ሐዋሳ – መስከረም 10 / 2014
1ኛ) “የወንድማማቾች ጠብ ነው፣ መክረን ተቆጥተን፣ ተቻችለን እናስቁመው” ለምትሉ፣
2ኛ) “ጦርነቱን ያመጣው የፖለቲከኞች (የወያኔና የብልጽግና) ግትርነት ነው፣ ስለዚህ ጦርነቱን እንዲያቆሙ ጫና እናድርግባቸውና ይደራደሩ፣ የሽግግር መንግሥት ያቋቁሙ” ለምትሉ፣
3ኛ) አሁን ደግሞ አብርሃ ደስታ (ከአረና)፣ ለ30 ዓመት የዘር ጭፍጨፋ የፈጸሙ፣ በሰብዓዊ ፍጡራን ላይ ወንጀል የሠሩ፣ ትውልድን በብዙ መልኩ ያመከኑ፣ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ደም ያቃቡና ያጋደሉ፣ አንድነታችንና ኢትዮጵያን ያቆሰሉ፣ የሰላማዊ ዜጎችን ንብረት ያወደሙ፣ ከተሞችን ያፈረሱ፣ ቤተክርስቲያንና መሰጊዶችን ያቃጠሉ፣ አገልጋዮችንና ምዕመናንን ያረዱ፣ የሐገርን መሬትና ኃብት ቀምተውና በአድልዎ ከቤተሰባቸው ጋር ተቀራምተው (ወልቃይት–ሑመራ/አማራ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ፣ አዲስ አበባና ዙሪያው/ ኦሮሚያ ወዘተ የጅምላ ዘረፋ የፈጸሙ ወንጀለኞች “በሕግ አይጠየቁ” እያለን ነው!
ከ2013 ጥቅምት ወዲህ በመከላከያ ሠራዊታችን፣ በትግራይ፣ በአፋርና በአማራ ሕዝባችን ላይ በድጋሚ ለመናገር እንኳን የሚቀፍና የሚያሳፍር ወረራና ግፍ የፈጸሙ ወንጀለኞች በሕግ ሳይጠየቁ “ወደየቤታቸው/ ወደአሻቸው ሥፍራ ይሂዱ“፣ የሕግ የበላይነት አይከበር እያለን ነው፤ አብርሃ ደስታ።
የዚህ ጥያቄ ሌላ ተጓዳኝ ትርጉሙ ደግሞ ይህ ነው፤ በሕግ ጥላ ሥር / በእሥር ላይ የሚገኙት እነ ስብሐት ነጋ እና ከለውጡ ወዲህ የታሠሩ (እነ አብዲ ኢሌና አረመኔዎቹ የደህንነት ኃላፊዎችና መርማሪዎች) ሁሉ በነጻ ወደየቤታቸው ይሂዱ ነው፤
ኢትዮጵያን አሁንም እየወጉ ያሉት ሽፍቶቹ እነ ደብረጽዮን፣ ጌታቸው ረዳ፣ ጻድቃን “በሕግ አይጠየቁ” እያሉ “ጥያቄአችን ግን በእሥር ላይ የሚገኙትን እነ ስብሐት ነጋን አይመለከትም” ሊሉን አይችሉም! የ“ተሸፈኑ ላሞኛችሁ፣ ተጎንበሱ ልጋልባችሁ” ዘመን ላይመለስ ሄዷል!
ድርድርና እርቅ ይደረግ የምትሉን “ገለልተኛ ምሑራን“፣ የማኅበረሰብ “አንቂዎች“፣ ኢትዮጵያውያን የሰብዓዊ መብቶች “ተሟጋቾች“፣ “ፖለቲከኞች“፣ ትግራይ ብልጽግና ወስጥ ያደፈጣችሁ ግብረ–ወያኔዎች … እይታችሁንም ሆነ ምክረ ሀሳባችሁን ሳታድበሰብሱ በተጨባጭ ነገሮች ላይ መሥርታችሁ ግለጹልን፣
* ጦርነቱን ያመጣው የፖለቲከኞች (የዓቢይና የደብረጽዮን) የሥልጣን ሽኩቻ ነው? ኢትዮጵያውያንን አታልለውን ነው እንጂ ጉዳዩ የሚመለከተን የህልውና ጉዳይ አይደለም እያላችሁን ነው፣ አይደል?!
