“የዘርአ ያዕቆብ (ወርቄ) እና የሬኔ ዴካርት ፍልስፍና” (ፈንታሁን ጥሩነህ)

የኢትዮጵያና የአውሮጳ ፍልስፍና አንድነትና ልዩነት
(የዘርአ ያዕቆብ እና የሬኔ ዴካርት ፍልስፍና)
ከፈንታሁን ጥሩነህ

ዘርአ ያዕቆብ ከአክሱም የመነጨ ፈላስፋ ነው። ዴካርት ደግሞ ከፈረንሳይ ሀገር ይመነጫል። ሁለቱም ፈላስፋዎች በአንድ ዘመን ኖረዋል። በትውልድ ዓመትም ብዙ አይራራቁም። ሬኔ ዴካርት እንደ አውሮጳውያን ዘመን አቆጣጠር 1596 ዓ.ም ላይ ሲወለድ ዘርዓ ያዕቆብ ደግሞ በ1599 ዓ.ም ላይ ተወለደ። (1)

ሬኔ ዴካርት የሚታወቀው የመጀመሪያ ፈረንሳዊ ብሎም አውሮጳዊ ፈላስፋ በመሆኑ ነው። የመጀመሪያውን የፍልስፍና መጽሐፍ በ1641 ዓ.ም ላይ አሳትሞ ይፋ አደረገ። የመጽሐፉ ርእስም Meditations Concerning Primary Philosophy (ቀደምት ፍልስፍና ላይ የቀረቡ እሳቤዎች) ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ዘርአ ያዕቆብ እስካሁን ያለውን መጠነኛ ታዋቂነት ያገኘው ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ተብለው በታወቁት ሊቅ ከግዕዝ ወደአማርኛ ተርጉመው ባሳተሙት ኢትዮጵያውያን ፊሎሶፊዎች፤ ሐተታ ዘዘርአ ያዕቆብ አክሱማዊ ወወልደ ሕይወት እንፍራዛዊ በተሰኘው መጽሐፍ ሳቢያ ነው።

ሊቁ ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያውያን ስለመምህሩ ዘርአ ያዕቆብና ስለ ደቀመዝሙሩ ስለ ወልደሕይወት ያስተዋወቁ ናቸው። እነዚህ ፈላስፋዎች ጽፈው የተዉልንን ሁለት የፍልስፍና መጻህፍት በአንድ መጽሐፍ አካተው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቅ ባደረጉት ጥረት ታሪክ ሲያስታውሳቸው ይኖራል። ዘርአ ያዕቆብ ፍልስፍናውን የጻፈበትን ጊዜ ለማወቅ ባደረግሁት ሙከራ በኔ ስሌት እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1668 ዓ.ም ገደማ ይሆናል። ይህ ግምታዊ ተመን የተቀመረው በዘርአ ያዕቆብ ጽሁፍ ላይ ሰፍረው ከሚገኙት አሀዞች ጋር አብሮ የቀረበውን ማብራሪያ መነሻ በማድረግ ነው። በሌላ በኩል ይህ መጽሐፍ የተጻፈበትና ይፋ የወጣበት ጊዜ በብዙ ዓመት ሊለያይ የሚችልበት ሁኔታ አለ። ዘርአ ያዕቆብ ራሱ እንደጻፈው፥

“ከእኔ በኋላ የሚመጡ እንዲያውቁኝ ግን እስክሞት ድረስ በእኔ ዘንድ ሸሽጌ የምይዘው(ን) ይህን ጽሑፍ ልጽፍ ወደድሁ።” ይላል:: (2)

እንዲህ ከሆነ በእርግጥ መጽሐፉ የተጀመረበትን ጊዜ ማወቅ አያስችልም። ከደቀመዝሙሩ ከወልደሕይወት ጽሁፍ ስንነሳ ደግሞ መጽሐፉ ከተጻፈ በኋላ ዘርአ ያዕቆብ ለ25 ዓመታት በህይወት መኖሩን ይገልፃል። ከተማሪው ላይሸሽግ ይችላል የሚባል ከሆነ በርግጥ በ68 ዓመቱ ማለትም በ1660 ዓ.ም (በኢትዮጵያ) ወይም በ1668 (በአውሮጳውያን) ተጻፈ ልንል ነው።

