March 6, 2022
42 mins read

ብልጽግና እና ስርዓታዊ ሽብርተኝነት-ገለታው ዘለቀ

Abiyfበዚህ ምጥንና በጣም ቁጥብ በሆነ ጽሁፍ ውስጥ  በተለይ መንግስትን የተቆጣጠረውን  ብልጽግናን የሚመለከት ሃሳብ አካፍላለሁ። የዚህ ሃሳብ አላማ  ብልጽግና  ፓርቲ የመንግስትን ስልጣን  የተቆጠጠረ ስለሆነና የሃገራችን ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢነቱ እየጨመረ በመምጣቱ ነው ይህንን ሃሳብ የውይይት መነሻ እንዲሆን ለማንሳት ያስገደደኝ።  በመሆኑም አላማው ለውይይት የሚሆኑ ሃሳቦችን ማጫር ሆኖ በተለይ ብልጽግና ከውስጥ ወደ ውስጥ ራሱን በሚገባ እንዲያይ ራሱን እንዲያውቅ ጥያቄ  ለማጫር፣  ህዝቡም  ይህንን ፓርቲና የሃገራችንን  መዋቅራዊ  እንቅፋቶች  የበለጠ  እንዲረዳ ነው።

መቼስ አንድ ስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ  በጎ ሲሰራ ሃገር ያተርፋል፣ ሲያበላሽ ደግሞ ሃገር ይጎዳል።  የያዘው አቅጣጫ ሃይ ሊባል የሚገባው ከሆነ ዜጎች ሁሉ  ሃይ ካላሉት ሃገርን ገደል ሊከት ይችላል።  ስለዚህ እኔም እንደዜጋ  ይህንን ፓርቲ ለመተቸት የተነሳሁት  ሁኔታውና  ጉዞው ስላሳሰበኝ ነው። አድረን በጎ ነገር መስማት ስለጠፋ ነው።  እስቲ ወደ ነጥቦቼ ልመለስና  የሚከተሉትን  እያነሳን እንወያይ።

ብልጽግና ምን ላይ የቆመ ፓርቲ ነው?

የቅርብ ጌዜ ታሪክ  እንደሆነው  ብልጽግና ተፈልፍሎ የወጣው  ከራሱ ከኢህአዴግ  ስብስብ ውስጥ ነው። ብልጽግና የሚለው ስያሜ አዲስ ቢሆንም የፓርቲው መሪዎችና አባላት ግን ቀደም ባለው  ጊዜ በኢሃዴግ ውስጥ የነበሩ መሪዎች ናቸው።  እነዚህ መሪዎች የአስተሳሰብ ለውጥ ውስጥ ገብተናል ቀደም ያለው አካሄድ አደገኛ ነው ነበር ያሉት። ህወሃትን በተለይ ራስ ወዳድና አብሮ ለመስራት፣ ለእኩልነት የማይመች የለውጥ አሜኬላ ነው ብለውት ነበር።

ከህወሃት ጋር ያለውን ግንኙነት ተወት አድርጌ ይህ ፓርቲ ታዲያ ለውጥ ታይቶኛል ሲል ከየት ወዴት ነው መለወጥ የፈለከው? ለሚለው መዋቅራዊ ጉዳዮች ግልጽ የሆነ ሮድማፕ አላሳየም። ከሁሉ በላይ ግን ብልጽግና ራሱን በሚገባ ያውቃል ወይ? ተክለሰውነቱን ተረድቶታል ወይ? ፓርቲው ምን ላይ እንደቆመ ተረድቱዋል ወይ? የታየው ራእይ አለ ወይ? የኢትዮጵያ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ለውጦች ገብተውታል ወይ? በሚለው ላይ መወያየት መልካም ነው።

ብልጽግና አንድ ተቃዋሚ ፓርቲ ቢሆን ይህንን አላነሳም ነበር። ነገር ግን ይህ ፓርቲ ገዢ ስለሆነ ለመተቸት ተገደድኩ።

እንግዲህ ብልጽግና ውህደት ያደረኩ አንድ ሃገራዊ ፓርቲ ነኝ ያላል። መቼስ በመርህ ደረጃ ውህደትን ሁላችን እንደግፋለን። ነገር ግን ይህ ፓርቲ በሚከተሉት መዋቅራዊ ችግሮች ላይ የወደቀ መሆኑን ማወቅ አለብን ። ፓርቲው ራሱን ሲመረምር የሚከተሉትን ልብ ማለት አለበት

