የዘውድ ስርአት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ማስተባበር ይችላል! – ግዛቸው ጥሩነህ (ዶ/ር)

ግዛቸው ጥሩነህ (/)
ጥር 13 ቀን 2014 .

ከአንድ አመት በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄደው የእርስበርስ ጦርነት፤ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ህይዎታቸውን ከማጣታቸውም በላይ፤ እጅግ በጣም ከፍ ያለ የንብረት፤ የትምህርት ተቋማት፤ ሆስፒታሎች፤ ክሊኒኮች፤ ፋብሪካዎችና የመንግስት መስሪያቤቶች ውድመት ተከትሏል፡፡ በዚህም ጦርነት፤ ለህሊና የሚዘገንኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ከመታየታቸውም በላይ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ ህዝቦች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ይህንንም በማስተዋል፤ በቅርቡ የኢትዮጵያ መንግስት የሀገራዊ ምክክር እንደሚደረግ እቅድ እንዳለው ገልጿል፡፡ እኔም ለዚህ ድንቅ አላማ ይረዳል ብዬ የማስበውን ሀሳብ ለማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ይኧውም ስላምንና አንድነትን በኢትዮጵያ ውስጥ ለማምጣት የሚረዳው፤ የሰለሞናዊው ንጉሣዊ ስርአት ይመለስ የሚል ነው፡፡  ከንግሥት ማክዳ ና ከንጉሥ ሰለሞን ግዜ እንደተጀመረ የሚነገርለት፤ ከዚያም በጥንታዊው የዳሞት (ዳማት) መንግሥት እንደቀጠለ የሚታሰበውና በኋላም በትግራይና በሸዋ ግዛቶች ውስጥ ገንኖ የነበረው የሰለሞናዊው ስርዎመንግሥት፤ ከኢትዮጵያ ታሪክ ጋር አንድ አካል ሆኖ የኖረ ነው፡፡ ይህ ጥንታዊና እስከቅርብ ግዜ ድረስ ስልጣን ላይ የነበረው የዘውድ ስርአት በኢትዮጵያ ውስጥ ቢመለስ፤ የሀገሪቱን አንድነትና የህዝቦቿን ህብረት ማጠናከር ይችላል፡፡