ሁለቱም ፈላስፎች (ዴካርት እና ዘርአ ያዕቆብ) ከጻፏቸው ቁም ነገሮች መካከል የኢትዮጵያዊውንና የአውሮጳዊውን ፍልስፍና ያጣመረ ጥያቄ የአምላክ ህልውና ጥያቄ ነበር። በዚህ ፍልስፍና ዙሪያ የተለያዩ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ። ለጊዜው ግን ከሁለቱ ፈላስፎች ተጽፈው ከተላለፉልን ፍልስፍናዎች ሁለቱን አመሳስሏቸው የተገኘውን ምዕራፍ ልጥቀስ። ዘርአ ያዕቆብ እንዲህ ይላል፤

“አንድ ቀን ግን ወደማን እፀልያለሁ? በእውነት የሚሰማኝ እግዚአብሔር አለን ብየ አሰብሁ። በይህም ሃሳብ በጣም አዝኘ እንደይህ አልሁ፥ ዳዊት እንዳለ እንዴት ምንኛ ልቤን በከንቱ አፀደቅሁኣት? ሁዋላም አሰብሁ ይህ ዳዊት እንደይህ የሚለው ጆሮን የተከለ አይሰማምን? በእውነት እንድሰማበት ጆሮ የሰጠኝ ማን ነው? አዋቂስ አድርጎ የፈጠረኝ ማን ነው? ወደ ይህስ ዓለም እኔ እንደምን መጣሁ? ከወደየትስ መጣሁ? ከዓለም በፊት ብኖር የህይወቴ(ን) መጀመሪያና የእውቀቴ(ን) መጀመሪያ ባወቅሁ [ነበር]:: እኔ በገዛ እጄ ተፈጠርሁን? ነገር ግን እኔ በተፈጠርሁ ጊዜ ባልኖርሁም። አባት እናቴ ፈጠሩኝ ብልም እንደገና ለወላጆቸና ለወላጆቻቸው ወላጅ የሌላቸው በሌላ መንገድ ወደይህ ዓለም የመጡት እንጅ እንደኛ ወደአልተወለዱ እስከፊተኞቹ እስኪደርሱ ድረስ ፈጣሪያቸው(ን) ይፈልጋል። እነርሳቸውም ቢወለዱ እምሃበ አልቦ የፈጠራቸው አንድ ህላዌ አለ እንጂ ከማለት በቀር የጥንት ወላጆቻቸው[ን] አላውቅም። የአልለና በሁሉ ዓለም የሚኖር የሁሉ ጌታ ሁሉን የያዘ መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ዓመቱ የማይቆጠርና የማይለወጥ ያልተፈጠረ ፈጣሪ አልለ እላለሁ። ፈጣሪስ አልለ ፈጣሪስ ባይኖር ፍጥረት ባልተገኘም እላለሁ። እኛ ብንኖርም ፍጡራን እንጂ ፈጣሪዎች አይደለንምና የፈጠረን ፈጣሪ አልለ እንል ዘንድ ይገባናል። ይህም የፈጠረን ፈጣሪ አዋቂና ተናጋሪ ካልሆነ በቀር ከእውቀቱ በተረፈ አዋቂዎችና ተናጋሪዎች አድርጎ ፈጥሮናል። ሁሉን ፈጥሩአልና ሁሉን ይይዛልና ሁሉን ያውቃል።” (3)

ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የፈረንሳዩ ፈላስፋ ዴካርት በዚሁ በተመሳሳይ የእግዚአብሔር ህልውና ጥያቄ ላይ ያቀረበውን ክርክር እንመልከት፥

