“የግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መምጣት” ጌታቸው ኃይሌ

የግማደ መስቀል ወደ ኢትዮጵያ መምጣት

ጌታቸው ኃይሌ

ግጽው፦

የግማደ መስቀል መገኘት በብዙ የታሪክ መዛግብት ተመዝግቧል። ይህ ጽሑፍ እንደሚያሳየው፥ ከእኛ ዘንድ የተገኘው ታሪክ በሁለት ነገር ይለያል። አንደኛ፦ መስቀሉን አፈላልጋ ስላገኘችው ስለ ንግሥት  እሌኒ ታሪክ የሚነገረው ከሌላ ዘንድ የሌለ ሰፋ ያለና ሲያነቡት የሚጥም ነው። ሁለተኛ፦ ስለግማደ መስቀሉ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ብዙ የታሪክ ሰነዶች መስክረዋል።

*****

ኢየሱስ ሃይማኖት ሲያስተምር ክስ ቀርቦበት በስቅላት ይሙት በቃ እንደተፈረደበት መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ከጊዜ ብዛት ክርስቲያኖች እየበዙ ሲሄዱ ጥንታዊ የሆነ የሃይማኖት ተጨባጭ ቅርስ መፈለግ ጀመሩ። በዚህም ምክንያት በአንዳንድ ሀገር እስከዛሬ ድረስ የቅዱስ እገሌ፥ የሐዋርያው እገሌ፥ የሰማዕታቱ እገሌ ዐጽም እየተባለ በሳጥን በሙዳይ የሚጠበቁ ከጥንቱ እንዳሉ ሰምተናል። በዓይናችን ያየንም እንኖራለን። ለምሳሌ ኢየሱስ የተገነዘበት ገርዜን (ልብስ) ነው እየተባለ ስለሚነገርለት ጨርቅ በልዩ ልዩ የዜና ማሰራጫዎች አንበናል፤ ሰምተንማል። (The Holy shroud of Turin)

ከነዚህም ቅዱሳት ቅርሶች ዋናው ግማደ መስቀል እንደሆነ ለመገመት ይቻላል። ጥያቄው እንግዲህ “ያ መስቀል ዛሬ የት ነው?” የሚል ነው። ኢየሱስ በተሰቀለ ጊዜ መስቀሉ እንደ ጠላት ይታይ እንደሆነ ነው እንጂ እንደ ዛሬው ይከበር አይመስለኝም። ለምሳሌ ዛሬ አንድ ሰው በጥይት ተደብድቦ ቢሞት የሟቹ ቤተ ዘመዶች፥ “ያንን ጠመንጃ አታሳዩን” ቢሉ እንጂ “ለማስታወሻ ስጡን” ይሉ አይመስለኝም። በዚህ ሁኔታ ኢየሱስም የተሰቀለበት እንጨት (ለጊዜው) እዚያው ወድቆ ቀርቷል። ቦታው የወንጀለኞች መስቀያ ስለነበረ እዚያው ቦታ ሌሎች ብዙዎች መስቀሎችም አይጠፉም። አንዳንዶቹም ብዙ ወንጀለኞች በየጊዜው ተሰቅለውባቸው ይሆናል። ኢየሱስ የተሰቀለ ዕለት እንኳን ሁለት ሰዎች (ፊያታዊ ዘየማንና ፊያታዊ ዘፀጋም) አብረውት በዚያው ሰዓት ተሰቅለዋል።

