ለሰምና ወርቅ መጽሔት
ስለሊቀ ሊቃውንት ጌታቸው ኀይሌ በምናነሳበት ጊዜ በተደጋጋሚ የተገለጠውን ታሪካቸውን ለመድገም ሳይሆን በተለይ ለሰምና ወርቅ ሁለ- ገብ የጥናትና የምርምር መጽሔት ያደረጉትን አስተዋጽዖ ከግል ታሪካቸው እንደ አንድ ምዕራፍ አድርገን ለማስተዋወቅ ከሚል ዓላማ ተነስተን ነው። በቅድሚያ ግን የመጽሔታችን አዘጋጆች ለሊቀ ሊቃውንት ጌታቸው ኀይሌ ያለንን አድናቆት በአንክሮ መግለጥ እንፈልጋለን፤ የመጽሔቱ ባለውለታ ናቸውና።
ገና ከመቅድሙ ሰምና ወርቅ በ1979 ዓ.ም ሲቋቋም በየአራት ወር በወረቀት እየታተመ ይወጣ ነበር። መጽሔቱ ሁለት ቅጾች ካወጣ በኋላ ስለመጽሔቱ የሚገልጥ ደብዳቤ ለሊቀ ሊቃውንት ጌታቸው ኀይሌ ተጽፎላቸው ነበር። በሰጡት መልስ እጅግ ትምህርታዊ የሆኑ ምክሮችን ልከውልን በደስታ ተቀብለን ሥራ ላይ አውለናቸዋል። በስልክም ስንነጋገር በፈቀዱት ኢትዮጵያ- ነክ ርዕስ ላይ ጽሑፍ እንዲያበረክቱ ስንጋብዛቸው ያለማመንታት ፈቃደኛነታቸውን ገልጸውልናል። ቃል በገቡት መሠረት አንድ በተዋበ ብእር በእጅ የተጻፈ መጣጥፍ በፖስታ ቤት ተልኮልን በሶስተኛው ቅፅ ላይ አውጥተን አስነብበናል። ከዚህ በኋላም ራሳቸው በመረጧቸውና እኛም በጠየቅናቸው ርዕሶች በተከታታይ መጣጥፎች አበርክተዋል።
የሊቀ ሊቃውንት ጌታቸው ኀይሌ በሰምና ወርቅ መሳተፍ የመጽሔቱን ተነባቢነት እንዲጨምር አድርጎታል። መጽሔቱን ያነበቡ ብዙ ሰዎች ከተለያየ ሃገርና አህጉር የሚኖሩ ስለሊቁ መጣጥፎች ትምህርታዊነት አድንቀው በደብዳቤዎቻቸው ገልጠውልናል።
እኔ በበኩሌ በዋና አዘጋጅነት የመጀመሪያ የእጅ ጽሑፋቸውን በፖስታ ቤት በኩል ስቀበል የነበረኝ ደስታ ወደር አልነበረውም። መጽሔቱ ለተቋቋመበት ዓላማ ግቡን የመታ መሆኑን ማረጋገጫ የሆነኝ አንዱ የሊቁ መሳተፍና መሳተፍ መቀጠላቸው ጭምር ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በምናደርጋቸው የቴሌፎን ግንኙነቶች ሁሉ ሊቁ የሚያቀርቡት ምክር- አዘል ሃሳብ ሁሉ ለመጽሔቱ እድገት ወሳኝ አስተዋጽዖ ነበረው። ለብዙ አንባቢዎችና ለእኛም ለአዘጋጅዎች ትምህርታዊ ሆኖ ያገኘነው የአማርኛ ቋንቋ ችሎታቸው በጽሑፋቸው ሲንጸባረቅ በማየታችን ከብዕራቸው