ምዕራባውያ እንዲህ ሰላማችን የሚነሱን ለምንድን ነው? – ጊዜ ለኩሉ

በአሜሪካ ህንዶች መፈናቀልና የዘር ጭፍጨፋ፣ በአፍሪካ ባሮች ጉልበት የዛሬ ~250 አመት በተመሠረተ፣ የአለምን ጥሬ ሀብትና የሰለጠነ የሰው ሃይል በማግበስበስ በጠነከረ እና የአለምን ስልጣኔዎች ሁሉ እያፈረሰ ባለ አሜሪካ በተባለ አገር፣ ሰባዊ መብትና እርዳታ በሚል ሽፋን ልንታወክ አይገባም። የምዕራባዊያን የአፍሪካን መንግስታት፣ በመፈንቅለ መንግስት፣ በግድያ፣ በርስ በርስ ጦርነት፣ በሕዝብ አመጽ የማስወገድ ዘዴ እንደሚከተሉ ይታወቃል። ምዕራባውያን መሪዎቻችንን ሲመርጡልን ከርመዋል። አሁንም እሱን ለማስቀጠል፣ በርስ በርስ ጦርነት እያፋጁን ነው። የአሜሪካና የቻይና ውድድር በእኛ በደካሞቹ የፈጠረው ችግር በጣም ግዙፍ ነው። የቻይናን ወደ አፍሪካ የመግቢያ በር የመዝጊያ መንገድ ደግሞ ኢትዮጵያን መበጥበጥ ሆኗል። የትናንትናው የቀኝ ግዛት፣ የአሁኑ ኒዮሊብራሊዝም እንቅፋት፣ ኢትዮጵያ ያላት ስቴራቴጂክ አቀማመጥ፣ ያላትና ይኖራታል ተብሎ በሚታሰበው የማዕድንና የነዳጅ ሃብት፣ የአፍሪካ የእድገት አረዕያ እንዳንሆንና የጥሬ እቃ ማግኛና የሸቀጥ ማራገፊያቸው እንዳይነጥፍ ጠንክረው እየሰሩ ነው።

የውጪና የአደጉ አገራት ተጽዕኖ እንዴት ይገለፃል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያለበት አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። የሚገለጥበት መንገዶች ሃይማኖት ልስበካችሁ፣ የትምህርት ካሪክለም ልቅረጽላችሁ፣ እርዳታ እንስጣችሁ፣ የሆሊውድ ፊልምና ሙዚቃ፣ ትልቆቹ ሚዲያዎች እነሱን ከፍ ሌላውን ዝቅ የማድረግ ስነልቦናዊ ተጽዕኖ፣ በቀኝ እንያዝና እናሰልጥናችሁ፣ ከፖለቲካና ኢኮኖሚ ማግለል፣ የእነሱና እናንተ የከፋፍለህ ግዛ፣ የአለም ባንክና የአለም የገንዘብ ጅርጅት የፖሊሲ ተጽዕኖ፣ አገሮች ወደ ጦርነት እንዲገቡ ገንዘብ ለመረጡት ቡድን መርዳት ወዘተ ይሆናሉ። ይህን ሁሉ የሚያደርጉት ደግሞ ጥቅማቸውን ለማስከበር በኛው ሃይል፣ በነሱ እውቀትና ብዙ ትርፍ በሚያመጣ ትንሽ ወጪ ነው። አሁንም። የአሜሪካ መንግስት African Growth and Opportunity Act (AGOA) የንግድ ተጠቃሚነት ኢትዮጵያን አስወጥቻለሁ ብሏል። ይህን የማድረግ መብት ያላቸውን ያህል፣ ነጻነታችንን በኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ሰበብ አሳልፈን የማንሰጥ መሆናችንን ሊያውቁ ይገባል። ማደግ የምንችለው አሜሪካ፣ እንግሊዝ ወይም የአውሮፓ ህብረት የፖለቲካ መንገዱን ስላሳዩን፣ የአለም ባንክ ወይም አለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ገንዘብ ስለሰጡንና የኢኮኖሚ ፖሊሲያችን ስላስቀየሩን፣ በተረኝነት ከስልጣን ማማ ላይ ስለወጣን፣ ዜጎቻንን ስላሳደድን፣ የተገነቡ ከተሞችን ስላወደምን አይደለም። ማደግ የምንችለው ለሁላችንም የሚሆነ ስርዓት መገንባት ስንችል ብቻ ነው።

