ድምጻዊት ጠለላ ከበደ ከአርበኛ አባትዋ አቶ ከበደ ወርቄና ከእናቷ ወ/ሮ ደስታ ብሩ ከጣልያን ወራሪ ጋር ሲዋጉ ቆይተው ወደ ኬንያ ተሰደው ሲኖሩ ሲኦሎ በምትባል የኬንያ ከተማ በህዳር 12/1931 ዓ.ም ተወለደች። አራት አመቷ ሲሆን ነፃነት መጣ ተብሎ ሁሉም ወደ አገሩ ሲመለስ ጠለላ ከበደም ከቤተሰቦቿ ጋር ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል።
ጠለላ ከበደ እንደማንኛውም የዚያን ወቅት ተማሪ አዲስ አበባ ውስጥ ሰፈሯ በሚገኝ የቄስ ት/ቤት ፊደል ከቆጠረች በኋላ ዲታ ዲባ የሚባሉ ጣልያናዊ ት/ቤት፤ ከዚያም ጊዮርጊስ ት/ቤት፤ ሃኪም ወርቅነህ የሚባል የማዘጋጃ ት/ቤት፤ በመጨረሻም ሚሲዮን ላዛሪስት የአሁኑ ሴንትሜሪ ት/ቤት እሰከ አምስተኛ ክፍል ገብታ ተምራለች።
የዘፋኝነት ተሰጥኦ የነበራት ጠለላ ከበደ በ ቀዳማዊ ኅ/ሥላሴ ያሁኑ ብሄራዊ ትያትር ለመጀመርያ በዘፋኝነት ተቀጥራ ስትሰራ የ 15 አመት ወጣት ነበረች። በወጣትነት እድሜዋ ጀምራ በሙያዋ ለ 32 አመት ስታገለግል ከቆየች በኋላ ከደርግ ካድሬዎች ጋር ስለማትስማማ በ 1982 ዓ.ም በፈቃዷ ጡረታ ወጥታለች።
ጠለላ ከበደ ከወጣትነቷ ጊዜ ጀምሮ በነበራት ከፍተኛ የሀገርና የህዝብ ፍቅር ከሙያዋ ባሻገር ለዴሞክራሲ ፍትህና እኲልነት ስትታገል ቆይታለች። በአካባቢዋ፤ በሙያ ባልደረቦቿ በጣም ተወዳጅ የነበረችው ጠለላ ከበደ ለቆመችለት አላማ ወደኋላ የማትል፤ ፍትህ ሲጓደል ድምጿን ለማሰማት የማታፈገፍግ፤ አድርባይነትን በጣም የምትጠየፍና አካፋን አካፋ እያለች በቃሏ የኖረች እውነተኛ የህዝብ ልጅና ጀግና ናት።
“ሎሚ ተራ ተራ” የሚለውን ዘፈን ዘፈንሽ በመባል ጠለላ ከበደና ከሷ ጋር ሌላ ስድስት የሙዚቃ ባለሙያዎች በ 1967 ዓ.ም በደርግ ካድሬዎች ለአራት ወር ከስድስት ቀን ለእስር ተዳርገዋል።
Telela Kebede – Lomi Tera Tera and Alemiye
ጦር ፍርድ ቤት ቀርበው በዋስ ከተፈቱ በኋላም ጠለላ ከበደ ለሁለት አመት ያህል ከአዲስ አበባ አካባቢ እንዳትንቀሳቀስ፤ ከናዝሬት አልፋ እንዳትሄድ፤ በግዞት እንድትቆይ ተፈርዶባታል።
በ መስከረም 10/1987 ዓ.ም ፕሮፌሰር አስራት በወያኔ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ ፍትህን ለመጠየቅና ድምፃቸውን ለማሰማት በፍርድ ቤቱ አካባቢ ከነበሩት ለእስር ከተዳረጉት 1500 ሰዎች መካከል አንዷ ጠለላ ከበደ ነበረች። በዚያን ቀን እየተደበደቡ ሰንዳፋ ተወስደው ፀጉራቸው ተላጭቶ ታስረዋል።
1000 ሰዎች ይቅርታ እዲጠይቁ ተደርገው ሲለቀቁ ጠለላ ከበደ ከሌላ 500 ሰዎች ጋር ይቅርታ አንጠይቅም በማለታቸው ለተጨማሪ 25 ቀናት ታስረው
በከፍተኛ የህዝብ ግፊትና የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመፈታት በቅተዋል። ከእስር ከተፈታች ከሶስት ወር በኋላ አማራጭ ሃይልና መላው አማራ መስቀል አደባባይ በጠራው ሰልፍ ላይም ከፍተኛ ተሳትፎ አድርጋለች።
በስደት ሰሜን አሜሪካ ከመጣች ከ 1995 ዓ.ም ጀምሮ የ ኢሕአፓ ጠንካራ ደጋፊ በመሆን ለረጅም አመታት ስታገለግል ነበር። ድምጻዊት ጠለላ ከበደ የእድሜ ባለፀጋ፤ ሰፊ ተተኪ ቤተሰቦች ያፈራች የሰባት ልጆች እናትና አያት ነበረች።
ድምጻዊት ጠለላ ከበደ በአደረባት ህመም በህክምና ስትረዳ ቆይታ በተወለደች በ83 ዓመቷ በስደት ትኖርበት በነበረው ሰሜን አሜሪካ ሜሪላንድ ግዛት ህዳር 13/2014 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች። ለመላ ቤተሰቡ ወዳጅ ዘመድ እና አድናቂዎቿ በሙሉ መጽናናትን እየተመኘሁ የሟችን ነፍስ ይማር!
-https://youtu.be/wF2Zqn2KxnY