  1. ፓርቲው ህገ መንግስታዊ አለመሆኑን
  2. ፓርቲውንየሚሸከም የፌደራል ስርዐት አለመኖሩን
  3. ፓርቲውን የሚሸከም ቅርጸ መንግስት (Government structure) አለመኖሩን
  4. ፓርቲውየጠራ ራእይ የሌለው መሆኑን

እነዚህን ከፍ ሲል ያነሳሁዋቸውን ነጥቦች ዝቅ ሲል እንወያይባቸው

  1. ብልጽግናህገ መንግስታዊ ፓርቲ አይደለም

መቼም ፓርቲው ህገ መንግስታዊ አይደለም ሲባል ምን ማለት ነው የሚል ጥያቄ ፈጥኖ ይነሳል። እውነት ነው አስደንጋጭ ነገር ነው። ፓርቲው ህገ መንግስታዊ ኣይደለም የሚያስብለን እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ህገ መንግስት የሰዎችን የመደራጀት መብት ቢፈቅድም የህገ መንግስቱ ስሪት ግን የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቃል ኪዳን ሰነድ ነው። ኢትዮጵያን እንደ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ (indivisible political union ) የማያይ ህገ መንግስት ነው። የዚህ ህገ መንግስት ዋና ምሰሶና ዶክትሪን ብሄሮች ሁሉ በየራሳቸው የፖለቲካ ምህዋር ላይ ዘዋሪ ናቸው የሚል ነው። ይሄ ጉዳይ ደግሞ ዋና ዶክትሪን ነው። ህገ መንግስቱ የተቀረጸው በዚህ መንፈስ ላይ ነው። ህገ መንግስቱ ኢትዮጵያን የሚረዳት የተለያዩ ብሄሮች የፖለቲካ ኮሚኒቲ ሆነው በተወሰኑ የፌደራል ተቁዋማት በጋራ ይተዳደራሉ በሚል መነጽር ውስጥ ነው። ይህ ህገ መንግስት ኢትዮጵያን እንደ አንድ የፖለቲካ ኮሚዩኒቲ ወይም ማህበር ኣይተው የሚደራጁ ፓርቲዎችን የሚያውቅ አይደለም። በርግጥ ይህ ጉዳይ ለብልጽግና ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ነን ለሚሉ ፓርቲዎች ሁሉ ህገ መንግስታዊ መንፈሱ አይቀበላቸውም። በርግጥ በኣንድነት ላይ የተደራጁት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የመንግስትን ማሽነሪዎች የማዘዝ ስልጣን ስለሌላቸው ምንም ተጽእኖ ሳይኖራቸው እየተቃወሙ ይኖራሉ። ነገር ግን አንድ የፖለቲካ ኮምዩኒቲ የሆነ ፓርቲ የመንግስትን ማሽነሪ ለመረከብ ቢሞክር ግን ግጭቶች ይፈጠራሉ። ለዚህ ነው ኣሁን ብልጽግና ሲዋሃድ ህገ መንግስታዊ ግጭቶች የሚነሱት። ህገ መንግስቱ በብሄር ብሄርሰብ ቃል ኪዳን ላይ የተመሰረተች አገር ናት እያለ የለም በዜግነት ላይ ተደራጅቼ ነው የምመራው ያለ ፓርቲ ሲመጣ መጀመሪያ የሚላተመው ከህገ መንግስት ጋር ነው። ህገ መንግስቱ ዜጎችን የሚያውቀው በብሄራቸው መለያ ከመጡ በሁዋላ ነው። የብሄር ማንነት ያልተለጠፈበትን ሰው ህገ መንግስቱ ማየት አይችልም።  በህገ መንግስቱ ፊት ሞገስ ያለው ማንነት ሲሆን ዜግነት ማንነት ሲጠየቅ  በሚሰጠው እውቅና የሚገኝ ሁለተኛ ጉዳይ ነው። ስለዚህ አንድ ፓርቲ ተዋሃድኩ ካለ ከዚህ ከህገ መንግስቱ መንፈስ ጋር ይጋጭና ስራው ሁሉ ይደናቀፋል።  የብልጽግና አንድ ዋና ችግር ይሄ ነው። ብልጽግና ከህገ መንግስት ማሻሻል ቀድሞ ተዋሃድኩ ሲል ሊመጣ የሚችለው ችግር ይህ ነበር። የብሄር ፖለቲካ በጋራ ቃል ኪዳን ሳይፈርስ ህዝብን ለማስደሰት ብቻ ብልጽግና ተብያለሁ ተዋሃድኩ ቢልም ቀጥሎ ህገ መንግስቱ ከፍተኛ ደንቃራ ይሆናል። የፓርቲው ውህደት ሃቀኛ ነው አይደለም የሚለውን እንተወውና ከተዋሃደ ፓርቲ የሚጠበቅን ነገር ለማድረግ የህገ መንግስት አሜኬላዎች የበዙበት ፓርቲ መሆኑን መገመት ተገቢ ነበር። በአንድ ሃገር ላይ እንዲህ አይነት የፖለቲካ ለውጥ (radical change) ሲደረግ ህጋዊ ጉዳዮች መታየት ነበረባቸው።