ከብዙ ጊዜ በኋላ ክርስቲያኖች እየበዙ ሲሄዱ “በመስቀል ዳንን፤ መስቀል መድኃኒታችን ነው፥ (መስቀል ኃይልነ፥ መስቀል ጽንዕነ፥ መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ፥)” የሚለውን በጥሬ ትርጉሙ ስላዩት “መስቀሉ ወዴት ነው?” ማለት ተጀመረ። “ተፈልጎ ተገኘ” የሚል ታሪክ ከወደ መካከለኛው ምሥራቅ ተገኝቶ ወደ ግዕዝ ተተርጉሟል። ታሪኩም በግዕዝ ድርሳን መልክ፥ በስንክሳር፥ በፍትሐ ነገሥት መቅድም ተጽፎ ይገኛል። እነዚህ ምንጮች የሚናገሩት ታሪክ አንዱ ከሌላው ሰፋ ይላል እንጂ አንዱ ከሌላው አይፋለስም። ሁሉም መስቀሉን ያገኘችው የኒቂያ ጉባኤን (325 AD) የሰበሰበው የታላቁ ቆስጠንጢኖስ (የሮማው ቄሳር) እናት ንግሥት እሌኒ መሆኗን ይናገራሉ። ታሪኩን ከፍትሐ ነገሥትና ከጸሎተ ሃይማኖት (EMML70) መቅድሞች እጠቅሰዋለሁ፤

“ሮሃ የሚሉት ሀገር ነበረ። በዚያ ሀገር ተርቢኖስ የሚሉት በጎ ምእመን ሰው ነበረ። ሶርያዊ ነጋዴ ነው፤ ሚሽቱን እሌኒ የሚሏት ማእምንት ፈራሂተ እግዚአብሔር ነበረች ይባላል። ንግድ ሲሄድ ጊዜ ግምቡን ዘግቶ ቈልፎ፥ በኖራ ደፍኖ ለቅልቆ፥ ቅጽሩንም አጽንቶ ይሄድ ነበረ። የሚሽቱም ዘለዓለም ስፍራዋ በግምብ ውስጥ ነው፤ ሰውም አያያትም አያውቃትም። እንበለ ርሱ (=ከርሱ በቀር) ከንግድ ሂዶ እስኪመለስ የዘጋውን ደጅ ማንም አይከፍተውም። ንግዳቸውም ርኁቅ ሀገር ነው፤ በ፫ት በ፪ት ዓመት እንጂ አይገቡም (=አይመለሱም) ይላል። ከዚያ ኋላ በ፫ት ዓመታቸው ከነጋዶች ጋራ ሲመለሱ ባሕርን አልፈው ከሰፈሩበት ሲጫወቱ ስብሐታተ እግዚአብሔር አግብተው (=ለእግዚአብሔር ጸሎት አድርሰው) ከእጅግ መከራ አወጻን ብለው ሲያመሰግኑ ደግሞም የቤታቸውን የሚስታቸውን ነገር አንስተው ሲጫወቱ ሚስታችን ከሌላ ወልዳ ለሞግዚት ሰጥታ (=ደብቃ) ብታሳድግ ምን እናውቃለን ሲሉ የእሌኒ ባል አመጻና (=መለሰና) የኔስ ሚስት እንዲህ ያለ ነገር አታውቅም። በጊዜያት (=በሰዓታት) በጸሎት ብትውል እንጂ እንዲህ ያለ ነገር አያውቃትም። በጎ ፍጥረት ናት፥ አላቸው። ከርሳቸው (=ከማህላቸው) ከብዙ በጎ አንድ ክፉ፥ በብዙ ክፉ አንድ በጎ አይታጣምና አንዱ ተነሳና ምነው አንተ ሚስትኽን ትንዳታለህ (=ታደንቃታለህ) ከማን ትሻላለች፤ አሁን (ሂጄ) ተገናኝቻት ብመጻስ፤ የሴት ጭምት አላት፤ ጠቃሽ ባይኖርባት (ነው እንጂ) አለው። ያም በጎ ሰው መለሰና ጠባይዋን ባያውቅ (=አታውቅም) የኔን ሚስት እንኳን ትገናኛት መልኳን ብታያት (=አታየውም) ስንኳ መልኳን፥ ድምጿን ብትሰማት ከመርከቤ ወርጄ ከቤቴ ወጽቼ ልሂድልህ። ሰብአ ነጋድ ሁሉ ምስክር ይሁን። እግዚአብሔር ምስክር ይሁንብኝ። እኔ ከወጻሁ እስክመለስ ድረስ የቈለፍኩትን ተመልሼ ብከፍተው እንጂ ሌላ አይከፍተውም። እርሷም አትወጻም። ሰውም አይገባም፥ አላቸው። ነጋዶችም አመጹና (=መለሱና) ይልሃል፥ (=እንወራረድ ይልሃል) እንድያወጻህ አይተህ ግባ (=ተወራረድ) አሉት። እርሱም የከብት (=የገንዘብ) ፍቅር ሰይጣን አሳይቶታልና ይቻለኛል አለ። ያም በጎ ሰው አመጻና (=መለሰና) ይህነን ነገር አድርገህ የመጻህ እንደሆን ወረቴም (=ሸቀጤም) ግምጃየም፥ ብሬም፥ ባርያዬም አግማላቴም (=ግመሎቼም) ያለ ሁሉ ከብቴም (=ገንዘቤም) እንበለ ልብሴ (=ከልብሴ በቀር) ሌላ[ው] ያንተ ይሁን አለው። ከዚያ ኋላ ሄደ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ለተፈናቃዮች ሀገራቸው የት ነው?

