አማራና አፋር ክስ መመሥረት አለባቸው – አንዱ ዓለም ተፈራ

አርብ፣ ጥር ፳ ፯ ቀን፣ ፳ ፻ ፲ ፬ ዓ. ም. (2/4/2022)
አንዱ ዓለም ተፈራ፤

በአንድ ኢትዮጵያና በአንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ የፀና እምነት አለኝ። አንድ አገር፣ አንድ ሕዝብ መሆናችንን አጥብቄ እቀበላለሁ። አንድ መንግሥትና አንድ ሰንደቅ ዓላማ ብቻ እንዲኖርም እመኛለሁ። ይህ የኔ ምኞት ነው። በኢትዮጵያ፤ ይህ እንደ ነውር የሚታይበት ወቅት ላይ ደርሰናል። በኔ እምነት፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር የወረረው የኢትዮጵያን ሕዝብና መሬት እንጂ፤ የሁለት ክልልን ሕዝብና መሬት አይደለም። በርግጥ አካባቢው እውቅ ነው። አንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግሥት ቢኖር ኖሮ፤ ይህን ወረራ ገና ሲጠነሰስ ባጭሩ ማስቀረት ይቻል ነበር። አንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ መንግሥት ቢኖር ኖሮ፤ ባጭር ጊዜ ሕዝቡን አነሳስቶ፤ ይሄን ወራሪ ድባቅ ማግባት ይቻል ነበር። ይህ ማለት፤ መንግሥት በቂ የገንዘብና የውጭ አገራት ድጋፍ ነበረው ማለት አይደለም። በትክክል የገንዘብ አቅሙንና በውጪ አገራት የተሴረበትን ጉንጉን ተንኮል ሁላችን እናውቀዋለን፤ ቀላል አልነበረም። ይህ ሁሉ ግን፤ ከሕልውና አንጻር ሲታይ፤ ቦታ ያጣል። መጀመሪያ ኢትዮጵያ መኖር አለባት። ያየነው ይሄን አልነበረም። መጀመሪያ ወረራውን፤ ትግሬዎች በአማራና በአፋር ላይ ያደረጉት የሚል ትርክት ተነፋ። የትግራይ ሕዝብ አይደለም ወረራውን የፈጸመው። አዎ! በአማራና በአፋር ወገናችን ላይ ከፍተኛ ጥፋት ደረሷል። ይባስ ብሎ ደግሞ፤ ይሄን ጥፋት ያደረሱት የአረመኔው ቡድን መሪዎች፤ በነፃ ተለቀቁ። ዘርፈው የወሰዱት ንብረት ተመለሰላቸው። ከፊሎቹ ይሄ ሲደረግላቸው፤ ከፊሎቹ አሁንም በአማራውና በአፋሩ ላይ ጭፍጨፋቸውን አጦዙት። እነ ስብሃት መቀሌ ሲገቡ ተደለቀላቸው። በአንጻሩ የአማርና የአፋር እናቶች እንደገና ሰቆቃቸው ጨመረ። የአማራና የአፋር ብልፅግና መሪዎች የአዲስ አበባው መሪ መስተጋብሮች በመሆን፤ ተልዕኮ አስፈጻሚ ብቻ ሆነው ተገኙ! ታዲያ እንዴት ብላ ነው የአማራና የአፋር እናት ከዚህ ግፍና በደል ወጥታ ሕልውናዋን የምታገኘው! ይህ ነው የዚህ ጽሑፍ መልዕክት።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የመሪ ያለህ! - በዶ/ር ፍቅሬ ቶለሳ (ወቅታዊ ግጥም)