  1. ብልጽግናየሚሸከመው የፌደራል ስርዓት የለም

ይህ ፓርቲ ኢሃዴግ በነበረበት ዘመን ሁሉም የክልል ፓርቲዎች በየክልላቸው አስተዳዳሪ ይሆናሉ ደግሞ በጋራ ኢሃዴግ ሆነን እንኖራለን የሚል ትምህርት ነበረው። ይህ በራሱ ግልጽ አልነበረም። የሆነ ሆኖ ኢ ህ አ ዴ ግ በብዙ ተቃውሞ ተሰንጎ ሲያዝ ከዚያው ፓርቲ ውስጥ ውህደት ያስፈልጋል አንድ ሃገራዊ ብሄራዊ ፓርቲ መሆን አለብን ያሉ አባላት ብልጽግና የተሰኘ ፓርቲ ፈጠሩ። ብልጽግና ተዋሃድኩ ሲል ግን ይህ ውህደት በመዋቅር በፌደራል ስርዓቱ የተደገፈ ስላልሆነ እዚህ ጋር ሁላችንም ተዋህደን ኣንድ ብልጽግና የሚባል ሃገራዊ ፓርቲ ፈጥረናል ይሉና ወደየክልላቸው ሲሄዱ የኦሮሞ ብልጽግና፣ የጋምቤላ ብልጽግና፣ የኣማራ ብልጽግና ወዘተ እያሉ በየቤታቸው ያድራሉ። ይህ ግጭት የመጣው ፓርቲው ተዋህጄ አንድ ፓርቲ ሆኛለሁ ቢልም በተግባር ስራውን ሊሰራ ሲነሳ ወደ አልተዋሃዱ እስከ መገንጠል ስልጣን ወደተሰጣቸው ክልሎቹ ስለሚሮጥ ነው። ይህ ግጭት በአንድነት ፍላጎትና መሬት ላይ ባለ የፌደራል ስርዐት መካከል የሚፈጠር የመዋቅር ግጭት ነው። አንዱ የሃገራችን ችግር የኣንድነት ሃይል የሆነ ፓርቲ በዚህ የፌደራል ስርዓት ውስጥ የመንግስትን ስልጣን ይዞ ለመስራት የሚያስችል ስርዓት (Administrative ground) የለውም። ብልጽግና የገጠመው ኣንዱ መሰረታዊ ግጭት ይሄ ነው። አንድ ጊዜ ሃገራዊ ፓርቲ ነኝ ይልና ወደየብሄሩ ሲሄድ ደግሞ በብልጽግና ላይ የብሄሩን ስም ይቀጥልና ይለያያል። ብልጽግና የሚለው ስም ወደየብሄሩ ክልል ሲሄድ ዋና ስያሜ መሆኑ ቀርቶ ቅጽል ስም ይሆናል።  ይህ ግጭት ፓርቲውን የሚጎዳ ከመሆኑም በላይ በቋፍ ለሆነችው ሃገር ደግሞ ትልቅ ችግር ጠማቂ ጉዳይ ሆኖብናል። ተዋህዶ ነበር የተባለው ፓርቲ በየክልሉ የብሄሩን ጥግ ይዞ የሚጋጩ መግለጫዎችን እያወጣ እርስ በርስ እስከ መንጓጠጥ ሲሄድ ይታያል። ይህ ችግር የመጣው ይህ ፓርቲ የሚሸከመው የፌደራል ስርዓት ላይ አይደለምና ነው። መቀመጫውን ሳይዘረጋ ውህደቱን በህገ መንግስት ሳያውጅ በራሱ የተዋሃደ ፓርቲ ስለሆነ በተግባር ይህ ችግር ገጥሞታል። የዚህ ችግር ቀጥተኛ የሆኑና ቀጥተኛ ያልሆኑ ተጽእኖዎች መዘዛቸው ብዙ ነው። ለውጥ ከማደናቀፍ አልፈው አዳዲስ ችግሮችን በማምረት ችግሮችን እያባባሱ ይሄዳሉ።