አጣጣል፣ ከጽሑፍ አቀራረብ ስልታቸው፣ ለአንባብያን አስበው ጠጠር ያሉ ቃላትን ለመተርጎም ባሳዩት ጥረት አያሌ ትምህርት መዝገን ችለናል። ምንም እንኳ በትምህርት ቤት እያለን የርሳቸው ተማሪዎች ለመሆን ባንታደልም አብረውን በቆዩበት ረጅም ዘመን በመጽሔቱ ሳቢያ ብዙ ተምረናል ከርሳቸው። ለሃገራቸው ሰዎች ባላቸው ከፍተኛ ፍቅር ተነሳስተው ጽሑፎችን በመጻፍና ለንባብ ለማቅረብ ያሳዩት ፈቃደኛነት እና ትብብር ለብዙዎቻችን መልካም አርአያ ሆኖናል። ፈጣሪ አምላክ የኒህን ታላቅ ምሁርና ሊቅ የሊቀ ሊቃውንት ጌታቸው ኀይሌን ነፍስ በመንግሥቱ ይቀበልልን።
ከዚህ ቀጥሎ ሊቀ ሊቃውንት ጌታቸው ኀይሌ የመጀመሪያ መጣጥፋቸውን ለሰምና ወርቅ መጽሔት ዝግጅት ክፍል በላኩበት ጊዜ ምክር- አዘል የሆነ አባሪ ደብዳቤ ልከውልን ነበር። መጽሔቱን ለመቀጠል መልካም መሪ ቃል በመሆኑ አንባቢ እንዲመለከተው የእጅ ጽሑፋቸውን እንዳለ አቅርበነዋል።
ሊቀ ሊቃውንት ጌታቸው ኀይሌንና የሰምና ወርቅ አዘጋጆችን ያገናኘን ከልብ የመነጨ የሃገርና የወገን ፍቅር ብቻ ነው። ከዚህም የተነሳ የተቻለንን ያህል በሀገራችን ሰዎች መሃከል እውቀት የዋዛ ፈዛዛ ቀልድንና ቧልትን ተክቶ እንዲገኝ ለማድረግ ከብዙ ዓመታት ጀምሮ ጥረት አድርገን ብዙ ውጤት አስገኝተናል። ሊቁ እድሜ ልካቸውን ለሃገራቸውና ለወገኖቻቸው ያለምንም ክፍያ ወይም ጥቅም አገልግሎት በሰጡበት ጊዜ እርግጥ ነው ሥራቸውን ያጠኑና ጠቀሜታውን ያወቁ ለመልካም ዓላማ የተሰማሩ አንዳንድ ድርጅቶች ለሊቁ ሥራ እውቅናን ለመስጠት የገንዘብ ሽልማት አድርገውላቸዋል። ሆኖም ግን ሊቀ ሊቃውንት ጌታቸው ኀይሌ የተቀበሉትን ገንዘብም ቢሆን አሁንም ለሃገራቸው ምሁራን መጠቀሚያ የሚሆኑ የተለያዩ መጻሕፍትን በማሳተም ተጠቀመውበታል። መጽሔታችን ይህን ያህል እድሜ ሊኖረው የቻለው በመጽሔቱ ዓላማ ያመኑ እንደሊቁ ጌታቸው ኀይሌ ያሉ ምሁራን እና ሊቃውንት ባደረጉት መስዋእትነት ነው። የነርሱ ከኛ ጎን መቆም ብርታት እየሰጠን እኛም የመጽሔቱ አዘጋጆች የግል ህይወታችንን መስዋእት አድርገን የመጽሔቱን እድሜና ግልጋሎት ለማስቀጠል ቀን ተሌት እንታትራለን። የሊቀ ሊቃውንት ጌታቸው ኀይሌን ነፍስ በአፀደ ገነት ያኑርልን!
