“ተገድጀ ነው” የአቶ ደመቀ ነገር!!! – ወንድይራድ ኃይለገብርኤል

ክቡር አቶ ደመቀ ከ 12ኛው የአዴፓ ጉባዔ ጀምሮ፡ ጉባዔ አልፎ ጉባዔ በመጣ ቁጥር በተደጋጋሚ ጊዜ የሚለቋት “ተገድጀ ነው” የተሰኘች ነጠላ ዜማ አለቻቸው።

ይችኑ ነጠላ ዜማ በትናትናው ዕለት ቅላፄዋን ሚክስ አድርገው ዳግም ዘፍነዋታል።

“አብይ ነቅነቅ ማለት የለም ብሎ አስገድዶኝ እንጅ እኔስ እባካችሁን አሰናብቱኝ ብየ ተማፅኘ ነበር” ብለውናል አቶ ደመቀ።

ክቡር አቶ ደመቀ ሆይ ያለ ፍላጎተዎ የውስጥ ተነሳሽነት ሳይኖረዎ በግድ በተጫነበዎ ስልጣን ለዘርፈ ብዙ የህልውና ችግር የተዳረገውን የአማራን ህዝብ እንዴትስ አድርገው ይታደጉት ይሆን?

ካስገደደዎም ህዝበዎ ላይ የተጋረጠው መጠነ ሰፊ የህልውና ችግር ሊያስገድደዎ ይገባ ነበር። ያ ግን አልሆነም። “አስገደደኝ” ያሉን በአማራ ህዝብ ላይ የደረሰው/እየደረሰ ያለው አሰቃቂ እልቂት ሳይሆን ክቡር ጠ/ሚሩን ነው።

ያገኟትን ድምፅ የሰጡዎም የሌሎች ብሔር/ብሔረሰባት ብልፅግና ጉባዔተኞች እንጅ አማሮቹ እንዳልሆነ ውስጥ አዋቂ ነን የሚሉ ወገኖች መረጃ እየሰጡ ነው። እርሰዎ በሚመሩት የአማራ ብልፅግና ፓርቲ 222 ባለሙሉ ድምፅ ጉባዔተኞች ሳይመረጡ ከማን ጋር ሊሰሩ ነው? ማንንስ ሊመሩ ነው?

አሳሳቢ ነው!

ትንፋሽ ወስደው፡ አደብ ገዝተው፡ ግራ ቀኙን አማትረው፡ አልመው፡ አነጣጥረው ውሳኔ ሊሰጡበት የተገባ ብርቱ ጉዳይ ገጥሞወታል ጌታየ። ቢችሉ ከራሰዎ ጋር ካልሆነም “አስገድዶ በግፍ ሾመኝ” ከሚሉት አካል ጋር ይምከሩበትና ለዕርሰዎም በተለይም ደግሞ ለህዝባችን የሚበጀውን ውሳኔ ቢያሳልፉ መልካም ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ያልተጠናቀቁ የኮንዶሚኒዬም ቤቶች ነዋሪዎችን አማረሩ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share