  1. ብልጽግናየሚሰራበት ቅርጸ መንግስት የለውም

የኢትዮጵያ ቅርጸ መንግስት የተመሰረተው በህገ መንግስቱ መሰረት ነው። ኢትዮጵያ የብሄሮች ጥርቅም ብቻ አድርጎ የሚያያት ህገ መንግስት የብሄሮች ስምምነት ውጤት ናት በሚለው ሃሳብ መሰረት የፌደሬሽን ምክር ቤት አለው። ይህ ቤት ከየብሄሩ የተውጣጡ ኣባላት የሚቀመጡበት ቤት ነው። ይህ ቤት የዜጎች ቤት ሳይሆን የብሄሮች ቤት ነው። በዜጎች ሳይሆን በብሄሮች የፖለቲካ ውክልና የሚዋቀር ቤት ነው። ተቋማት ሁሉ ሃገሪቱን አንድ የፖለቲካ ማህበር አድርገው የሚያሰሩ አይደሉም። ተወካዮች ምክር ቤት፣ ፍርድ ቤቶች፣ ፖሊስ፣ አጠቃላይ የመንግስት ማሺነሪዎች ሁሉ ለብሄር የተሰጡ የብሄር ተቋማት ናቸው። የኦሮምያ ፖሊስ፣ ባንክ፣ ፍርድ ቤት እንዳለ ሁሉ ብሄሮች ሁሉ ቅርጸ መንግስታቸው እንደዚህ የሚነበብ ነው። እንግዲህ  አንድ ፓርቲ ተዋህጃለሁ ብሄራዊ ፓርቲ ወጣኝ ካለ በሁዋላ ተመልሶ እነዚህን ማሽነሪዎች የሚነዳ ሲሆን የሚፈጠረውን ጥያቄና ግጭት መገመት ቀላል ነው። ይህ መዋቅራዊ ግጭት የቅርጸ መንግስት ግጭት እንለዋለን።  በኣንድ በኩል አንድ የፖለቲካ ማህበር ነን የሚል ፓርቲ በሌላ በኩል በተግባር ደግሞ የብሄር ተቋማትን የሚመራ ሲሆን እንደ ሃገር ከባድ ግጭት ይፈጠራል። ግራ መጋባትና የኣሰራር ትርምስ በሃገሪቱ ውስጥ ይፈጥራል። አንዱ የኢትዮጵያ ችግር በዚህ ቅርጸ መንግስት የኣንድነት ሃይሉ ሀገር ለመምራት የሚያስችል ሆኖ አለመፈጠሩ ነው። በአጠቃላይ የሰራነው ቤት ለውሁድ ፓርቲ መፈናፈኛ የለውም ብቻ ሳይሆን ውህድ ፓርቲን ጠልፎ የሚጥል ቅርጸ መንግስት ነው። ብልጽግና የተጣደው እዚህ ላይ ነው።