ከዚህ ቀጥለን በሰምና ወርቅ ሁለ -ገብ የጥናትና የምርምር መጽሔት ያበረከቷቸውን መጣጥፎች ዝርዝር ለተመራማሪዎች ይረዳ ዘንድ እናቀርባለን።
1- “ከታሪክ ገጽ፤” ቁጥር 3፣ 1980 ዓ.ም
2 – “ረኀብና ተስቦ በኢትዮጵያ፤” ቁጥር 5 እና 6 ልዩ እትም፤ 1981ዓ.ም ፤
3- “የአፄ ዮሐንስ መቶኛ ዓመት ፤” ቁጥር 7 ፤ 1983ዓ.ም፤ (1990)
4 – “የፕሮፌሰር ጌታቸው ኀይሌ ሥራዎች፤” ቁጥር 7፤ 1983 ዓ.ም፤ (1990)
በዚህ እትም የቀረበው የሊቁ ሥራዎች ዝርዝር የመጽሔቱ አዘጋጅ ክፍል በጠየቃቸው መሠረት ራሳቸው አዘጋጅተው የላኩልን ነው።
5 – “ዴሞክራሲ፤” ቁጥር 8 እና 9 ፣ ልዩ እትም። 1984 ዓ.ም (1991)
ከዚህ እትም በኋላ የመጽሔቱ ሥራ ለ25 ዓመታት ተቋርጦ ስለነበር ሊቀሊቃውንት ጌታቸው በሚቀጥለው እትም እንዲወጣ ልከውት በቁጥር 10 ላይ ሊወጣ እንደተዘጋጀ ሳይታተም ቀረ። መጽሔቱ እንዲቀጥል የተለያዩ ወጣቶች በተለያየ ጊዜ ግፊት ያደርጉ ስለነበር መጽሔቱን እንደገና ለመቀጠል የጥንት አዘጋጅዎችና ከወጣቱ ደጋፊዎች ጭምር ተውጣጥተን በተደራጀን ጊዜ ከ25 ዓመት በፊት በቁጥር 10 እንዲወጡ ተዘጋጅተው ከነበሩት መጣጥፎች መካከል አንዱ የሆነውን ስለግማደ መስቀሉ የተጻፈውን ቅጂ ለሊቁ ልከንላቸው የመጽሔቱን ማንሰራራት ባበሰርናቸው ጊዜ በጣም ተደሰቱ፣ በጣምም ተገረሙ። ያስገረማቸው ከ25 ዓመት በፊት ጽፈው የላኩልን መጣጥፍ ወረቀቱ እንኳ ምንም ሳይነትብና ቀለሙ ሳይደበዝዝ እንዳለ በመቆየቱ ነበር። ጽሑፉንም አሻሽለው ለመላክ ቃል ገብተው ስለነበረ በወቅቱ ልከውልን ልናትመው ችለናል። እርሳቸውም በፈንታቸው በዚህ ርእስ መጣጥፍ አዘጋጅተው ከላኩልን ጊዜ ጀምሮ ጥናታቸውን በማስፋፋት በእንግሊዝኛ አንድ መጽሐፍ አዘጋጅተው በመታተም ላይ እንዳለ አበሰሩን። እኛም ከዚህ በኋላ ዘመኑ በፈቀደው በአዲሱ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ቀጣይ የጽሑፍ ዝግጅቶችን በኮምፒውተር በመተየብ ማቅረብ ስለጀመርን የርሳቸውን ውብ የሆነ የእጅ ጽሑፋቸውን ለማየት አልታደልንም።
6- “ የግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት፤” ቁጥር 10፣ 1989 ዓ.ም (2016)
7- “ ያላዩት አገር ሲናፍቅ፤” 2010 ዓ.ም (ጁላይ 2018)።
8- “የአስማት ጸሎት፤ “(ሳዶር አላዶር)፤ ሚያዝያ 15 ቀን 2011 ዓም (2019)
የአስተማሪያችንና ምሁራችን የሊቀ ሊቃውንት ጌታቸው ኀይሌን ነፍስ ፈጣሪ አምላክ በመንግሥቱ ይቀበልልን!
ለቤተሰቦችና ለሚያፈቅሯቸው ሁሉ መጽናናትን እንመኛለን።
ፈንታሁን ጥሩነህ / በመጽሔቱ አዘጋጆች ስም
****** ******* ****** ******
በፕሮፌሰር ጌታቸው ሞት ትልቅ ቅርስ ነው ያጣነው (ከአምኃ መርስዔ ኀዘን)