የምዕራባዊያንን የቀኝ ግዛት መስፋፋት ለማገዝ ተግባር ላይ ከዋሉ ዘዴዎች መካከል፣ የስነ ልሳንና የዘር አመጣጥ ታሪክን ማጥናት ይገኝባቸዋል። ይህንም መረጃ ሕዝብን ለመነጣጠልና አንድነቱን ለማድከም፣ ብሎም የቀኝ ግዛታቸውን ለማስፋፋት ተጠቅመውበታል። ለዚህም ነው፣ የሰውን ልጅ የካም፣ የሴምና የያፌት በሚል የእምነት መሠረት ያለው ክፍፍል በማድረግ ካምን የተረገመው ጥቁር፣ ሴሙን ከያፌት እኩል ያልሆነው ነጭ?፣ ያፌትን ባለ ትልቅ አዕምሮ አሳቢ አድርገው የሳሉት። አገራችንን በተመለከተ እዚህ ላይም አላቆሙም። ቋንቋችንን ሴሜቲክ፣ ኩሺቲክ፣ ኦሞቲክና ናይሎቲክ ብለው ከፍለው የጊዜ ልዩነት ቢኖረውም ሁላችንን በስደት የመጣን ስደተኞች አድርገውናል። እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ የእኛው ታሪክ ጸሐፊዎች ይህንን መንገድ መከተላቸው ነው። ይህንን የሐሰት የቀኝ ገዢዎች ክፍፍል የኛው ፖለቲከኞች ሲጠቀሙበት ማየትም ያሳፍራል። እውነቱ ግን ከአጎራባቾቻችን የተዳቀልን የዚህችው ምድር ውጤት የሆንን፣ ቋንቋችንም እንደሰፈርንበት እርቀትና ቅርበት ያለው፣ በታሪክ ሂደት ሲቀያየር የኖረ ነው። የጀነቲክስ ምርምሮችም የሚያሳዩት በእኛ ጎሳዎች መካከል የጎላ ልዩነት አለመኖሩንና ጎረቤት ከሆኑት ቅርብና እሩቅ ምስራቅ ዝምድና እንዳለን ብቻ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አሁናዊ የኢትዮ ኒውስ ልዩ መረጃዎች! | በዓድዋ ድል አከባበር በአዲስአበባ የሆነው ምንድነው?

ምዕራባዊያን፣ ባለራዕዩ መሪያችን አፄ ቴዎድሮስ እራሱን እንዲያጠፋ አድርገዋል፣ በሂወት ስምምነት ምክንያት ከመሃዲ ድርቡሾች ጋር እንድንጣላና አፄ ዮሃንስ ህይወታቸውን እንዲያጡ አድርገዋል፤ የአባይን ውሃ እንዳንጠቀም የሚያግድና ለቀኝ ግዛታቸው ግብጽና ሱዳን ብቻ የሚጠቅም ውል ፈርመዋል፤ በስትሬሳው የሆርላቫልሞሶሎኒ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያን በጣልያን አስወርረዋል፤ በንጉሣዊ ስልጣን እጃቸውን በማስገባት ለእያሱ ስልጣን መልቀቅና ሞት ምክንያት ሆነዋል፤ መንግስቱን ያለ አማራጭ በማሰቀረት ተገፍቶ የሶሻሊስት ጎራ እንዲገባና አገሪቱ በእርስ በርስ ጦርነት እንድትታመስ አድርገዋል፤ አገራችንን በዚያድባሬ የታላቋ ሶማሊያ ትርክት እንድንወረር አድርገዋል፤ አገራችንን ያለ ወደብ አስቀርተዋል፤ አማጺው ትህነግ መንግስታዊ ስልጣን እንዲይዝ፣ አገራችን በዘር እንድትከፋፈል፣ የአገር ሃብት እንዲባክንና አሁን ደግሞ በዚሁ ቡድን አነሳሽነት የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ አስገብተውናል። ትግራይ ክልል ግጭት ሲጀመር፣ የምእራባውያን ጋዜጠኞች ያስነበቡን መጣጥፍ፣ ሱዳን ኢትዮጵያን መውረር እንዳለባት የሚያትት ነበር። እሱንም የሱዳን የወታደራዊ መንግስት እውን አድርጎታል። የትህነግን መመታት ተከትሎ ምዕራባውያን ያደረጉት ደግሞ የኢትዮጵያን መንግስት በጦር ለመወንጀል፣ በቲዊተርና በየቴሌቪዥን ጣቢያዎቻቸው የስም ማጥፋት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ ደግሞ በትግራይ ጉዳይ በየጊዜው መሰብሰብ ነው።