“እንዲህም ሲል ቀጠለ [ዴካርት] ‘እስቲ ሀሳቤን ልቀጥልና ምናልባት እንዲህ ዓይነት ህልው ከሌለ እኔ እራሴ (ይህን ሃሳብ የማውጠነጥነው ሰው) ራሴን ፈጥሬው እንደሆነ ልጠይቅ።’ ቀጠለና፥ ‘እንግዲያውስ ህልውናዬን ከማን አገኘሁት፥ ከራሴ ወይስ ምናልባት ደግሞ ከወላጆቸ ወይስ ከሌሎች…ሆኖም ግን ራሴን በራሴ ብፈጥር ኖሮ ማንኛውንም ነገር ባልተጠራጠርኩ፥ ባልተመኘሁ፥ ባልጠላሁ ነበር። እራሴም እግዚአብሔር [ፈጣሪ] ስለምሆን ስለማስበው ማናቸውም ሀሳብ ፍፁምነትን ለራሴ ባደልሁ [በሰጠሁ] ነበር። ደግሞም ህልውናዬን ከሌላ ነገር ላይ ባመነጨው በተዋረድ ሄጀ ራሱን በራሱ ከፈጠረ [ህልውናውን ከራሱ ባመነጨ] ህልው ላይ ማሳረፍ እገደዳለሁ። እንግዳውስ ይህ ክርክር እንደመጀመሪያው መላ ምት ማለትም ህልውናዬን ከራሴ አመነጨሁት ከሚለው የሚለይ አይደለም።” (4)

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወ/ት ብርትኳን ሚዴቅሳ ወደ ኢትዮጵያ ልትገባ ነው

እነዚህ ሁለት ምዕራፎች የሚመሳሰሉት በአምላክ መኖር አለመኖር ጥይቄ ላይ ማተኮራቸው ሲሆን የሚለያያቸው ደግሞ ዘርአ ያዕቆብ የዘመኑን የአካባቢ ተፅዕኖ በመፍራት (የካህንነት ጀርባ ጫና ስለነበረበት) ለጥያቄው መልስ ለመስጠት ከአንድ አጭር ምዕራፍ ያላለፈ ሓተታ በመስጠቱ፥ ዴካርት ግን የዘመኑ አካባቢ ሁኔታ የተሻለ በመሆኑ ሰፋ ያለ ትንተና ማቅረቡ ላይ ነው። በጣም የሚያመሳስላቸው ነጥብ ግን ይህን የአምላክ ህልውና ጥያቄ በድፍረትና ለመጀመሪያ ጊዜ ምክንያታዊ ድልዳል (በአመክንዮ የተመሰረተ) ለመስጠት ያደረጉት ሙከራ በመሆኑ ነው።

ዴካርትና ዘርአ ያዕቆብ በቀጥታ ግንኙነት ሳይኖራቸው ሁለቱም እጅግ በተራራቀ ቦታ ስለፍጥረትና ስለፈጣሪ ተዛምዶ ሐተታ በማቅረብ መልስ ለማግኘት ሙከራ በማድረጋቸው ይታወቃሉ። አክሱማዊው ዘርአ ያዕቆብ የምርምርን ሐቲት ለመጀመሪያ ጊዜ በማስተዋወቁ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ ያደርገዋል። ዴካርትም በአውሮጳ የመጀመሪያውን ሐቲት በማቅረቡ ለአውሮጳ የመጀመሪያው ዘመናዊ ፈላስፋ በመሆን ይታወቃል። ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ፍልስፍና በዘርአ ያዕቆብ አማካኝነት የሐቲት መልክ ይዞ ይቅረብ እንጅ ከጥንት ጀምሮ በተለያየ መልክ ሲገለፅ የኖረ ነው። እንቆቅልሾች፥ ተረቶች፥ በኋላም የቅኔ ግጥሞች የተለያዩ መግለጫዎች ነበሩ፥ ናቸውም።