ፕሮፌሰር ጌታቸው ኀይሌ ዕውቀታቸው ሰፊና ጥልቅ፤ ዕውቀታቸውንም ምን ጊዜም በደስታ ለሌሎች ለማካፈል ሁልጊዜ ዝግጁ የነበሩ ትልቅ ሊቅ ናቸው። ለእኔ ትዝታቸው ምን ጊዜም ከልቤ የማይጠፋ አበረታቼ፣ ደጋፊዬ ነበሩ። የጠየቅኋቸውን ሁልጊዜ በደስታ ይመልሱልኝ ነበር። መልሳቸውም ሙሉ፣ አጭርና ግልጽ ነው። የአባቴን የብላታ መርስዔ ኀዘንን ያልታተሙ ጽሑፎች በማዘጋጅበት ጊዜ ለሁለት መጻሕፍት፣ ለየሐያኛው ክፍለ ዘመን የዘመን ታሪክ ትዝታ እና ለዘመናት ማገናዘቢያ በበጎ ፈቃዳቸው መቅድም ጽፈውልኛል። እንዲሁም በእርማት እጅግ በጣም ረድተውኛል። ግልጽ ያልሆነልኝ፣ ሌላ ቦታ መልሱን ለማግኘት ያዳገተኝ ጥያቄ ሲኖረኝ ሁሌ የምጠይቀው ፕሮፌሰር ጌታቸውን ነበር። ለምሳሌ ያህል አንዱን ልጥቀስ። አሁን እያዘጋጀሁት ያለሁት የብላታ መርስዔ ኀዘን ስብስብ ሥራዎች ላይ አኵስምን ስለ መጐብኘት የሚል አንድ ጽሑፍ አለ። ጽሑፉ ላይ፣ “ወደ ቅጽር ስንገባ ንጉሥ ‘መኑ አንተ’ የሚባልባቸውን የቆሙ ትክል ድንጋዮች አየን።” የሚል አለ። “መኑ አንተ“ በግእዝ አንተ ማነህ ማለት ነው። ንጉሡ “አንተ ማነህ“ ታሪካዊና ባህላዊ አመጣጥ እንዳለው በመገመት የታሪክ መጻሕፍትን መረመርሁ፣ አኵስምም ያሉ ሰዎችን አስጠየቅሁ። ምንም ዓይነት አጥጋቢ መልስ ማግኘት ሲያቅተኝ እንደተለመደው ፕሮፌሰር ጌታቸውን ጠየቅኋቸው። እሳቸውም ታሪኩን በአጭሩ አድርገው ለግርጌ ማስታወሻ እንድጠቀምበት ከዚህ በታች የተጻፈውን ላኩልኝ።
የጥንት ነገሥታት ዘውድ ሲጭኑ (ንጉሥ ሲሆኑ) የሚደረግ የንግሥ ሥነ ሥርዓት ነው። መኑ አንተ አንተ ማነህ ማለት ነው። “ንጉሡ ወደ ገበዘ አኵስም የሚመለሰው የሐውልት ጽሕፈት በአለችበት በምሥራቅ መንገድ መጥቶ ነው። ስሟ ምዕራፍ ነው። የሕግ ሰዎችና የመንግሥቱ ሠራዊቱ ሁሉ በየማዕርጋቸው፣ ካህናትም በክፍላቸውና በየሥርዓታቸው ተሰልፈው ይጠብቁታል። የጽዮን ልጃገረዶች እዚያ ይጠብቁታል። የሐር ፈትል ይዘው በቀኝና በግድም ሆነው፣ እንዳያልፍ መንገዱን በሐር ፈትል እንደ መጋረጃ አጥረው ይጠብቁታል። ከነሱ አንዷ መጀመርያ “ማነህ አንተ?” ብላ ትጠይቀዋለች። “ንጉሡ ነኝ” ይላታል። “አይደለህም” ትልና ደግሞ፣ “የማን ንጉሥ ነህ?” ትለዋለች። “ንጉሡ ነኝ” ይላታል። “ንጉሣችን አይደለህም” ትለውና በሦስተኛው ጊዜ፣ “የማን ንጉሥ ነህ?” ትለዋለች። በዚህ ጊዜ ሰይፉን በእጁ መዞ የሐሩን ፈትል ይበጥስና “የጽዮን ንጉሥ ነኝ” ይላል። “እውነት እውነት፤ የጽዮን ንጉሥ ነህ” ትላለች። ሰዉ ሁሉ እንደዚያ ይላል። ከፍ ያለ የደስታ ጩኸት ይሰማል። እዚያ ወርቅ ይበተናል። የሕግ ሰዎች ማለት የገበዝ ቤቶች ይለቅሙታል። ከላይኛው ደጀ ሰላም በሰላም ከገባ በኋላም ወርቅ ይበተናል። ለቤተ ክርስቲያን የጽዮን በረከት ይሆናል። ይኸንን ሁሉ ሥሪት የሠራ ርቱዓ ሃይማኖት ንጉሥ ገብረ መስቀል ነው።”
በፕሮፌሰር ጌታቸው ሞት ትልቅ ቅርስ ነው ያጣነው። ከእርሳቸው ጋር አንድ ትልቅ ኢንሳይክሎፒዲያ አልፏል። እንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ የሆኑብንን ጥያቄዎች ማን ነው ወደፊት የሚመልስልን?