ይህን የተዛባ ምስል በሰው አእምሮ ውስጥ ለመፍጠር የምትለፉበት የውስጥ መሻታችሁ ምን ሊሆንእንደሚችል የማንጠይቅ፣ የማንመረምርና ዕውነቱ ላይ መድረስ የማንችል ቶሎ የምንረሳ (short memory) እና የማናመዛዝን አድርጋችሁናል እንዴ?!
* ዕውን ጦርነቱ እየተካሄደ ያለው በወያኔና በብልጽግና መካከል ነው ወይስ በወያኔና በመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል?
* በየዘርፉ፣ በየደረጃው ያለን በርካታ ሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚሆነውን በማን? ለምን ወዘተ መሆን እንዳለበት/እንደሌለበት ማገናዘብና መወሰን የማንችል፣ በዓቢይ ጭንቅላትና ጡንቻ የምንነዳ አድርጋችሁናል ማለት ነው? ይህ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመላ መናቅ ነው!
* መንግሥት ከአሜሪካ ጋር አላስፈላጊና ተደጋጋሚ እሰጥ አገባ (የቃላት ጦርነት) ውስጥ ገብቶም ከሆነ ማሳያ አቅርቡልን፣
* ከማንስ ጋርና በምንስ ዙሪያ ነው “እንደራደር፣ ተቀራርበን እንሥራ” የምትሉት?
ግልጽ አድርጉት፣ የአሜሪካን ጫና ፈርተን፣ ሐገር አፍራሹና አሸባሪው ወያኔ እና የኢትዮጵያ መንግሥት/ሕዝብ ተደራድረው የተኩስ አቁም ስምምነት ያድርጉ ነው የምትሉት?
ግልጽ አድርጋችሁ ንገሩን፤ “ሲዖል ገብተንም ቢሆን ኢትዮጵያን እናፈርሳለን“፣ ኋላም በግብጽ ቲቪ ላይ ወጥቶ “ዓላማችን (የወያኔ) ነጻ የትግራይ መንግሥት መመሥረትና ሌሎች ብሔሮችም የኛን ፈለግ እንዲከተሉ ማገዝ (በአጭሩ ኢትዮጵያን መበታተን) ነው” ከሚለው ወያኔ ጋር እንደራደር ነው የምትሉን?
* “አሜሪካ ማለት ዓለም እንደማለት ስለሆነች፣ ትዕዛዟን ጥሰን ከምትጎዳን ወያኔን መልሰን እናንግሥላትና ከማዕቀቧ እንትረፍ” እያላችሁን ነው? ከዚያስ ከወያኔም ሆነ ከአሜሪካ ምን ልናገኝ?! …
ከሁለቱ ፈተናዎች የትኛው ይብስብናል?
የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ከፍለን ሉዓላዊነትን/ነጻነታችንን ማስከበር፣ በጽናትና በሕብረት ሠርተን ከድህነትና ከጥገኝነት ለአንዴና ሐመጨረሻ ጊዜ መላቀቅና በኩራት መኖር፣
ወይስ
ለአሜሪካ ጫና ተንበርክከን፣ እነርሱ በሚያነግሡልን ተላላኪ መንግሥት እየተገዛን፣ ኃብታችንን ሁሉ እያስዘረፍን፣ ዕድሜ ልካችንን የበይ ተመልካችና የሥንዴ ተመጽዋች ሆነን፣ (From the people of the USA፣ 7% እየተባለልን) “ሳይጠሩት አቤት፣ ሲያዙት ወዴት” እንደሚል ተላላኪ ሆን፣ አንገት ደፍተን በጥገኝነት “መኖር” ይብስብናል?
“ለወያኔ፣ ወይ በ4 ኪሎ ቤተመንግሥት ቦታ እንስጠው፣ ቢያንስ ግን መቀሌ ላይ ይንገስና እንደ ሶማሊያ የጦር አበጋዞች (War Lords) ተከባብረን እንኑር” እያላችሁን ነው? ጤና ይሰጠናል?
ዘረኛው፣ ግፈኛው፣ ዘራፊው፣ ሐገር አፍራሹ፣ ዘር ጨፍጫፊው … ወያኔ “ተመልሶ ወደ ሥልጣን ይምጣ” ነው የምትሉን?!
* ይህን ሁሉ የምትሉን ወያኔን ከመሞት ለማዳንና ተመልሶ እንዲያንሰራራና እንዲመጣብን ካልሆነ ሌላ ዓላማችሁ ምን ሊሆን ይችላል?
* መላው ዓለም እንዳይነሳብን የምትሉትስ፣ ዓለም በኢትዮጵያ ላይ ያደመው ገና ዛሬ ነው እንዴ?!
ከጥንት ጀምሮስ መች ተኝተውልን ያውቃሉና?!
በተለይ ደግም ቅኝ ገዢን ረግጠን፣ አሸንፈን ካባረርንበትና ለነጭ የበላይነት “እምቢኝ” ካልንበት ቀን ጀምሮ ምን ያልሠሩብን ሻጥርና ያላደረሱብን ጉዳት አለ?! የነጭ ቁጭትና ቂምም እኮ አለ?! የኢትዮጵያን የአፍሪካና ነጭ ያልሆኑ ሕዝቦች የነጻነት ቀንዲልነትና ተምሳሌትነት ከምድረ ገጽ ብቻ ሣይሆን ከታሪክ ማኅደርም የመፋቅ የዘመናት እኩይ ፍላጎትም አለ እኮ!
ምን እያላችሁ ነው?!
ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የተጎዳነው እኮ፣ በአንድ በኩል በእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች ሻጥርና አፈና በሌላ በኩል ደግሞ በገዢዎቻችን ራስ ወዳድነት፣ “እኔ አውቅላችኋለሁ” ባይነት፣ ልፍስፍስነት፣ ተላላኪነትና ራዕይ አልባነት ነው።
ተከፋፍለን፣ ተልፈስፍሰን፣ አፈግፍገን፣ እጅ ሰጥተን፣ ጊዜና መድረክ ሰጥተናቸው እንደነ ኢራቅ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ ሶሪያ ይበታትኑን?!
ሌላውን ሁሉ ተዉት፣
– ያ ሁሉ መዓት ለወረደበት የአማራና የአፋር ሕዝብ (ልዩ ኃይሉና ሚሊሻው–ለመስዋዕትነቱ)፣
– ያ ሁሉ ክህደትና ጭፍጨፋ ለተፈጸመበትና ያን ሁሉ መስዋዕትነት ለከፈለው መከላከያ ሠራዊታችን፣
– ከሌለው ላይ እየሰጠ ለመከላከያችን ደጀን ሆኖ፣ ለተጎዱ ወገኖቹ ፈጥኖ ደራሽ ሆኖ፣ ልጆቹን መርቆ ወደ ግንባር በመላክ ዘርፈ ብዙ መስዋዕትነት እየከፈለ ላለው ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብስ (እርሱ የማያየውን)
ምን ጥቅም አይተን ከወያኔ ተደራደርን፣ ታረቅን ልትሉት ነው?!
በስመ አብ!!!
* ወያኔ 30 ዓመት የፈጸመብን ግፍ ይቆይና፣ በ2013 ዓ.ም. ብቻ ያወረደብንን መከራ ሁሉ ረስተን፣ መልሰን ወደ ሥልጣን እናምጣው የምትሉ፣ እናንተው ራሳችሁ በጭምብል የተሸፈናችሁ ወያኔዎች አለያም የሲ አይ ኤ ተላላኪዎች እንጂ ሌላ ምን – ማን ልትሆኑ ትችላላችሁ?! ካልሆናችሁ አስረዱን!
ምን አልባት የምክረ ሀሳባችሁን ጭብጥ (ለምሳሌ አብርሃ፣ ሐጎስ) ስቼ ከሆነ (To give you the benefit of doubt) እንደገና ቀለልና ይበልጥ ግልጽ አድርጋችሁ ብታስረዱን ለሁላችንም ጠቃሚ ነው።
አለበለዚያ …
ይቀጥላል።