ብዙዎች ቁራጭ አምባገነን ይሉታል። ብዙዎችም ያደንቁታል። ለአራት ዓመታት የቱርክ ዋና ከተማ ኢስታንቡል ከንተቢ ነበር። በመቀጠልም ለአስራ አንድ ዓመታት የትዉልድ ሀገሩ ቱርክ ጠቅላይ ሚንስትር ሆኖ አገልግሏል። በመጨረሻም የሀገሪቱን ወሳኝ ስልጣን በሕዝብ ዉሳኔ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ወደ ፕሬዘዳንታዊ ስርሃት ይሻገር ዘንድ አድርጎ በአብዛኛዉ የሀገሪቱ ዜጋ የተመረጠ ፕሬዘዳንት ሆነ። ኤርዶጋን!
አሁን አሁን ቱርክ ከዲሞክራሲ ወደ ቀጭን አምባገነን የተቀየረች ሀገር ይሏታል። አዉሮፓዊያንም ሆነ አሜሪካ ቱርክን በአብዛኛዉ መጎንተሉን ተያይዘዉታል። ኤርዶጋንና ቱርካዊያን ግን ዓይናቸዉና ቀልባቸዉ ቻይናና ሩሲያ ላይ ካረፈ ሰነባብቷል። በዲሞክራሲ የምትመፃደቀዉ አሜሪካ የመንና ፍልስጥኤም በሳዉዲ አረቢያና እስራኤል ቀን ከለሊት ሲደበደቡ እንዳላየ እና እንዳልሰማ ዝምታን ስትመርጥ ሰዉ ሰዉ የሚሸት ተቃዉሞ እያቀረቡ ካሉት ዉስጥ አንዱ ኤርዶጋን ነዉ። በኢትዮጵያ ላይ እየዘመቱ ላሉት ነጭ ጁንታዎችም ፊቱን ማጥቆሩ ይነገርለታል። ኤርዶጋን።
ታዲያ ይህን ሰዉ በመፍራት ይሁን የእኛዉን ጠቅላይ ሚኒስተር የወደፊት ዕጣ በመተንበይ ጥቂቶች የዶክተር አብይን ጉዞ ኤርዶጋዊያን ሲሉት ይደመጣሉ። መቼም የቱርክን ታላቅነት የሚመኝ ኤርዶጋንን ሊጠላ የሚችለዉ በአሜሪካ እና በአዉሮፓ አስመሳይ የዲሞክራሲ ሰበካ ከተጃጃለ ብቻ የመሆኑን ያክል ጠ/ሚ አብይንም ከልቡ የሚጠላ የኢትዮጵያ ታላቅነት ወዳጅ ይሆናል ብዬ መመስከር ይከብደኛል።
በእርግጥ በርካታ ችግሮች አሉብን። አሜሪካም ችግር አለባት። እኛ ዘቅዝቀን ስንሰቅል እነሱ ሀገር ነጭ ፖሊስ የጥቁር አንገት ላይ ከአስር ደቂቃ በላይ በመቆም ሲገድል አይተናል። በየቀኑ በአሜሪካ ከተሞች በፖሊስ እና በዱርዬ የሚገደለዉንም ሰዉ ለሚታዘብ ኢትዮጵያ ገነት መሆኗን መመስከር አይከብደዉም። በእርግጥ ትግራይ ጦርነት አለ።
ወደ ኤርዶጋዊያን እንመለስ። የአንዳንዶች ስጋት አብይ አህመድ ሕገ መንግስቱን በማሻሻል ከጠቅላይ ሚንስትርነት የምርጫ ዘይቤ በመዉጣት ሀገሪቷን ወደ ቀጥተኛ ፕሬዘዳንታዊ ስርሃት በመቀየር ዳግም ስልጣኑን የሚያደላድል ቀጭን አምባገነን ይሆናል የሚል ፍርሃት አለቸዉ። ለእኔ ይህ እዉነትነቱ የገዘፈ ግምት ቢሆንም የምመኘዉ ብቸኛ የኢትዮጵያ ተስፋ ነዉ ብል አላጋነንኩም። ፀሎቴም ነዉ ብዬ ብናገር ፍፁም አላፍርበትም።
ምናልባት በአምባገነኑ ኮረኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ዘመን ተወልጄ በማደጌ የኤርዶጋንነት ጥማቴ የአምባገነን ናፍቆት ሊሆን ይችላል በማለት ጥቂቶች ሊቀልዱ ቢሞክሩም እኔ ግን ፑቲንን የመሰለና የቻይናዉን ኮሚኒስት ፓርቲ የመሰለ መልካም አምባገነን (benevolent dictatorship) ካልሆነ ኢትዮጵያን ከገባችበት የብሔር ብሔረሰብ ጠባብ አርንቋ የሚያወጣት ፖለቲካዊ ኀይል ያለ አይመስለኝምና ለእምዬ ኢትዮጽጵያ ስል ኤርዶጋናዊ መልካም አምባገነን ፀሎቴ ይቀጥላል።