የዘርአ ያዕቆብንና የዴካርትን ፍልስፍና የሚያመሳስለው አንዱና ዋነኛ ነጥብ የሁለቱም የምርምራቸው መሰረት ስነመለኮታዊ መሆኑ ነው። በነበሩበት ዘመን አብዛኛው የሰው ልጅ አስተሳሰብ የሚካሄደው በሃይማኖቶች ዙሪያ ስለነበር እነዚህ የማይተዋወቁ በመልክዐ ምድር የተራራቁ ፈላስፋዎች ስለእግዚአብሔር ህልውና ጠለቅ ያለ ጥያቄ አንስተው መልስ ለማግኘት መሞከራቸው “አብዮታዊ” ወይም “እምርታዊ” የሚያሰኝ እርምጃ ነበር። ሆኖም ግን ሁለቱም ፈላስፎች ምርምራቸውን የጀመሩበት ጉዳይ ይለያያል።

ዴካርት ማንኛውንም የተፈጠረ ሀሳብ ያለምርምር መቀበል አደገኛ ነው በሚል እምነት እውነት እየተባለ የሚቀርብን ሃሳብ ሁሉ እንዳለ ከመቀበል አደጋ ለመከላከል ሳይንስን የማያጣራጥር ድልዳል ለመስጠት ነበር ጥረቱ። ዘርዐ ያዕቆብ ያቀረበው ሐቲታዊ ዘዴ ግን የሰዎችን ውሸት ማለትም እግዜር ገለጠልኝ እያሉ ሰዎችን የሚከፋፍል አስተሳሰብ የሚያሰራጩትን ለመግታት የታቀደ ዘዴ ነበር። ዴካርትና ዘርአ ያዕቆብን የሚለያያቸው ዋናው ነጥብ ዘርአ ያዕቆብ ከእግዚአብሔር በሚሰጥ አመክንዮ ሲመካ ዴካርት ግን በራሱ አስተሳሰብ በመመካቱ ነው። ስለዚህ ዴካርት ‘በነጠረ አስተሳሰብ’ ሲተማመን ዘርአ ያዕቆብ ግን በሰዎች በራሳቸው አስተሳሰብና ከእግዜር በመነጨ አስተሳሰብ መካከል ያለውን ልዩነት እንዲሁም ቤተክህነት በምታስተምረው ትምህርትና ሰዎች እየጨመሩ በሚያስተምሩት መካከል ያለውን ልዩነት አፍረጥርጦ መግኘት ነበር ዓላማው። (5)

ስለዚህ “የነጠረ አስተሳሰብ” የሚለው ፅንሰ ሃስብ ለዴካርት “መሰረታዊ መተክል” ሆኖ ማንኛውንም ስለሰው ፍጥረትም ሆነ ስለፈጣሪ እራሱ እውነቱን ለማግኘት የሚጠቀምበት ሐቲታዊ ዘዴ ነበር። ዋናው ዓላማም ትውፊታዊ አስተሳሰቦችን ጥያቄ ውስጥ ማስገባትና የቅመራን (የሂሳብን) ዘዴ ለሳይንሳዊ ምርምር መጠቀም ነበር። የዘርአ ያዕቆብ ፍልስፍናዊ መሰረት ደግሞ “የፍጥረት ሁሉ መልካምነት” ነበር። ስለዚህ በዘርአ ያዕቆብ አመለካከት ትዳርም ሆነ ምግብ መልካም ነው ብሎ ሲያስብ ብህትውናንና የጾምን ትውፊት አይቀበልም ነበር። ሆኖም ግን የሰውን ልጅ ነፃነትና ከፍጥረታት ሁሉ የበላይነቱን ያምንበት ነበር። (6)

ዴካርት የመጀመሪያውን የፍልስፍና ጽሁፍ አሳትሞ ሲያበረክት ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አውሮጳውያንና የምዕራቡ ዓለም ፈላስፋዎች ዴካርት አንስቶ የተነተናቸውን ሐቲቶችና ዘዴዎች በመጠቀም በጥያቄ መልክ ለተዋቸውም ጥርጣሬዎቹ መልስ ለማግኘት ሰፊ የፍልስፍና አውድማ አበርክተዋል።
ባንጻሩ የዘርዐ ያዕቆብ ፍልስፍና እንኳን ሊስፋፋ ይቅርና ለሕይወቱም አስጊ ሁኔታ ስለፈጠረበት እየተሽሎከሎከ ከመኖር ውጪ ሃሳቡን የሚያስፋፋበት እንኳ በቂ ሰላም አላገኘም። በድብብቆሽ እያለ ወልደሕይወትን በማስተማሩ ግን ቢያንስ አሁን ወደእኛ ትውልድ ሊደርስ የቻለውን የፍልስፍና መጽሐፍ ማግኘት ችለናል።