መንግሥት፤ በሕዝቡ ፈቃድ፤ የሕዝቡን ፍላጎት የሚፈጽም አካል ነው። ሕዝብ የመንግሥትን ፈቃድ ፈጻሚ አይደለም። መንግሥት ሲሳሳት ጠያቂው ሕዝብ ነው፤ የመንግሥት ባለቤት ሕዝቡ ነውና! ባላለቀው ጦርነት የነስብሃት መፈታትና ለድርድር መዘጋጀት፤ የአማራውንና የአፋሩን ጩኸት ዋጋ ማሣጣት ነው። መንግሥት እየተሳሳተ ብቻ ሳይሆን፤ ለአማራውና ለአፋሩ ደንታ ቢስ እየሆነ ነው። ስለዚህ፤ አፋሩና አማራው በደረሰበትና እየደረሰበት ባለው እልቂት፤ አጥፊዎችን ለፍርድ የማቅረብ ግዴት አለበት። ያለ ርህራሄ ሕዝቡን የፈጁ፤ ንብረቱን የዘረፉና ሰቆቃውን ያበዙ ሁሉ መጠየቅ አለባቸው! የአፋሩና የአማራው ወገናችን፤ እኒህን ወንጀለኞች ለፍርድ ማቅረብ አለበት። የማዕከላዊው መንግሥት በቦታው አለመገኘቱና የክልል መሪዎች የማዕከላዊው መንግሥት ጉዳይ አስፈጻሚዎች የሆኑበት እውነታ፤ ሕዝቡ የራሱ መዋቅር አበጅቶ እነ ስብሃትን ለፍርድ የማቅረብ የሕልውና ግዴታ አለበት። ይሄን የሚያደርጉት ኢትዮጵያን ለማዳንና የራሳቸውን ሕልውና በማያዳግም መንገድ ለማስረገጥ ነው። ክስ መሥራቾች የትም ሊሆኑ ይችላሉ። ክስ መሥራቾች ጥቂቶች ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ። ብቻ ይጀመር! ይህ ወደፊት እንዳይሄድ እንቅፋት የሚሆን ካለ፤ ይህ ግለሰብም ሆነ ቡድን፤ የአማራና የአፋር ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ነው። አባሪነቱም ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ጋር ነው።

ክሱን በሚመለከት!

የመጀመሪያው ጥያቄ ጥፋት ደርሷል ወይ? ነው። ይሄን አሌ የሚል የለም። ይልቁንስ የጥፋቱ መጠን ምን ያህል ነው? የሚለውን መጠየቅ ይቀላል። የሟቹን ቁጥር፣ የግፉን ዓይነት፣ የግድያውን ቦታ፣ ከርስቱ የተፈናቀለው ወገናችን ያጣው ማንነቱና ሕልውናው፣ የተሰረቀው ንብረትና የወደመው ንብረት፣ አረመኔነትን አንድ ደረጃ ወደ ላይ ከፍ አድርጎታል። ታዲያ ለምን ክስ አይመሠረትም! እናም ጠበቆች፣ ሕግ አዋቂዎችና ተቆርቋሪዎች ተነሱ! እነሱን ለማስፈታት በድብቅ የተደረገው ስምምነት፤ ግልጥነት የጎደለው፣ ስውር፣ ፀረ-ሕዝብና ጸረ-ኢትዮጵያ ስለሆነ፤ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት የለውም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የግብረሰዶማዊነት አደጋ - (የአቡነ ሳሙኤል ወቅታዊ ጽሑፍ)

ለሚገጥሙ እክሎች!

ከባለቤቱ ከትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ሌላ፤ በመንግሥት መዋቅር ውስጥም ሆነ ከዚያ ውጪ፤ ከውጪ አገራትም ሆነ ድርጅቶች፤ ጫናው ቀላል አይሆንም። ይህ ግን ከተያዘው ዓላማ አኳያ ሲታይ፤ በጣም ቀላል ነው። አፋርና አማራ ይሄን አድርገው ወደ ስብዕናቸው ካልተመለሱ፤ ይህን እንደ አዙሪት ይዘን የምንቀጥለው አባዜ ይሆናል። ለቅሶን ወደ ውስጥ ቢዉጡት እንጀትን በጣጥሶ አእምሮ ያስታል። ተመልሰን ወደ ጦርነት! ምኞት መመሪያ እንጂ ተጨባጭ እውነታ አይደለም። በምኞት ሰላም አይመጣም! በምኞት ያጣነውን አናገኝም! እናም አፋሩና አማራው፤ በተቆርቋሪ ልጆቻቸው፤ በጥብቅ ተደራጅተውና በሕግ ተመሥርተው፤ ይሄን ግብ ላይ እንደሚያደርሱት ጥርጥር የለኝም!

ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን ናት። ልጆቿ ይታደጓታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share