በፋኖ ላይ ጣት መጠቋቆሙ ለሃገር ጥቅምና አንድነት ታስቦ ሳይሆን የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ፍላጎት ከሟሟላት ላይ የተመሰረተ ነው፤ የፋኖ መኖር የማይስማማቸው አካላት ከኢትዮጵያ አንድነት በተቃራኒ የቆሙ ናቸው።
ለአላማቸው ይስማማ ዘንድ ተራ ሽፍትነትን ከፋኖ ጋር ሲያጋምዱት ይታያል።
ሽፍታና ፋኖ
ሽፍታ
ብዙውን ጊዜ የግለሰብ ተደፈርኩ ወይም ተናቅሁ በሚል ወይም ደም ለመመልስ ሰው ገድሎ ወደጫካ የሚገባ ወይም መንግስት የለም ብሎ ሲያምን ለዘረፋ የሚሰማራ ፣ በመሰረቱ በግል ጥቃትና እምነት/ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ከሌሎች ጋር የአላማ አንድነትና ሌሎችን ከጥቃት የመታደግ ሃሳብ የሌለው፣ ህዝብን ማጥቃት እንጂ ለህዝብ መቆም ባህሪው ያልሆነ በግልም በቡድንም አሸባሪ ነው። ለጥንቃቄም ሆነ ለዘረፋ ሲሉ በእርግጥ የተለያዩ ሽፍቶች ባንድ ላይ ይንቀሳቀሳሉ። ዋናው ነገር ሁሉም የየግል አላማ ያሰባሰበው መሆኑ ላይ ነው። ሽፍታ ሰርቶ አይበላም፣ ኑሮው ሌሎች ላባቸውን አንጠፍጥፈው ባፈሩት ሃብት ላይ የተመሰረተ ነው፣ ከዚያም አልፎ ብዙ ብልግኛወችን በሴቶች ላይ ማድረስ የተለመደ ነው። ባጭሩ ሽፍታ ዘራፊና የህዝብን ሰላም የሚነሳ የህዝብ ጠላት ነው። ሽፍታ አነገኔን ዘረፈ፣ አዋረደ ሲባል የገጠሪቱ ኢትዮጵያ የምታውቀው ታሪክ ነው።ሽፍታ የተለመደው በገጠሪቱ ኢትዮጵያ ቢሆንም በከተማም በተለይ የመንግስት ክንድ ሲዝል ተመሳሳይ ወንጀል የሚፈጽሙ የከተማ ወንበዴወችም አሉ።
ከሽፍታ በትርና ዘረፋ ለመዳን ጉልበትን ለማጠንከር ነጋዴ ከአንድ ቦታ ወደሌላ ሲንቀሳቀስ በአንድ ላይ ተጠራቅሞ ጉዞውን ይጀምር እንደነበር ይታወቃል። ህዝብ ላይ ምን ያህል ሰቆቃ ይፈጥር እንደነበረ መገመት አይከብድም። በአጭሩ ሽፍታ አሸባሪ ነው፣ ደግሞ ጉልበቱ የሚጠነክረው ጉልበት በሌለው ደሃ ህዝብ ላይ ነው።
ፋኖ>>>> በታሪካችን ፋኖ ሃገር ስትወረር፣ ማእከላዊ መንግስት ሲዳከም አካባቢውን ለማዳን የሚሰባሰብ የሃገር አለኝታ ነው። አላማውም ሆነ እንቅስቃሴው የወል/የጋራ ነው። ፋኖ መንግስት በተረጋጋበትም ጊዜ ገዥዎች በሚፈጥሩት ለከት የልሽ በደል መሪ የጎበዝ አለቃውን መርጦ ያምጻል። ከውጭ በመጣው ጠላትም ሆነ በገዥወች ለሚደርሰው በደል አላማው የጋራ ነጻነት ላይ ያተኮሮ የጋራ የትግል ጉዞ ነው የሚያልመው:: ፋኖ ከህዝቡ በፈቃደኝነት የሚሰጠውን ይበላል እንጅ ህዝብን አይዘርፍም ካላማው ውጭ ነውና። ከጣሊያን ጋር የተደረገው ጦርነትና ድል የፋኖዎች ቆራጥ የትግል ውጤት ነው። ፋኖ ስነምግባርና ዲሲፕሊን ያለው የህዝብ ልጅ ነው። በልብ ወለድ ታሪክ በአዲስ አለማየሁ ፍቅር እስከመቃብር ላይ ያለውን የህዝብ ጠበቃ አበጀ በለውን አይነት ነው ፋኖ ማለት።