ከጣልያን ወረራ ጀምሮ እስከነፃነት ማግኘትና ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ የተደረጉትን የዲፕሎማሲ ትግሎች መልክ አሁን እየደረሰብን ካለው ጫና ጋር በሚመሳሰል መንገድ ነበር። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን እስከ በጣልያን መወረር ድረስ፣

ዘዴያቸው ሕዝቡ በባርነት እየማቀቀ ነው የሚል ነበር። በዚህ ጊዜ፣ በየአገራቱ የሚኖሩና በባርነት ወደየአህጉሩ የተወሰዱ ጥቁሮች የመምረጥም ሆነ ሌላው ነፃነት አልነበራቸውም። በተለይም የኤርትራ፣ ከኢትዮጵያ ጋር መወሃድ እውን እየሆነ ሲመጣ፣ በዘውዳዊ መንግስት እየተዳደረ ከአለ አገር ጋር ሌላውን በፌዴሬሽን ማዋሃድ የሚያመጣው ችግር ሳይታያቸው ቀርቶ ሳይሆን ችግሩን ለራሳችው ጥቅም መፈለጋቸውን ያሳያል። የግብጽን ሁሉ ድጋፍ ያገኘ መሆኑም የዚሁ ግልጽ ማሳያ ነው። የታላቋ ትግራይ፣ የታላቋ ሶማሊያ፣ የአባይ ሸለቆ ህብረት የሚሉ ሃሳቦች ፍጥረት ምክንያትም ይኸው አፍሪካን እንዳታድግ አስሮ የመያዝ መንገድ ነው። ይህም የ30 አመት ጦርነትን፣ የሃብትና የሰዎች እልቂትም አስከተለ። ከሰላሳ አመት በኋላም ውጤቱ ለኤርትራም፣ ለኢትዮጵያም ኪሳራ እንጂ ትርፍ አላመጣም።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ሰበር የድል ዜና ከአጣየ! //"የገባው አልወጣም"

አሁንም ይኸውን ዘዴ በትግራይ እየተገበሩት ነው። የትግራይ ጉዳይን በየቀኑ ሳያነሱ አያልፉም። ምክንያቱም፣ በእነሱ ለ30 አመታት የነገሱትና ታዛዦቻቸው መሬት ግባታቸው እየተረጋገጠ ስለሆነ ነው። ችግሩ ይህ የሚሉት ሁሉ በእነሱ በቬትናም፣ በኢራቅ፣ በሶሪያ፣ በሊቢያ፣ በአፍጋኒስታን፣ በየመን ወዘተ የተፈጸመ መሆኑ ነው። እነዚሁ ሃብታም አገሮች አማጺ ቡድን የሆነውን ትህነግ ከጫካ አምጥተው አራት ኪሎ የሚኒሊክ ቤተ መንግስት ሲያስገቡትም የተገበረው ይኸውን የሃብታም አገሮች ፖሊሲ፣ የኢትዮጵያን እንደ አገር ቀጣይነት የሚያዳክም መንገድ መከተል ነው። ለዚህም የአገርን አንድነት የሚያደክም ህገ መንግስት፣ ከፌዴሬሽን ይልቅ ወደ ኮንፌዴሬሽን የሚያደላ የክልላዊ መንግስት በማቋቋም፣ የራሳቸውን የክልል ጦር በማቋቋም፣ እስከ ጊዜው ልገዛ፣ ከዚያ እገነጠላለሁ አይነት መንገድ እንዲከተሉ አድርጓል። ይህ ካልገዛሁ እገነጠላለሁም፣ የምዕራባዊያን ስራ እንደሆነ እያየን ነው። ተበድያለሁ ልገንጠል ሳይሆን፣ ካልገዛሁ፣ ካልዘረፍኩ ልገንጠል ነውና።

