንና አገራቸውን አስከብረዋል።

 

ከዚህ ላይ ግን አንድ ሊሰመርበት የሚገባ ነጥብ አለ። ሰደተኛ  በውጭ ቢሞላው  ቢደላው  ማን እንደ ሐገር እንዲሉ ብዙዎች ሥጋቸው በስደት አገር ቢሆንም ሕሊናቸው ግን  ከአገራቸው ጋር ነው። ብዙ  ኢትዮጵያዊያን በሰው አገር  ከመኖር ይልቅ በአገራቸው መኖርን የሚመርጡ እንዳሉ ሲናገሩ የሚደመጡ አሉ። እርግጥ ነው የአገራችን ሕዝብ ትብብርና ፍቅር ተመልሶ ለሚቃኝ የስደት ኑሮ እጅ እጅ ይላል። ነገር ግን ምኞታቸው እንዳይሳካ ፖለቲካው እሾህ አሚካላ እየሆነባቸው የሚሉትን በተግባር ለማሳየት እንደሚቸገሩ እርግጥ ነው።

 

የሰው ልጅ ሰደትን የሚመርጥበት ምክንያት ብዙ ነው። በጣሊያን ወረራ 1928 ዓ.ም ተመልሰን ስንቃኝ አጼ ኃ.ሥላሴ ከተወሰኑ ሰዎች ጋር ተሰደው ነበር። በዚህ ወቅት በስደት ወገናቸውን እንዳጡና ምንስ ጥቅም እንዳገኙ ተገንዝበዋል። ዛሬም እንደ ጥንቶች ለስደት ምክኒያት የሆነውን ታግሎ አስወግዶ አገሩን ለመግባት የግድ የተባበረ ትግል ይጠይቃል።

 

በሃያ ዓመት ውስጥ በዓለም የተበተነው ሕዝባችን ቁጥሩን በትክክል ለማስቀመጥ አስቸጋሪ እንደሚሆን አያጠያይቅም። የሰው ልጅ በሰው አገር ሲኖር የባሕሪ ለውጥ ብቻ ሳይሆን የአእምሮ ልሽቀትም ማስከተሉ አልቀረም። አንድ ሰው ከተወለደበት አገር ተለይቶ በሰው አገር ሲኖር እርስ በርስ መፈቃቀርና አንድነት እንደሚያስፈልግ ሁሉም የሚስማማበት ይመስለኛል። ነገር ግን “ሰው መጣ ነገር መጣ” እየሆነ ፍቅራችን እጅጉን ቀንሷል ቢባል ከሃቅ መውጣት አይመስለኝም።

 

ከላይ ለተጠቀሰው ማስረጃ በኮሚኒቲው ማኅበርም ሆነ በሌላ ስብሰባ ላይ እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል የተሳሳተ አካሄድ እንጠመዳለን። ውሳኔ ላይ ሳንደርስ የምንለያይበት አጋጣሚ ይስተዋላል። ወይም ላንስማማ ተስማምተናል በሚል ፈሊጥ የምንበተንበት አጋጣሚ ብዙ ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን ከአገራችንና ከሕዝባችን ተለይተን በስደት ስንኖር የደረሰብንን የአእምሮ ችግር ምን መሆኑ ተለይቶ ሊታወቅ ግድ ይላል። ለፍተን ጥረን በሰው አገር  የምናካብተው ንብረትም ሆነ የምቾት ኑሮ ሕይወታችን ወደ  ምቾት ኖሮ የተለወጠ ይምሰል እንጂ በብዙ ሁኔታ ተጐድተናል።

 

በተሰደድንበት አገር ባሕላችን አክብረን አንድነታችን አጠንክረን በማኅበራችን ተደራጅተን በፍቅርና በመተሳሰብ ለመኖር የብዙዎች ፍላጐት መሆኑ አይካድም። ይሁን እንጂ ዘመኑ በወለደው የጐሳ ፖለቲካ ምክንያት አንዳንዶች በሚፈጥሩት ልዩነት የርስ በርስ መጠላለፍ አለ። ነገር ግን የችግሩን መንስዔ ደፍሮ ለመናገር ይሉኝታ እየታከለበት ሊቀለበሱና ሊታጠፉ የሚችሉ ጥቃቅን ችግሮች በዝምታ ይታለፋሉ። በዚህ የተነሳ የአብሮነት የጋራ ኑሮ በራቸው  እየጠበበ፤ ክብራችንና ማንነታችን እየተደፈረ ባሕሪያችን የሚስማማ አልሆነም።

 