የዲሞክራሲ ምሁር የሆነው ሲይመር ማርቲን ሊፕሰት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1959 ዓ.ም ሲጽፍ፤ በአለም ላይ በወቅቱ ከነበሩት 12 ዲሞክራሲያዊ ሀገሮች ውስጥ፤ አስሩ በህገመንግስታዊ ዘውድ ስርአት የሚመሩ እንደነበሩና ከነዚህም ውስጥ እንደ ታላቋ ብሪታኒያ፤ ሆላንድ፤ ስዊድን፤ ኖርዌና ዴንማርክ እንደሚገኙባቸው አትቷል፡፡ በሊፕሰት አስተሳሰብ፤ እነዚህ ሀገሮች አዲስ የመሰረቱትን የዲሞክራሲ ስርአት በህዝብ እንዲደገፍና እንዲታቀፍ የረዳቸው፤ ህገመንግስታዊ የሆነ የዘውድ ስርአት እንዲኖራቸው በመወሰናቸው ነው፡፡ ህገመንግስታዊው የዘውድ ስርአት፤ በተለይም መሳፍንቱ፤ ባላባቱ፤ የቤተክህነት ሰዎችና ሌሎችም ወግ አጥባቂ (ኮንሰርቫቲቭ) ቡድኖች፤ ዲሞክራሲን እንዳይፈሩና እንዲያቅፉት ገፋፍቷቸዋል፡፡ በሊፕሰት ግምት፤ የዲሞክራሲያዊው ስርአት ደግሞ፤ ወግ አጥባቂ ቡድኖችንና እንደ ሰራተኛ፤ የገንዘብ ከበርቴና ምሁራን ያሉትን ለውጥ ፈላጊ (ፕሮግሬሲቭ) አካሎች፤ በመካከላቸው ትብብርና መቻቻል እንዲኖር ረድቷቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ግን፤ የዘውዱ ስርአት በ1966 ዓ.ም በተነሳው አብዮት ምክንያት ወድቋል፡  አብዮቱ ሊፈነዳ የቻለው፤ የቀዳሚዊ ኃይለ ሥላሴ መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ ወቅታዊ የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጦች ለማምጣት ባለመቻሉ ነው፡፡ እንደ መሳፍንቱና የመሬት ከበርቴ ያሉት ወግ አጥባቂ ቡድኖችም በተለያዩ ምክንያቶች ከአብዮቱ ፍንዳታ በኋላ ጠፍተዋል ወይም ተዳክመዋል፡፡ ንብረታቸውም በደርግ መንግስት ተወርሷል፡፡ በፈረንሳይ (1789)፤ በሩሲያ (1917)፤ በቻይና (1911) ና በመሳሰሉት ሀገሮች የተካሄዱት አብዮቶችም፤ ለነበሩት የዘውድ ነገስታት መውደቅ ምክንያት ሆነዋል፡፡ ሆኖም ግን፤ የሰለሞናዊው ስርዎመንግስት ወድቆ ይቀራል ለማለት ያዳግታል፡፡ አርኖልድ ቶይንቢ የተባለው ምሁር እንደጻፈው፤ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ሀገሮች ሁሉ ልዩ የሚያደርጓት ሁለት ነገሮች አሉ፡፡ አንደኛ፤ በአውሮፓውያን የቅኝ ግዛት ያልወደቀች አፍሪካዊ ሀገር እሷ ብቻ ናት፡፡ ሁለተኛ፤ የሰሜንና የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች በ7ተኛው ክፍለዘመን የእስልምና ሃይማኖት ተቀባይ ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያ የክርስትና ሃይማኖቷን ይዛ የቀረች ሀገር ናት፡፡ ቶይንቢ ባለው ላይ ለመጨመር፤ የሰለሞናዊው ስርዎመንግስት በዛግዌ ስርዎመንግስት ተሸንፎ ከ11ኛው እስከ 13ተኛው ክፍለዘመን ተዳክሞ ከቆየ በኋላ፤ በ1262 ዓ.ም ወደ ስልጣን ተመልሷል፡፡ በዘመነ መሳፍንት ግዜም የሰለሞናዊው ስርዎመንግስት ለ68 አመታት ቢቋረጥም፤ ከ1845 ዓ.ም ጀምሮ በአፄ ቴዎድሮስ፤ በአፄ ዮሃንስና በአፄ ምኒልክ ጥረት ስልጣኑን ተቀዳጅቷል፡፡ ታዲያ ታሪክ ራሱን ደጋግሞ፤ የሰለሞናዊው ስርዎመንግስት እንደገና እንዲመለስ ያደርግ ይሆን? ሺህ አመታት ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ታሪክ፤ ሚዛናዊ ክብደቱ አይሎና የብዙ ኢትዮጵያውያንን ፍላጎትና ዝንባሌ አሳድጎ፤ የዘውዱን ስርአት ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ እንዲመለስ ያደርገው ይሆን?

ተጨማሪ ያንብቡ:   በጦርነት እየተዳከመች የምትገኘው ኢትዮጵያ ምን አይነት የጦርነት ኢኮኖሚ መርህ ያስፈልጋታል? -  አክሎግ ቢራራ (ዶር)

የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት ከሆነ፤ የዘውዱ ስርአት ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ መቋቋም ይችላል፡  ህገመንግስታዊ ያልሆነ የዘውድ ስርአት ግን ግዜ ያለፈበት በመሆኑ ተመልሶ የመምጣት እድል  አይኖረውም፡፡ የህገመንግስታዊው ዘውድ ስርአት ዋናው ሃላፊነት፤ ነገስታቱ የኢትዮጵያ አንድነትና ባህል ምልክት እንዲሆኑ ነው፡፡ የዘውድ ስርአቱ፤ ዘመናዊ ከሆኑት የሰውልጅ እኩልነትና ግለሰባዊ ነጻነት (ወይም ዲሞክራሲ) ጋር መሄድ የሚችለው፤ ህገመንግስታዊ ሲሆንና ቀን በቀን ከሚካሄደው የፖለቲካ ስራ ራሱን ማግለል ሲችል ብቻ ነው፡፡ ህገመንግስታዊ የዘውድ ስርአት፤ ንጉሥ እንጂ ንጉሠነገስት አያስፈልገውም፡፡ ንጉሠነገስት የሚለው ቃል የሚያመለክተው፤ በንጉሠነገስቱ ስር ያሉ ንጉሦች በሀገሪቱ ውስጥ እንዳሉ ነው፡፡