ዴካርት ስለአእምሮ አፈጣጠር በጻፈው ድርሰት “እኔ ምንድር ነኝ” ለሚለው የግል ጥያቄው “የማስብ ነገር ነኝ” ከማለት በተጨማሪ “አእምሮ” ነኝ ወደሚል ድምዳሜ ይደርሳል። እኔ “የሚያስብ ነገር ነኝ” ብሎ ማሰቡ ሰውን ከግዑዝ ነገር ጋር የሚያመሳስል ድምዳሜ በመሆኑ የሰውን ልጅ ክብር ዝቅ የሚያደርግ ነው። እውነትን በሐቲታዊ ዘዴ ለማግኘት የታቀደው “ሳይንሳዊ” እርምጃ የአእምሮን የበላይነት ሲያሰምርበት የሰውን ፍጥረት ግን ከግዑዝ ነገር ጋር በማዛመዱ መሰረታዊ ስህተት ላይ ጥሎታል። የዚህንም ፍልስፍና ከሳርነት ዝቅ ብየ ለማሳየት እሞክራለሁ። የእግዚአብሔርን (የአምላክን) ህልውናም የሚመዝነው ከርሱ ከራሱ ህልው መሆን ጋር በማያያዝ እንጂ የእግዚአብሔር/የአምላክ ፈጣሪነት የሰው ልጅ ደግሞ ተፈጣሪነት  መልኩን ይዞ አልቀረበም። ፍቅርንና እግዚአብሔርን ለያይቶ ይተነትናል። ይህም ማለት የነአሪስቶትልን ፍልስፍና ጥያቄ ውስጥ በማስገባት ሳቢያ በመጽሕፍ ቅዱስ ላይ ተፅፎ የሚገኘውንና “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” የሚለውን አስተምህሮ አብሮ የመጠራጠሩን ሁኔታ ይከስትበታል::

ተጨማሪ ያንብቡ:  በምዕራብ ወለጋው ጥቃት ወቅት ታግተው የተወሰዱ ሰዎች እንዳሉ ተገለጸ

የአውሮጳና የኢትዮጵያ ፍልስፍና ልዩነት

በዴካርት የሚመራው የአውሮጳውያን ፍልስፍና መሰረቱ በአእምሮ ሃሳብ ላይ ያረፈ ሲሆን በዘርአ ያዕቆብ የሚመራው የኢትዮጵያውያን አስተሳሰብ ደግሞ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሰረተ ልባዊ አስተሳሰብ መሆኑ ላይ ነው።

የዴካርት ፍልስፍናዊ መነሻ ሁሉንም ነገር በመጠርጠር ላይ ነበር። ስለዚህ በአእምሮው እየተመካ ሃሳቦችን በማጣራት የእግዚአብሔርን መኖርና አለመኖር፥ እውነት እየተባለ የቀረበለትን ሁሉ በራሱ ተማምኖ፥ ከትውፊት የተላለፈለትን ዕውቀት ሁሉ ለመመርመር ተነሳ።

