የአዲስ አበባ ተወላጆች ፖሊስ ለመሆን ፍላጎት የላቸውም የሚባለው ሐሰት ነው!

የአዲስ አበባ መስተዳድር የከተማዋን የፖሊስ ቁጥር ወደ 50,000/ሃምሳ ሺህ/ ለማሳደግ በያዘው እቅድ መሠረት፣ አብዛኛውን ፖሊስ ከኦሮሚያ ክልል ለመመልመል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የውስጥ አዋቂ ምንጮች በተለይ ለባልደራስ ጥቆማ ሰጥተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ተወላጆች በፖሊስ ሠራዊት ውስጥ እንዳይቀጠሩ ፍላጎት እንዳለም ተናግረዋል፡፡ ስለዚህም፣ በከተማዋ ውስጥ ጠንከር ያለ የምልመላ እንቅስቃሴ እንዳይከናወን ተደርጓል፡፡ ይህ አሰራር በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ በህወሓት ጊዜ የተጀመረና፣ ከህወሓት ውድቀት በኋላም የቀጠለ ነው፡፡ በከተማዋ የፖሊስ ሠራዊት ውስጥ የአዲስ አበባ ተወላጆች በጣም አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ሲሆኑ፣ ለዚህም የሚቀርበው ምክንያት የከተማዋ ተወላጆች በፖሊስነት ለመቀጠር ፍላጎት የላቸውም የሚል ነው፡፡
ይህ ግን ከእውነታ የራቀ መሆኑን፣ ለዚህም እንደ ማስረጃ የሚቀርበው የከተማዋ ተወላጆች አነስተኛ ክፍያ ባላቸው ስራዎች ላይ በብዛት ተሰማርተው የሚገኙ መሆናቸው ነው። ሁሉም የመንግሥት ስራዎች(ፖሊስን ጨምሮ) ደምወዛቸው አነስተኛ ቢሆንም፣ በመላው አገሪቷ በጣም ተፈላጊ እንደሆኑ ጥናቶች ማረጋገጣቸውን፣ ለዚህም በዋናነት ምክንያት የሆነው የመንግሥት ተቀጣሪ መሆን የስራ ዋስትና ያለው በመሆኑ እንደሆነ ምንጮቹ ይገልፃሉ፡፡
በፌደራልም ሆነ በከተማ መስተዳድር ደረጃ የፖሊስ ቅጥሩ በሁሉም ክልሎች እንዲደረግ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ተፈፃሚ እየሆነ ቢሆንም፣ ውስጥ ውስጡን ግን ለመንግሥት ታማኝ የሚሆኑ ፖሊሶች በዋናነት ሊገኙ የሚችሉት ከኦሮሚያ ክልል መሆኑን እምነት እንዳለና፣ በዚህ እምነት መሠረት ምልመላው የሚተገበር መሆኑንና፣ ከኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ጋር በመመሳጠር ምልመላው እየተደረገ መሆኑንም ምንጮቹ ይናገራሉ።
#መረጃ #ኢትዮጵያ
ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