ቀድሞም (ሰውየው) ኅሱመ ምግባር (=ክፉ ሠሪ) ነበረ ይላል። ደረሰና ሀገረ ሮሃ ከተርቢኖስ ሚስት አገናኙኝ አለ። እሷንስ ስንኳን ሰው ፀሐይም አያያት አሉት። ባይሆን ከገረዲቷ ጋር አገናኙኝ አላቸው፤ አገናኙት። ከሩቅ ሀገር የመጻ ሰው ልገናኝሽ ይላል ብለሽ ንገሪያት አላት፤ ሔዳ ነገረቻት። ወትሮን ዛሬ እንዲህ ያለ ግብር ታውቂብኛለሽ አለቻት። ሔዳ አልሆነልህም አለችው። ይህን ያህል ወርቅ እሰጥሻለሁ ብሏል በያት አላት። ገብታ ነገረቻት። የተርቢኖስን ምሽት በከብት (=በገንዘብ) ብላ (ተቈጥታ) በያዘችው መታቻት፤ ደማች፤ ደሟን እያዘራች ሔዳ አይሆንልህም ስልህ አስመታኸኝ፥ ሂድልኝ አለችው። ይህን ወርቅ ላንቺ እሰጥሻለሁ ሁለቱ (ባልና ሚስቱ) የሚያውቁት ሌላ የማያውቀው ገንዘብ (=እቃ) እንዳለ ስጭኝ አላት። ይህንንስ አደርግልሃለሁ ብላ ያንገቷን ዕንቁ ወስዳ ሰጠችው፤ ይዞ ሄደ፤ እንደምን ሆነህ መጻህ አለው። ወድጃት ወዳኝ፤ ለምጃት ለምዳኝ መጻሁ አለው። አብለህ (ውሸትክን) አለው። ይኸውልህ ብሎ ዕንቊን ሰጠው። የሞኝ ሚስት በምልክት እንዲሉ፥ ልዋል ልደር፥ ልመርምር ሳይል ቢደርስባት ነው እንጂ ይህን ማን ይሰጠው ነበር ብሎ ወረቱን ለቆለት ሄደ።