አንዱ የሰራው ጥሩ ሥራ ለሌላው እንደ መጥፎ እየታየ በሀሜት፤ በሽሙጥ ወገኑን ለማጥቃት በጓሮ የሚደረገው መጐሻሸም አሳፋሪ ነው። የዚህ ዓይነት ትግል መፈራራትና መተማመን እያጠፋ ሲሄድ አንድነትን ይጐዳል። ይህ ደግሞ ባለንበት አገርም ሆነ በሌሎች ማኅበረሰብ ዘንድ ማስናቅ ብቻ ሳይሆን ማስወቀሱ አይቀሬ ነው። እንደ ተገነዘብኩት ከሆነ በየጊዜው የመከፋፈል ችግሮች እየተከሰቱ ያሉት በድርጅቶች በኮሚኒቶች በእምነት ቤቶች በኩል ይመስለኛል። ለዚህ ችግር በዋናነት የመሪዎች ሲሆን እንዲሁ መሪዎች በተሳሳተ ጐዳነ ሲነጉዱና ክፍፍሉ እያየለ ሲመጣ በደጋፊነት ያሉትንም ዝምታ ይጨምራል። ከዚህ ውጭ ሰደተኛው በግራም በቀኝም እየተወዛወዘ የሚችለውን እያደረገ ነው። ችግሩ ግን ከላይ ነው።

 

ለማጠቃለል ያህል-መጀመሪያ ስለትብብር ስለድርጅት፤ ስለኮሚኒቲ፤ ስለእምነት ቤታችን አንድነት ወዘተ ከማውራታችን በፊት ሁላችን ሊጠቅምና ሊያስማማ በሚያስችል ሁኔታ ሰፋ  ያለ ውይይት ማድረግ ያሻል። ያ ነበር የተባለው አልፎ ካለፈው ተሞክሮ  በመነሳት ዘርን ሳይለይ የውይይት መድረክ የግድ አስፈላጊ ነው። ይህ የውይይት መድረክ እንዲህ በቀላሉ እንዳለፈው በይሁን ይሁን የሚዋቀር ከሆነ ፋይዳ ሊኖረው እንደማይችል ከዚህ በፊት የተጀመሩት ዋቢ ናቸው። ድርጅት የመሰረቱም ቢሆን በቡድንና በቤተሰብ ሳይወሰኑ የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ከሌሎች ጋር አዋድደው የጋራ ትግል ቢጀምሩ ሕዝቡ ሳይከፋፈል ኃይል ይሆናቸዋል። በቤተክርስቲያን በኩልም እንዲሁ ነው።

 

ስደተኛውን ለማስተባብርና ለማታገል የሚችሉ በሕዝብ ገንዘብ የተማሩ ሰዎች እንዳሉ ግልጽ ነው። ከራሳቸው ፍላጐት የማኅበረሰባቸውን ፍላጐት ማሟላት የሚችሉ፤ የዲፕሎማሲ ሥራ መሥራት የሚችሉ፤ የሚናገሩት በሕዝብ ሊደመጡ የሚችሉ ሰዎች ለትግሉም ሆነ ለአንድነቱ ማስፈለጉ እርግጥ ነው። እነዚህ አርቆ አሳቢዎች በቅንነትና በበጐ ጥረት እናደራጃለን ብለው ከተነሱ የተፈጠረውን ድክመት መልሶ  መገንባት ይቻላል። ለዚህ ቅን ተግባር ለሚነሱ ወገኖች ሁሉም ወገንተኝነት ሳያጠቃው ማኅበረሰቡ ቀና ድጋፍ ሰጥቶ ካበረታታቸው ለትግሉም ለተናጥልና ለማኅበራዊ ኑሮ እጅግ ተጠቃሚ ያደርገናል።

 

ነገር ግን አንዳንዶች በሰመ ድርጅትና ኮሚኒቲ ጥቅማጥቅም ፍለጋ ተመሳጥረው አባላትን እርስ በርስ አጣልተው  ብቻቸውን የሚፈልጉትን ከያዙ በኋላ እርስ በርስ በሚደረገው ሽኩቻ ትግሉ አሮጌን ዓመት በአዲስ መቁጠር ካልሆነ የሚፈይደው ነገር እንደማይኖር ከዚህ በፊት ታይቷል።

 

እኛ ኢትዮጵያዊያን በሰለጠነና ዴሞክራሲ በሰፈነበት አገር እየኖርን አንድ ሆነን መደራጀት ካልቻልንና የራሳችን አንድነት እየናድን በዚህ  በተበታተነ ኑሮ በአፍ ኢትዮጵያ የምንለው ሁሉ ከንቱና ብላሽ ይሆናል። በመሆኑም ትግሉን ማሳደግ ያልቻልንበት ምክኒያት ሊያሳስብና  ሊያስቆጭ ግድ ይላል።

 

አስተያየት ለመስጠት   Taklo.teshome@gmail.com

 

Go toTop