  1. ብልጽግና የጠራ ርእዮት የለውም

በኢትዮጵያ የፓርቲዎች ታሪክ ውስጥ በርእዮት ደረጃ እንደ ብልጽግና ግራ ተጋብቶ አለምን ሁሉ ግራ ያጋባ ፓርቲ አለ ብየ አላምንም። ርእዮት የኣንድ ፓርቲ ውሳኔ ነው። አቅጣጫውን የወሰነ፣ ዋጋውን ተምኖ የወጣ ፓርቲ ነው ሃገር መምራት ያለበት። በጠራ አቋም የሚጠፋ ጥፋት ይሻላል ባልጠራ አቋም ከሚጠፋ ጥፋት። ከጥፋት ለመማርም የሚያስችለው ኣቋማችን ግልጽ ሲሆን ነው። ብልጽግና አላማየ ሃገሪቱን የበለጸገች ማድረግ ነው ይላል። ለመሆኑ ለዚህ ያልቆመ ፓርቲ ማን አለ? ሁሉም ፓርቲ ለሁለንተናዊ ብልጽግና ነው የሚሰራው። ዋናው ጉዳይ በየሴክተሩ ፖሊሲዎችን ኣውጥቶ ለዚያ መስራት ነው የሚሻለው። ብልጽግና አልፎ ኣልፎ መደመር ነው ራእያችን ይላል። ይሄ በውነት እንደ ሃገር ኣሳሳቢ ነው። በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ ዋና  ተፈላጊ ነገር አንድ ደማሪ ኖሮ ሌላው እየዘለለ እንዲደመር ሳይሆን እርስ በርስ ስልጣን፣ ሃሳብ በመካፈል በመቻቻል የምንኖርበት ስርዓት ነው። መደመር ሄዶ ሄዶ አውራ ፓርቲን ለማፋፋት በር የሚከፍት ልዩነትን ፈጠራን ኢኖቬሽንን የሚያቀጭጭ ነው። ደግሞም ኣንድን ህዝብ ማስተማር ያለብን መደመር ሳይሆን ማካፈልን ነው። መደመር በህይወት ውስጥ ቀላሉና የታችኛው የህሊናችን ክፍል (ego) የሚሰላና የሚገዛ ነው። ከባዱና ሱፐር ኢጎን የሚጠይቀው ለሰፊው ማህበራችን የሚያስፈልገው ትምህርት ማካፈል (sharing) ነው። ይህ የማካፈል ሃሳብ በተለያዩ ፖሊሲዎች ሊገለጽ ይገባል እንጂ መደመር ለኣንድ ፓርቲ ርእዮት ሊሆን ኣይችልም። መደመር ማካፈልን ዋና ጉዳዩ አድርጎ ካልያዘ በራሱ አጥፊ ነው። ብልጽግና ኣንዴ ለዴሞክራሲና ለለውጥ ተነስቼ ያለሁ ፓርቲ ነኝ ሲል በሌላ በኩል ደግሞ መደመር ነው መንገዴ ካለ ወደሚፈለገው ብልጽግና ኣይወስድም። ከሁሉ በላይ መደመር የሚፈጥረው የፌደራል ስርዓት ምን ኣይነት ነው? መደመር የሚፈጥረው ቅርጸ መንግስት ምንድን ነው? መደመር በባህልና ቋንቋ ፖሊሲ አንዴት ይገለጻል? የሚለው ጉዳይ ምንም ኣይታወቅም። ይህ የሚያሳየው ይህ ሃስብ ተዘርዝሮ ፖሊሲ የሚወጣው እንዳልሆነ ነው። ይህንን ርእዮት አድርጌ ነው ሃገር የምመራው ያለ ፓርቲ ይህቺን ሃገር ገደል እንዳይከታት ሃይ መባል አለበት። ራሱን ተክለ ሰውነቱን የቆመበትን መሰረት በትክክል ማወቅ አለበት።