ከቤቱ ገብቶ ያዝን ይቆረቆር ጀመር። ወትሮ ስንኳን ይኸን ያህል ዘመን ኑረህ መጥተህ ወጥተህ ስትመለስ ብዙ ታጫውተኝ ነበር፤  ባልንጀሮችህ ተድላ፥ ደስታ ያደርጋሉ። አንተ ታዝናለህ፥ ምን ሁነሀል አለችው። እነሱ ከነወረታቸው ገብተው ነው። እኔ ግን ስንት ዓመት የለፋሁበትን ወረቴን ማዕበል፥ ሞገድ፥ ተነሥቶ አሠመጠብኝ። ምን ላድርግ፤ እኔ ያላዘንኩ ማን ይዘን አላት። እሷም እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሣ ይላል፤ ያየነውን ቢነሣን፥ ያላየነውን ይሰጠን የለምን፥ ያንተ አምሳ ሥልሳ፥ የኔ አምሳ ሥልሳ ዘመድ ቢኖረን ከነዚያ ተበድረህ እንደቀደመው ትነግዳለህ። ምን ያሳዝንሃል፤ አለችው። እኔስ አበድርበት በነበረው ሀገር ተበድሬ፤ በከበርኩበት ሀገር ተዋርጄ አልኖርም፥ ወዳገሬ እሄዳለሁ። አንቺን ግን ሁሉ ያከብርሻል፤ ሁሉ ይወድሻል፤ ከወደድሽው ኑሪ ብሎ በነገር ይነካታል። እርሷም አንዱ አካል ሲሄድ አንዱ አካል ይቀራልን፤ እኔስ ወዴት እቀራለሁ አለችው።

ከወደድሽውማ ብሎ በሣጥን አድርጎ በገመል ጭኖ ይዟት ሄደ። ከባሕር ሲደርስ መርከብ ተከራይቶ ይዟት ገባ። ከጥልቅም ባሕር ሲደርስ መንፈሰ ቅንዓት ተነሣበት። ምነው እሌኒ ሳምንሽ ከዳሽኝ፤ ስወድሽ ጠላሽኝ አላት። አንተን ክጄ ማንን ሳምን፤ አንተን ጠልቼ ማንን ስወድ አለችው። ይኸውልሽ ብሎ ዕንቊን ሰጣት። የሰጠኸኝ ገረድ ልገናኝሽ ብሎ ላመጣው ሰው ወስዳ ሰጥታዋለች እንጂ የሰውየውን ስንኳን ግብሩን መልኩን አላየሁትም አለችው። ሥራሽ ይግደልሽ፥ ሥራሽ ያድንሽ ብሎ በሳጥን እንዳለች ገፍትሮ ከባሕር ጣላት። መንፈስ ቅዱስ መጋቢ፥ መላኩ ቀዛሬ ሁነው ከባሕር አውጥተው በበራንጥያ (Byzantium) ወደብ አኖሯት።

ቊንስጣ (Constantius Chlorus) እንዳጋጣሚ ከባሕር ዳር ነበረ፤ ሳጥኑን አይቶ ማዕበል፥ ሞገድ ከነጋድያን ነጥቆ ያመጣው ነው ብሎ አስመጥቶ ከፍቶ ቢያይ እንደ ፀሐይ የምታበራ ሴት ወይዘሮ አገኘ። አሕዛብ ለፈቲው አይቸኩልምና መንፈቅ የውስጥ ርስሐት (=ቁሻሻ) የሚያጸራ ሽቱ እያጠጣ፥ መንፈቅ የአፍአ ርስሐት (=የውጭ ቁሻሻ) የሚያጸራ ሽቱ እየቀባ አኖራት። ከዚያ በኋላ ተገናኛት፤ ቈስጠንጢኖስ (Constantine the Great) ተወለደ። በተወለደ በ፲፬ዓመት አባቱ ንጉሥ ቊንስጣ ሞተ። እሱ ነገሠ። ፍርድ አወቀ፤ ለሰው እጅግ አነጋገሡ በጀ።