ፕሮፌሰር ጌታቸው በታሪክ፣ በሥነ ጽሑፍ በቋንቋ ጥናት ረገድ ያደረጉት አስተዋጽዖ በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው። በታሪክና በሥነ ጽሑፍ ለተሰማሩ ሰዎች ዕውቀታቸውን ሳይቆጥቡ የሚያካፍሉትና አበረታችነታቸው ደግሞ የማይተኩ ብቸኛ የሀገር ቅርስ ያደርጋቸዋል።
******* ******* ******* *******
ጌታቸው ኀይሌን ነው አብረን የምንዘክር፤
ሊቀ ሊቃውንቱ ታላቁ ሰው መምህር።
ከማርታ ቀፀላ
ሲቃኝ በታሪኩ – ማንነት ሲገለጥ፣
ተዘርዝሮ እማያልቅ – ጥልቀታዊው እውቀት፣
በምርምር ጥበብ – ይዘቱ ሲመረት ።
መነሻው ሲጀመር – ከጥንት መሠረቱ፣
ሃገር ያበቀለው – ባህልና ስልቱ።
ተወካይ ተጠሪ – መግለፅ የተቻለው፣
ባመነበት ፀንቶ – ሚዛን ላይ ያዋለው።
የመንፈሳዊን ሃይል – ቆፍሮ አበጥሮ፣
ሃቁን በመፈልፈል – አይቶ ተመራምሮ፣
ኦሪትን ሐዲስን – ብሉይ ኪዳን አቅፎ፣
ቅዱስ መጽሐፍን – መረጃ አስደግፎ፣
የሃረጉን ይዘት – በወንጌል አጣምሮ፣
ግዕዝ መሠረቱን – ሃይሉን አጠናክሮ።
ማነው ኤትዮጵያዊው – በዚህ የዘለቀ !
ለማወቅ ሳይሰለች – በመማር የላቀ።
በሀገር ሳይወሰን – በውጭም እርቆ፣
በቋንቋው መመራት – ከያለበት ጠቅሶ፣
በእብራይስጥ በግሪክ – ጀርመን ላቲን ይዞ፣
በማንነት ድርሻው – እውቀቱን አካፍሎ፣
ትስስሩ እንዲህ ነው – ባንድነት ተባብሮ።
ምሁሩ ሊቀሊቅ – በመንፈስ የቆመ፣
በምግባር በባህሪው – ስሙ የገነነ፣
በስምም ጌታቸው – ኀይሌ እንደነበረ፣
ድንቅ ታሪክ ተክሏል – ለትውልድ የኖረ።
ብዙ መጻሕፍቱ – ባይነቱ ቀርበዋል፣
“አንድ አፍታ ላውጋችሁ” – ከዚህም ቀጥሏል።
የትዝታን ጉዞ – አቅጣጫው በሙሉ፣
አጋጣሚው ሆኖ – የነበረው ሁሉ፣
ከልብ የማይጠፋ – የነበረ ውሉ።
ፈገግ እያረገ – ቁምነገሩን አዝሎ፣
ከትከሻ እማይወርድ – ሃላፊነት ጥሎ።
ከጃቸው ተጣምራ – ህይወት ብራናቸው፣
ላሳለፉት ሁሉ – ምስክሮች ናቸው።
የሃገር ግዴታ – ወገናዊ ምርኩዝ፣
ይህን ጀግና ማጣት – ታሪክ የሚያናዝዝ።
ሃዘንን እንራቀው – ኑዛዜ አለንና፣
ያደራ ጉዟችን – ይቀጥላልና።
ስንብት አይቀርም – መጓዝ መሰናበት፣
ሰማያዊውም ቤት የሚሰጥ ነው እረፍት ።
ሳይጠቀስ ማለፍ – አይቻልምና፣
ላደረጉት ሁሉ – ለዋሉት ምሥጋና፣
በጋሪ እየገፉ – ሆነው ከጎናቸው፣
ያች ምሥራቅ ተሰማ – ውዷ ትዳራቸው፣
መጽናናትን ሰጥቶ – አምላክ ይባርካቸው ።
ለቤተሰብ ሁሉ – ፅናት ያብዛላቸው!!!