የአፄ ቴዎድሮስና አፄ ኃይለስላሴ የዘመናዊነት ፕሮጀክት የወደቀበትም ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያን ዘመናዊነት ከማይፈልግጉት አገሮች እገዛ ጋር የተጣበቀ ስለነበር ነው። ይህም ማነኛውንም የእድገት ውጥናችንን ከተቻለ በራሳችን፣ ካልተቻለ ወዳጅ መፈለጉ ላይ ጠንቃቆች መሆን ይኖርብናል። ለዚህም የህዳሴ ግድባች ወደ መጠናቀቁ መቅረብ ትልቅ ማሳያ ነው። ለወደፊቱም ትልቅ ትምህርት የሚሆን ነው። እድገት፣ የአገር ደህንነት፣ የሕብረት ውጤት መሆኑንም ማሳያ ነው። የጣልያን ወረራ ወቅት፣ የተማሩና በአለአቅም ዜጎች ተጨፍጭፈዋል። አሁን ተምረናል የምንባለውም፣ ከእኛነታችን በሚያወጣና መሠረት የለሽ በማድረግ፣ የጣልያኑን የመግደል አላማ የሚያሳካ፣ እያሉ አለመኖርን የሚያስከትል፣ የምዕራባውያን የትምህርት ስርዓት ውጤቶች አድርገውናል። ይህም ለአገራችን ጥሩ ማበርከት እንዳንችል፣ ለስደት ወደ ውጭ የምናይ አድርጎናል።

ምዕራባውያን ችግሩ እንዲሰፋ እንጂ እንዲፈታ የሚፈልጉ ከመሰለን ተሳስተናል። ምዕራባዊያን ማንንም ደገፉ ማንንም፣ የሚደግፉት ለማንም አስበው ሳይሆን የራሳቸውን ጥቅም አስልተው መሆኑን አንርሳ። የሚደግፉትም፣ የሚቃወሙትም አብሮ ሲደክም ማየት የደስታ ምንጫቸው ነው። የሚፈልጉት፣ የደከመና የአገሩን ሃብት የማይጠቀም፣ ሃብቱን ለእነሱ ሰጥቶ፣ ለነሱ የሸቀጥ ማራገፊያና ከነሱ የሚለምን ምስኪን ተመጥዋች ሕዝብ ማየት ነው። ማዕቀብ ፈርቶ፣ ሞትን ፈርቶ መሠራት ካለበት መሸሸትም ለነገ የባሰ ችግር ውስጥ ለመግባት መንገድ መጀመር ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ለምዕራባውያን፣ ኢትዮጵያን በእርዳታ ስም ለማወክ የሚሄዱበትን መንገድ እንዲያቆሙ፣ የእርዳታ ድርጅት መሪዎችና ሰራተኞችም+ ሰላዮችና የችግር ምንጮች መሆናቸውን ማስገንዘብ፣ እርዳታ በኢትዮጵያ መንግስትና ሌሎች አካላት በትብብር እንጂ በተናጠል የሚደረግ አለመሆኑን፣ አገር ከፍታችሁ ስጡንና እናፍርሳችሁ የማይሰራ መሆኑን፣ ያለዚያ እርዳታቸውን ይዘው ከእኛ እንዲርቁ በግልጽ ቋንቋ ሊነገራቸው ይገባል። እርዳታ፣ ጥገኝነትን እንጂ ምን ፈየደልን? በእርዳታስ ያደገው አገር የትኛው ነው? ማዕቀብስ ቢሆን በራሳችን መቆም እንድንችል ያስተምረን ይሆናል እንጂ ምን ያህል ሊጎዳን?