ከዚያ በኋላ ቈስጠንጢኖስ በዝ ትመውዕ ፀርከ (=ቈስጠንጢኖስ ሆይ፥ በዚህ ጠላትህን ታሸንፋለህ) የሚል በአየር ነገር አየ (በመስቀል ታሸንፋለህ ሲለው ነው)። እናቱ እሌኒም በሕልም አየች። ሑሪ ሀበ ሀገረ ኢየሩሳሌም ወአርእዪ መስቀሎ ለኢየሱስ ክርስቶስ (=ኢየሩሳሌም ከተማ ሂጂና የኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ግለጪ) አላት። ይህነን ነገር ለቈስጠንጢኖስ ነገረችው። እርሱም የቀደመ ነገሩን ልብ አደረገና ሂጂ አላት። እርሷም ሄደች። ምስለ ሠራዊተ ወልዳ (=በልጇ ሠራዊት ታጅባ) ሌሊት በፋና ገሰገሰች። መስከረም ፲፮ቀን ስትሻ ስትመረምር በየሀገሩ ስታድር እስከ ጎልጎታ ደረሰች። ከዚያ ኋላ በተቀበረበት ሀገር ደርሳ ሹሙን ቄሰ ገበዙን አስራ ብታስመረምር እኛ ቢሆን አናውቅም ከአዕሩግ የሰማነው ግን በጉድፍ መጣያ ሲሉ ብለው ተመረመሩ፥ አሮጊት ቢመረምሩ ከበር ሜዳ ጉድፍ ነው ስትል ተመረመረች። ኋላም ቄስ አስመጽታ ጫን ዕጣን አስወገረችና (=አስጨሰችና) ቀኖና አስያዘች። እሷም ያዘች፤ ዕጣን ቢወግሩ አየር ወጽቶ ተመልሶ በመስቀል እራስ ላይ እንደቀስተ ደመና ተተከለ። ጢስ ከተተከለበት ብታስምስ በ፲ ክንድ የፀጋማይ መስቀል ተገኘ። የዕውር [ሰው ዓይን] ቢያብሱ አላበራም አለ። የሐንካሳ [ሰው እግር] ቢያብሱ አላረታም አለ፤ ለለምጻም ቢያብሱ አላነጻም አለ፤ ለድውይ ቢያብሱ አልፈውስም አለ፤ ሙት አላነሳም አለ። ደግማችሁ ማሱ የጌታዬ መስቀል አይደለውም አለችና ደግሞ ብታስምስ በ፲ ክንድ የየማናይ መስቀል ወጻ። እንዲያው (=እንደዚያው) አልፈውስም አለ። ደግሞ ብታስምስ ፲ ክንድ ታላቅ ደንጋይ ተገኘ፤ ደንገያን አውጽቶ ደግሞ ቢምሱ ፲ ክንድ የክርስቶስ መስቀል ተገኘ። ከዚያ ኋላ አውጽተው ለሙት ቢያስነኩት ሙት አነሳ፤ ድውይ ፈወሰ፥ ለምፅ አነጻ፤ ዕውር አበራ፥ ሐንካሳ አረታ። ያነግዜ ይህ የጌታዬ መስቀል ነው አለችና ያሬድ እንዳለ የበበት ዮም እሌኒ አጽሐሰት በእገሪሃ ወጠፍሐት በእደዊሃ መስቀል ኃይልነ፥ መስቀል መድኃኒተ ነፍስነ ብላ ስትል ረገፀች ይላል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሸዋሮቢት ከተማ ለታሪክ ምስክርነት የተረፈ ንብረት የለም፤ ሙሉ በሙሉ ወድሟል

መስቀሉን ስትፈልግ ወዲያ ወዲህ እያለ ይላላካት የነበረ ይሁዳ የሚባለውን የኢየሩሳሌም ሰው አስጠምቃ ጳጳስ አስሹማ ስሙን ኪራኮስ አሰኝታ ወደሀገሯ ተመለሰች።”

መስከረም ፲፮ ደመራ የምናከብረው ይኸንኑ እሌኒ (St. Helena 255-330 A.D.) መስቀሉን ያገኘችበትን ቀን ለማስታወስ ነው። እሌኒ ወደልጇ ስትመለስ እግረ መንገዷን በቀድሞው ባሏ በተርቢኖስ ሀገር ደርሳ ያደረገችውን እንተወውና ከዚህ ከተገኘው መስቀል ግማድ (ቁራጭ) ወደኢትዮጵያ ስለመምጣቱ እንጻፍ።