በነገራችን ላይ ሚኸኤል ጎርቫቾቭን በዲሞክራሲ ስም አንበርክከዉ ሲያበቁ ቀጣዩን የሩሲያ መሪ ቦሪስ የልሲንን አልከስክሰዉና ታላቁን የሩሲያ ሕዝብ በርሃብና በስራ አጥነት በሚያሸመደምዱበት ወቅት ነበር ፑቲን መልካም አምባገነን ሆኖ ብቅ ያለዉ። ከሃያ ዓመታት በኋላ ሩሲያ ዳግም ክብሯን ተጎናፅፋ ከአዉሮፓና አሜሪካ ከመገዳደርም አልፋ ለእኛም መከታ ለመሆን በቅታለች። መቼም በፀጥታዉ ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ በመሻር መብቷ ከሱዳንና ግብፅ ጋር የተባበረችዉን አስመሳይ አሜሪካ ሰሞኑን ደጋግማ እንዳሳፈረችልን የምንዘነጋ አይመስለኝም።
ስለዚህ አብይ ኤርዶጋንን ይሁን ስል ኢትዮጵያን ስለምወድ እንጂ የግለሰብ ደቀመዝሙር ሆኜ አይደለም። ዐፄዎቻችንም በሙሉ ኤርዶጋዊያንን ስለመሰሉም ነበር በኢትዮጵያ ታሪክ የገዘፉት:: ዐፄ ቴዎድሮስ ከጎንደር እስከ ሸዋ፣ እንዲሁም ዐፄ ሚኒሊክ ከወሎ እስከ ሞያሌ ተዋግተዉ ኢትዮጵያን ያቆዩልን መልካም አምባገነን ስለነበሩ እንጂ ዲሞክራሲያዊ ሆነዉ ስለተለማመጡ አይደለም። ዛሬ አሜሪካና አዉሮፓ አጎንብሱልን እያሉ እንደሚያስፈራሩን ዐፄ ቴዎድሮስ ለእንግሊዝ፣ ዳግማዊ ዐፄ ሚኒሊክም ለጣሊያን ማስፈራሪያ አጎንብሰዉ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የዐፄዎቹ የግል ታሪክም የእኛ ኢትዮጵያዊያን ማንነትም የዉርደት ይሆን ነበር።
በነገራችን ላይ ሱዳን መሬታችንን እያረሰች አውሮፓና አሜሪካ ስለ ኤርትራ ወታደሮች የሚጨናነቁት ለኢትዮጵያ ወይም ለትግራይ አዝነዉ አለመሆኑ የማይገባን ከመሰላቸዉ እናዝናለን።፤ ስለ እኛ ምርጫ ታዛቢ የሚልኩትም ስለዲሞክራሲ ተጨንቀዉ አለመሆኑን የመንን እና ፍልስጥኤምን በማሳየት ልንሳለቅባቸዉ እንችላለን።
በመጨረሻም ኤርዶጋንም ይሁን ፑቲን፣ ቻይናም ትሁን ኢትዮጵያ ከዘመናት የአዉሮፓና አሜሪካ በዲሞክራሲ ስም የማሸማቀቅና የማንበርከክ ቀንበር ሙሉ ለሙሉ የተላቀቁ ባይሆንም ሚስጥሩን ግን በሚገባ ተረድተዋል። ስለዚህም የራሳቸዉን ጉዞ ጀምረዋል። መመፃደቅ የሌለበት ሀገር የመገንባትን ጉዞ ቻይና ከሰላሳ ዓመታት በፊት፣ ሩሲያ ከሃያ ዓመታት በፊት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት በፊት ተያይዘዉታል። ስለዚህም ቆፍጠን ያለዉ ጅምራችን እንደ ቻይናና ሩሲያ መቀጠል አለበት።
አንቀፅ ሰላሳ ዘጠኝን በመሰረዝ፣ ኢትዮጵያዊያንን የሀገርና የመሬት ባለቤት በማድረግ፣ የብሔር አጥሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመናድ፣ ከጠቅላይ ሚንስትርነት ወደ ፕሬዘዳንታዊ ስርሃት የሚወስደንን ኦርዶጋናዊ ጉዞ መያያዝ ይበጀናል።
ኢትዮጵያ ትቅደም።
ዶ/ር መኮንን ብሩ