የሽፍታና የፋኖ አንድነት ሁሉም ነፍጥ አንግበው በዳዮቻችወን(ሽፍታ ተበደልኩ ካለ ግለሰባዊ ነው) ለመፋለም መውጣታቸው ላይ ነው የሚያቆመው። የአላማ አንድነት ቀርቶ ተመሳሳይነይት የለም። አንዱ ይዘርፋል ሌላው ለህዝብ ተቆርቋሪ ሆኖ ይፋለማል። ሽፍታ ድሃውን ግብር ያስከፍላል፣አፍኖ ወስዶ በሰው ህይወት ላይ በገንዘብ ይደራደራል። ሳይሆን ሲቀርም ያለርህራሄ ነፍስ ያጠፋል። የፋኖ ስነምግባር ህዝብ ለመታደግ እንጂ የህዝብ ህይወት ለምቅሰፍ አይደለም። ፋኖ አላማ አለው ለሃገር ለወገን የመቆም፣ የሽፍታ አላማ ዘረፋና ሽብር ነው።
ሽፍታንና ፋኖን ለይቶ የማውቅና ወንጀለኛን መቅጣት የመንግስት ስራ ነው። በደፈናው ስንዴውን ከእንክርዳዱ እየደባለቁ እንወቃለን ማለት ግን የሃገር ጠላትነት ነው። ብዙወች ገንዘብ እየዘረፉ ለሽሽት በሚዘጋጁበት ፈታኝ ወቅት ፋኖ ነፍጥ አንግቦ ጠላትን ያርበደበደ ሃይል ነው። በፋኖ ስም የሚዘርፈው የሚገድለው ሽፍታ ነው። ይህ ቡድን በሚያደርጋቸው ድርጊቶች ሁሉ ከፋኖ ጋር ማቆራኘት ለህዝብ ያለን ንቀትኛ ጥላቻ የሚያሳይ ነው። ወያኔያውያንና ኦንጋውይን ፋኖን የማጥፋት ጽኑ ፍላጎታቸው እንድሆነ አያጠያይቅም፤ ግራ የሚያጋባው ግን በአማራው አስተዳደር ውስጥ ያሉ ተግዥወች የያዙን ልቀቁን ዳንኪራ ነው።
ዛሬ በኢትዮጵያ ያለውን የፋኖ ጉዳይ በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። ብዙዎች ለሃገራቸው አንድነት ከመንግስት ባለስልጣናት በተሻለ ተዋድቀዋል። ይህን ደርቅ ሃቅ ወደ ጎን ማድረግ ፍትሃዊም አይደለም ሃገርንም አይጠቅምም። የኦነግን ፍላጎት ለማርካት ደማቸውን ባፈሰሱ ጀግኖች ላይ መዶለት ሃገር ለማፍረስ ከቆረጠው የትግሬ ወራሪና ጋሻጃግሬዎቻችው ጋር አንሶላ መጋፈፍ ነው።
በፋኖ ስም ችግር አልተፈጠረም አይደለም፤ ቁም ነገሩ የደቦ ውግዘቱንና ጥቃቱን አቁሞ ማን ፈጠረው ብሎ ጥፋተኛውን ለፍርድ ማቅረብ ነው። ይህ ደግሞ የመንግስት በተለይ የአማራው መንግስት ሃላፊነት ነው። ትዕዛዝ እየተቀበሉ ወደ ታች ማውረድ ብቻ እይደለም የዚህ መንግስት ሃላፊነት፤ ማጣራትንና ህዝብን መታደግም ስራው ነው ፋኖንም ጭምር።
ፋኖ ድሮም የነበረ ዛሬም ያለ ነገም የሚኖር ነው። ይህን ሃቅ ከመጋፋት ይልቅ አስመሳዩን ከውነተኛው የሚለይ ሃቀኛ መንግስት እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው።