ለቸኮለ! ረቡዕ ጥቅምት 17/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

 

1፤ አሜሪካ ለአፍሪካ ሀገራት ከሰጠችው የቀረጥ ነጽ ንግድ (አጎዋ) ዕድል ኢትዮጵያን እንዳታግድ የአሜሪካ ኢምባሲ እገዛ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ መማጸናቸውን ኮሚሽኑ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል። ኮሚሽነር ለሊሴ ተማጽኖውን ያቀረቡት በአሜሪካ ኢምባሲ ከአሜሪካ ንግድ ወኪል ያሱኢ ፓይ ጋር በአካል ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት ነው። በተያያዘ የአሜሪካ ሕግ መምሪያ እና ሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶች ሁለት አባላት ኢትዮጵያ ከቀረጥ ነጻ ንግድ ተጠቃሚነቷ እንዳትሰረዝ ከተፈለገ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራዩ ጦርነት የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ማስቆም እንዳለበት በትዊተር ባሰራጩት መግለጫ አሳስበዋል። ኢትዮጵያ ከአጎዋ ከተሰረዘች ሃላፊነቱን የሚወስደው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል አባላቱ።

2፤ ከትግራዩ አማጺ ሕወሃት ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተዘጉ ፋብሪካዎች እና ሌሎች ንግድ ድርጅቶች በመንግሥት አስተዳዳሪ ተመድቦላቸው እንደገና ሥራ ሊጀምሩ እንደሆነ ሪፖርተር ጋዜጣ የፍትህ ሚንስቴር ደዔታ ፍቃዱ ጸጋን ጠቅሶ አስነብቧል። በድርጅቶቹ ላይ የሚደረገው የወንጀል ምርመራ ግን ሥራ ከጀመሩም በኋላ እንደሚቀጥል ፍቃዱ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከተማ አክሱም፣ ንግሥተ ሰባ፣ ካሌብ፣ ኔክሰስ እና ሐርመኒ የተባሉ ትላልቅ ሆቴሎች እስካሁን ተዘግተው ከሚገኙት መካከል እንደሚገኙበት ዘገባው ጠቅሷል።

3፤ አዲስ የተቋቋመው የፌደሬሽን ምክር ቤት አባላት ለቀጣዩ ቅዳሜ አስቸኳይ ስብሰባ እንደተጠሩ ምክር ቤቱ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ምክር ቤቱ በአስቸኳይ ስብሰባው በምን አጀንዳ ላይ እንደሚወያይ ግን መረጃው አላብራራም። የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አገኘሁ ተሻገር አፈ ጉባዔ ሆነው ከተመረጡ ወዲህ፣ ምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ ሲያካሂድ የቅዳሜው የመጀመሪያው ይሆናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ቴድሮስ አድሐኖም ለሕወሓት ባለስልጣናት የሳተላይት ስልኮች የጤና ድርጅቱን ሽፋን በማድረግ ማስገባቱን የሚገልጽ ሰነድ ይፋ ሆነ

4፤ የአፍሪካ ኅብረት ሰላምና ደኅንነት ምክር ከትናንት ወዲያ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት የተደረገባትን ሱዳንን ከአባልነት ማገዱን ኅብረቱ በድረገጹ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል። ከሥልጣኑ በኃይል የተወገደው ሲቪሉ ሽግግር መንግሥት ወደ ሥልጣኑ እስኪመለስ ሱዳን ከማናቸውም የኅብረቱ እንቅስቃሴ ታግዳ እንደምትቆይ ምክር ቤቱ ገልጧል። ጦር ሠራዊቱ ያሰራቸውን ሚንስትሮች ባስቸኳይ እንዲለቅና ለደኅንታቸውም ተጠያቂ እንደሚሆን ያስጠነቀቀው ኅብረቱ፣ ለቀውሱ መፍትሄ ለማፈላለግ ወደ ካርቱም ልዑካን እንደሚልክ ጠቁሟል። ሱዳን በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ ከምትሳተፍባቸው መድረኮች አንዱ ኅብረቱ ዋና አደራዳሪ የሆነበት የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር እንደሆነ ይታወቃል።

5፤ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣናቸው ተወግደው ለሁለት ቀናት በጦር ሠራዊቱ ቁጥጥር ስር የቆዩት የሱዳን ሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚንስትር ሐምዶክ ወደ መኖሪያ ቤታቸው እንደተመለሱ ዓላማቀፍ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሐምዶክ በቤታቸው በቁም እስር ላይ ይሁኑ አይሁኑ ግን አልተረጋገጠም። የሀገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጀኔራል አል ቡርሃን ሐምዶክን ለደኅንነታቸው ሲሉ በራሳቸው መኖሪያ ቤት እንዳቆዩዋቸው ትናንት ተናግረው ነበር። አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ አውሮፓ ኅብረት፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ኔዘርላንድ፣ ስፔን እና ስዊዘርላንድ ዛሬ ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ አሁንም የሱዳን ሕጋዊ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ ናቸው በማለት አስታውቀዋል። ሀገራቱ በካርቱም የሚገኙ አምባሳደሮቻቸው ሐምዶክን በአካል አግኝተው የሚያነጋግሩበት መንገድ ባስቸኳይ እንዲመቻችላቸውም የጠየቁ ሲሆን፣ ጦር ሠራዊቱ የዜጎችን በአደባባይ ሰላማዊ ተቃውሞ የማድረግ መብት እንዲያከበርና የኃይል ርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠብ አሳስበዋል።

6፤ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን በሚወዛገቡባት አቢዬ ግዛት በሠፈረው የተመድ ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ዕጣ ፋንታ እና በግዛቲቷ እያሽቆለቆለ በመጣው የጸጥታ ሁኔታ ላይ ዛሬ እንደሚወያይ በተመድ የአየርላንድ ቋሚ መልዕክተኛ በትዊተር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። በግዛቲቷ የሠፈሩት የኢትዮጵያ ወታደሮች ሲሆኑ፣ ሱዳን ግን ተመድ የኢትዮጵያን ወታደሮች አስወጥቶ በሌሎች እንዲተካላት በይፋ መጠየቋ እና ተመድም ጥያቄውን እንደተቀበለ መገለጡ ይታወሳል።

  1. በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን የምትገኘውን ሐይቅ ከተማ የአማጺው ሕወሃት ታጣቂዎች ተቆጣጥረዋታል በማለት ከቀናት በፊት የዘገቡ ሁለት የአሐዱ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጋዜጠኞች እንደታሠሩ ዶይቸቬለ ዘግቧል። የታሠሩት ጋዜጠኞች የዜናው ዘጋቢ እና የዕለቱ የዜና ክፍል ሃላፊ ሲሆኑ፣ ጣቢያው ግን መረጃው የተሳሳተ እንደሆነ ጠቅሶ በኋላ በይፋ ይቅርታ ጠይቆ እንደነበር የጣቢያው ዋና አዘጋጅ ሊዲያ አበበ ተናግረዋል። ፖሊስ ጋዜጠኞቹ ከአማጺው ሕወሃት ጋር ግንኙነት አላቸው በማለት ፍርድ ቤት አቅርቦ የምርመራ ቀጠሮ ጠይቆባቸዋል ተብሏል።
ተጨማሪ ያንብቡ:  አቶ ግደይ ዘርዓጽዮን ዝምታቸውን ሰበሩ

[ዋዜማ ራዲዮ]

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share