ተጨማሪ ያንብቡ:  ያልዘሩትን ማጨድ ከቶ አይቻልም! (ግንቦት7)

ምዕራባዊያን የሚፈልጉት አገራዊ አመለካከት ያለውን ማነኛውንም ማህበረሰብ ማድከምና ኢትዮጵያን ማፍረስ ነው። እኛ ግን ይህን የምንወጣበትን መንገድ ማሰብና መስራት ሲገባን በተረኝነት ተጠፍረን ታስረን እየተቸገርን ነው። ይህ ደግሞ ሁላችንን እንድንሸነፍ የሚያደርግ፣ ለአገር አንድነትም እንቅፋት የሚሆን ነው። የዲፕሎማሲ ግንኙነትን በተመለከተ፣ ማየት ያለብን ወደ ምዕራብ ወይም ወደ ምስራቅ አይደለም። ማየት ያለብን ወደ እራሳችን ነው። ወደ እራስ ማየት እራስን ችሎ ለመቆም፣ ከሁሉም ጋር የሚበጅን ለመምረጥ፣ ጠላትን ለመቀነስ ይጠቅማልና። ከአንዱ ወደ ሌላው ማየት አለቃን የመቀያየር የባርነት አባዜ ነው። መሆን ያለበት፣ እኛ እነሱን የምንፈልጋቸውን ያህል፣ እነሱም እኛን እንዲፈልጉን የሚያስችል ስትራቴጂ መዘርጋትና መተግበር ነው። የጦርነቱ አላማ ችግር ፈጣሪውን በጊዜ በማስወገድ፣ ሞትን መቀነስ ነው። የተሻለው በጊዜ ሂደት ከያንዳንዱ ክልል የሰለጠነ ሚሊሻንና ልዩ ሃይልን፣ ከአዲስና ነባር ወታደሩ ጋር በመጨመርና መልሶ በማደራጀት፣ በየስርቻውና በየቤቱ የተሰገሰገን ህወሓትና ኦነግ ማጽዳት ብቻ ነው። ይህ ጣልቃ ገብነት የሚቆመው፣ እኛ ኢትዮጵያዊያን በማነኛውም መንገድ ከችጋራችን መውጣት፣ ለዚህም የሚያስፈልገውን እውቀት መገብየት ስንችል ነው። ያለዚያ የምዕራቡ አለም ባርነታችን ይቀጥላል።

