በኢትዮጵያ የተከሰተዉ የዉጪ ምንዛሪ እጥረት በመንግሥት የልማት ፕሮጀክቶች ላይ አሉታዊ ተፅኖ እያሳደረ ነዉ:: ዛሬ የሀገሪቱ ሕዝቦች ችጋር እና የኑሮ ውድነት ስንግ ይዟቸው መንግስት በፍጠረው ችግር ምክንያት ከዓለም የደሀዎች ደሀ የምትመደበው ሀገራችን ይህ የውጭ ምንዛሬ እጥረት መከሰቱ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል::
የመንግስት ባለስልጣናት ”በእኛ አመራር የመጣ ልማት ነው; ኢኮኖሚያችን ከሚገባው በላይ አድጓል”” እያሉ በሰፊው እየተናገሩ ቢሆንም ችግሮች አግጥጠው እየታዩ ይገኛሉ:: ረሀብ እና የኑሮ ውድነት እያሰቃየው ያለው ሕዝብ ችግሬ ከዛሬ ነገ ይቃለላል እያለ በተስፋ እየተጠባበቀ ባለበት ወቅት የውጭ ምንዛሬ በሀገሪቱ ባለመኖሩ ፋብሪካዎች በአደጋ ላይ ሲሆኑ ሰራተኞችም በመበተን አደጋ ውስጥ ወድቀዋል::
ሙሉ ለሙሉ በብሔራዊ ባንክና በንግድ ባንክ ውስጥ የውጭ ምንዛሬ የሌለ በመሆኑ ነጋዴዎች ጥሬ እቃ ከውጭ ሀገር ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ከመቸገራቸውም በላይ በሀገር ውስጥ የተሰማሩበት ሥራ በመቆሙ ሀገሪቱ ወትሮ ከነበረችበት ችግር የባስ አዘቅት ውስጥ እየገባች መሆኑን የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ይገልጻሉ::
ነዳጅ በዓለም አቀፍ ላይ ከ50 ዶላር በታች እያሽቆለቆለ ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ግን በሚገርም ሁኔታ ላይ ነው ያለው:: በአሜሪካ ከሁለት ወር በፊት ከነበረው የነዳጅ ዋጋ አሁን በግማሽ ያህል እየተሸጠ ሲሆን በኢትዮጵያ ግን በሳንቲም ደረጃ ቅናሽ ያደረገው:: ይህ የሆነበት ምክንያት የረከሰውን ነዳጅ ለመግዛት የውጭ ምንዛሬ ስለሌላቸው በነዳጅ እጥረት ሕዝቡ እየታመሰ ይገኛል::
አሁን የተከሰተው የውጭ ምንዛሬ እጥረት መንግሥት የልማት እቅዶቹን በቁነና እንዲያፅ ፈፅም ወይም በጣም-አስፈላጊና አስፈላጊ የሚል ቅደም ተከተል እንዲያወጣ እያስገደደዉ ነዉ:: ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖችና የምጣኔ ሐብት አዋቂዎች እንደሚሉት በእጥረቱ ምክንያት መንግሥት በጣም አስፈላጊ ለሚላቸዉ የልማት ፕሮጄክቶች ቅድሚያ እንዲሰጥ አስገድዶታል:: ይህ ደግሞ የሀገሪቱን ደሀ ሕዝብ በእጅጉ ይጎዳል:: መንግስት የምንዛሬው እጥረት የመጣበትን ምክንያት በውል እንደማያውቅ ቢገልጽም ተቃዋሚዎች ግን ”በብድር እና በእርዳታ የሚመጣውን የውጭ ሀገር ገንዝብ በራሳቸውና በቤተሰቦቻቸው ስም እየቦጠቦጡ በውጭ ሀገር ባንኮች ውስጥ እያከማቹ ሀገሪቱን ባዶ በማስቀረታቸው የንግዱ ማሕበረሰብ የንግድ እንቅስቃሴ እንዳያድግ ሲገደብ; አሁን ደግሞ ብዙ ፋብሪካዎች ለመዘጋት እንደተገደዱ” ይናገራሉ::