እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ልዩ ልዩ ፀጋዎችን አድሏል። እነሆ ለአንዱ የማስተማር ፀጋ፣ ለሌላው የመምከር፣ ለአንዱ የህክምና ጥበብ፣ ለሌላው የስነ ፅሁፍ ችሎታ ፣ ለአንዱ የማስተዳደር ለሌላው ስነ ስእል፣ ለአንዱ የወታደርነት ጥበብ ለሌላው የማስተባበር፣ ለአንዱ የቴክኒክ ስራ ለሌላው የንግድ ስራ……. ወዘተ. ለሰው ልጆች ሁሉ ፈጣሪ ፀጋዎችን አድሏል። ያለ ፀጋ ወደዚህ አለም የመጣ ሰው የለም። ሁሉም ፀጋዎች ውብና ድንቅ ናቸው።
ታዲያ እነዚህ ውስጣችን ያሉ ፀጋዎች ከፍተኛ ድምፅ አላቸው። ሁላችን አንደኛ ደረጃ ወደ ሆነው ፀጋዎቻችን እንድናዘነብል ውስጣችን ዘወትር ይገፋናል። ይሁን እንጂ በተለይ እኛ ድሃ ሃገራት ያለን ሰዎች በውስጣችን ያለውን ልባችንን የሞላውን ፀጋ ከመከተል ይልቅ ጥሩ ገበያ ወደ አለው የስራ መስክ ራሳችንን እናሰማራለን። በዚህ ምክንያት ከያኒው የአስተዳዳሪውን ቋንቋ ያጠናና እያስመሰለ አስተዳዳሪ ሆኖ ኑሮውን ይገፋል። ግንበኛው ፓለቲከኛ ይሆናል። ወታደሩ መካሪ ይሆናል። አስተማሪው ደላላ ይሆናል። ሃኪሙ ነጋዴ ይሆናል……።
ታዲያ ይህ መዘበራረቅ በሃይል ሲከሰት በማህበራችን ውስጥ ትርምስ ይበዛል። የሰው ልጆች ማህበር መስርተን ስንኖር በማህበራችን ውስጥ ለምንሰራቸው የጋራ ስራዎች ሁላችን በፀጋችን ልክ ካልተሰለፍን በዚያ ማህበር ውስጥ የፀጋዎች አልተገናኝቶም ይፈጠራል። ይህ የፀጋ አልተገናኝቶም ሲበዛ ደግሞ ኑሯችን ሁሉ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደ ኋላ እያልን ቁልቁል እንሄዳለን።
አንድ ታሪክ ትዝ አለኝ። በአንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መባ በሚሰበሰብበት ጊዜ ለስለስ ያለ ሙዚቃ የሚጫወቱ አንድ አገልጋይ ነበሩ። እኚህ ሰው በዚህች አጭር የፅሞና ጊዜ በሚጫወቱት መዝሙራዊ ሙዚቃ የብዙዎችን ሰዎች መንፈስ ወደ ጌታ ያቀናሉ። ከቤተ ክርስቲያኒቱ መስራቾች አንዱ ናቸው። ታዲያ ከእለታት አንድ ቀን እኔም መስበክ አለብኝ አሉ ይባላል። እኔም እንደሁላችሁም መስራችና ነባር አገልጋይ ነኝና እባካችሁ ልስበክ አሉ። የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎች ህፍረት ይይዛቸውና አንድ የስብከት ፕሮግራም ተሰጣቸውና እኚህ ሰው ፑልፒቱን ያዙ። የሚያሳዝነው በዚህ ፕሮግራም ላይ ለመድረኩ የማይመጥን ነገር በመናገርና የማይሆኑ ነገሮችን በመዘባረቅ ጉባኤውን አስደነገጡ። አሸማቀቁ። ሽማግሌዎችም አፈሩ። ደግነቱ እኒህ ሰውም ይህ ነገር ታወቃቸው። ስለሆነም ማንም ደፍሮ ሳይናገራቸው ይቅርታ እኔ ይሄ ቦታየ አይደለም ብለው ወደ ሙዚቃቸው ተመለሱና አልተገናኝቶምን ወደ ተገናኝቶም ቀየሩ። ዘይደዋል።
አደጉ የሚባሉት ሃገሮች ስኬት ይሄ ነው። በተቻለ መጠን ሰው ባለው ፀጋ እንዲሰራ ለዜጎች በሮች ክፍት ናቸው። ሁሉም ከተፈጥሮ አንደኛ ፀጋውና ጥሪው ጋር ሲገናኝ ሃገር ያብባል። ስለዚህ ሃገራችን ውስጥ በተለይ በአሁኑ ሰዓት የምናያቸው ችግሮች አብዛኛው ችግር አልተገናኝቶም ሆኖ በግልፅ ይታያል። እግዚአብሄር ይርዳንና ስራና ሰራተኛው ይገናኝልን። ከፀጋዎች አልተገናኝቶም ይታደገን።