1 Comment

  1. እንደዛሬው ጊዜው ሳይጨልም ሰው በሰውነቱ ሲታሰብ የሶስት ሰዎች ታሪክ እንሆ፡ አምቦ – ሰውዬው በከተማው የታወቁና ሰው አስታራቂ በጊዜው የገበሬ ባለጠጋ ነበሩ። ከጎጃም ተነስቶ አምቦ የገባው የ 14 ዓመት ልጅ ደግሞ መኖሪያ አልነበረውም። ቤ/ክርስቲያን ለመሳለም ሲያልፉ ልጅን ያዪና ያስጠሩታል። ልጅም ሰው እንደማያውቅና ከቤተሰብ ጠፍቶ በጭነት መኪና እዚህ መድረሱን ይነግራቸዋል። እሳቸውም ልጅን ወስደው አሳድገው፤ አስተምረው ዛሬ አሉ ከሚባሉት የኮምፒውተር አዋቂዎች አንድ ነው። ጎንደር – ባለሱቁ በዛሬው አባባል ኤርትራዊው ባለሃብት አንድ የጎንደር የገጠር ልጅ ወስደው ከልጆቻቸው ጋር አሳድገውና አስተምረው በጎንደር የህክምና ኮሌጅ ዶክተር አረገው ያስመርቁታል። ያ ልጅ ዛሬ በሥራውና በህይወት አለ። ጋሽ ሃጎስ – ጋሽ ሃጎስ መቀሌ ውስጥ ማለፊያ ቡና ቤቶች ከነበሩት አንድ ነው። ያው ሁሉም ያለ ሃሳብ የሚዝናናበት ዘመን ስለነበር ጮቤ ረገጣ ነው። ታዲያ በዚህ መካከል ጋሽ ሃጎስ አንዲት ሴት ልጅ ይዞ ይመጣል። እንዴ ሃጎስ ይህች ደግሞ የማን ልጅ ናት ይሉታል። ልጄ ናት ሽዋ የወለድኳት አሁን አስመጥቻት ይላል። ሚስጢሩ ግን ከእናቷ ጋር ዘመድ ልትጠይቅ መታ እናቷ በመኪና አደጋ ሞታ እርሷ ተርፋ መሄጃ አጥታ ነው። ያችን ልጅ ጋሽ ሃጎስ አሳድጎ አስተምሮ ዛሬ ስዊድን ውስጥ ማለፊያ ሙያ ይዛ ትኖራለች። እነዚህን ወገኖች ለቁም ነገር ያበቁት እነዚያ ወገኖች ግን በህይወት ዛሬ የሉም። ግን አንዳቸውም በዘር፤ በቋንቋ ወይም በሃይማኖት ሰውን አልገፉም። የዛሬ የዘር ፓለቲካ እብዶች ግን በራፋቸው ላይ ቆመው ዓለምን አየን ይሉናል።
    አንባቢ ምን እያልከን ነው ይህ ሁሉ ከላይ ካለው ሃሳብ ጋር ምን ያገናኘዋል ትሉ ይሆናል። እውቁ ኢትዮጵያዊ አሰፋ ጫቦ አንዴ በአሜሪካን ሃገር ከአሜሪካው የስለላ ድርጅት ጋር ግንኙነት ያለው ሰው ከዚያም በፊት የሚተዋወቁ ምሳ ይጋብዘዋል። ምሳ ለማዘዝ ቁጭ ካሉ በህዋላ ብሄርህ ምንድን ነው ብሎ ይጠይቀዋል። የአንተ ብሄር ምንድን ነው ብሎ አሰፋ ጫቦ ነጩን ሲጠይቀው እኔ እማ አሜሪካዊ ነኝ ይለዋል። እኔም ኢትዮጵያዊ ነኝ በማለት ምሳው ሳይበላ ይለያያሉ። አሰፋ ጫቦን አስገድለውት ይሆን እላለሁ አንዳንዴ ሳስብ።
    አሜሪካ የሰላምና የመረጋጋት ጸር ናት። አሁን ወደ አዲስ አበባ ያቀናው ፊልትማን ሊያስፈራራም ጭምር ነው የሄደው። በወያኔ ልመና ነው የተላከው። እርቅ የሚሉት ጭራሽ የእብደት ምርጫ ነው። 27 ዓመት የኢትዮጵያን ህዝብ በአደባባይ በጥይት ሲቆላ ምንም ያላረጉት እነዚህ ሽንኮች አሁን ወያኔን ለማዳን ለምን እንደሚፍጨረጨሩ ህዝባችን ሊገባው ይገባል። ከላይ የተጠቀሰው አይነት ህብረትና መተጋገዝ እንዳይኖር ይሰራሉ፤ ያሰራሉ። ሌላ የቆየ ሃሳብ ልጨምር። የኤርትራን ሪፈረንደም በተመለከተ (በንጉሱ ጊዜ የሆነውን) የኤርትራ ፓርላማ እንዲፈርስና ሌላው ሁሉ እንዲሆን በውስጥ በንጉሱ ላይ ጫና ያደረጉት አሜሪካኖች ነበሩ። ያ አልፎ ሌላ ዘፈን ሲመጣ ደግሞ ከሻቢያ ጋር በመሆን እሳት እያቀበሉና እሳት እየጫሩ ለ 30 ዓመት ያጫረሱን እነርሱ ናቸው። አሁን