ሌላው የብልጽግና የህዝብ ግ ንኙነት ጉዳይ ነው። እንደማየው ቅስቀሳዎቹ የኔ ነው በልና ተቀበል (name it and claim it) የሚባለውን ትምህርት ይከተላል። ይሄ እንደ ሃገር አደጋ ነው። አንድ አነቃቂ (motivational speaker) ቢናገረው ችግር የለም። መልካምም ይሆናል። ነገር ግን መንግስት ህዝብ በስንት መከራ ላይ እያለ በዚህ ትምህርት ማማለል በጣም ስህተት ነው። መንግስት የዛሬውን ችግር እየፈታ ለወደፊቱ እያቀደ መምራት ነው ያለበት። መልካም ነገር መናገር መልካም ነው። ይሁን እንጂ እዚህ ህዝብ እያለቀ እየተፈናቀለ እኛ የድግስ ፓርቲ እያደረግን መደነስ የለብንም። በአስራ ዘጠኝ ስልሳዎቹ ህዝቡን በጣም ያበሳጨው ነገር የወሎ ህዝብ ረሃብ ላይ እያለ ንጉሱ ኬክ ከውጪ አምጥተው ይመጻደቃሉ የሚል ነበር። ፈረንሳይ ውስጥም ተመሳሳይ ተቃውሞ ነበር። የህዝብን ብሶትና ነባራዊ ኖሩ እያቀለሉ ላም አለኝ በሰማይ አይነት ንግግር የተጎዳውን ስሜት ይጎዳል። ብልጽግናን በሃይል የተጣባው ጉዳይ ነው። ይህ ለለውጥ አደጋ ነው።  ስለዚህ ስለጠራ ራእይ ሳነሳ የፓርቲው መሪዎች ዋና ዋና በሚባሉ ጉዳዮች ላይ በህገ መንግስቱ ላይ ሳይቀር የተደበላለቀ ነገር ሲናገሩ ይደመጣል። በጠራ ራእይ ስር እንዳልተሰባሰቡ ያሳያል። ይሄ በጣም ያሳስባል።

እንደ ማጠቃለያና  እንደ መፍትሄ

የብልጽግናን ተክለ ሰውነትና የቆመበትን መሰረት ስናይ በዚህ ደረጃ አደገኛ ግጭቶችን ይዞ የሚሄድ አስገራሚ ፓርቲ ስለሆነ ከፍተኛ ስርዓታዊ ሽብርን (systemic violence) እያመረተ ያለ ፓርቲ ሆኑዋል። የምናያቸው ግጭቶች፣ መፈናቀሎችና ግራ መጋባቶች የሚያያዙት ይህ ፓርቲ ካለበት የፖለቲካ ቁርጠኝነት (political commitment ) ችግር በላይ መዋቅራዊ ወጥመዶች ውስጥ ስለገባ ነው ቀውሶች የበዙት። የሰአባዊ መብት ጥሰቶችና ሌሎች ችግሮችን ሁሉ ሳላነሳ መዋቅራዊ ችግሮቹን ብቻ ያነሳሁት አብዛኛው ችግር ከዚህ ከመዋቅር ግጭቶች የሚመነጭ ስለሆነ ነው።

እንደምናየው የብልጽግና በዚህ መዋቅራዊ ችግሮች መካከል መጣድና መዋል ማደር ዋና ዋና ምክንያቶቹ ሁለት ናቸው። አንደኛው ከፈረሱ ጋሪው መቅደሙ ነው። አንድ ፓርቲ በተለይም የፖለቲካ ስልጣን የያዘ ፓርቲ ውህደት ሲያስብ መጀመሪያ ማሰብ ያለበት ተዋህጄ የምቀመጥበት ቅርጸ መንግስት አለኝ ወይ? ህገ መንግስታዊ ነኝ ወይ? የፌደራል ስርዐቱ ይህንን ውህደቴን እንዴት ያስተናግደዋል? የጠራ የጋራ ራእይ አለኝ ወይ ? የሚሉትን ከባድ ጥያቄዎች መመልከት ነበረበት ። እነዚህ ሁኔታዎች መሬት ላይ ሳይኖሩ አብዛኛው ህዝብ ይደሰታል፣ ይከተለናል በሚል ብቻ ተዋህጃለሁ ማለት በማግስቱ የምናየውን ግጭት አምርቶብናል። የዚህ ፓርቲ ችግር መዘዝ ሁላችንን ሃገራችንን ይጎዳል። ብልጽግና የሚሸከመውን መዋቅር ሳይዘረጋ የተፈጠረ ፓርቲ ነው። ቀደም ብሎ ህገ መንግስት ማሻሻል፣ የፌደራል ስርዐት ማስተካከል ወዘተ ስራዎችን ሰርቶ በህገ መንግስት ኢትዮጵያ አንድ የፖለቲካ ኮምዩኒቲ ሆናለች የሚል እንቀጽ አስገብቶ ውህደቱ ቢከተል ውህደት ይሳለጥ ነበር ደግሞም ይህ ሁሉ መዋቅራዊ ግጭት አይኖርም ነበር።