ዘርአ ያዕቆብ የእግዚአብሔርን ቃል መሰረት አድርጎ ከዚህ ቃል ያፈነገጠውን ሃሳብ ሁሉ የሚመረምርበትና እውነቱን የሚስያስረግጥበት የሐቲት ዘዴ አቋቋመ። ሁለቱም ፈላስፎች ያልተለመዱ የአስተሳሰብ ፈለጎች በማስተዋወቃቸው አንድ ሲሆኑ በዓላማ ግባቸው ግን ይለያያሉ። እንዲያውም አውሮጳውያን ከጭንቅላታቸው በመነጨ ሃሳብ ላይ ትኩረት በማድረጋቸው የዜጎቻቸውን መራከስ ያስከተለባቸው ይኸው ከዴካርት የመነጨው “ሳይንሳዊ” አስተሳሰብ ነው ማለት ይቻላል። በጭንቅላት ሃይል መመካት የእግዚአብሔርን (የፈጣሪን) ሕልውና እና ሃይል በቀላሉ ለመካድና ለማስካድ ጥቅም ላይ የዋለ መሳሪያ ይመስላል። ስለዚህም በአውሮጵውያንና በሞላ የምዕራቡ ዓለም ፈጣሪ አምላክ ተረስቶ ሰው የራሱን አምባገነንነት ተክቷል፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር የሚባል ባሕል ጨርሶ በመጥፋት ላይ ነው። ከነርሱም ተርፎ እንደብርቅ አስተሳሰብና እንደዘመናዊነት ፍልስፍና ለአፍሪቃ ህዝቦች በየመጽሐፉ፤ በየቪዲዮው፤ በየፊልሙ፤ በየጽሑፋቸው እያስተዋወቁት ይገኛሉ።

የዘርአ ያዕቆብ ልባዊ እውቀት ከፈጣሪ ትእዛዛት የሚወጣ ፍልስፍና አይደለም። ይልቁንም እግዚአብሔር የሰጣቸውን የተቀደሱ ትእዛዛት ንፅሕና ለማስከበርና እንዳለ ለማቆየት የታቀደ ስነመለኮታዊ ሐቲት እንጂ። የዴካርት አስተሳሰብ የሚመነጨው ጭንቅላት (አእምሮ) ራሱን ችሎ ንፁህ ሃሳብ ያፈልቃል ብሎ ከማመን ነው። ነገር ግን ሃቁ አእምሮ ከልብ የሚመነጨውን ሃሳብ እንዲያደራጅ እንጂ ራሱን ችሎ ሃሳብ እንዲያፈልቅ የተሰራ አካል አይደለም። የእግዚአብሔር ማደሪያ ልብ ነው እንጂ ጭንቅላት አይደለም። ጭንቅላት የሰውን ልጅ ኑሮ እንዲመራ ሲደረግ ነው ዓለም አሁን ያለችበትን ቀውጢ ፈጥራ መውጫ ያጣችው። የዚህ ሁሉ የሰው ልጅ አበሳ በሰፊው የጀመረውና ዓለም የጦርነት አውድማ የሆነችው ዴካርት ለጭንቅላት ዕውቀት የበላይነት በመስጠት የተሳሳተ ፍልስፍናዊ መሰረት በመጣሉ ነው ብለን መደምደም እንችላለን።
ዘርአ ያዕቆብ ልባዊ እውቀትን መሰረት ያደረገ፥ እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን በማመን ላይ የተመሰረተ ሞራላዊ ምክሮች ለሰው ልጆች ያበረክታል። ዴካርት የሚታወቅበት ስንኝ “ስለማስብ እኔ ነኝ” ነበረ፤ አሁንም ነው። ዘርአ ያዕቆብ ግን “እኔ ፍቅር ነኝ” ብሎ ከፈጣሪው ጋራ ተዛምዶውን እንደገለፀ የሚያመለክት ሐተታ በደቀመዝሙሩ በወልደሕይወት በኩል እንደሚከተለው ተዘርዝሮ ተቀምጧል፤