በርግጥ የዘውድ ስርአቱን መመለስ የማይፈልጉ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ መገመት አያስቸግርም፡፡ ለምሳሌ እኒህ ግለሰቦች፤ የዘውድ ስርአቱ ግዜ ያለፈበት ነው ሊሉ ይችላሉ፡፡ የኢትዮጵያ አብዮት ፈንድቶ፤ ከ1966 እስከ 1983 ዓ.ም የተካሄደውን ለውጥ ሲያዩና ከአብዮቱም በኋላ የተቋቋሙትን የሪፓብሊክ መንግስታት ሲያስቡ፤ የዘውድ ስርአቱን መመለስ ላይደግፉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ የተካሄደውን የሀገሪቱን የፖለቲካ ታሪክ ስናይ፤ ሪፓብሊኳ ኢትዮጵያ ብዙ ችግር እንደደረሰባት፤ እንዲያውም የሚያሳዝን ስቃይ ውስጥ የወደቀች መሆኑን ማጤን እንችላለን፡፡ በደርግ ግዜ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ አልቋል፡፡ የሀገሪቱ የወደፊት ንብረትና አለኝታ ይሆናል ተብሎ የታሰበው የተማረው ህዝብ ተጨፍጭፏል፡፡ በኢህአዴግም ሆነ በአሁኑ የብልጽግና ፓርቲ ግዜ ደግሞ የኢትዮጵያ አንድነት አዳጋ ላይ እየወደቀ ነው፡፡ የዘርና የክልል ፖለቲካ፤ ከኢትዮጵያዊነት በላይ እየታየ በመምጣት ላይ ነው፡፡

በተጨማሪም እንደ ኦሮሞ ካሉ ብሄረሰቦች የተወለዱ አንዳንድ ግለሰቦች፤ ሰለሞናዊው የዘውድ ስርአት የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ባህል የሚወክል አይደለም ሊሉ ይችላሉ፡፡ በርግጥ ሰለሞናዊው ስርዎመንግስት፤ በመካከለኛው ሰሜንና በሰሜን ኢትዮጵያ ከሚገኙት የአምሀራና የትግሬ ብሄረሰቦች ባህል ጋር ተሳስሮ የመጣና ያደገ ነው፡፡ ይህም ሆኖ፤ ሰለሞናዊው ስርዎመንግስት ከዛሬ 300 አመታት አካባቢ ከነገሱት ከአፄ እያሱ (1723-1747) ዘመነመንግስት ጀምሮ ከኦሮሞ ብሄረሰብ ጋር ተዋልዷል፡፡ የአፄ እያሱ ባለቤት ኦሮሞ ስለነበሩ፤ ልጃቸው አፄ እዮአስ (1747-1761) ግማሽ ኦሮሞ ነበሩ፡፡ በቅርብ ግዜ የሆነውን ብናይ፤ አፄ ኃይለ ሥላሴ በእናታቸው፤ እቴጌ መነን አስፋው በአባታቸው ኦሮሞነት እንደነበራቸው ይነገራል፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ የልጅ ልጅ ልዕልት ሰብለ ደስታም፤ ኦሮሞውን ደጃዝማች ካሳ ወልደማሪያምን አግብተው ልጆች ወልደዋል፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ልጅ ልዑል ሳህለሥላሴም፤ ኦሮሞዋን ልዕልት ማጽንተ ሃብተማርያምን አግብተው ነበር፡፡ የአሁኑም የኢትዮጵያ ዘውድ ምክርቤት ፕሬዘዳንት፤ ልዑልነታቸው ልዑል ኤርሚያስ ሳህለሥላሴ፤ የልዕልት ማጽንተ ሃብተማርያምና የልዑል ሳህለሥላሴ ልጅ ናቸው፡፡ ባጭሩ፤ የኦሮሞ ህዝብ የሰለሞናዊውን ስርዎመንግስት የራሱ አድርጎ የመቁጠር መብት አለው ማለት ነው፡፡ ዳነልድ ለቪን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1974 ዓ.ም በጻፈው መጽሃፉ በትክክል እንዳስቀመጠው፤ ኢትዮጵያ በግዜ ብዛት የብዙ ብሄረሰቦች ቅልቅል እየሆነች የመጣች ሀገር ናት፡፡ ስለሆነም የኦሮሞ ህዝብ በዚህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ሂደትና ባህላዊ ውህደት ትልቅ አስተዋጾ አድርጓል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በሳይንስና በፍልስፍና መነፅር መታየት ያለባቸውና መልስ የሚያስፈልጋቸው የብሄረሰብ፣ የጭቆናና የማንነት ጥያቄዎች !!

ሌላው ደግሞ፤ የሰለሞናዊው ስርዎመንግስት ነገሥታት ሃይማኖት ክርስትና መሆኑ ነው፡  ስለሆነም የእስልምና ተከታይ የሆኑት ኢትዮጵያውያን፤ የዘውድ ስርአቱን መመለስ ሊደግፉ ይችላሉ ዎይ? በርግጥ የሰለሞናዊው ነገስታትና በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የእስልምና ተከታይ ብሄረሰቦች፤ ከ13ተኛው ክፍለዘመን ጀምሮ፤ ግጭትም ሰላማዊ ግንኙነትም እንደነበራቸው ታሪክ ይነግረናል፡፡ ለምሳሌ በአፄ አምደጽዮን (1297-1327) ዘመነመንግስት፤ የአዳል ህዝብ መብቱን ለማስከበር ወደኋላ እንደማይል ንጉሠነገስቱ ሲረዱ፤ ለዚህ ኩሩ ብሄረሰብ የራስ አስተዳደር መብቱን እንደጠበቁለት ይነገራል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከአለቅሳንደሪያ ጳጳስ እንዲመጣላት በጠየቀች ቁጥር፤ የግብጽ ሱልጣኖች የኢትዮጵያን ነገስታት በሀገራቸው ውስጥ ያለውን የእስልምና ተከታይ የሃይማኖት መብት እንዲጠብቁ ይጠይቋቸው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ነገስታትም ቃላቸውን ይጠብቁ እንደነበር ይነገራል፡፡ ከሁሉም በላይ፤ በኢትዮጵያ ክርስትያኖችና እስላሞች መካከል በተለይም ከ20ኛው ክፍለዘመን ጀምሮ ይህ ነው ለማለት በቀላሉ የማይቻል፤ የመቻቻልና የመከባበር ባህል በመካከላቸው ለመኖሩ ጥርጥር የለውም፡፡ ሆኖም ግን የዘውድ ስርአቱን መመለስ፤ የእስልምና ተከታይ የሆኑት ኢትዮጵያውያን ምን ያህል እንደሚደግፉት በወቅቱ ለማወቅ ያስቸግራል፡፡ አንድ ነገር ግን ይታወቅ፡፡ የዘውድ ስርአቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ተመልሶ ሊቋቋም የሚችለው፤ በሀገሪቱ ውስጥ ሙሉ የሃይማኖት ነጻነት መኖር ሲችል ብቻ ነው፡፡

እንግዲህ ዶ/ር ጌታቸው መካሻ በ1983 ዓ.ም በኢትዮጵያን ሪቪው መጽሄት ውስጥ በእንግሊዝኛ ያሳተሙትን ጽሁፍ ልጥቀስ፡  በዚህ አርቆ አስተዋይነት ላይ በተመረኮዘ የጽሁፋቸው ርእስ (እውነተኛ ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ መምጣቱን በቅርብ እንረዳለን)፤ ከደርግ ውድቀት በኋላ ዲሞክራሲ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመጣ ከተፈለገ፤ የዘውድ ስርአቱ መመለስ አለበት ብለዋል፡፡ ሆኖም ግን የዶ/ር ጌታቸውን ምክር በወቅቱ የነበሩ የፖለቲካ ሰዎች አልተቀበሉትም፡፡ አሁንም ቢሆን የኒህን ምሁር ምክር ለመቀበል ግዜ አለ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  “ኩሽ!” እያላችሁ ምን ያንኮሻኩሻችኋል? - ወንድሙ መኰንን, ዶ/ር

ሰለሞናዊው የዘውድ ስርአት ቢመለስ፤ ለኢትዮጵያ ህዝብ ጠቃሚ ንብረት እንጂ ጉዳት አምጪ ተቋም አይሆንም፡፡ ነገስታቱ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ህብረት አጠናካሪ አካልና አባታዊ ምስል ሆነው ሁሉንም የሀገሪቱ ብሄረሰቦች ማገልገል ይችላሉ፡፡ የባህልና የታሪክ ምልክቶችና አካሎች በመሆን፤ ነገስታቱ በሀገሪቱ ውስጥ በመዳከም ላይ ያለውን የመተማመን፤ የመከባበርና የመቻቻል ባህሪዎች እንደገና እንዲዳብሩ ይረዳሉ፡፡ ነገስታቱ፤ ለሀገሪቱ የፖለቲካ ስርአት ህዝቡ ድጋፍ እንዲሰጥ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ህገመንግስታዊ የዘውድ ስርአት በኢትዮጵያ ውስጥ ከተቋቋመ፤ በሀገሪቱ ውስጥ የጠነከረ ዲሞክራሲ ይሰፍናል፡፡

 


ይህ ጽሁፍ በ2008፤ 2011 ና 2014 ዓ.ም በእንግሊዝኛ ቋናቋ በኢትዮጵያ ማህበራዊ መጽሄቶች ካሳተምኩት የተተረጎመና የተሻሻለ እንደዚሁም የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ የዳሰሰ ነው፡፡ የእንግሊዝኛውን ጽሁፌን ለማንበብ ወይም የተጠቀምኩባቸውን የዋቢ ጽሁፎች ለማየት ከፈለጉ በሚከተለው ርእስ ያገኙታል [An Institution That Can Unite All Ethiopians].

 

 

2 Comments

  1. ውድ ወንድሜ ዶ/ር ግዛቸው ጥሩነህ፣

    “የዘውድ ስርዓት ሁሉንም ኢትዮጵያውያን ማስተባበር ይችላል” በሚለው አርዕስት ስር የጻፍከውን መጣጥፍህን በዘሃበሻ ላይ ውጥቶ አነበብኩት። ሃሳብህ ማለፊያ ነው። ችግሩ ግን ንጉስ ወይም ንጉሰ-ነገስት ከየት ማምጣት ይቻላል? ምናልባት በጭንቅላትህ ውስጥ የመዘገብካቸው ለንጉስነት የሚታጩ ሰዎች ሊኖሩ ይችሉ ይሆናል። እኔ በበኩሌ ይህ ሰው ለንጉሳዊነት ይስማማል የምለው ሰው በፍጹም የለም። አንዳንድ አሜሪካን ተቀምጠው የዘውድ አገዛዝ ይመለስ፣ ባለፉት አርባ ዓመታት በአገራችን ምድር የሰፈኑት አገዛዞች በሙሉ ተፈጥሮአዊና ከኢትዮጵያ ባህልና ታሪክ ጋር የሚስማሙ አይደሉም እያሉ አልፈው አልፈው ድምጻቸውን የሚያሰሙ እንዳሉ አውቃለሁ። እነዚህ ዐይነቶቹ አሜሪካን አገር ሲኖሩ ከአርባ ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል። ባለፉት አርባ ዓመታት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚካዊ አወቃቀሩ በመጥፎም ሆነ በጥሩ ነገር ተለውጠዋል። የህዝባችንም የሳይኮሎጂካል ሜክ አፕ፣ በተለይም የከተሜው ተለውጧል። በተለይም ወያኔ ስልጣን ይዞ ልዩ ዐይነት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ካደረገ በኋላ የከተሜው ህዝብ አስተሳሰብ በቀላሉ ሊገለጽ በማይችል መልክ ተቀይሯል። ታዲያ በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥና አንተም በጠቃቀስከው የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ ውስጥ ያንተን ሃሳብ የሚቀበል ታገኛለህ ወይ? የሚቀበል አለ ብንል እንኳ ለንጉሰ-ነገስትነት የሚስማማ ሰው አለ ወይ? እንደምታውቀው አንድን ሰው ከውጭ አምጥተህ በህዝባችን ላይ መጫን አትችልም። በዚህ ረገድ በሌሎች አገሮች ላይ ከውጭ መጥተው በህዝቦቻቸው ላይ የተጫኑ መሪዎች የህዝቦቻቸውን ችግሮች በፍጹም አላቃላሉም፤ እንዲያውም እያወሳሰቡት ሊመጡ ችለዋል። ምናልባት አሜሪካን አገር ካሉት ውስጥ ከንጉሳውያን ቤተሰብ የተወለድን ነን የሚሉትን በጭንቅላትህ ውስጥ ቋጥረህ ይሆናል። እነዚህ ደግሞ ኦሪጂናል አስተሳሰብ ያላቸው አይደሉም። ሁሉም ማለት ይቻላል በአሜሪካን ድጋፍ የሚኖሩና በተዓምር ስልጣን ላይ ቢወጡ እንኳ አዲስ ዐይነት የፖለቲካ ስልት ይከተላሉ የሚል ግምት የለኝም። ሌላው መገንዘብ ያለብን ጉዳይ ንጉሳዊ አገዛዝ በአንድ አገር ውስጥ ኦርጋኒካሊ ማደግ አለበት። የአገራችንን የንጉሳዊ አገዛዝ ታሪክ በደንብ ተከታትለህ እንደሆን፣ በጉልበትም ሆነ ዘርን በመቁጠር ስልጣን ላይ የወጡት ሁሉ ከዚያው የበቀሉና በዚያው የማህበራዊ ሁኔታ ያደጉ ናቸው። ይህም ማለት እንደነዚህ ነገስታቶች ግለሰብአዊ ብቻ ሳይሁኑ በተቋም ደረጃም ቀስ በቀስ እየዳበሩና ተቀባይነትን እያገኙ የመጡ ናቸው።
    ይህንን ትተን ወደ ሌሎች ጉዳዮች ስንመጣ ምናልባት ከእኔ በተሻለ መልክ እንደምታውቀው ንጉሳዊ አገዛዝም ይሁን ሌላ በምድር ላይ የሚታዩ ህብረተሰብአዊ ችግሮችን፣ እንደ ኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን የሚቀርፉ መሆን አለባቸው። አንድ ንጉሳዊ አገዛዝ ስልጣን ላይ ተቀምጦ የህዝቡን መሰረታዊ ችግሮች ለመፍታት የማይችል ከሆነ ችግሩቹ የባሰውኑ እየተደራረቡና ለተከታታዩ ትውልድ እየተላለፉ የሚሄዱ ይሆናሉ ማለት ነው። የአገራችንን የተወሳሰቡ ችግሮች ጠጋ ብለህ ተመልክተህ እንደሆን በባህል ቀውስ፣ በአካባቢ ቀውስ፣ በስነ-ልቦና ቀውስ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ቀውስ የሚገለጽና ህዝባችንም በእነዚህ ነገሮች የሚሰቃይ ነው። ታዲያ አንድ ንጉሳዊ አገዛዝ እነዚህን ነገሮች በሙሉ ከሳይንስ አንፃር በመመርመር ሊፈታቸው ይችላል ወይ? እንዚህን ነገሮች መመለስ የሚያስፈልግ ይመስለኛል። እንደምታውቀው ዘመኑ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዘመን ነው። ከኋላችን የተነሱ አገሮች በብዙ ሺህ ማይልሶች ርቀውን ሄደዋል። ለህዛባችንም መልስ የሚሆነው የሳይንስና የቴክኖሎጂን ትርጉም የተረዳና ቀስ በቀስ የህብረተስብአችንን ችግር የሚፈታ አገዛዝ መሆን አለበት።
    የአገራችን ዋናው ችግር የንጉሳዊ አገዛዝ መኖርና አለመኖር ሳይሆን፣ በፖለቲካው ዓለም ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንና ስልጣንንም የጨበጡ ኃይሎች የአዕምሮ ብስለት የሚጎድላቸው ናቸው። ራሺናሊ ለማሰብ የሚችሉ አይደሉም። አብዛኛዎቹ ለፖለቲካ እንታገላለን ቢሉም ከምሁራዊና ከሳይንሳዊ ዓለም በሚሊዮኖች ማይሎች ርቀው የሚገኙ ናቸው። አብዛኛዎቹ ከፊዩዳል አስተሳሰብ የተላቀቁ አይደሉም። ከብሄረሰብ የተውጣጡ ፖለቲከኛ ነን ባዮች ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ የዝቅተኝነት ስሜት ያጠቃቸዋል። ስልጣን ላይ በሚወጡበት ጊዜ ተበድለው እንዳደጉና እንደኖሩ ቁጭታቸውን በሙሉ ለመወጣት ይፈልጋሉ። ወያኔም ሆነ የዛሬው አገዛዝ በምሁራዊ ክንዋኔ፣ በማንበብና የአገራችንን ችግሮች ከምሁራዊ አንፃር በመመርመር ችግሮችን ለመፍታት ስልጣን ላይ የወጡ ሳይሆኑ በተሳሳተ ትረካ ጭንቅላታቸው የተሞላና ጊዜው የኛ ነው በሚል የራሳቸውን አዲስ የተበላሸ ታሪክ ለመስራትና ለመጻፍ የሚፈልጉ ናቸው። ዕውቀትም ስለሌላቸው የውጭ ኃይሎች አሻነጉሊት በመሆን የሚሆን የማይሆን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማውጣት እንደምታየው ወንጀለኛ የህብረተሰብ ክፍል ይፈጥራሉ ማለት ነው።

    ከዚህ ስንነሳ የአገራችን ችግር ይበልጥ የሚገለጸው የበሰለ፣ የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታና የዓለምን ፖለቲካ በቅጡ ለመረዳት የሚችል አለመኖሩ ነው። በአገራችን ምድር ከፍተኛ የሆነ ምሁራዊ ክፍተት አለ። ይህ ዐይነቱ ክፍተትም በብዙ የአፍሪካና የላቲን አሜሪካ አገሮች የሚታይ ነው። በእነዚህ አገሮች ያለው ችግር ትንሽ ለየት ያለ ቢመስልም በአብዛኛዎቹ አገሮች የሰፈኑት አገዛዞች ዘራፊ መንግስታት ናቸው። በከፍተኛ ደረጃ በመሳሪያ በመታጠቅ ህቦቻቸውን የሚያሰቃዩ ናቸው።
    ወደ አገራችን ስንመጣ የአገራችን ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ከፖለቲካው መስክ ባሻገር ነው። ይህም ማለት በሳይንስ፣ በፍልስፍና፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሶስዮሎጂ፣ በአርትስ፣ በሙዚቃና፣ በአጠቃላይ ሲታይ የባህላዊ እንቅስቃሴ ሲካሂድና አብዛኛውን ህዝብ ሲያቅፈው ብቻ ነው። ለምሳሌ የአሜሪካንን ህዝብ አንቆ የያዘው ከኢኮኖሚው ባሻገር፣ በሙዚቃ፣ በፊልም ኢንዱስትሪ፣ በሞድ፣ በስነ-ጽህፍና በሳይንስ በኩል የሚደረገው እንቅስቃሴና ምሁራዊ አስተዋፅዖ ነው። ለምሳሌ በአሜሪካን አገር በሳይንስ ዘርፍ አካባቢ የሚደረገውን ምሁራዊ ውይይት በደንብ ተመልክተህ ከሆነ የሳይንስ፣ የሙዚቃና ሌሎችም ባህላዊ ክንዋኔዎች የፖለቲካውን መስክ በብዙ ሚሊዮን ማይልስ ርቀው የሄዱ ናቸው። ችግሩ ግን ስልጣን ላይ ያሉት ፖለቲከኛ ነን ባዮች ቴክኖሎጂን በማይሆን ተግባር ላይ በማሰማራት ህዝብን መጨረሻ እያደረጉት ነው። በዚህ ዐይነቱ ሂደት በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ጊዜ ውስጥ በአሜሪካን ምድር ከፖለቲካው መስክ የሚነሳ ከፍተኛ የማህበራዊና የጎሳ ግጭት ይፈጠራል። ትረምፕ እንደገና ሲመረጥ የባሰ በህዝቡ ዘንድ ያለውን ቅራኔ ያፋጥነዋል። ለማለት የምፈልገው ሳይንስና ፖለቲካዊ አስተሳሰብ አንድ ላይ መጓዝ አለባቸው። የአንድን አገር ችግር ከብዙ አቅጣጫ በመመርመር ብቻ ነው መፍታት የሚቻለው። ይህም ደግሞ በፖለቲካው መስክ ህዝባዊ ተሳትፎን ይፈልጋል። ዕውቀት በሰፊው ህዝብ ዘንድ መስፋፋት አለበት። የተገለጸላቸው ተቋማት መገንባት አለባቸው። እነዚህን ሁሉ መመለስ የሚችል ከሆነ በአንተ የንጉሳዊ አስተሳሰብ ለመስማማት እንችል ይሆናል።

    ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)

  2. ኢትዮጵያ ዘውዳዊ አስተዳደር ያስፈልጋታል ወይስ አያስፈልጋትም?ጉዳዩን እስከወዲያኛው ለመቁዋጨት ሕዝበ-ውሳኔ ሊሰጥበት ይገባል።እንደ ቦርኬና ዘሓበሻም ይህንን አስተያዬቴን ሳንሱር ካደረገ የፋሺሽት ሥርዓት አሻጋሪትን ይከጅላል እንደማለት ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share