ሁለተኛው የዚህ ፓርቲ ችግር ደግሞ የፍጥነት ችግር ነው። መልካም ይህ ፓርቲ የሚቀመጥበት ስርዐት ሳይኖረው በችኮላ ተዋሃደ እንበል። የሚያሳዝነው ከተዋሃደ በሁዋላ በፍጥነት ወደ መዋቅራዊ ለውጥ ለመግባት አዝጋሚ መሆኑ ነው።  የሚያሰራ መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ውሎ ማደር አያስፈልግም ነበር። በጣም የዘገየ ስለሆነ ለውጡ እየቸከ እየቸከ  እየቸከ ፓርቲውን ራሱን ስርዐቱ እየጠለፈው እንዲሄድ አድርጎታል። በዚህም የዚህ ፓርቲ ቅቡልነት መሬት ላይ ነው ዘጭ ያለው። በለውጥ ውስጥ ፍጥነት በጣም ወሳኝ ነገር ነው። ብዙ ለውጦች የሚመክኑት ከፍጥነት ማነስ የተነሳ ነው ይላሉ ባለሙያዎች ። ፍጥነት ስንል መጣደፍ ሳይሆን ፍጥነት ያስፈልጋል ለማለት ነው። ይህ ሳይሆን አራት አመት ቆየንና ይህ ፓርቲ በየጊዜው ችግር ውስጥ ሲወድቅ ለሃገር ስጋት መሆኑን እየጨመረ ቀጥሏል፡፡

በሌላ በኩል ይህ ፓርቲ ውህደ የፈጸመው ስልጣን ላይ እያለ መሆኑ በጣም ያስደነግጣል። መቸም ይህቺ ሃገር ያልተሸከመችው ጉድ የለም እንጂ ስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ እንደ ፈለገ መዋሃድ፣ መፈረካከስ፣ አዲስ ፓርቲ መሆን የማይገባ አደገኛ ነገር ነው። ከህዝብ ላይ መፍረስ መቅለጥ አይቻልም። ፓርቲዎች ይህንን ጣጣ ስልጣን ላይ ሳይወጡ በፊት በጉዋዳቸው ጨርሰው ነው ወደ ስልጣን የሚመጡት ። ምርጫ ቦርድም ይህንን መከታተል ነበረበት ።

እንግዲህ ችግሮችን ካነሳን ዘንዳ አሁን ምን ይሻላል የሚል ጥያቄ ይነሳል። አሁን የሚሻለው ነገር በፍጥነት ወደ ሃገራዊ ምክክር መግባትና መዋቅራዊ ለውጦችን በፍጥነት ማምጣት ነው። የሚመጣውን ከእስካሁኑ የከፋውን ክፉ ነገር እናስቀር ዘንድ ፍጥነትን ከማስተዋል ጋር አያይዘን መራመድ ያስፈልጋል፡፡  ለዚህ ምክክር ደግሞ የሁሉንም ተሳትፎ ማግኘት የግድ ነው። ብሄራዊ ምክክር እንደሚያስፈልግ ሁሉም ያምናል። ነገር ግን በኮሚሽኑ አመሰራረት ላይ  ፓርቲዎች ቅሬታ ሲያሰሙ ይታያል። እኔ እንደሚገባኝ እውነት አላቸው። አመሰራረቱ ትክክልነት ይጎድለዋል። የምክክር ኮሚሽን እንደመሆኑ ፓርቲዎች ንቁ ተሳታፊ መሆን ነበረባቸው። ለፖለቲካው ቅርብ የሆኑና የኢትዮጵያን ማህበረ ፖለቲካ ያጠኑ መሆን አለባቸው። የፓርቲዎች ውክልናም ያስፈልጋል። ፓርቲዎች ቁጭ ብለው ተሳታፊ ሳይሆኑ ዋና ተዋናይ ናቸውና ኮሚሽኑ ይህንንም ማገናዘብ አለበት። በፍጥነት በሚመለሱ የመዋቅር ለውጦች ላይ አተኩረን በሚያድግ ዴሞክራሲና በካሳ የሚመለሱ ጥያቄዎችን በጊዜ እንፈታቸዋለን። ይህ ሲሆን በጠራ ሁኔታ ይህንን የለውጥ ችግር መቅረፍ እንችላለን።