የግማደ መስቀሉ ወደኢትዮጵያ መምጣት

የዚህ የመስቀል ቁራጭ (ግማደ መስቀል) ወደኢትዮጵያ መምጣት ያፍ ታሪክ አይደለም። ብዙ የታሪክ ምንጮች መዝግበውታል። ከነዚህም ውስጥ ታሪከ ነገሥታት፤ አምባ ግሼን (ወሎ) የሚገኘው ወንጌልና ሲኖዶስ የተጻፈበት መጽሐፈ ጤፉት፣ ገድለ መርቆሬዎስ፣ እግዚአብሄር ነግሠ ይገኙበታል። መስቀሉ ወደኢትዮጵያ የመጣልን በአፄ ዳዊት ዘመን ነው። (1375-1403 ዓ.ም።)  የመስቀሉ ቁራጭና ሌሎችም ቅድሳት ቅርሳት ለዳዊት የተላከለት ከግብፅ የእስላም መንግሥት ጋራ በክርስቲያኖች መጨቆን አለመግባባት ተፈጥሮ ስለነበረ ለመታረቂያ ነው። ንጉሥ ዳዊት ከግብፁ ጳጳስ “ተገፋዕኩ ብዙኃ…ወአኮ አነ ባሕቲትየ ዘተገፋዕኩ አላ ኲሎሙ ጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት ወአብያተ ክርስቲያናት መኲሎሙ ምእመናን ክርስቶሳውያን በእዴሁ ለሥልጣነ ምስር [=ግብፅ]…” የሚል ደብዳቤ ሲደርሰው ሠራዊቱን አስከትቶ በሱዳን በኩል ገሠገሠ። ስናር ሲደርስ የግብፁ ሡልጣን ከክርስቲያኖች ጋር ታረቀ። ሌላ ደብዳቤ መጣ። ገድለ መርቆርዮስ እንደሚነግረን፦

ወበጽሐ ንጉሥነ ዳዊት እስከ ምድረ ስናር። ወሶበ ሰምዐ ዜና ምጸአቱ ሥልጣነ ምስር ፈርሀ ጥቀ ወጸበበቶ ምድር በምልኣ። ወገብረ ዕርቀ ምስለ ሊቀ ጳጳሳት በብዙኀ አስተብቊዖ ወፈነወ ሊቀ ጳጳሳት መጽሐፈ መልእክት ምሰለ መስቀለ ኢየሱስ እንዘ ይብል፤ ግባእ ውስተ ሀገርከ በሰላም እስመ ገበርኩ ዕርቀ።… “ንጉሣችን ዳዊት ምድረ ሲናር ድረስ መጣ። የመምጣቱን ዜና የግብፁ ሡልጣን በሰማ ጊዜ በጣም ፈራ። ምድር በመላዋ ጠበበችው። በብዙ አማላጅ ከሊቀ ጳጳሳቱ ጋር ታረቀ። ሊቀ ጳጳሳቱም ከኢየሱስ መስቀል ጋር እንዲህ ሲል ደብዳቤ ላከ። ወደሀገርህ በሰላም ተመለስ፤ ታርቄያለሁና።…”