የኤርትራው መሪ በአሜሪካ ላይ ያለው ብረት ለበስ አቋሙ ከዚሁ ተመክሮ ባገኘው ብልሃት ነው። ተንኮላቸውን ጠልቆ ያውቀዋል። አሁን ለ 11ኛ ጊዜ ተመድ በኢትዪጵያ ጉዳይ እንዲሰበሰብ፤ የኢኮኖሚ ማዕቀብ በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ እንዲጣል ሌላም የቀጥታና የእጅ አዙር መተት የሚያደርጉት አሜሪካኖች የጥቁር ህዝብን ክፍ ማለት አይወድም። በቅርቡ አፍጋንስታንን እንለቃለን ብለው ግርግር ሲፈጥሩ የአሸባሪ መኪና ባሉት ላይ ተኩሰው 11 ሰላማዊ ሰዎችንና ህጻናትን ጭምር መግደላቸው ይታወቃል። ግን በቅርቡ ፔንታጎን ያወጣው ዘገባ በዚህ ጥቃት ማንም ስህተት አልሰራም ይላል። ለተራፊ ዘመድ አዝማድ ግን በየቀኑ ከሚያትሙት ዶላር እንካችሁ ካሳ ማለታቸውን ልብ ልንል ይገባል። ማንም ጠያቂ የለባቸውም። የሌላውን ሃገር ሲያምሱ፤ ሲያፈርሱ፤ ሲገድሉና ሲያሳድድ ዓለም ጸጥ ብሎ ያያቸዋል። የዛሬን አያርገውና የሰሜኑ ዘመዶቼ ” ዓለም ዘጠኝ ናት” ይሉ ነበር። እንዲህ ነው ጎበዝ። የነጭ ህይወት መስፈሪያው ከልክ ያለፈ ነው። የሌላው ህይወት ደግሞ በተጠራመሰ ጣሳ ውስጥ ግባ ቢባል የማይገባ ነው። መቼ ነው የምንነቃው? ፊታቸው፤ ፈገግታቸው ቃላቸው ተግባራቸው እንዳልሆነ አውቀን እርስ በእርስ መገዳደል አቁመን ለጥቁር ህዝቦች ሰላምና ደህንነት የምንሟገተው? ምዕራባዊያን ሰላም የሚነሱት ነጭ ያልሆነውን ዓለም ነው። ሊቢያን ያፈራረሷት፤ ኢራቅን ያወደሟት፤ሶሪያን የመከራ ናዳ የሚያዘንብቧት፤ የመንን በተሸመተ የጦር እቃ በሳውዲ ወኪሎቻቸው የሚያምሷት ለዛ ነው። አሁን እንሆ ሰሜን ኮሪያና ኢራን አፋቸውን ሞልተው እስቲ ንኩንና እናሳያችሁሃለን ማለታቸው የዘመነ የጦር መሳሪያ በመታጠቃቸው ነው። አበው እኮ ድሮ ተናግረው ጨርሰውታል። ረጅም በትር (ድላ) ባይመቱበት ያስፈራሩበት። አሁን አዲስ አበባ የገባውን ፊልትማንን መልሶ ማባረረ ነው። አሜሪካኖች ለእነርሱ ላደረ መንግስት – ተላላኪያቸው ለሆነ ሁሉን ይሆናሉ። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፓሊሲና የስለላ መረብ ለሰው ልጆች መብት ደንታ የማይሰጠው ለራሱ ጥቅም ብቻ የቆመ ነው። ኢትዮጵያንም የሚያምሷት የኢኮኖሚ እድገቷ ተገትቶ፤ ሃገሪቱ ፈራርሳ እነርሱ በፈለጉት መልክ መልሰው ሊሰሯት ፈልገው ነው። አንድ ነገር ላክልና ይብቃኝ። በአንድ በኩል ከጠ/ሚሩ ጋር በስልክም በፊት ለፊትም ሉዕካን ልከው እያናገሩ። በዋሽንግተን በድብቅ የኦሮሞ አክራሪዎችን ሰብስበው ስለመገንጠል የሚመክሩ እብዶች ናቸው። ሰው በሰፈረው መስፈሪያ መሰፈሩ አይቀርም። እንኳን አሜሪካ 29 ቲሪሊዪን እዳ ውስጥ ተዘፍቃ ያለችው ቀርቶ በእንግሊዝ ግዛት ጸሃይ አይጠልቅም የተባለላት ተፍረክርካለች። የሮም መንግስትም አይወድቁ ውድቀት ወድቋል። ግን የሃበሻው በአጠቃላይ የጥቁሩ ህዝብ ችግር ይበልጡ ራሳችን የምናመነጨው ነው። የማስተካከያ ዘመቻው ከራስ ከጀመረ፤ የውጭ ሃይሉን ጣልቃ ገብነት ለመግታት ጉልበት ይሆናል። በቃኝ!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share