“ልጀ ሆይ በምር እንዳትፀፀትና በቁጣህም ላይ ፀሐይ እንዳትጠልቅብህ ከቶ ቁጡ አትሁን። ባልንጀራህን ብታሳዝነውም ለእሱ ያደረግህበትን ተሎ ተነስተህ ስለክፉ መልካም መልስለት እንጂ አትዘግይ። ከስህተትም ለመመለስ ትጋ። አምላክ እንዲባርክህና ሰላም እንዲሆንላችሁ ከእርሱ ከባለእንጀራህ ጋር ሰላማዊ ሰው ሁን። ከችግረኞችና ከሃዘንተኞች ጋር አፅናኝና ርሕሩሕ ሁን። እግዚአብሔር ዋጋህን ይከፍልሀልና ምፅዋት ማድረግን አትርሳ። እግዚአብሔር በመልካም ነገር ሁሉ እንዲያጠግብህ እንጀራ ቢኖርህ ከተራቡት ወንድሞችህ ጋር ተካፈለው።
ያስጥልሃል እንጂ እግዚአብሔር የሓጥአንን በትር ባንተ ላይ አያሳርፈውምና ኅይል ቢኖርህ የእሚባረሩ ወንድሞችህን አስጥላቸው። እግዚአብሔር የተሰወረውን ምስጢር እንዲያሳይህና እንዲያስታውቅህ ጥበብ ካለህ ዕውቀት ለሌላቸው አስተምራቸው። እግዚአብሔር አምላካችን ፍቅር ነውና የሚቻልህ ከሆነ ለሁሉም ሰው መልካም ታደርግ ዘንድ ውደድ። በፍቅር ወንድሙን በመውደድ የሚኖር ሰው እርሱ ከእግዚአብሄር ጋር ነው፤ እግዚአብሔርም ከእርሱ ጋር ነው። ፍቅር የሰውን ኑሮ ሁሉ ያሳምራል፤ ችግርንም ሁሉ ያቃልላል።
በእውነትና በስራ ብቻ እንጂ በአፍና በምላስ እንፋቀር ዘንድ አይገባንም። በአፋቸው የክስርስቶስን ፍቅር እያስተማሩ በልባቸው ፍቅር የሌላቸው ሲሳደቡና ሲጋደሉ፥ እርስ በርሳቸውም ስለሃይማኖቶቻቸው ሲወጋገዙ እንደሚኖሩት እንደሃገራችን ክርስቲያኖች አንሁን። ይህን የመሰለ ፍቅር ከእግዚአብሔር ዘንድ አይደለምና ምንም አይጠቅምም። ዳግመኛም ከምላሳቸው በታች የእባብ መርዝ እያለ በአፋቸው የእውነትና የፍቅር አስመስለው እንደሚናገሩት ግብዞች አንፋቀር፤ ልባቸው ሁልጊዜ መጣላትና መከራከር ይስባልና። ፍቅራቸው ፍፁም አይደለምና የሃይማኖት ወገኖቻቸውን የወደዱና በሃይማኖት የማይተባበሯቸውን እብዶችን እንደሚጠሉ አድርገን አንፋቀር። ሁሉም ሰዎች በተፈጥሯቸው ትክክል ናቸው፤ ሁሉም የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውን ልብ አድርገን ማወቅ ይገባናል። እኛ ያንዳንዱ ሰው እውነት መስሎ የታየውን ሃይማኖት ስላመነ ብንጠላው እንሳሳታለን። ሃይማኖት በውቀትና በትምህርት እንጂ በሃይልና በግዝት በሰው ልብ ሊፀናና ሊቀና አይችልም። ሰዎችን ስለዕውቀታቸው ልንጠላቸው አይገባም።” (7)

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሁሉም አማራ ወደ ግንባር እንዲሰለፍ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጥሪ አቀረቡ

ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም በተዋበው የህይወት ታሪክ መፅሐፋቸው ላይ ያነሱትን ነጥብ ጠቅሼ እደመድማለሁ። ከዚህ ቀጥሎ የሰፈረው ትችት ሩስያውያን ወዳጆቻቸው በተለይም አያቴ የሚሏቸው የሴት አያት ተክለሐዋርያት ትምህርት ጨርሰው ሲመረቁ የሰጧቸውን የምክር ገፀበረከት ነው፤