ከዚህ በፊት የምክክሩ ዋና አጀንዳ ቢሆኑ ያልኩዋቸውን ነጥቦች አንስቼ አጠቃልላለሁ።

  1. በህብረታችንወይም በአብሮነታችን ፍፁምነት ላይ ውይይት ያስፈልጋል ። ህብረታችንና የጋራው ቤታችን በምን ያህል አቅም ወይም በምን ያህል የአብሮነትና የወዳጅነት የቃልኪዳን ልክ ይታተም? የሚለው ዋና የምክክር አጀንዳ ነው። አሁን ያለው መተሳሰሪያ መርሆ የህብረታችንን ልክ በመገንጠል የወሰነው ሲሆን አሁን ይህንን የህብረት ልክ እንዴት እናሳድገው የሚለውን ቁልፍ ጉዳይ ነው  ለዚህ ነው Towards a More perfect Union እያልኩ የፃፍኩት:: ውይይታችን የጋራውን ቤት ፍፁም ወደ ማድረግ እንዲሆን መወያየት ያስፈልጋል :: ህገ መንግስቱን ለማሻሻልና ህብረታችንን ለማጽናት ይህ አጀንዳ ወሳኝ ነው።
  2. በቅርፀ መንግስት ላይ (Government Structure ) ምክክር ያስፈልጋል ። ቅርፀ መንግስት በምርጫ መንግስት ሲመጣና ሲሄድ የሚቀየር አይሆንም። በዚህ አንድ ኢትዮጵያን የመሰለ ቅርፀ መንግስት መስፋት አለብን። ይህ ጉዳይ ሀገሪቱ ፓርላመንታሪ ትሁን ወይስ ፕሬዝደንሺያል? የፌደራል ሥርዓቱ ምን መልክ ይያዝ? የመንግስት ቅርፁ ምን ይጨምር ምን ይቀንስ? ለምሳሌ የህገመንግስት ዳኛ ይኑር ወይስ እንዴት እንቀጥል ወዘተን ይመለከታል :
  3. ብሄራዊማንነትንና የብሄር ማንነትን እንዴት እንንከባከብ። በምን አይነት ምህዋር ይዙሩ? እንዴት ሳይጠላለፉ ይኑሩ በሚለው ላይ ምክክር ያስፈልጋል።በማንነቱ ፖለቲካ ላይ ውይይት ያስፈልጋል :: Identity politics and Identity vote on the scale of democracy and justice መቀመጥ መመዘን አለበት ::
  4. ብሄራዊ ምልክቶችን በተመለከተ መመካከር ያስፈልጋል። ባንዲራን መዝሙርን ወዘተ ይመለከታል።
  5. የመሬት ላራሹ ጥያቄ ምክክር ውስጥ መግባት አለበት። ቀጭን የፓሊሲ ጉዳይ አይደለም ይህ አጀንዳ።
  6. ያለፈመጥፎ ትውስታዎች እንዴት ይታዩ? (Past bad memories) የሚለውን ማንሳት ተገቢ ነው።
  7. ቋንቋና ተግባቦትን በሚመለከት ውይይት ያስፈልጋል። ይህ ጉዳይ የአንድ ፓርቲ ፓሊሲ ሳይሆን የቋንቋ አያያዛችን ላይ የጋራ አቋም መያዝ ይቻላል።

እነዚህ ናቸው አጀንዳዎቻችን። በነዚህ ላይ የምናደርገው ስምምነት ህገ መንግስት የሚያሻሽሉ ሃሳቦችን ያመርትልንና ወደ ህገ መንግስት መሻሻል ስራ እንገባለን ስምምነቱ በጋራ ቃል ኪዳን ይፀናል ማለት ነው። ህዝቡም በዚህ ስምምነት ላይ ተሳትፎ ሊኖረው ይገባል።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ።

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop