ማርቲን ሉተር ኪንግና የአሜሪካ የፍፁም ህብረት ራእይ – ገለታው ዘለቀ

ዛሬ በአሜሪካ ውስጥ የማርቲን ሉተር ኪንግ በድምቀት ይከበራል። ማርቲን ሉተር ኪንግ ይታገል የነበረው የዘር መድልዎን ነበር። ጥቁሮች በዚህ ሃገራዊ ማህበራችን ውስጥ መብታችን ተጥሷል፣ ህገ መንግስታችን ወደ የበለጠ ፍፁም ህብረት (Toward A More Perfect Union) ቢልም  በዘር መድልዎ አያሌ ግፎች ምክንያት ህብረታችን ወደ ፍፁም ህብረት አላደገም። ህብረታችን ፍፁም የሚሆነው በአሜሪካ ሰማይ ስር ያለን ጥቁሮች፣ነጮች፣ስፓኒሾች፣እስያውያን…….. ሁላችን እኩል መብት ሲኖረን፣ እኩል ስንታይ ነው በሚል ታላቁ ማርቲን ሉተር ኪንግ አሜሪካንን በአደባባይ በሰላም መንገድ  ሞግቶ አሸንፏል።

አሜሪካውያን ራእያቸው ወደ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ማደግ ብቻ ሳይሆን ሁል ጊዜም ህብረታቸውን እያሳመሩ እያነፁ መሄድ እንዳለባቸው ገብቷቸዋል። የኔሽን ቢዩልዲንግ ስራ ቀጣይነት ያለው ስራ ነው። በየጊዜው በቡድኖች መካከል፣ በፆታ መካከል፣ በግለሰቦች ልዩነት መካከል፣ መከባበርንና እኩልነትን ለማሳደግ ዘወትር ሳይታክቱ ይሰራሉ። ወደ ፍፁም ህብረት ዘወትር ይዘረጋሉ………

አንድ ጊዜ ታላቁን የነፃነት ታጋይ ማርቲን ሉተር ኪንግን  አንድ ጋዜጠኛ እንዲህ ሲል ጠየቀው።

ማርቲን ሉተር ኪንግ ለመሆኑ በአሜሪካ ውስጥ ጥቁር ፕሬዝደንት የሚሆንበት ዘመን ይመጣ ይመስልሃል?

ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዲህ ሲል መለሰ

በርግጥ ይህ ዘመን ይመጣል!

 

ጋዜጠኛው ቀጥሎጠየቀ።  መቼ ይሆናል ብለህ ታስባለህ?

ከአርባ አመት በሁዋላ

ህልመኛው ኪንግ ልክ እንደተነበየው ፕሬዚደንት ኦባማ በአርባኛው አመት ግድም የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ። አሜሪካውያን ኦባማን ሲመርጡ ያለቀሱትን ያህል ሌሎች ፕሬዝደንቶችን ሲሾሙ አላነቡም። በቅርብ ከማውቀው ቤተሰብ እንኳን የእኔ የባለቤቴ እና ባለቤቴም ኦባማ ሲመረጡ ከልብ አንብተው ነበር።  ፕሬዚደንት ኦባማ ህልማቸውን ሲናገሩ ህልሜ ወደ ፍፁም ህብረት (Toward a more perfect union ) ነው ነበር ያሉት። የኦባማ ራእይ የማርቲን ሉተር ኪንግን ራእይ መቀጠል ነው። አሜሪካ ወደ ፍፁም ህብረት………. አሉ ፕሬዝደንት ኦባማ መንበረ ስልጣን ሲረከቡ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኦሮሚያ ክልል ገላን ከተማ በሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ በአፈና የቆዩ 38 ግለሰቦች ደርሶብናል ያሉትን ኢሰብአዊ ድርጊት ለችሎት ተናግሩ

የአሜሪካ ህዝቡም ነፍሱ የምትነግረው አንድ ነገር አለ። በሃይማኖቱም በባህሉም ተቀባይነት የሌለው የዘር መድልዎ ህብረቱን የሚበጠብጥ ተዋጊ በሬ ነው። ስለዚህ ህብረቱን ውብና የተቀደሰ ለማድረግ ነጭና ጥቁሩ እጅ ለእጅ ተያይዞ እኩልነትን ማርበብ አለበት። በመሆኑም ወደ የላቀ ፍፁም ህብረት ለማደግ ዘወትር ነፍሱ ይራባል። በፍፁም ህብረት መርህ ተግዝቶ ሁል ጊዜም ወደፊት…..

ፕሬዝደንት ኦባማ ሲመረጡ አሜሪካውያን ያነቡት እሰየው ህብረታችን እየተሻሻለ ነው፣ ወደ እኩልነት እያደግን ነው፣ ከእግዚአብሔር በታች የማንከፋፈል አንድ ህዝብ ነን የምንለውን መሃላ ጠብቀናል ማለት ነው በፍፁም ህብረት ጎዳና ላይ ነን ማለት ነው የሚለው ስሜት ነፍሳቸውን ነክቶ ነው።

ማርቲን ሉተር ኪንግ የመራው የእኩልነት ጥያቄ ዛሬም ድረስ እየተካሄደ ነው። ባለፈው አመት  በማርቲን ሉተር ቀን የመብት ታጋዮች Toward A More Perfect Union የሚል ትእይንት አካሂደዋል። አሜሪካውያን የህብረታቸው ውበት የሚለካው በተለይ በዘር እኩልነትና በግለሰብ ነፃነት በኩል ሲገለፅ እንደሆነ ገብቷቸው ዛሬም ወደ ፍፁም ህብረት በሚል መርህ የኔሽን ቢዩልዲንግ ስራቸውን በአጭር ታጥቀው ይሰራሉ። ፕሬዝደንት ባይደን ሲመረጡ ይህንኑ ቃል አፅንተዋል። ጉዟችን ፍፁም ህብረትን ወደማጠናከር ነው ብለዋል።

ፕሬዝደንት ኦባማ የመረቁትን የማርቲን ሉተር ኪንግን ሃውልት ስጎበኝ ታላቁ ማርቲን ሉተር ኪንግ በህይወት ያለ ያህል ተሰማኝ። እውነት ነው ስራው ህያው ነውና ሞቶም አልሞተም…….

ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ከማርቲን ሉተር ኪንግ የምንማረው ትልቅ ትምህርት አለ። ኢትዮጵያችን የግለሰቦችና የቡድኖችን መብት ያከበረች ህብረቱዋን ወደ ፍፁም የማይከፋፈል ህብረት እያነፀች የምትኖር ሃገር እንድትሆን በፅናት መታገል አለብን። ህብረታችንን የብሄር ጥያቄ ሊበጠብጠው አይገባም። በብሄር ጥያቄ ዙሪያ አርባ አመት አንድ ተራራ መዞር የለብንም። እኩልነትን እያነፅን ነገር ግን ፍፁም ወደ ሆነች ኢትዮጵያ ለማደግ ዘወትር እንዘርጋ።  መልካም የማርቲን ሉተር ኪንግ ቀን።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጸመው ሰውን የማቃጠል ድርጊት፤ የመንግስት የጸጥታ አባላት መሳተፋቸውን ማረጋገጡን ኢሰመኮ አስታወቀ

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share