“ሰው ምንም የተማረ ቢሆን ምዕራባዊ አውሮፓን ካልጎበኘ የአውሮፓን ስልጣኔ በትክክል ለመረዳት አይችልም። ዕውቀቱም ሙሉ አይሆንም። ምዕራባውያን እኛን ሩስያኖችን ከግብዞች፥ ከገልቱዎች ይቆጥሩናል። ለዚህም ምክንያት ይገኝላቸዋል። እነሱ ከኛ በፊት መሰልጠናቸው በታሪክ ላይ የታመነ ነው። አሁንም ቢሆን ከኛ በፊት መሰልጠናቸው አያጠራጥርም። ነገር ግን እንዴት ነው የሰለጠኑት? አንጎላቸውን፥ አንደበታቸውን፥ እጆቻቸውን፥ አኗኗራቸውን አሰልጥነዋል። ልቡናቸው ግን ወደጨካኝነት ተዛውሯል። ሃይማኖታቸውን፥ ፍቅርን፥ ቁም ነገርን ትተዋል። ነውርን ንቀዋል። ቅሌተኛነት አያስጠይፋቸውም።
ይህ ሁሉ ያረጀ ፈሊጥ ይመስላቸዋል። ፈጣሪን ክደዋል፤ ማቴሪያሊስቶች ሆነዋል። እምነታቸውንና ተስፋቸውን በነዋይ ላይ ብቻ አድርገዋል። ዕውቀት የሚያስፈልጉት ለምድራዊ ኑርዋቸው ማደላደያ የጥበብና የዘዴ ማከናወኛ መስሪያ እንዲሆናቸው ነው እንጂ ለልቡናቸው ነፍሳዊ ሃይል እንዲሰጣቸው አይደለም። ዕውቀታቸው የስሌት፤ የሒሳብ ነው። ጥቅምን ለመፍጠሪያ ነው። ጥቅምን እየፈጠሩ ወዲያውም ችግርን ይፈጥራሉ። ነጋዴዎች ናቸው። ሁሉንም ለገንዘብ ይለውጡታል። ጥበባቸው ሁሉ ወደ ጥፋት የሚወስድ ነው። ሁሉ ምዕራባውያን የሚገሰግሱት ከሌሎች ሕዝቦች በፊት፥ ለሌላው አጥፊዎች ራሳቸውም ጠፊዎች ለመሆን ነው።” (8)

ከዚህ መገንዘብ የምንችለው በነዴካርት የተጀመረው በጭንቅላት የመተማመን ፍልስፍና ከዘመናት በኋላ ያመጣውን አስከፊ መዘዝ ነው። መሰልጠን መሰይጠንን ያስከተለበት አቢይ ምሳሌ በዚህ ተገልጿል። ስለዚህ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ ሌሎች የምዕራቡን ነገር ሁሉ እንደብርቅና ድንቅ አድርገን ከመቀበል ይልቅ እንደ ዘርአ ያዕቆብ ሁሉ በመንፈሳዊ እይታ አስቀድሞ መመርመር እንደሚያስፈልግ ጠቋሚ ትምህርት ነው•።

Abstract: This article, written 25 years ago and now presented with some additional materia,l attempts to indicate the emergence of new forms of inquiry in Ethiopia and in Europe. The Ethiopian philosopher, Zara Yacob and Rene Descartes, the French philosopher lived contemporaneously. Moreover, they both made similar inquiries about the existence of God. Based on their approaches to their inquiries, this paper makes a brief introduction to a subject that needs more examination by comparing the differences of the theories of both philosophers and how their approaches have deeper consequences to the latter societies they represented.

ዋቢ መነሻዎች

1. Claude Sumner, “The First Afro-Asian Philosophy Conference, Cairo 13-16 March 1978; The Rise of Philosophical Thought Within Black Africa.” Abba Salama, A Reiview of Association of Ethio-Hellenic Studies, V.10; p 242
2. ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ፤ “ሓተታ ዘዘርዓ ያዕቆብ”፣ ገጽ 42
3. ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ ፤ “ሓተታ ዘዘርዓ ያዕቆብ” ፣ ገጽ 16
4. Descartes: on Meditation Three
5.  Abba Salama,  V.10; p 242-3
6. እንደላይኛው፤ ገጽ 234::
7. ዘመንፈስ ቅዱስ አብርሃ፤ “ሓተታ ዘወልደ ሕይወት”፤ ገጽ 64::
8. ኦቶባዮግራፊ [የሕይወቴ ታሪክ]፤ ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ። ገፅ 139- 40::

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share