ከግማደ መስቀሉ ጋር ቅዱስ ሉቃስ የሳላቸው ሰባት የማርያም ሥዕሎች፥ አንድ ቅዱስ ዮሐንስ የሳለው የጌታ ሥዕል (ኲርዐተ ርእሱ) እና መቶ ሀያ ሺህ የወርቅ ዲናር እንደተላከለት መጽሐፈ ጤፉት ይናገራል። ወርቁን ግን በኩራት አልተቀበለም። መስቀሉን ንግሥት እሌሊ ካገኘችው ጀምሮ ጉራጁ ወደ ኢትዮጵያ እስከመጣ ድረስ ያለው ታሪክ ብዙ አይታወቅም። ምናልባት ግብፆች ድርሻ አግኝተው ከዚያ ይሆናል የላኩልን። መስቀሉ የመጣው በዳዊት ዘመን መሆኑን ማስረጃዎች ሁሉ ቢስማሙም አለመግባባት የተፈጠረው በአጼ ሠይፈ አርዕድ ጊዜ ነው የሚሉ አሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፓርላማ ለምን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አራዘመ | የአብኑ አበባው ደሳለው ፓርላማውን አስጨነቀው | አብይ በቀጥታ 200 በላይ ሰዎችን አስገደለ

እነዚህ ቅዱሳን ቅርሶች በቤተ መንግሥት ሲኖሩ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ (ከዳዊት ልጆች አንዱ) ነገሠ። እሱም በሕልሙ አንብር መስቀልየ ዲበ መስቀል (=መስቀሌን ከመስቀል ላይ አስቀምጥ፥) ሲለው ሰማ። ይኸ ሕልም የሚያመለክተው የመስቀል ቅርጽ ያለውን አምባ ግሼንን (ወሎ) ነው ብሎ ከዚያ ልኮ አስቀመጠው። የግራኝ ወታደሮች እስኪመዘብሩት ድረስ ገዳሙ የነገሥታት እቃ ማከማቻና ልዑላን እንዳይሸፍቱ መጠበቂያ ነበር። ስለዚህ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ እነዚህን እቃዎች ወደዚያ ለመላክ ሕልም ማየትም ባላስፈለገው ነበረ።

መጽሐፈ  ጤፉት ውስጥ ተመዝግቦ የተገኘው የአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ደብዳቤ እንደሚመሰክረው በዚህ ንጉሥ ጊዜም ተጨማሪ የመስቀል ጉራጅና ሌሎችም ቅዱሳን ቅርሶች ወደኢትዮጵያ መጥተዋል።

የአፄ ዘርዓ ያዕቆብ ደብዳቤ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ…አሜን። ተፈነወት ዛቲ ክርታስ እምኀበ ንጉሣነ ዘርዓ ያዕቆብ ዘተሰምየ ቈስጠንጢኖስ ኀበ ኲሎሙ ማኅበረ እስራኤል ወሀበ ኲሎሙ ካህናተ ደብተራ ዘመርጡል ለእለ ትነብሩ ኀበ ደብረ እግዚአብሔር አብ ወውእቱ አቡነ ወውእቱ እምነ ወውእቱ ዓቃቤ ነፍሳቲነ። ወይእዜኒ ይዕቀብክሙ….አሜን።…

ወናሁ ፈኖነ ለክሙ ዓቢያተ ባሕርያት ዘኢይትረከብ ኢበወርቅ ወኢበዕንቊ ወኢበምንትኒ ንዋያተ ዓለም ዘኢይትረከብዎን ፈኖነ ለክሙ መስቀሎ ለወልደ እግዚአብሔር ዘተሰቅለ ቦቱ እግዚአ ሰማያት ወምድር ወከለሜዳሂ ዘአልበስዎ በዕለተ ስቅለት ወሰፍነግሂ ዘአስተይዎ ቦቱ ብሂአ ዘምስለ ሐሞት ወከርቤ ቱሱሕ ዘወፀአ በመዋዕሊነ እምብሔረ አፍርንግ ወተካፈልዎ ሰብዓቱ ነገሥተ አፍርንግ። ወለአቡየሂ ዳዊት ፈነው እምውእቱ መስቀል ዘብዓቱ መስቀል ወይእዜኒ ፈነው ለነ እም ውእቱ መስቀል ዘምስለ ከለሜዳ ወሰፍነግ ከለሜዳሰ ወሰፍነግ። ኢወቀአ እምቅድመዝ ዘእንበለ ይእዜ በመዋዕሊነ።… (B.L.Or. 481, ff.208-209)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ፩ አምላክ።… አሜን።

ይህቺ ደብዳቤ ቈስጠንጢኖስ ከተባለው ንጉሣችን ከዘርዓ ያዕቆብ ለእስራኤል ማኅበር ሁሉ (የነገሥታቱ ዘሮች እስራኤል ነበረ የሚባሉት) እንዲሁም በደበረ እግዚአብሔር አብ (ግሼን) መቅደስ ለምትኖሩ ካህናት ሁሉ ተላከች። እሱ (እግዚአብሔር) አባታችንም እናታችንም ነው። የነፍሳችን ጠባቂ ነው። አሁንም ይጠብቃችሁ።…አሜን።….

እነሆ በወርቅ፥ በዕንቊ እንዲያውም በማንኛውም የዚህ ዓለም ገንዘብ የማይገኙ ታላላቅ ቅርሶች (?) ልከንላችኋል። የሰማዮችና የምድር ጌታ የተሰቀለበትን የእግዚአብሔር ልጅን መስቀል፥ የተሰቀለ ዕለት ያለበሱትን የለምድ ልብስ፥ መጻጻ ሐሞት፥ ከርቤ በጥብጠው ያጠጡበትን ሰፍነግ ልከንላችኋል። (እነዚህ ሁሉ) በኛ ዘመን ከፈረንጅ ሀገር የመጡ ናቸው። ሰባቱ የፈረንጅ ሀገር ንጉሦች ተካፍለውት ነበር። ለአባቴ ለዳዊት ከዚህ መስቀል ላይ (ቈርጠው) ልከውለት ነበር። አሁን ደግሞ ለኛ ከዚሁ መስቀል ላይ (ቈርጠው) ከከለሜዳውና ከሰፍነጉ ጋር ላኩልን። ከለሜዳውና ሰፍነጉ አሁን በኛ ዘመን እንጂ ከዚህ በፊት (ወደኛ ሀገር) አልመጣም ነበረ።…

ደብዳቤው ረጅም ነው። ጥናቱ ስላላለቀልኝና ላሁን ጽሑፍ ይህ ስለሚበቃ በአጭሩ ጠቅሸዋለሁ።

ዘርዓ ያዕቆብ በሱ ዘመን የመስቀሉ ጉራጅ መምጣት ምክንያት አድርጎ ስለመስቀሉ ክብር መስከረም ፳፩፥ መጋቢት ፲፥ ነሐሴ ፲፬፥ መስከረም ፲፯፥ መስከረም ፲፮ እንዲከበሩ በደብዳቤው ውስጥ አዟል። መስከረም ፳፩ ቀን (የማርያም ዕለት) የሚከበረው መስቀሉ በዚያን ቀን ስለመጣለት፥ መስከረም ፲፮ ቀን የሚከበረው የጥንት (የእሌኒ) በዓል ስለሆነ፥ መስከረም ፲፯ ቀን የሚከበረው በአባቱ በዳዊት ዘመን መስቀሉ ወደኢትዮጵያ ስለመጣ (ዘወፅአ መስቀል በመዋዕለ አቡየ ዳዊት) መሆኑን አብራርቷል። በአፄ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን ሌሎቹ ቅርሶች መጥተው ይሆናል እንጂ ግማደ መስቀሉ በሱ ዘመን መምጣት ተጨማሪ መረጃ አላገኘሁም።

Abstract

The story of the finding of the Cross is preserved in many Apostolic Churches, including the Ethiopian Orthodox Tewahido Church. The Amharic text on the subject, edited here, differs from other sources in that it contains a new information on the rise of Saint Helen who toiled to discover the Cross. Furthermore, the article refers to sources that support the local tradition that a piece of the Cross was sent to Ethiopia from Egyptian authorities as present to king Dawit (1379-1413).

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share